መጻሕፍት እንደሚያስተምሩን "የዕለት እንጀራችንን ስጠን" የሚለው ጸሎት ለመነኮሳት ሲሆን "ለዕለት"፣ በዓለም ለሚኖሩ ሰዎች ሲሆን ደግሞ "ለዓመት" የሚሆን እንጀራ ስጠን ማለት ነው። ታዲያ ለምን አንዳንዶች ከዓመት የሚተርፍ ብዙ እንጀራ ሲያገኙ፣ ሌሎች ደግሞ ለዕለት እንኳን የሚሆን ቁራሽ ያጣሉ ? መቼም 'ለሰው ፊት የማያዳላ' እግዚአብሔር "አድልዎ ቢኖርበት ነው" ብለን የድፍረት ቃል በእርሱ ላይ አንናገርም። (ሐዋ 10፥34) ይህ የሆነው እንደ ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ ትምህርት አትርፈው ያገኙ ሰዎች ምንም የሌላቸውን እንዲረዱ እና መግቦት የባሕርይው የሆነውን አምላካቸውን በጸጋ እንዲመስሉት ነው። በዚሁም ላይ በፈጠራቸው ሰዎች መካከል ያለውን የመተዛዘንና የፍቅር ትስስር የበለጠ ለማጠናከር ነው፡፡
'የዕለት እንጀራችንን ስጠን ለዛሬ' ብለን የለመንነው አምላክ ከዓመት እንጀራችን በላይ አትርፎ የሚሰጠን፣ የሚበቃንን ያህል ተመግበን በቀረው ለሌሎች አድራሽ መልእክተኞች እንድንሆን ነው። ስለዚህ ይህን የተጣለብንን አምላካዊ አደራ ባለመወጣት ድሆችን አንበድል፤ ተማርረው ከፈጣሪያቸውም ጋር እንዲጣሉ አናድርጋቸው።
(ዲያቆን አቤል ካሳሁን)