ጸሎት ከእግዚአብሔር ጋር መነጋገርያ ነው። ጸሎት የተበደለ ድሀ ወደ ንጉሥ እንደሚጮህ ሁሉ የሰው ልጅ ለችግሮቹ ለእግዚአብሔር የሚያቀርበው አቤቱታ ነው።
ጸሎት ሲቀርብ ባላፈው ፈጣሪን እያመሰገንን፣ ለሚመጣው እየለመንን፣ ኃጢአታችንን አምነን፣ ፈጣሪን ይቅርታ እየጠየቅን መሆን አለበት።
ጸሎት ስናደርግ ማድረግ ያሉብን ነገሮች አሉ። እነርሱም: ቀጥ ብሎ መቆም ፤ ወገብን መታጠቅ፣ ፊትን ወደምሥራቅ ማድረግ፣ በመስቀል ምልክት ማማተብ፣ በፍርሃት ማንበብ እና መስገድ ናቸው።
ጸሎት ልንጀምር ስንል እና ነገረ መስቀልን የሚያነሳ ቃል ስናነብ በመስቀል ምልክት ማማተብ ይገባል። ጸሎት ሲጀመር ሦስት ጊዜ ሰግዶ ይጀምራል። ጸሎቱ ሲያልቅም ሦስት ጊዜ ይሰገዳል። በቆረቡበት ቀን መስገድ አይገባም።
እጅን ዘርግቶ ዓይንን ወደ ሰማይ አንጋጦ መጸለይ ይገባል። ሁሉም ሰው መዝሙረ ዳዊት አብዝቶ ሊጸልይ ይገባል። በውስጡ ምስጋና ልመና አለበትና። አንድ ሰው ቢያንስ በዕለት ሰላም ለኪ፣ አቡነ ዘበሰማያት እና መዝሙር ፫/፬፣ መዝሙር ፵ ከዚ ከጠነከረ መዝሙር ፺ እና ፻፳ መጸለይ ይኖርብናል።
ማንኛውም ምእመን በቀን ቢያንስ ሰባት ጊዜ መጸለይ አለበት፤ ሰዓታቱም:
1. ጸሎተነግህ (ጠዋት ፲፪ ሰዓት)
2. ከጠዋቱ ፫ ሰዓት
3. በቀትር (፮ ሰዓት)
4. ከቀኑ ፱ ሰዓት
5. ጸሎተ ሠርክ
6. ማታ ፫ ሰዓት
7. ሌሊት ፮ ሰዓት ናቸው።
ጸሎተ ነግህ
ጠዋት የምንጸልየው ጽልመተ ሌሊቱን አሳልፈህ ለዚህያ ደረስኸን ብለን ነው። አዳም የተፈጠረበት ነው። ጌታም ሰውን ለማዳን በጲላጦስ ፊት የተመረመረበት ነው። ይህንን እያሰብን እንጸልያለን።
፫ ሰዓት
ዳንኤል የጸለየበት ጊዜ ነው። ድንግል ማርያም ብሥራተ መልአክን የሰማችበት ነው፣ ሔዋን የተፈጠረችበት ነው፣ ጌታ በጲላጦስ ፊት የተገረፈበት ነው።
፮ ከሰዓት
አዳም የሳተበት፣ ጌታ የተሰቀለበት ሰዓት ነው። አጋንንት ይሰለጥኑበታልና በእነርሱ ተንኮል እንዳንወድቅ መጸለይ ይገባል።
፱ ሰዓት
መላእክት የሰውን ምግባር የሚያሳርጉበት ነው። ጌታ ነፍሱን ከሥጋው የለየበት ነው።
ሠርክ
የምጽአት ምሳሌነው። ጌታ ወደ መቃብር የወረደበት ሰዓት ነው። ጸሎተ ንዋም (ማታ ፫ ሰዓት) "ቀኑን አሳልፈህ ዕረፍተ ሌሊትን ያመጣህልን" ብለን ነው። ጌታ የጸለየበት ነው።
መንፈቀ ሌሊት
መንፈቀ ሌሊት ላይ ተነስተን እጃችንን ታጥበን እንጸልያለን። ጌታ የተወለደበት፣ የተጠመቀበት፣ የተነሣበት፣ ዳግም ምጽአት የሚሆንበትነው።
የጠዋቱን እና የሠርኩን ጸሎት በቤተክርስቲያን ቢጸልዩ መልካም ነው።
በሌሎች ጊዜያት ከየትኛውም ቦታ ምእመን በቃል መጸለይ ባይችል በልቡ ይጸልይ። መንገድ ለመሄድ ስንጀምር፣ ችግሮች ሲደርሱብን፣ እንዲደረግልን የምንፈልገው ነገር ካለ በማንኛውም ሰዓት መጸለይ መልካም ነው። ምግብ ከመብላታችን በፊትና በኋላ መጸለይ ተገቢ ነው።
http://youtube.com/@EMislene