በእንተ ቅዱሳን ኅሩያን (ከገድላት አንደበት) @kegedilatandebet27217 Channel on Telegram

በእንተ ቅዱሳን ኅሩያን (ከገድላት አንደበት)

@kegedilatandebet27217


ይኽ ለ3ኛ ጊዜ የተከፈተ አዲስ ቻናል ነው። በየቀኑ ገድለ ቅዱሳንና የተለያዩ አገልግሎቶች በጽሑፍና በድምፅ ይተላለፉበታል።

በእንተ ቅዱሳን ኅሩያን (ከገድላት አንደበት) (Amharic)

በእንተ ቅዱሳን ኅሩያን (ከገድላት አንደበት) የታሪኩን ስነስርዓት የተማሪዎችን ማስታወቂያዎችን እና ጽሑፍን ከአፈቃላይ መልእክት ማወቅ ይችላሉ ። እስካሁንም ገድላት የኅሩያን ወንድሞችን እና ሴትሞችን ለመመልከት መረጃዎች ይሰጡበታል። ብቁ ከገዳብ ልብ ውስጥ የሚደረጉትን ውይይት ሰልቦና በኮንትራቨኝ መናገር ይችላሉ።

በእንተ ቅዱሳን ኅሩያን (ከገድላት አንደበት)

21 Nov, 05:30


ኅዳር 12-በዓለ ሢመቱ ለቅዱስ ሚካኤል ሊቀ መላእክት
https://youtube.com/watch?v=w6H3ZdB2s8U&si=igPzoe3YDXaNlGQ2

በእንተ ቅዱሳን ኅሩያን (ከገድላት አንደበት)

21 Nov, 05:30


መልክዐ ቅዱስ ሚካኤል ሣልሲት፡ ገብረ ሥላሴ

በእንተ ቅዱሳን ኅሩያን (ከገድላት አንደበት)

21 Nov, 05:29


‹‹ክብርህ ከመላእክት ኹሉ ክብር ከፍ ያለ የምሕረት መልአክ ቅዱስ ሚካኤል ሆይ! መሬትና ውኃ ለአልተቀላቀለበት ከነፋስና እሳት ብቻ ለተፈጠረው መልአካዊ ገጽታህ ሰላም እላለሁ፤ ከላይ ከሰማይ ተልከህ በምትመጣበት ጊዜ በሲኦል የሚኖሩ ግዞተኞች ኹሉ ‹ቅዱስ ሚካኤል ሆይ! መጣኽልን ደረስኽልን› እያሉ ደስታቸውን ይገልጣሉ፡፡›› (መልክዐ ቅዱስ ሚካኤል)

በመላው ዓለም የምትኙ ኦርቶዶክሳውን እና ኦርቶዶክሳውያት ኹላችሁ እንኳን ለሊቀ መላእክት ለቅዱስ ሚካኤል ዓመታዊ በዓል አደረሳችሁ አደረሰን! ለሀገራችን ሰላም ለሕዝባችን ፍቅር አንድነትን ያድለን!

በእንተ ቅዱሳን ኅሩያን (ከገድላት አንደበት)

20 Nov, 19:14


አንድ አምላክ በሚሆን በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም አሜን
ኅዳር 12-ከጽንፍ እስከ ጽንፍ የሚበር ንሥረ አርያም የሚባል ውዳሴው እንደ ማር የጣፈጠ ንዑድ ክቡር የሆነ ለፍጥረቱ ሁሉ የሚማልድ የመላእክት አለቃ ቅዱስ ሚካኤል የተሾመበት ዕለት ነው፡፡
+ ጻዲቁ ንጉሥ በእደ ማርያም ዕረፍታቸው መሆኑን ስንክሳሩ በስም ይጠቅሳቸዋል፡፡
+ የመጥምቁ ዮሐንስ ራስ በደብረ ማህው የታየችበት ዕለት መሆኑን ስንክሳሩ ይጠቅሳል፡፡
የመላእክት አለቃ ቅዱስ ሚካኤል፡- ሚካኤል ማለት በዕብራይስጥ ቋንቋ ሚ-መኑ' ካ-ከመ' ኤል-አምላክ ማለት ሲሆን በአንድነት ሲነበብ ‹‹መኑ ከመ አምላክ-እንደ እግዚአብሔር ያለ ማን ነው›› ማለት ነው፡፡ አንድም ለእግዚአብሔር አሸናፊ ድል አድራጊ የቸርነትና የርህራሄ መገኛ መዝገብ ማለት ነው፡፡
ገናናው መልአክ ቅዱስ ሚካኤል ዲያብሎስን ወደ ጥልቁ ጥሎት በእርሱ ምትክ ከሁሉ የበላይ ሆኖ በተሾመበት በዚህ ዕለት በበዓሉ መታሰቢያ በኅዳር 12 ቀን የክብር ባለቤት በሆነ በእግዚአብሔር ፈቃድ ክንፎቹን ወደ ሲኦል ያወርዳል፣ ኃጥአንንም ወደ አዲሲቱ ምድር ያወጣቸዋል ይኸውም የመላእክት አለቃ የሚካኤል ሠራዊት ይሆናሉ፡፡ ይቅርታ የተደረገላቸውና ምሕረት አግኝተው በአንድ ጊዜ በክንፉ ያወጣቸው ስፍር ቁጥር የላቸውም፡፡ ቅዱስ ሚካኤል በየዓመቱ በኅዳር 12 ቀን እንዲህ እያደረገ እልፍ ነፍሳትን ያወጣል፡፡ የቤተ ክርስቲያን ወገኖች የሆኑትን ሁሉ እንደሥራቸው ወደ ምሕረት ቤት ወደ ሰማያዊት ኢየሩሳሌም ይወስዳቸዋል፡፡ ከዚህም በኋላ ወደ አብ መጋረጃ ውስጥ ይገባል፣ በዚህች ዕለት ምድራዊትና ሰማያዊት ስለሆነች ምሕረቱም ከመንበሩ በታች ይሰግዳል፡፡ ስለውኃ ምንጮች፣ ስለ ወይን ቦታዎች፣ ስለ ምድር ፍሬዎች በምድርም ላይ ስለሚኖሩ ስለ ሰው ልጆች ነፍስ ሁሉ፣ ስለ እንስሳትም፣ ስለ ሰማይ ወፎችም፣ ስለ ባሕር ዓሣዎችም፣ በምድር ላይና በባሕር ውስጥ ስለሚንቀሳቀሱ ሁሉ የምሕረት ባለቤት ከሆነ ከአብ ዙፋን በታች ሁልጊዜ በማመስገን ይሰግዳል፤ ልመናውንም እስኪሰማውና የምሕረትንም ቃል እስኪያስተላልፍለት ድረስ ከእግረ መንበሩ ሥር አይነሣም፡፡
ለዚህ ዓለም ምሕረትን የሚለምኑ ቅዱሳን መላእክትም በየዓመቱ ኅዳር 12 ቀንበእግዚአብሔር የዙፋኑ ዓውደ ምሕረት ዙሪያ ተሰብስበው ስለ ሰውና ስለ እንስሳትም ሁሉ ምሕረትን የሚለምን ቅዱስ ሚካኤል ከአብ መጋረጃ ውስጥ በወጣ ጊዜ ቸርና መሐሪ አብ ለቅዱስ ሚካኤል የሰጠው ልብሱን እነዚያ መላእክት ይመለከታሉ፣ ይቅርታን የማግኘት ምልክታቸው ነውና፡፡ ስለዚህ እነዚህ ቅዱሳን መላእክት በምድር ላይ ምሕረት እንደተደረገ ሰውንም እንስሳትንም ይቅር እንዳለ በዚህ ዓለምም የሚሆነውን ሁሉ አይተው ቅዱስ ሚካኤል በለበሰው ልብስ አምሳል ያውቁታል፡፡
ስንክሳሩ እንደሚለው ይህ እጅግ የከበረ ገናና መልአክ ቅዱስ ሚካኤል ‹‹ከቅዱሳን ሰማዕታት ጋራ በመሆን ገድላቸውን እስኪፈጽሙ ድረስ የሚያጽናናቸውና የዘወትር ጠባቂአቸው ሆኖ የሚራዳቸው እርሱ ነው፡፡›› የብዙዎቹንም ቅዱሳን ገድል ስንመለከት የዘወትር ጠባቂያቸው ቅዱስ ሚካኤል ነው፡፡
ቅዱሳን በሕይወት ሳሉ ይህ ገናና መልአክ ቅዱስ ሚካኤል ረዳትና የዘወትር ጠባቂ፣ እንደጓደኛም አማካሪ ሆኖ የተበቃቸውን ስንቱን ቅዱሳን ዘርዝረን እንቸላለን፡፡ እርሱ ያልረዳው ቅዱስ የለም፡፡ መከራውን ያላስታገሰው ሰማዕት የለም፡፡ ለቅዱሳኑ እንዲህ እንደጓደኛቸው ሆኖ ሲጠብቃቸው ይኖራል፡፡ ነገር ግን ቅዱስ ሚካኤል ለኃጥአንና አምላካቸውን ለካዱ ሰዎች ደግሞ በቁጣ ለመቅሰፍት ይመጣባቸዋል፡፡ ሰናክሬም በእግዚብሔር ላይ ክፉ በመናገሩ በአንዲት ሌሊት ብቻ 185,000 (መቶ ሰማንያ አምስት ሺህ) ሠራዊቱን ቅዱስ ሚካኤል በብርሃን ሰይፉ ፍጅቷቸው አድሯል፡፡ 2ኛ ነገ 19፡35፣ ኢሳ 37፡36፡፡
እግዚአብሔርን ለሚወዱና እርሱንም ለሚያከብሩት መታሰቢያውንም ለሚያደርጉለት ግን ከሚፈልጉት ነገር ከቶ አያሳጣቸውም፣ ዘወትርም ይጠብቃቸዋል፣ በኋላም በአማላጅነቱም ከሲኦል እሳት ያድናለቸዋል፡፡ እነሆ ይህ ገናና ክቡር መልአክ ቅዱስ ሚካኤል ያደረገው ተአምር ይህ ነው፡- ‹‹የእግዚአብሔር ወዳጅ የሆነ ስሙ ዱራታዎስ የሚባል አንድ ሰው ነበረ፡፡ የሚስቱም ስም ቴዎብስታ ነው፡፡ እነርሱም ሁልጊዜ ያለማቋረጥ የዚህን የከበረ መልአክ የቅዱስ ሚካኤልን የበዓሉን መታሰቢያ ያደርጉ ነበር፡፡ ከዚህም በኋላ በሀገር ውስጥ ችግር በሆነ ጊዜ ገንዘባቸው አለቀ፡፡ ለቅዱስ ሚካኤልም ለበዓሉ መታሰቢያ የሚያደርጉትን እስኪያጡ ድረስ ቸገራቸው፡፡ ዱራታዎስም ሸጦ ለመልአኩ በዓል መታሰቢያ ያደርገው ዘንድ የእርሱንና የሚስቱን ልብስ ይዞ ወጥቶ ሄደ፡፡
የመላእክት አለቃ ቅዱስ ሚካኤልም በታላቅ መኮንን አምሳል ለዱራታዎስ ተገለጠለትና ወደ ባለጸጎች ሄዶ በእርሱ ዋስትና በአንድ ዲናር አንድ በግ እንዲወስድ፣ ሁለተኛም ወደ ባለ ስንዴ ዘንድ ሄዶ በእርሱ ዋስትና ስንዴን እንዲወስድ ዳግመኛም ወደ ዓሣ አጥማጅ ዘንድ ሄዶ አንድ ዓሣ እንዲወስድ ነገር ግን ወደቤቱ ሳይርስ የዓሣውን ሆድ እንዳይቀድ አዘዘው፡፡ ዱራታዎስም እንደታዘዘው አደረገ፡፡ ወደቤቱም በተመለሰ ጊዜ ቤቱ ሁሉ በበረከት ተመልቶ አገኘው፡፡ እርሱም እጅግ ተደስቶ የዚህን የክበር መልአክ የመታሰቢያውን በዓል አደረገ፡፡ ጦም አዳሪዎችንና ድኆችን ጠርቶ አጠገባቸው፡፡
ከዚህም በኋላ ለዱራታዎስና ለሚስቱ ቅዱስ ሚካኤል ሁለተኛ ተገለጠላቸው፡፡ ዱራታዎስንም የዓሣውን ሆድ እንድሰነጥቅ አዘው፡፡ በሰነጠቀውም ጊዜ 300 የወርቅ ዲናር በዓሣው ሆድ ውስጥ ተገኘ፡፡ ቅዱስ ሚካኤል ዱራታዎስንና ሚስቱን ቴዎብስታን እንዲህ አላቸው፡- ‹‹ከዚህ ዲናር ወስዳችሁ ለባለ በጉ፣ ለባለ ዓሣውና ለባለ ስንዴው ዕዳችሁን ክፈሉ፡፡ የቀረውም ለፍላጎታችሁ ይሁናችሁ እግዚአብሔር አስቧችኋልና በጎ ሥራችሁን፣ መሥዋዕታችሁንና ምጽዋታችሁን አስቦ በዚህ ዓለም አሳመረላችሁ፣ በኋለኛውም መንግሥተ ሰማያትን አጀጋጀላችሁ›› አላቸው፡፡
እነርሱም ይህን ነገር ሲሰሙ ደነገጡ፡፡ የከበረ ገናናው መልአክም ‹‹ከመከራችሁ ሁሉ ያዳንኳችሁ የመላእክት አለቃ እኔ ሚካኤል ነኝ፣ መሥዋዕታችሁንና ምጽዋታችሁን ወደ እግዚአብሔር ፊት ያሳረግሁ እኔ ነኝ፡፡ አሁንም በዚህ ዓለም ከበጎ ነገር እንድታጡ አላደርጋችሁም›› አላቸው፡፡ ይህንንም ከነገራቸው በኋላ ወደ ሰማያት ወጣ፡፡ እነርሱም በፍርሃትና በክብር ሰገዱለት፡፡››
የመላእክት አለቃ ቅዱስ የሚካኤል ጥበቃው አይለየን! ከበዓሉ በረከት ይክፈለን!

በእንተ ቅዱሳን ኅሩያን (ከገድላት አንደበት)

20 Nov, 00:55


አንድ አምላክ በሚሆን በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም አሜን
ኅዳር 11-ክብርት እመቤታችን ድንግል ማርያም ወላዲተ አምላክን የወለደቻት ቅድስት ሐና ዕረፍቷ ነው፡፡ ሐና ማለት ‹‹ጸጋ›› ማለት ነው፡፡ አምላክን የወለደች የእመቤታችን የቅድስት ድንግል ማርያም እናት ናት፡፡ እርሷም ከኢየሩሳሌም አገር ከሌዊ ነገድ ከካህኑ አሮን ትውልድ የሌዊ የሜልኪ ልጅ ለሆነ ለማጣት ልጁ ናት፡፡ የቅድስት ሐና አባት ማጣትና እናቷ ሄርሜላ ከእርሷ በተጨማሪ ሶፍያና ማርያም የሚባሉ ሌሎች ሁለት ሴት ልጆችን ወልደዋል፡፡ ቅድስት ሐና ከይሁዳ ነገድ የሆነውን ጻድቅ ኢያቄምን አግብታ ቅድስት ድንግል ማርያምን ወለደች፣ ድንግል ማርያምም መድኃኔዓለም ክርስቶስን ወለደች፡፡ ሶፍያ ኤልሳቤጥን ወለደች፣ ኤልሳቤጥም መጥምቁ ዮሐንስን ወለደች፡፡ ከሦስቱም ታናሽ የሆነችው ‹‹ማርያም›› የተባለችው የማጣትና የሄርሜላ ልጅ ደግሞ ሰሎሜን ወለደቻት፡፡
ይህችም ታላቅ እናት ቅድስት ሐና አምላክን በድንግልና ሆና በሥጋ ለወለደችው ለቅድስት ድንግል ማርያም ወላጇ ትሆን ዘንድ የተገባት ሆናለችና ከሴቶች ሁሉ እንደምትበልጥና እንደምትከብር እንረዳ፡፡ ለዓለም ሁሉ ድኅነት የተደረገባትን ልዩ ስጦታ የሆነች ድንግል ማርያምን እርሷ አስገኘቻት፡፡ የዚህች ክብርት እናት የትውልዷ ጥንተ ነገሩ እንዲህ ነው፡- ጴጥርቃ እና ቴክታ የሚባሉ የከበሩ ደጋግ ሰዎች በኢየሩሳሌም በአንድነት ተጋብተው በሕገ እግዚአብሔር ይኖሩ ነበር፡፡ እነዚህም በእግዚአብሔር የሚያምኑ የተወደዱ ጻድቃን ደግ ሰዎች ናቸው፡፡ እነርሱም በእግዚአብሄርም በሰውም ዘንድ የተመሰከረለላቸው ባለጸጎች ነበሩ፡፡ ነገር ግን መካን ስለነነበሩ የሚወርሳቸው ልጅ አልነበራቸውም፡፡
አንድ ቀን ጴጥርቃ ቴክታን እንዲህ አላት፡- ‹‹እህቴ ሆይ! ይህን ሁሉ የሰበሰብነውን ገንዘባችንን ምን እናደርገዋለን? ልጅ የለን የሚወርሰን፣ አንቺም መካን ነሽ እኔም ካንቺ በቀር ሌላ ሴት አላውቅም›› አላት፡፡ እርሷም ‹‹ወንድሜ ሆይ! አምላከ እስራኤል ለእኔ ልጅ ቢነሳኝ አንተም እንደኔው ሆነህ ትቀራለህን? ከሌላ ደርሰህ ውለድ እንጂ›› ብላ ብታሰናብተው እንደዚህ ያለ ነገር እንኳንስ ላደርገው በልቦናዬም እንዳላስበው አምላከ እስራኤል ያውቃል›› አላት፡፡ እርሷም ‹‹አምላከ እስራኤል የሚያደርገውን የሚያውቅ የለም፣ ትላንትና ማታ በህልሜ ነጭ ጥጃ ከማኅፀኔ ስትወጣ ያችም ነጭ ጥጃ ሌላ ነጭ ጥጃ ስትወልድ እንዲሁ እስከ 7ት ትውልድ ሲዋለድ ሰባተኛይቱ ጨረቃን ስትወልድ፣ ጨረቃዋም ፀሐይን ስትወልድ አየሁ›› አለችው፡፡ እርሱም በጠዋት ከህልም ፈቺ ዘንድ ሔዶ የነገረችውን ሁሉ ነገረው፡፡ ያም ህልም ፈቺ ‹‹እግዚአብሔር በምሕረቱ አይቷችኋል፣ በሳህሉ መግቧአችኀል፣ 7 አንስት ጥጆች መውለዳችሁ 7 ሴቶች ልጆች እና የልጅ ልጆች ትወልዳላችሁ፤ ከቤታችሁ ሰባተኛይቱ ጨረቃ መውለዷ ከሰው የበለጠች ከመላእክትም የከበረች ደግ ፍጥረት ትወልዳላችሁ የፀሐይ ነገር ግን አልታወቀኝም›› አለው፡፡
ጴጥርቃም ሕልም ፈቺው የነገረውን ሁሉ ሔዶ ለሚስቱ ነገራት፡፡ እርሷም ‹‹እንጃ አምላከ እስራኤል የሚያደርገውን ማን ያውቃል!?›› ብላ ዝም አለች፡፡ ከዚያም ፀንሳ ሴት ልጅ ወለደች፡፡ ስሟንም ሄሜን ብለው አወጡላት፤ ሄሜንም አድጋ ለአካለ መጠን ስትደርስ አጋብተዋት ሴት ልጅ ወለደች፣ በስምንተኛ ቀኗም ዴርዲ ብለው ስም አወጡላት፡፡ ዴርዲም አድጋ እንዲሁ ሴት ወለደችና ቶና አለቻት፣ ቶናም እንዲሁ ሴት ልጅ ወልዳ ሲካር አለቻት፣ ሲካርም እንዲሁ ሴት ልጅ ወልዳ ሴትና አለቻት፣ ሴትናም እንዲሁ ሴት ልጅ ወልዳ ሄርሜላ አለቻት፣ ሄርሜላም እንዲሁ ሴት ልጅ ወልዳ ንጽህት ቅድስት ክብርት የምትሆን እመቤታችንን የምትወልደውን ሐናን ወለደች፡፡
ይህቺም ሐና በሥርዓት አድጋ ለአእምሮ ስትበቃ አካለ መጠን ስትደርስ ከቤተ መንግስት ወገን ከነቅዱስ ዳዊት ወገን ከሆነው ከቅዱስ ኢያቄም ጋር አጋቧት፡፡ እነዚህ ቅዱሳን ኢያቄምና ሐና በአንድነት ተጋብተው ሲኖሩ ልጅ አጡ፡፡ እነርሱም እጅግ ደጋግ ሰዎች ነበሩ፡፡ አንድ ልጅ እንኳ ስላልነበራቸው እጅግ ያዝኑ ነበር፡፡ ወደ ቤተመቅደስ እየሄዱ እግዚአብሔር ልጅ ይሰጣቸው ዘንድ አጥብቀው ይለምኑት ነበር፡፡ መብዓ ይዘው ለሊቀ ካህኑ ሲሰጡት ሊቀ ካህኑም እንኳ ሳይቀር ‹‹እግዚአብሔር ብዙ ተባዙ ያለውን ሕግ በእናንተ ላይ እንዳይፈጸም አድርጎ ልጅ የከለከላችሁ ኃጢአተኛ ብትሆኑ ነውና መብዓችሁን አልቀበልም›› ብሎ በእጅጉ አሳዝኗቸዋል፡፡ በሊቀ ካህኑ እያዘኑና እየተከዙ ሲመለሱ ከድካማቸው ያርፉ ዘንድ ዛፍ ሥር ተቀመጠው ሳለ እርግቦች ጫጩቶቻቸውን ሲያጫውቱ ተመልክተው ‹‹ለእነዚህ ወፎች እንኳ ልጆችን የሰጠህ አምላክ ለእኛስ መች ይሆን ልጅ የምትሰጠን?›› ብለው እጅግ አምርረው አለቀሱ፡፡
ሲያዝኑ ሲጸልዩ ውለው ወደቤታቸው ሲመለሱ ርግብ ከልጆቿ ጋር ስትጫወት አይታ ‹‹አቤቱ ጌታዬ ለዚች እንስሳ ልጅ የሰጠህ አምላክ ምነው ለኔ ልጅ ነሳኸኝ?›› እያለች ምርር ብላ አለቀሰች፡፡ እንዲህ ብለው ሲያዝኑ ሲጸልዩ ውለው ከዘካርያስ ከሊቀ ካህናቱ ሄደው ‹‹አቤቱ ጌታችን ሆይ ወንድ ልጅ ብንወልድ ተምሮ ቤተ እግዚአብሔርን አገልግሎ እንዲኖር እንሰጣለን፤ ሴት ልጅም ብንወልድ ውኃ ቀድታ መሶብ ወርቅ ሰፍታ መጋረጃ ፈትላ ካህናትን አገልግላ እንድትኖር እንሰጣለን›› ብለው ስዕለት ገቡ፡፡ ዘካርያስም ‹‹እግዚአብሔር ጸሎታችሁን ይስማችሁ ስዕለታችሁን ይቀበልላችሁ የልቦናችሁን ሀሳብ ይፈጽምላችሁ›› ብሎ አሳረገላቸው።
ከዚህም በኋላ ቅድስት ሐና እና ቅዱስ ኢያቄም ዕለቱን ራእይ አይተው ነገር አግኝተው አደሩ፡፡ ራእዩስ እንዴት ነው ቢሉ ኢያቄም ‹‹7ቱ ሰማያት እንደ መጋረጃ ተገልጠው ከላይኛው ሰማይ ነጭ ወፍ ወርዶ በራሴ ላይ ሲቀመጥ አየሁ›› አላት፡፡ ‹‹ወፍ›› የተባለው ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ነው፤ ነጭነቱ ንጽሐ ባህሪው ነው፤ ‹‹ከላይኛው ሰማይ ነጭ ወፍ ወርዶ በራሴ ላይ ሲቀመጥ አየሁ›› ማለቱ የኢያቄምን (የሰውን) ባህርይ ባህርይ እንዳደረገው ዕወቅ ሲል ነው፡፡ 7ቱ ሰማያት የተባሉ የጌታችን ልዩ ልዩ ባሕርይው ምልአቱ ስፋቱ ርቀቱ ልዕልናው ናቸው፡፡ ሐናም ‹‹እኔም ደግሞ አየሁ እንጂ›› አለችው፡፡ ‹‹ምን አየሽ?›› ቢላት ‹‹ነጭ ርግብ መጥታ በራሴ ላይ ወርዳ በጆሮዬ ገብታ በማህጸኔ ስትተኛ አየሁ›› አለችው፡፡ ‹‹ርግብ›› የተባለች እመቤታችን ድንግል ማርያም ናት፤ ነጭነቱ ንጽህናዋ ቅድስናዋ ድንግልናዋ ነው፡፡ ‹‹ነጭ ርግብ መጥታ በራሴ ላይ ተቀምጣ ከራሴ ወርዳ በጆሮዬ ገብታ በማኅፀኔ ስትተኛ አየሁ›› ማለቷ ብሥራተ ገብርኤልን በጆሮዋ ሰምታ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ጌታችንን መፀነሷን ነው፡፡ ይህንኑም ራእይ ያዩት ሐምሌ 30 ዕለት ነው፡፡
እነርሱም እንዲህ ያለ ራእይ ካየን ነገር ካገኘን ብለው ዕለቱን በሩካቤ ሥጋ አልተገናኙም ይልቁንም ፈቃደ እግዚአብሔር ቢሆን ብለው አዳምንና ሔዋንን ‹‹‹ብዙ ተባዙ ምድርንም ምሉአት›› ብሎ ያበሰረ አምላክ ለእኛስ ይልክልን የለምን?›› ብለው ዕለቱን አልጋ ምንጣፍ ለይተው እስከ 7 ቀን ድረስ ለየብቻቸው ሰነበቱ፡፡ ነሐሴ በባተ በሰባተኛው ቀን ‹‹‹ከሰው የበለጠች ከመላእክት የከበረች ደግ ፍጥረት ትወልዳላቹህና ዛሬ በሩካቤ ሥጋ ተገናኙ› ብሎሏችኀል ጌታ›› ብሎ መልአኩ ለቅድስት ሐና ነገራት፡፡ በፈቃደ እግዚአብሔርር በብሥራተ መልአክ እመቤታችን እግዝእትነ ማርያምን ፀነሰቻት፡፡

በእንተ ቅዱሳን ኅሩያን (ከገድላት አንደበት)

20 Nov, 00:55


እግዚአብሔር አምላክ አብርሃምን እና ሳራን የተመለከተ አምላክ በኢያቄምና ሐና አማካኝነት ለዓለም ድኅነት ምክንያት የሆነችውን እና ዓለም ሳይፈጠር በአምላክ ልቦና ታስባ ትኖር የነበረች የተነገረላት ትንቢት ሊፈጸም የአባት የእናቷ የቅድመ አያቶቿ ራእይ ሊተረጎም ጌታ የፈቀደበት ጊዜ ሲደርስ እመቤታችን እግዝእትነ ማርያም እሁድ እለት ነሐሴ 7 ቀን በ16 ዓ.ዓ ተፀነሰች፡፡
እመቤታችን ከተፀነሰች በኋላ አይሁድ ቀንተው ተነሱባቸው ቅናቱ እንዴት ነው ቢሉ ሳሚናስ የሚባል የጦሊቅ ልጅ ከኤዶቅ ካጎቱ ቤት ሄዶ ሞተ፤ እነርሱም እንቀብራለን ብለው ባልጋ ይዘው ሲሄዱ ከመንገድ አሳረፉት፡፡ ቅድስት ሐናም የአጎቷ ልጅ ነበርና ለማልቀስ ብትደርስ ዘመዶቿ ሁሉ ተሰብስበው ሲላቀሱ ቆዯአት፤ እርሷም አብራ እየዞረች ስታለቅስ ጥላዋ ቢያርፍበት መግነዝ ፍቱልኝ ሳይል ብድግ ብሎ ተነሥቶ "ስብሃት ለኪ ማርያም እሙ ለፀሐየ ጽድቅ ለአብ ሙሽራው ለወልድ ወላዲቱ ለመንፈስ ቅዱስ ጽርሃ ቤቱ ተፈስሂ ደስ ይበልሽ" ብሎ ሰገደላት፡፡ አይሁድም ይህ ተአምር ሲደረግ ከዚያው ነበሩና "ምነው ሳሚናስ ምን አየህ? ምን ትላለህ?" ቢሉት "ከዚች ከሐና ማኅፀን የምትወለደው ሕፃን ሰማይ ምድርን አየርን የፈጠረ አምላክን ትወልዳለች እያሉ መላእክት ሁሉ ሲያመሰግኗት ሰማሁ" አላቸው፡፡ ዳግመኛም "እኔንም ያነሣችኝ የፈወሰችኝ ያዳነችኝ እርሷ ናት" አላቸው፡፡ አይሁድም "በል ተወው ሰማንህ" ብለው ቅናት ጀመሩ፡፡ ሐና በእርጅናዋ ጊዜ መፀነሷን የተመለከቱ ዘመዶቿና ያገሯ ሰዎች ተገርመው እየመጡ ይጠይቋት ነበር፡፡ እመቤታችን ማርያም በፅንስ እያለች ብዙ ታምራትን አድርጋለች። ከእነዚህም መካከል ዐይነ ስውር የነበረችው የአርሳባን ልጅ ወደ ሐና መጥታ እውነትም ሐና መጸነሷን ለማረጋገጥ ሆዷን ዳሰሰቻት፡፡ እርሷም ሳታስበው ዐይኗን ስትነካ ዐይኗ በራላት፡፡ እመቤታችንም በተፀነሰች በ9 ወር ከአምስት ቀን የግንቦት መባቻ ዕለት ግንቦት 1 ተወለደች፡፡
አምላክን የወለደች የድንግል ማርያም እናት የክብርት ሐና ዐፅሟን አባቶቻችን ከቅዱስ መስቀሉ ጋር ወደ አገራችን ኢትዮጵያ አምጥተውልናል፡፡ የጌታችን ቅዱስና ክቡር መስቀል ካለበት በወርቅ ከተለበጠው ከዕንጨቱ ሣጥን ውስጥ ዐፅማቸው በክብር ከተቀመጡ ብዙ የከበሩ ቅዱሳን ውስጥ አንዱ ይህ የእናታችን የቅድስት ሐና ዐፅም ነው፡፡ ይህንንም መጽሐፈ ጤፉት በደንብ ይገልጸዋል፡፡
የእናታችን የቅድስት ሐና ረድኤት በረከቷ ይደርብን፣ በጸሎቷ ይማረን!

በእንተ ቅዱሳን ኅሩያን (ከገድላት አንደበት)

16 Nov, 17:12


አንድ አምላክ በሚሆን በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም አሜን
ኅዳር 8-አርባዕቱ እንስሳ (ኪሩቤል) የሥሉስ ቅዱስን መንበር ለመሸከም የተሾሙበት ዕለት ነው፡፡
+ ሊቀ መላእክት ቅዱስ አፍኒን የተሾመበት ዓመታዊ በዓሉ ነው፡፡
+ የአረማዊ መኮንን ልጅ የነበረው ቅዱስ ቅፍሮንያ ዕረፍቱ ነው፡፡ ይኸውም ቅዱስ አስቀድሞ የአረማዊ መኮንን ልጅ የነበረ ነው፡፡ እርሱም ልጅ ሆኖ ሳለ ከአባ ጳኩሚስ ገዳም ወደ አገሪቱ የመጣው ስሙ መርቆሬዎስ የሚባል መነኩሴ ይህ የአረማዊን ልጅ ደገኛ ክርስቲያን እንደሚሆን ትንቢት ተናገረ፡፡
ከጥቂት ወራትም በኋላ ቅፍሮንያ ገዳማትን ሊያጠፋ የአባቱን ሠራዊት ሰብበስቦ ወደ ግብፅ ዘመተ፡፡ ወደ አባ ጳኩሚስ ገዳም በደረሰ ጊዜ ግን የሆነው ሌላ ነው፡፡ የዚህም ቅዱስ ጥሪው የሐዋርያው የቅዱስ ጳውሎስን ጥሪ ይመስላል፡፡ ቅፍሮንያ ገዳሙን ለማጥፋት መጥቶ ሳለ ገና የገዳሙን ድንበር እንደረገጠ ልቡ ራደ፣ አእምሮው ታወከ፡፡ ዐይነ ልቡናውም በርቶላት አበ ምኔቱን ባያቸው ጊዜ ብቻቸውን ገለል አድርጎ እንዲያመነኩሱት ጠየቃቸው፡፡ እርሳቸውም ስለ እርሱ አስቀድመው በመንፈስ ዐውቀው ነበርና በጄ አሉት፡፡ ቅፍሮንያም ሠራዊቱን ወደ አገራቸው እንዲመለሱ ነገራቸውና እርሱ በዚያው መንኩሶ ቀረ፡፡ ከዚህም በኋላ የምንኩስናን ሥራ ሌት ተቀን በመሥራት በመንፈሳዊ ተጋድሎው በረታ፡፡ ጾም ጸሎትን በማብዛት መጋደል እንደጀመረ ሰይጣን በፈተና ከሕይወት መንገድ ሊያስወጣው ነገረ ሠሪ አስነሣበት፡፡ በዚህም ምክንያት የአገሪቱ መኳንንት ሁሉ ‹‹‹አገራችን ያጠፋ የመኮንን ልጅ ከዚህ አለ›› ብለው ቅፍሮንያን ወስደው ሊገድሉ መጥተው ገዳሙን ወረሩት፡፡ ነገር ግን እግዚአብሔር ቅዱስ ቅፍሮንያን ሠወረባቸውና ፈጽመው ሊያገኙት አልቻሉም፡፡ እርሱንም ማግኘት ባልቻሉ ጊዜ ራሱን ነገረ ሠሪውን ገድለውት ተመለሱ፡፡
ቅዱስ ቅፍሮንያም በገድል ላይ ገድል እየጨመረ ትሩፋትን አበዛ፡፡ በየሰባት ቀንም ይጾም ጀመር፡፡ የሚመገበውን መራራ የአደንጓሬ ፍሬን ብቻ ሆነ፡፡ እርሱ በነበረበትም ወራት የምድር አውሬ እንስሶቻቸውን እየገደለ በገዳሙ ላይ ታላቅ ጥፋት አደረሰ፡፡ አባ ቅፍሮንያም ወደዚህ ክፉ አውሬ መጥቶ እንደበግ ይዞ አሠረው፡፡ ክፉውም አውሬ እንደታሠረ 10 ዓመት ኖሮ ሞተ፡፡ ከዚህም በኋላ ቅዱስ ቅፍሮንያ የታዘዘ መልአክ እየመራው ኢየሩሳሌም በአንዲት ቀን አደረሰው፡፡ በዚያም ብዙ ምሥጢርን እግዚአብሔር ገለጠለት፡፡ ከከበሩ ቦታዎችም ተባርኮ ወደ በዓቱ ተመልሶ ተጋድሎውን ፈጽሞ በሰላም ዐረፈ፡፡
ረድኤት በረከቱ ይደርብን፣ በጸሎቱ ይማረን!
+ + +
አርባዕቱ እንስሳ (ኪሩቤል)፡- እነዚህም የእግዚብሔርን መንበሩን የሚሸከሙ የእግዚአብሔር ሠረገላዎቹ ናቸው፡፡ ስለ እነርሱም ወንጌል የጻፈ ቅዱስ ዮሐንስ እንዲህ ሲል ጻፈ፡- ‹‹በዚያ ዙፋን ፊት በረድ የሚመስል ባሕር አለ፣ በዙፋኑም ዙርያ አራት እንስሶች አሉ በፊትም በኋላም ዐይንን ተመሉ ናቸው፡፡ የፊተኛው አንበሳ ይመስላል፣ ሁለተኛውም ላም ይመስላል፣ ሦስተኛውም የሰው መልክ ይመስላል፣ አራተኛውም ሚበር አሞራ ይመስላል፡፡›› እነዚህም የአራቱ እንስሶች እንያንዳንዱ ክንፋቸው ስድስት ስድስት ነው፣ ሁለተንተናቸውም ዐይኖችን የተመሉ ናቸው፡፡ በመዓልትና በሌሊት ዕረፍት የላቸውምና ‹‹የነበረ የሚኖር የአማልክት አምላክ እግዚአብሔር ጽኑዕ ክቡር ልዩ ነው›› እያሉ ያለመሰግናሉ፡፡ ራእ 4፡7፡፡
ዳግመኛም ነቢዩ ኢሳይያስ በራእይ ያየውን ሲናገር ስለ እነርሱ እንዲህ አለ፡- ‹‹ንጉሡ ዖዝያን በሞተበት ዓመት እግዚአብሔርን በረጅምና ከፍ ባለ ዙፋን ላይ ተቀምጦ አየሁት፤ የልብሱም ዘርፍ መቅደሱን ሞልቶት ነበር፡፡ ሱራፌልም ከእርሱ በላይ ቆመው ነበር፥ ለእያንዳንዱም ስድስት ክንፍ ነበረው፤ በሁለት ክንፍ ፊቱን ይሸፍን ነበር፥ በሁለቱም ክንፍ እግሮቹን ይሸፍን ነበር፣ በሁለቱም ክንፍ ይበር ነበር፡፡ አንዱም ለአንዱ ‹ቅዱስ ቅዱስ ቅዱስ የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር ምድር ሁሉ ከክብሩ ተሞልታለች እያለ ይጮኽ ነበር፡፡ የመድረኩም መሠረት ከጭዋኺው ድምፅ የተነሣ ተናወጠ፣ ቤቱንም ጢስ ሞላበት፡፡ ኢሳ 61-4፡፡
ነቢዩ ዳዊትም ‹‹እግዚአብሔር በኪሩቤል ላይ ተቀምጦ በረረ›› አለ፡፡ ሁለተኛም በኪሩቤል ላይ የተቀመጠ እርሱ ምድርን አናወጻት›› አለ፡፡ ሕዝቅኤልም ‹‹ከወደ ሰሜን እነሆ ጥቅል ነፋስ ሲመጣ አየሁ፣ ታላቅ ደመናም አለ፣ በዙሪያውም ብርሃን አለ፣ ከእርሱም እሳት ቦግ ብሎ ይወጣል፡፡ በደመናውም መካከል ባለ በእሳቱ ውስጥ እንደ አራት እራስ አሞራ መልክ የሚመስል አለ፣ በመካከሉም እንደ አራቱ ኪሩቤል መልክ ያለ አለ፡፡››
ወንጌላዊ ዮሐንስም ዳግመኛ እንዲህ አለ፡- ‹‹በዙፋኑ ዙሪያ የብዙ መላእክትን ድምፅ ሰማሁ፣ የእንስሶቹንም የእነዚያ አለቆችንም ቃል ሰማሁ ቁጥራቸውም እልፍ አለቆች ያሏቸው ብዙ የብዙ ብዙ ነው፡፡ ለዚያ ለተገደለው በግ ኃይል ባለጸግነትን ጥበብን ጽናትን መንግሥትን ክብርን ጌትነትን ምስጋናን ገንዘብ ሊያደርግ ይገባዋል›› ብለው በታላቅ ቃል ተናገሩ፡፡ ዳግመኛም ‹‹በሰማይና በምድር ከምድርም በታች በባሕር ውስጥ የተፈጠረው ፍጥረት ሁሉ ጌትነት ክብር ኃይል በረከት በዙፋኑ ለተቀመጠው ለእርሱ ለበጉም ለዘለዓለሙ ይባዋል፡፡›› እነዚህም አራቱ እንስሶች አሜን ይላሉ፣ እነኚያም አለቆች ይሰግዳሉ፡፡
ስለ እርባዕቱ እንስሳ ስለ ልዕልናቸውና ስለ ክብራቸው ከብሉይና ከሐዲስ ብዙ መጻሕፍት መስክረዋል፡፡ መሐሪ ይቅር ባይ ልዑል እግዚአብሔርም ስለሁሉ ፍጥረት ይለምኑት ዘንድ ቀራቢቆቹ አደረጋቸው፡፡ ገጸ ሰብእ ስለ ሰው ፍጥረት ይለምናል፣ ገጸ አንበሳ ስለ አራዊት ይለምናል፣ ገጸ ላሕም ስለ እንስሳት ይልምናል፣ ገጸ ንስርም ስለ አእዋፍ ይለምናል፡፡ ከሰማይ ሠራዊት ሁሉ እነርሱ በእግዚአብሔር ዘንድ በባለሟልነት እጅግ ቀረቡ ናቸውና፡፡ ስለዚህም በዓለሙ ሁሉ በስማቸው አብያተ ክርስቲያናት እንዲታነጹ በዚህችም ቀን መታሰቢያቸው እንዲደረግ አባቶች አዘዙ፡፡
+ + +
ዳግመኛም በዚህች ዕለት ሊቀ መላእክት ቅዱስ አፍኒን የተሾመበት ዓመታዊ በዓሉ ነው፡፡ ይህም ሱራፌልና ከኪሩቤል ጋር የልዑልን የጌትነቱን ዙፋን የሚጠብቅ ነው፡፡ ስለዚህም ክቡር መልአክ ሄኖክ እንዲህ አለ፡- ‹‹…ያንን ቤት ሱራፌልና አፍኒን ዙሪያውን እየዞሩ ይጠብቁታል፣ እነርሱም የልዑልን የጌትነቱን ዙፋን ሲጠብቁ የማያንቀላፉ ናቸው፡፡›› ቅዱስ ዮሐንስ በራእዩ ‹‹በእግዚአብሔር ፊት የሚቆሙ 7 መላእክትን አየሁ›› (ራዕ 8፡2) እንዳለ ሊቃነ መላእክት በቁጥር 7 ናቸው፡፡ እነርሱም፡- ቅዱስ ሚካኤል፣ ቅዱስ ገብርኤል፣ ቅዱስ ሩፋኤል፣ ቅዱስ ራጉኤል፣ ቅዱስ ዑራኤል፣ ቅዱስ ፋኑኤልና ኅዳር 8 ቀን የተሾመበትን ዓመታዊ በዓሉን የምናከብርለት ቅዱስ አፍኒን ናቸው፡፡

የሥሉስ ቅዱስን መንበር ለመሸከም የተሾሙ የአርባዕቱ እንስሳ (ኪሩቤል) እና የሊቀ መላእክት የቅዱስ አፍኒን ጥበቃና ምልጃ አይለየን!

በእንተ ቅዱሳን ኅሩያን (ከገድላት አንደበት)

16 Nov, 17:11


ሰውነቱ ሁሉ ደከመ፤ መናገርም ተሳነው፣ እነዚያ ቅዱሳን ግን ዕረፍቱን አይቶ ምስክር ይሆን ዘንድ ገብረ እንድርያስን ሊጠሩት ሔዱ ቅዱሳኑም ወደ እርሱ ደርሰው የአቡነ ገብረ መንፈስ ቅዱስን ዕረፍት ነገሩት። እርሱም

በሰማ ጊዜ እጅግ አዘነ፤ መራራ ለቅሶንም አለቀሰ፤ ተነሥቶም ከእነርሱ ጋር ሔዶ ብፁዓዊ አባታችን ወዳለበት ደረሰ። ያንጊዜም ቅዳሜ ማታ ለእሑድ አጥቢያ ነበረ።”

የቅዱሳን አባቶቻችን የአቡነ ገብረ እንድርያስና የአቡነ ገብረ መንፈስ ረድኤት በረከታቸው ይደርብን፣ በጸሎታቸው ይማረን።

በእንተ ቅዱሳን ኅሩያን (ከገድላት አንደበት)

16 Nov, 17:11


ኅዳር 7 ቀን በዓመታዊ የዕረፍት በዓላታቸው ታስበው የሚውሉት የቦረናው አቡነ ገብረ እንድርያስ ወደ ኢየሩሳሌም ሲመላለሱ በታላቅ ድንጋይ ላይ ተጭነው ነበር፣ ድንጋዩም በደመና አምሳል ይታዘዛቸው የነበረ ሲሆን አስገራሚው ጠበላቸው ውስጥ እንጨት ሲነከርበት እንጨቱ በተአምራት ነጭ መቁጠሪያ ሆኖ ይወጣል፡፡ (የፎቶው ላይ የሚታየውም ይኸው ዕንጨቱ ከጠበላቸው ውስጥ በተአምራት ነጭ መቁጠሪያ ሆኖ የወጣው መቁጠሪያ ነው፡፡ እርሱም ለእንቅርትና ለልዩ ልዩ ሕመሞች መድኃኒት ነው፡፡)

አቡነ ገብረ እንድርያስ ደብረ ቆበት የሚባለው ገዳማቸው ደቡብ ወሎ ከዓዲ ከተማ በስተ ምዕራብ አቅጣጫ ከባሕር ጠለል 6652 ጫማ ከፍታ ላይ ያገኛል። ገዳሙ በአባይ ተፋሰስ ዙሪያ ከወተት ወንዝ በስተሰሜን፡ ከደብረ ዘመዶ ማርያም (ዘሞድ) መንደር በስተደቡብ ምሥራቅ እና ከደብረ ሰኮሩ ሥላሴ በስተምዕራብ አቅጣጫ ላይ ይገኛል።

ደብረ ቆዘት አቡነ ገብረ እንድርያስ ገዳም የተመሠረተው በ995 ዓ ም 10ኛው መ/ክ /ዘ ላይ ነው። የገዳሙም መሥራች አባ ገብረ ክርስቶስ የተባሉ ታላቅ ጻድቅ መሆናቸውን የአቡነ ገብረ እንድርያስ ገድል ይናገራል።

ገዳሙ ያለበት አካባቢ አቡን ውኃ ተብሎ ይጠራል። ከገዳሙ ፊት ለፊት ከጣቀት ወንዝ ማዶ ደግሞ ዳቆን ውኃ (ደቶኑ) የሚባል አካባቢ ይገኛል። እነዚኽ አካባቢዎች ይኽንን መጠሪያ ያገኙት ቀድሞ በዚኽ አካባቢ በርካታ ገዳማትና አብያተ ክርስቲያናት የነበሩበት እንደሆነና የቦታዎች መጠሪያም በቦታው ካሉ ምእመናን መኖሪያ ጋር የተያያዘ መሆኑን አባቶች ይናገራሉ። አቡን ውኃ በሚባለው አካባቢ አባ ኤልሳዕ፣ አባ ጎርጎርዮስ፡ አባ ገብረ ክርስቶስ አባ ቅዱስ አባ መስቀል አባ ጉባ የተባሉ ሰባት ቅዱሳን አባቶች በቦታው ይኖሩ እንደነበርና ከዚኽ ብዙ ሳይርቅ የዲያቆኖች መኖሪያ ሰፈር ስለነበር ቦታው ወደቆኑ የሚለውን ስያሜ እንደተሰጠው አባቶች ሲናገሩ አካባቢው ዛሬም ድረስ ይኸንን መጠሪያ እንደያዘ ነው። አቡን በቀድሞው ዘመን ለጳጳስ ብቻ ሳይሆን ሥልጣነ ክህነት ላላቸው ቀሳውስትና መነኲሳት መጠሪያነት ያገለግል እንደ ነበር ፕሮፌስር ጌታቸው ኃይሌ ባሕረ ሀሳብ በሚለው መጽሐፍቸው ላይ ገልጠዋል

የአቡነ እንድርያስ አባታቸው ተንሥአ ክርስቶስ
እናታቸው አርሴማ ይባላሉ። ሁለቱም ደጋግ ቅዱሳን ናቸው። ዕድሜያቸው ለትምህርት ሲደርስ ለመምህር ሰጧቸው። መምህሩም ጸጋ እግዚአብሔር እንዳደረባቸው ዐውቀው ብዙዎችን የምታድን ጻድቅ ትሆናለህ ብለው ትንቢት ነግረዋቸዋል። የመጻሕፍትንም ትርጓሜ በሚገባ ካስተማሯቸው በኋላ ንፍታሌም ይባል የነበረውን ስማቸውን ለውጠው ገብረ እንድርያስ አሏቸው። ጻድቁ በአቡነ ዮሐንስ ከማ ገዳም ለረጅም ጊዜ በታላቅ ተጋድሎ አገልግለዋል። አባታችን ሙታንን በማስነሣትና ድውያንን በመፈወስ ብዙ ተአምራትን ሲያደርጉ ኖረዋል። የትዉልድ ሀገራቸው በቤተ አምሃራ ክፍል ሀገረ ወለቃ ከገዳማቸው ቅርብ ርቀት ላይ "ደብረ ደብቄ ማርያም" እንደሆነና የአቡነ ገብረ ክርስቶስ ደቀ መዝሙር እንደነበሩ እንዲሁም የመጀመሪያ ስማቸው ንፌታሌም ይባል እንደነበር፣ ካህንና የአምስት ልጆች አባትም እንደሆኑ በገድላቸው ላይ ተጽፎ ይገኛል።

አቡነ ገብረ ክርስቶስ ጽኑ የሆነውን ተጋድሏቸውንና መልካም አገልግሎታቸውን ፈጽመው በሞት ከማረፋቸው በፊት የገዳሙ አበምኔት ሆነው እንዲያገለግሉ ንፌታሌምን (አቡነ ገብረ እንድርያስን) መርጠው እንደሾሟቸው በመጽሐፈ ገድላቸው ላይ ተጽፏል። አቡነ ገብረ እንድርያስ ዘደብረ ቆዘት ከሀገረ ወለቃ እስከ ጎጃም ድረስ ስብከተ ወንጌል እንዳስፋፉ የቤተ ክርስቲያን መዝገበ ቃላት በሚለው መጽሐፍ ላይ ተጽፎ ይገኛል።

አቡነ ገብረ እንድርያስ በደብረ ርስኩር (በአሁኑ ደብረ ብርሃን ሰኮሩ ሥላሴ) ቤተ ክርስቲያን በሱባኤ ላይ እንዳሉ መልአኩ ቅዱስ ዑራኤል በወርቅ ጽዋ ሰማያዊ ወይንና ሰማያዊ ኅብስት መግቧቸዋል። እንዲሁም አምላክን የወለደች ክብርት እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ሦስት ጽዋ ማየ ሕይወት ካጠጣቻቸው በኋላ ሕሙማንን እንደፈወሱ፣ ዕዉራንን እንዳበሩ፣ ሙት እንዳስነሡ በገድላቸው ላይ ተጽፏል።

የአቡነ ገብረ እንድርያስ አባት የሆኑት የአቡነ ገብረ ክርስቶስ ጥንታዊ ውቅር ቤተ ክርስቲያን በአሁኑ ጊዜ ጠፍ ሆኖ ስለቀረ ከዚሁ ገዳም አቅራቢያ የልጃቸው የአቡነ ገብረ እንድርያስ ገዳም ተመሥርቶ አገልግሎት እየሰጠ ይገኛል። አዲሱ ቤተ ክርስቲያን ለመጀመርያ ጊዜ የተሠራው በዐፄ ድል ነአድ ዘመነ መንግሥት ሲሆን ከዚያም በኋላ በተደጋጋሚ እድሳት ተደርጎለታል

ጻድቁ አቡነ ገብረ እንድርያስ እግዚአብሔር ኀጥአንን እንዲምርላቸው ጣቀት ንዝ ከተባለው ቦታ ላይ በአንገታቸው ላይ ትልቅ ድንጋይ እየተሸከሙ ይጸልዩ እንደነበርና ይጸልዩበት ከነበረው ወንዝ ውስጥ በተኣምራት መቍጠሪያ የሚሠራ መል እንደፈለቀላቸው በገድላቸው ላይ ተጽፏል።

ከገዳሙ በስተደቡብ አቅጣጫ እግዚአብሔር ኀጥአንን እንዲምርላቸው ጣቀት ወንዝ ከተባለው ቦታ ላይ በአንገታቸው ድንጋይ አሥረው ይጸልዩበት ከነበረው ጣቀት ወንዝ ላይ በተኣምራት መቍጠሪያ የሚሠራው የአባ ጎርጎርዮስ ( ወንበረ ሥላሴ) ጠበል እና ሌሎችም በርካታ ጠበሎች ይገኛሉ። እነዚኽም ጠበሎች ሕሙማን ከተለያዩ በሽታዎች ለመፈወስ ከማገልገላቸውም በላይ መነኰሳት ለጸሎት የሚገለገሉበትን መቍጠሪያ በተኣምራት ይሰጣሉ። አዘገጃጀቱም እንዲህ ነው- በመጀመርያ በጠበሉ ላይ ገመድ ሣር ወይም ቀጭን ዕንጨት በመንከር ኩቆይታ በኋላ በተነከረው ገመድ፣ ሣር ወይም ዕንጨት ላይ ጠንካራ ዓለት ይሠራል፤ ጠበሉ ውስጥ በተነከረው ገመድ ወይም ክር ላይ ውኃው በተኣምራት ወደ ጠንካራ ዓለትነት ይቀየራል። ከዚያም ገመዱን ወይም ክሩን ወይም ዕንጨቱን እሾልኮ በማውጣት ውስጡ ክፍት ስለሚሆን ያንን አስተካከለው እየከረከዉ | መቍጠሪያ መሥራት ይቻላል።

አቡነ ገብረ እንድርያስ ዘወትር ዐርብ ዐርብ ወደ ኢየሩሳሌም ሔደው የጌታችን የአምላካችን የኢየሱስ ክርስቶስን መካነ መቃብር ተሳልመው ቅዱስ ሥጋውን ክቡር ደሙን ተቀብለው ለመምጣት ይመላለሱ የነበረው በአንድ ትልቅ ድንጋይ ላይ ተቀምጠው ነው። ድንጋዩንም እንደ ደመና ይጠቀሙበት ነበር።

ከዚኸም ሌላ ጻድቁን የዛፍ ዋርካ እንደ ጥላ ሆኖ ያገለግላቸው ነበር። እርሳቸውም ድንጋይ
እንደ ሠረገላ፣ ዋርካውን እንደ ጥሳ እየተጠቀሙባቸው ወደ ኢየሩሳሌም ይመላለሱ እንደነበር በገድላቸው ላይ ተጽፏል። ያ እንደ ደመና ሠረገላ ሆኖ ለመጓጓዣነት ያገለግላቸው የነበረው ትልቅ 'ንጋይ ዛሬም ድረስ በገዳማቸው ውስጥ በክብር
ተቀምጦ ይገኛል። በዓለ ዕረፍታቸውም ኅዳር 7 ቀን በገዳማቸው በታላቅ ድምቀት ይከበራል።

አቡነ ገብረ እንድርያስ ታላቁን ጻድቅ አቡነ ገብረ መንፈስ ቅዱስን ያሟሟቱ ታላቅ ጻድቅ ናቸው፣ ይኸም ማለት ኣቡዪ ደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ክፍል በሚገኘው ገዳማቸው በምድረ ከብድ ባረፉ ጊዜ አቡነ ገብረ እንድርያስ ከደቡብ ወሎ ወለቃ በእግዚአብሔር መንፈስ ተመርተው በቅዱሳንም ጥሪ ተደርጎላቸው ወደ ምድረ ከብድ መጥተዋል። ይኸም በአቡዬ ገድል ገጽ 83 ላይ እንዲህ ተብሎ በግልጽ ተጽፏል፤ የአባታችን የገብረ መንፈስ ቅዱስ ዕለተ ዕረፍቱ በደረሰ ጊዜ ብዙ ኅቡዓን ቅዱሳን ወደእርሱ መጡ ስማቸውም ፍሬ ቅዱስ ዘርዐ ቡሩክ፡ ያዕቆብ ብንያም፤ ዮሴፍ ነው አባታችንም በሞት እንደሚያርፍና ቃልኪዳን እንደተሰጠው ነገራቸው። እነርሱም ስለ አባታችን ዕረፍት አዘነ እርሱ ርእሰ ባሕታውያን ነውና። በቀዳሚት ሰንበትም እያላበው በድካም እንደልማዱ ለፍጥረቱ ሁሉ ወደ አምላኩ መማለድን ሳያቋርጥ ዋለ። በመሸም ጊዜ

በእንተ ቅዱሳን ኅሩያን (ከገድላት አንደበት)

16 Nov, 17:10


ልጅን እርስ በእርስ እንዲተያዩ አድርጎ በሁለት መስቀሎች ላይ እርቃናቸውን ሰቀላቸው፡፡ በዚያን ጊዜም ደመና መጥታ ሸፈነቻቸው፡፡ በዚህም ጊዜ ብዙዎች በጌታችን አመኑ፡፡
ዳግመኛም ንጉሡ ቅድስት ዘኖብያንና ልጇን ቅዱስ ዘኖቢስን በብረት ወንበሮች ላይ አስሮ በማስቀመጥ ከሥር በሚነድ እሳት አቃጠላቸው፡፡ ጌታችንም ከዚህ ሥቃይ አዳናቸው፡፡ በወንበሩም ላይ ሆነው በእሳት እየተቃጠሉ ሳለ ሕዝቡን ያስተምሩ ጀመር፡፡ ንጉሡም ይህንን ባየጊዜ እጅግ ተቆጥቶ ቁመቱና ጎኑ ሃያ ሃያ ክንድ የሆነ ጉድጓድ ቆፍረው በውስጡም እሳትን እንዲያነዱበትና ቅዱሳኑን ከዚያ እንጨምሯቸው አደረገ፡፡ ነገር ግን አሁንም ቅድስት ዘኖብያና ልጇ ቅዱስ ዘኖቢስ ወደ እግዚአብሔር በጸለዩ ጊዜ እሳቱ ፈጥኖ ጠፋ፡፡
ንጉሡም ከዚህ በኋላ ማሠቃየት በሰለቸው ጊዜ በሰይፍ አንገታቸውን ቆርጠው እንገድሏቸውና እስከ በነጋታው ድረስ በድናቸውን ጠብቀው በእሳት እንዲያቃጥሉአቸው በነፋስም ውስጥ እንዲበትኑአቸው አዘዘ፡፡ ቅዱሳኑንም በገደሏቸው ጊዜ ነጎድጓድ መብረቅ ንውጽውጽታ ሆነ፣ ዝናብም ዘነበ፡፡ በዚህም ታላቅ ንውጽውጽታ ምክንያት 54 ሰዎች ሞቱ፡፡ በሌሊትም ምእመናን መጥተው የቅዱሳኑን ሥጋ በሥውር ወስደው ቀበሯቸው፡፡ በማግሥቱም ንጉሡ በድናቸውን በፈለገ ጊዜ የሆነውን ሁሉ ተረዳ፡፡ የሆነውን ሁሉ ባስተዋለ ጊዜ ዐይነ ልቡናው በራለትና በጌታችን አምኖ ንስሓ ገብቶ ተጠመቀ፡፡
+ + +
ሰማዕቱ አባ ናህርው፡- ይኸውም ቅዱስ ከግብጽ አገር ከፍዩም መንደር የተገኘ ታላቅ ሰማዕት ነው፡፡ ይኸውም ቅዱስ ፈሪሃ እግዚአብሔር በእጅጉ ያደረበት ደገኛ ክርስቲያን ነው፡፡ በእስክንድርያ አገር በከሃዲያን መኳንንት የሚሠቃዩትንና የሚሞቱትን የክርስቲያኖቹን ዜና በሰማ ጊዜ ለስም አጠራሩ ክብር ምስጋና ይሁንና ስለ ጌታችን ስለ ስሙ ሰማዕት ይሆን ዘንድ ተመኘ፣ የሰማዕትነት ክብርንም ይቀዳጅ ዘንድ ወደ እግዚአብሔር ጸለየ፡፡ እግዚአብሔር ጸሎቱን ሰማውና በራእይ ተገልጦለት ‹‹ወደ አንጾኪያ አገር ሂድ በዚያ በሰማዕትነት ትሞት ዘንድ አለህ›› አለው፡፡
አባ ናህርው ከዚህ በኋላ ወደዚያ እንዴት መድረስ እችላለሁ ብሎ ሲያስብ እግዚአብሔር ቅዱስ ሚካኤልን ላከለትና መልአኩ ይህንን ቅዱስ በክንፎቹ ተሸክሞ ወደ አንጾኪያ አገር አደረሰው፡፡ አንጾኪያ አገር ላይ ያለው ንጉሥ ደግሞ እጅግ ጨካኝ የሆነው የክርስቲያኖችን ደም በዓለም ዙሪያ ያፈስ የነበረው ዲዮቅልጥያኖስ ነበር፡፡ እናም አባ ናህርው በከሃዲው ንጉሥ ዲዮቅልጥያኖስ ፊት በደረሰ ጊዜ የእግዚአብሔርን ክብር መሰከረ፡፡ ንጉሡም ስሙንና አገሩን ጠየቀው፡፡ እርሱም ከግብጽ አገር እንደሆነ አስረዳው፡፡ ንጉሡም ቃሉን ከሰማ በኋላ ለጣዖታቱ ቢሠዋለት ብዙ ገንዘብና ሥልጣን እንደሚሰጠው ቃል ገባለት፡፡ ነገር ግን አባ ናህርው በጌታችን ታመነ፡፡ ንጉሡም ‹‹ትእዛዜን አልሰማም ካልክ አሠቃይቼ ለሞት እዳርግሃለሁ›› እያለ በተደጋጋሚ ቢናገረውም አባ ናህርው ግን ከሥቃዩ የተነሣ አልፈራም፡፡
ከዚህም በኋላ ንጉሡ ቅዱስ አባ ናህርውን በብዙ ዓይነት ሥቃዮች እንዲያሠቃዩት አደረገው፡፡ በእሳት ውስጥ ቢጨምሩት ረድኤተ እግዚአብሔር ጠብቆት ምንም ሳይቃጠል ቀረ፡፡ ዳግመኛም ለተራቡ አንበሶች ቢሰጡት አንበሶቹም ምንም ሳይነኩት ቀሩ፡፡ በሌላም ጊዜ በትልቅ ወጪት አድርገው በእሳት ቀቀሉት ነገር ግን አሁንም ምንም አልሆነም፡፡ ከዚህም በኋላ ንጉሡ ዲዮቅልጥያኖስ አባ ናህርውን ማሠቃየት በሰለቸው ጊዜ በዚህች ዕለት አንገቱን በሰይፍ አስቆረጠውና የቅዱስ አባታችን የሰማዕትነት ፍጻሜአቸው ሆነ፡፡
ከዚህም በኋላ የከሃዲውን ንጉሡ የዲዮቅልጥያኖስን ፍጻሜ ማየቱ ተገቢ ነው፡፡ ይህንን ከሃዲ ንጉሥ የልዳው ፀሐይ ሰማዕቱ ቅዱስ ጊዮርጊስ በተአምራት እንደገደለውና ፈጽሞ እንዳጠፋው በቅዱሱ ገድሉ ላይ ተጽፏል፡፡ እጅግ የከበሩ ታላላቆቹን ሰማዕታት እነ ቅዱስ ፋሲለደስንና አራቱን ልጆቹን አውሳብዮስን፣ መቃርስንና ሁለቱን ሴቶች ልጆቹን፣ ቅዱስ አባድርና እኅቱ ቅድስት ኢራኒን፣ ቅዱስ ፊቅጦርን፣ ምሥራዊ ቅዱስ ቴዎድሮስ፣ ቅዱስ ገላውዴዮስን፣ የንጉሡን ልጅ ቅዱስ ዮስጦስን፣ ቅዱስ አቦሊንና ቅድስት ታውክልያን… እነዚህንና ሌሎቹንም እጅግ የከበሩ ቅዱሳን ሰማዕታት በግፍ አሠቃይቶ የገደለው ከሃዲው ዲዮቅልጥያኖስ በዓለም ላይ እንደ እርሱ ያለ ቤተ ክርስቲያንን ያጠፋ የለም፡፡ በዓለም ላይ ከ470,000 ሺህ በላይ ሰማዕታትን በግፍ እንዳስገደለ በተለያዩ መዛግብት ላይ ተጠቅሷል፡፡
ኅዳር 7 ቀን የልዳው ፀሐይ ሰማዕቱ ቅዱስ ጊዮርጊስ በተአምራት ከሃዲውን ዲዮቅልጥያኖስን በክፉ አሟሟት ለገደለበት ተአምሩ መታሰቢያ በዓሉ ነውና አንድም ደግሞ ቅዳሴ ቤቱ ስለሆነ ይህንኑ ተአምሩን ቀጥሎ እንመለከታለን፡- በዚህች ዕለት የልዳው ፀሐይ የሊቀ ሰማዕታት የቅዱስ ጊዮርጊስ ቤተ ክርስቲያኑ የከበረችበት ዕለት ነው፡፡ ዳግመኛም ጌታችን በውስጧ ላደረገው ድንቅ ተአምር መታሰቢያ ሆነ፡፡ ይኸውም የሆነው እንዲህ ነው፡- በቅዱስ ጊዮርጊስ ቤተ ክርስቲያን ውስጥ ድንቅ ድንቅ ተአምራት እየተፈጸሙ እንደሆነ ከሃዲው ንጉሥ ዲዮቅልጥያኖስ በሰማ ጊዜ ይህችን ቤተ ክርስቲያን ሊያፈርሳት ወደደ፡፡ ሄዶም ፈጽሞ እንዲያፈርሳት ስሙ አውህዮስ የተባለ መኮንኑንም ከብዙ ሠራዊት ጋር ትእዛዝ ሰጥቶ ላከው፡፡ ያም መኮንን ከቦታው ልዳ በደረሰ ጊዜ ከቅዱስ ጊዮርጊስ ቤተ ክርስቲያን ውስጥ ገብቶ በሚያበራ ብርጭቆ ቀንዲል ተተክሎ መብራት እየበራ በፊቱም የሰማዕቱን የቅዱስ ጊዮርጊስን ሥዕል በተመለከተ ጊዜ ተቆጣና ፈጥኖ መስቀለኛውን ቀንዲል ሰበረው፡፡ ነገር ግን ወዲያው የመስተዋቱ ቀንዲል ስባሪው በራሱ ላይ ተሰካበትና አናቱ ቆስሎ በሰበሰ፣ በትልም ተወረረ፡፡ ተዘርሮ በወደቀ ጊዜ ጭፍሮቹም እጅግ ደንግጠውና በፍርሃት ተውጠው ከቤተ ክርስቲያን ተሸክመው አውጥተው እስከ ባሕሩ ዳርቻ ድረስ በቃሬዛ ወሰዱት፡፡ በመርከብም ውስጥ ሳለ ተሠቃይቶ ክፉ አሟሟት ሞተና ወስደው ከባሕር ውስጥ ጣሉት፡፡ ወደ ሀገራቸውም አፍረው ተመለሱ፡፡
አንጾኪያ ደርሰው የሆነውን ሁሉ ለንጉሥ ዲዮቅልጥያኖስ ነገሩት፡፡ እርሱም ይህንን በሰማ ጊዜ እጅግ ተቆጥቶ ከቀድሞው የበዛ ሠራዊት ይዞ የሰማዕቱን ቤተ ክርስቲያን ፈጽሞ ለማጥፋት እርሱ ራሱ ተነሥቶ ልዳ ወደምትባለው አገር ሄደ፡፡ ከቤተ ክርስቲያኒቱም ውስጥ ገባና በውስጣዊ ክፍል በመካከሉ ላይ ዙፋኑን ዘርግቶ ተቀመጠ፡፡ እግዚአብሔርም የመላእክት አለቃ ቅዱስ ሚካኤልንና ቅዱስ ጊዮርጊስን ከሰማይ ወደዚህ ከሃዲ ላካቸው፡፡ እነርሱም ሄደው የዲዮቅልጥያኖስን ዙፋን በገለበጡት ጊዜ በግራና በቀኝ የነበሩት የወርቅ አባባ ጌጦች ከግራና ከቀኝ ተገናኝተው በሁለቱም ዐይኖቹ ተሰኩና ዐይኖቹን አጠፉት፡፡ በዚህም ሠራዊቱ ሁሉ አፍረው ጥለውት እየሸሹ ወጡ፡፡ ከእርሱ ጋር አንድም ሰው እንኳን አልተገኘም ነበር፡፡ መንግሥቱም አለፈች፡፡ ከዚህም በኋላ ዲዮቅልጥያኖስ በታላቅ ሃፍረት ተመልቶ በእያንዳንዱ ምእመን ደጃፍ እየቆመ ምጽዋትን እስኪለምን ድረስ እጅግ የተዋረደ ሆነ፡፡
ከዕለታትም በአንደኛው ቀን ያንን ሁሉ ክፉ ሥራ ሲያሠራውና በዓለም ላይ ከ500 ሺህ በላይ ሰማዕታትን በግፍ ሲያስገድለው የኖረው ሰይጣን በገሃድ ለዲዮቅልጥያኖስ ተገለጠለትና ‹‹ወዳጄ ሆይ እንደምን አለህ?›› አለው፡፡ እርሱም ‹‹ወግድ ከእኔ ራቅ ክርስቲያኖች በመተታቸው እንደምታየኝ ይህን አደርገውብኛልና›› አለው፡፡ ሰይጣንም መልሶ ‹‹ዐይኖችህን ባበራልህና መንግሥትህንም ብመልስልህ ምን ወሮታ ትከፍለኛለህ?›› አለው፡፡ ዲዮቅልጥያኖስም ‹‹ይህንንስ ካደረክልኝ በምድር ላይ አንድ

በእንተ ቅዱሳን ኅሩያን (ከገድላት አንደበት)

16 Nov, 17:10


አንድ አምላክ በሚሆን በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም አሜን
ኅዳር 7-የልዳው ፀሐይ ሊቀ ሰማዕታት ቅዱስ ጊዮርጊስ በዓለም ላይ ከ470,000 ሺህ በላይ ሰማዕታትን በግፍ ያስገደለውን ከሃዲው ንጉሥ ዲዮቅልጥያኖስን በክፉ አሟሟት ለገደለበት ተአምሩ መታሰቢያ በዓሉ ነው፡፡ ቅዳሴ ቤቱም በዚሁ ዕለት ነው፡፡
+ በታላቅ ድንጋይ ላይ ተጭነው ወደ ኢየሩሳሌም ይመላለሱ የነበሩትና ፣ ድንጋዩም በደመና አምሳል ይታዘዛቸው የነበረ አስገራሚው ጠበላቸው ውስጥ እንጨት ሲነከርበት እንጨቱ በተአምራት ነጭ መቁጠሪያ የሚሆነው አቡነ ገብረ እንድርያስ ዕረፍታቸው ነው።
+ ዳግመኛም በዚህች ዕለት ሌላኛው የእስክንድርያው ሰማዕት ቅዱስ ጊዮርጊስ ዕረፍቱ ነው፡፡
+ አቡነ ሚናስ ዘሀገረ ተመይ ዕረፍታቸው ነው፡፡
+ ወንድማማቾቹ ሰማዕታት ቅዱስ መርቆሬዎስና ቅዱስ ዮሐንስ የሰማዕትነታቸው ፍጻሜ ሆነ፡፡
+ ቅድስት ዘኖብያ እና ልጇ ቅዱስ ዘኖቢስ በሰማዕትነት ዐረፉ፡፡
+ አባ ናህርው በሰማዕትነት ዐረፉ፡፡
ሰማዕቱ ቅዱስ ጊዮርጊስ ዘእስክንድርያ፡- አባቱ በእስክንድርያ አገር በንግድ ሥራ ይተዳደር የነበረ ሲሆን ልጅ ስላልነበረው በልዳው ኮከብ ቅዱስ ጊዮርጊስ ስም ወደተሠራች አንዲት ቤተ ክርስቲያን ሄዶ በቅዳሴ ቤቱ ክብረ በዓል ቀን ልጅ እንዲሰጠው ሰማዕቱን በስዕለት ጠየቀው፡፡ ስዕለቱም ተሰምቶለት ልጅ ሲወልድ ስሙን በሰማዕቱ ስም ጊዮርጊስ ብሎ ጠራው፡፡ ሚስቱም የእስክንድርያው አስተዳዳሪ የአርማንዮስ እኅት ናት፡፡ ጊዮርጊስ ከተወለደ በኋላ ብዙም ሳይቆዩ እናትና አባቱ ስለሞቱ አስተዳዳሪ አጎቱ ወስዶ አሳደገው፡፡ አጎቱም ጣዖትን የሚያመልክ ነው፡፡ ነገር ግን ጊዮርጊስ እስከ 20 ዓመቱ ድረስ በሃይማኖቱም እጅግ ጠንካራ ሆነ፡፡ በጾም በጸሎት እየተጋ ነዳያንን አብዝቶ ይመግብ ነበር፡፡ የጽድቅ ሥራውንም ሰው አያውቅበትም ነበር፡፡
የአስተዳዳሪው ብቸኛ ሴት ልጅ ልዩ ልዩ የተዋቡ ቦታዎችን ትጎበኝ ዘንድ ከቤት ወጥታ ወደ ደብረ ቁስቋም ስትደርስ የቤተ ክርስቲያንን የቅዳሴ ዝማሬ ሰምታ ልቧ እጅግ ደስ ተሰኘ፡፡ የአክስቷ ልጅ የሆነ ጊዮርጊስንም መነኮሳቱ ስለሚያሰሙት ዝማሬ ጠየቀችው፡፡ እርሱም ምንነቱን ካስረዳት በኋላ በዚያውም የሃይማኖትን ነገር በደንብ አስተማራት፡፡ ልጅቱም ወደ ከሃዲው አስተዳዳሪው አባቷ ዘንድ ቀርባ ስለ ጌታችን ክብር ትመሰክር ጀመር፡፡ አባቷም ሊሸነግላት ቢሞክር ነገሩን እንዳልሰማችው ሲያውቅ ብቸኛና አንድያ ልጁን አንገቷን በሰይፍ አስቆረጠው፡፡ ከዚህም በኋላ ‹‹ልጅህን አስተምሮ ያሳታት የእኅትህ ልጅ የሆነው ጊዮርጊስ ነው›› ብለው ለመኰንኑ ነገሩት፡፡ ቅዱስ ጊዮርጊስንም ይዞ ጽኑ ሥቃይን ካሠቃየው በኋላ ኅዳር 7 ቀን አንገቱን በሰይፍ ቆረጠውና ሰማዕትነቱን በድል ፈጸመ፡፡
+ + +
አቡነ ሚናስ ዘሀገረ ተመይ፡- ተመይ የምትባለው አገር ኤጲስ ቆጶስ የሆነው የአቡነ ሚናስ ወላጆቹ የመነኮሳትን ሥራ የሚሠሩ ደጋጎች ነበሩ፡፡ የቤተ ክርስቲያንንም ትምህርት እያስተማሩ አሳደጉት፡፡ ሲያድግም ያለፈቃዱ ሚስት አጋቡት፡፡ ወደ ጫጉላ ቤትም በገባ ጊዜ ድንግልናቸውን ይጠብቁ ዘንድ ከሚስቱ ጋር ተማክሮ ሁለቱም በንጽሕናና በድንግልና ሆነው በአንድነት ሊኖሩ ተስማሙ፡፡ ሌሊቱንም ሁሉ ለጸሎት ቆመው ያድሩ ነበር፡፡ እርሱም በዓለም እየኖሩ የምንኩስናን ሥራ ከመሥራት ይልቅ መንኩሶ ገዳም መግባት እንደሚሻል ለሚስቱ ሲነግራት ሸኝታ አሰናበተችው፡፡ አቡነ ሚናስም ወደ አቡነ እንጦንስ ገዳም ገባ ነገር ግን በንጉሡ ትእዛዝ ቤተሰቦቹ ቢያስፈልጉትም ጌታችን ሰውሮታል ሊያገኙት አልቻሉም፡፡ ከዚህም በኋላ ወደ አስቄጥስ ገዳም ሄደ፡፡

በዚያም ሁለቱ ብርሃን ከዋክብት አባ አብርሃምንና አባ ገዐርጊን በማገልገል ልጅ ሆናቸው፡፡ ተጋድሎአቸውንና ትምህርታቸውን በሚገባ ከተማረ በኋላ እርሱም በተጋድሎው አባ አብርሃምና አባ ገዐርጊ እስኪያደንቁትና እስኪገረሙበት ድረስ ከፍ ከፍ አለ፡፡ ከዚህም በኋላ ኤጲስ ቆጶስነት ይሾም ዘንድ ጌታችን መርጦት ለሊቀ ጳጳሳቱ እንዲሾመው ነገረው፡፡ ሊቀ ጳጳሳቱም ጠርተው ሲያስመጡት እምቢ ቢላቸውም የእግዚአብሔር ትእዛዝ መሆኑን ነግረውት ተመይ በሚባል አገር ላይ ሾሙት፡፡ አቡነ ሚናስ ከዚህም በኋላ ሀብተ ፈውስም ተሰጥቶት ብዙ ድውያንን የሚያድናቸው ሆነ፡፡ ሁለተኛም የተሰወረውን የማወቅ ሀብት ተሰጠውና በሰው ልቡና የታሰበውን የሚያውቅ ሆነ፡፡ አቡነ ሚናስ ለአራት ታላላቅ አባቶች አባት ሆኖ እጁን በላያቸው ላይ ጭኖ ሾሟቸዋል፡፡ እነርሱም ለእስክንድርያ አገር ሊቃነ ጳጳሳት የሆኑት አባ እለእስክንድሮስ፣ አባ ቆዝሞስ፣ አባ ቴዎድሮስና አባ ሚካኤል ናቸው፡፡ አባታችን በመጨረሻም ከዚህ ዓለም ድካም የሚያርፍበትን ጊዜ ዐውቆ ካህናቱንና ሕዝቡን ሁሉ ሰብስቦ በቀናች ሃይማኖት ጸንተው እንዲኖሩ ከመከሯቸው በኋላ ኅዳር 7 ቀን በሰላም ዐረፉ፡፡
+ + +
ሐዲስ ቅዱስ መርቆሬዎስና ወንድሙ ቅዱስ ዮሐንስ፡- እነዚህም ቅዱሳን የደጋግ ክርስቲያን ልጆች ናቸው፡፡ የታላቁ ስም ሙናሂ ነበር ሲመነኩስ ግን መርቆሬዎስ ተባለ፡፡ የታናሹም ስም አቡፈረዥ ነበር እርሱም ሲመነኩስ ዮሐንስ ተባለ፡፡ ሁለቱም ወንድማማቾች ወደ ሊቀ ሠራዊት ቅዱስ ቴዎድሮስ ገዳም ገብተው ጽኑ የሆነ ተጋድሎአቸውን ጀመሩ፡፡ ለመነኮሳቱ ሁሉ የሚላላኩና የሚያገለግሉ ሆኑ፡፡ ጣዕም ካላቸው ምግቦችና መጠጦች እንዲሁም ከእንቅልፍ እርቀው በታላቅ ተጋድሎ ኖሩ፡፡ የሚመገቡትም በሦስት ቀን አንድ ጊዜ ሆነ፡፡ የግብፅንና የሌላውንም ጽሕፈት ተምረው መጻሕፍትን መረመሩ፡፡ እነዚህም ወንድማማቾች አንድ ቀን አብረው ሳሉ የታዘዘ መልአክ ተገለጠላቸውና ወደ ምስክርነት አደባባይ ሄደው ስለጌታችን ስለ ስሙ እንዲመሰክሩና ሰማዕትነታቸውን እንዲፈጽሙ ነገራቸው፡፡
እነርሱም እንደታዘዙት በከሃዲው መኰንን ፊት ሄደው ስለ ጌታችን ክብር መሰከሩ፡፡ መኰንኑም የተለያዩ ጽኑ ሥቃዮችን አሠቃያቸው፡፡ ከብዙ ሥቃይም በኋላ በወህኒ ቤት ተጥለው ሳለ ሌላ መኰንን ተሹሞ እርሱም ሊተዋቸው በወደደ ጊዜ የአገሩ ሰዎች እነርሱን ካልገደልካቸው በንጉሡ ዘንድ እንከስሃለን›› አሉት፡፡ ይህም መኰንን ሕዝቡን ከመፍራቱ የተነሣ ፈቃዳቸውን ይፈጽምላቸው ዘንድ አሳልፎ ሰጣቸው፡፡ ሕዝቡም ኅዳር 7 ቀን ሐዲስ የተባለ የቅዱስ መርቆሬዎስንና የወንድሙ የቅዱስ ዮሐንስን ራስ በሰይፍ ከቆረጧቸው በኋላ የሰማዕትነት ፍጻሜአቸው ሆነ፡፡
+ + +
ቅድስት ዘኖብያ እና ልጇ ቅዱስ ዘኖቢስ፡- እነዚህም ቅዱሳን ተበይስ ከምትብል አገር ከታላላቅ ወገኖች የተገኙ ሰማዕታት ናቸው፡፡ እነርሱም ክርስቲያኖች እንደሆኑ በከሃዲው ንጉሥ ዘንድ ዜናቸው ተሰማ፡፡ ንጉሡም ወደ እርሱ ካስመጣቸው በኋላ እምነታቸውን መረመራቸው፡፡ እነርሱም ‹‹አገራችን ተበይስ ነው የምናመልከውም የክብርን ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስን ነው›› አሉት፡፡
ከዚህም በኋላ ንጉሡ እናትና ልጅን ‹‹ለአማልክት ሠው›› አላቸው፡፡ ቅዱሳኑም ‹‹እኛስ ለእውነተኛው አምላክ ለክርስቶስ እንሠዋለን እንጂ ለረከሱ ጣዖታት አንሠዋም›› አሉት፡፡ ንጉሡም በዚህ ጊዜ እጅግ ተቆጥቶ ቅድስት ዘኖብያንና ልጇን ቅዱስ ዘኖቢስን ጽኑ በሆነ ሥቃይ አሠቃያቸው፡፡ ልብሳቸውን ገፈው በራሳቸው ጸጉር ሰቅለው እየደበደቡ እንዲያሠቃዩአቸው አደረገ፡፡ ቅዱሳኑም ወደ እግዚአብሔር በጸለዩ ጊዜ ማሰሪያው በተአምራት ተፈታላቸው፡፡ የብርሃን ልብሶችንም ለብሰው ሕዝቡ ሁሉ አዩአቸው፡፡ ይህንንም ባዩ ጊዜ ‹‹የእነዚህ ቀዱሳን አምላካቸው ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ ይክበር ይመስገን እኛም በአምላካቸው አምነናል›› እያሉ ጮኹ፡፡ ንጉሡም በታላቅ ቁጣ ሆኖ እናትና

በእንተ ቅዱሳን ኅሩያን (ከገድላት አንደበት)

16 Nov, 17:10


ስንኳ ክርስቲያን ሳላስቀር ጨርሼ አጠፋቸዋለሁ›› አለው፡፡ በዚህም ጊዜ ሰይጣኑ ተሳለቀበትና ‹‹እንግዲህስ ወዮልህ ወዮታ አለብህ፣ ፈጽመህ ሙተህ ኑሮህ ከእኔ ጋር በሲኦል ነው›› አለው፡፡ የሰይጣን መጨረሻው ይህ ነው፣ የሰው ልጅ በሕይወት ሳለ ሲያስክድ፣ ሲያስት ፣ ክፉ ሥራን ሲያሠራ ይኖርና በመጨረሻ መክዳትና በሲኦል ማጋዝ ባሕርይው ነው፡፡ በዚያም ለዘለዓለም የሲኦል ባሪያ አድርጎ በታላቅ ሥቃይ ሲያሠቃይ ይኖራል፡፡ ዲዮቅልጥያኖስም ይህን ቃል ከሰይጣን ከሰማ በኋላ ደንግጦ በክፉ አሟሟት ሞቶ ዘላለማዊ ፍርዱን አግኝቶ ወደ ሲኦል ወረደ፡፡
የልዳው ፀሐይ ሰማዕቱ ቅዱስ ጊዮርጊስ እና የሌሎቹም ሰማዕታት ረድኤት በረከታቸው ይደርብን፣ በጸሎታቸው ይማረን!

በእንተ ቅዱሳን ኅሩያን (ከገድላት አንደበት)

15 Nov, 09:49


ኅዳር 6-እመቤታችን ከስደት የተመለሰችበት በዓል (በዓለ ቊስቋም) እና ገድለ አቡነ አላኒቆስ አአ ላይ ለሽያጭ የቀ...
https://youtube.com/watch?v=9qCEelfP93M&si=mwjEO2xOzvsvIeN7

በእንተ ቅዱሳን ኅሩያን (ከገድላት አንደበት)

15 Nov, 09:48


የአቡነ አላኒቆስ ዘማይበራዝዮ ገዳም ገድላቸው አ.አ ላይ ለገበያ ቀርቧል!

ኻያ ኹለት ዓመት ተረግዞ ኖሮ በኃላ በጸሎታቸው ኃይል ፂምና ጥርስ ያለው ልጅ እንዲወለድ ያደረጉት፣ ታቦተ ጽዮንን 40 ዓመት ያጠኑ፣ አንበሳን 7 ዓመት ውኃ ያስቀዱት፣ ንግሥናን ንቀው የመነኑ ታላቅ ጻድቅ ናቸው-አቡነ አላኒቆስ።

(ከነገረ ቅዱሳን አገልግሎታችን ውስጥ አንዱ ከዚኽ በፊት ያልታተሙ አዳዲስ ገድላትን ለገዳማት በማሳተም ሕዝበ ክርስቲያኑም በነፍስ በሥጋ እንዲጠቀም ለማድረግ የአቅማችንን ሞክረናል። አሁንም እግዚአብሔር ፈቅዶ የአቡነ አላኒቆስንና
በዐፄ ሱስንዮስ ዘመን የነበረውን የቤተ ክርስቲያንን ጥፋት ላለማየት ሳይወለዱ በእናታቸው ማሕፀን 7 ዓመት ከ6 ወር የቆዩትን የአቡነ አብራኒዮስን ገድል የኹለቱን ቅዱሳን ገድል ብዛት 3ሺህ ኮፒ አሳትመን ለገዳሙ ስናስረክብ እጅግ ደስታ ይሰማናል። ከጻድቁ ከበዓለ ዕረፍታቸው ከጥቅምት 21 በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ አ.አ ላይ ገድሉ ከዛሬ ከኅዳር 6 ቀን ጀምሮ እየተሸጠ ይገኛል።)

የገጽ ብዛት= 468
ዋጋ= 500
ቦታ፦ 6 ኪሎ ቅዱስ ማርቆስ ቤተ ክርስቲያን ሕንፃ ቁ.11 እና ፒያሳ ገነተ ጽጌ ቅዱስ ጊዮርጊስ ክርስቲያን ሕንፃ 2ኛ ፎቅ ቤተ ጳውሊ የጉዞ ወኪል ቢሮ ውስጥ ያገኙታል።
እንዲሁም ገድላትና ድርሳናት በሚሸጡባቸው ቦታዎች ላይ ያገኙታል።

የገዳሙ ተወካይ ስልክ፦
+251910862062 (አባ ገብረ መስቀል)

በእንተ ቅዱሳን ኅሩያን (ከገድላት አንደበት)

14 Nov, 17:51


አንድ አምላክ በሚሆን በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም አሜን
ኅዳር 6-በዚህች ዕለት ክብርት እመቤታችን ከተወደደ ልጇ ጋር ከስደት በሚመለሱበት ጊዜ ደብረ ቁስቋም ገብተው ካገኛቸው ድካም ዐረፉ፡፡
አምላክን የወለደች በድንጋሌ ሥጋ በድንጋሌ ነፍስ የጸናች ክብርት እመቤታችን ከስደት በተመለሰች ጊዜ እንዲህ ሆነ፡- የብርሃን እናቱ ክብርት እመቤታችን ልጇን ይዛ ከእነ ዮሴፍ ጋር ወደ ምድረ ግብፅ ስትሰደድ ግብፅ ደርሰው በዚያ ቢቀመጡም ነገርን ግብፅ አልተመቸቻውም፡፡ ሕዝቡም በሰላም አልተቀበላቸውም፡፡ እንዲያውም በምድረ ግብፅ ብዙ ተሠቃይተዋል፡፡ ከግብፅም ተነሥተው ወደ ኢትዮጵያ በመጡ ጊዜ ግን ኢትዮጵያ ሕዝብ ሁሉ በሰላምና በፍቅር ተቀበላቸው፡፡ ከመንገዱና ከርሃብ ጥሙ ጽናት የተነሣ እጅግ ደክማለችና የኢትዮጵያ ሰዎች እመቤታችንን አይተው እጅግ አዘኑላት፡፡ ‹‹ይህችስ የነገሥታት ዘር ትመሥላለች ነገር ግን አንዳች ችግር አጋጥሟት ተሰዳ ወደ ሀገራችን መጥታለች..›› ብለው እንክብካቤን አደረጉላት፡፡ እግራቸውን አጥበው በክብር ማረፊያዎች ላይ አሳረፏቸው፡፡ መልካም መስተንግዶም አደረጉላቸው፡፡ እመቤታችንም ከድካሟ ካረፈች በኋላ ሀገሪቱን በእጅጉ ወደደቻትና የተወደደ ልጇን ‹‹ይህን ሀገርና ሕዝቧን በመላ ወድጃቸዋልሁና በዚህ እስከ መጨረሻው እንኑር›› አለችው፡፡ ጌታችንም ክብርት እናቱን ‹‹ይህች ቅድስት ሀገር ናት፣ በኋለኛው ዘመን የቅዱሳን መነኮሳት ቦታ ትሆናለች፡፡ በውስጧም እስከ ዓለም ፍጻሜ ድረስ እመሰገንባታለሁ፤ የአንቺም ስም ሳይጠራ አይውልባትም›› አላት፡፡
ከዚህም በኋላ ጌታችን ደመና ጠቅሶ በእርሷ ላይ ተቀመጡ፡፡ መልአኩ ቅዱስ ዑራኤልም መጣና እየመራቸው መላ ኢትዮጵያን ጎበኟት፡፡ እመቤታችንም ሀገሪቱንና ሕዝቦቿን ወዳቸዋለች ደስም ተሰኝታባቸዋለችና ጌታችን ለክብርት እናቱ ‹‹ይህችን ቅድስት ሀገር አሥራት አድርጌ ሰጠሁሽ›› አላት፡፡ እመቤታችንም እጅግ ተደስታ ‹‹ልጄ አምላኬ›› ብላ አመሰገነችው፡፡ ከዚህም በኋላ ከአንዱ ቦታ ወደ አንዱ ቦታ እየተዘዋወሩ መላዋ ኢትዮጵያን በኪደተ እግራቸው ባረኳት፡፡ ጌታችንም ‹‹በዚህ ቦታ እንዲህ ዓይነት ቤተ ክርስቲያን ይታነጻል፤ እከሌ የሚባል እንዲህ ዓይነት ቅዱስ ይነሣል…›› እያለ ብዙ ምሥጢራትን ለክብርት እናቱ ነገራት፡፡ ከዚህም በኋላ የስደቱ ዘመን ሲያልፍ ሄሮድስም በመጨረሻ ክፉ አሟሟትን ሲሞት መልአኩ ወደ ገሊላ አውራጃ እንዲመለሱ ነገራቸው፡፡ እመቤታችንም ‹‹ከዚህች ሀገርስ ባንሄድ እመርጣለሁ›› ስትለው የተወደደ ልጇ ግን ‹‹እናቴ ሆይ ጽድቅንና ፈቃድን ሁሉ ልንፈጽም ይገባናል›› ብሎ አጽናናትና ወደ ሀገራቸው ተመልሰው ሄዱ፡፡
ተመልሰውም ሊሄዱ ሲነሡ የኢትዮጵያ ሰዎች ልዩ ልዩ አምሐ እጅ መንሻ ሰጧቸው፡፡ ልዩ ልዩ ልብሶች፣ ወርቅ፣ ዕጣን፣ ከርቤ፣ ሽቱ እና ሥንቀቸውን በግመሎች ላይ ጭነው እመቤታችንንና የተወደደ ልጇንም በበቅሎ ላይ አስቀምጠው በክብር ሸኟቸው፡፡ እመቤታችንም ልጇን ታቅፋ በበቅሎ ተቀምጣ በበረሃው በመጓዝ ወደ መጣችበት አገር ሄደች፡፡ ኢትዮጵያንም የሰጧትን ብዙ እጅ መንሻዎች በግመሎች ጭና ይዛ ወደ አገሯ በተመለሰች ጊዜ ከአንድ ባሕር ዳር ደረሰች፡፡ ከዚያም የጀልባውን ባለቤት ‹‹እግዚአብሔርን ስለመውደድ አሻግረኝ›› ብላ ለመነችው፡፡ ባለጀልባውም ‹‹እነሆ ዕቃ የተጫኑ አምስት ግመሎችና ከአንቺ ጋር ከዚህም ሕፃን ጭምር አምስት ሰዎች እመለከታለሁ፣ አንቺ የተቀመጥሽባት በቅሎም አለች፡፡ ጀልባዋም ታናሽ ናት፣ የመቀመጫ ክፍሏም በውስጧ የተሳፈሩት ሰዎችም ተጨናንቀው ነው ያሉት፡፡ ስለዚህ እንዴት ላሻግርሽ እችላለሁ? ነገር ግን እመቤቴ ሆይ! ይቅርታ አድርጊልኝ ይህን በክፋት አላደረግሁትምና›› አላት፡፡
ክብርት እመቤታችንም የጀልባው ባለቤት ሊያሻግራት እንዳልቻለ በተረዳች ጊዜ ‹‹ልጄ ሆይ የእግዚአብሔር ልጅ እንደመሆንህ ይህን ትልቅ ወንዝ ለመሻገር የአምላክነትህን ሥራ ትሠራ ዘንድ እለምንሃለሁ›› ስትል ማለደችው፡፡ ያንጊዜም ጌታችን ክብርት እናቱን ‹‹የወለደሽኝ እናቴ ሆይ! አትዘኝ›› ብሎ አረጋጋት፡፡ ዳግመኛም ‹‹በእኔ ፈቃድ በአባቴ ፈቃድ በመንፈስ ቅዱስ ፈቃድ ካንቺ ሰው ሆኛለሁና ሰው መሆኔንም ከአባቴ በቀር መስተፍሥሒ ከሚሆን ከመንፈስ ቅዱስም በቀር ያወቀ የለም፡፡ ዳግመኛም በሕያዋንና በሙታን ለመፍረድ ለሁሉም እንደየሥራው እከፍለው ዘንድ እመጣለሁ፡፡ ያችንም ሰዓት የሰማይ መላእክትም ቢሆኑ የአዳም ልጆችም ቢሆኑም ከእኔና ከአባቴ ከመንፈስ ቅዱስም በቀር የሚያውቃት የለም፡፡ ያንጊዜ ‹ዐመፅን የሚናገር አንደበት ሁሉ ይዘጋል› ብሎ አባትሽ ዳዊት እንደተናገረ እከራከራለሁ የሚል አንደበት እንደድዳ ምላሽ ያጣል›› አላት፡፡
ክብርት እመቤታችን ማርያምም ይህንን ሁሉ ምሥጢር የተወደደ ልጇ የነገራትን ታስተውለው በልቧም ትጠብቀው ነበር፡፡ ጌታችንም አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስም ለክብርት እናቱ ይህንን ከነገራት በኋላ ቀኝ እጁን ዘርግቶ ከወንዙ ማዶ ጢር በሚባል ተራራ ያሉትን ድንጋዮች ጠቀሳቸው፡፡ ያንጊዜም እነዚህ ድንጋዮች እየተገለባበጡ መጥተው እንደ ጀልባ ሆነው በወራጁ ወንዝ ላይ ተንሳፈፉ፡፡ ከዚያም እመቤታችንን ከሕፃኑ ጋር ከነቤተሰቧና ከነጓዟ አሻገረሯት፡፡
እነዚህንም ድንጋዮች ያዩ ሰዎች ሁሉ እጅግ አድንቀው ‹‹ብቻውን ድንቅ ተአምራት ያደረገ፣ እስራኤልን የፈጠረ እግዚአብሔር ይክበር ይመስገን የጌትነቱም ስም የተመሰገነ ነው›› እያሉ አመሰገኑ፡፡ እነዚህም የተባረኩ ሰዎች ወንዙን ከተሻገሩ በኋላ በዚህች አገር ለስምንት ቀን ተቀመጡ፡፡ ከዚህም በኋላ አምላክን የወለደች በድንጋሌ ሥጋ በድንጋሌ ነፍስ የጸናች ክብርት እመቤታችን ስለደረገላት መልካም ሥራ ሁሉ እግዚአብሔርን ፈጽማ እያመሰገነች ወደ አባቷ ወደ ዳዊት አገር ተመለሰች፡፡
ዳግመኛም በኋለኛው ዘመን ጌታችን በዚህ በደብረ ቍስቋም ቅዱሳን ሐዋርያቶቹን ሰበሰባቸውና ታቦትንና ቤተ ክርስቲያንን አክብሮ የቍርባን መሥዋዕትንም ሠርቶ ቅዱስ ሥጋውንና ክቡር ደሙን ለወገኖቹ ሰጣቸው፡፡ ለዚህም ነገር የእስክንድርያ አገር ሊቃነ ጳጳሳት ቅዱሳን አባቶቻችን ቄርሎስና ቴዎፍሎስ ምስክሮቹ ሆኑ፡፡
ክብርት እመቤታችን ከስደቷ በረከት ትክፈለን!
+ ዳግመኛም በዚህች ዕለት አባ ፊልክስ ዐረፈ፡፡
አባ ፊልክስ፡- ይኸውም ቅዱስ ምግባር ሃይማኖቱ፣ ትሩፋት ተጋድሎው ያማረ ሆኖ ቢያገኙት በእግዚአብሔር ፈቃድ የሮሜ አገር ሊቀ ጳጳሳት አድርገው ሾሙት፡፡ በዘመኑም ከሃዲው ቴዎስድሮስ ቄሳር ነግሦ ምእመናንን ሲያሠቃያቸውና ሲግድላቸው ሊቀ ጳጳሳት አባ ፊልክስንም ብዙ አሠቃጥቷቸዋል፡፡ አባ ፊልክስም በክርስቲያኖች ላይ እየደረሰ ያለው ጽኑ መከራ እንዲቆም ወደ እግዚአብሔር በጸለየ ጊዜ ይህን ከሃዲ ንጉሥ በነገሠ በ2ኛ ዓመቱ አጠፋው፡፡
ከዚህም በኋላ የክርስያኖችን ደም እንደውኃ ያፈሰሰው ከሃዲው ዲዮቅልጥያኖስ ነገሠና ክርስቲያኖችን በዓለም ላይ እያደነ ማሠቃየትና መግደል በጀመረ ጊዜ ይህ አባት አባ ፊልክስ የክርስቲያኖችን ሥቃይ እንዳያሳየው ወደ እግዚአብሔር በጸለየ ጊዜ ወዲያው በመጀመሪያው ዓመት ዐረፈ፡፡ ይህም አባ ፊልክስ ለክርስቲያን ወገኖች እጅግ ጠቃሚ የሆኑ ብዙ ድርሳናትንና ትግሣጻትን የጻፈ ነው፡፡ ረድኤት በረከቱ ይደርብን፣ በጸሎቱ ይማረን!

በእንተ ቅዱሳን ኅሩያን (ከገድላት አንደበት)

14 Nov, 09:36


ጎንደር ቊስቋም በዚህ ሰዓት በዋዜማው!

በእንተ ቅዱሳን ኅሩያን (ከገድላት አንደበት)

14 Nov, 08:24


በተፈጥሮአዊ አቀማመጡ እጅግ ድንቅ የሆነው ደብረ ዓሣ አባ ዮሐኒ ገዳም!
በዛሬዋ ዕለት ኅዳር 5 ቀን በሞት ፋንታ የተሰወሩት አባ ዮሐኒ የእናታቸውን ጡት ፈጽሞ ጠብተው አያውቁም ይልቁንም የታዘዘ ንስር አሞራ በክንፎቹ ጋርዶ እያለበሳቸው እና ቶራ (ሰሳ) እያጠባቻቸው ነው ያደጉት፡፡ አባታችን ስለጽድቅ ብለው 500 ሜትር ርዝመት ካለው ከዚህ ትልቅ ተራራ ላይ ራሳቸውን ቁልቁል ቢወረውሩ መሬት ሳይደርሱ መልአኩ ቅዱስ ገብርኤል በአየር ላይ እንዳሉ ተቀበላቸው፡፡ ወዲያውም አባ ዮሐኒ ክንፍ አውጥተው ከቅዱስ ገብርኤል ጋር ጎን ለጎን ሆነው በዛሬው ዕለት ኅዳር 5 ቀን ወደ ብሔረ ሕያዋን ይዟቸው ገባ።ብሔረ ሕያዋን ያሉ እነ ሄኖክና ኤልያስም ‹‹ሰው ከሚሞትበት ሀገር ሞት ወደሌለበት አገር ማን አመጣው?›› አሉ፡፡ መልአኩም በዚህ ጊዜ እግዚአብሔር ባዘዘኝ ጊዜ እኔ ገብርኤል ነኝ ያመጣሁት›› አላቸው፡፡ ቀጥሎም መልአኩ ‹‹አንተ ሄኖክ ምንም ንጹሕ ብትሆን በሥርዓተ ሥጋ ተወልደህ በሥርዓተ ሥጋ አድገህ ሚስት አግብተህ ወልደሃል፣ እግዚአብሔርም እዚህ ያደረሰህ በንፅህናህ ነው፤ አንተም ኤልያስ ምንም ድንግል ብትሆን በሥርዓተ ሥጋ ተወልደህ በሥርዓተ ሥጋ አድገህ ከዚህ ደርሰሃል፤ ይህ አባ ዮሐኒ ግን ከተወለደ ጀምሮ የእናቱን ጡት አልቀመሰም፣ ቀን ቀን ሰሳ እያጠባችው ሌሊት ሌሊት ንስር አሞራ በክንፎቹ እያለበሰው አድጓል እንጂ›› ብሎ ነገራቸው፡፡ ቀጥሎም መልአኩ የአባ ዮሐኒን ገድል ዘርዝሮ ከነገራቸው በኋላ ሊሞት ያለበትንም የአሟሟቱን ነገር ከነገራቸው በኋላ ‹‹ታዲያስ እንዲህ ያለውን አምጥቼ ከብሔር ሕያዋን ባስገባው ፍርዴ እውነት አይደለምን?›› አላቸው፡፡ ሄኖክና ኤልያስም ይህን ጊዜ ‹‹ይገባዋል›› ብለው አባ ዮሐኒን በምስጋና ተቀበሉት፡፡ ገዳሙ ውስጥ ሦስት ቤተ መቅደሶች ያሉ ሲሆን አንዱን አቡነ ተክለ ሃይማኖት ይቀድሱበት የነበረው ነው፡፡ ገዳሙ ደብረ ዓሣ እየተባለ ይጠራል፡፡ ምክንያቱም ቤተ ክርስቲያኑ በመሬት መንቀጥቀጥ ከመፍረሱ በፊት ጣራው የዓሣ አንበሪ ቅርጽ ነበረው፡፡ ዐፄ ገብረ መስቀልም በወቅቱ በዚህ ዓሣ ምስል ያሠሩት ቅዱስ መስቀል በገዳሙ ውስጥ ይገኛል፡፡ አንድም ደግሞ በመጀመሪያ ዐፄ ገብረ መስቀል እና ሌሎቹም ቅዱሳን አበው በገዳሙ ውስጥ ሱባኤ ገብተው ሳለ ቅዱሳን በዓሣ ተመስለው ሲወጡና ሲገቡ በማየታቸው ነው ገዳሙ ‹‹ደብረ ዓሣ አባ ዮሐኒ›› የተባለው ሌላው በተፈጥሮአዊ አቀማመጡ እጅግ ድንቅ በሆነው በዚህ ገዳም ውስጥ አስገራሚ የመቃብር ጉድጓዶች አሉት፡፡ መቃብሮቹ የተፈለፈሉ ዋሻዎች ናቸው፡፡ አንዱ ዋሻ በአንድ ጊዜ ከ6 ሰዎችን ጎን ለጎን አስተኝቶ መያዝ አይችልም ነገር ግን በጣም የሚገርመው የመቃብር ጉድጓዶቹ እስከዛሬም ድረስ አልሞሉም፡፡ አንድ ሰው ከተቀበረ ከዓመት በኋላ አስክሬኑ ይጠፋል፣ አጥንቱም አይገኝም፡፡ ሰሌኑ ግን እስከ ሁለት ዓመት ይቀመጣል፡፡ ለአባ ዮሐኒ ለዚህ ገደማቸው ዕጣን ጧፍ ዘቢብ የሰጠ ሰው ቢኖር ስጦታውን እንደ አቤል መሥዋዕት አድርጎ ጌታችን እንደሚቀበልለት ለጻድቁ ቃልኪዳን ገብቶላቸዋል፡፡
ረድኤት በረከታቸው ይደርብን፣ በጸሎታቸው ይማረን!
ከገድላት አንደበት
✞ ✞ ✞

በእንተ ቅዱሳን ኅሩያን (ከገድላት አንደበት)

13 Nov, 13:19


የአባ አበይዶ፣ የአባ አሞኒ እና የአባ ዮሐኒ ረድኤት በረከታቸው ይደርብን፣ በጸሎታቸው ይማረን!

በእንተ ቅዱሳን ኅሩያን (ከገድላት አንደበት)

13 Nov, 13:19


አባ አሞኒ ልጃቸው አድጎ 12 ሲሆነው ከዚህም በኋላ ዲቁና ሊያሾሙትና አክሱም ጽዮን ወስደው ሊያስባርኩት ቤተ ካህናት ከተባለው ቦታ ይዘውት ሲሄዱ ልዩ ስሙ ሲሂታ ከሚባለው ቦታ ሲደርሱ ከወገባቸው በላይ እራታቸውን የሆኑ እንስራ የተሸከሙ ዓሥር ሴቶች አገኙ፡፡ አባ ዮሐኒም አባታቸውን ‹‹አባቴ እነዚህ ደረታቸው ላይ ቀንድ ያላቸው ጽጉራቸው የረዘመ ምንድናቸው? እንደእኛ የሆኑ መስህታን የሚባሉት እነዚህ ናቸውን?›› አሏቸው፡፡ አባ አሞኒም ‹‹አይደሉም ልጄ ዝም ብለህ ሂድ›› አሏቸው፡፡ በኋላ ግን ትዝ ሲላቸው ‹‹በዱር እንስሳት ያሳደኩት ልጄ ወንድና ሴት ለይቶ ሲያውቅ በዚያው ሊሳሳት አይደልምን?›› ብለው በማሰብ ዲቁናና ክህነቱ ይቅርበት ብለው ተመልሰው ወደ በዓታቸው ይዘውት ገቡ፡፡
ከዚህም በኋላ አባ አበይዶ ወደ አባ አሞኒ መጣና እሳቸውን ከአባ ዮሐኒ ጋር እያገለገሏቸው ተቀመጡ፡፡ ዮሐኒ እየጻፈ አበይዶ የሚጻፍበትን ቆዳ እያዘጋጁ ሦስቱም በአንድነት በተጋድሎ መቀመጥ ጀመሩ፡፡
አባ ዮሐኒ 20 ዓመት አባ አሞኒ ደግሞ 40 በሆናቸው ጊዜ መልአኩ ቅዱስ ገብርኤል ለአባ አሞኒ ተገለጠላቸውና ‹‹አሞኒ ሆይ ከእንግዲህስ እግዚአብሔር ወደኔ ና ብሎሃል›› አላቸው፡፡ እሳቸውም ልጆቻቸውን አባ ዮሐኒንና አባ አበይዶን ጠርተው ‹‹በሉ እንግዲህ እኔ ወደ እግዚአብሔር መሄዴ ነውና ጸልዩልኝ›› አሏቸው፡፡ ከማረፋቸውም በፊት አባ ዮሐኒን ለብቻቸው ጠርተው ‹‹አንተ አባ ዮሐኒ ካሁን በፊት ሲሂታ ላይ ያየሃቸው ሴቶች ናቸው፣ አዳምንም ከገነት ያስወጡ ናቸው፡፡ ወደፊትም እንደ እነርሱ ያለ የደረሰብህ እንደሆነ ካለህበት ገደል ተወርውረህ ውደቅመ በባሕር ውስጥ ጥለቅ›› ብለው ነግረዋቸው በዛሬዋ ዕለት ኅዳር 5 ቀን በሰላም ዐረፉና ወደ ጠራቸው እግዚአብሔር ሄዱ፡፡
አባ አሞኒ ካረፉ ከ12 ዓመት በኋላ የአባ ዮሐኒ ወላጅ እናታቸው የልጇን ነገር ስታጠና ኖራ ነበርና አሁን ባሏም ስለሞተ አባ አሞኒም ስላረፉ ልጇን ልታይ ከ32 ዓመት በኋላ መጣች፡፡ ቀሚስ ለብሳ ፀጉሯን ተሠርታ በሴትነቷ ልጇ ካለበት ቦታ በመሄድ ማነጋገር እንደማትችል ስላወቀች ፀጉሯን ተላጭታ የወንድ ልብስ ቁምጣ ለብሳ በሁለመናዋ ወንድ መስላ ወደ ደብረ ዓሣ ተራራ አመራች፡፡ እዚያም እንደደረሰች በቅዱሳን ሥርዓት መሥረት ሦስት ጊዜ ‹‹አውሎ ግሶን፣ አውሎ ግሶን፣ አውሎ ግሶን›› አለች፡፡ ሰይጣን ይህን ስም ሲሰማ 40 ክንድ ይርቃል፡፡ የደብረ ዳሞ መነኮሳት እንደ ሰላምታ መለዋወጫ ይጠቀሙበታል፡፡ አባ ዮሐኒም ይህን ድምጽ ከውጭ በሰሙ ጊዜ ‹‹አንተ ማነህ?›› አሉ፡፡ እርሷም ‹‹ዓመተ መንፈስ ቅዱስ ነኝ›› አለቻቸው፡፡ አባታችንም አንድም ድምፁዋ ወትሮ ከሚያውቁት ድምፅ ስተለየባቸው ደግሞም ትዝ ሲላቸው እነዚያ እንስራ አዝለው ደረታቸው ላይ ቀንድ ያላቸው ሆነው ውኃ ቀድተው ሲሄዱ በመነገድ ያዩአቸው ሴቶች ድምፅ ሆነባቸው፡፡ ደግሞም ‹‹ወልደ እከሌ፣ ክንፈ እከሌ›› ሲባል እንጂ ‹‹ዓመተ፣ ወለተ›› ሲባል ሰምተው አያውቁም ነበርና አባታቸው አባ አሞኒ የነገሯቸው ትዝ አላቸው፡፡ በዚያውም ቅጽበት የሚጽፉባትን ብዕር ጆሮአቸው ላይ እንደሰኩ 500 ሜትር ርዝመት ካለው ትልቅ ተራራ ላይ ራሳቸውን ቁልቁል ወረወሩ፡፡ ነገር ግን መሬት ሳይደርሱ መልአኩ ቅዱስ ገብርኤል በአየር ላይ እንዳሉ ተቀበላቸው፡፡ ብዕራቸው ግን መሬት ላይ ወድቃ ሸምበቆ ሆነች፡፡ ወዲያውም አባ ዮሐኒ ክንፍ አውጥተው ከቅዱስ ገብርኤል ጋር ጎን ለጎን ሆነው በዛሬው ዕለት ኅዳር 5 ቀን ወደ ብሔረ ሕያዋን ይዟቸው ገባ፡፡
ብሔረ ሕያዋን ያሉ እነ ሄኖክና ኤልያስም ‹‹ሰው ከሚሞትበት ሀገር ሞት ወደሌለበት አገር ማን አመጣው?›› አሉ፡፡ መልአኩም በዚህ ጊዜ እግዚአብሔር ባዘዘኝ ጊዜ እኔ ገብርኤል ነኝ ያመጣሁት›› አላቸው፡፡ ቀጥሎም መልአኩ ‹‹አንተ ሄኖክ ምንም ንጹሕ ብትሆን በሥርዓተ ሥጋ ተወልደህ በሥርዓተ ሥጋ አድገህ ሚስት አግብተህ ወልደሃል፣ እግዚአብሔርም እዚህ ያደረሰህ በንፅህናህ ነው፤ አንተም ኤልያስ ምንም ድንግል ብትሆን በሥርዓተ ሥጋ ተወልደህ በሥርዓተ ሥጋ አድገህ ከዚህ ደርሰሃል፤ ይህ አባ ዮሐኒ ግን ከተወለደ ጀምሮ የእናቱን ጡት አልቀመሰም፣ ቀን ቀን ሰሳ እያጠባችው ሌሊት ሌሊት ንስር አሞራ በክንፎቹ እያለበሰው አድጓል እንጂ›› ብሎ ነገራቸው፡፡ ቀጥሎም መልአኩ የአባ ዮሐኒን ገድል ዘርዝሮ ከነገራቸው በኋላ ሊሞት ያለበትንም የአሟሟቱን ነገር ከነገራቸው በኋላ ‹‹ታዲያስ እንዲህ ያለውን አምጥቼ ከብሔር ሕያዋን ባስገባው ፍርዴ እውነት አይደለምን/›› አላቸው፡፡ ሄኖክና ኤልያስም ይህን ጊዜ ‹‹ይገባዋል›› ብለው አባ ዮሐኒን በምስጋና ተቀበሉት፡፡
ከዚህም በኋላ መልአኩ ቅዱስ ገብርኤል ወደ ደብረ ዓሣ ተመልሶ መጥቶ ለአባ አበይዶ ተገለጠላቸውና አባ ዮሐኒን ብሔረ ሕያዋን እንዳስገባው ነገራቸው፡፡ በመጀመሪያ ሄኖክና ኤልያስ አላስገባ ብለው እንደነበርና በኋላም መልአኩ ራሱ የአባ ዮሐኒን ገድላቸውን ከነገራቸው በኋላ በምስጋና እንደተቀበሉት ለአባ አበይዶ ነገራቸው፡፡ ቀጥሎም መልአኩ የአባ ዮሐኒን ገድላቸውን እንዲጽፉትና እንዲያስተምሩበት ለአባ አበይዶ አዘዛቸውና ዐረገ፡፡ አባ አበይዶም አባ ዮሐኒ ከገደሉ ተወርውረው ሲወደቁ አንድ ደስ የሚል ወንድ ሲቀበለው አይተው ነበርና አሁን መልአኩ ሲነግራቸው እጅግ ደስ አላቸው፡፡ አባ አበይዶም በታዘዙት መሠረት የአባ ዮሐኒን ገድል ጻፉት፡፡ እርሳቸውም ትናንት ኅዳር 4 ቀን በሰላም ዐረፉ፡፡

በፎቶው ላይ እንደምታዩት ተንቤን የሚገኘው የአባ ዮሐኒ ቤተ ክርስቲያን አቀማመጡ እጅግ አስደናቂ ነው፡፡ ተራራው መሀል ላይ ወደሚገኘው ቤተ ክርስቲያኑ ለመውጣት 150 ሜትር ተራራውን መውጣት ይጠይቃል፡፡ ሽቅብ ከተወጣ በኋላ አፈ ጽዮንን ትገኛለች፡፡ ከአፈ ጽዮን በኋላ ከድንጋይ የተፈለፈለ 12 መድረክ ያለው የውስጥ ለውስጥ የጨለማ መንገድ አለ፡፡ በመጨረሻ ብርሃን ወዳለብ ስፍራ ሲወጣ በስተግራ በኩል 12 ሜትር ርቀት ላይ ቤተ መቅዱሱ ይገኛል፡፡ ቤተ ክርስቲያኑ 13 ጉልላቶች አሉት፡፡ ገዳሙ ጥንት 58 ዓምደ ወርቅ ነበረው፡፡ በአንድ ወቅት በመሬት መንቀጥቀጥ ምክንያት 22ቱ ሲሰባበሩ አሁን ያሉት 36ቱ ብቻ ናቸው፡፡ ገዳሙ ውስጥ ሦስት ቤተ መቅደሶች ያሉ ሲሆን አንዱን አቡነ ተክለ ሃይማኖት ይቀድሱበት የነበረው ነው፡፡ ገዳሙ ደብረ ዓሣ እየተባለ ይጠራል፡፡ ምክንያቱም ቤተ ክርስቲያኑ በመሬት መንቀጥቀጥ ከመፍረሱ በፊት ጣራው የዓሣ አንበሪ ቅርጽ ነበረው፡፡ ዐፄ ገብረ መስቀልም በወቅቱ በዚህ ዓሣ ምስል ያሠሩት ቅዱስ መስቀል በገዳሙ ውስጥ ይገኛል፡፡ አንድም ደግሞ በመጀመሪያ ዐፄ ገብረ መስቀል እና ሌሎቹም ቅዱሳን አበው በገዳሙ ውስጥ ሱባኤ ገብተው ሳለ ቅዱሳን በዓሣ ተመስለው ሲወጡና ሲገቡ በማየታቸው ነው ገዳሙ ‹‹ደብረ ዓሣ አባ ዮሐኑ›› የተባለው፡፡
ሌላው በተፈጥሮአዊ አቀማመጡ እጅግ ድንቅ በሆነው በዚህ ገዳም ውስጥ አስገራሚ የመቃብር ጉድጓዶች አሉት፡፡ መቃብሮቹ የጠፈለፈሉ ዋሻዎች ናቸው፡፡ አንዱ ዋሻ በአንድ ጊዜ ከ6 ሰዎችን ጎን ለጎን አስተኝቶ መያዝ አይችልም ነገር ግን በጣም የሚገርመው የመቃብር ጉድጓዶቹ እስከዛሬም ድረስ አልሞሉም፡፡ አንድ ሰው ከተቀበረ ከዓመት በኋላ አስክሬኑ ይጠፋል፣ አጥንቱም አይገኝም፡፡ ሰሌኑ ግን እስከ ሁለት ዓመት ይቀመጣል፡፡ ለአባ ዮሐኒ ለዚህ ገደማቸው ዕጣን ጧፍ ዘቢብ የሰጠ ሰው ቢኖር ስጦታውን እንደ አቤል መሥዋዕት አድርጎ ጌታችን እንደሚቀበልለት ለጻድቁ ቃልኪዳን ገብቶላቸዋል፡፡

በእንተ ቅዱሳን ኅሩያን (ከገድላት አንደበት)

13 Nov, 13:19


አንድ አምላክ በሚሆን በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም አሜን
ኅዳር 5-ኢትዮጵያዊው ታላቅ ጻድቅ የደብረ ዓሣው አባ ዮሐኒ የተሰወሩበት ዕለት ነው፡፡ አባታቸው አባ አሞኒም በዚህች ዕለት ዐርፈዋል፡፡
+ የቅዱስ ሌንጊኖስ ራስ የታየችበትና ተአምር ያረገችበት ዕለት ነው፡፡
+ የሠራዊት አለቃ የቅዱስ ቴዎድሮስ ቅዱስ ሥጋው ከሀገረ ሰጥብ ወደ ሀገረ አስዩጥ የፈለሰበት ዕለት ነው፡፡
የቅዱስ ለንጊኖስ ራስ የታየችበት ተአምር ያረገችበት ዕለት፡- ይኸውም ቅዱስ ለንጊኖስ በመጀመሪያ ጌታችንን ጎኑን በጦር የወጋው ነው፡፡ የመድኃኔዓለም የፍቅሩ መጠን ልክ የለውምና ይህንንም ጎኑን በጦር የወጋውን ሰው በወቅቱ ዕውር የነበረችውን አንድ ዐይኑን አበራለት በኋላም በስሙ አምኖ ወንጌልን ሰብኮ በሰማዕትነት እንዲያርፍ መረጠው፡፡ በሙሉ ልቡ አምኖ እስከሞት ድረስ ለመታመን ተዘጋጅቶ በክፉዎች አይሁድ ፊት ስለ ጌታችን አምላክነት መመስከር ጀመረ፡፡ አይሁድና ሮማውያንም በምስክርነቱ እጅግ ተቆጥተው ያሳድዱት ጀመር፡፡ ወደ ታናሹዋ እስያ ወደ ቀጵዶቅያ ሄዶ በዚያ ወንጌልን እንደ ሐዋርያት በመስበክ ብዙዎችን ወደ ቀናች እምነት መልሷቸዋል፡፡ አይሁድም በክፋት ተነሥተው የሐሰት ምስክር አቁመው በመኳንንት ዘንድ በሐሰት ወንጅለው በቀጵዶቅያ አገር ሐምሌ 23 ቀን አንገቱን በሰይፍ አስቆረጡት፡፡ ራሱንም ብቻዋን ወደ ኢየሩሳሌም ወሰዷት፡፡ በምስክርነቱ የቀኑና የተናደዱ በዚያ የሚኖሩ አይሁድም ራሱ ተቆርጣ ባዩአት ጊዜ እጅግ ተደስተው ከከተማ ውጭ በአንድ ኮረብታ ላይ ቀበሯት፡፡
ከብዙ ቀንም በኋላ በቅዱስ ለንጊኖስ ስብከት ያመነች አንዲት ሴት በቀጵዶቅያ አገር ራሱን ከቆረጡበት ጊዜ ጀምራ በተቆረጠበት ቦታ በመቆም ስለእርሱ ታለቅስ ነበር፡፡ ከጊዜም በኋላ ዐይኖቿ ታወሩ፡፡ የጌታችንን መቃብር ለመሳለም ተነሥታ ከነልጇ ወደ ኢየሩሳልም መጣች፡፡ ኢየሩሳልም በደረሰችም ጊዜ ልጇ ሞተ፡፡ በሀዘንም ሆና ሳለ ወደ ሀገሯ መርቶ የሚወስዳት ስላጣች መሪር ልቅሶን አልቅሳ ደክሟት ተኛች፡፡ ተኝታም ሳለ ቅዱስ ለንጊኖስን ከሞተ ልጇ ጋር በራእይ አየችው፡፡ ራሱ ተቀብራ ያለችበትንም ቦታ ነገራትና ሄዳ እንድታወጣ አዘዛት፡፡
ቅዱስ ለንጊኖስ ወዳመለከታት ወደ ቦታው ሄዳ ስታስቆፍረው መዓዛው እጅግ ጣፋጭ የሆነ የሽቱ መዓዛ ወጣ፡፡ አማኟም ሴት የቅዱስ ለንጊኖስ ራሱ ያለችበት ቦታ ስትደርስ ታላቅ ብርሃን ተገለጠላትና ዐይኖቿ በሩላት፡፡ የቅዱስ ለንጊኖስን ራስና የልጇን ሥጋ ይዛ ወደ ሀገሯ ወስዳ ባማረ ቦታ አኖረቻት፡፡ ይኸም ተአምር ኅዳር 5 ቀን የተፈጸመ ነው፡፡
የቅዱስ ለንጊኖስ ረድኤት በረከቱ ይደርብን፣ በጸሎቱ ይማረን!
+ + +
ዳግመኛም በዚህች ዕለት የሠራዊት አለቃ የቅዱስ ቴዎድሮስ ቅዱስ ሥጋው ከሀገረ ሰጥብ ወደ አስዩጥ ሀገር የፈለሰበት ዕለት ነው፡፡ (የዕረፍቱን ዕለት ሐምሌ ሃያን ይመለከቷል)
+ + +
አቡነ አሞኒና ልጃቸው አቡነ ዮሐኒ፡- መጽሐፍ አባታቸውን ዘስዩመ ተንቤን እሁሁ ይላቸዋል፡፡ እናታቸው ደግሞ ዓመተ መንፈስ ቅዱስ የሚባሉ ደገኛ ምግብራቸው ያማሩ ሀገር ወዳድ ናቸው፡፡ አቡነ አሞኒ የካቲት 5 ቀን አክሱም ውስጥ ሲወለዱ ሰይጣናት የወላጆቻቸውን ቤት ከበው በማየታቸው እንደተወለዱ በእጃቸው ቢያመለክቱ በአንድ ጊዜ 60 ሰይጣናት ተሸንፈው እንደጢስ በነው ጠፍተዋል፡፡ አሞኒ ማለት አሸናፊ ማለት ነው፡፡
አባ አሞኒ የራስ ፀጉራቸው ልብስ መጎናጸፊያ ሆኖላቸው የኖሩ ታላቅና ቀደምት አባት ናቸው፡፡ በደመና ተጭነው ደብረ ዘይት ድረስ በመሄድ ከአባ እብሎይ ጋር ተገናኝተው ብዙ ምሥጢርን አውርተዋል፡፡ አባ ዮሐኒን ያሳደጉት አስተምረው ያሳደጓቸው አባ አሞኒ ናቸው፡፡ የእናቱን ጡት ፈጽሞ ጠብቶ የማያውቀውን የመንፈስ ቅዱስ ልጃቸውን አባ ዮሐኒን እሳቸው እያጫወቱት የታዘዘ አሞራ በክንፎቹ እያለበሰው ቶራ (ሰሳ) እያጠባችው ነው ያደገው፡፡ መነሻ ታሪኩም እንዲህ ነው፡-
የተንቤን አውራጃ ገዥ የነበረው ሰው በዘመኑ ዐፄ ካሌብ የነበሩበት ዘመን ነበርና አብሯቸው ወደ ምድረ ኖባ ሄደው ሰባት ዓመታትን የፈጀ የጦር ዘመቻ ክርስያኖችን በሚያሠቃዩ ነገሥታት ላይ አዳሄዱ፡፡ የተንቤኑ አውራጃ ገዥም ወደ ዘመቻው ከሄደ ቆይቶ ነበርና ታናሽ ወንድሙ የገዥውን ሚስት ‹‹ወንድሜ የቀረው ሞቶ ነው እንደ ኦሪቱ ሕግ እኔው ላግበሽና ልጆቹን ላሳድግ›› አላት፡፡ እርሷም ‹‹ባሌ ቢሞት ይነገረኝ ነበረዘመቻ የሄደው ሁሉ አልተመሰም›› ብላ እምቢ ብትለው በግድ ተገናኛት፡፡ በዚህም ጊዜ አባ ዮሐኒ ተፀነሱ፡፡ በሚያዝያ 5 ቀንም ተወለዱ፡፡
ከዘጠኝ ወር በኋላ ማሏ ከዘመቻ መጣና ወደ ቤቱ ተመለሰ፡፡ የአካባቢውም ሰው ወጥቶ በክብር ሲቀበለው ሚስቱ ግን ምጥ ተይዛ ታማ ስለነበር ወጥታ አልተቀበለችውም፡፡ ‹‹የት ሄደች? ምንስ ሆነች?›› ብሎ ሲጠይቅ ልጅ አይደብቅምና አንድ ሕፃን ‹‹አርግዛ ልትወልድ በምጥ ላይ ትገኛለች›› አለው፡፡ የአውራጃውም ገዥ ያለችበት ድረስ ሄዶ ቢያያት ያማረ ወንድ ልጅ ታቅፋ አገኛት፡፡ ከዚህም በኋላ ከቤቱ ምሰሶ ጋር ጥፍንግ አድርግ አስሮ እየገረፋትና እያስጨነቃት ከማን እንዳረገዘች ጠየቃት፡፡ እርሷም የወንድሙን ምሥጢር ለመጠበቅና ወንድማማቾቹን ላለማጣላት ሥቃዩን ታግሳ ዝም አለች፡፡ በዚህ ቅጽበት የራማው ልዑል ቅዱስ ገብርኤል 40 ዓመት ሙሉ ዘግተው በበረሃ ለሚኖሩት ለአባ አሞኒ ተገለጠላቸው እንደ አውሎ ነፋስ አምዘግዝጎ ወስዶ አውራጃ አገረ ገዥው ቤት አደረሳቸው፡፡
እንደደረሱ ዓመተ ማርያም በጽኑ ድብደባና ግርፋት እየተሠቃየች እያለ አባ አሞኒ የጸጉራቸውን አጽፍ ለብሰው ራቁታቸውን ደጇ ላይ ቆመው አየቻቸው፡፡ በዚህም ጊዜ ለባሏ ‹‹ያውና ከዚህ መነኩሴ ነው የወለድኩት›› አለቸው፡፡ አተንቤቱ አውራጃ አገረ ገዥውም አባ አሞኒን ይዞ ጽኑውን ግርፋት በወታደሮቹ አስገረፋቸው፡፡ በመቀጠልም ገና የእናቱን ወተት እንኳን ያልቀመሰውን ጨቅላ ሕፃን አንሥቶ ‹‹እንካ ልጅህን ይዘህ ጥፋ ከዚህ›› ብሎ ሰጣቸው፡፡ አባ አሞኒም በዚህ ጊዜ ‹‹ዮ ሀበኒ ዮ ሀበኒ›› አሉ፡፡ በትግርኛ እሽ ስጠኝ ማለት ነው፡፡ ከዚህ በመነሳት ነው ሕፃኑ በኋላ ላይ ‹‹አባ ዮሐኒ›› የተባሉት፡፡ አባ አሞኒም ሕፃኑን ተረክበው ወደ ደብረ ዓሣ ተራራ ሥር ሄደው ልጁን ከወይራ ዛፍ ሥር አስተኝተው ‹‹አምላኬ ኢየሱስ ክርስቶስ ሆይ! ኃጢአቴን ተመራምረህ ይህንን ሕፃን የሰጠኸኝ አላጠባው ጡት የለኝ አላበላው እህል የለኝ›› ብለው የጨቅላው ሕፃን ነገር እጅግ ቢያስጨንቃቸው ምርር ብለው አለቀሱ፡፡ ጸሎታቸውንም እንደጨረሱ ተራራውን በመስቀል ምልክት ቢባርኩት በተራራው መሐል ላይ እንደመደብ ያለ አልጋ በተአምራት ተሠርቶ አገኙት፡፡ ሕፃኑንም ከዚያ አስተኝተው ድጋሚ ጸሎት ሲጀምሩ ቶራ (ሰሳ) መጥታ እግርና እግሯን አንፈራጣ ሕፃኑን አጠባችውና ሄደች፡፡
አባ አሞኒም በዚህ ደስ ተሰኝተው ሕፃኑን ‹‹የምግብህ ነገር ከተያዘ ግዴለም›› ብለው ሌሊቱን ሙሉ ሲጸልዩ አድረው መለስ ቢሉ ዳግመኛም ሕፃኑን የታዘዘ ንስር አሞራ በክንፎቹ ጋርዶ አልብሶትና አቅፎት እንዳደረ ተመለከቱ፡፡ አባታችንም እጅግ ደስ ተኝተው እግዚአብሔርን አመሰገኑት፡፡ እንደዚሁ ሁሉ ቀን ቀን ቶራዋ እያጠባችው ሌሊት ሌሊት ንስር አሞራው አልብሶት እያደረ ሕፃኑ ሦስት ዓመት ሆነው፡፡ አባ አሞኒም ከሰባት ዓመቱ ጀምረው እስከ 12 ዓመቱ ድረስ ፊደል፣ ንባብ ከነትርጓሜው፣ ብሉይንና ሐዲስን፣ ምግባር ሃይማኖትን ሥርዓተ ቤተ ክርስያንን ሁሉ አስተማሩት፡፡

በእንተ ቅዱሳን ኅሩያን (ከገድላት አንደበት)

12 Nov, 23:55


እዚያ ሚስኪን የትግራይ ሕዝብ ላይ በግድ የተጣበቁ መዥገሮች!
ይሄን ቃሌን መዝግባችሁ ያዙልኝ!!! ዛሬ ላይ ፖለቲካውን ተገን አድርገው ሀገር ስለመሆን ሲለፍፉ ውለው ያድራሉ እንጂ የእነ አባ ሰረቀ መጨረሻ ምንፍቅና እና በእግዚአብሔር የማያምን ትውልድን መፍጠር ነው!!! ገና ከአሁኑ ትውልዱን ግብረ ሰዶማዊነትን እያለማመዱት እንደሆነ ከዚያው ከወደ መቀሌ የሚወጡ መረጃዎችና የዐይን እማኞች በቂ ምስክሮች ናቸው።
ከእግዚአብሔር ቍጣም ሆነ ከምድራዊ የፖለቲካ ችግር የተነሣ ሕወሓትም ሆነች እነ ሰረቀ ነገ ላይ ሕዝቡን የባሰ መከራ ያመጡበታል እንጂ ፖለቲካዊ መፍትሔ መቼም አይሰጡትም። በጥርነፋ እስራት ውስጥ ነውና ሕዝቡ ይሔን ጠንቅቆ ቢያውቅም መፍትሔ ግን ማምጣት አልቻለም። የጽዮናውያንን ምሕላና ጸሎት ሰምቶ ፈጣሪ ይድረስለት በእውነት!

በእንተ ቅዱሳን ኅሩያን (ከገድላት አንደበት)

12 Nov, 23:54


አንድ አምላክ በሚሆን በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም አሜን
ኅዳር 4-የአባ ዮሐኒ ደቀ መዝሙር የሆኑት የኢትዮጵያዊው አቡነ አበይዶ ዕረፍታቸው ነው፡፡
+ ከሮሜ አገር የተገኙት ቅዱሳን አቢማኮስና አዛርያኖስ በሰማዕትነት ዐረፉ፡፡
+ የደማስቆው ቅዱስ ቶማስ በግብፅና በሶርያ እስላሞች በነገሡ ጊዜ በአሕዛብ እጅ በሰማዕትነት ዐረፈ፡፡
+ ቅዱሳን ሰማዕታት ዮሐንስና ያዕቆብ በፋርሱ ከሃዲው ንጉሥ በሳቦር እጅ ሰማዕት ሆኑ፡፡
ሰማዕታቱ ቅዱስ አቢማኮስና ቅዱስ አዛርያኖስ፡- እነዚህም ቅዱሳን ክርስቶስን የሚያምኑ እንደሆኑ ከሃዲው ንጉሥ መክሲምያኖስ በሾመው መኮንን ዘንድ ወነጀሏቸው፡፡ መኮንኑም ቅዱሳኑን ወደ እርሱ አስቀርቦ ስለ ሃይማኖታቸው ጠየቃቸው፡፡ እነርሱም በጌታችን የሚያምኑ መሆኑን ነገሩት፡፡ መኮንኑንም ሰማይንና ምድርን የፈጠረውን እውነተኛውን አምላክ ክዶ ጣዖት ስለማምለኩ የዘለፋን ቃል እየተናገሩ ገሠጹት፡፡ መኮንኑም ከድፍረታቸው የተነሣ አደነቀና አንገታቸውን በሰይፍ ይቆርጧቸው ዘንድ አዘዘ፡፡ እንደትእዛዙም ቅዱስ አቢማኮስንና ቅዱስ አዛርያኖስን አንገታቸውን በሰይፍ ቆረጧቸው፡፡ የሰማዕትነት አክሊልንም ተቀዳጁ፡፡
+ + +
ሰማዕታቱ ቅዱስ ዮሐንስና ቅዱስ ያዕቆብ፡- ይኸውም ቅዱስ ዮሐንስ የፋርስ አገር ኤጲስቆጶስ ነው፡፡ የፋርሱ ንጉሥ ሳቦር ፀሐይን፣ ጨረቃን፣ እሳትን የሚያመልክ ከሃዲ ነበርና እነዚህ ቅዱሳን ኤጲስቆጶሱን ቅዱስ ዮሐንስንና ቅዱስ ያዕቆብንም ለፀሐይና ለጨረቃ እንዲሰግዱ አዘዛቸው፡፡ እነርሱም ‹‹ፀሐይንና ጨረቃን ፍጥረቱንም ሁሉ የፈጠረውን አምላክ እናምናለን ለእርሱም ብቻ እሰግዳለን›› አሉት፡፡ በዚህም ጊዜ ንጉሥ ሳቦር ጽኑ በሆኑ ልዩ ልዩ ሥቃዮች አሠቃያቸው፡፡ እነርሱም በታላቅ ሥቃይ ውስጥ እያሉ ሕዝቡን በማስተማር ከብር ይግባውና በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ሃይማኖት ያጸኗቸው ነበር፡፡
ንጉሡም ቅዱስ ዮሐንስንና ቅዱስ ያዕቆብን የልባቸውን ጥንካሬ በሥቃይም ውስጥ መታገሳቸውን ማስተማርንም አለመተዋቸውን ባየ ጊዜ በእጅጉ ተናደደና ከእቶን እሳት ውስጥ እንዲጥሏቸው አዘዘ፡፡ ቅዱሳኑም በዚያው የሰማዕትነታቸው ፍጻሜ ሆነና ነፍሳቸውን ለጌታችን አስረከቡ፡፡ እርሱም የሰማዕትነት አክሊልን አቀዳጃቸው፡፡
+ + +
አቡነ አበይዶ፡- የታላቁ አባት የአባ ዮሐኒ ደቀ መዝሙር ናቸው፡፡ አባ ዮሐኒ ዕረፍታቸው ኅዳር 5 ስለሆነና የአቡነ አበይዶም ታሪክ ከአባ ዮሐኒ ጋር የተገናኘ ስለሆነ በዚሁ ዕለት አንድ ላይ እናየዋለን፡፡ ኅዳር 4 ቀን ግን የአቡነ አበይዶ ዕረፍታቸው መሆኑን ብቻ ጠቅሰን እናልፋለን፡፡ ስንክሳሩም ስማቸውን ብቻ ጠቅሶት ያልፋል፡፡
+ + +
የደማስቆው ቅዱስ ቶማስ፡- የደማስቆው ኤጲስቆጶስ የሆነው ቅዱስ ቶማስ እስላሞች በግብጽና በሶርያ በነገሡ ጊዜ በእነርሱ እጅ ሰማዕት የሆነ ነው፡፡ እርሱም ከእስላሞቹ ከመምህኖቻቸው ውስጥ አንደኛው በተከራከረው ጊዜ ቅዱስ ቶማስ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሰማይንና ምድርን በውስጣቸው ያለውንም ሁሉ የፈጠረ አምላክ እንደሆነ በማስረዳት አይሎበት እስላሙን መምህር ረታው፡፡
ያም እስላም መምህር ባፈረ ጊዜ ወደ መኮንናቸው ዘንድ ሄዶ ‹‹ይህ ክርስቲያናዊ ሰው ቶማስ ሃይማኖታችንን አቃለለብን›› ብሎ ወነጀለው፡፡ አሕዛባዊው መኮንንንም ቅዱስ ቶማስን አስቀርቦ ‹‹በውኑ ሃይማኖታችንን ትነቅፋለህን?›› አለው፡፡ ቅዱስ ቶማስም ‹‹የነቀፌታ ወይም የመርገም ቃልስ ከአፌ አልወጣም ነገር ግን ክርስቶስ እውነተኛ አምላክ እንደሆነ ከእርሱም ሕግ በኋላ ሌላ ሕግ እንደማይመጣ ከመጣም ፍጹም ሐሰት እንደሆነ አጽንቼ እናገራለሁ እንጂ›› ብሎ መለሰለት፡፡ ከዚህም በኋላ መኮንኑ ‹‹የእኛስ ሕግ ከእግዚአብሔር ነውን ወይስ አይደለም?›› ብሎ ቅዱስ ቶማስን ጠየቀው፡፡ ቅዱሱም ‹‹ከእግዚአብሔር አይደለም፣ መጽሐፋችሁ ሐሰተኛ መጽሐፍ፣ ነቢያችሁም ሐሰተኛ ነቢይ ነው›› አለው፡፡ በዚህም ጊዜ መኮንኑ ተቆጥቶ ቅዱስ ቶማስን ራሱን በሰይፍ ይቆርጡት ዘንድ አዘዘ፡፡ ቅዱስ ቶማስም በዚህች ዕለት አንገቱን ተሰይፎ በሰማዕትነት በማረፍ የሰማዕትነት አክሊልን ተቀዳጀ፡፡
የቅዱሳን ሰማዕታቱ ረድኤት በረከታቸው ይደርብን፣ በጸሎታቸው ይማረን!

በእንተ ቅዱሳን ኅሩያን (ከገድላት አንደበት)

31 Oct, 14:37


ጥቅምት 21-የእመቤታችን ወዳጅ የአቡነ አላኒቆስ ገድልና ተኣምር
https://youtube.com/watch?v=CP9lk112GkM&si=XV2e8XPqa3DgCWcZ

በእንተ ቅዱሳን ኅሩያን (ከገድላት አንደበት)

31 Oct, 14:37


አባታችን ዮሐንስም ጎልጎታ ደርሰው ከቅዱሳት ቦታዎች ተባርከው ወደ አስቄጥስ ገዳም ሔዱ። በዚያም 500 ዓመት የኖረ ኹለተኛ እንጦንስ የተባለ አንድ ባሕታዊ ኣገኙ። እመቤታችንም አባ እንጦንስን ታቦተ ኢየሱስን፣ ታቦተ ኪዳነ ምሕረትን እና ታቦተ ጽዮንን እያስጠበቀችው ይኖር ነበር። አባ እንጦንስም ኣቡነ ዮሐንስን ባገኛቸው ጊዜ በልቡ ተደስቶ በመንፈሱ ረክቶ በዐይኖቼ አንተን ያሳየኝ በጆሮዎቹም ቃልህን ያሰማኝ የአባቶቻችን አምላክ እግዚአብሔር ይክበር ይመስገን፤ እመቤታችን ማርያም ከልጇ ከወዳጇ ከኢየሱስ ክርስቶስ ጋር በእጇ የሰጠችኝን ያስጠበቀችኝን እነዚኽን ታቦታት ተቀበለኝ›› ብለው ሦስቱን ጽላት ‹‹ወደ ሀገርህ ይዘህ ሒድ›› ብለው ሰጧቸው። አባታችን ዮሐንስም ‹‹…እኔ እርሱ አይደለሁም እንዴት አወከኝ?› ሲሏቸው አባ እንጦንስም ፈገግ ብለው ከሞተ ሦስት መዓልትና ሦስት ሌሊት የሆነውን ሰው በጸሎትህ ከሞት ካስነሣኸው በኋላ ከሀገርሀ ከኢትዮጵያ ከዋልድባ ገዳም ከተነሣኽ ዘጠኝ ወር ነው፤ ይኸንንም የእግዚአብሔር መላእክት ነገሩኝ መምጣቱን ተስፋ የምታደርገው ኢትዮጵያዊው ጻድቅ ከሀገሩ ዛሬ ተነሣ አሉኝ አሏቸው። አባታችን ዮሐንስም እመቤታችን ማርያምን እንዴት አገኘሃት? አሏቸው። አባ እንጦንስም ከልጇ ከወዳጇ ጋር በብርሃን መርከብ ላይ ተቀምጣ መላእክት፣ ነቢያት፣ ሐዋርያት ጻድቃን፣ ሰማዕታት ሲከቧትና በክብር በምስጋና ሲሰግዱላት ግንቦት 21 ቀን በደብረ ምጥማቅ አገኘኋት አሏቸው። እመቤታችንም ልጇን ኢየሱስ ክርስቶስን ፈቃድህን ለሚያደርጉ ለኢትዮጵያ ሕዝብና ለዓለሙ ሁሉ የመዳን ተስፋ ስጠኝ አለችው። ጌታችንም ያንጊዜ መላእክትን ከገነት ዕንጨትና ዕብነ በረድ፡ ከጎልጎታ መቃብሩና ከጌቴሴማኒ አፈር እንዲያመጡ አዘዛቸው። መላእክትም የታዘዙትን አምጥተው በሰጡት ጊዜ ጌታችን ከገነት የመጡትን ዕንጨትና ዕብነ በረድ ሦስቱን ታቦታት አድረጋቸው በማለት አባ እንጦንስ ለአባ ዮሐንስ ነገሯቸው።

አቡነ ዮሐንስም ሦስቱን ጽላት ይዘው አንዲት እንደፀሓይ የምታበራ ድንጋይ እየመራቻቸው ሰኔ 12 ቀን ጎጃም ደረሱ። ድንጋዩዋንም መንገድ እንድትመራቸው የሰጣቸው ጌታችን ነው። ከዚያም ውሮ ተብሎ የሚጠራ አንድ ባላባት ቤት ገብተው አድረው በሚገባ ተስተናግደው በቀጣዩ ቀን ድንጋዩዋ እየመራቻቸው ቅዱሳን ከነበሩበት ጫካ ወስዳ አገናኘቻቸው። ቅዱሳኑም ለአቡነ ዮሐንስ የጠበቅንልህን ይኸችን ቦታ ተረከበን የዘለዓለም ማረፊያህ ናትና› ብለው እነርሱ ወደ ኢየሩሳሌም ሔዱ። አባታችንም ታቦተ ኢየሱስን በዚኽች ገዳም ተክለው ቦታዋን መጀመሪያ በተቀበላቸው ሰው በውሮ ስም "ውራ ኢየሱስ ብለው ሰየሟት።

ከዘጠኝ ዓመትም በኋላ መልአኩ ቅዱስ ዑራኤል እየመራቸው ወደ ጣና ወስዶ ዘጌ አደረሳቸውና ታላቋን ዑራ ኪዳነ ምሕረትን ተከለ።

ከዚያ ቀጥለው ታቦተ ጽዮንን አዴት አካባቢ ተከሉ። እነዚህን ሦስት ገዳማት አቅንተው ከኖሩ በኋላ መልካም የሆነውን ተጋድሏቸውን ፈጽመው ጥቅምት 22 ቀን ዐርብ በ9 ሰዓት ዐረፉ። ከማረፋቸውም በፊት ጌታችን እመቤታችንን፣ መላእክትን፣ ቅዱሳንን ሰማዕታትን አስከትሎ መጥቶ “…ጸሎት አድርጎ መልክህን የደገመ እባብ አይነድፈውም፤ መብረቅ አይገድለውም የሚል ድንቅ የምሕረት ቃልኪዳን ገባላቸው። ዳግመኛም ስምህን የጠራውን መታሰቢያህን ያደረገውን፤ በበዓልህ ቀን ማኅሌት የቆመውን የገድልህን መጽሐፍ የጻፈውን ያጻፈውን ያነበበውን የሰማውን፣ እጅ መንሻ ለቤተ ክርስቲያን የሰጠውን እምርልሃለሁ፤ ልጆቹንም እስከ 15 ትውልድ እባርክልሃለሁ፤ በገዳምህ በውራ መብረቅ ነጎድጓድ፣ እባብ ሰውን አይገድልም የማይጸድቅ ሰው ወደ ገዳምህ አይመጣም" አላቸው።

አባታችንም ካረፉ በኋላ መነኰሳት ልጆቻቸው ሥጋቸውን ተሸክመው ከደብረ ጽዮን ኮቲ ተነሥተው ወደ ውራ ኢየሱስ ለመውሰድ ሲጓዙ በበረሓ ሣሉ መሸባቸውና ፀሓይ ገባች፣ ወዲያውም ሰባት አንበሶች መጥተው እንዳይፈሯቸው መነኰሳቱን በሰው አንደበት ካናገሯቸው በኋላ የአቡነ ዮሓንስን ዐፅም ተሸክመው ሰባት ምዕራፍ ያህል ወሰዱት። ወቅቱ ቢመሽባቸውም በእግዚአብሔር ፈቃድ ፀሓይ ግን በተኣምራት ወጣችላቸውና ውራ ኢየሱስ ገዳም በሰላም ደረሱ። ያንጊዜም ፀሓይ ገባች፤ አንበሶቹም እጅ ነሥተው ወደ ቦታቸው ተመለሱ።

አቡነ ዮሐንስ መላ ዘመናቸውን የማያዩ ዐይነ ሥውራንን እንዲያዩ፣ የማይሰሙ እንዲሰሙ፣ የማይራመዱ እንዲራመዱ በማድረግ፤ ሕሙማንን በመፈወስ፣ ሙታንን በማስነሣት በርካታ ተኣምራትን በማደረግ ወንጌልን በመስበክ ያገለገሉ ሲሆን ከዕረፍታቸውም በኋላ በርካታ ድንቅ ድንቅ ተኣምራትን አድርገዋል። ከተኣምራታቸውም አንዱ ይኸ ነው፡- ንዑድ ክቡር ልዩ በሚሆን በአባታችን ዮሐንስ የዕረፍታቸው ቀን ጥቅምት 22 ቀን አንድ ዐረማዊ እስላም ሰው ለተሳልቆና ለመዘባበት ወደ ቅድስት ቤተ ክርስቲያን ገብቶ ቈረበ። በአባታችን በዓል ዕለትም ቅዱስ ሥጋውንና ክቡር ደሙን ተቀብሎ ወጥቶ እየተቻኮለ ሔዶ ከእስላሞች መስጊድ ገብቶ በአባታችን በዮሐንስ በዓል ምክንያት የቆረበውን ቍርባን ተቀብሎ በወገኖቹ በከሃዲያኑ እስላሞች ፊት ተፋው። ወዲያውም የዚያ እስላም ሰው መላ ሰውነቱ አበጠ በንፋስ ገመድነትም ታንቆ ሰዎች እስኪያዩት ድረስ በሰማይና በምድር መካከል ተሰቀለ።

በተሰቀለበትም ቦታ ወፎችና አሞራዎች ይበሉት ጀመር፤ ሥጋውንም በሉት። በዚኽም ጊዜ ያ እስላም ድምፁን ከፍ አድርጎ ‹‹እኔ ንዑድ ክቡር ልዩ በሆነ በአባታችን በዮሐንስ አምላክ አምኛለሁ ብሎ መሰከረ። እግዚኣብሔርም የገዳማት ኮከብ በሆነው በብፁዕ ዮሓንስ ልመናና ጸሎት ፈጽሞ ይቅር አለው። ከዚኽም በኋላ ለብቻው ቀኖና ገባ የቀኖና ሥርዓቱንም ጨርሶ ንስሓ ገብቶ ከባለቤቱ ከልጆቹ ከቤተሰቦቹና ከዘመዶቹ ከጎረቤቱቹ ሁሉ ጋር የክርስትና ጥምቀትን ተጠመቀ ስሙንም ገብረ ዮሐንስ አሉት ትርጓሜውም የዮሐንስ ባለሟል ማለት ነው።

የአቡነ ዮሐንስ ረድኤት በረከታቸው ይደርብን፣ በጸሎታቸው ይማረን።

በእንተ ቅዱሳን ኅሩያን (ከገድላት አንደበት)

31 Oct, 14:37


አንድ አምላክ በሚሆን በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም አሜን
ጥቅምት 22-ወንጌላዊው ቅዱስ ሉቃስ ዕረፍቱ ነው፡፡
+ ውራ ኢየሱስ ገዳምን የመሠረቱትና ጌታችን ከገነት ዕንጨቶች የተሠሩ ታቦታት አምጥቶ የሰጣቸው ታላቁ ጻድቅ አቡነ ዮሐንስ ዘውራ ኢየሱስ ዕረፍታቸው ነው።
+ + +
ቅዱስ ሉቃስ:-ሀገሩ አንጾኪያ ሲሆን ቁጥሩ ከ72ቱ አርድእት ነው፡፡ ከአቴናና ከእስክንድርያ ሊቃውንት የሕክምና ሙያን አጥንቷል፡፡ ከሕክምና መያው በተጨማሪ የሥዕል ሙያም ነበረው፡፡ በይህ ምክንያት በወንጌሉና በሐዋርያት ሥራ መጽሐፉ ላይ ከሌሎቹ በተለየ ሁኔታ ሥዕላዊ አገላለጽን ሲጠቀም ተስተውሏል፡፡ በእጁ የሣላቸው ቅዱሳት ሥዕላትም በተለያዩ ሀገራት ይገኛሉ፡፡
ቅዱስ ሉቃስ የሣላቸው የእመቤታችን ሥዕላት በእኛም ሀገር እንደ ደብረ ዠመዶ፣ ዋሸራና ተድባበ ማርያም፣ ደብረ ወርቅ ማርያም… ባሉ ታላላቅ ቅዱሳት ገዳማት ውስጥ ይገኛሉ፡፡ ቅዱስ ሉቃስ የከበሩ ቅዱሳን ሐዋርያትን ጴጥሮስንና ጳውሎስን ያገለግላቸው ነበር፡፡ ለታኦፊላም ወንጌልንና የሐዋርያትን ዜና የጻፈው እርሱ ነው፡፡ ቅዱሳን ሐዋርያት ጴጥሮስና ጳውሎስ በሰማዕትነት ካረፉ በኋላ በሮሜ ወንጌልን በሰፊው ሰብኳል፡፡ መልእክቶችንም ይጽፍላቸው ነበር፡፡ ጣዖት አምላኪዎችም ከክፉዎቹ አይሁድ ጋር ተማክረው በሐሰት ከሰውት በንጉሥ ኔሮን ፊት አቆሙትና ‹‹ብዙ ሰዎችን በሥራዩ ወደ ክርስትና እምነት አስገብቷልና በሞት ይቀጣ›› ብለው ጮኹ፡፡ ቅዱስ ሉቃስም በሰማዕትነት እንደሚሞት አስቀድሞ ዐውቆ ወደ ባሕር ዳርቻ በመሄድ ዓሣ የሚያጠምድ አንድ ሽማግሌ ሰው አገኘና ወንጌልን ከሰበከው በኋላ መጻሕፍቶቹንና ደብዳቤዎቹን ‹‹ወደ እግዚአብሔር መንገድ ያደርሱሃልና እነዚህን መጻሕፍት ጠብቀቸው›› ብሎ በአደራ ሰጠው፡፡ ሽማግሌውም በክብር በዕቃ ቤቱ አስቀምጦአቸው ለቀጣዩ ትውልድ አስተላልፏቸዋል፡፡
ቅዱስ ሉቃስ በንጉሡ ኔሮን ፊት በቀረበ ጊዜ ንጉሡ ‹‹በሥራይህ ሕዝቡን ሁሉ የምታስት እስከመቼ ነው?›› አለው፡፡ ቅዱስ ሉቃስም ‹‹ለሕያው እግዚአብሔር ልጅ ለጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሐዋርያ ነኝ እንጂ እኔስ ሥራየኛ አይደለሁም›› አለው፡፡ ንጉሡም ‹‹እየጻፈች ሰዎችን የምታስት ይህችን እጅህን እቆርጣታለሁ›› ካለው በኋላ ቀኝ እጁን አስቆረጠው፡፡ ቅዱስ ሉቃስም የጌታችንን ኃይሉን ያሳየው ዘንድ ወደደና የተቆረጠች የቀኝ እጁን በግራ እጁ አንሥቶ ከተቆረጠችበት ቦታ ላይ በማገናኘት እንደ ድሮው ደኅነኛ እጅ አደረጋት፡፡ በዙሪያውም የነበሩ ሰዎች ሁሉ የንጉሡም የሰራዊት አለቃ ከነሚስቱ በአጠቃላይ ቁጥራቸው 477 ሰዎች ሁሉም በጌታችን አመኑ፡፡ ንጉሡም እጅግ ተናዶ ከቅዱስ ሉቃስ ጋር ራሶቻቸውን ይቆርጧቸው ዘንድ አዘዘ፡፡ እነርሱም ሰማዕት ሆነው የክብር አክሊልን ተቀበሉ፡፡ የቅዱስ ሉቃስንም ሥጋ በአሸዋ በተመላ ከረጢት ውስጥ አስገብተው ወደ ባሕር ጣሉት ነገር ግን በእግዚአብሔር ትእዛዝ ወደ አንድ ደሴት ደረሰና ምእመናን አግኘተውት ወስደው በክብር አኖሩት፡፡
የቅዱስ ሉቃስ ረድኤት በረከቱ ይደርብን፣ በጸሎቱ ይማረን!
+ + + + +
አቡነ ዮሐንስ ዘውራ ኢየሱስ:-የአባታቸው ስም የማነ ብርሃን የእናታቸው ስም ሐመረ ወርቅ ይባላል።በመጀመሪያ እናታቸው ሐመረ ወርቅን ወላጆቿ ያለ ፈቃዷ ሊድሯት ሲሉ እርሷ ግን “ደብረ ሊባኖስ ሔጄ ከአባታችን ተክለ ሃይማኖትና ከሌሎቹም ቅዱሳን መቃብር ሳልባረክ አላገባም በማለት ነሐሴ 16 ቀን ወደ ደብረ ሊባኖስ ሔደች። በዚያም ሳለች አቡነ ተክለ ሃይማኖት በራእይ ተገለጡላትና የብርሃን ምሰሶ አሳይተዋት ይኸ ለአንቺና ለባልሽ ለየማነ ብርሃን ነው› አሏት። ይኽንንም ራእይ ለሰባት ቀን የገዳሙ አባቶችና አበ ምኔቱ አባ ዳንኤል አዩት። ከዚኸም በኋላ ባለጸጋውና ሃይማኖትን ከምግባር አስተባብሮ የያዘው የማነ ብርሃን ከዘርዐ ያዕቆብ ሀገር በእመቤታችን ትእዛዝ ወደ ደብረ ሊባኖስ ሲመጣ አበ ምኔቱ አባ ዳንኤል የማነ ብርሃንን እና ሐመረ ወርቅን ኹለቱ ተጋብተው የተባረከ ልጅ እንደሚወልዱ በራእይ ያዩትን ነገሯቸው፤ ከዚኽም በኋላ በአባታችን በተክለ ሃይማኖት የዕረፍታቸው በዓል ዕለት ነሐሴ 24 ቀን ተጋቡ። እነርሱም በሃይማኖት በምግባር እግዚአብሔርን ደስ አሰኝተው ሲኖሩ እግዚአብሔር ልጅ ሰጣቸውና አቡነ ዮሓንስ ነሐሴ 24 ቀን ተፀንሰው ግንቦት 24 ቀን ተወለዱ።

የፈለገ ብርሃን ናዳ ማርያም እና የክብረ ደናግል ናዳ ቅዱስ ላሊበላ አንድነት ገዳም አበምኔት፣ የቅኔ፣ የትርጓሜ መጻሕፍት፤ የፍትሐ ነገሥት እና የባሕረ ሐሳብ መምህር የሆኑት ሊቀ ብርሃናት ቆሞስ ይባቤ በላይ ከግእዝ ወደ አማርኛ የተረገሙት የአቡነ ዮሐንስ ዘውራ ኢየሱስ ገድል እንደሚናገረው ጻድቁ በሰባት ዓመታቸው ይኸችን ዓለም ንቀው የአቡነ ተክለ ሃይማኖት ኹለተኛ ልጅ ወደሆነው አባ ጸጋ ኢየሱስ ዘንድ ሔደው 5 ዓመት እየተማሩ ተቀምጠው በ12 ዓመታቸው መነኰሱ። ከዚኽም በኋላ አቡነ ዮሐንስ ወደ ዋልድባ በመሔድ አባቶችን ማገልገል ጀመሩ። መነኰሳቱም ሌሊትና ቀን እንዲገለግሏቸው በሥጋ ቍስል ሁለንተናው
ለተላና ለሸተተ ግብሩ ለከፋ ለአንዲ መነኵሴ ሰጧቸው። በሽተኛውም መነኵሴ አቡነ ዮሐንስን ይረግማቸው አንዳንድ ጊዜም ይደበድባቸው ነበር፣ ነገር ግን አቡነ ዮሐንስ በዚህ ከማዘን ይልቅ ደስ እያላቸው ያንን ሊቀርቡት የሚያሰቅቅ በሽተኛ በማገልገል ለዓመታት አስታመመ።

እንዲሁም የዋልድባ መነኰሳትን መኮሪታ በማብሰል፣ ቋርፍ በመጫር እና ዕንጨት በመልቀም፣ ውኃ በመቅዳት ገዳማውያንን ያገለግሉ ነበር። ከዕለታትም በአንደኛው ቀን በዋልድባ የሚኖር በክፉ በሽታ ተይዞ የሞተ አንድ መነኩሴ ሞቶ ሣለ ሽታውን ፈርተው መነኰሳቱ ለመገነዝ ፈሩ፡ ነገር ግን አበ ምኔቱ ለመገነዝ ወደ ውስጥ ሲገባ አቡነ ዮሐንስ አብረው ገቡ። አቡነ ዮሐንስም ወደሞተው መነኵሲ ቀርበው አቀፉት፣ በዚኸም ጊዜ ጥላቸው ቢያርፍበት ያ የሞተው መነኵሴ አፈፍ ብሎ ከሞት ተነሣና ከሞትሁ 3ኛ ቀኔ ነው አይቶ የጎበኘኝ የለም፣ ዛሬ ግን የእግዚአብሔር ሰው የገዳማት ኮከብ የቅድስት ውራ ገዳም መነኰሳት አባት፣ የማይጠልቅ ፀሓይ፣ የማይጠፋ ፋና ወደ ሰባቱ ሰማያት ወጥቶ ከ24ቱ ካህናተ ሰማይ ጋር የሥላሴን ዙፋን የሚያጥን አባታችን ዮሐንስ ባቀፈኝ ጊዜ ነፍሴ ከሥጋዬ ጋር ፈጽማ ተዋሐደች፤ አምላክን የወለደች እመቤታችን ማርያምም ንዑድ ክቡር ቅዱስ በሆነ በዮሐንስ ጸሎት ከሞት አስነሥቶ ሕያው አደረገህ አለችኝ› ብሎ ተናገረ። ዳግመኛም እመቤታችን አባ ዮሐንስን ወደ ኢየሩሳሌም ሔደው እርሳቸውን ሲጠብቁ የኖሩትን ሦስት ታቦታት ያመጡ ዘንድ አቡነ ዮሐንስን እንዳዘዘቻቸው ተናገረ። በዚኽም ጊዜ የዋልድባ መነኰሳትና የገዳሙ አለቃ ለፍላጎታችን አገልጋይና ታዛዥ አደረግንህ ይቅር በለን ብለው ከእግራቸው ሥር ወድቀው ለመኗቸው። አባታችንም ‹‹አባቶቼ ሆይ! እናንተ ይቅር በሉኝ፡ ይህ የሆነው ስለ እኔ አይደለም፡ ስለ ክብራችሁ ነው እንጂ አሏቸው። መነኰሳቱም በትሕትናቸው ተገርመው እያለቀሱ ወደ ኢየሩሳሌም ሸኟቸው። በዚኸም ጊዜ አባታችን ዕድያቸው ገና 19 ነበር።

በእንተ ቅዱሳን ኅሩያን (ከገድላት አንደበት)

31 Oct, 04:24


ባሕርን ለኹለት የከፈሉት ዳግማዊ ሙሴ አቡነ አላኒቆስ!

በውድም አርዕድ ዘመነ መንግሥት አባታችን አላኒቆስ ቅዱሳንን ይጐበኙ ዘንድ በፍጹም ፍቅርና ሰላም በአንድነት ወደሚኖሩ ወደ ዋልድባ አባቶች ዘንድ ሔደው ቅዱሳን አባቶችን ከጠየቁ በኋላ ወደ ገዳማቸው ተመለሱ፤ መነኰሳትም አብረዋቸው ነበሩ፡፡ ጊዜውም የክረምት ወራት ሐምሌ ኻያ ሰባት ቀን ነበርና የተከዜን ወንዝ ሞልቶ ስለአገኙት የአባታችን አላኒቆስ መነኰሳት ልጆች ፈጽመው በአዘኑ ጊዜ አባታችን ‹‹ልጆቼ ሆይ! እጃችሁን ዘርግታችሁ ወደ አምላካችን ጸልዩ እንጂ አትዘኑ›› አሏቸው፡፡ እነርሱም እጃቸውን ዘርግተው ጸለዩ፡፡ አባታችንም ከመነኰሳት ልጆቻቸው ጋር ጸሎታቸውን ከጨረሱ በኋላ በትረ መስቀላቸውን አንሥተው የተከዜን ውኃ በባረኩት ጊዜ ወደ ቀኝና ወደ ግራ ተከፈለ፡፡

በባሕሩም መካከል በሰላም ከተሻገሩ በኋላ መሸ፡፡ ጊዜው ዐርብ ስለነበር መነኰሳቱ ‹‹አባታችን ሆይ! ጊዜው መሽቷልና በወዴት እናድራለን?›› ብለው ጠየቁ፡፡ አባታችን አላኒቆስም ቆመው ወደ ሰማይ ተመልክተው ፀሐይን ጠቀሷት፡፡ ፀሐይም ወደ ኋላ ተመለሰች፡፡ እነርሱም ወደ አባ በአሚን ገዳም ደረሱ፡፡ ዳግመኛም ፀሐይን ጠቀሷትና በአባታችን አላኒቆስ የጸሎት ኀይል ፀሐይ ገባች፡፡ ይኽንንም ታላቅ ተኣምር የተመለከቱ ኹሉ እጅግ አድንቀው ‹‹አባታችን ሆይ! በልዩ በረከትህ ባርከን›› ብለው ኹሉም ተባረኩ፡፡ አባታችንም ‹‹ወደ ዋልድባ ገዳም ሔዳችሁ እግዚአብሔርን አገልግሉት›› ብለው ስለአዘዟቸው እነርሱም ወደ ዋልድባ ገዳም ተመለሰው የምንኵስናቸውን ሥርዐት አጽኑ፡፡

እንደ እግዚአብሔር መልካም ፈቃድ የአቡነ አላኒቆስ ዘማይበራዝዮ ገዳም ገድላቸው ታትሞ ዛሬ ወጥቷል!

ሃያ ኹለት ዓመት ተረግዞ ኖሮ በኃላ በጸሎታቸው ኃይል ፂምና ጥርስ ያለው ልጅ እንዲወለድ ያደረጉት፣ ታቦተ ጽዮንን 40 ዓመት ያጠኑ፣ አንበሳን 7 ዓመት ውኃ ያስቀዱት፣ ንግሥናን ንቀው የመነኑ ታላቅ ጻድቅ ናቸው-አቡነ አላኒቆስ። ጥቅምት 21 ቀን ዕረፍታቸው ነው፡፡

(ከነገረ ቅዱሳን አገልግሎታችን ውስጥ አንዱ ከዚኽ በፊት ያልታተሙ አዳዲስ ገድላትን ለገዳማት በማሳተም ሕዝበ ክርስቲያኑም በነፍስ በሥጋ እንዲጠቀም ለማድረግ የአቅማችንን ሞክረናል። አሁንም እግዚአብሔር ፈቅዶ የአቡነ አላኒቆስንና
በዐፄ ሱስንዮስ ዘመን የነበረውን የቤተ ክርስቲያንን ጥፋት ላለማየት ሳይወለዱ በእናታቸው ማሕፀን 7 ዓመት ከ6 ወር የቆዩትን የአቡነ አብራኒዮስን ገድል የሁለቱን ቅዱሳን ገድል ብዛት 3ሺህ ኮፒ አሳትመን ለገዳሙ ስናስረክብ እጅግ ደስታ ይሰማናል። ከጻድቁ ከበዓለ ዕረፍታቸው ከጥቅምት 21 በኋላ አ.አ ላይ ገድሉ የሚሸጥበትን ቦታና ሌሎች ተያያዥ ጉዳዮችን እንገጥላችኋለን።)

በድጋሚ የአቡነ አላኒቆስ ረድኤት በረከታቸው ይደርብን፣ በጸሎታቸው ይማረን!

በእንተ ቅዱሳን ኅሩያን (ከገድላት አንደበት)

31 Oct, 04:12


አቡነ ዐሥራተ ወልድ

አቡነ ዐሥራተ ወልድ በዳሞት አውራጃ ልዩ ስሟ እነሴ በምትባል ቦታ በዐፄ ሠርጸ ድንግል ዘመነ መንግሥት በ1584 ዓ.ም ተወለዱ። አባታቸው ፃማ ክርስቶስ እናታቸው ፅጌ ማርያም ይባላሉ። ኹለቱም በሕገ እግዚአብሔር ጽንተው የሚኖሩ በሃይማኖት በምግባር የተመሰገኑ በተጋድሎ በትሩፋት የታወቁ ክርስቲያኖች ነበሩ" ነገር ግን ልጅ ስላልነበራቸው እንደ ዘካርያስና ኤልሳቤጥ የተባረከ ልጅ ይሰጣቸው ዘንድ ሁልጊዜ እግዚአብሔርን በጸሎት ይጠይቁ ነበር አምላክን የወለደች ክብርት እመቤታችንንም ይማጸኗት ነበር።

ኹለቱም እግዚአብሔርን የሚፈሩ በምድራዊ ሀብትም የበለጸጉ ነበሩ፤ ለድኖችና ለምስኪኖች አብዝተው ይመጸውቱ ስለነበር ከጾማቸው በኋላ ያለ ድኖችና ምስኪኖች ብቻቸውን አይመገቡም ነበር። እግዚአብሔርም ጸሎት ልመናቸውን ተቀብሎ የተባረከ ልጅ ይሰጣቸው ዘንድ ወደደ። ከዕለታትም በአንደኛው ቀን የእግዚአብሔር ሰው ለጽጌ ማርያም ታይቶ “ዝናው በአራቱ ማዕዘን ኹሉ የሚደርስ በሕይወተ ሥጋ እያለ የብዙ ሰዎችን ነፍስ በጸሎቱ ከኀጢአት ወደ ጽድቅ የሚያወጣ ወደ ሰማይም ወጥቶ የሥላሴን ምሥጢር የሚያይ የተባረከ ልጅን ትወልጂ ዘንድ አለሽና ደስ ይበልሽ በማለት ካበሠራት በኋላ አቡነ ዐሥራተ ወልድ ሰኔ ሃያ ቀን ተወለዱ።

ጻድቁም በተወለዱ በስምንተኛ ቀናቸው ለአብ ምስጋና ይገባል ለወልድ ምስጋና ይገባል ለመንፈስ ቅዱስ ምስጋና ይገባል›› ብለው ፈጣሪያቸውን አመስግነዋል። እስከ ዐሥራ ኹለት ዓመታቸውም ድረስ ውኃ በመቅዳት ዕንጨት በመስበር ወላጆቻቸውን ካገለገሉ በኋላ ወላጆቻቸው ወደ ታላቁ ጻድቅ ወደ አቡነ ተጠምቀ መድኅን ዘንድ ወስደው እንዲያስተምሩላቸው አደራ ብለው ሰጧቸው።

አቡነ ተጠምቀ መድኀንም ዐሥራተ ወልድን ተቀብለው የቅዱሳት መጻሕፍትን ምሥጢር ኹሉ አስተማሯቸው። በሚማሩበትም ጊዜ መንፈስ ቅዱስ በአፋቸው ያቀብላቸው ስለነበር አስቀድመው የተማሩ ይመስሉ ነበር። በሦስት ዓመትም ውስጥ መጻሕፍተ ብሉያትን መጻሕፍተ ሐዲሳትን መጻሕፍተ መነኰሳትን፣አዋልድ መጻሕፍትንም ኹሉ ከነትርጓሜያቸው ከአቡነ ተጠምቀ መድኅን ተምረው እግዚአብሔርም ከሐሰት መጻሕፍት ከሟርት ከጥንቆላ መጻሕፍት በቀር ያልገለጠላቸው የመጻሕፍት ምሥጢር የለም። የመላእክትንና የቅዱስ ያሬድንም ዜማ ገለጠላቸው።

ከዚኽም በኋላ አቡነ ዐሥራተ ወልድ ለመመንኰስ ወላጆቻቸውን አስፈቅደው ከመምህራን ጋር ወደ ታላቁ ገዳም ወደ ደብረ ዳሞ ሔደው በዚያም መነኮሳቱን እያገለገሉ ለ25 ዓመታት ያህል በተጋድሎ ከኖሩ በኋላ በዐፄ ፋሲል ዘመን መንግሥት በ40 ዓመታቸው በ1624 ዓም መንኰሱ። ከሊቀ ጳጳሱ ከአቡነ ሚካኤልም እጅ የቅስና ማዕረግ ተቀበሉ። ከዚኽም በኋላ ከመምህራቸው ከአቡነ ተጠምተ መድኅን ጋር ወደ ጋሾላና ጉሓን ገዳማት ሔደው ተጋድሏቸውን ጨምረው መጾም መጸለይን አበዙ። ወደ ተራራ ሔደው ዳዊት ሲያነቡ ያድራሉ፣ ምሥራቅም ዙረው እምስት መቶ ጊዜ ይሰግዳሉ፤ ወደ ምዕራብም ዙረው አምስት መቶ ጊዜ ይሰግዳሉ፤ ወደ ሰሜንም ዙረው አምስት መቶ ጊዜ ይሰግዳሉ ወደ ደቡብም ዙረው እምስት መቶ ጊዜ ይሰግዳሉ፤ እንዲህም እያደረጉ በየዕለቱ ኹለት ሺህ ይሰግዱ ነበር። ላባቸው እንደ ውኃ ፈስሶ ምድርን እስኪያርስ ድረስ ይሰግዳሉ፤ የቆሙበትም ምድር እንደ ጉድጓድ ይጎደጉዳል። እንደዚህ ባለ ታላቅ ተጋድሎ ጸንተው ብዙ ዘመን ኖሩ። የጌታችንንም ዐርባ ጾም ምንም ሳይቀምሱ በርባውን ቀን ይጾሙ ነበር።

ከዚኸም በኋላ አቡነ ዐሥራት ወልድ ጃባ በሚባለው ቦታ ዐሥራ አንድ ዓመት በተጋድሎ ኖሩ። አባታችን ያከብሯት የነበረች ቅዱስ ሉቃስ የሣላት የክብርት እመቤታችን ሥዕል በዚያ ነበረችና እርሷም ድንቅ ድንቅ ተኣምራትን ታደርግላቸው ነበር። ጃባ በምትባል ቦታም ዘወትር ታነጋግራቸው ነበር። በአንደኛውም ሌሊት ተኝተው ሳሉ አምላክን በድንግልና የወለደች ክብርት እመቤታችን ተገልጣላቸው ልጄ ወዳጅ ዐሥራተ ወልድ ሆይ! በጸሎትና በልመናህ የጃባ ሰዎች ኹሉ ይድናሉ፣ በቃልህ ክርስቶስን አምነው በእጅህ ቅዱስ ሥጋውንና ክቡር ደሙን ይቀበላሉ አለቻቸው።

ከዚኽም በኋላ የታዘዘ የእግዚአብሔር መልአክ ለኹለቱም ቅዱሳን ተገልጦላቸው አቡነ ተጠምቀ መድኅንን ወደ ጋዝጌ እና ወደ መተከል ሔደው የከበረች ወንጌልን እንዲያስተምሩ ሲያዛቸው አቡነ ዐሥራተ ወልድን ደግሞ ወደ ጫራ ምድር ሔደው በዚያ ወንጌልን ይሰብኩ ዘንድ አዘዛቸው። ኹለቱም ቅዱሳን እርስ በርሳቸው በመንፈሳዊ ሰላምታ እጅ ተነሣሥተው ለሐዋርያዊ አገልግሎት ተለያይተው ወደታዘዙባቸው ቦታዎች ሔዱ። አባታችን ዐሥራተ ወልድም እየጸለዩ ስምንት ዓመት ከስድስት ወር በርበር በምትባል በረሓ ውስጥ ሳሉ በአራቱም ማዕዝናት እየተዘዋወሩ በምሥራቅ አንድ ሽህ በምዕራብ አንድ ሺህ በሰሜን አንድ ሺህ በደቡብ አንድ ሺህ ጊዜ ይስግዱ ጀመር የክብር ባለቤት ጌታችን አምላካችን ኢየሱስ ክርስቶስም በዚህ ጊዚ ተገልጦላቸው ወዳጀ ዐሥራተ ወልድ ሆይ! ለምን ሥጋህን እንደዚህ አደከምህ አላቸው አባታችንም ጌታ ሆይ! ኀይላቸውን በስግደት ቀንና ሌሊት በመትጋት የሚያደክሙ በመንግሥትህ እይደሰቱምን በዓለም የደከመ ለዘለዓለም ይድናል ጻድቃን ዳግመኛም በብዙ ድካምና መከራ ወደ እግዚአብሔር መንግሥት እንገባ ዘንድ ይገባናል እንዳለ በማለት መለሱ። ጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ " ድካምህ በከንቱ አትቀርም በሰማያውያን መላእክት በተባረኩጻድቃን ድል በነሱ ሰማዕታት ንጹሐን በሚሆኑ ደናግል በፍጹማን መነኰሳት ፊት የድካምህን ዋጋ እሰጥሃለሁ። እንግዲህ ከዛሬ ጀምረህ ወደ ኣዘዝኩህ ቦታ ሒድ፣መንግሥተ ሰማያትም ቀርባለች እያልህ የመንግሥትን ወንጌል አስተምር፣ ኃይሌ ከአንተ ጋር ይኖራልና ብሎ አዘዛቸው። ጌታችን ይህን ሲነግራቸው አውሎ ነፋስ መጥቶ ጉርብ ወደ ምትባለው ዋሻ ወስዶ አደረሳቸው።

በሥራ የሚኖሩ የሀገሩ ሰዎችም የአባታችን ዐሥራተ ወልድን መምጣት ሰምተው ተቆጥተው በአባታችን ላይ በጠላትነት ተነሡባቸው፣ ጋሻቸውንና ጦራቸውን ይዘው የመጡ ቢሆንም አባታችን ግን የከበረች የክርስቶስን ወንጌል አስተምረው አሳምነው አጠመቋቸው። የጫራንም ሕዝብ አምስት ዓመት ካስተማሯቸው በኋላ ዳግመኛ የሻሽናን ሕዝብ ያስተምሯቸው ዘንድ የእግዚአብሔር መልአክ እየመራው ሻሽና አደረሳቸው። አባታችን በዚያም የሀገሩን ሕዝብ አስተምረው አጠመቁ።

የጐንደር ንጉሥ ጻድቁ ዮሐንስ የአባታችን ዐሥራተ ወልድን ቅድስናና ገድል በሰማ ጊዜ ወደ እርሱ ያመጧቸው ዘንድ መልእክተኞችን ላከ፤ መልእክተኞችም አባታችንን በሻሽና አገኟቸው፤ አባታችን ግን መልእክተኞቹን ‹‹ልጆቼ እኔ ኃጢአተኛ ስሆን ከጐንደር እስከ ሻሽና ንጉሡ ምን ብሎ ላካችሁ?›› አሏቸው። ይኸንንም ተናግረው የንጉሥን ጭፍራ ወደ እናንተ እስክመለስ ድረስ ከዚኸ ጠብቁ›› ብለው ወደ ንጉሡ ዘንድ ከመሔዳቸው በፊት ወደ ጸሎት ቤት ገብተው ከዳዊት መዝሙር ጸለዩ።

ጸሎታቸውንም ከፈጸሙ በኋላ አባታችን ወደ እነርሱ ተመልሰው ‹‹እኔ ሽማግሌ ሰው ነኝ ወደ ጐንደር ለመሔድ አልችልም›› አሏቸው። እነርሱም ‹አባታችን ሆይ! አንተ ከእኛ ጋር ካልሔድህ ተመልሰን አንሔድም›› አሉ። አባታችንም እጅግ አዝነው "ልጆቼ ሒዱ እኛ እርሰ በእርሳችን በንጉሡ ቤት እንገናኘለን አሏቸውና ተመልስው ሔዱ ተመልስው ከሔዱ በኋላ ወደ ንጉሡ ቤት ቢደርሱ አባታችንን ከንጉሡ ጋር ተቀምጠው አገኟቸው ።የንጉሡ መልእክተኞችም ለንጉሡ " እኛ ከሻሽና ከተነሣን እስከዚህ ዘጠኝ ቀናችን ነው ይኽ አባት የሚያስደንቅ ተኣምር እያደረገ በየት አለፈን? " ብለው እጅግ ተገረሙ ።ንጉሡም ይኽን ድንቅ ተኣምር

በእንተ ቅዱሳን ኅሩያን (ከገድላት አንደበት)

31 Oct, 04:12


በስማ ጊዜ ከአባታችን እግር ሥር ሰገደ አቡነ ዐሥራተ ወልድንም አባቴ ሆይ አስተምረህ ላሳመንኽውና ለአጠመቅኽው ሕዝብ ታቦትን ወስደህ ቤተክርስቲያን ሥራ ከታቦታትም የወደዱኻውን ምረጥ ።በማለት ጠየቃቸው። ብፁዕ አባታችን ዐሥራተ ወልድም በጣም የምወዳት እንደ ምግብ የምመገባት እንደ መጠጥ የምጠጣት እንደ ልብስ የምለብሳት፣ እንደ ምርጉዝ የምደገፋት በፍቅሯ የምረካባት የኪዳነ ምሕረት ታቦት ናትና እርሷን እወዳታለሁ›› ብለው መረጡ፤ ንጉሡም ቃላቸውን ሰምቶ ታላቅ ደስታ ተደሰተ ፈቀደላቸውም።

ከዚኽም በኋላ አቡነ ዐሥራተ ወልድ ወደ ኢየሩሳሌም ሔደው በዚያ ጌታየ ሆይ መሰቀልህን በቅዱሳት መጻሕፍት ሰማሁ ይኽን በዐይኔ አሳየኝ›› እያሉ አንድ ዓመት ቆመው ጸለዩ። የክብር ባለቤት ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስም ለአባታችን ተገለጠላቸውና መጀመሪያ አይሁድ እንዴት እንደሰቀሉት የእሾኽ አክሊልን እንደአቀዳጁት፣ ጐኑን በጦር እንደተወጋ አሳያቸው። አቡነ ዐሥራተ ወልድም የጌታችንን ስቅለት በተመለከቱ ጊዜ እጅግ ደንግጠው ወደቁ።

በዚያን ጊዜም ጌታችን ወደ እርሳቸው መጥቶ ልታይ የማትችለውን ዕለተ ዐርብ ለምን ለመንከኝ? እንግዲህ ተነሣና ወደ ሀገርህ ተመለስ የሰበሰብሃቸው መንጋዎችህ አንተን በማጣታቸው ተበትነዋልና» አላቸው። ከዚኽም በኋላ ጌታችን ታላቅ የምሕረት ቃልኪዳን ገብቶላቸው በክብር ዐረገ። አባታችን ዐሥራተ ወልድም ከገዳማቸው ወጥተው ወደ ኢየሩሳሌም ሔደው አንድ ዓመት ከቆዩ በኋላ በትንሣኤ ዕለት ቅዱስ ሥጋውንና ክቡር ደሙን ተቀብለው በመንፈስ ቅዱስ ኃይል ተመስጠው ካህናት ጸሎተ ቅዳሴውን ሳይጨርሱ ገዳማቸው ዙርዙር ኪዳነ ምሕረት ደረሱ።

ከዚኽም በኋላ አባታችን ጉርብ በምትባል ዋሻ ውስጥ በአድያም ሰገድ ኢያሱ ዘመን ቤተ ክርስቲያንን ሠርቶላቸው መቶ ዐሥር ዓመት ከኖሩና ጌታችንም ታላቅ የምሕረት ቃልኪዳን ከገባላቸው በኋላ የጥቅምት ወር በባተ በሃያ አንድ ቀን ከዚኽ ዓለም ድካም በሰላም ዐርፈዋል።

የአቡነ ዐሥራተ ወልድ ረድኤት በረከታቸው ይደርብን፣ በጸሎታቸው ይማረን።

በእንተ ቅዱሳን ኅሩያን (ከገድላት አንደበት)

30 Oct, 11:32


አንድ አምላክ በሚሆን በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም አሜን
ጥቅምት 21-አምላክን በድንግልና የወለደች እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ተአምራት አድርጋ ደቀ መዝሙር ማትያስን ከእሥር ቤት ያዳነችበት ዕለት ነው፡፡
+ ታላቅ ጻድቅ አቡነ አላኒቆስ ዕረፍታቸው ነው፡፡
+ ነቢዩ ቅዱስ ኢዩኤል ዕረፍቱ ነው፡፡
+ ጌታችን ከሞት ያስነሣው አልዓዛር የሥጋው ፍልሰት ሆነ፡፡
+ ዳግመኛም በዚህች ዕለት ዳግማዊ ቆስጠንጢኖስ በተባለው በንጉሣችን በዐፄ ዳዊት ዘመን የነበሩትና ከእርሱም ጋር መልካም ግንኙነት የነበራቸው የኢየሩሳሌሙ አባ ዮሐንስ ዐርፈዋል፡፡
ነቢዩ ቅዱስ ኢዩኤል፡- ይኸውም ቅዱስ ነቢይ የእስራኤልን ልጆች የሚያስተምርና የሚገሥጻቸው ነበር፡፡ ስለ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በኢየሩሳሌም መኖርና የሕይወትን ትምህርት ማስተማሩን በትንቢት ተናግሯል፡፡ ደግሞም በጌታችን ላይ ይደርበት ዘንድ ስላለው መከራው ትንቢት ተናገረ፡፡ በሐዋርያት፣ በሰባ ሁለቱ አርድእትና በሠላሳ ስድስቱ ቅዱሳት አንስት ላይ የመንፈስ ቅዱስን መውረድ እንዲህ ሲል ተናገረ፡- ‹‹በሥጋዊ በደማዊ ሰው ሁሉ ከመንፈሴ አሳድርበታለሁ፤ ሴቶች ልጆቻችሁና ወንዶች ልጆቻችሁ ትንቢትን ይናገራሉ፣ አለቆቻችሁ ሕልምን ያልማሉ ጎልማሶቻችሁም ራእይን ያያሉ፡፡ ያንጊዜም ከተራራው ማር ከኮረብታውም ወተት ይፈሳል በቤተ እግዚአብሔር አጠገብ ካሉ ከይሁዳ አገሮች ሁሉ ምንጩ ከላይ ወደታች ይፈሳል፡፡››
ነቢዩ ኢዩኤል ዳግመኛም ሙታን በሚነሡ ጊዜ ስለሚሆነው የፍርድ ሰዓት ትንቢት ሲናገር ‹‹ፀሐይና ጨረቃ ይጨልማሉ፣ ከዋክብትም ብርሃናቸው ይጠፋል›› አለ፡፡ ነቢዩ የትንቢቱን ወራት ከፈጸመ በኋላ እግዚአብሔርን አገልግሎ በዚህች ዕለት በሰላም ዐርፏል፡፡ ረድኤት በረከቱ ይደርብን፣ በጸሎቱ ይማረን!
+ + +
የቅዱስ አልዓዛር የሥጋው ፍልሰት፡- ይኸውም ቅዱስ አልዓዛር ከሞተ ከ4 ቀን በኋላ ጌታችን ከሞት ያስነሣውና ተአምሩን ያደረገለት ሲሆን እርሱም ወንጌልን እየሰበከ ልዩ ልዩ ተአምራትን እያደረገ ክርስትናን አስፋፍቷል፡፡ በተሾመባት ቆጵሮስ ከተማም የመጀመሪያው ጳጳስ በመሆን እግዚአብሔርን ሲያገለግል ኖሮ መጋቢት 17 ቀን በሰማዕትነት ዐርፏል፡፡
ቅዱስ አልዓዛር በሰማዕትነት ካረፈ ከብዙ ዘመን በኋላ ከክርስቲያን ነገሥታት መካከል አንዱ የቅዱስ አልዓዛር ሥጋው በቆጵሮስ እንዳለ በሰማ ጊዜ ከቆጵሮስ ደሴት ወደ ቁስጥንጥንያ አፈለሰው፡፡ ሊያፈልሱትም በወደዱ ጊዜ በከበረ የድንጋይ ሣጥን ውስጥ ሆኖ በምድር ውስጥ ተቀብሮ አገኙት፡፡ በላዩም እንዲህ የሚል ጽሑፍ ነበረ፡- ‹‹ይህ በመቃብር ውስጥ አራት ቀን ከኖረ በኋላ ከሙታን ለይቶ ላስነሣው ክብር ይግባውና የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ወዳጁ የሆነ የቅዱስ አልዓዛር ሥጋ ነው፡፡›› ይህንንም ጽሑፍ ባነበቡ ጊዜ ደስ ተሰኝተው ተሸክመው ወደ ቁስጥንጥንያ አገር ወሰዱት፡፡ ካህናቱም ሁሉ በዝማሬ በክብር ተቀበሉት፡፡ ባማረ ቦታ አስቀምጠውት በዚህች ዕለት በዓሉን አደረጉለት፡፡ ረድኤት በረከቱ ይደርብን፣ በጸሎቱ ይማረን!
+ + +
የኢየሩሳሌሙ አባ ዮሐንስ፡- ከደጋግ ክርስቲያን ቤተሰብ ተወልደው የቤተ ክርስቲያንን ትምህርት ተምረው ነው ያደጉት፡፡ በቅስና ማዕረግ ቤተ ክርስቲያንን ሲያገለግሉ ኖረዋል፡፡ አባ ዮሐንስ በጾም በጸሎት ምጽዋትም በመሥጠት፣ድኆችን በመርዳትና በስብከታቸው በእጅጉ ይታወቃሉ፡፡ ከብዙ ተጋድሎአቸውም በኋላ የኢየሩሳሌም ሊቀ ጳጳሳት ሆኑ፡፡ ሰውም ስለ ቅድስናቸው በጣም ይወዳቸው ነበር፡፡ ጻድቁ እግዚአብሔርን በትጋት እያገለገሉ ሳለ የእስክንድርያው ሊቀ ጳጳሳት አባ ማርቆስ አባ ዮሐንስን ወደ ኢትዮጵያ በመላክ ዐፄ ዳዊትን እንዲለምኗቸው ነገሯቸው፡፡ እስላሞች በእስክንድርያ እያመፁ ሲያስቸግሩ የኢትዮጵያው ንጉሥ ዐፄ ዳዊት ሄዶ ፈጅቷቸው ነበር፡፡ ከዚህም በኋላ ዳግመኛ ዐፄ ዳዊት እስላሞችን እንዳይፈጃቸው መልአክት ይነግሩት ዘንድ ሊቀ ጳጳሳት አባ ማርቆስን የምስር አገሩ ንጉሥ ጠየቃቸው፡፡
አባ ማርቆስም ወደ ኢትዮጵያው ንጉሥ ዐፄ ዳዊት የሚላኩ ሰዎችን ከመኳንንቱና ከኤጲስ ቆጶሳቱ ከሀገር ታላላቅ ሽማግሌዎች ጋር ተማክሮ የኢየሩሳሌምን አባ ዮሐንስንና የምስሩን አገር አባ ሳዊሮስን በአስተዋይነታቸው፣ በዕውቀታቸውና በቅድስናቸው መርጠዋቸው ወደ ኢትዮጵያ ላኳቸው፡፡ እነዚህም ሁለት ቅዱሳን ታዛዥ ሆነው ወደ አገራችን መጡ፡፡ ንጉሡ ዐፄ ዳዊትም መምጣታቸውን በሰማ ጊዜ እጅግ ደስ ብሎት አሽከሮቹን አስከትሎ ወጥቶ ሄዶ አክብሮ ተቀበላቸው፡፡ ከእነርሱም በረከትን ተቀበለ፡፡ እነርሱም የአባ ማርቆስን ደብዳቤ ሰጡት፡፡ ዐፄ ዳዊትም ደብዳቤውን ተቀብሎ አንብቦ ለሊቀ ጳጳሳቱ ቃል ታዛዥ መሆኑን ገለጠላቸው፡፡ ከዚህም በኋላ አባ ዮሐንስና አባ ሳዊሮስን ወደ ሀገረ ስብከታቸውና ሕዝባቸው ተመልሰው ይሄዱ ዘንድ አልተዋቸውም ስለ ቅድስናቸውና ስለ ትምህርታቸው ጣዕም በጣም ወዷቸዋልና በእርሱም ዘንድ እንደ መላእክት ሆነዋልና፡፡ ከጥቂት ወራትም በኋላ አባ ዮሐንስን ከዚህ ዓለም ድካም ያሳርፋቸው ዘንድ እግዚአብሔር ወዷልና ጥቂት ሕማም ካገኛቸው በኋላ ዐርፈዋል፡፡ የአባ ዮሐንስ ረድኤት በረከታቸው ይደርብን፣ በጸሎታቸው ይማረን!
+ + +
እመቤታችን ለሐዋርያው ማትያስ ያደረገችለት ተአምር፡- የከበሩ ቅዱሳን ወንጌልን በዓለም ዞረው ይሰብኩ ዘንድ ዕጣ ሲጣጣሉ ለቅዱስ ማትያስ ዕጣ የደረሰው ሰውን ወደሚበሉ ሰዎች አገር ነበር፡፡ ይህችም ሀገር እስኩቴስ የተባለች ሩሲያ እንደሆነች የቤተ ክርስቲያን ታሪክ ጸሐፊዎች ፍንጭ ሰጥተዋል፡፡
ማትያስም እነዚህ ሰውን የሚበሉ ሰዎች አገራቸው እንደደረሰ ዐይኑን አውልቀው አሠሩት፡፡ ምግባቸውም የመጻተኛ ሰው ሥጋ ነው፡፡ በልማዳቸው መሠረት መጻተኛን ሰው ገና እንደያዙት ዐይኖቹን ዐውልቀው በእሥር ቤት ያኖሩታል፡፡ እስከ 30 ቀንም ድረስ ሳር እያበሉ ያስቀምጡትና በ30ኛው ቀን አውጥተው አርደው ይበሉታል፡፡ ሐዋርያው ማትያስንም በልማዳቸው መሠረት ዐይኖቹን አውልቀው አሠሩት፡፡ ሐዋርያውም በእሥር ቤት ሆኖ በዚያ ላይ ዐይኖቹን ታውሮ ሳለ በጭንቅ ወደ ጌታችንና ወደ እመቤታችን ይለምን ነበር፡፡ ነገር ግን እመብርሃንና ልጇ መድኃኔዓለም 30ኛው ቀን ሳይፈጸም ሐዋርያው እንድርያስን ወደ እርሱ ላኩለት፡፡ ማትያስም ዐይኑን ፈወሱለትና ማየት ቻለ፡፡
እንድርያስም በተዘጋው በር በተአምራት ገብቶ አሥርቤቱ ውስጥ ያሉ እሥረኞችን በስውር አውጥቶ ከከተማው ውጭ ካስቀመጣቸው በኋላ ሁለቱ ሐዋርያት ተመልሰው ሰውን ለሚበሉት ሰዎች ተገለጡላቸው፡፡ እነርሱም ይዘው በአንገታቸው ገመድ አግብተው ለ3 ቀን በሀገራቸው ጎዳናዎች ላይ ሁሉ ጎተቱዋቸው፡፡ ሁለቱም ሐዋርያት በጸሎታቸው ከእሥር ቤቱ ምሰሶ ሥር ውኃ አፈለቁና ውኃው ሀገራቸውን ሁሉ እስኪያጥለቀልቅና ሰዎቹንም እስከ አንገታቸው ድረስ እስከሚደርስ ሞላ፡፡ ሁሉም በተጨነቁ ጊዜ ሁለቱ ሐዋርያት በፊታቸው ተገለጡና ‹‹በጌታችን እመኑ ትድናላችሁ›› በማለት ወንጌልን ሰብከውላቸው አሳመኗቸው፡፡ ምሥጢራትንም ሁሉ ገለጡላቸው፡፡ ደግሞም የአራዊት ጠባይን ከሰዎቹ ያርቅላቸው ዘንድ ወደ ጌታችንና ወደ ተወደደች እናቱ ከጸለዩ በኋላ በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም አጠመቋቸው፡፡ ያ የአውሬነት ጠባያቸውም ጠፍቶላቸው የዋህ፣ ቅንና ሩኅሩኆቸ ሆኑ፡፡ ሐዋርያትም ሃይማኖትን እያስተማሯቸው 30 ቀን አብረዋቸው ከተቀመጡ በኋላ አገልጋይ ኤጲስ ቆጶሳትን፣ ካህናትንና ዲያቆናትን ሾመውላቸው ወደ ሌላ ሀገር ሄዱ፡፡

ለሐዋርያት ሞገሳቸው ጣዕመ ስብከታቸው የኾነች ክብርት እመቤታችን ለእኛም ትለመነን!

በእንተ ቅዱሳን ኅሩያን (ከገድላት አንደበት)

30 Oct, 02:46


የአቡነ ዮሐንስ ሐጺር የሥጋው ፍልሰት፡- ይኸኸም የሥጋው ፍልሰት የሆነው በቁልዝም ገዳም ካረፈ በኋላ ነው፡፡ ለአባቶች ሊቃ ጳጳሳት 48ኛ የሆነው አባ ዮሐንስ ወደ አስቄጥስ ገዳም በሄደ ጊዜ መነኮሳት ‹‹የቅዱስ ዮሐንስ ሐጺርን ሥጋውን አፍልሰን በዚህ በቤተ ክርስቲያኑ ሥጋው ባለበት ለፈጣሪያችን እንስገድ›› አሉት፡፡ የአቡነ ዮሐንስ ሐጺር ሥጋው ይጠበቅ የነበረው የኬልቄዶንን ጉባኤ በሚቀበሉ ከሃዲያን ነበር፡፡ አባ ዮሐንስም መልእክት ጽፎ ወደ ቁልዝም አገር ቢልክም እነዚህ ከሃድያን የቅዱሱን ሥጋ ከለከሏቸው፡፡ ነገር ግን ሥጋው ያለበትን ቦታ አዩት፡፡

ከጥቂት ቀን በኋላ ከታላላቅ ዐረቦች ወገን የሆነ ለቁልዝም አገር መኮንን ሆኖ ተሾመ፡፡ እርሱም ለአገሪቱ ኤጲስ ቆጶስ ለአባ ሚካኤል ወዳጁ ነው፡፡ አባ ዮሐንስም ይህንን ሲሰማ ስለ ቅዱስ ዮሐንስ ሐጺር የሥጋው ፍልሰት መነኮሳትን እንዲረዳቸው ለአባ ሚካኤል መልአክት ላከ፡፡ አባ ሚኤልም ከከሃድያን እጅ ሊወጣ መሆኑን አስቦ ደስ አለው፡፡ ጉዳዩንም ወዳጁ ለሆነው መኮንን ነገረውና ሁለቱም መነኮሳቱን አስከትለው ወደ ገዳሙ ሄዱ፡፡ መኮንኑም መነኮሳቱን ይዞ ወደ ገዳሙ እንዴት እንደሚገባ ካሰበ በኋላ መነኮሳቱን ከላይ የዐረቦቹን ልብስ አስለብሶ ብዙ ፈረሰኞችን ይዞ ቁልዝም ገዳም ደረሱ፡፡ መኮንኑም በዚያ የሚኖረውን የመለካውያንን ኤጲስቆጶስ ‹‹በዚህች ሌሊት በዚህ ገዳም ማደር እፈልጋለሁና ያንተን መነኮሳት ከገዳሙ አስወጣቸው›› ብሎ አዘዘው፡፡ ኤጲስቆጶሱም እንደታዘዘው አደረገ፡፡ ከዚህም በኋላ መነኮሳቱ የቅዱስ ዮሐንስ ሐጺርን ሥጋ ይዘው ወደ ምስር አገር ከደረሱ በኋላ አስቄጥስ ገዳም ደረሱ፡፡ የአባ መቃርስ ገዳም መነኮሳትም ወንጌልን፣መስቀሎችን፣ መብራቶችን ይዘው እየዘመሩ በታላቅ ክብር ተቀበሏቸው፡፡ ወደ አባ መቃርስ ሥጋም አቅርበውት የቁርባን ቅዳሴን ቀደሱ፡፡ በቅዳሴው ላይ ቅዱስ ወንጌል በተነበበ ጊዜ ታላቅ የሆነ ድንቅ ተአምር ተፈጸመ፡፡ ቤተ ክርስቲያኒቱ ሁለመናዋ በሰማያዊ ብርሃን ተጥለቀለቀች፡፡ ከቶ እንደ እርሱ ሆኖ የማያውቅ በጎ መዓዛም ሸተተ፡፡ ይህም ተአምር ለ7 ቀናት ቆየ፡፡

ከዚህም በኋላ የቅዱስ ዮሐንስ ሐጺርን ሥጋ ወደ ራሱ ቤተ ክርስቲያን በክብር ወስደው ሲያኖሩት አሁንም ድንቅ ድንቅ ተአምራት ተፈጽመው ታዩ፡፡ አባ ማርቆስም የእስክንድርያ አገር ታላላቅ ሰዎችን አስከትሎ ወደ ቤተ ክርስቲያኑ ገብቶ የቅዱስ ዮሐንስ ሐጺርን ሥጋ የተጠቀለለበትን ሰሌን ገልጦ ሲሳለመው ታላቅ መብረቅና ነጎድጓድ ሆነ፡፡ ወዲያውም በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ያሉት ሁሉም ደንግጠው ወደቁ፡፡ ሊቀ ጳጳሳቱም ሰሌኑን መልሶ ሥጋውን በጠቀለለ ጊዜ ሰላም ሆነ፡፡ እነርሱም እንዲህ እያሉ ቅዱስ ዮሐንስ ሐጺርን አመሰገኑት፡- ‹‹ፈጣን ደመና ሆነህ የመንፈስ ቅዱስን ዝናብ የተሸከምህ፣ ሠለስቱ ደቂቅ ወዳሉበት ወደ ባቢሎን የሄድህ፣ በላይ ባደረ በመንፈስ ቅዱስ ኃይል ወደ እስክንድርያ የተመለስህ፣ ሁለተኛም ወደ ቁልዝም አገር የሄድህ፣ የጣዖታትን ቤቶች አፍርሰህ ሃይማኖትን የሰበክህ፣ ሕሙማንን የፈወስህ አጋንንትን ያወጣህ ወደ ርስትህም የተመለስህ አንተ የበረከት ማደሪያ ነህ›› እያሉ አመሰገኑት፡፡

የቅዱስ ዮሐንስ ሐጺር ረድኤት በረከቱ ይደርብን፣ በጸሎቱ ይማረን!

በእንተ ቅዱሳን ኅሩያን (ከገድላት አንደበት)

30 Oct, 02:46


አንድ አምላክ በሚሆን በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም አሜን
ጥቅምት 20 -ታላቁ ጻድቅ አቡነ ዮሐንስ ሐፂር ዕረፍቱ ነው፡፡
+ ዳግመኛም በዚኽች ዕለት ነቢዩ ቅዱስ ኤልሳዕ ዓመታዊ መታሰቢያ በዓሉ ነው፡፡

አቡነ ዮሐንስ ሐፂር፡- አቡነ ዮሐንስ ሐጺር ቁመታቸው አጭር ስለነበር ‹‹ዮሐንስ ሐጺር›› አጭሩ ዮሐንስ ተብለዋል፡፡ በ309 ዓ.ም ከተወለዱ በኋላ በ18 ዓመታቸው አስቄጥስ ገዳም ገቡ፡፡ አበምነቱ አባ ባይሞይ የምንኩስና ኑሮ እጅግ ከባድ መሆኑን በመንገር ወደ ቤታቸው እንዲመለሱ ቢመክሯቸውም እሳቸው ግን በቁርጥ ሀሳብ ወሰኑ፡፡ አባ ባይሞይ ግን የዚህን ወጣት ዕጣ ፈንታ ግለጥልኝ ብለው ሱባኤ ያዙ፡፡ የታዘዘ መልአክም መጥቶ ‹‹እርሱ የተመረጠ ዕቃ ይሆናልና ተቀበለው ብሎሃል›› ብሎ ነገራቸው፡፡ እንደታዙትም ተቀበሉት፡፡ አቡነ ዮሐንስም ገዳሙ እንደገቡ በብዙ ተጋድሎ ሲኖሩ ምንጣፍ ሳያነጥፉ መሬት ላይ ነበር የሚተኙት፡፡

አባታችን በታዛዥነታቸው በእጅጉ ይታወቃሉ፡፡ ይህንንም ለመፈተን አንድ ቀን አባ ባይሞይ የደረቀ እንጨት አንስተው ለአቡነ ዮሐንስ ሰጧቸውና ‹‹ይህን ደረቅ እንጨት ትከለውና ውሃ እያጠጣህ አብቅለው፣ ፍሬ እስኪያፈራም ተንከባከበው›› አሏቸው፡፡ አቡነ ዮሐንስም በፍጹም መታዘዝ እሺ ብለው ደረቁን እንጨት ተከለው ሦሰት ዓመት ሙሉ ከሩቅ ቦታ በቀን ሁለት ጊዜ ውኃ እየቀዱ በማምጣት ማጠጣት ጀመሩ፡፡ በ3ኛውም ዓመት ደረቁ እንጨት ጸድቆ ለመለመ፣ ታላቅ ዛፍም ሆኖ አብቦ አፍርቶ ጣፋጭ ፍሬ አፈራ፡፡ አባ ባይሞይም ፍሬውን ቆርጠው ወስደው ‹‹የታዛዡን የትሑቱን ፍሬ እነሆ ቅመሱ›› እያሉ ለቅዱሳን ሰጧቸው፡፡ ቅዱሳኑም እግዚአብሔርን እያመሰገኑ ተመገቡት፡፡ ዛፉም ‹‹የመታዘዝ ዛፍ›› እየተባለ መጠራት ጀመረ፡፡
ቅዱሳን ትልቁ የቅድስና ደረጃ ላይ ሲደርሱ ቀና ቢሉ ሥሉስ ቅዱስን ይመለከታሉ ዝቅ ቢሉ ደግሞ እንጦሮጦስን ያያሉ፡፡ አቡነ ዮሐንስ ሐጺር በታላቅ ተጋድሎአቸው ሥሉስ ቅዱስን በገሃድ ለማየት የበቁ ታላቅ አባት ናቸው፡፡ በአባ ቴዎፍሎስ እጅ በገዳሙ ላይ አበምኔትነት ሲሾሙ ይገባዋል የሚል ድምፅ ከሰማይ ተሰምቷል፡፡ ሊቀ ጳጳሳቱ አባ ቴዎፍሎስ አቡነ ዮሐንስን የቅዱሳን የሠለስቱ ደቂቅን ሥጋቸውን እንዲያመጡ ወደ ባቢሎን ልከዋቸው ሄደው አምጥተዋል፡፡
አባ ባይሞይ ጋር መንፈሳዊ ምክርንና ስለ ምንኩስና ትምህርት ለማመር ወደ እርሳቸው የሚመጡትን ሁሉ ወደ አቡነ ዮሐንስ ዘንድ ይልኳቸው ነበር፡፡ አቡነ ባይሞይ ጊዜ ዕረፍታቸው ሲደርስ መነኮሳቱን ሰብስበው የአቡነ ዮሐንስን እጅ በመያዝ ‹‹በምድር ያለ መልአክ ነውና ተቀበሉት›› ብለው ገዳማቸውንና ልጆቻቸውን እንዲጠብቁላቸው አደራ ሰጧቸው፡፡ አቡነ ዮሐንስ የበቃውንና ያልበቃውን ያውቁ ስለነበር ያልተገባው ሰው ሥጋ ወደሙን ሊቀበል ሲመጣ ንስሓ ገብቶ እንመለስ ይነግሩታል፡፡ አባታችን ሲቀድሱ ቅዱስ ቁርባንን መቀበል የማይገባቸውን ሰዎች በመንፈስ ቅዱስ ዐውቀው እየለዩ ‹‹ዛሬ ሄዳችሁ ንስሓ ገብታችሁ ተመለሱ›› ይሏቸዋል፡፡ የወደፊቱንም በትንቢት ይናገሩ ነበር፡፡ አንድ ሰው በኃጢአት ወድቆ ባዩ ጊዜ እንዲህ ይሉ ነበር፡- ‹‹ይህ ወንድሜ ኃጢአት የሠራው ዛሬ ነው፣ ምናልባት እኔ ደግሞ ነገ ኃጢአት እሠራ ይሆናል፡፡ እርሱን በፈተና የጣለ ሰይጣን እኔንም ይጥለኝ ይሆናል፡፡ እርሱ ዛሬ ቢበድል ነገ በንስሓ ይታጠባል፣ አቤቱ እኔ ግን ከኃጢአቴ የምነጻበት ሰዓት አይኖረኝ ይሆናል›› እያሉ አምርረው ያለቅሳሉ፡፡

የቅድስና ሕይወታቸውንም እንዴት ዕለት ዕለት እንደሚጠብቁ እንዲህ በማለት ተናግረዋል፡- ‹‹አንድ ሰው በጾምና በርሃብ ከጸና የነፍሱ ጠላቶች ይደክማሉ፤ እኔ በትልቅ ዋርካ ሥር የተቀመጠንና አራዊት ሊጣሉት የመጣን ሰው እመስላለሁ፣ ሊቋቋማቸው እንደማይችል ከተረዳ ሸሽቶ ወደ ዛፉ በመውጣት ነፍሱን ያድናል፡፡ በእኔም የተፈጸመው ይሄው ነው፡፡ በበዓቴ ተቀምጬ ክፉ ሀሳቦች ሊቃወሙኝ ሲመጡ ልቋቋማቸው እንደማልችል ባወቅሁ ጊዜ በጸሎት ወደ እግዚአብሔር ሸሽቼ እመሸጋለሁ፡፡ በዚያም ከጠላቶቼ ፍላጻ እድናለሁ›› በማለት እንዴት የቅድስና ሕይወታቸውን ይጠብቁ እንደነበር ተናግረዋል፡፡

አቡነ ዮሐንስ ሐጺር ሌላው የሚታወቁበት አንድ ትልቅ ግብራቸው የአትናስያን ሞት ወደ ሕይወት የለወጡበት ነው፡፡ አትናስያ መጀመሪያ ላይ ጻድቅ ነበረች፣ በገንዘቧ ገዳማትንና መነኮሳትን የምትረዳ አገልጋዮችን የምትራዳ ደግ ሴት ነበረች ነገር ግን በኋላ ላይ ጠላት ሰይጣን በወጥመዱ ጣላትና በዝሙት እንድትወድቅ አደረጋት፡፡ ዘማዊ ሴትም ሆነች፡፡ በቀድሞ የቅድስና ሕይወቷ የሚያውቋት መነኮሳት ሁሉ መክረው ሊመልሷት ቢሞክሩ አልመለስላቸው አለች፡፡ ይልቁንም ሊመክሯት ሲመጡ እየሳቀችባቸው ታሾፍባቸው ጀመር፡፡ በመጨረሻም መነኮሳቱ አቡነ ዮሐንስ ሐጺርን ላኳቸው፡፡ እርሳቸውም ተራ ሰው መስለው ወደ ቤቷ ገቡ፡፡ ለዝሙት የመጣ ተራ ሰው መስሏት በደስታ ተቀበለችው፡፡ ልታጫውተውም ስትሞክር ዮሐንስ ሐጺር ማልቀስ ጀመረ፡፡ ‹‹ለምን ታለቅሳለህ?›› ብትለው ‹‹መልክሽ ደስ ብሎኝ›› አላት፡፡ እርሷም ‹‹ታዲያ ደስ የሚል መልክ ያስቃል እንጂ መች ያስለቅሳል?›› ስትለው ‹‹የለም ነገ ገሃነም እንደምትወርጂ ታይቶኝ ነው፣ እነሆ የሰይጣን ማደሪያ ሆነሽ ብዙ አጋንንት በሰውነትሽ ሲወጡ ሲወርዱ አያለሁ…›› እያሉ ብዙ መክረው አስተማሯት፡፡ እርሷም ዓይነ ልቡናዋ ተከፍቶላት ወደ ልቧ ተመለሰች፡፡

አትናስያም በጣም ደንግጣ በመጸጸት ‹‹ታዲያ ምን ባደርግ ይሻለኛል?›› አለቻቸው፡፡ ‹‹ንስሃ ግቢ›› አሏት፡፡ ‹‹በውኑ አሁን እኔ ምሕረት አገኛለሁን? ኃጢያቴ ብዙ ነው፣ ከእግዚአብሔር ጋር ማን ያስታርቀኛል?›› ስትላቸው ‹‹እኔ አስታርቅሻለሁ ተከተይኝ›› ብለው ወጥተው ሄዱ፡፡ እርሷም ልዋል ልደር ሳትል በሯ እንደተከፈተ ቤት ንብረቷን ትታ አባ ዮሐንስን ተከተለቻቸው፡፡ እሳቸው ላይ ለመድረስ እየሮጠች ስትሄድ በልስላሴ የኖረ እግሯ እየቆሰለና እየተሰነጣጠቀ ደሟ እንደ ውኃ በመሬት ላይ ፈሰሰ፡፡ ሲመሽ ከገዳሙ በር ላይ ደርሳ የምታርፍበትን ቦታ ለይተው ሰጧትና እዚያ ተኛች፡፡ አባ ዮሐንስ ሌሊት ለጸሎት ሲነሡ መላእክት ሲወጡ ሲወርዱ ተመልክተው ‹‹ይህ የማየው ነገር ምንድን ነው?›› በማለት አንዱን መልአክ ጠየቁት፡፡ ‹‹ትላንትና አንተን ተከትላ የመጣችው ሴት ሞታ ነፍሷን እያሳረግን ነው›› አላቸው፡፡ ‹‹እግዚኦ ንስሓ ሳትገባ›› ብለው ደነገጡ፡፡ መልአኩም ‹‹አንተን ልትከተል ገና አንድ እግሯን ከቤት ስታወጣ ኃጢአቷ በሙሉ ተፍቆላታል፤ አሁን ወደ ገነት እየወሰድናት ነው›› አላቸው፡፡ አባ ዮሐንስ ሐጺርም ተገርመው እግዚአብሔርን እያመሰገኑ ‹‹የመቃብሯስ ነገር እንዴት ነው?›› ብለው ጠየቁት፡፡ መልአኩም ‹‹አንበሶች ይመጣሉ የመቃብሯን ቦታ ለክተህ አሳያቸው›› ብሏቸው ተሰወረ፡፡ አንበሶቹም መጥተው አባ ዮሐንስ ቦታውን ለክተውላቸው አንበሶቹ መቃብሩን ቆፍረው በክብር ቀብረዋታል፡፡ በአንዲት ዕለት ወደ በዓታቸው ሲገቡ ጌታችን ተገልጦላቸው ዕለተ ሞታቸው መቅረቡን ከነገራቸው በኋላ ታላቅ ቃልኪዳን ሰጥቷቸው ጥቅምት 20 ቀን 409 ዓ.ም በሰላም ዐርፈዋል፡፡

በእንተ ቅዱሳን ኅሩያን (ከገድላት አንደበት)

28 Oct, 17:57


በባሕር ላይ የታነጸው ቤተመቅደስ እና የቅዱስ ይምርሐነ ክርስቶስ መካነ መቃብር
"ይምርሐነ ፍታኝ! "
ጌታችን "ሥጋዬን እየፈተትህ ለሕዝቦቼ ትነግሥላቸው ዘንድ መንግሥትን ለአንተ ሰጠሁህ" ብሎ በተቀደሱ እጆቹ የንግሥና ቅባትን ቀባው፡፡ በዚህም ጊዜ ይምርሐነ ክርስቶስ "...አምላኬ ሆይ እኔ ከሁሉ ይልቅ ታናሽ ነኝና እባክህ ታነግሥ ዘንድ ሌላ ሰው ምረጥ" ብሎ ከጌታችን ጋር በትሕትና ተከራከረ፡፡ ጌታችን በቅዱስ ቃሉ "ክህነትህ ምድራዊ አይደለም፣ ሰማያዊ ነው እንጂ" ብሎታል፡፡

ቅዱስ ይምርሐነ ክርስቶስ ገና ሲወለድ አንደበቱን ፈቶ እግዚአብሔርን በአንድነቱ በሦስትነቱ ያመሰገነ ታላቅ ጻድቅ ሲሆን 40 ዓመት ሙሉ ሰማያዊ ኅብስትና ሰማያዊ ጽዋ ከሰማይ እየወረደለት ቀድሷል፡፡

የእግዚአብሔርን ጌትነትና የይምርሃነ ክርስቶስ የቅድስና ሕይወት በዓለም ሁሉ መሰማት እንደጀመረ የሮም ሰዎችም ወደ እርሱ መጥተው 55 ውድ መስቀሎችን በስጦታ ገበሩለት፡፡ እግዚአብሔር በእርሱ ላይ የሚያደርገውን ተአምርና ቅድስናውን የሰሙ ቁጥራቸው 5740 የሆኑ የግብፅና የሮም ጳጳሳትና ኤጲስቆጶሳት፣ ቀሳውስትና ዲያቆናት እንዲሁ መነኮሳት ቅዱስ ይምርሃነ ክርስቶስ የሚወርድለትን ሰማያዊ ኅብስትና ሰማያዊ ጽዋ በእጁ ለመቀበልና በመስቀሉ ለመባረክ መጡ፡፡ የግብፁ ሊቀ ጳጳስ ቅዱስ አትናቴዎስም ‹‹ከዚህ ቅዱስ የእግዚአብሔር አገልጋይ እጅ በረከትን መቀበል እሻለሁ›› ብሎ ወደ ኢትዮጵያ መጥቶ ከቅዱስ ይምርሃነ ክርስቶስ ጋር ተገናኝቶ ሁለቱም በረከትን አንዳቸው ከአንዳቸው ተቀብለዋል፡፡ ቅዱስ ይምርሃነ ክርስቶስም ወደ እርሱ ለመጡት 5740 ደጋግ ጳጳሳትና ኤጲስቆጶሳት፣ ቀሳውስትና ዲያቆናት እንዲሁ መነኮሳት ሁሉ ቀድሶ ሰማያዊውን ሥጋ ወደሙን አቀብሏቸዋል፡፡ እነርሱም ሰማያዊውን ሥጋና ሰማያዊውን ደሙን ከተቀበሉ በኋላ "ይህን ባየንበትና በቀመስንበት ሌላ አናይም አንቀምስም" ብለው የተወሰኑት ወደሌሎች የአገራችን ገዳማት የሔዱ ሲሆን ብዙዎቹ ደግሞ ከእርሱው ጋር አብረው በዚያው ዐርፈው ተቀብረዋል፡፡ ዛሬም ድረስ የእነዚህ ቅዱሳን ዐፅም ቤተ መቅደሱ ካለበት ጀርባ በኩል በሚገኘው ትልቅ ዋሻ ውስጥ በክብር ተቀምጦ ይገኛል፡፡

በመጀመሪያ ቅዱስ ይምርሐነ ክርስቶስ በድንኳን ውስጥ ህብስቱና ወይኑ ከሰማይ እየወረደለት ሕዝቡን ያቆርብ ነበር፡፡ ጌታችንም ተገልጾለት "እስከ ዕለት ምጽአት ድረስ ፈጽሞ የማትፈርስ ቤተ መቅደስ ትሠራለህና ተነሥተህ ሂድ ቦታውን ገብርኤልና ሩፋኤል ይመሩሃል" አለው፡፡ በመንገዱም ዕውራንን እያበራና ተአምራትን እያደረገ ተጓዘ፡፡ ቦታው ላይ ሲደርስም ጌታ አሁንም ተገልጾ ስለ ቤተ መቅደሱ አሠራር ነገረው፡፡ ቤተ መቅደሱንም እንዲሠራ ያዘዘው ከባሕር ላይ ነው፡፡ "በዚህ ባሕር ላይ እንዴት አድርጌ እሠራለሁ?" ብሎ ጌታችንን ቢጠይቀው እንጨት፣ ድንጋይና ጭቃ እየረበረበ እንዲሠራ ነገረው፡፡ ዕቃዎቹንም ከኢየሩሳሌም በደመና ሠረገላ እየተመላለሰ አምጥቶ እንደታዘዘው አድርጎ አንጾታል፡፡ የቤተ መቅደሱ ልዩ የሆነ የአሠራር ዘዴ ባሕሩን ከታች እንዲሰወር ቢያደርገውም በባሕር ላይ ለመሠራቱ ዛሬም ድረስ ምልክቱ በግልጽ ይታያል፡፡ ቤተ መቅደሱን በሰባቱ ሰማያት መስሎና ከፍሎ ያስጌጠበት ጥበብ ዛሬ በዓለም ላይ የትኛውም አርክቴክት ፈጽሞ ሊሠራው አይችልም፡፡

ጥቅምት 19-ንግሥናን ከክህነት ጋር አስተባብሮ በመያዝ 40 ዓመት ሙሉ ሰማያዊ ኅብስትና ጽዋ ከሰማይ እየወረደለት የቀደሰው ጻድቁ ንጉሥ ቅዱስ ይምርሐነ ክርስቶስ ዕረፍቱ ነው፡፡ ሕዝቡንም የሚባርክበት መስቀል ከሰማይ የወረደለት ሲሆን ቤተ መቅደሱን በባሕር ላይ እንዲሠራ ራሱ ጌታችን በቃሉ ከነአሠራሩ ጭምር ያስረዳው ነው፡፡

ጌታችንም በድጋሚ ከመላእክቶቸቱ ጋር ተገልጾ ቃልኪዳን ሰጠው፡፡ “ለኃጢአተኞች መዳን ምክንያት ሆነህ ታድናቸው ዘንድ እኔ ወደቦታህ እመልስሃለሁ፤ እኔና የባሕርይ አባቴ አብ የባሕርይ ሕይወቴ ምንፈስ ቅዱስ ካልፈቀድንለት በቀር ቦታህን ማንም አይረግጥብህም፤ በቦታህም መጥቶ መካነ መቃብርህን እየዞረ አቡነ ዘበሰማያት እያለ አምላከ ይምርሃነ ክርስቶስ ማረኝ ያለውን ሰው ዕለቱን እንደተጠመቀ ከእናቱም ማኅፀን እንደተወለደ ሕፃን ልጅ አደርገዋለሁ፡፡ ቦታዋም ዳግማዊ ኢየሩሳሌም ትሁንልህ…” የሚል ድንቅ ቃልኪዳን ገብቶለታል፡፡ በዚህ ቃልኪዳን መሠረት ቅዱስ መካነ መቃብሩ እየተዞረና አቡነ ዘበሰማያት ከተባለ በኃላ ሦስት ጊዜ "ይምርሐነ ፍታኝ! " ይባላል፡፡ እስከ ቅርብ ጊዜም ድረስ ከቅዱስ መካነ መቃብሩ "እግዚአብሔር ይፍታህ" የሚል ጽምፅ ይሰማ ነበር፡፡ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ግን አባቶቻችን በሱባኤ ጠይቀው ድምፁ እንዲጠፋ አድርገውታል፡፡

የቅዱስ ይምርሃነ ክርስቶስ ረድኤት በረከቱ ይደርብን፣ በጸሎቱ ይማረን!

"ይምርሐነ ፍታኝ! "

በእንተ ቅዱሳን ኅሩያን (ከገድላት አንደበት)

26 Oct, 18:51


እንደ እግዚአብሔር መልካም ፈቃድ የአቡነ አላኒቆስ ዘማይበራዝዮ ገዳም ገድላቸው ታትሞ ዛሬ ወጥቷል!

ሃያ ኹለት ዓመት ተረግዞ ኖሮ በኃላ በጸሎታቸው ኃይል ፂምና ጥርስ ያለው ልጅ እንዲወለድ ያደረጉት፣ ታቦተ ጽዮንን 40 ዓመት ያጠኑ፣ አንበሳን 7 ዓመት ውኃ ያስቀዱት፣ ንግሥናን ንቀው የመነኑ ታላቅ ጻድቅ ናቸው-አቡነ አላኒቆስ። ጥቅምት 21 ቀን ዕረፍታቸው ነው፡፡

አቡነ አላኒቆስ የትውልድ ቦታቸው ሸዋ አንኮበር ሲሆን አባታቸው ንጉሡ ዐፄ ይኩኖ አምላክ ነው፡፡ ንጉሡ አባታቸው ‹‹አግባና መንግሥቴን ይዘህ ተቀመጥ›› ቢላቸው እርሳቸው ግን ንግሥናን በመናቅ እምቢ ብለው ሄደው ከእመቤታችን ሥዕል ሥር ወድቀው ቢለምኗት እምቤታችን ተገልጣላቸው ‹‹ክፍልህ ምናኔ ነው፣ የአባትህ መንግሥት ያልፋል የልጄ መንግሥት ግን ዘላለማዊ ነው›› አለቻቸው፡፡ ጻድቁም ወደ ሐይቅ እስጢፋኖስ ሄደው በዚያው መንኩሰው ገዳሙን እያገለገሉ ተቀመጡ፡፡ ከጸሎታቸው በኋላ ራሳቸውን ወደ ባሕሩ ይጥሉ ነበርና አንድ ቀን እንዲሁ ራሳቸውን ወደ ባሕሩ ሲጥሉ መላእክት አውጥተዋቸዋል፡፡ አቡነ አላኒቆስ ወደ አክሱም እንዲሄዱ ታዘው ከሄዱ በኋላ በዚያም የጽላተ ሙሴ የታቦተ ጽዮን አጣኝ ሆነው 40 ዓመት ተቀምጠዋል፡፡ እመቤታችንም ተገልጣላቸው በዓታቸውን እንዲያጸኑ ከነገረቻቸው በኋላ ከአክሱም ወጣ ብሎ የሚገኘውን ማይበራዝዮ ገዳምን መሠረቱ፡፡ በዚያም እጅግ አስገራሚ ተአምራትን እያደረጉ ወንጌልን እያስተማሩ አገልግለዋል፡፡

አንድ ቀን መኰንኑ ወደ ሩቅ ቦታ ሲሄድ ቤተሰባቸውን ለንስሓ አባታቸው አደራ ሰጥተው ሄዱ፡፡ የንስሓ አባታቸውም የአቡነ አላኒቆስ ጓደኛ ነበሩ፡፡ መኰንኑም ከሄዱበት ሲመለሱ ሚስታቸው ከአሽከሯ አርግዛ ጠበቀቻቸው፡፡ ‹‹ከማን አረገዝሽ?›› ብለው ጽኑ ግርፋት ቢገርፏት ዋሽታ ‹‹ያረገዝኩት ከንስሓ አባቴ ነው›› አለች፡፡ መኰንኑም መነኩሴውን እገላለሁ ብሎ ሲነሣ መነኩሴውም ወደ አቡነ አላኒቆስ ሄደው አለቀሱ፡፡ አቡነ አላኒቆስም የመኰንኑን ሚስት ቢጠይቋት ባሏን ፈርታ ‹‹አዎ ከመነኩሴው አባት ነው ያረገዝኩት›› አለች፡፡ እሳቸውም ‹‹የተረገዘው ከዚህ መነኩሴ ከሆነ በሰላም ይወለድ፣ ካልሆነ ግን አይወለድ›› ብለው በቃላቸው አስረውና ገዝተው ሸኟቸው፡፡
በግዝታቸው መሠረት ሴቲቱ ድፍን 22 ዓመት ሙሉ ሳትወልድ በጭንቅና በጣር ኖረች፡፡ በአልጋ ላይ ሆና ተጨንቃ ስትኖር በመጨረሻ ለቤተሰቦቿ ተናግራ ወደ አቡነ አላኒቆስ ዘንድ በቃሬዛ ወሰዷትና ይቅርታ ጠይቃ እውነቱን ተናገረች፡፡ እሳቸውም ‹‹እግዚአብሔር ይፍታሽ›› ቢሏት 22 ዓመት ሙሉ ተረግዞ የነበረው ልጅ ትልቅ ሰው ሆኖ ጥርስ አውጥቶ፣ ፂም አብቅሎ በሰላም ተወለደ፡፡ እርሱም ከተወለደ በኋላ አባቱ ማን እንደሆነ ተናገረ፡፡ ጻድቁ አባታችንም ልጁን አሳድገውት አስተምረው አመንኩሰውታል፡፡ ስሙንም ተወልደ መድኅን አሉት፡፡ በስሙ የተሠሰራ ቤተ ክርስቲያን በትግራይ ጽንብላ ወረዳ ይገኛል፡፡

ጻድቁ አቡነ አላኒቆስ ሌላም የሚታወቁበት አንድ ግብር አላቸው፡፡ የማይበራዝዮ ገዳማቸው አገልጋይ የሆነው መነኩሴ በሬ ጠምዶ ሲያርሱ አንበሳ ከጫካው ወጥቶ አንዱን በሬ በላው፡፡ መነኩሴውም መጥተው ለአቡነ አላኒቆስ ነገሯቸው፡፡ እሳቸውም ‹‹ጸሎቴን እስክጨርስ ድረስ ወደ ጫካው ሂድና አንበሳውን ‹አላኒቆስ ባለህበት ጠብቀኝ እንዳትንቀሳቀስ ብሎሃል› ብለህ ተናገር›› ብለው ለመነኩሴው ነገሯቸው፡፡

መነኩሴውም እንደታዘዙት ወደ ጫካው ሄደው ጮኸው በሉ የተባሉትን ተናገሩ፡፡ አቡነ አላኒቆስም ጸሎታቸውን ሲጨርሱ ወደ ጫካው ሄደው አንበሳውን የበላውን በሬ አስተፍተውት በሬውን ነፍስ ዘርተውበት ከሞት አስነሥተው ዕለቱን እንዲታረስ አድርገውታል፡፡ አንበሳውንም ገዝተው ወደ ገዳማቸው ወስደው ሰባት ዓመት ውኃ እያስቀዱት እንዲያገለግላቸው አድርገውታል፡፡

አቡነ አላኒቆስ አንበሳውን አስረው ያሳድሩበት የነበረው ዛፍና ውኃ ያጠጡበት የነበረው ትልቅ የድንጋይ ገበታ ዛሬም ድረስ በገዳሙ ይገኛል፡፡ ከ22 ዓመት እርግዝና በኋላ ሴቲቱ ጥርስና ፂም ያለው ልጅ እንድትወልድ ያደረጉበት ትልቅ ጠፍጣፋ ድንጋይም ከነቅርጹ በገዳሙ በግልጽ ይታያል፡፡ ጻድቁ ጥቅምት 21 ቀን ዐርፈው በዚያው በማይባራዝዮ ገዳማቸው ተቀብረዋል፡፡
የአቡነ አላኒቆስ ረድኤት በረከታቸው ይደርብን፣ በጸሎታቸው ይማረን!

(ከነገረ ቅዱሳን አገልግሎታችን ውስጥ አንዱ ከዚኽ በፊት ያልታተሙ አዳዲስ ገድላትን ለገዳማት በማሳተም ሕዝበ ክርስቲያኑም በነፍስ በሥጋ እንዲጠቀም ለማድረግ የአቅማችንን ሞክረናል። አሁንም እግዚአብሔር ፈቅዶ የአቡነ አላኒቆስንና
በዐፄ ሱስንዮስ ዘመን የነበረውን የቤተ ክርስቲያንን ጥፋት ላለማየት ሳይወለዱ በእናታቸው ማሕፀን 7 ዓመት ከ6 ወር የቆዩትን የአቡነ አብራኒዮስን ገድል የሁለቱን ቅዱሳን ገድል ብዛት 3ሺህ ኮፒ አሳትመን ለገዳሙ ስናስረክብ እጅግ ደስታ ይሰማናል። የገዳሙ አበ ምኔት ዛሬ መጥተው መጽሐፉን ማተሚያ ቤት ሔደው አይተው በእጅጉ ተደስተው መልእክታቸውን አስተላልፈዋል። ወቅቱ ማሕሌተ ጽጌ የሚቆምበት ስለሆነ ዛሬ ማታ እንደከዚኽ በፊቱ በቀጥታ ስርጭት (live) አባን ለማቅረብ ባንችልም መልእክታቸውን ቀድተን በጻድቁ የዕረፍት በዓል ቀን ጥቅምት 21 የምናስተላልፍላችሁ ይሆናል። በዕለቱ ሙሉ ታሪካቸውንና ተኣምራታቸውን በንባብ የምናቀርብ ይሆናል። እንድሁም ከጻድቁ ከበዓለ ዕረፍታቸው ከጥቅምት 21 በኋላ አ.አ ላይ ገድሉ የሚሸጥበትን ቦታና ሌሎች ተያያዥ ጉዳዮችን እንገጥላችኋለን።)

በድጋሚ የአቡነ አላኒቆስ ረድኤት በረከታቸው ይደርብን፣ በጸሎታቸው ይማረን!

በእንተ ቅዱሳን ኅሩያን (ከገድላት አንደበት)

26 Oct, 18:51


መልክዐ ቅዱስ እስጢፋኖስ ካልእ (ዘአኅተሞ ገብረ ሥላሴ)

በእንተ ቅዱሳን ኅሩያን (ከገድላት አንደበት)

26 Oct, 18:50


ግራኝን ከእነ ሰራዊቱ ያሳደደው የቅዱስ እስጢፋኖስ ሰራዊት!

ግራኝ የተባለው አሕዛባዊ ዓመፀኛ በተነሣና በክርስቲያኖች ላይ ጦርነትን በዐወጀ ጊዜ በየአውራጃውና በየመንደሩ ፍጅትና ሁከት ሆነ።

ግራኝም የረከሰች ሃይማኖታቸውን ያልተቀበለውን ኹሉ እንዲገድሉ ለሰራዊቱም ኹሉ ትእዛዝ ሰጠ። ብዙዎች ክርስቲያኖችም በግፍ በጭካኔ በሰይፍ ተገደሉ። በእሳትም የተቃጠሉ አሉ፤ በመጋዝ የተሰነጠቁ አለ፤ ወደጥልቅ ጉድጓድ ተጥለው የሞቱ አሉ፤ ከየመንደራቸውም ወጥተው ወደተራራዎችና ዋሻዎች የተሰደዱ አሉ። ጠንበላ በምትባል የቅዱስ እስጢፋኖስ ቤተ ክርስቲያን ባለችበት አውራጃም የግራኝ ሰራዊቶች ደርሰው ይኽችን የጠንበላን አውራጃ ከበቧት። የሀገሪቱም ሰዎች ወደ ቅዱስ እስጢፋኖስ ቤተ ክርስቲያን ገብተው ሰማዕቱን ይማጸኑት ጀመር። የግራኝም የወታደሮች አለቃ ለመሸመቅ አስቦ ወደ አንድ ዋሻ ሲገባ ዋሻው በተአምር ተደርምሶ ገደለው፣ በውስጡም ቀበረው። ርጉም ግራኝም እሳት ይዞ ጠንበላ አውራጃ የምትገኘውን የቅዱስ እስጢፋኖስን ቤተ ክርስቲያን ሊያቃጥላት ቀረበ። ነገር ግን ቅዱስ እስጢፋኖስ ቤቱን እንዲያቃጥል አልፈቀደለትምና ሊያቃጥላት አልቻለም። ይልቁንም በቅዱስ እስጢፋኖስ ትእዛዝ በቤተ ክርስቲያኑ ጠፈር ላይ የነበሩ ንቦች ተነሥተው ከነሰራዊቱ እስከሩቅ አውራጃ ድረስ አሳደዱት። ግራኝም ከነሰራዊቱ በፍርሃትና በመንቀጥቀጥ ፈጥኖ ሸሸ። የጠንበላ ሀገር ሰዎችም ከግራኝ ያዳናቸውን የቅዱስ እስጢፋኖስን አምላክ ልዑል እግዚአብሔርን አመሰገኑ።

ሊቀ ዲያቆናት ቀዳሜ ሰማዕት ቅዱስ እስጢፋኖስ ከዘመኑ ግራኞች ሀገራችንን ይታደግልን።
✞ ✞ ✞

ዳግመኛም ሊቀ ዲያቆናት ቀዳሜ ሰማዕት ቅዱስ እስጢፋኖስ በአንድ አሕዛብ ላይ ያደረገው ተኣምር ይኽ ነው፡- ከዕለታት በአንደኛው ቀን ከአሕዛብ ወገን የኾነ አንድ ሰው "የክርስቲያኖች አምላካቸው ምን ያደርገኛል?" ብሎ ታበየ። "ክርስቲያኖች ወደሚያምኑበት የጠበል ሥፍራ ብገባስ መግባቴን ያውቅ ዘንድ ማን ይቻለዋል?" ብሎ እግዚአብሔርን ተፈታተነ። ይኽንንም ብሎ ክርስቲያን መስሎ ወደ ቀዳሜ ሰማዕት ቅዱስ እስጢፋኖስ መካነ ጠበል በድፍረት ገባ።

ይኽም ደፋር አሕዛብ ወደ ጠበሉ በድፍረትና በመታበይ በገባ ጊዜ ሊቀ ዲያቆናት ቅዱስ እስጢፋኖስ ተገልጦ ይዞ ያንፈራግጠው ወደታችና ወደላይ ያንከባልለው ጀመር። ያም ሰው በታላቅ ቃል "የክርስቲያኖች ወዳጅ ቅዱስ እስጢፋኖስ ሆይ! እባክህ እዘንልኝ፣ እንደዚህ መድፈርን አልደግምም፣ በአምላክህ እግዚአብሔር ስም እምላለሁ። ከእንግዲህም ክርስቲያን እሆን ዘንድ እጠመቃለሁ...." እያለ ጮኸ። በዚያ የነበሩ ካህናትም ይነግራቸው ዘንድ ሲጠይቁት እርሱም አንድ ቀይ ሰው ተገልጦ በምድር ላይ ጥሎ እንደገሠፀውና እንደቀጣው ከነገራቸው በኋላ "ከእንግዲህስ ሳልጠመቅ ያሳለፍኩት ያለፈው ዘመኔ ይበቃኛል" አላቸው። እንዲያጠምቁትም ጠየቃቸው። እነርሱም አስተምረው በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም አጠመቁት። እርሱም ጽኑ ክርስቲያን ኾኖ ቀዳሜ ሰማዕት ቅዱስ እስጢፋኖስን ቤተ ክርስቲያንን የሚያገለግል ሆነ።

የሊቀ ዲያቆናት የቀዳሜ ሰማዕት የቅዱስ እስጢፋኖስ ረድኤት በረከቱ ይደርብን፣ በጸሎቱ ይማረን።

(ምንጭ፦ ሞረትና ጅሩ ወረዳ የሚገኘው ጠንበላ ቅዱስ እስጢፋኖስ ቤተ ክርስቲያን ያሳተመው ገድለ ቅዱስ እስጢፋኖስ)
✞ ✞ ✞

(ፎቶው፦ የመስከረም 15 ቀን 2015 ዓ.ም የፍልሠተ ዐፅሙ ክብረ በዓል በታላቁ ሐይቅ ቅዱስ እስጢፋኖስ ገዳም ሲከበር የሚያሳይ ነው።
+ + +

ተአምር ከእግዚአብሔርና ከሰይጣን ሲሆን ልዩነቱ !
ይኸውም የቀዳሜ ሰማዕት የቅዱስ እስጢፋኖስ ተአምርና በሬውን በጆሮው እፍ ብሎ ቢተነፍስበት በምትሃት ለሁለት የሰነጠቀውና በተአምር ወደ አየር የበረረው የጠንቋዩ ናኦስ ተአምር ነው።
ቀዳሜ ሰማዕት ሊቀ ዲያቆናት ቅዱስ እስጢፋኖስ በአህዛብ ፊት ያደረጋቸው ተአምራት እጅግ ድንቅ ናቸው፡፡ ቅዱስ እስጢፋኖስ በአህዛብ መካከል ቆሞ ሲያስተምር ከቆየ በኋላ አንድ አንደበቱ ዲዳ የሆነ ሰው አጠገቡ ቢመጣ በጆሮው የሕይወት እስትንፋስ እፍ ቢልበት መስማት የማይችለው መስማት ቻለ፡፡ በዚህም ጣኦት አምላኪው ናኦስ እና ተከታዮቹ ሁሉ ወደ ቅዱስ እስጢፋኖስ ተመለሱ፡፡ ጣኦት አምላኪው ናኦስ በድርጊቱ በጣም ከመናደዱ የተነሣ በአጠገቡ የቆመውን በሬ ጠንቋዩ ናኦስ በጆሮው እፍ ብሎ ቢተነፍስበት በሬው በምትሃት ለሁለት ተሰንጥቆ በመሞቱ ወደ ቅዱስ እስጢፋኖስ የተመለሱት በናኦስ ምትሃታዊ ድርጊት በመሳባቸው እንደገና ወደ ናኦስ ተመለሱ፡፡
ቅዱስ እስጢፋኖስም በዚህ ጊዜ የአህዛብ ልቡና ወላዋይ እንዳይሆንና እንዳይጠፉም በማሰብ ናኦስ እፍ ብሎ ለሁለት ሰንጥቆ የገደለውን በሬ መልሶ በሕይወት እንዲያስነሣው ናኦስን ጠየቀው፡፡ ነገር ግን ናኦስ ያንን ማድረግ አልቻለም፡፡ ከዚህም በኋላ ቅዱስ እስጢፋኖስ ‹‹ናኦስ ዳግመኛ ሕይወት ዘርቶ ማስነሣት ካልቻለ እኔ ነገሩ ሀሰተኛ ነው ማለት ነው፣ እኔ ግን በእግዚአብሔር ኃይልና ድንቅ ሥራ ይህን ለሁለት ተሰንጥቆ የሞተውን በሬ ዳግመኛ ሕይወት ዘርቶ እንዲነሣ አደርገዋለሁ›› በማለት ወደ እግዚአብሔር ከጸለየ በኋላ በሬውን አስነሣው፡፡ ይህንንም ተአምር አድርጎ በማስተማር ልቦናቸው ተጠራጥሮ ወደ ናኦስ የተመለሱትን አህዛብ ገንዘቡ እንዲሆኑ በእግዚአብሔር ኃይልነት እንዲያምኑ አድርጓል፡፡ ናኦስ በአልሸነፍ ባይነትና በአጋንንት ረዳትነት ራሱን ወደ ላይ እንዲንሣፈፍ አድርጎ በአየር ላይ ቢወጣ ቅዱስ እስጢፋኖስ የእግዚአብሔርን ተአምር በማሳየት በትዕግስት ጠብቆ በአጋንንት ረዳትነት ወደ ላይ የተነሳውን ናኦስ በትምዕርተ መስቀል ቢያማትብበት ይዘውት የነበሩት አጋንንት ሁሉ ለቀውት ሲበተኑ ናኦስም ምድር ደርሶ ተንኮታኩቶ በመውደቁና ክፉ አሟሟት በመሞቱ በጣኦት አምላኪነት የነበሩ ሁሉ ዳግም ወደ ቅዱስ እስጢፋኖስ ተመልሰዋል፡፡

ዛሬ ድረስ ተአምር በሚመስል ከንቱ ማታለል ሕዝቡን ከቤተክርስቲያን የሚለዩ በግብር ናኦስን የሚመስሉ በርካታ ሐሳውያን ተአምር ማድረግ የሚችሉ በመምሰል፣ መልእክት ከእግዚአብሔር ወይም ከእመቤታችን የመጣላቸው በማስመሰል፣ እውቀት ከማጣት የተነሣ የጠፋውን ብዙውን መንጋ ምእመን በፈውስና በጥምቀት ስም ወደ ሞት ይነዱታል!

ከቀዳሜ ሰማዕት ሊቀ ዲያቆናት ከቅዱስ እስጢፋኖስ ከበዓለ ዕረፍቱ በረከት ይክፈለን!

በእንተ ቅዱሳን ኅሩያን (ከገድላት አንደበት)

26 Oct, 18:50


አንድ አምላክ በሚሆን በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም አሜን
ጥቅምት 17-ቀዳሜ ሰማዕት ቅዱስ እስጢፋኖስ የተሾመበት ዓመታዊ በዓሉ ነው፡፡
+ ቅዱስ ፊልያስ በሰማዕትነት ዐረፈ፡፡
+ አቡነ ዲዮስቆሮስ 2ኛ በዓለ ዕረፍታቸው ነው፡፡
+ የነቢዩ ሳሙኤል እናት ቅድስት ሐና ልደቷ ነው፡፡
+ የቅዱስ ባስልዮስ ወንድም ቅዱስ ጎርጎርዮስ የዕረፍቱ መታሰቢያ ነው፡፡
ሰማዕቱ ቅዱስ ፊልያስ፡- እኚህም ቅዱስ የሀገረ ቀምስ ኤጲስቆጶስ ናቸው፡፡ በዘመናቸው ቍልቍልያኖስ የተባለ ከሃዲ መኮንን ነበረና አባታችንን ወደ ፍርድ አደባባይ አቀረባቸውና ‹‹ለአማልክቶቼ ሠዋ›› አላቸው፡፡ አቡነ ፊልያስም ‹‹እኔ ሰማይንና ምድርን ፈጥሮ ለሚገዛ ለልዑል እግዚአብሔር ብቻ ነው የምሠዋው›› አሉት፡፡ መኮንኑ ቍልቍልያኖስም ‹‹እግዚአብሔር ምን ዓይነት መሥዋዕት ይሻል?›› አላቸው፡፡ አባታችንም ‹‹ቅን ትሑት የሆነ ንጹሕ ልቡናን፣ ዕውነተኛ ፍርድን፣ ቁም ነገርንና እንዲህ የመሰለውን መሥዋዕት እግዚአብሔር ይወዳል›› አሉት፡፡
ቍልቍልያኖስም አቡነ ፊልያስን ‹‹የምትጋደለው ስለ ነፍስህ ነው ወይስ ስለ ሥጋህ?›› ሲላቸው ‹‹ስለ ነፍስና ስለ ሥጋ ነው፣ እነርሱ በአንድነት ይነሣሉና›› አሉት፡፡ ከዚህም በኋላ ቍልቍልያኖስ ‹‹የምትወዳት ሚስትና የምትወዳቸው ልጆች ወይም ዘመድ አለህን?›› አላቸው፡፡ አቡነ ፊልያስም ‹‹ከሁሉም የእግዚአብሔር ፍቅር ይበልጣል›› አሉት፡፡ ከሃዲውም መኮንን ‹‹እግዚአብሔር ከበጎ ሥራ የሠራው ምንድነው?›› አላቸው፡፡ አቡነ ፊልያስም እንዲህ አሉት፡- ‹‹እግዚአብሔር ያደረገልን ይህ ነው፡- ሰማይንን ምድርን በውስጣቸው ያሉትን ሁሉ ፈጠረልን፡፡ ዳግመኛም ከጠላታችን ከሰይጣን እጅ ያድነን ዘንድ ከሰማያት ወርዶ ከቅድስት ድንግል ማርያም ሰው ሆኖ ተወለደ፤ የሕይወትንም መንገድ በዓለም ውስጥ ተመላልሶ አስተማረ፣ መከራንም በሥጋው ተቀብሎ ተሰቅሎ ሞተ፣ በሦስተኛውም ቀን ከሞት ተነሥቶ በ40 ቀን ወደ ሰማይ ዐረገ፣ ዳግመኛም ለፍርድ ይመጣል፡፡ ይህንንም ሁሉ ስለእኛ አደረገ›› አሉት፡፡ ቍልቍልያኖስም ይህን በሰማ ጊዜ ‹‹አምላክ ይሰቀላልን?›› ብሎ ጠየቃቸው፡፡ አባታችንም ‹‹አዎን የዘላለም ሕይወትን ይሰጠን ዘንድ ስለእኛ ፍቅር ሞተ›› አሉት፡፡
ከዚህም በኋላ ከሃዲው መኮንን ቍልቍልያኖስ አባታችንን ‹‹አንተ የከበርክ እንደሆንህ ዐውቃለሁና እኔ እንዳከበርኩህ ልጣላህም እንዳልፈለግሁ ዕወቅ፡፡ አሁን ለአማለክቶቼ ሠዋ፣ እምቢ ካልክ ግን በክፉ አሟሟት ትሞታለህ›› አላቸው፡፡ አቡነ ፊልያስም ‹‹እኔንስ ደስ ማሰኘት ከወደድህ እንዲያሠቃዩኝና እንዲገድሉኝ እዘዝ›› አሉት፡፡ ቍልቍልያኖስም በዚህ ንግግራቸው በጣም ተቆጥቶ የአባታችንን ራሳቸውን በሰይፍ ይቆርጧቸው ዘንድ አዘዘ፡፡
አባታችንንም ሊገድሏቸው ሲወስዷቸው ዘመዶቻቸውና የሀገሩ ታላላቅ ወገኖች ወደ እርሳቸው መጥተው ለመኮንኑ በመታዘዝ ለአማልክቶቹ እንዲሠው አባታችንን እጃቸውንና እግራቸውን እየሳሙ ለመኗቸው፡፡ አባታችንም ይህን ጊዜ ‹‹የጌታዬን የኢየሱስ ክርስቶስን መከራ መስቀል ልሸከም እሄዳለሁና እናንተ አሳሳቾች ከእኔ ወግዱ›› ብለው ገሠጹዋቸው፡፡ ከመገደያቸውም ቦታ በደረሱ ጊዜ ፊታቸውን ወደ ምሥራቅ መልሰው በመጸለይ ምእመናንንም ለጌታችንን በአደራ አስጠብቀውና ተሰናብተዋቸው አንገታቸውን ለሰያፊዎቹ አሳልፈው ሰጧቸው፡፡ ሰያፊዎቹም የአባታችንን ራስ ቆረጡትና የሰማዕትነትን አክሊልን ተቀዳጁ፡፡
የቅዱስ ፊልያስ ረድኤት በረከቱ ይደርብን፣ በጸሎቱ ይማረን!
+ + +
ቅዱስ ዲዮስቆሮስ 2ኛ፡- ይህም ቅዱስ አባት በዘመኑ ካሉ ትውልድ እርሱን የሚመስል ያልተገኘ በጠባዩ ቅን፣ የዋሕ፣ በዕውቀቱም አስተዋይ በበጎ ሥራው ሁሉ ፍጹም የሆነ ነው፡፡ በመንፈስ ቅዱስ ፈቃድ 31ኛው የእስክንድርያ ሊቀ ጳጳሳት ሆኖ በማርቆስ መንበር ላይ ተሾመ፡፡ ከሹመቱም በኋላ መልእክትን ጽፎ ለአንጾኪያው ሊቀ ጳጳሳት ለአቡነ ሳዊሮስ ላከለት፡፡ መልአክቱም ስለ ሥሉስ ቅዱስ አንድነትና ሦስትነት የሚያስረዳ ነው፡፡ እንዲሁም ስለ ምሥጢረ ሥጋዌና ስለ እመቤታችን ንጽሕና ጽፎ ለአቡነ ሳዊሮስ ላከለት፡፡ አቡነ ሳዊሮስም መልእክቱን ተቀብሎ ባነበባት ጊዜ ፈጽሞ ደስ ተሰኘባትና ለአንጾኪያ ሕዝቦች አስተማረባት፡፡ ሁሉም በዚህ ደስ አላቸው፡፡
አቡነ ሳዊሮስም በመልሱ መልእክት ጻፈለትና ‹‹በኒቅያ ከተማ ተሰብስበው ሃይማኖታቸው የቀና 318 ቅዱሳን አባቶቻችን በቀናች ሃይማኖት አጽንተው የሠሯትን ቤተ ክርስቲያን እንድትጠብቅ ለዚህች ለከበረች አገልግሎት የመረጠህ እግዚአብሔርን አመሰግነዋለሁ›› በማለት በሃይማኖት እስከመጨረሻው ጸንቶ ምእመናንንም እንዲያጸና አስገነዘበው፡፡ ብዙ ድርሳናትንም ጨምሮ ላከለት፡፡ አቡነ ዲዮስቆሮስ ሁለተኛም መልአክቱን ተቀብሎ ለሕዝቡ አስተማረባት፡፡ ሁልጊዜም ቅዱሳት መጻሕፍትን በማስተማር ምእመናንን በሃይማኖት እንዲጸኑ በማስተማር ብዙ ካገለገለ በኋላ መልካም አገልግሎቱን ፈጽሞ በሰላም ዐረፈ፡፡ረድኤት በረከቱ ይደርብን፣ በጸሎቱ ይማረን!
+ + +
ዳግመኛም ይህች ዕለት ቀዳሜ ሰማዕት ቅዱስ እስጢፋኖስ የተሾመባት ዕለት ናት፡፡ እስጢፋኖስ ማለት ‹‹መደብ›› ማለት ሲሆን በግሪክ ቋንቋ ‹‹አክሊል›› ማለት ነው፡፡ በግብሩ የቀን ሃሩር የሌሊት ቁር የማይለውጠው፣ መብራት ማለት ነው፡፡ ትውልዱ ከነገደ ብንያም ሲሆን አባቱ ስምዖን እናቱ ሐና ይባላሉ፡፡ እነርሱም እግዚአብሔርን ከሚፈሩ ከነቢያትና ከጻድቃን ወገን ናቸው፡፡ በመጀመሪያ ሁለት ወንድ ልጆችን ወለዱ፡፡ አንዱ ይሁዳ ሲባል ሁለተኛውም ቅዱስ እስጢፋኖስ (አስተፓኖስ) ነው፡፡ እስጢፋኖስ የተወለደው ጥር 1 ቀን በእስራኤል ሃገር ውስጥ ልዩ ስሟ ሐኖስ በተባለች ቦት ነው፡፡ የተወለደውም በስለት ነው፡፡ እርሱም ከመጥምቁ ዮሐንስ እግር ሥር በመሆን ተምሯል፡፡ በኋላም ወደ ቅዱሳን ሐዋርያት በመሄድ ይላላካቸውና ያገለግላቸው ነበር፡፡ በኢየሩሳሌም ቤተ ክርስቲያን ከተሾሙት ከ7ቱ ዲያቆናት አንዱ ሲሆን የዲያቆናት አለቃ እርሱ ነው፡፡ ቅዱስ እስጢፋኖስ ወንጌልን በማስተማሩና ብዙዎችን ክርስቶስን ወደማመን ስለመለሳቸው ክፉዎች አይሁድ በጠላልትነት ተነስተውበት ጥር 1 ቀን በ34 ዓ.ም ከጌታችን ቀጥሎ ከምእመናን ወገን የመከራውን ገፈት ስለተቀበለ (በድንጋይ ተወግሮ በሰማዕትነት ስላረፈ) ‹‹ቀዳሜ ሰማዕት›› ተሰኘ፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ ‹‹ሊቀ ዲያቆናት ቅዱስ እስጢፋኖስ›› እየተባለ ይጠራል፡፡ ይኸውም የከበሩ ቅዱሳን ሐዋርያት በሰባቱ ዲያቆናት ላይ አለቃ አድርገው በሾሙት ጊዜ የተሰጠው ስያሜ ነው፡፡
የመጀመሪያ ክርስቲያኖች የአማኞች ቊጥር በከፍተኛ ሁኔታ እየጨመረ በሄደ ጊዜ የማኅበራዊው ኑሮ አስተዳደር ማለትም የምግብንና የመሳሰሉትን ቁሳቁሶች (ገንዘብም ጭምሮ) በትክክልና በእኩልነት የማከፋፈሉ ሥራ በሐዋርያት ዘንድ አስቸጋሪ ሆኖ ተገኘ፡፡ እነርሱም ደግሞ ዋና ተግባር አድርገው በትጋት ለመያዝ የፈለጉት ማስተማርን ነበር፡፡ ስለዚህም አማኞችን ሁሉ ሰብስበው ከመካከላቸው በመልካም ጠባያቸው የተመሰገኑ በመንፈስ ቅዱስና በጥበብ የተሞሉ ሰባት ሰዎችን እንዲመርጡ አሳስቧቸው፡፡ አማኞችንም ነገሩ አስደስቷቸው ሰባት ሰዎችን መረጡ፡፡ እነርሱም፡- ቅዱስ እስጢፋኖስ (ዕረፍቱ ጥር 1)፣ ቅዱስ ጵሮኮሮስ (ሰኔ 8)፣ ቅዱስ ጢሞና (ሚያዝያ 16)፣ ቅዱስ ፊልጶስ (ጥቅምት 14)፣ ቅዱስ ጰርሜና (መስከረም 1)፣ ቅዱስ ኒቃሮና (3 ጊዜ ሞቶ የተነሣ)፣ ቅዱስ ኒቆላዎስ (ሚያዝያ 15) ናቸው፡፡ ሐዋ 6፡5፡፡

በእንተ ቅዱሳን ኅሩያን (ከገድላት አንደበት)

26 Oct, 18:50


እነዚህንም ቅዱሳን በከበሩ ሐዋርያት ፊት ባቆሟአቸው ጊዜ ጸልየው እጃቸውን በራሳቸው ላይ ጭነው ሾሟቸው፡፡ በከበሩ ሐዋርያት ጫንቃ ላይ ተጭኖ የነበረው ከባድ ሸክም ባሎቻቸው የሞቱባቸውን ሴቶችና ወላጆቻቸው የሞቱባቸውን ደሀ አደጎች በመርዳት ችግሮቻቸውን አቃለሉላቸው፡፡ በከበሩ ሐዋርያት ከተመረጡት ሰባቱ ዲያቆናት መካከል ሊቀ ዲያቆናት ተደረጎ የተመረጠው ቅዱስ እስጢፋኖስ ሲሆን ሌሎቹም ዲያቆናት እስከ ሕይወታቸው ፍጻሜ ወንጌልን በማስተማርና የመጀመሪያ ክርስቲያኖች በማስተዳደር በጽናት ተጋድለዋል፡፡
እነዚህም ሰባቱ ዲያቆናት ከአባቶቻቸው ከከበሩ ሐዋርያት አይተው የእነርሱንም መንፈስ ተቀብለው ያልተማሩ አህዛብን ልቡናቸውን ለመስበርና የእግዚአብሔርን ኃይልነት ተረድተው እንዲገነዘቡ በማሰብ ብዙ ድንቅ ድንቅ ተአምራትን ያደርጉ ነበር፡፡ ከእነርሱም ውስጥ በዋነኛነት ቅዱስ እስጢፋኖስ በአህዛብ ፊት ያደረጋቸው ተአምራት እጅግ ድንቅ ናቸው፡፡ ቅዱስ እስጢፋኖስ በአህዛብ መካከል ቆሞ ሲያስተምር ከቆየ በኋላ አንድ አንደበቱ ዲዳ የሆነ ሰው አጠገቡ ቢመጣ በጆሮው የሕይወት እስትንፋስ እፍ ቢልበት መስማት የማይችለው መስማት ቻለ፡፡ በዚህም ጣኦት አምላኪው ናኦስ እና ተከታዮቹ ሁሉ ወደ ቅዱስ እስጢፋኖስ ተመለሱ፡፡ ጣኦት አምላኪው ናኦስ በድርጊቱ በጣም ከመናደዱ የተነሣ በአጠገቡ የቆመውን በሬ ጠንቋዩ ናኦስ በጆሮው እፍ ብሎ ቢተነፍስበት በሬው በምትሃት ለሁለት ተሰንጥቆ በመሞቱ ወደ ቅዱስ እስጢፋኖስ የተመለሱት በናኦስ ምትሃታዊ ድርጊት በመሳባቸው እንደገና ወደ ናኦስ ተመለሱ፡፡
ቅዱስ እስጢፋኖስም በዚህ ጊዜ የአህዛብ ልቡና ወላዋይ እንዳይሆንና እንዳይጠፉም በማሰብ ናኦስ እፍ ብሎ ለሁለት ሰንጥቆ የገደለውን በሬ መልሶ በሕይወት እንዲያስነሣው ናኦስን ጠየቀው፡፡ ነገር ግን ናኦስ ያንን ማድረግ አልቻለም፡፡ ከዚህም በኋላ ቅዱስ እስጢፋኖስ ‹‹ናኦስ ዳግመኛ ሕይወት ዘርቶ ማስነሣት ካልቻለ እኔ ነገሩ ሀሰተኛ ነው ማለት ነው፣ እኔ ግን በእግዚአብሔር ኃይልና ድንቅ ሥራ ይህን ለሁለት ተሰንጥቆ የሞተውን በሬ ዳግመኛ ሕይወት ዘርቶ እንዲነሣ አደርገዋለሁ›› በማለት ወደ እግዚአብሔር ከጸለየ በኋላ በሬውን አስነሣው፡፡ ይህንንም ተአምር አድርጎ በማስተማር ልቦናቸው ወላውሎ ወደ ናኦስ የተመለሱትን አህዛብ ገንዘቡ እንዲሆኑ በእግዚአብሔር ኃይልነት እንዲያምኑ አድርጓል፡፡ ናኦስ በአልሸነፍ ባይነትና በአጋንንት ረዳትነት ራሱን ወደ ላይ እንዲንሣፈፍ አድርጎ በአየር ላይ ቢወጣ ቅዱስ እስጢፋኖስ የእግዚአብሔርን ተአምር በማሳየት በትዕግስት ጠብቆ በአጋንንት ረዳትነት ወደ ላይ የተነሳውን ናኦስ በትምዕርተ መስቀል ቢያማትብበት ይዘውት የነበሩት አጋንንት ሁሉ ለቀውት ሲበተኑ ናኦስም ምድር ደርሶ ተንኮታኩቶ በመውደቁ በጣኦት አምላኪነት የነበሩ ሁሉ ዳግም ወደ ቅዱስ እስጢፋኖስ ተመልሰዋል፡፡
የሰማዕታት መጀመሪያ የሆነው ቅዱስ እስጢፋኖስ በትምህርቱና በተአምራቱ ብዙዎችን ወደቀናች ሃይማኖት ስለመለሰ ክፉዎች አይሁድ ቀኑበትና የሐሰት ምስክር አዘጋጁበት፡፡ ‹‹በእግዚአብሔርና በሙሴ ላይ የስድብን ቃል ሲናገር ሰምተነዋል›› ብለው በሐሰት ከሰሱትና በሸንጎአቸው አቆሙት፡፡ ቀዳሜ ሰማዕት ቅዱስ እስጢፋኖስም ከአብርሃም ጀምሮ እስከ ጌታችን ያለውን ሁሉንም እየጠቀሰ የሃይማኖትን ነገር አስተማራቸው፡፡ ነቢያትን ስለማሳደዳቸውና ስለመግደላቸው እየወቀሰ ሲናገራቸው በትምህርቱ ተናደው ጆሮአቸውን ይዘው በመጮህ በድንጋይ ወግረው ይገድሉት ዘንድ እየጎተቱ ከከተማው ውጭ አወጡት፡፡ ቅዱሱም በድንጋይ ወግረው ሲገድሉት ከጌታችን የተማረውን ‹‹አባት ሆይ የሚያደርጉትን አያውቁምና ይህን ኃጢአት አትቁጠርባቸው›› እያለ ስለገዳዮቹ ምሕረትን ይለምን ነበር፡፡ ሰማይም ተከፍቶ የእግዚአብሔርን ክብር ተመለከተ፡፡
ቅዱስ ጳውሎስ ይኸውም የቀድሞው ሳውል ቅዱስ እስጢፋኖስን በድንጋይ ሲወግሩት የገዳዮቹን ልብስ ይጠብቅና ድንጋይ ያቀብል ነበር፡፡ ‹‹የሰማዕትህንም የእስጢፋኖስን ደም ባፈሰሱ ጊዜ፥ ራሴ ደግሞ በአጠገባቸው ስቆም ተስማምቼ የገዳዮችን ልብስ እጠብቅ ነበር አልሁ›› ብሎ ራሱ ቅዱስ ጳውሎስ መስክሯል፡፡ ሐዋ 22፡20፡፡ የቅዱስ እስጢፋኖስ መምህር የነበረው ምሑረ ኦሪቱ ገማልያልና ልጁ አቢብ በእስጢፋኖስ ትምህርትና የሞቱ ሰዎች የሰጡትን ምስክርነት አይተው ከይሁዲነት ተመልሰው በክርስቶስ አምነው ተጠምቀዋል፡፡ ስለ ሰማዕቱ ቅዱስ እስጢፋኖስ በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ እንዲህ ተብሎ ነው የተጻፈው፡- ‹‹እስጢፋኖስም ጸጋንና ኃይልን ተሞልቶ በሕዝቡ መካከል ድንቅንና ታላቅ ምልክትን ያደርግ ነበር፡፡ የነፃ ወጪዎች ከተባለችው ምኵራብም ከቀሬናና ከእስክንድርያም ሰዎች ከኪልቅያና ከእስያም ከነበሩት አንዳንዶቹ ተነሥተው እስጢፋኖስን ይከራከሩት ነበር፤ ይናገርበት የነበረውንም ጥበብና መንፈስ ይቃወሙ ዘንድ አልቻሉም፡፡ በዚያን ጊዜ በሙሴ ላይ በእግዚአብሔርም ላይ የስድብን ነገር ሲናገር ሰምተነዋል የሚሉ ሰዎችን አስነሡ፡፡ ቀርበውም ያዙት ወደ ሸንጎም አመጡትና ‹ይህ ሰው በዚህ በተቀደሰው ስፍራ በሕግም ላይ የስድብን ነገር ለመናገር አይተውም፤ ይህ የናዝሬቱ ኢየሱስ ይህን ስፍራ ያፈርሰዋል ሙሴም ያስተላለፈልንን ሥርዓት ይለውጣል ሲል ሰምተነዋልና› የሚሉ የሐሰት ምስክሮችን አቆሙ፡፡ በሸንጎም የተቀመጡት ሁሉ ትኵር ብለው ሲመለከቱት እንደ መልአክ ፊት ሆኖ ፊቱን አዩት፡፡›› 6:8-15፡፡
የአይሁድ በቅዱስ እስጢፋኖስ ላይ ያቀረቡት የክሳቸው ምክንያት ጌታችንን ከከሰሱት ክስ ጋር በሁለት ነጥቦች ይመሳሰላል፡፡ የመጀመሪያው ክሳቸው ‹‹የሙሴን ሕግ ሽሯል›› የሚል ነው፡፡ ‹‹የሙሴን ሕግ በመሻር ኦሪት አትጠቅምም አትመግብም አታድንም፤ ሐዲስ ኪዳን (ወንጌል) ግን ትመግባለች ታድናለች›› ብሏል ብለው ከሰሱት፡፡ ሐዋ 6፡13፡፡ ሁለተኛው ክሳቸው ‹‹እግዚአብሔርንም ይሰድባል›› የሚል ነው፡፡ ሐዋ 7፡50፡፡ አይሁድም የቅዱስ እስጢፋኖስን የወንጌል ቃል ንግግሮች በእግዚአብሔር ላይ እንደተሰነዘሩ ስድቦች በመቁጠር ነበር የወነጀሉት፡፡ የኦሪት የካህናት አለቃውም ቅዱስ እስጢፋኖስ ለተከሰሰበት መልስ ይሰጥ ዘንድ ሲጠይቀው እርሱ ግን ለተከሰሰበት መልስ ከመስጠት ይልቅ ከአብርሃም ጀምሮ እስከ ክርስቶስ ድረስ ያለውን የመጽሐፍ ቅዱስ ጽሑፍ በዝርዝር በሚገባ ተረከላቸው፡፡
ቅዱስ እስጢፋኖስም እንዲህ አላቸው፡- ‹‹ከነቢያትስ አባቶቻችሁ ያላሳደዱት ማን ነው? የጻድቁንም መምጣት አስቀድሞ የተናገሩትን ገደሉአቸው፤ በመላእክት ሥርዓት ሕግን ተቀብላችሁ ያልጠበቃችሁት እናንተም አሁን እርሱን አሳልፋችሁ ሰጣችሁት ገደላችሁትም፡፡ ይህንም በሰሙ ጊዜ በልባቸው በጣም ተቈጡ ጥርሳቸውንም አፋጩበት፡፡ መንፈስ ቅዱስንም ተሞልቶ ወደ ሰማይ ትኵር ብሎ ሲመለከት የእግዚአብሔርን ክብር ኢየሱስንም በእግዚአብሔር ቀኝ ቆሞ አየና፡፡ እነሆ ሰማያት ተከፍተው የሰው ልጅም በእግዚአብሔር ቀኝ ቆሞ አያለሁ አለ፡፡ በታላቅ ድምፅም እየጮኹ ጆሮአቸውን ደፈኑ፣ በአንድ ልብ ሆነውም ወደ እርሱ ሮጡ፤ ከከተማም ወደ ውጭ አውጥተው ወገሩት፡፡ ምስክሮችም ልብሳቸውን ሳውል በሚሉት በአንድ ጎበዝ እግር አጠገብ አኖሩ፡፡ እስጢፋኖስም ‹ጌታ ኢየሱስ ሆይ ነፍሴን ተቀበል› ብሎ ሲጠራ ይወግሩት ነበር፡፡ ተንበርክኮም ‹ጌታ ሆይ ይህን ኃጢአት አትቍጠርባቸው› ብሎ በታላቅ ድምፅ ጮኸ፡፡ ይህንም ብሎ አንቀላፋ፡፡ ሳውልም በእርሱ መገደል ተስማምቶ ነበር፡፡ 7:52-60፡፡ ቅዱስ እስጢፋኖስ ስለንጽሕናው ስለድንግልናው፣ ስለሰማዕትነቱ ስለተጋድሎው እና ስለስብከቱ ስለተአምራቱ ሦስቱ

በእንተ ቅዱሳን ኅሩያን (ከገድላት አንደበት)

26 Oct, 18:50


አክሊላት ተቀዳጅቷል፡፡
ቅዱስ እስጢፋኖስ አምላኩን ክርስቶስን በብዙ ነገር መስሏል፡፡ በመጨረሻዋ የመሞቻው ሰዓት ላይ እንኳን ሆኖ አምላኩን አብነት አድርጎ ተገኝቷል፡፡ ጌታችን ‹‹ነፍሴን ተቀበላት›› እንዳለ ሁሉ ቅዱስ እስጢፋኖስም ‹‹አቤቱ ጌታ ሆይ ነፍሴን ተቀበላት›› ብሏል፡፡ ጌታችን ‹‹አባት ሆይ የሚያደርጉትን አያውቁምና ይቅር በላቸው›› እንዳለ እስጢፋኖስም ‹‹ጌታ ሆይ ይህን ኃጥአት አትቁጠርባቸው የሚያደርጉትን አያውቁምና›› በማለት ለገዳዩቹ ምሕረትን ለምኗል፡፡ በጌታችን ጸሎት እነ ፊያታዊ ዘየማንን ጨምሮ እልፍ ነፍሳት ወደ ንስሐ ተመልሰው ገነት መንግስተ ሰማያትን እንደወረሱ ሁሉ በቅዱስ እስጢፋኖስም ጸሎት ብዙ ነፍሳት ድነው ገነት መንግስተ ሰማያትን ወርሰዋል፡፡ የጌታችን ቅዱስ መስቀል እልፍ ሙታንን ያስነሣ ድውያንን ይፈውስ እንደነበር ሁሉ የቅዱስ እስጢፋኖስም ዐፅም ሙታንን ያስነሣ ድውያንን ይፈውስ ነበር፡፡ ቅዱስ እስጢፋኖስ የተወገረበት ድንጋይ ሰባት አብያተ ክርስቲያናት ታንጸውበታል፡፡
የቅዱስ እስጢፋኖስ ልደቱና ዕረፍቱ ጥር 1 ቀን ነው፡፡ መእመናንም ሥጋውን ወስደው በክብር ቀበሩት፡፡ ጥቅምት 17 የተሾመበት ነው፡፡ መስከረም 15 ቀን ፍልሰተ ሥጋው ነው፡፡ የቅዱስ እስጢፋኖስ ቅዱስ ዐፅሙ ሙትን ያስነሣ ድውይን ይፈውስ ነበርና አይሁድ በቅናት ተነሥተው እንደ ጌታችን ቅዱስ መስቀል የቅዱስ እስጢፋኖስን ዐፅም አርቀው በመቆፈር ቀብረው በላዩም ቆሻሻ በመጣል ለ300 ዓመት ያህል ተቀብሮ ኖሮ በመጨረሻ በፈቃደ እግዚአብሔር እንደ ቅዱስ መስቀሉ ተቆፍሮ በመውጣት መስከረም 15 ቀን ቅዱስ ዐፅሙ ወጥቶ በክብር በስሙ በታነጸው ቤተ ክርስቲያን በክብር ተቀምጧል፡፡ ይኸውም የሆነው እንዲህ ነው፡- ሰማዕቱ ቅዱስ እስጢፋኖስ ካረፈ ከ300 ዓመት በላይ በሆነ ጊዜ ጻድቁ ንጉሥ ቆስጠንጢኖስ ሲነገሥና ሃይማኖትን በመላው ዓለም አቀና፡፡ ተዘግተው የነበሩ ገዳማትና አብያተ ክርስያናት ተከፈቱ፡፡ በዚህም ወቅት የቅዱስ እስጢፋኖስ ሥጋው በሚገኝበት በኢየሩሳሌም አካባቢ ሉክያኖስ ለሚባል ሰው ቅዱስ እስጢፋኖስ በራእይ ተገለጠለትና ‹‹እኔ እስጢፋኖስ ነኝ፣ ሥጋዬ በዚህ ቦታ ተቀብሯል›› በማለት ሥጋውን ያወጡ ዘንድ አዘዘው፡፡ ሉክያኖስም ለኢየሩሳሌሙ ኤጰስ ቆጶስ ሄዶ ነገረውና ወደ ቦታው ሄደው ሲቆፍሩ ታላቅ ንውጽውጽታ ሆነና ሳጥኑ ተገኘ፡፡ ከሳጥኑ እጅግ ደስ የሚል በዓዛ ወጣ፡፡ በዚያ ቦታም ቅዱሳን መላእክት ሲያመሰግኑ ተሰሙ፡፡ ኤጲስ ቆጶሳቱና ካህናቱም የቅዱስ እስጢፋኖስን ሥጋ በክብር በታላቅ ዝማሬ ወስደው አስቀመጡት፡፡
ከዚህም በኋላ እንዲህ ሆነ፡- በኢየሩሳሌም የሚኖር የቁስጥንጥንያ ተወላጅ የሆነ ስሙ እለእስክንድሮስ የሚባል ሰው ነበር፡፡ እርሱም ለቅዱስ እስጢፋኖስ ውብ የሆነች ቤተ ክርስቲያን ሠርቶለት ሥጋውን አፍልሰው በዚያ በክብር አኖሩት፡፡ ከ5 ዓመት በኋላም እለእስክንድሮስ ዐረፈና ሚስቱ በቅዱስ እስጢፋኖስ አስክሬን ጎን ቀበረችው፡፡ ከሌሎች ከ5 ዓመቶችም በኋላ ሚስቱ የባሏን አስክሬን ወደ ቁስጥንጥንያ አገር ይዛ ልትሄድ አስባ ወደ መቃብሩ ስትሄድ የባሏን አስክሬን የወሰደች መስሏት በእግዚአብሔር ፈቃድ የቅዱስ እስጢፋኖስን ሣጥን ወስዳ እስከ አስቃላን ከተማ ድረስ ተሸከመችውና በመርከብ ተሳፍራ ወደ ቁስጥንጥንያ ሄደች፡፡
የእለእስክንድሮስም ሚስት በመርከብ ስትጓዝ ጣዕም ያለው የመላእክትን ዝማሬ ሰማች፡፡ ልታየውም በተነሣች ጊዜ ሣጥኑ የቅዱስ እስጢፋኖስ ሥጋ ያለበት መሆኑን ዐወቀቸ፡፡ ወደ ኢየሩሳሌምም ለመመለስ አልተቻላትም ይልቁንም ይህ እንዲሆን የእግዚአብሔር ፈቃድ መሆኑን ዐውቃ ለዚህ ክብር ስላበቃት አመሰገነች፡፡ ቁስጥንጥንያም እንደደረሰች ለሊቀ ጳጳሱ በእግዚአብሔር ፈቃድ የቅዱስ እስጢፋኖስብ ሥጋ ይዛ እንደመጣች ላከችበት፡፡ ካህናቱና ሕዝቡም ሁሉ በታላቅ ደስታ ወጥተው በክብር ተቀበሏት፡፡ ከሥጋውም ብዙ ተአምራት ተገልጠው ታዩ፡፡ ከዚህም በኋላ ሥጋውን በበቅሎ ጭነው ሲጎትቱ ቁስጣንጢኖስ ከሚባል ቦታ ሲደርሱ የቅዱስ እስጢፋኖስን ሥጋ የያዘችው በቅሎ አልንቀሳቀስ አለች፡፡ እግዚአብሔር የቅዱስ እስጢፋኖስ ሥጋው በዚህ ቦታ እንዲኖር የፈቀደ መሆኑን ዐወቁ፡፡ ሥጋውን የተጫነው በቅሎም በሰው አንደበት ‹‹የቅዱስ እስጢፋኖስን ሥጋ በዚህ ሊያኖሩ ይገባል›› ብሎ ተናገረ፡፡ ይህንንም ያዩና የሰሙ ሁሉ እጅግ አደነቁ፡፡ የበለዓምን አህያ ያናገረ አምላክ አሁንም የቅዱስ እስጢፋኖስን ሥጋ የተሸከመችውን በቅሎ እንዳናገራት ዐውቀው ደስ አላቸው፡፡ የሀገሪቱም ንጉሥ በቦታው ላይ ውብ ቤተ ክርስቲያን ሠርተውለት ሥጋውን በውስጧ በክብር አኖሩ፡፡ ከሥጋውም ብዙ አስገራሚ ተአምራት ተፈጽመው ታዩ፡፡
የቅዱስ እስጢፋኖስ ረድኤት በረከቱ ይደርብን፣ በጸሎቱ ይማረን!

በእንተ ቅዱሳን ኅሩያን (ከገድላት አንደበት)

26 Oct, 03:05


ዛሬ ማታ ላይ የአንድ ትልቅ ገዳም አበ ምኔት ወደ አአ ስለሚመጡ የገድላትን ኅትመት በተመለከ ማታ የምንነግራችሁ ታላቅ የምስራች ይኖረናል።

በእንተ ቅዱሳን ኅሩያን (ከገድላት አንደበት)

25 Oct, 16:32


እንደነበር አባቶች ያስረዳሉ። አሁንም ድረስ ዋርካው በሥፍራው ላይ ሕያው ማስረጃ ሆኖ ይገኛል።

ገዳሙ ከአቡነ ኢያሱ ዕረፍት ከዘመናት በኋላ በግራኝ አህመድ ወረራ ጥቃት ደርሶበት መነኰሳቱም ተበታትነው ለ247 ዓመት ጠፍ ሆኖ ከቆየ በኋላ በ1747 ዓ.ም አቡነ ዮሴፍ የተባሉት ጻድቅ በሊቀ መላእክት በቅዱስ ሚካኤል መሪነት ከአምባሰል ተነሥተው መጥተው ገደሉን ቦርቡረው ቅኔ ማሕሌት፣ ቅድስትና ቅዱሳንን ያሟላ ቤተ መቅደስ በማነጽ ዳግም ገዳሙን በማቅናት የቀደመውን የአባቶችን ታሪክ ማስቀጠል ችለዋል። በግራኝ አህመድ ወረራ ወቅት ቅርሶቹና ነዋየ ቅዱሳቱ አደጋ እንዳይደርስባቸው አባቶች ሰብስበው በስውር ከተቀበሩ ከረጅም ጊዜ በኋላ የቀበሩበት ቦታ ጠፍቶባቸው ነበር ነገር ግን የወንዙ ውኃ አቅጣጫውን ቀይሮ ሽቅብ ፈስሶ ቅርሶቹ ያሉበትን ቦታ አመላክቷል።

መካነ ሱባኤ ወተመስጦ ጀር ቅድስት ሥላሴ አቡነ ኢያሱ ገዳም የበርካታ መናንያን አበው በኣት ከመሆኑም ባሻገር የወንዶች ብቻ ገዳም ሲሆን መናንያኑ ከአራዊት ጋር ተስማምተው የሚኖሩበት ነው። ዙሪያው በገደል የተከበበ ሲሆን ወደ ገዳሙ ለመውረድ የዕንጨት መሰላልን ተጠቅሞ መጓዝ ግድ ይላል። ወደ ገዳሙ መግቢያ የሚያስወርደው መሰላል ደቡብ ወሎ ከሚገኘው ከታላቁ አባ ጊዮርጊስ ዘጋስጫ ገዳም መግቢያ ጋር ይመሳሰላል። የመሰላሉ ርዝመት ከ15 ሜትር በላይ ይሆናል።

ገዳሙ ከእግዚአብሔር ጋር በሱባዔ ለመገናኘት ፍጹም ጸጥታ የሰፈነበት ከመሆኑም በላይ ረድኤተ እግዚአብሔር ያለበት ቅዱስ ቦታ ነው። ዋሻው የሚከፈተው ዐቢይ ጾም ላይ እና በእመቤታችን የፍልሰታ ጾም ወቅት ነው። በዋሻው ውስጥ ሱባዔ የሚያዘው በደረቅ ሽምብራ ቆሎ እና በአንድ ኩባያ በሶ ብቻ ነው። አባቶች በኣት ዘግተው ጾመ ፍልሰታን፣ ጾመ ነቢያትን፣ ጾመ ሐዋሪያትን በይበልጥ በምነና ሕይወት የሚያሳልፉበት የበረከት ገዳም ነው።

በጀር ሥላሴ የሚገኘው ታሪካዊ ታላቅ ተራራ በልበሊት ኢየሱስን ግራኝ አሕመድ ሲያቃጥል ሁለት በወርቅ የታነጹ አብያተ ክርስቲያናት በፍቃደ እግዚአብሔር እንደሰወረ አባቶች ይናገራሉ። ይኸም ጥንታዊና ታሪካዊ ተራራ አሁንም በቦታው የሚገኝ ሲሆን በዋሻው ውስጥ የክብር ባለቤት ጌታችን በስደቱ ወራት ከእናቱ ድንግል ማርያም፣ ከዮሴፍና ከሰለሜ ጋር ለጥቂት ጊዜ የተቀመጠበት ሲሆን አቡነ ዜና ማርቆስና አቡነ ተክለ ሃይማኖትም በምነና የተጋደሉበት ታላቅ ዋሻ ነው። ዋሻው እስከ ኢየሩሳሌም ድረስ ውስጥ ለውስጥ የሚያስኬድ ሲሆን በውስጡ ከ40 በላይ አብያተ ክርስቲያናት እንደተሰወሩበት አባቶች ይናገራሉ።

በግራኝ አሕመድ ወረራ ወቅት የግራኝ ሠራዊት አብያተ ክርስቲያናቱን እናጠፋለን ብለው ሲመጡ በተኣምራት ሰምጠው እንደጠፉ አባቶች ያስረዳሉ። አዛዦቹንም በዋሻ ውስጥ የሚገኙት ወፍ የሚያህሉ ተርቦች ነድፈው ጨርሰዋቸዋል። እነዚያ ተርቦች አሁንም ድረስ በገዳሙ ውስጥ ያልተፈቀደ ነገር ሲደረግ በመናደፍና በመከልከል ዋሻውን የሚጠብቁ ሲሆኑ አንዱ ተርብ ከነደፈ ሕይወት ሊያጠፋ እንደሚችል የገዳሙ አባቶች ይናገራሉ። ከዚኸም በላይ ዋሻው በነብርም ይጠበቃል።

ገዳሙ ባለብዙ ቃልኪዳን ሲሆን ብዙ ስውራን አበው ዛሬም የሚኖሩበት ትንቢታቸው የማይነጥብ ብዙ ግሁሳን የከተሙበት ነው። ስውራኑ አበው ዛሬም እግዚአብሔር ለፈቀደለት ሰው ይገለጣሉ። ደገኞቹ የኢትዮጵያ ቀደምት ነገሥታት የገዳሙን ክብር በመረዳት ቦታው ድረስ በመሔድ በረከት ይቀበሉ ነበር። ዳግማዊ ምኒሊክ ለጀር ሥላሴ ገዳምና ለገዳማውያኑ አለኝታ ስለነበሩ በገዳሙ የታሪክ መዝገብ ስማቸው ዘወትር ይነሳል። ግርማዊ ዐፄ ኀይለ ሥላሴ ቦታውን ይንከባከቡት የነበረ ሲሆን ለገዳሙ መርጃ የሚሆን አዲስ አበባ ላይ የሚከራይ ቤት አሠርተው በኪራዩ ገቢ ገዳሙ እንዲጠቀም አድርገው ነበር። በአካልም ገዳሙ ድረስ በመሔድ በረከትን ይቀበሉ ነበር።
የአቡነ ኢያሱ ረድኤት በረከታቸው ይደርብን፣ በጸሎታቸው ይማረን!
ከገድላት አንደበት
✞ ✞ ✞

በእንተ ቅዱሳን ኅሩያን (ከገድላት አንደበት)

25 Oct, 16:32


አንድ አምላክ በሚሆን በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም አሜን
+ ጥቅምት 16 የእስክንድርያ ሊቀ ጳጳሳት አባ ያቃቱ ዕረፍቱ ነው።
+ጀር ሥላሴ ገዳምን የመሰረቱትና የጻድቁ አቡነ ሀብተማርያም እረድዕ የነበሩት አቡነ ኢያሱ ዘጀር ሥላሴ ዕረፍታቸው ነው።
ጥቅምት 16-የብርሃን እናቱ ድንግል ወላዲተ አምላክ በስደቷ ወራት ያደረገችው ተአምር ይህ ነው፡- ክብርት እመቤታችን ከተወደደ ልጇ ከአምላካችን ከመድኃኒታችን ከኢየሱስ ክርስቶስ ጋር በስደታቸው ወራት ከአንዱ ሀገር ወደ ሌላው ሀገር እየተዘዋወሩ ወደታችኛው ግብጽ ቤጎር ቆላ ደረሱ፡፡ በዚያም ግብፃውያን እንደ ሕጋቸው ለአማልክቶቻቸው ላሞችን አርደው ሠውላቸው፡፡ በጎሽ፣ በአውራሪስ፣ በነጭ ዝንጀሮ የሚመሰሉ አጋንንትም መጡ፡፡ እመቤታችንም ከሩቅ ሆና ተመልክታቸው እነዚያን አጋንንት በጸሎቷ እንደጢስ በተነቻቸው፡፡ ግብፃውያንም ፈርተው እየጮኹ ሸሹ፡፡ በዚያም ወራት ‹‹ረዳት አማልክቶቻችንን ጠፉብን›› ብለው እያዘኑ ሳለ ዮሴፍን ሲጸልይ አግኝተውት አስረው በምድር ላይ አስተኝተው 40 ግርፋት ገረፉት፡፡ እርሱም በዚህ ጊዜ ‹‹እመቤቴ ሆይ ስለ አንቺና ስለ ልጅሽ ይህ መከራ አግኝቶኛልና እርጂኝ›› ብሎ በኀይል ጮኸ፡፡ እመቤታችንም ድምጹን ስትሰማ የሄሮድስ ጭፍሮች የመጡ መስሏት እጅግ ደነገጠች፡፡ ቅዱስ ገብርኤልም ተገልጦ ካረጋጋት በኋላ ዮሴፍን በኀይል ይደበድቡ የነበሩትን በእሳት ሰይፉ ጨረሳቸው፡፡ ዮሴፍንም በእጆቹ ዳሰሰውና ፈወሰው፡፡ እመቤታችንም ዮሴፍን ባየችው ጊዜ ‹‹ይህ ሁሉ መከራ ያገኘህ በእኔና በልጄ ምክንያት ነው›› ብላው አንገት ለአንገት ተቀቅፈው ተላቀሱ፡፡ መልአኩም ‹‹ይሄ ሀዘናችሁ በደስታችሁ ጊዜ ይረሳል…›› እያለ አረጋጋቸውና ዐረገ፡፡ የሀገሩ ሰዎችም ይወጓቸው ዘንድ ወጡና ክፉ ውሾችን ለቀቁባቸው፡፡ ነገር ግን ውሾቹ በሰው አንደበት እመቤታችንን እያነጋገሯት ሰግደው የእግሯን ትቢያ ልሰው በመመለስ ባለቤቶቻቸውን መልሰው መናከስ ጀመሩ፣ ብዙዎቹንም ገደሏቸው፡፡ አረጋዊ ዮሴፍም ‹‹እመቤቴ ሆይ በዚህ ሀገር ከምንኖርስ በዱር በበረሀ ብንኖር ይሻለናል›› ብሏት ወደለ ሌላ ትርጓሜዋ የሰላም ሀገር ወደሆነች ዲርዲስ ሀገር ደረሱ፡፡ ሰዎቹም ‹‹ይህችስ የነገሥታት ወገን ትመስላለች በላያችን ላይ ትነግሥብናለች›› ብለው በክፉ ሲነሱባቸው በማግስቱ ደመና ነጥቃ ወስዳ ኤልሳቤጥ በሞት ካረፈችበት በረሀ አደረሰቻቸው፡፡ ዮሐንስ በእናቱ በድን ላይ ሆኖ እያለቀሰ ሳለ ዮሴፍንና ሰሎሜን ባያቸው ጊዜ ደነገጠ፡፡ ጌታችንም አረጋጋው፡፡ እመቤታችንም ስለ ኤልሳቤጥ ሞት እጅግ መሪር የሆነ ልቅሶን ስታለቅስ ልጇ ድንቅ ምሥጢርን ከነገራት በኋላ አረጋጋት፡፡ እመቤታችንም ‹‹እናቱ ሞታበታለችና በዚህም በረሀ ማንም የለውምና ዮሐንስን ከእኛ ጋር እንውሰደው›› ስትለው ጌታችን ‹‹ዕድሉ በዚህ በረሀ ነው›› ብሎ አረጋጋት፡፡

ከዚህም በኋላ ደመና ነጥቃ ወስዳ ወደ ጋዛ ምድር አደረሰቻቸውና በዚያ አተር የሚያበራዩ ሰዎችን አግኝታ እመቤታችን ‹‹ለልጄ አተር ስጡኝ›› አለቻቸው፡፡ እነርሱም ክፉዎች ነበሩና ‹‹ይህ አተር ሳይሆን ድንጋይ ነው›› አሏት፡፡ ሕፃኑ ልጇም ‹‹እናቴ ሆይ እንደቃላቸው ይሁንላቸው ተያቸው›› አላት፡፡ ያንጊዜም አተሩ ድንጋይ ሆነ፣ ይህም እስከዛሬም ድረስ አለ፡፡
+ + + + +
አባ ያቃቱ:- ከእርሱ በፊት የነበረው አቡነ ብንያሚን በሞት ባረፈ ጊዜ ይህን ቅዱስ አባት መርጠው በእስክንድርያ አገር ላይ ሊቀ ጵጵስና ሾሙት፡፡ እርሱም ለአባቶች ሊቃነ ጳጳሳት 49ኛ ነው፡፡ በዘመኑ ከሃዲያን ብዙ ያሠቃዩት አባት ነው፡፡ ስሙ ቴዎዶስዮስ የሚባል መለካዊ ካሃዲ ሰው ነበር፡፡ እርሱም ወደ ደማስቆ ንጉሥ ዘይድ ዘንድ ሄዶ ብዙ እጅ መንሻን ሰጥቶ ለእስክንድርያ አገረ ገዥ ሆኖ ተሾመ፡፡ ከተሾመም በኋላ አባ ያቃቱንን ማሠቃየት ጀመረ፡፡ በየዓመቱ ግብር እያለ ሰባት ሺህ የወርቅ ዲናር ከአባታችን እየተቀበለ እግዚአብሔር እስካጠፋው ድረስ አባታችንን እጅግ አሠቀያቸው፡፡

በአባታችን ዘመን የብዙዎች ቅዱሳን አባቶች አባት የሆነው የአባ መቃርስ ቤተ ክርስቲያን ሕንፃዋ ተፈጸመ፡፡ በአንዲት ሌሊት ከእግዚአብሔር የታዘዘ መልአክ ለአቡነ ያቃቱን ተገለጠላቸውና ፍዩጥ በሚባል አገር በአባ መቃርስ ቤተ ክርስቲያን ውስጥ የሚያገለግል ዮሐንስ የሚባል ጻድቅ መነኮስ እንዳለ ነገራቸው፡፡ ዳግመኛም መልአኩ ዮሐንስን አስመጥተው በእሳቸው ቦታ እንዲሾሙት ነገራቸው፡፡ አባታችንም ሰዎችን ልከው ቅዱስ ዮሐንስን ካስመጡት በኋላ ሥራቸውን ሁሉ አስረክበውት በዚህች ዕለት በሰላም ዐርፈዋል፡፡
የአባ ያቃቱ ረድኤት በረከታቸው ይደርብን፣ በጸሎታቸው ይማረን
+ + + + +
አቡነ ኢያሱ ዘጀር ሥላሴ:-አቡነ ኢያሱ በ15ኛው መቶ ክፍለ ዘመን በሰሜን ሸዋ የተነሡ ሲሆን ምንኵስናቸውን ከደብረ ሊባኖሱ ከዕጨጌ አቡነ መርሐ ክርስቶስ እንደተቀበሉ ታሪካቸው ያስረዳል። ትውልዳቸው አምሐራ ሳይንት ሲሆን መካነ ሱባኤ ወተመስጦ ጀር ቅድስት ሥላሴ ገዳምን የመሠረቱ ታላቅ ጻድቅ ናቸው።

እርሳቸው የመሠረቱት ጀር ቅድስት ሥላሴ ገዳም በግራኝ ወረራ ሳይወድም ስለቀረ ጥንታዊነቱን እንደጠበቀ ስለሚገኝና ታላቅ የበረከት ቦታ የቅዱሳን መናኸሪያ ስለሆነ ብዙዎች ነገሥታት ገዳሙን እየሔዱ ተሳልመው በረከት አግኝተውበታል። የአቡነ ኢያሱን ገድላቸውን ከአቡነ ሀብተ ማርያም ገድል ጋር ጣልያናዊው ራይኔሪ በሀገሩ ሮም እንዳተመው ቀሲስ ዶ/ር አምሳሉ ተፈራ ጽፈዋል። (0s valdo Raineri, Atti di Habta Māryam (†1497) e.di Iyasu (†1508), Santi Monaci Etiopici, Roma 1990 (Or ChrA 235), 165-265.)

የጻድቁ በዓለ ዕረፍታቸው ጥቅምት 16 በገዳሙ በታላቅ ድምቀት የሚከበር ሲሆን ስለ ጻድቁ ገድል በዝርዝር ተጽፎ አላገኘንም፣ ይልቁንም አቡነ ኢያሱ ስለገደሙት ታላቁ ጀር ቅድስት ሥላሴ ገዳም ነው በብዛት የሚነገረው።

አቡነ ኢያሱ ጀር ስላሴ ከመምጣታቸውም በፊት አስቀድመው በአቡነ ዜና ማርቆስ ገዳም፣ በደብረ ሊባኖስ እና በሌሎችም ገዳማት እየተዘዋወሩ በተጋድሎ ሲቀመጡ ‹‹ቦታህ ይኸ አይደለም›› ተብለው በሊቀ መላእክት በቅዱስ ሚካኤል መሪነት ነው ወደ ጀር ሥላሴ የመጡት። ወደ ቦታው ከመምጣታቸው በፊት አካባቢው ባእድ አምልኮ የተስፋፋበት ነበር፣ ነገር ግን ጻድቁ ሕዝቡን ክርስትናን አስተምረው ወደ አምልኮተ እግዚአብሔር መልሰውታል። የምንኵስናን መሠረት ጥለውበታል። የአቡነ ኢያሱ የዕረፍታቸው ቦታ ደብረ ሊባኖስ ቢሆንም መታሰቢያቸው በመራቤቴ በሚገኘው አስደናቂ ገዳማቸው ይታሰባል። በገዳሙ በክብረ በዓሉ ወቅት ታቦት አይወጣም፣ ከበሮ አይመታም። ምክያቱም ፍጹም የጸሎት የጽሞና ቦታ ስለሆነ ነው።

መካነ ሱባኤ ወተመስጦ ጀር ቅድስት ሥላሴ አቡነ ኢያሱ ገዳም በተፈጥሮአዊ አቀማመጡ እጅግ አስደናቂ ሲሆን በአማራ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን እንሳሮ ወረዳ በደንቢ ግራርጌ ቀበሌ ጀር በሚባል ስፍራ የሚገኝ ታላቅ ገዳም ነው። ገዳሙ ከአዲስ አበባ 137 ኪ.ሜ ከደብረ ብርሃን 91 ኪ.ሜ ከለሚ ከተማ 4 ኪ.ሜ ርቀት ላይ የሚገኝ ከጥንት ጀምሮ ስዉር ገዳም ሆኖ የቆየ ነው። ገዳሙ በ1495 ዓ.ም በዐፄ ናኦድ ዘመነ መንግሥት በቅዱስ ሚካኤል መሪነት ጻዲቁ አቡነ ኢያሱ ወደዚህ ቦታ መጥተው መሥርተውታል። በጅረት ታጂቦ ስለሚገኝ ነው ጀር ሥላሴ የተባለው። የክብር ባለቤት ጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በራእይ አስመልክቶ ከመሠረታቸው ገዳማት አንዱ ነው። አቡነ ኢያሱም በገዳሙ በሚገኘው አንድ ትልቅ ዋርካ ሥር ቆመው ይጸልዩ

በእንተ ቅዱሳን ኅሩያን (ከገድላት አንደበት)

25 Oct, 03:04


አንድ አምላክ በሚሆን በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም አሜን
ጥቅምት 15-ይኽቺ ዕለት የቅዱሳን ሐዋርያት የዕረፍታቸው መታሰቢያ ትሆን ዘንድ አባቶቻችን ሥርዓት ሠሩ፡፡
+ ከኒቆምድያ አገር ቅዱስ ቢላሞን በሰማዕትነት ዐረፈ፡፡
+ ቁጥራቸው 158 የሆኑ የቅዱስ ቢላሞን ማኅበርተኞችም አብረውት በሰማዕትነት ተሰይፈዋል፡፡
ሰማዕቱ ቅዱስ ቢላሞን፡- ይህም ቅዱስ አባቱ ጣዖት አምላኪ ነው እናቱ ግን ክርስቲያን ናትና ልጇን ቢላሞንን በጥበብ አሳደገችው፡፡ ቢላሞንም ስሙ አርማላስ ከተባለ ቄስ ጋር ተገናኘና በጌታችን ማመንን አስተማረው፡፡ አስተምሮትም ሲጨርስ የክርስትናን ጥምቀት አጠመቀው፡፡ ቢላሞንም ከተጠመቀ በኋላ በጾም በጸሎት በእጅጉ ይተጋ ጀመር፡፡ ታላላቅ የሆኑ ድንቅ ድንቅ ተአምራትን እስኪያሳይ ድረስ በመንፈሳዊ ተጋድሎ ኖረ፡፡ በአንዲት ዕለትም ለዐይኖቹ መድኃኒት እንዲያደርግለት አንድ ዐይነ ሥውር ሰው ወደ ቅዱስ ቢላሞን መጣ፡፡ ይህን ጊዜ ቅዱስ ቢላሞን በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም እያለ በዐይነ ሥውሩ ዐይኖች ላይ የመስቀል ምልክት ሲያደርግ ያንጊዜ የዐይነ ሥውሩ ዐይኖች በሩ፡፡
ከሃዲና አረመኔ የሆነው የአገሪቱም ንጉሥ ዐይኖቹ የበሩለትን የዚያን ሰው ዜና በሰማ ጊዜ ሰውየውን ወደ እርሱ አስቀረበውና ‹‹ዐይኖችህን ማን አዳነህ?›› አለው፡፡ ሰውየውም ‹‹ቅዱስ ቢላሞን ፈወሰኝ በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ እያለ በመስቀል ምልክት አማተበብኝ ያንጊዜም ማየት ቻልኩ›› ብሎ ከነገረው በኋላ ‹‹እኔም ክርስቲያን ነኝ፣ በቅዱስ ቢላሞን አምላክ አምኛለሁ›› ብሎ መሰከረ፡፡ ንጉሡም በዚህ በጣም ተቆጥቶ የሰውየውን ራስ በሰይፍ አስቆረጠውና የሰማዕትነትን የድል አክሊል እንዲቀዳጅ አደረገው፡፡
ከዚህም በኋላ ንጉሡ ወታደሩን ልኮ ቅዱስ ቢላሞንን አስመጣውና ለ ሃይማኖቱ ጠየቀው፡፡ ቅዱስ ቢላሞንም ‹‹እኔ መድኃኒትና ሕይወት በሆነ ሰማይንና ምድርንም በፈጠረ በኢየሱስ ክርስቶስ የማምን ክርስቲያን ነኝ›› ብለ በከሃዲውና አረመኔው ንጉሥ ፊት ታመነ፡፡ ንጉሡም ብዙ ሽንገላዎችን በመሸንገል ከእምነቱ ሊያስወጣው ብዙ አባበለው፡፡ ብዙ ቃልኪዳንም ገባለት፡፡ ነገር ግን ቅዱስ ቢላሞን ቃሉን እንዳልሰማው ሲያውቅ በእርሱ ላይ ተቆጥቶ ድምጹን ከፍ አድርጎ ‹‹የምነግርህን ምክሬን ካልሰማኸኝ ጽኑ በሆኑ ልዩ ልዩ ሥቃዮች አሠቃይሃለሁ›› አለው፡፡ ቅዱሱም ይህን ጊዜ ‹‹እኔ አንተ ከምታሠቃየኝ ሥቃይ ፈርቼ ሃይማኖቴን ለውጬ ፈጣሪዬን አልክድም›› አለው፡፡ ንጉሡም በታላቅ ቁጣ ሆኖ ለብዙ ቀናት ሲያሠቃየው ቆየ፡፡ ጽኑ የሆነ ግርፋትን አስገረፈው፣ በስቅላትም አሠቃየው፣ በባሕር ውስጥ አሰጠመው፣ በሚነድ እሳት ውስጥ ወረወረው ነገር ግን ቅዱስ ቢላሞንን ጌታችን በመከራዎቹ ሁሉ ጽናትንና ብርታትን ይሰጠው ቁስሎቹንም ይፈውስለትና ጤነኛ ያደርገው ነበር፡፡
በመጨረሻም ቅዱስ ቢላሞን በታላቅ ሥቃይ ውስጥ ሳለ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ቅዱስ ቢላሞንን ባጠመቀው ቄስ አምሳል ተገለጠለትና ‹‹የመረጥኩህ ቢላሞን ሆይ! ደስ ይበልህ እነ ሰማያዊ መንግሥትን አዘጋጅቼልሃለሁና›› አለው፡፡ የንጉሡ ጭፍሮችም ይህንን የደስታ ቃል በሰሙ ጊዜ ክብር ይግባውና በጌታችን አመኑ፡፡ በንጉሡም ፊት የጌታችንን ክብር ሲመሰክሩ ንጉሡ በቁጣ በሰይፍ ራስ ራሶቻቸውን አስቆረጣቸው፡፡ ቁጥራቸው 158 የሆኑ ሰዎች ከቅዱስ ቢላሞን ጋር ተሰይፈው የሰማዕትነት አክሊልን ተቀበሉ፡፡
ቅዱስ ቢላሞን ረድኤት በረከቱ ይደርብን፣ በጸሎቱ ይማረን!
+ + +
ዳግመኛም ይህቺ ዕለት የቅዱሳን ሐዋርያት የዕረፍታቸው መታሰቢያ ትሆን ዘንድ አባቶቻችን ሥርዓት ሠሩ፡፡ የእነዚህም የከበሩ ቅዱሳን ሐዋርያት የዕረፍታቸው በዓል በአጭሩ እንደሚከተለው ነው፡-
የዐሥራ ኹለቱ ሐዋርያት ሰማዕትነት፡- ጌታችን አምላካችን ኢየሱስ ክርስቶስ ምስክሮች (ሰማዕትታ) የሚለውን ስያሜ መጀመሪያ የተጣቸው ለሐዋርያቱ ነው፡፡ ‹‹በኢየሩሳሌም፣ በይሁዳ፣ በሰማርያ እስከ ዓለም ዳርቻ ድረስ ምስክሮቼ ትሆናላችሁ›› ብሏቸዋልና፡፡ ሐዋ 1፡8-22፡፡ በዚኽም አምላካዊ ቃል መሠረት ሁሉም ሐዋርያት ወንጌልን የሰበኩት በብዙ ሰማዕትነት ነው፡፡ ዐሥራ ኹለቱም ሐዋርያት ሰማዕታት ናቸው፡፡ 36ቱ ቅዱሳት አንስት፣ 72ቱ አርድእት በአጠቃላይ የሐዲስ ኪዳንን ክርስትና በዓለም ያስፋፉት መቶ ሃያውም ቤተሰብ ሰማዕትነትን ተቀብለዋል፡፡ በዚኽም መሠረት፡-
1. ቅዱስ ጴጥሮስ፡- ገዳዮቹን ‹‹እኔ እንደጌታዬ ልሰቀል አይገባኝም እንደ ጌታዬ ሳይሆን ቁልቁል ዘቅዝቃችሁ ስቀሉኝ›› ብሎ በመለመን ሐምሌ 5 ቀን 67 ዓ.ም ቁልቁል ተሰቅሎ ሰማዕትነቱን በድል ፈጽሟል፡፡
2. ቅዱስ ዮሐንስ፡- ጣዖት አምላኪዎች በፈላ ውኃ እያቃጠሉ ብዙ ካሰቃዩትና በፍጥሞ ደሴት ካጋዙት በኋላ ጥር 4 ቀን ወደ ብሔረ ሕያዋን ሔደ፡፡
3. ቅዱስ እንድርያስ፡- ከክብሩና ከፍቅሩ አንጻር ‹‹ጌታዬ በተሰቀለበት ዐይነት መስቀል አትስቀሉኝ›› ብሎ ገዳዮቹን ለምኖ የእንግሊዝኛው ኤክስ (X) ፊደል ቅርጽ ባለው መስቀል ላይ ተሰቅሎ ታኅሣሥ 4 ቀን በክብር ዐረፈ፡፡
4. ቅዱስ ፊሊጶስ፡- ኅዳር 18 ቁልቁል ተሰቅሎ ሰማዕትነቱን ፈጽሞ የድል አክሊልን ተቀዳጀ፡፡
5. ቅዱስ በርተሎሜዎስ፡- መስከረም 1 ቀን አሸዋ በተሞላ ትልቅ ከረጢት ውስጥ ታሥሮ ከነሕይወቱ ባሕር ውስጥ ተጥሎ በሰማዕትነት ዐረፈ፡፡
6. ቅዱስ ቶማስ፡- እጅና እግሩን ታሥሮ ቆዳው እንደፍየል ቆዳ ተገፎ ስልቻ ተስፍቶበት በውስጡም አሸዋ ተሞልቶ ራሱን ቶማስን አሸክመውት ገበያ ለገበያ ሲያዞሩት ከዋሉና ቁስሉንም በጨው እያሹ ብዙ ካሠቃዩት በኋላ በመጨረሻ በ72 ዓ.ም ግንቦት 26 ቀን አንገቱን በሰይፍ ቆርጠውት ሰማዕተነቱን በድል ፈጽሟል፡፡
7. ቅዱስ ማቴዎስ፡- ጥቅምት 12 ቀን አንገቱን ተሰይፎ ሰውነቱም ብዙ ቦታ ተቆራርጦ ሥጋው ለሰማይ ወፎች ተሰጥቶ በሰማዕትነት ዐረፈ፡፡
8. ቅዱስ ያዕቆብ ወልደ እልፍዮስ፡- በንጉሥ ቀላውዴዎስ ትእዛዝ ክፉዎች አይሁድ በድንጋይ ወግረው ገድለውት ሰማዕትነቱን የካቲት 10 ቀን በድል ፈጸመ፡፡
9. ቅዱስ ያዕቆብ ወልደ ዘብዴዎስ፡- ንጉሥ ሄሮድስ ሰይፍ መዞ አንገቱን ቆርጦት ሚያዝያ 17 በሰማዕትነት ዐረፈ፡፡
10. ቅዱስ ናትናኤል፡- አረማውያን ሐምሌ 10 ቀን አንገቱን በሰይፍ ቆርጠውት ሰማዕትነቱን በክብር ፈጸመ፡፡
11. ቅዱስ ማትያስ፡- አረማውያን በብረት አልጋ ላይ አስተኝተው ከሥሩ 24 ቀን ሙሉ እሳት አንድደው ካቃጠሉት በኋላ መጋቢት 8 ዐረፈ፡፡
12. ቅዱስ ታዴዎስ፡- ክፉዎች አረማውያን በብዙ አሠቃቂ መከራዎች ካሰቃዩት በኋላ ሐምሌ 2 ቀን በሰማዕትነት ገድለውታል፡፡
የከበሩ ቅዱሳን ሐዋርያት ከዕረፍታቸው መታሰቢያ በዓል ረድኤት በረከት ይክፈሉን!!!

በእንተ ቅዱሳን ኅሩያን (ከገድላት አንደበት)

24 Oct, 03:51


በሀገራችን የሚገኘው የረድኡ ሐዋርያ የቅዱስ ፊሊጶስ ካቴድራል-
"ደብረ ምጥማቅ ቅዱስ ፊልጶስ ካቴድራል!"
ይኸውም ሐዋርያ ቅዱስ ፊሊጶስ እግዚአብሔር ልኮት ኢትዮጵያዊውን ጃንረባ ባኮስን ያጠመቀው ነው። የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን ታረክ፣ ምስረታ እና ልደት የሚያወሳ የታሪክም ሆነ የቤተክርስቲያን ምሁር ሐዋርያው ቅዱስ ፊልጶስን እና ቅዱስ ባኮስን ሳያነሳ ማለፍ አይቻለውም፡፡ ምክንያቱም በኢትዮጵያ የኢየሱስ ክርስቶስ ወንጌል እንዲሰበክ መነሻ የሆኑ ለእኛ ለኢትዮጵያውያን የወንጌል አባታቶቻችን ስለሆኑ ነው፡፡

ከሰባቱ ሊቀ-ዲያቆናት አንዱ ሆኖ የተሾመው ቅዱስ ፊልጶስ ትውልዱ ኢሲዶር ከምትባል የቄሳሪያ የወደብ ከተማ ሲሆን በቅዱስ እስጢፋኖስ ሞት ምክንያት ደቀመዛሙርት ከኢየሩሳሌም እስከተበተኑ ድረስ በኢየሩሳሌም ከሐዋርያት እግር ስር ሆኖ ተምሯል፡፡ ከመንፈስ ቅዱስ መገለጥ በኋላ ሐዋርያት በኢየሩሳሌም ባደረጉት የመጀመሪያ የስብከት አገልግሎት በርካታ ምዕመናን አምነው ተጠመቁ፤ የምዕመናኑ ቁጥር እጅግ በመጨመሩ እና የአገልግሎቱ ዘርፉም እየበዛ በመሄዱ አገልጋዮችን መጨመር አስፈላጊ መሆኑን በአመኑ ጊዜ ሐዋርያት ቀደም ሲል በአእርድትነት ሲያገለገሉ ከነበሩት መካከል ሰባቱን ሊቀ-ዲያቆናት ለመጋቢነት መረጡ፡፡ ምዕመኑን በመጋቢነት እንዲያገለግሉ ከተመረጡት ሰባቱ ሊቀ-ዲያቆናት መካካል አንዱ ቅዱስ ፊልጶስ ሐዋርያ ዘሰማርያ ወኢትዮጵያ ነው፡፡ በ35ዓ.ም. ቅዱስ እስጢፋኖስ በአይሁድ እጅ በሰማዕትነት ማለፉ ተከትሎ በኢየሩሳሌም የነበሩት ማኅበረ ምዕመናን ተበተኑ፤ ቅዱስ ፊልጶስም ጊቶን ወደ ምትባል የስሞን መሠርይ የትውልድ ስፍራ ወደሆነች የሰማርያ ከተማ ሄደ፡፡ በዚህያም ሐዋርያዊ አገልግሎቱን በማጠናከር በእርካታ ምዕመናን በኢየሱስ ክርስቶስ አምላክነት አምነው እንዲጠመቁ አስችሏል፡፡ በተለይ በጥንቆላ ግብሩ የሚታወቀውን ሲሞን መሠርይን በማሳመን ማጥመቁን ቅዱስ መጽሐፍ ዘግቦለታል፡፡ ሐዋ 8፡13።

በሰማርያ ሳለ የጌታም መልአክ ፊልጶስን ተነሥተህ በደቡብ በኩል ከኢየሩሳሌም ወደ ጋዛ በሚወርደው በምድረ በዳው መንገድ ሂድ አለው፡፡ እርሱም ተነሥቶ ሂደ፡፡ እነሆ የኢትዮጵያ ንግሥት የህንደኬ ባላሟል እና የሀብት ንብረቷ ሁሉ አዛዥ የሆነ አንድ ኢትዮጵያዊ ጃንደረባ አገኘ፡፡ ይህም ሰው ሊሰግድ ወደ ኢየሩሳሌም መጥቶ ነበር፡፡ ሲመለስም በሠረገላ ተቀምጦ የነቢዩን የኢሳይያስን መጽሐፍ ያነብ ነበር፡፡ መንፈስም ፊልጶስን “ሂድ ወደዚህ ሠረገላ ቅረብ” አለው፡፡ ፊልጶስም ፈጥኖ ወደ ሠረገላው ሂደ፤ ጃንደረባውም የነቢዩን የኢሳይያስን መጽሐፍ ሲያነብ ሰምቶ “ለመሆኑ የምታነበውን ታስተውለዋለህን?” አለው፡፡ ጃንደረባውም “የሚያስረዳኝ ሰው ሳይኖር እንዴት አድርጌ አስተውለዋለሁ” አለው፤ ቅዱስ ፊልጶስም ስለጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ወንጌል ሰበከለት፡፡ በመጓዝ ላይ ሳሉም ውሃ ካለበት ስፍራ ደረሱ ጃንደረባውም “እነሆ ውሃ እዚህ አለ ታዲያ እንዳልጠመቅ የሚከለክለኝ ምን ነገር አለ?” አለው፡፡ ፊልጶስም “በፍጹም ልብህ ካመንህ መጠመቅ ትችላለህ” አለው፡፡ ጃንደረባውም ‹‹ኢየሱስ ክርስቶስ የእግዚአብሔር ልጅ እንደ ሆነ አምናለሁ›› ሲል መለሰለት፤ ሠረገላውም እንዲቆም አዘዘ፡፡ ከዚያም ሁለቱም አብረው ወደ ውሃው ወረዱ፤ ፊልጶስም ጃንደረባውን አጠመቀው፡፡ ከውሃውም በወጡ ጊዜ የጌታ መንፈስ ፊልጶስን ነጥቆ ወደ አዛጦን ወሰደው። ሐዋ 8፣ 26-39። ወደ ቂሣርያ እስኪመጣ ድረስም በእየከተሞቹ ሁሉ እየተዘዋወረ ወንጌልን ሰብኳል፡፡ በቂሳርያ ሳለ ሚስት አግብቶ 4 ሴቶች ልጆችን ወለደ፤ እነርሱም ሀብተ ትንቢት የተሰጣቸው ደናግናል ነበሩ፡፡ ሐዋ 21፣8። በረጅም የወንጌል አገልግሎቱ ብዙ አይሁድን እና ሳምራዊያንን ወደ ክርስትና መልሶ ጥቅምት 14 ቀን በሰላም ማረፉን የታረክ መዛግብት ይናገራሉ፡፡
✞ ✞ ✞

አ.አ ኮልፌ አጠናተራ የሚገኘው የቅዱስ ፊልጶስ ካቴድራል ሊመሠረት የቻለው በወቅቱ በአዲስ አበባ አድባራት ከፍተኛ የሆነ የቀብር ቦታ እጥረት ስለነበር 700 የሚደርሱ እድርተኞች መዘጋጃ ቤት በመሄድ ቀብር ቦታ ይሰጠን በማለት በማመልከታቸው ምክንያት ኮልፌ አጠናተራ እስላም መቃብር ፊት ለፊት ያለው ባዶ መሬት እንዲወስዱ ተፈቀደላቸው፡፡ ነገር ግን የተፈቀደላቸው ቦታ አቶ ስፍር መዝጊያ የሚባሉ ግለሰብ ይኖሩበት ስለነበር እድርተኞቹ ቦታውን ለቀብር ቦታ እንደሚፈልጉት ገለጹላቸው፡፡ አቶ ስፍርም በህልሜ እዚህ ቦታ መኖር እንደማልችል ታይቶኝ ነበር በማለት በ45,000 ብር በመሸጥ ለቀቁላቸው፡፡ ከዚህም በመቀጠል ፍቃድ ለማግኘት ወደ ቤተክህነት የእድሩ ሊቀመንበር አቶ አበባው ግዛው እና አቶ ወልደ ሚካኤል እና ሌሎችም በመሆን በጊዜው የኢ/ኦ/ተ ፓትርያርክ የነበሩት ብፁዕ አቡነ ተክለሃይማኖት በመሄድ ስለሁኔታው በግልጽ ቦታውን እንዲባርኩላቸው ጠየቁ፡፡ አባታችንም ክርቲያን ቤተክርስቲያን በሌለበት ቦታ አይቀበርም ብለው በመመለሳቸው የእድሩ አባላት በአማኑኤል ቤተክርስቲያን ተሰብስበው ተወያዩ፡፡ በውይይታውም አቶ ስፍር ይኖሩበት የነበረውን ቤት እንደቤተክርስቲያን ለመጠቀም በመነጋገር ወደ አቡነ ተክለሃይማኖት ሄደው ሀሳባቸውን ገለፁላቸው፡፡ ብፁእ አባታችንም ፈቃዳቸው ሆኖ ጊዜያዊ ወደፊት ግን ቤተክርስቲያን ስሩለት በማለት ቤተክርስቲያን ለመሆን የሚያባውን ጸሎት በማድረግ ከመኖርያ ቤተ ወደ ቤተክርስቲያን የካቲት 20 ቀን 1978 ዓ.ም ሃያ አራት ሊቃነ ጳጳሳት በማስከተል የዲያቆኑን የቅዱስ ፊልጶስ ታቦትን አምጥተው ቤተከልርስቲያኑን መሠረቱት፡፡ ቤተክርስቲያኑን እንዲያስተዳድሩ ለሊቀ ካህናት ክፍሌ ገ/መስቀል ጽላቱን ደግሞ ለጳውሎስ ካህን ለነበሩት ለቄስ ዘመንፈስ በአደራ አስረከቧው፡፡ በዕለቱም ጥቅምት 14 እረፍቱ፣ የካቲት 20 ቅዳሴ ቤቱ በጋራ እንዲያከብሩ በማሳሰብ ተናገሩ፡፡ ከተወሰነ ጊዜ በኃላም በቆርቆሮ የተሰራ መቃኞ በማዘጋጀት ታቦቱ ወደዚያ ገባ፡፡ አሁን ላይ በዚህ መልኩ በሚያምር ሁኔታ የተሠራው የደብረ ምጥማቅ ቅዱስ ፊልጶስ ካቴድራል ተሠርቶ አልቆ የተመረቀው ጥቅምት 14 ቀን 2000 ዓ.ም ሲሆን አሁን ላይ ካቴድራሉ 34 ዓመት ሆኖታል፡፡

የቅድስት ሀገራችን ኢትዮጵያ ባለውለታ የሆነው የጥምቀት የክርስትና አባታችን የሐዋርያው የቅዱስ ፊልጶስ በዓለ ዕረፍት ጥቅምት 14 ቀን አዲስ አበባ ኮልፌ አጠና ተራ በሚገኘው በደብረ ምጥማቅ ቅዱስ ፊልጶስ ካቴድራል በደመቀ ሁኔታ ይከበራል። እርስዎም ከቦታው ተገኝተው የበረከቱ ተሣታፊ ይሆኑ ዘንድ በአምላከ ቅዱስ ፊልጶስ ስም በክብር ጠርተንዎታል።
(የካቴድራሉ ሰንበት ት/ቤት)

የሐዋርያ የቅዱስ ፊሊጶስ ረድኤት በረከቱ ይደርብን፣ በጸሎቱ ይማረን!

አምላከ አቡነ አረጋዊ፣ አምላከ ቅዱስ ገብረ ክርስቶስ
አምላከ ቅዱስ ፊሊጶስ፣ በሰማዕትነት ያረፉትን ወገኖቻችንን ከሰማዕታት ማኀበር ይደምርልን! እኛንም እስከመጨረሻው እርሱን በማመን ያጽናን!

በእንተ ቅዱሳን ኅሩያን (ከገድላት አንደበት)

21 Oct, 13:22


አንድ አምላክ በሚሆን በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም አሜን
ጥቅምት 12-ወንጌላዊው ቅዱስ ማቴዎስ ዕረፍቱ ነው፡፡
+ ድንግልና ንጹሕ የዋሕ የሆነ ተካሌ ወይን የተባለ ቅዱስ ድሜጥሮስ ዕረፍቱ ነው፡፡
+ ዳግመኛም በዚህች ዕለት መልአኩ ቅዱስ ሚካኤል ለቅዱስ ዳዊት ጎልያድን የሚገድልበትን ልዩ ኃይል ሰጥቶታል፡፡
+ ሊቀ መላእክት ቅዱስ ሚካኤል ከእግዚአብሔር ዘንድ ተልኮ ቅዱስ ዳዊትን በሳኦል ፈንታ እንዲሾመው ለሳሙኤል የነገረበት ዕለት ነው፡፡
የመላእክት ሁሉ አለቃ ቅዱስ ሚካኤል በዚህች ዕለት ወደ ነቢዩ ሳሙኤል ዘንድ ተልኮ የዳዊት አባት ወደሆነው በቤተልሔም ወደሚኖር ወደ እሴይ ቤት ሄዶ በሳኦል ፈንታ ቅዱስ ዳዊትን ያነግሠው ዘንድ አዘዘው፡፡ ሳሙኤልም ወደ እሴይ ቤት ሄዶ ‹‹ልጆችህን ሁሉንም አቅርብልኝ›› አለው፡፡ እሴይም ከዳዊት በቀር ሁሉንም አቀረባቸው፡፡ እርሱ ዳዊት በእርሻ ውስጥ በጎችን ይጠብቅ ነበርና፡፡
ሳሙኤልም የመንግሥት ቅባት ያለበትን ብልቃጥ በራሳቸው ላይ ከፍ ከፍ ባደረገ ጊዜ እግዚአብሔር አልመረጣቸውም፡፡ ነቢዩ ሳሙኤልም እሴይን ‹‹ልጆችህ እነዚህ ብቻ ናቸውን?›› ብሎ የጠቀው፡፡ እሴይም ‹‹በጎች የሚጠብቅ አንድ ትንሽ ልጅ አለ›› አለው፡፡ ሳሙኤልም ደግሞ እሴይን ‹‹እርሱ ሳይመጣ ምሳ አልበላምና ልከህ አስመጣው›› አለው፡፡ እሴይም ዳዊትን ልኮ አስመጣው፡፡ መልኩም ቀይ፣ ዐይኖቹ የተዋቡ፣ አርአያውም ያማረ ነው፡፡ እግዚአብሔርም ሳሙኤልን ‹‹ይህ ይበልጣቸዋልና ተነሥተህ ቅባው›› አለው፡፡ በዚያም ጊዜ ሳሙኤል ለዳዊት የመንግሥት ቅባት ያለበትን ቀንድ አምጥቶ በወንድሞቹ መካከል ቀባው፡፡ ከዚያችም ቀን ጀምሮ ሁልጊዜ የእግዚአብሔር መንፈስ በዳዊት ላይ አደረበት፡፡ በእስራኤል ልጆችም ላይ ነገሠ፡፡
የሊቀ መላእክት የቅዱስ ሚካኤል ጥበቃው አይለየን፣ በጸሎቱ ይማረን!
+ + +
ወንጌላዊው ቅዱስ ማቴዎስ፡- የመጀመሪያ ስሙ ሌዊ ሲሆን በቀድሞ ሥራውም ቀራጭ (ባንክ መንዛሪ) ነበር፡፡ ግብር ከሚያስገብርበት ቦታ ተቀምጦ እየቀረጠ ሳለ ነው ጌታችን በአጠገቡ አልፎ ‹‹ሌዊ ተከተለኝ›› ብሎ የጠራው፡፡ እርሱም ሳያቅማማና ሳያመነታ ወዲያው ተነሥቶ ተከተለው፡፡ ቅዱስ ማቴዎስ ጌታችን ቀድሞ በነቢያት የተነገረለት መሢሕ መሆኑን ለማስረገጥ ሲል አንድን ታሪክ ከጻፈ በኋላ ‹‹በዚህም… ተብሎ በነቢይ የተነገረው (የተጻፈው) ተፈጸመ›› ብሎ ይመሰክራል፡፡ ከፍልስጤም ተነሥቶ በእስያ አድርጎ ደቀ መዝሙሩን ማርቆስንና ሌለቹን በግብፅ ትቶ እርሱ እስከ ኢትዮጵያ ድረስ መጥቶ ወንጌልን ሰብኳል፡፡ ከዚህም በኋላ ወደ ብዙ ሀገሮች ተዘዋውሮ ወንጌልን ከሰበከ በኋላ ወደ ካህናት አገር ደረሰ፡፡ አንድ ወጣትም አግኝቶ ወደ ከተማው እንዴት እንደሚገባ ጠየቀው፡፡ ወጣቱም ‹‹ራስህንና ጺምህን ተላጭተህ በእጅህ ዘንባባ ይዘህ ካልሆነ መግባት አትችልም›› አለው፡፡ ይህም ነገር ቅዱስ ማቴዎስን እያስጨነቀው እያለ ያ መጀመሪያ ያገኘው ወጣት ቅዱስ ማቴዎስን በስሙ ጠራው፡፡ ማቴዎስም በስሙ ስለጠራው ደንግጦ ‹‹ስሜን ወዴት ታውቀዋለህ?›› አለው፡፡ እርሱም ‹‹እኔ ጌታህ ኢየሱስ ነኝ፣ አሁንም እንደነገርኩህ አድርግ እኔም ከአንተ ጋር አለሁ ከአንተም አልርቅም›› አለው፡፡ ማቴዎስም እንደታዘዘው ራሱንና ጺሙን ተላጭቶ በእጁም ዘንባባ ይዞ ወደ ከተማዋ ገባ፡፡ እንደገባም ለአማልክት ካህናት አለቃቸው የሆነውን አርሚስን ተገናኘውና ከእርሱ ጋር ስለ አማልክቶቻቸው አወራ፡፡ ድንቅ ተአምርንም በማድረግ ጣዖቶቻቸውን አቃጠላቸው፡፡ አርሚስንና የአገሩንም ሰዎች ሁሉ አስተምሮ በማሳመን አጠመቃቸው፡፡ ከሰማይም ማዕድ አውርዶ መግቧቸዋል፡፡

የሀገሩም ንጉሥ ይህን ሲሰማ እጅግ ተቆጥቶ ቅዱስ ማቴዎስንና አርሚስን እሳት ውስጥ ጨመራቸው፡፡ ነገር ግን ጌታችን ፈወሳቸው፡፡ ንጉሡም የሚያሠቃይበትን ነገር ሲፈልግ ድንገት ልጁ ሞተ፡፡ ማቴዎስም ንጉሡን ‹‹ልጅህን ከሞት እንዲያነሡት ወደ አማላክትህ ለምን አትለምንም?›› አለው፡፡ ንጉሡም ‹‹አማልክት እንዴት የሞተን ያስነሣሉ›› ብሎ መልሶ ጠየቀው፡፡ ቅዱስ ማቴዎስም ‹‹ብታምን ግን የእኛ አምላክ የሞተውን ልጅህን ያስነሣልሃል›› አለው፡፡ ንጉሡም ‹‹ልጄ ከሞት ከተነሣ በአምላክህ አምናለሁ›› አለው፡፡ ማቴዎስም ወደ ጌታችን ከጸለየ በኋላ ልጁን ከሞት አስነሣው፡፡ ይህንንም ያዩት ንጉሡና የሀገሩ ሰዎች በጌታችን አመኑ፡፡ ቤተ ክርስቲያንም ሠርቶላቸው አገልጋዮችን ሾመላቸውና ወደ ሌላ አገር ሄደ፡፡ በዚያም አስተምሮ ብዙዎችን አሳምኖ እንዲጠመቁ በማድረጉ አገረ ገዥው ማቴዎስን ይዞ አሠረው፡፡
በአሥር ቤትም አንድን የሚያሳዝን ሰው ተጨንቆ ሲያለቅስ አገኘው፡፡ ምን እንደሆነም ሲጠይቀው የጌታው ብዙ ገንዘብ ከባሕር ውስጥ እንደሰጠመበት ነገረው፡፡ ቅዱስ ማቴዎስም ያንን ምስኪን ገንዘቡን ከባሕሩ ዳርቻ እንደሚያገኘውና ወደ ወንዙም ሄዶ ገንዘቡን ወስዶ ለጌታው እንዲሰጠው ነገረው፡፡ ሰውየውም ወደ ባሕሩ ሲሄድ ማቴዎስ እንደነገረው ገንዘቡን ከባሕሩ ዳርቻ አገኘው፡፡ ይህንንም ያዩ የሀገሩ ሰዎች በጌታችን አመኑ፡፡ አገረ ገዥውም ይህን ሲሰማ በቁጣ ገንፍሎ ቅዱስ ማቴዎስን ጥቅምት 12 ቀን አንገቱን በሰይፍ አስቆረጠው፡፡ ሰውነቱንም ብዙ ቦታ ቆራርጦ ሥጋውን ለሰማይ ወፎች ሰጠው፡፡ ምእመናንም ሥጋውን በሥውር ወስደው በመልካም ቦታ አኖሩት፡፡ ከሥጋውም ብዙ አስገራሚ ተአምራት ተፈጽመው ታዩ፡፡
የወንጌላዊው የቅዱስ ማቴዎስ ረድኤት በረከቱ ይደርብን፣ በጸሎቱ ይማረን፡፡
+ + +
ቅዱስ ድሜጥሮስ ተካሌ ወይን፡- ዲሜጥሮስ ማለት ‹‹መስተዋት›› ማለት ነው፡፡ ይህም ታላቅ ጻድቅ ለአባቶች ሊቃነ ጳጳሳት 12ኛ የሆነ የእስክንድርያ ሊቀ ጳጳሳት ነው፡፡ ከአባቱ ከአርማስቆስና ከእናቱ ኢላርያ መጋቢት 12 ቀን ተወለደ፡፡ አስቀድሞ መጻሕፍትን ያልተማረ ሕዝባዊ ገበሬ ስለነበር በወላጆቹም የወይን አትክልት ቦታዎች ይሠራ ነበር፡፡
በትንሽ ዕድሜውም ልዕልተ ወይን የምትባል ሚስት አጋቡት፡፡ እርሷም የአጎቱ ልጅ ነበረች፡፡ ባልና ሚስት ሆነው በአንድ አልጋ አብረው እየተኙ ነገር ግን በግብር ሳይተዋቁ መልአክ እየጋረዳቸውና እየጠበቃቸው ለ48 ዓመታት አብረው ኖሩ፡፡ ድንግልናቸውን ንጽሕናቸውን እየጠበቁ ሲኖሩ ይህንን ምሥጢራቸውን ከእግዚአብሔር በቀር ማንም የሚያውቅ የለም፡፡ ከሐዋርያው ማርቆስ ቀጥሎ በእርሱ መንበር 11ኛው ሊቀ ጳጳሳት የነበረው አቡነ ዮልዮስ ዕረፍቱ በደረሰ ጊዜ መልአክ ተገልጦለት ‹‹ነገ የወይን ዘለላ ይዞ ወደ አንተ የሚገባ ሰው አለ፣ ከአንተ በኋላ ሊቀ ጳጳሳት የሚሆነው እርሱ ነውና ያዘው›› አለው፡፡ በዚያችም ቀን ድሜጥሮስ ወደ አትክልቱ ቦታ ገብቶ ሳለ ያለጊዜዋ ያፈራች የወይን ዘለላ አገኘ፡፡ እርሱም ‹‹ይህችንስ የወይን ዘለላ ለሊቀ ጳጳሳቱ ሰጥቻቸው በረከት እቀበልባታለሁ›› ብሎ አሰበና ወደ አባ ዮልዮስ ዘንድ ይዞ ሄደ፡፡ በመንገድም ሳለ ሊቀ ጳጳሳቱ አባ ዮልዮስ ዐርፈው ጳጳሳቱና ሕዝቡ ሊቀብሯቸው ሲወስዷቸው አገኛቸው፡፡ እርሳቸውም ከማረፋቸው በፊት ከእርሳቸው በኋላ ማን እንደሚሾም ለሕዝቡ ምልክት ነግረዋቸው ነበር፡፡ ይኸውም ‹‹ያለጊዜዋ ያፈራች የወይን ዘለላ ይዞ የሚመጣውን ሰው በእኔ ቦታ እንድትሾሙት የእግዚአብሔር መልአክ አዞኛል›› ብለው ነግረዋቸው ስለነበር አሁን ሊቀብሩ ሲወስዷቸው ድምጥሮስን ያለጊዜዋ ያፈራች የወይን ዘለላ ይዞ ሲመጣ አገኙትና ከቀብራቸው በኋላ ወስደው በሐዋርያው በቅዱስ ማርቆስ መንበር 12ኛው ሊቀ ጳጳሳት አድርገው በተወለደበት ዕለት መጋቢት 12 ቀን ሾሙት፡፡

በእንተ ቅዱሳን ኅሩያን (ከገድላት አንደበት)

21 Oct, 13:22


ከሹመቱ በኋላ በቍርባን ጊዜ ጌታችንን በግልጽ ያየው ነበር፡፡ የሰዎቹም ሁሉ ድብቅ ኃጢአት በግልጽ ይታየው ስለነበር የበቃውንና ያልበቃውን እለየለ ንስሓ ይሰጣቸው ነበር እንጂ በኃጢአት ውስጥ እንዳሉ እንዲሁ በድፍረት ወደ ሥጋወደሙ አያቀርባቸውም ነበር፡፡ በዚህም ብዙዎቹን በቅድስና ጠበቃቸው ነገር ግን ክፉዎች ቀንተውበት ‹‹እራሱ ሚስት አግብቶ ጋለሞታ ይዞ ሳለ ድንግል ሳይሆንና ሳይገባው በወንጌላዊው ማርቆስ መንበር እየኖረ…›› ብለው አሙት፡፡ በዚህም ጊዜ መልአኩ ቅዱስ ሚካኤል ተገልጦለት ‹‹በአንተና በሚስትህ መካከል ያለውን ቅድስና ለሕዝቡ ግለጥላቸው›› አለው፡፡ ድሜጥሮስም ከቅዳሴ በኋላ ሰው እንደተሰበሰበ ደመራ አስደምሮ ልብሰ ተክህኖውን እንደለበሰ በሚነደው እሳት ውስጥ ገብቶ መጸለይ ጀመረ፡፡ በእሳት ውስጥ እንዳለ ከእሳቱ ፍም አንስቶ በሚከናነብበት ቀጸላ አደረገ፡፡ ሚስቱንም ጠርቶ መጎናጸፊያሽን ዘርጊ አላትና በመጎናጸፊያዋ የእሳቱን ፍም ጨመረ፡፡ ነገር ግን የእርሱን ቀጸላና የሚስቱን መጎናጸፊያ ምንም እሳት አልነካውም ነበር፡፡ በእሳቱም መካከል በአንድነት እየጸለዩ በቆሙ ጊዜ ሕዝቡ ይህን ተመልክቶ እጅግ አደነቀ፡፡ እርሱም የእሳቱን ፍሕም እያነሳ ቢረጨው ሐሜተኞችን ብቻ እየመረጠ አቃጠላቸው፡፡ ሕዝቡም ቅድስናውንና ንጽሕናውን አይተው በመጸጸት ‹‹ይቅር በለን›› ብለው ይቅር ብሏቸው ስለ ኃጢአታቸው ጸልዮላቸዋል፡፡
ቅዱስ ዲሜጥሮስንም የተአምራቱን ምሥጢር በጠየቁት ጊዜ እንዲህ አላቸው፡- ‹‹ይህን ሥራ የሠራሁት ከንቱ ውዳሴ ሽቼ አይደለም፣ እንናተ እኔን አምታችሁ እንዳትጎዱ ከዚህችም ሴት ጋር በመካከላችን ተሰውሮ ያለውን ምሥጢር እገልጥላችሁ ዘንድ የእግዚአብሔር መልአክ ስላዘዘኝ ነው እንጂ፡፡ እርሷ የአባቴ የወንድሙ ልጅ ናት፡፡ በሕፃንነቷም አባቷ ስለሞተ በአባቴ ቤት ከእኔ ጋር አደገች፡፡ አካለ መጠንም በደረስን ጊዜ አባቴ እርሷን አጋባኝ፡፡ ወደ ጫጉላ ቤትም በገባን ጊዜ ‹እኔ እኅትህ ስሆን ለአንተ እንዴት አጋቡኝ› አለችኝ፡፡ እኔም የምትፈቅጂ ከሆነ ድንግልናችንን ጠብቀን በአንድነት እንኑር ይህንንም በመካከላችን ያለውን ምሥጢር የሚያውቅ ማንም አይኑር አልኳት፡፡ በዚህም ተስማምተን በአንድ ቤት ውስጥ በአንድ አልጋ እየተኛን አንድ መጎናጸፊያም እየተጎናጸፍን 48 ዓመት ያህል ኖርን፡፡ ይህንንም ሥራችንን ከእግዚአብሔር በቀር የሚያውቅ የለም፡፡ እኔም እርሷ ሴት እንደሆነች አላወቅኋትም እርሷም እኔን ወንድ እንደሆንኩ አታውቅም፡፡ በየሌሊቱም ሁሉ በንስር አምሳል ወደ መኝታ ቤታችን እየገባ ክንፎቹን አልብሶን ያድራል ሲነጋም ከእኛ ይሠወራል›› አላቸው፡፡
ቅዱስ ድምጥሮስ መንፈስ ቅዱስ አድሮባልና የብሉይና የሐዲሳትን መጻሕፍት ሁሉ አንብቦ ተረጎማቸው፣ ምሥጢራትም ተገለጡለት፡፡ ባሕረ ሀሳብ የተባለውንም ድንቅ የሆነ የዘመን መቁጠሪያ ሠርቶ ያዘጋጀው ይህ ቅዱስ ድሜጥሮስ ነው፡፡ ቅድስት ቤተ ክርስቲያናችንም ይህ ጻድቅ በመንፈስ ቅዱስ መሪነት የቀመረውን ይህን የድሜጥሮስን ቀመር በሚገባ እየተጠቀመችበት ነው፡፡ በዚህ የቀን አቆጣጠር ቀመር መሠረት የደብረ ዘይት፣ የሆሳዕና፣ የትንሣኤና የጰራቅሊጦስ በዓላት ሁልጊዜ በየዓመቱ ከእሁድ አይወጡም፡፡ ስቅለትም ሁልጊዜ ከአርብ አይወጣም፡፡ የጌታችን የዕርገቱም በዓል ከሐሙስ አይወጣም፡፡ ቀመሩንም አዘጋጅቶ ሲጨርስ ለኢየሩሳሌም፣ ለሮሜ፣ ለኤፌሶንና ለአንጾኪያ አገሮች ላከላቸው፡፡ ጻድቁ አርጅቶና ሸምግሎ በደከመ ጊዜም ሕዝቡ በአልጋ ላይ አስቀምጠው ተሸክመው ወደ ቤተ ክርስቲያን ያደርሱትና ያስተምራቸው ነበር፡፡ ቅዱስ ድሜጥሮስ በተወለደ በ115 ዓመቱ ጥቅምት 12 ቀን በታላቅ ክብር ዐርፏል፡፡
የቅዱስ ድሜጥሮስ ረድኤት በረከቱ ይደርብን፣ በጸሎቱ ይማረን፡፡

በእንተ ቅዱሳን ኅሩያን (ከገድላት አንደበት)

20 Oct, 14:28


አንድ አምላክ በሚሆን በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም አሜን
ጥቅምት 11-ቅዱስ ገብርኤል ተገልጦ "ግዝትህን አንሣ" ብሎ እስካዘዛቸው ድረስ የዓባይን ወንዝ ከኢትዮጵያ እንዳይወጣ በጸሎታቸው ገዝተው ያቆሙት የውቅሮው አቡነ ኤልያስ መታሰቢያ በዓላቸው ነው፡፡
+ በአንጾኪያ አገር አስቀድማ በኃጢአት ትኖር የነበረችውና በኋላም በንስሓ የተመለሰችው ገድለኛዋ ቅድስት ጲላግያ ዕረፍቷ ነው፡፡
+ የአንጾኪያው ሊቀ ጳጳሳት አቡነ ያዕቆብ ዕረፍቱ ነው፡፡ ይኸውም ቅዱስ አባት አርዮሳውያን መናፍ*ቃን በተደጋጋሚ እያሳደዱት በስደት ደሴት ላይ ሰባት ዓመት የኖረ የሃይማኖት አርበኛ ነው፡፡ ስለቀናች ሃይማኖቱ ብዙ መከራን ተቀብሏል፡፡ ረድኤት በረከቱ ይደርብን፣ በጸሎቱ ይማረን!
+ + + + +
ቅድስት ጲላግያ፡- ከአንጾኪያ አገር የተገኘች ቅድስት ናት፡፡ ወላጆቿ የማያምኑ ከሃድያን ናቸው፡፡ እርሷም አስቀድማ ከረከሰች ሃይማኖቷ ጋር በረከሰ ሥራ ጸንታ መኖርን ገንዘብ ያደረገች ነበረች፡፡ በመሸ ጊዜ በጨዋታ ቤት በመዋል ስትሣለቅና ስትዘፍን ስታመነዝርም ኖራለች፡፡ በእንደዚህ ዓይነቱ የረከሰ ሕይወት ውስጥ ከኖረች በኋላ ግን ከዕለታት በአንደኛው ቀን የገሀነም እሳትና የዘላለም ሥቃይን እንደሚጠብቃቸው እያሳሰበ ዝንጉዎችንና አመንዝራዎችን ሲገሥጻቸው ኤጲስቆጶስ ጳውሎስን ሰማችውና ምክሩን በልቧ አሳደረች፡፡

ከዚህም በኋላ ቅድስት ጲላግያ ሲያስተምር ወደሰማችው ኤጲስቆጶስ ጳውሎስ ዘንድ ሄዳ የሠራችውን ኃጢአቷን ሁሉ ተናዘዘች፡፡ እርሱም አጽናንቶ የቀናች ሃይማኖትን አስተማራትና ከነበረችበት የእርኩሰት ሕይወት አወጣት፡፡ አስተምሮ ካሳመናትም በኋላ አንድ አምላክ በሚሆን በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም አጠመቃት፡፡ እርሷም በቀደመው ክፉ ሥራዋ እየተጸጸተች በጾም፣ በጾሎት፣ በስግደትና በመልካም ሥራዎች ሁሉ እየተጋች ሰውነቷን ማድከም ጀመረች፡፡ ተጋድሎዋንም ለማብዛት ባሰበች ጊዜ የወንድ ልብስ ለብሳ ወደ ኢየሩሳሌም ሄዳ የከበሩ ቅዱሳት ቦታዎች ሁሉ ተሳልማ ሰገደችና ወደ ኢየሩሳሌሙ ሊቀ ጳጳሳት ዘንድ ሄደች፡፡ እርሱም ከኢየሩሳሌም ከተማ ውጭ ወደሚገኘው የደናግል ገዳም አስገባት፡፡ እርሷም የምንኩስናን ልብስ ለብሳ በጽኑ ገድል ተጠምዳ 30 ዓመት ኖረች፡፡ እግዚአብሔርንም እያገለገለች በጽኑ ተጋድሎ ኖራ በዚህች ዕለት በሰላም ዐረፈች፡፡
ረድኤት በረከቷ ይደርብን፣ በጸሎቷ ይማረን!
+ + + + +

አቡነ ኤልያስ ዘውቅሮ፡- አቡነ ኤልያስ ዘውቅሮ የትውልድ ሀገራቸው አክሱም ነው፡፡ የአቡነ አረጋዊ 3ኛ የቆብ ልጅ ናቸው፡፡ አባታቸው ውቅሮ የሚገኘው የጥንታዊው የአብርሃ ወአጽብሓ ቤተ መቅደስ አጣኝ ነበሩ፡፡ ይህ ጻድቅ የሚታወቁበት አንድ ትልቅ ገድል አላቸው፡፡ በቀን 548 ጊዜ አቡነ ዘበሰማያትን እየጸለዩ 666 ጊዜ ይሰግዱ ነበር፡፡ ቅዱስ ያሬድ ዓባይ የሀገራችንን አፈርና ዛፉን ሁሉ ጠራርጎ ሲወስድ ቢመለከት ድምጹን ከፍ አድርጎ ኦ አባይ አይቴ ተሐውር ወለመኑ ተሐዲጋ ለኢትዮጵያ ብሎ ሲዘምር ዓባይ ቀጥ ብሎ ቆሟል፡፡ መልአኩም ወዲያው መጥቶ ‹‹ለምን ትደክማለህ? ለምንስ ተፈጥሮን ትከለክላለህ? ሕጉን አታፍርስ›› ሲለው ቅዱስ ያሬድ ደንጎጦ ‹‹አጥፍቻለሁ ዓባይ ሆይ ሂድ የተፈጥሮ ግዴታህን ፈጽም›› ብሎ አሰናብቶታል፡፡ የኢትዮጵያ ብርሃኗ ቅዱስ ያሬድ በዜማው ዓባይን ቀጥ አድርጎ እንዳቆመው ሁሉ አቡነ ኤልያስ ዘውቅሮም በጸሎታቸው ዓባይን ከኢትዮጵያ እንዳይወጣ አድርገውት ነበር፡፡

ታቦተ አብርሃ ወአጽብሓን ይዘው ከኢትዮጵያ ጠረፍ ዳር ኑብያ ሄደው ድንጋይ ከዓባይ ዳር ደርድረው ታቦቱን አስቀምጠው ሥዕለ ማርያምን አድርገው መሥዋዕት ሰውተው ‹‹ዓባይ ከኢትዮጵያ እንዳትወጣ ገዝቼሃለሁ›› ሲሉት ዓባይም ተመልሶ ቆሟል፡፡ ዓባይ ምድረ ኑብያን ሲያጥለቀልቃት መልአኩ ቅዱስ ገብርኤል ተገልጾ ‹‹ለምን የእግዚአብሔርን ስነ ፍጥረት ታስጨንቃለህ?›› ብሎ ተቆጣቸው፡፡ ጻድቁም ‹‹ውኃው ይሂድ ግን ዛፉን አፈሩን ይዞ ከኢትዮጵያ አይውጣ›› ብለው መልአኩን ጠየቁት፡፡ ቅዱስ ገብርኤልም ‹‹ውኃ ሲሞላ ዛፉን ቅጠሉን ይዞ መጓዙን እንዴት ትረሳዋለህ? የጸሎት ጊዜህ ደርሷልና ወደ በዓትህ ተመለስ›› ብሎ በቁጣ የእሳት ሰይፉን ሲያዛቸው ግዝታቸውን አንሥተው ታቦታቸውን ይዘው ወደ በዓታቸው ውቅሮ ተመልሰዋል፡፡ አባቶቻችን እንዲህ ናቸው እንኳን ሃይማኖት፣ ባህል፣ ታሪክ፣ ቅርስ፣ ስብዕና ማንነታችንን ይቅርና የሀገራችንን አፈር እንኳን ለባዕድ አሳልፈው የማይሰጡ ቅዱሳን ጻድቃን ነበሩ፡፡ የአባ ኤልያስ ረድኤት በረከታቸው ይደርብን፣ በጸሎታቸው ይማረን፡፡
ከገድላት አንደበት
✞ ✞ ✞

በእንተ ቅዱሳን ኅሩያን (ከገድላት አንደበት)

20 Oct, 06:51


ጥቅምት 10-አባ ዘወንጌል በዓለ ዕረፍታቸው ነው። በረከታቸው ይደርብን

በእንተ ቅዱሳን ኅሩያን (ከገድላት አንደበት)

20 Oct, 06:37


አንድ አምላክ በሚሆን በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም አሜን
ጥቅምት 10-ቅዱስ ሰርጊስ በሰማዕትነት ዐረፈ፡፡ ቅዱስ ሰርጊስና ባልንጀራው ቅዱስ ባኮስ በንጉሥ መክሲምያኖስ ግዛት (284-305) ውስጥ የጦር ኃይል ከፍተኛ ባለሥልጣናት ነበሩ፡፡ ንጉሡ ከሃዲ የነበረ ነው፡፡ እነዚህም ሁሉቱ ቅዱሳን በጌታችን የሚምኑ ክርስቲያኖች መሆናቸውን ግን ዐላወቀም ነበር፡፡ የንጉሡን እምነት የሚከተሉ ክፉዎች ሄደው ንጉሥ መክሲምያኖስን ‹‹የሾምካቸው ሰርጊስና ባኮስ በአንተ አማልክት የማያምኑ ናቸው›› ብለው ነገሩት፡፡ እነዚህም ሁለቱ ቅዱሳን ክርስቲያን በመሆናቸው ተወንጅለው ንጉሡ ፊት ቀረቡ፡፡ ንጉሡም ‹‹ለአማልክቶቼ ስገዱ›› ሲላቸው እነርሱም ‹‹እኛስ ሰማይንና ምድርን የፈጠረውን እውነተኛውን አምላክ የምናመልክ ነን፡፡ ለአንተ የረከሱ ጣዖታት አንገዛም›› አሉት፡፡ ንጉሡም ትእዛዙን እንዳልተቀበሉት ሲያውቅ በሰውነታቸው ላይ ታላቅ ሥቃይ አደረሰባቸው፡፡ ሰውነታቸውንና አንገታቸውን በሰንሰለት አሥሮ በከተማው ሁሉ እየገረፈ አዞራቸው፡፡ በማግስቱም ለአማልክቶቹ ይሰግዱ ዘንድ ድጋሚ አዘዛቸው፣ እነርሱ ግን ፈጽመው አልተቀበሉትም፡፡ ከዚህም በኋላ አሠቃይቶ ይገድላቸው ዘንድ ወደ ምሥራቃዊው የሶርያ ገዥ አንጥያኮስ ዘንድ ላካቸው፡፡

ንጉሥ አንጥያኮስ መጀመሪያ ሥልጣኑን ያገኘው በእነዚህ ሁለት ቅዱሳን አማካኝነት ስለነበር አሁን በግዞት ወደ እርሱ በመጡ ጊዜ ‹‹ረዳቶቼ የሆናችሁ አባቶቼ ሆይ! እኔስ በእናንተ ላይ አንዳች ክፉ ነገር ማድረግ አልፈልግም ነገር ግን የንጉሡን ትእዛዝ በመቀበል ለምን በሕይወት አትኖሩም? ትእዛዙንስ ለምን ትተላለፋላችሁ?›› አላቸው፡፡ ቅዱሳን የሆኑ ሰርጊስና ባልንጀራው ባኮስም ‹‹ለእኛ ሕይወት ክርስቶስ ነው፣ ስለ ስሙ ብለን ብንሞትም ማትረፊያ መንገዳችን ነው›› አሉት፡፡ ያንጊዜም ንጉሥ አንጥያኮስ ተናዶ ቅዱስ ሰርጊስን አሠረው፡፡ ቅዱስ ባኮስን ግን ጽኑ ድብደባ ካስደበደበው በኋላ በአንገቱ ከባድ ድንጋይ አንጠልጥሎ በኤፍራጥስ ወንዝ ውስጥ ጣለው፡፡ ባኮስም ቅድስት ነፍሱን ለእግዚአብሔር አሳልፎ ሰጠ፡፡ ዕረፍቱም ጥቅምት 4 ነው፡፡ የቅዱስ ባኮስ ሥጋውን እግዚአብሔር ጠብቆት ወደ ወደብ አደረሰው፡፡ በወደቡም አቅራቢያ በገድል ተጠምደው የሚኖሩ ማማ እና ባባ የሚባሉ ሁለት ባሕታውያንን ነበሩና እግዚአብሔር መልአኩን ወደ እነርሱ ልኮ ሄደው የቅዱስ ባኮስን ሥጋ ወደ በዓታቸው እንዲወስዱ አዘዛቸው፡፡ ባሕታውያኑም እንታዘዙት ሄደው የቅዱስ ባኮስን ሥጋ አንበሶችና ተኩላዎች ቀንና ሌሊት እየጠበቁት አገኙ፡፡ እነዚህም አውሬዎች ከእንስሳና ከሰው ሥጋ በቀር ሌላ የማይመገቡ ሲሆኑ ነገር ግን የቅዱስ ባኮስን ሥጋ አንድ ቀንና ሌሊት ሲጠብቁ ቆዩ፡፡ ባሕታውያኑም የቅዱስ ባኮስን ሥጋ ወስደው በታላቅ ክብር በበዓታቸው አስቀመምጠው ቀበሩት፡፡

ቅዱስ ሰርጊስን ግን ንጉሡ በወህኒ ቤት ውስጥ ካሠረው በኋላ እግሮቹን በብረት ችንካሮች ቸንክረው በፈረሶች እየጎተቱ ሩጻፋ ወደሚባል አገር ወሰዱት፡፡ በዚያም በደረሰ ጊዜ ብዙ ካሠቃዩት በኋላ አንገቱን በሰይፍ ቆርጠው እንዲገድሉት ንጉሡ ትእዛዝ አስተላለፈ፡፡ የቅዱስ ሰርጊስ እግሮቹን በችንካር ቸንክረው በፈረሶቻቸው ላይ አስረው እያዳፉ ሲወስዱት ደሙ በመሬት ላይ እንደውኃ ፈሰሰ፡፡ በመንገድ ላይ አንዲት ድንግል ብላቴና ቅዱስ ሰርጊስን አገኘችውና ውኃ አጠጣችው፡፡ ቅዱሱም ‹‹ሥጋዬን ትወስጂ ዘንድ እስከ ሩጻፋ ተከተይኝ›› አላትና ተከተለችው፡፡
የንጉሡም ጭፍሮች እንደታዘዙት ሩጻፋ የምትባለው አገር ከደረሱ በኋላ ቅዱስ ሰርጊስን ብዙ ካሠቃዩት በኋላ በመጨረሻ በዚህች ዕለት ጥቅምት 10 ቀን አንገቱን በሰይፍ ቆረጡትና የሰማዕትነቱ ፍጻሜ ሆነ፡፡ ያችም ብላቴና ወደ ቅዱሱ ቀርባ በጸጉሯ ባዘቶ ከአንገቱ የፈሰሰውን ደሙን ተቀበለች፡፡ የስደቱም ወራት እስካለፈ ድረስ ሥጋውን በክብር አስቀምጣ ስትጠብቅ ኖረች፡፡ ከዚህም በኋላ ያማረች ቤተ ክርስቲያን ሠርተውለት የቅዱስ ሰርጊስን ሥጋ በውስጧ አኖሩ፡፡ ከሥጋውም ብዙ አስደናቂ ተአምራት ተፈጽመው ታዩ፡፡ ከሥጋውም ሽታው እጅግ ጣፋጭ የሆነ የሽቱ ቅባት ይፈስ ነበር፡፡

የቅዱስ ሰርጊስና የባልንጀራው የቅዱስ ባኮስ ረድኤት በረከታቸው ይደርብን፣ በጸሎታቸው ይማረን!

በእንተ ቅዱሳን ኅሩያን (ከገድላት አንደበት)

18 Oct, 13:16


የአቡነ መዝገበ ሥላሴ ረድኤት በረከታቸው ይደርብን፣ በጸሎታቸው ይማረን!
+++
የአንጾኪያው ሰማዕት ቅዱስ እስጢፋኖስ፡- ይኸኛው እስጢፋኖስ በአንጾኪያ አገር የሰማዕታት መጀመሪያ ሆኖ የተጋደለ ታላቅ ሰማዕት ነው፡፡ ‹‹በአንጾኪያ አገር የሰማዕታት መጀመሪያ›› መባሉ በንጉሡ ዲዮቅልጥያኖስ ክህደት ምክንያት በአንጾኪያ አገር እጅግ የከበሩ ብዙ ታላላቅ ሰማዕታት የጌታችንን ክብር መስክረው በፈቃዳቸው ተሰይፈዋልና ነው፡፡ ከእነዚህም ውስጥ ቅዱስ ፋሲለደስ፣ የንጉሡ ልጅ ቅዱስ ዮስጦስ፣ የቅዱስ ፋሲለደስ ልጆቹ ቅዱስ አውሳብዮስና ቅዱስ መቃርስ፣ ቅዱስ አባድር፣ ቅዱስ ገላውዲዮስ፣ ቅዱስ ቴዎድሮስ በናድልዮስ፣ ቅዱስ አቦሊ… በጥቂቱ ይጠቀሳሉ፡፡ እነዚህ ሁሉ የነገሥታት ልጆች ቢሆኑም በከሃዲው ንጉሥ ዲዮቅልጥያኖስ ፊት ስለ ጌታችን ክብር ሲሉ በራሳቸው ፈቃድ የተሰየፉ ታላላቅ ሰማዕታት ናቸው፡፡ ነገር ግን በከሃዲው ንጉሥ በዲዮቅልጥያኖስ እጅ ሰማዕት በመሆን ይኽ እስጢፋኖስ የተባለው የአንጾኪያ ሰማዕት ከሁሉም ይቀድማል፡፡ እርሱም የፋሲለደስ ወንድም የሆነ የኒቆምዮስ ልጅ ነው፡፡ አባቱም በአንጾኪያ ከታወቁ ታላላቅ ወገኖች ውስጥ አንዱ ሲሆን እጅግ ባለጸጋም ነበር፡፡ እርሱም ለድኆችና ጦም አዳሪዎች የሚመጸውት ጌታችንን የሚወድ ነው፡፡ ልጁን እስጢፋኖስንም ከዳዊት መዝሙር ጀምሮ ብሉይንና ሐዲስን እያስተማረ በሃይማኖት በምግባር ኮትኩቶ አሳደገው፡፡ ሥጋዊ ጥበብንም ፈረስ መጋለብን፣ ጦር መወርወርን በቅዱስ ፋሲለደስ ቤት ከእነ ፊቅጦርና ገላውዲዮስ ጋር እየኖረ ተማረ፡፡
የሰማዕቱ የቅዱስ ፋሲለደስ የወንድሙ ልጅ ስለሆነ በቤቱ እንደ ልጁ ይታይ ነበር፡፡ የፋሲለደስ ዘመዶቹም ሁሉ በቀናች ሃይመኖት የሚያምኑ የክርስቶስ ተከታዮች ናቸው፡፡ በግብፅ አገር ፍየል ይጠብቅ በነበረውና አግሪጳዳ በሚባለው ሰው ሰይጣን መጥቶ አደረበት፡፡ ወደ አንጾኪያም ሄዶ የፈረሶች ባልደረባ ሆነ፡፡ የአንጾኪያውም ንጉሥ ሲሞት ልጁ እርሱን ሲዘፍን አግኝታው ወደደችውና አገባችው አነገሠችውም፡፡ ስሙንም ዲዮቅልጥያኖስ ብላ ሰየመችው፡፡ እርሱም በመጀመሪያው ቀን በግዛቱ ውስጥ ባሉ አገሮች ሁሉ አብያተ ክርስቲያናት እንዲዘጉ፣ የጣዖት ቤቶች እንዲከፈቱና ሕዝቡም ጣዖታቱን እንዲያመልኩ አዘዘ፡፡ ይህንንም የንጉሡን ትእዛዝ ተቀብሎ የማይፈጽም ቢኖር ንብረቱ ተወርሶ በጽኑ ሥቃይ እንዲሠቃይና እንዲገደል በአዋጅ ጽፎ በሁሉም ግዛቶቹ አስተላለፈ፡፡
ከዚህም በኋላ ዲዮቅልጥያኖስ የክብርን ባለቤት ክርስቶስ ኢየሱስን ክዶ ጣዖት አምላኪ ሆኖ ከነገሠ በኋላ ክርስቲያኖችን እያሠቃየ ይገድል ጀመር፡፡ የተመረጡ የነገሥታት ልጆችንም ሁሉ በግዞት እየላከ እያሠቃየ ያስገድላቸው ጀመር፡፡ በዚህም ጊዜ ይህ ሰማዕት ቅዱስ እስጢፋኖስ ሰማዕትነትን ይቀበል ዘንድ ጌታችንን ለመነው፡፡ ጌታችንም የልቡን መሻት ይፈጽምለት ዘንድ ለሰማዕትነት መረጠው፡፡ ቅዱስ እስጢፋኖስም ወደ ዲዮቅልጥያኖስ ዘንድ ቀርቦ የክብርን ባለቤት ክርስቶስን ስለመካዱና ስለ ጣዖት አምልኮው በእጅጉ ነቀፈው፡፡ ጣዖታቶቹንም ረገመበት፡፡ ዲዮቅልጥያኖስም በንዴት ሰይፉን መዞ የቅዱስ እስጢፋኖስን አንገቱን ቆረጠው፡፡ የቅዱስ እስጢፋኖስም ራስ ለብቻዋ ከወደቀችበት ሆና በሰው አንደበት መናገር ጀመረች፡፡ ዲዮቅልጥያኖስ ገና ወደፊት ይሠራው ዘንድ ስላለው ግፍና መከራ ትንቢት ተናገረች፡፡ በመጨረሻም ንጉሡ ዲዮቅልጥያኖስ ዐይኖቹ ታውረው ምጽዋትን እስከሚለምን ድረስ የተዋረደ እንደሚሆንና እንደሚጠፋ አሁንም ትንቢትን ተናገረች፡፡
በዚህም ትንቢት መሠረት ዲዮቅልጥያኖስ በልዳ ሀገር በምትገነው በሰማዕቱ በቅዱስ ጊዮርጊስን ቤተ ክርስቲያን ውስጥ ለጥፋት ገብቶ ሳለ ቤተ ክርስቲያኑን ሊያፈረስ ሥዕሉን ቀዶ በመንበሩ ላይ እቀመጣለሁ ሲል ወዲያው የታዘዘ መቅሰፍት መጥቶ መታውና 7 ዓመት ያህል ዐይኖቹ ታውረው አእምሮውንም አጥቶ አብዶ ቁራሽ እንጀራን እየለመነ ከኖረ በኋላ በመጨረሻ ክፉ አሟሟት ሞቷል፡፡ (ይኸውም ኅዳር 7 ቀን በሚነበበው ስንክሳርና በገድለ ቅዱስ ጊዮርጊስ ላይ በሰፊው ተጠቅሷል፡፡)
የመጥምቁ ዮሐንስ ራስ ንጉሥ ሄሮስን እንደዘለፈችው የቅዱስ እስጢፋኖስም ራስ ዲዮቅልጥያኖስን ዘለፈቸው፡፡ ብዙዎችም እየመጡ ይህንን ተመከቱ፡፡ በሕዝቡም ፊት ስለረከሱ ጣዖታቶቹ ዘለፈችው፤ አሳፈረችውም፡፡ በምድር ውስጥም ቀብረው እንዲደፍኗት አዘዘ፡፡ በምድር ውስጥም ደፍነዋት ሳለ ዝም አላለችም ሦስት ቀን ያህል አብዝታ ተናገረች እንጂ፡፡ ከተቀበረችበት አውጥቶም በሳጥን አድርጎ ወደ ባሕር ውስጥ ጣላት፡፡ የታዘዘ መልአክም መጥቶ ከባሕሩ አውጥቶ ዳር ላይ አስቀመጣት፡፡ እናቱም ወስዳ የሥቃይ ዘመን እስኪያልፍ ድረስ በድብቅ አኖረቻትና የሥቃዩ ዘመን ካለፈ በኋላ ቤተ ክርስቲያን ሠርተውለት በዚያ አኖሩት፡፡ የቅዱስ እስጢፋኖስም አስክሬን ድንቅ ድንቅ የሆኑ ተአምራትን እያደረገ ለሕሙማን ፈውስ ሆነ፡፡
የአንጾኪያው ሰማዕት ቅዱስ እስጢፋኖስ ረድኤት በረከቱ ይደርብን፣ በጸሎቱ ይማረን!
+ + +
አቡነ ሊዋርዮስ፡- ከታናሽነቱ ጀምሮ የቤተ ክርስቲያንን ትምህርት ተምሮ መንኩሶ ገዳም በመግባት በታላቅ ተጋድሎ የኖረ ታላቅ ጻድቅ ነው፡፡ ምግባር ሃይማኖቱን፣ ደግነት ትሩፋቱን አይተው አባቶች በሐዋርያት አለቃ በቅዱስ ጴጥሮስ ወንበር ላይ በእግዚአብሔር ፈቃድ የሮሜ አገር ሊቀ ጳጳሳት አድርገው ሾሙት፡፡ እርሱም ከተሾመ በኋላ በበጎ ጎዳና እየተጓዘ እግዚአብሔርን አገለገለ፡፡ ምእመናንንም በበጎ አጠባበቅ ጠበቃቸው፡፡ ሕገ እግዚአብሔርንም እያስተማረ በንስሓ መለሳቸው፡፡
ታላቁ ቆስጠንጢኖስ በሞት ባረፈ ጊዜ ከሃዲው ዑልያኖስ ነገሠና እግዚአብሔር እስካጠፋው ድረስ ክርስቲያኖችን እያሠቃየ ይገድል ነበር፡፡ ይህም ከሃዲ ዑልያኖስ ለቆስጠንጢኖስ የአባቱ እኅት ልጅ ነው፡፡ መንግሥትንም በያዘ ጊዜ አብያተ ክርስቲያናት ተዘግተው በምትካቸው የጣዖታት ቤቶች እንዲከፈቱና ሕዝቡም በጣዖታቱ እንዲያምን አዋጅ አስነገረ፡፡ ለትእዛዙ ያልተገዙትን ክርስቲያኖችን እያሠቃየ ይገድል ጀመር፡፡ ይህም ታላቅ አባት አቡነ ሊዋርዮስ ከሮሜ አገር ወደ ቂሣርያ መጥቶ ከአቡነ ባስልዮስ ጋር ተገናኘና ንጉሡን ሄደው ከስሕተቱና ከክህደቱ መክረው ይመልሱት ዘንድ ሁለቱ ቅዱሳን ተስማሙ፡፡ እነርሱም ከታናሽነታቸው ጀምረው እየተማሩ ከእርሱ ጋር በአንድነት ያደጉ ናቸውና፡፡
አቡነ ሊዋርዮስና አቡነ ባስልዮስ ወደ ንጉሡ ዘንድ ሄደው ከክህደቱ እንዲመለስ ሲያስተምሩትና ሲመክሩት እርሱ ግን በጌታችን ላይ በመሳለቅ ‹‹የጠራቢውን ልጅ ወዴት ተዋችሁት?›› አላቸው፡፡ ቅዱስ ባስልዮስም ‹‹አንተን በሲኦል ይቀበልህ ዘንድ ሣጥን ሊሠራልህ ተውነው›› ብሎ መለሰለት፡፡ ንጉሡም በቅዱስ ባስልዮስ መልስ ተበሳጭቶ ሁለቱን ቅዱሳን ወስዶ ከወህኒ ቤት ጣላቸው፡፡ ቅዱሳኑም የሰማዕቱን የቅዱስ መርቆሬዎስን ሥዕል አግኝተው በፊቱ እያለቀሱ ንጉሡ በጌታችን ላይ ያደረሰውን መሳለቅ አሳሰቡ፡፡ ወዲያውም እንቅልፍ መጣባቸውና ዐረፍ እንዳሉ ቅዱስ መርቆሬዎስ ለአቡነ አቡነ ሊዋርዮስ በራእይ ተገለጠላቸውና ‹‹ሰማይና ምድርን በፈጠረ በሕያው ፈጣሪዬ ላይ እንዲሳለቅ ይህን ከሃዲ በሕይወት ይኖር ዘንድ አልተወውም›› ሲል ነገራቸው፡፡ አቡነ ሊዋርዮስም ያዩትን ራእይ ለአቡነ ባስልዮስ ነገሯቸው፡፡ በዚያን ጊዜ ሥዕሉን ከቦታው አጡት፣ ሥዕሉ ከሃዲው ንጉሥ ዑልያኖስ ካለበት ሄደና፡፡ ንጉሡንም ሥዕሉ በጦር ወግቶ ገደለውና ወደ ቦታው ተመልሶ ተሰቀለ፡፡ ከጦሩም ጫፍ ደም ይንጠባጠብ ነበር፡፡

በእንተ ቅዱሳን ኅሩያን (ከገድላት አንደበት)

18 Oct, 13:16


አቡነ ሊዋርዮስና አቡነ ባስልዮስም ይህንን ድንቅ ተአምር ባዩ ጊዜ ‹‹መፈራትንና ባለሟልነትን የተመላህ የኢየሱስ ክርስቶስ ምስክር ሆይ! ዑልያኖስን ገደልከውን?›› ብለው ጠየቁት፡፡ ሥዕሉም ‹‹አዎን›› እንደሚል ዘንበል አለ፡፡ እነዚህም ቅዱሳን እጅግ ደስ ተሰኙ፡፡ ከዚህም በኋላ ጌታችንን የሚወደው ዩማንዮስ ነገሠና እነዚህን ሁለት ቅዱሳን ከእሥር ቤት አወጣቸውና ወደቦታቸው መለሳቸው፡፡ አቡነ ሊዋርዮስም አርዮሳውንን ከክርስቲያኖቹ እየለየ በማሳደድ መድረሻ ያሳጣቸው ነበር፡፡ መልካም ጉዞውንም ከፈጸመ በኋላ እግዚአብሔርን አገልግሎ ከሰባት ዓመት የሹመት ዘመኑ በኋላ በዚህች ዕለት በሰላም ዐረፈ፡፡ ረድኤት በረከቱ ይደርብን፣ በጸሎቱ ይማረን!
+ + +
አቡነ አትናስዮስ፡- ይህም ቅዱስ ከታናሽነቱ ጀምሮ መነኮሰ፡፡ ባሕታዊ ሆኖ የሚያገለግል ቅን፣ ትሑት፣ በበጎ ሥራ ሁሉ ፍጹም የሆነ ተጋዳይ ነው፡፡ ሊቀ ጳጳሳት አባ ሚካኤል ካረፈ በኋላ ኤጲስቆጶሳት ተሰብስበው አቡነ አትናስዮስን ሊቀ ጵጵስና ይሾሙት ዘንድ መረጡት፡፡ ፈጥኖ እንዲመጣና ከእነርሱ ጋር ይህን አባት እንዲሾም ወደ ሀገረ ሰልቅ ሊቀ ጳጳስ ወደ አባ እልመፍርያን መልአክትን ላኩ፡፡ ነገር ግን እርሱ መምጣትን ዘገየ፡፡ ኤጲስቆጶሳቱም ሃምሳ ቀናትን ያህል ጠብቀው አቡነ አትናስዮስን በእግዚአብሔር ፈቃድ በአንጾኪያ አገር ሊቀ ጳጳሳት አድርገው ሾሙትና ሁሉም ወደ ሀገረ ስብከታቸው ተመለሱ፡፡
ከዚህም በኋላ አባ እልመፍርያን መጣና ወደ ሶርያ አገር ድንበር ደርሶ ከአንድ ጳጳስ ጋር ተገናኘ፡፡ ያም ጳጳስ እርሱ ከመምጣት በዘገየ ጊዜ አቡነ አትናስዮስን እንደሾሙት ነገረው፡፡ አባ እልመፍርያንም ይህንን በሰማ ጊዜ ተቆጥቶ ‹‹በእኛና በእናንተ መካከል ያለውን ሕግ እንዲህ ትሽራላችሁን?›› በማለት ‹‹በቁርባንም ቢሆን ወይም በማዕጠንት የአባ አትናስዮስን ስም የሚጠራውን ሁሉ አውግዣለሁ›› ብሎ ወደ ሀገሩ ተመለሰ፡፡
አቡነ አትናስዮስም ይህን በሰማ ጊዜ እጅግ አዘነና ረዳቱን ጠርቶ ‹‹ልቤ ትመርቅህ ዘንድ ታዘዝልኝመ ሕዝቡ የፈለጉኝ እንደሆነ ‹በዋሻ ሱባዔ ውስጥ ነው› በላቸው፡፡ እኔ ወደ አንድ ቦታ ሄጄ አንድ ዓመት ያህል እቆያለሁና አንተም ሊሆን የሚገባውን ሥራ ሁሉ እዘዛቸው›› አለው፡፡ ከዚህም በኋላ አቡነ አትናስዮስ ተራ የድኃ ልብስ ለብሶ በሥውር ወጣና በእግሩ ሄዶ ሀገረ ሰልቅ ደረሰ፡፡ አዚያ እንደደረሰም የሊቀ ጳጳስ የአባ እልመፍርያንን ደጅ አንኳኳ፡፡ ደጅ ጠባቂውም ‹‹ምን ትፈልጋለህ?›› አለው፡፡ ቅዱሱም ‹‹የአባ እልመፍርያንን በረከት መቀበል እሻለሁ›› አለውና አስገብቶ ከአባ እልመፍርያን ጋር አገናኛቸው፡፡ አባ እልመፍርያንም አቡነ አትናስዮስን ‹‹ከወዴት ነህ?›› አለው፡፡ አቡነ አትናስዮስም ‹‹ከሶርያ አገር ነኝ፣ የዕለት ምግብና ልብስ አጥቼ መጣሁ፤ በእርስዎ ጥላ ሥር ሆኜ ላገለግልዎ እሻለሁ›› ብሎ መለሰ፡፡ ዳግመኛም አባ እልመፍርያን ‹‹ቄስ ወይም ደግሞ ዲያቆን ነህ?›› ብሎ አቡነ አትናስዮስን ሲጠይቀው እርሱም ‹‹አይደለሁም›› አለ፡፡ አባ እልመፍርያንም ሹሙን ጠርቶ አቡነ አትናስዮስን ከመነኮሳቱ ጋር እንዲያኖረው አዘዘው፡፡
ከዚህም በኋላ አቡነ አትናስዮስ የሊቀ ጳጳሱን የአባ እልመፍርያንን የቤት ውስጥ ሥራ እየሠራ የፈረሶችንና የበቅሎዎችን ፍግ እስከሚጠርግ ድረስ የሚሠራ ሆነ፡፡ ይፈጫል፣ ውኃ ይቀዳል፣ እንጀራ ይጋግራል፣ ወጥ ይሠራል፣ ምንም ምን ሥራ አይቀረውም ነበር፡፡ ለመነኮሳቱም ሁሉ ቤቶቻቸውን ይጠርግላቸዋል፣ ውኃ ይቀዳላቸዋል፣ የሚያስፈልጋቸውን ሁሉ ይሠራላቸዋል፡፡ መነኮሳቱም እጅግ አድርገው ወደዱት፡፡ ስለ ምግባር ትሩፋቱም አቡነ አትናስዮስን ዲቁና ይሾመው ዘንድ ሊቀ ጳጳሱን አባ እልመፍርያን ማለዱት፡፡ ሊቀ ጳጳሱም እሁድ ቀን ወደ ቤተ ክርስቲያን ገብቶ አቡነ አትናስዮስን ዲቁና ሊሾመው ሲል እርሱ ግን አልቅሶ ‹‹አባቴ ተውኝ እኔ ድኃ ነኝና›› አለው፡፡ ባልተወውም ጊዜ ‹‹አባቴ ይቅርታ አድርጉልኝ ይህስ ዲቁና አለኝ›› አለው፡፡ ሊቀ ጳጳሱም ትዕግሥቱን፣ ተጋድሎውንና ትሕትናውን ተመልክቶ አደነቀና በዲቁና እንዲያገለግል አዘዘው፡፡ አቡነ አትናስዮስም በዲቁና እያገለገለ ሰባት ወር ተቀመጠ፡፡
ዳግመኛም ሊቀ ጳጳሱ የአቡነ አትናስዮስን ትጋትና አዋቂነቱን ተመልክቶ ቅስና ሊሾመው ወደደ፡፡ እሁድ ቀንም ወደ ቤተ ክርስቲያን ጠርቶ ‹‹መንፈስ ቅዱስ ሊሾምህ ጠርቶሃል›› አለው፡፡ አቡነ አትናስዮስም በዚህ ጊዜ አለቀሰና እንዲተወው ለመነው፡፡ እንዳልተወውም ባወቀ ጊዜ ‹‹አባቴ ይቅር በለኝ እኔ ቄስ ነን›› አለ፡፡ ሊቀ ጳጳሱና መነኮሳቱም ሁሉ ይህንን ሲሰሙ አደነቁ፡፡ ዳግመኛም ሊቀ ጳጳሱ አባ እልመፍርያን የአቡነ አትናስዮስን አስተዋይነቱን፣ ተጋድሎውን፣ ምግባር ትሩፋቱን መልካም አገልግሎቱን አይቶ ጳጳስዋ ለሞተባት ለአንዲት አገር ጳጳስ አድርጎ ይሾመው ዘንድ ወደደና ጳጳሳትን፣ ኤጲስቆጶሳትን፣ ቀሳውስትን፣ ዲያቆናትን ሁሉ ሰብስቦ አቡነ አትናስዮስን በመካከላቸው አቅርቦ ‹‹የዚህች አገር ጳጳስ አድርጎ መንፈስ ቅዱስ መርጦሃል›› አለው፡፡ አቡነ አትናስዮስም በዚህ ጊዜ አምርሮ በማልቀስ እንዲተውት ለመናቸው፡፡ እንደማይተውት ባወቀ ጊዜ ግን የአንጾኪያ አገር ሊቀ ጳጳሳት መሆኑን ነገራቸው፡፡ የአመጣጡንም ምሥጢር ገለጠላቸው፡፡
በዚያንጊዜ አባ እልመፍርያን እጅግ ደንግጦ አክሊሉን ከራሱ ላይ አውርዶ በምድር ላይ ወደቀ፡፡ ለረጅም ጊዜ እንደሞተ ሆነ፡፡ በተነሣም ጊዜ ‹‹ወንድሞቼ እስኪ የማደርገውን ንገሩኝ እሳት ከሰማይ ወርዶ እንዳይበላኝ ምድርም አፏን ከፍታ እንዳትውጠኝ እፈራለሁና ጌታዬ የአንጾኪያ ሊቀ ጳጳሳት ውኃ እየቀዳ የፈረሶችና የበቅሎዎች ጉድፍ እየጠረገ በቤቴ ውስጥ እንደባሪያ ሲያገለግለኝ ኖሯልና ወዮልኝ ወዮታ አለብኝ›› እያለ ጮኸ፡፡ ጳጳሳቱና ሕዝቡም ይህንን በሰሙ ጊዜ ከአቡነ አትናስዮስ እግር ሥር ወደቀው ሰገዱለት፡፡ የክህነት ልብሶችንም ያለብሱት ዘንድ ተፋጠኑ፡፡ በመንበርም ላይ አስቀምጠው ከመንበሩ ጋር ተሸክመውት ሦስት ጊዜ አክዮስ አክዮስ አክዮስ (ይገባዋል ማለት ነው) እያሉ ቤተ ክርስቲያኑን አዙረው ወደ መቅደስ አስገቡት፡፡ ቀድሶ አቆረባቸው፣ ሕዝቡንና እነርሱንም ባረካቸው፡፡
በማግስቱ አባ እልመፍርያን አባ አትናስዮስን በክብር በቅሎ አስቀምጦ እርሱና ጳጳሳቱ በእግራቸው እየተከተሉት ወደ አንጾኪያ አገር አጅበው ወሰዱት፡፡ አባ አትናስዮስ ግን አባ እልመፍርያንን ‹‹አንተም በበቅሎ ተቀመጥና በአንድነት እንሂድ›› አለው፡፡ አባ እልመፍርያን ግን ‹‹ጌታዬ ለእኔ አይገባኝም፣ አንተ በእግርህ ወደ አገሬ እንደመጣህ እንዲሁ እኔም በእግሬ ወደ አገርህ አገርስሃለሁ›› አለው፡፡ የአንጾኪያ አገር ጳጳሳትም የአባ አትናስዮስን መምጣት በሰሙ ጊዜ ከሕዝቡ ሁሉ ጋር ወጥተው ተቀበሉትና ወደ ሹመቱ መንበር አስገቡት፡፡ ለአባ እልመፍርያንም ሁለተኛ ወንበር አድርገው በክብር አስመጡት፡፡ ደስ ብሏቸው በዓልን ካከበሩ በኋላ በፍቅር አንድነት ወደ አገራቸው ተመለሱ፡፡

በእንተ ቅዱሳን ኅሩያን (ከገድላት አንደበት)

18 Oct, 13:16


የአቡነ አትናስዮስ ረድኤት በረከቱ ይደርብን፣ በጸሎቱ ይማረን!
+ + +
ሐዋርያው ቅዱስ ቶማስ በሕንድ አገር ያደረገው ድንቅ ተአምር፡- ሐዋርያው ቶማስ እንደ ባርያ ተሸጦ ወደ ሕንድ አገር ከአበኒስ ጋር በገባ ጊዜ አበኒስ ወደ ንጉሥ ጎንዶፎር አቀረበውና ሐናፂ እንደሆነም ለንጉሡ ነገረው፡፡ ንጉሡ ሐዋርያውን ሲጠይቀው ቅዱስ ቶማስም ‹‹እኔ የጥርብ ሥራን ሁሉ ቀንበሮችን፣ ሚዛኖችን፣ ሠረገላዎችን፣ መርከቦችን፣ በግንብ ሥራም ቤተ መንግሥትን እሠራለሁ›› አለው፡፡ ንጉሡም በዚህ እጅግ ደስ ብሎት ‹‹በል ቤተ መንግሥት ሥራልኝ›› አለው፡፡ ከሚሻውም ቦታ ወሰደውና በምን ወር ትሠራለህ?›› አለው፡፡ ሐዋርያውም ከኅዳር መባቻ ጀምሬ በሚያዝያ ወር እጨርሳለሁ›› አለው፡፡ ንጉሡም አድንቆ ‹‹ሕንፃ ሁሉ በበጋ ይታነጻል አንተ ግን እንዴት በክረምት ወር ታንጻለህ?›› ሲለው ሐዋርያውም ‹‹ለዚህ ችግር የለውም›› አለው፡፡
ሐዋርያውም ከዚህ በኋላ ብዙ ገንዘብ ከንጉሡ ጎንዶፎር ተቀብሎ ሄደና ‹‹የንጉሥን መልሼ ለንጉሥ እሰጣለሁ›› ብሎ ገንዘቡን ሁሉ ለድኆችና ጦም አዳሪዎች መጸወተው፡፡ ዳግመኛም ‹‹የቤተ መንግሥቱ ግድግዳው አልቋል ነገር ግን ጣሪያው ቀርቷል›› ብሎ ለንጉሡ ላከ፡፡ ንጉሡም ተጨማሪ ገንዘብ ሲልክለት ቅዱስ ቶማስ እንደልማዱ አሁንም ወስዶ መጸወተው፡፡
ከዚህም በኋላ ንጉሡ የተሠራለትን ቤተ መንግሥቱን ለማየት ሲመጣ ቦታው ባዶ ነው፡፡ ገንዘቡም ሁሉ ለድኆችና ጦም አዳሪዎች ምጽዋት ሆኖ እንደተበተነ በሰማ ጊዜ እጅግ ተናዶ ቅዱስ ቶማስን በሚገድለው ነገር እስኪመከር ድረስ ካመጣው ከአበኒስ ጋር አሠረው፡፡ በዚያችም ሌሊት የንጉሡ ወንድም ጋዶን በድንገት ታመመና ሞተ፡፡ መላእክት ነፍሱን ወስደው ተመሳሳይ የሌለው በወርቅና በዕንቁ የተሠራ ቤተ መንግሥትን አሳዩት፡፡ ጋዶንም መላእክቱን ‹‹ይህ ቤተ ምንግሥት የማነው?›› ሲላቸው፡፡ እነርሱም ‹‹ሐዋርያ ቶማስ ለንጉሥ ጎንዶፎር የሠራለት ሰማያዊ ቤተ መንግሥት ነው›› አሉት፡፡ ከዚህም በኋላ ጋዶን ከሙታን ተለይቶ ተነሣና ያየውን ሁሉ ለንጉሥ ወንድሙ ነገረው፡፡ በዚያን ጊዜም ቅዱስ ቶማስን ከእስር ቤት አወጡትና በክብር ሰገዱለት፡፡ ንጉሡና የሀገሩ ሰዎችም አምነው በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም ተጠመቁ፡፡ ሐዋርያው ቅዱስ ቶማስም ከባረካቸው በኋላ ወደሌላ ሀገር ሄደ፡፡
የሐዋርያው የቅዱስ ቶማስ ረድኤት በረከቱ ይደርብን፣ በጸሎቱ ይማረን!

በእንተ ቅዱሳን ኅሩያን (ከገድላት አንደበት)

18 Oct, 13:16


አንድ አምላክ በሚሆን በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም አሜን
ጥቅምት 9-እግዚአብሔር በሦስትነቱና በአንድነቱ የተገለጠላቸው በስብከታቸው "የሐዋርያት አምሳል" የተባሉት ጻድቁ አቡነ መዝገበ ሥላሴ ዕረፍታቸው ነው፡፡
+ በከሃዲው ዲዮቅልጥያኖስ ዘመነ መንግሥት በአንጾኪያ አገር የሰማዕታት መጀመሪያ የሆነው ቅዱስ እስጢፋኖስ በሰማዕትነት ዐረፈ፡፡
+ ሐዋርያው ቅዱስ ቶማስ በሕንድ አገር ድንቅ ተአምር ያደረገበት ዕለት ነው፡፡
+ የከበሩ አባ ሊዋርዮስ ዕረፍታቸው ነው፡፡
+ አቡነ አትናስዮስ በዓለ ዕረፍቱ ነው፡፡
+ የኢትዮጵያው ጻድቅ ንጉሥ የዐፄ ዳዊት የዕረፍታቸው መታሰቢያ ነው፡፡
አቡነ መዝገበ ሥላሴ፡- አቡነ መዝገበ ሥላሴ በታሪካዊነቱና በያዛቸው ድንቅ ድንቅ ቅርሶች ከሚታወቀውና ኢትዮጵያዊውን ሀሳበ ዘመን በመቀመር ከሚታወቀው ከእውነተኛው የብህትውና ቦታ ከደብረ ገሪዛን ቅድስት ማርያም ጉንዳጉንዶ ገዳም የተገኙ ታላቅ አባት ናቸው፡፡ እነ አቡነ አበከረዙንን ጨምሮ የባሕረ ሐሳብ ፍልስፍናና የሥነ ጽሑፍ ማዕከል ከሆነው ከዚህ ገዳም የወጡ ገድል ተጽፎላቸው፣ ታቦት በስማቸው የተቀረጸላቸው ከ17 በላይ ታላላቅ ቅዱሳን አሉ፡፡ አቡነ መዝገበ ሥላሴም ከእነዚህ የበቁ ቅዱሳን ውስጥ አንዱ ናቸው፡፡ አባታቸው ሀብተ ጽዮን እናታቸው ማርያም ሞገሳ ሲባሉ እነርሱም በእግዚአብሔር ፊት ቅኖች ነበሩ፡፡ ማርያም ሞገሳ ዕለት ዕለት አምሃ(ስጦታ) እየያዘች ወደ ቤተ ክርስቲያን እየሄደች ስትጸልይ በአንደኛው ዕለት የታዘዘ መልአክ መጥቶ ‹‹በእግዚአብሔር ፊት ሞገስ ያገኘና የተባረከ ልጅ ትወልጃለሽ›› ብሎ አበሰራት፡፡እርሷም ‹‹ከማኅፀኔ እንደፀሐይ የሚያበራ ልጅ ሲወጣ አየሁ›› አለች፡፡ በዚህም መሠረት አቡነ መዝገበ ሥላሴ በምሥራቃዊ ትግራይ ዞን በገላውዴዎስ ዘመነ መንግሥት በ1532 ዓ.ም ተወለዱ፡፡ በ40ኛ ቀናቸውም ሲጠመቁ ሰጊድለአብ ተባሉ፡፡ ሰጊድለአብ ከዕለታት በአንደኛው ቀን የእግዚአብሔር መልአክ ከእናታቸው እቅፍ ውስጥ ነጥቆ ወስዶ ደብረ ከስዋ (ደብረ ገሪዛን) ጉንዳጉንዶ ቅድስት ማርያም ገዳም አደረሳቸው፡፡ ወደ ቅድስተ ቅዱሳኑም ካስገባቸው በኋላ በውስጥ የነበሩትን ንዋያት ሁሉ እያሳየ ‹‹አንተ ሕፃን ሆይ! ዕወቅ ይህ የምታየው ሁሉ የአንተ ነው፣ ትጠብቀውም ዘንድ እግዚአብሔር ሰጥቶሃል፡፡ ደግሞም የክርስቶስን በጎች ትጠብቅ ዘንድ ተሰጥቶሃልና ፈጽሞ ደስ ይበልህ›› አላቸውና ፈጥኖ ወደ እናታቸው እቅፍ መለሳቸው፡፡ ዕድሜአቸውም ለትምህርት ሲደርስ ወደ ጉንዳጉንዶ ተመልሰው የሁሉንም መጻሕፍትን ምሥጢር ጠንቅቀው ተማሩ፡፡ በገዳሙም የምንኩስናን ሥራ እየሠሩ በተጋድሎ ኖሩ፡፡ ክብርት እመቤታችንም ተገልጻላቸው ‹‹ልጄ በተፈቀደልህ ተጋድሎ አሰልጥኖሃልና ጨክን፣ በርታ እኔም ከአንተ አልለይም›› አለቻው፡፡ ከመነኮሱም በኋላ ስማቸው ‹‹አቡነ መዝገበ ሥላሴ›› ተባሉ፡፡
አቡነ መዝገበ ሥላሴ ስብከተ ወንጌልን በመላ ሀገራችን በማስፋፋት ብዙ የደከሙ ታላቅ አባት ናቸው፡፡ በዚህም ምክንያት ‹‹የሐዋርያት አምሳል›› ተብለዋል፡፡ የገዳሙ አበምኔት ሲያርፉ መነኮሳቱ በፈቃደ እግዚአብሔር አቡነ መዝገበ ሥላሴን ይዘው በግድ አበምኔትነት ሾሟቸው፡፡ እሳቸውም ከተሾሙ በኋላ በመላ ሀገራችን ተዘዋውረው ወንጌልን ሰብከዋል፡፡ ብዙ ድውያንን ፈውሰዋል፣ ሙታንን አንሥተዋል፡፡ በዓታቸውንም በማጽናት በጸሎት ተወስነው የዐይኖቻቸው ቅንድቦች እስኪላጡ ድረስ ጉንጮቻቸውም እስኪቀሉ ድረስ በጸሎት ይተጉ ነበር፡፡ 40 ቀንና 40 ሌሊትም ይጾማሉ፡፡ ስግደታቸውም በቀንና በሌሊት ያለ እረፍት እንደመንኮራኩር ፈጣን ሆነ፡፡ ወዛቸውና ዕንባቸው አንድ ላይ ተቀላቅሎ እንደጅረት እስኪፈስ ድረስ በጭንቅ ተጋድሎ እንደኖሩ ገድላቸው ይናገራል፡፡ እመቤታችንም ብዙ ጊዜ እየተገለጠችላቸው ከህመማቸው እየፈወሰች ታበረታቸው ነበር፡፡ ከዕለታትም በአንደኛው ቀን አቡነ መዝገበ ሥላሴ ራእይ ተመለከቱ፡፡ እነሆም ውበታቸው የሚያስገርም፣ መልካቸውም የሚያስደንቅ፣ የምስጋና ነፀብራቅ የከበባቸው፣ የራሳቸው ፀጉር ነጭ የሆነ ሦስት ወፎችን ተመለከቱ፡፡ አባታችንም አንድ ጊዜ ሦስት ሌላ ጊዜ ደግሞ አንድ ሲሆኑ ተመልክተው ፈጽሞ አደነቁ፡፡ እንዲህ እያደነቁ ሳለ እግዚአብሔር በቃሉ ጠርቶ ካነጋገራቸው በኋላ ብዙ ምሥጢራትን ነገራቸው፡፡ ለመረጣቸው ቅዱሳን እንዲህ መገለጥ ለእግዚአብሔር ልማዱ ነውና ለአባታችን ለአዳም፣ ለሄኖክ፣ ለኖኅ፣ ለአብርሃም በልዩ ልዩ ህብር ተገልጧል፡፡ ኦ.ዘፍ 3፡10፣ 5፡24፣ 6፡13፣ 18፡1 ፡፡ ለሕዝቅኤልም በኮበር ወንዝ፣ ለዳንኤል በሱሳ ግንብ፣ ለኢሳይያስ ሱራፌል እያመሰገኑት ተገልጦላቸዋል፡፡ ሕዝ 1፡1፣ ዳን 8፡1-3፣ ኢሳ 6፡1-3፡፡ አቡነ መዝገበ ሥላሴ በዘመን ደረጃ በኋለኛው ዘመን የተነሡ አባት ይሁኑ እንጂ በሰጡት ሐዋርያዊ አገልግሎትና ገንዘብ ባደረጉት የተጋድሎ ጽናት የከበሩ ቅዱሳን ሐዋርያትን መስለዋቸዋል፡፡ የታዘዘ መልአክ ወደ መንግሥተ ሰማያት ነጥቆ ወስዶ ማደሪያቸውን አሳይቷቸው መልሶ ወደ ምድር ካመጣቸው በኋላ የዕረፍታቸው ጊዜ እንደደረሰ ነገራቸው፡፡ ‹‹በሰኔ ወር ታርፋለህ›› ቢላቸው ‹‹በሰኔማ ልጆቼ ተዝካሬን ማድረግ አይችሉም›› አሉት፡፡ መልአኩም መልሶ ‹‹ዕረፍትህ በሐምሌ ይሁን›› ቢላቸው ጻድቁ አሁንም ‹‹አይሆንም›› ብለው ተከራከሩ፡፡ በነሐሴም እንደዚያው ሆነ፡፡ መልአኩም መስከረምን አሳልፎ በጥቅምት እንደሚያርፉ ነግሯቸው ዐረገ፡፡ ከዚህም በኋላ ለስም አጠራሩ ምስጋና ይግባውና ጌታችን ቅድስት እናቱን፣ መላእክትን፣ ቅዱሳን ጻድቃን ሰማዕታትን ሁሉ አስከትሎ መጥቶ ‹‹አንተ የዓሥራ አንደኛው ሰዓት ቅጥረኛ ወዳጄ ሆይ! (ከቅዱሳን ሁሉ በኋላ የተነሣህ-ማቴ 20፡1-5) የምስራች እነግርህ ዘንድ የድካምህም ዋጋ እሰጥህ ዘንድ መጥቻለሁ፡፡ እነሆ ከጠዋት ጀምሮ ከደከሙት ጋር አንድ አድርጌሃለሁ፡፡ ከአንተም ጋር ቃልኪዳን ገብቻለሁ፣ ስምህን በእምነት የጠራ፣ መታሰቢያህን ያደረገ፣ በጸሎትህም የታመነ እስከ ሰማንያ ሺህ ስድስት መቶ (80,600) ነፍሳት ዓሥራት ይሁኑህ…›› በማለት ቃልኪዳን ከገባላቸው በኋላ ወደ ሰማያት ዐረገ፡፡ በዚያን ጊዜም አቡነ መዝገበ ሥላሴ ፊታቸው እንደፀሐይ አበራና ጥቅምት 9 ቀን ከሌሊቱ በ6 ሰዓት እንደመልካም እንቅልፍ ዐረፉ፡፡ መላ ዘመናቸው 115 ሲሆን የደብረ ገሪዛን ጉንዳጉንዶ ቅድስት ማርያም ገዳም አበምኔት ሆነው ከመሾማቸው በፊት 62 ዓመት፣ ከተሾሙበት ጊዜ እስከ ዕለተ ዕረፍታቸው ድረስ 53 ዓመት ነው፡፡ መካነ መቃብራቸው እዚያው የደብረ ገሪዛን ጉንዳጉንዶ ቅድስት ማርያም ገዳም ይገኛል፡፡ በጉንዳጉንዶና አዲግራት በሚገኘው ገዳማቸው ውስጥ በስማቸው የፈለቁ ብዙ ፈዋሽ ጠበሎች አሉ፡፡ አዲግራት የሚገኘው ገዳማቸው ውስጥ ያለው ጠበል የትኛውንም በሽታ በአስቸኳይ ፈውስ በመስጠት ይታወቃል፡፡ ተጠማቂው ሰው የማይድንም ከሆነ ቶሎ ይሞታል እንጂ ከ7 ቀን በላይ አይቆይም፡፡ ጻድቁ ብዙ የተጋደሉበት ይህ ገዳም በግራኝ አህመድ ዘመን 44 ጽላቶች ተሰውረውበታል፡፡ ዮዲት ጉዲትም ልታገኘው ያልቻለችው ታላቅ ገዳም ነው፡፡ በአንድ ወቅት ከሃዲያን አሕዛብ ጦረኞች ወደ ገዳሙ ሲወጡ በተአምራት ወደ ፅድ ዛፍነት ተለውጠዋል፡፡ ፅዶቹ አሁንም ድረስ በገዳሙ ክልል ውስጥ የሚገኙ ሲሆን ፅዶቹን በእሳት አቃጥለው ከሰል ቢያደርጓቸው ደም ሆነው ይፈሳሉ እንጂ ፈጽሞ ከሰል መሆን አይችሉም፡ ፡ (ገድለ አቡነ መዝገበ ሥላሴ)

በእንተ ቅዱሳን ኅሩያን (ከገድላት አንደበት)

18 Oct, 03:05


‹‹በመቃብሩ ላይ ወድቃችሁ ይቅር በለን በሉት››

አባ ኪሮስ በጌታችን ትእዛዝ ወደ ሳት ገዳም በሄደ ጊዜ በቤተ ክርስቲያኒቱን ሲሳለማት የእመቤታችንን ሥዕል ተመለከተና ከዐይኖቹ ዕንባ እያፈሰሰ ‹‹እመቤቴ ሆይ አስቢኝ›› አላት፡፡ ሥዕሊቱም አፍ አውጥታ በሰው አንደበት ‹‹ኪሮስ ሆይ መምጣትህ መልካም ነው፣ ከዚህ ግን አልፈህ ወደ ሌላ ቦታ አትሂድ የአባትህን ዐፅም ትጠብቅ ዘንድ ይገባሃል›› አለችው፡፡ እርሱም ይህን ሰምቶ በፊቷ 700 ሰግደትን ሰገደ፡፡

ከዚኽም በኋላ አባ ኪሮስ በዚያ በተናቀ ቦታ ላይ በጽኑ ሕማም የታመመ ሰውን አገኘ፡፡ በታመመውም ሰው ራስጌ ቅዱስ ሚካኤል፣ በግርጌው ቅዱስ ገብርኤል፣ በቀኙ ቅዱስ ሩፋኤል፣ በግራው ቅዱስ ሰዳካኤል ሆነው በክንፋቸው ጋርደው ሲጠብቁት አገኛቸው፡፡ ከሰውም እነርሱም ማንም ያያቸው የለም፡፡ ለአባ ኪሮስም ሰላምታ በሰጡት ጊዜ እርሱም እጅግ አድንቆ ‹‹በልዕልና ነዋሪዎች ሆይ! ከዚህ ለምን ተቀመጣችሁ?›› አላቸው፡፡ እነርሱም ‹‹ይህን ድኃ እንጠብቀው ዘንድ እግዚአብሔር አዞናል›› አሉት፡፡ አባ ኪሮስም ‹‹እስከመቼ ነው የምትጠብቁት?›› ሲላቸው ቅዱሳን መላእክቱም ‹‹እግዚአብሔር እስኪያሳርፈው ድረስ›› አሉት፡፡ አባ ኪሮስም ወደ ድኃው ጠጋ ብሎ ‹‹በዚህ በተናቀ ቦታ ተጥለህ መኖር ከጀመርህ ምን ያህል ጊዜ ሆነህ?›› አለው፡፡ በሕማም የተያዘው ድኃውም ‹‹በዚህ ቦታ 65 ዓመት ኖርኩ›› አለው፡፡ ከዚህም ውስጥ ሃያውን ዓመት በሕማም እንደኖረ ነገረው፡፡ አባ ኪሮስም ‹‹የገዳሙ አበ ምኔትና የገዳሙ መነኮሳት ይጎበኙሃልን?›› አለው፡፡ ድኃው ሚሳኤልም ‹‹አባቴ ሆይ! የለም አይጎበኙኝም፣ ፊታቸውን ካየሁ 15 ዓመት ሆኖኛል›› አለው፡፡ አባ ኪሮስም ማንነቱን በደንብ እንዲነግረው ሚሳኤልን ለመነው፡፡ ድኃው ሚሳኤልም ‹‹አባቴ የኬልቄዶን ንጉሡ እናቴም የራሕራሕ ንጉሥ ልጅ ናት፡፡ አባቴ ሆይ ዕውነት እልሃለሁ በአባቴ ቤተ መንግሥት አገልጋዮቹ ወርቁን፣ ብሩን በእግሮቻቸው ይረግጡታል›› አለው፡፡ አባ ኪሮስም ‹‹ወደዚህ ገዳም ማን አመጣህ?›› አለው፡፡ እርሱም ‹‹እንደ አንተ ያሉ ሁለት ሰዎች በአባቴ መጥተው ባደሩ ጊዜ በእኩለ ሌሊት ፊቱ ብሩህ የሆነ ሰው ወደኔ መጥቶ ‹ሚሳኤል ሆይ ሲነጋ ተነሥተህ ከእነዚህ ሰዎች ጋር ሂድ› ሲለኝ እኔም ወጥቼ ከዚህ ቦታ ደረስኩ›› አለው፡፡ አባ ኪሮስም የአባቱን የአባ በብኑዳን ታሪክ ለሚሳኤል በመንገር አጽናናው፡፡

ከዚህም በኋላ አባ ኪሮስ በጽኑ ሕማም የተያውን ሚሳኤልን በሞት ያሰናብተው ዘንድ ወደ ጌታችን ለመነ፡፡ ጌታችንም እልፍ አእላፍ ቅዱሳን መላእክትን አስከትሎ ተገለጠለትና ‹‹ወዳጄ ኪሮስ ሆይ ጠርተኸኛልና መጣሁ›› አለው፡፡ አባ ኪሮስም ‹‹ጌታዬ ሆይ ይህ ሰው ሕማም በዝቶበታልና ያርፍ ዘንድ አናብተው›› ብለ ጌታችንን ለመነው፡፡ ጌታችንም ‹‹ወዳጄ ኪሮስ ምን ያህል እንደምወድህ የመላእክት ሠራዊት ያዩና ያውቁ ዘንድ ይህን በሕመም በተያዘው ወዳጄ ላይ ጣለው›› ብሎ በእጁ የያዘውን የገነት ተክል አበባ ለአባ ኪሮስ ሰጠው፡፡ አባታችንም ያንን የገነት ተክል አበባ ከጌታችን እጅ ተቀብሎ በሚሳኤል ፊት ላይ በጣለው ጊዜ ወዲያውኑ የሚሳኤል ቅድስት ነፍሱ ያለ ምንም ፃዕር ወጣች፡፡ ጌታችንም ያችን ቅድስት ነፍስ ተቀብሎ ሳማት፡፡ ከእርሱም ጋር በብርሃን ሠረገላ አስቀመጣት፤ አውጥቶም በሰማያዊ ክብር አኖራት፡፡

ከዚህም በኋላ አባ ኪሮስ ወደ ገዳሙ አበ ምኔት ሄዶ ድኃውን ይቀብሩት ዘንድ ለመነኮሳቱ እዘዝ አለው፡፡ አበ ምኔቱም በመታጀር ‹‹ምን ግዴታ አለብኝ?›› አለው፡፡ አባ ኪሮስም ባስጨነቀው ጊዜ ሰባት መነኮሳትን አዘዘለት፡፡ እነርሱም መዕጠንታቸውን ይዘው ሲነሡ በዚህ ጊዜ አባ ኪሮስ ‹‹የሚያጥኑት አሉና የረከሱ ማዕጠንቶቻችሁን አስወግዱ ነገር ግን ዝም ብላችሁ ቅበሩት›› አላቸው፡፡ በዚያም ጊዜ አራቱ የመላእክት አለቆች የቅዱስ ሚሳኤልን ሥጋ ሲያጥኑት መዓዛው ገዳሙን መላው፡፡ መነኮሳቱም ‹‹ይህ የሚሸተን እጅግ የሚጥም መዓዛ ምንድነው? ወይስ ይህ መነኩሴ ሥራይን ያውቅ ይሆንን?›› ተባባሉ፡፡ የቅዱስ ሚሳኤልንም ሥጋውን ወስደው ከቀበሩት በኋላ ከመቃብሩ ጠበል ፈለቀና ለብዙ ሕሙማን ፈውስ ሆነ፡፡

አባ ኪሮስም የአባ ሚሳኤልን ክብር ለእነዚያ ግብዝ መነኮሳትና ለአበ ምኔቱ በነገራቸው ጊዜ ፈጽመው አዘኑ፡፡ ከአባ ኪሮስ እግር ሥር ወደቀው ‹‹ይቅር በለን›› ባሉት ጊዜ እርሱም ‹‹በአባ ሚሳኤል መቃብር ላይ ወድቃችሁ እርሱን ይቅር በለን በሉት›› አላቸው፡፡ እነርሱም አባ ኪሮስ እንደነገራቸው ባሉ ጊዜ ‹‹በእናንተ ምክንያት ወደ መንግሥተ ሰማያት ገብቻለሁና እግዚአብሔር ይቅር ይበላችሁ›› የሚል ቃል ከአባ ሚሳኤል መቃብር ሰሙ፡፡

የአባ ኪሮስ የአባ ሚሳኤል ረድኤት በረከታቸው ይደርብን በጸሎታቸው ይማረን!

10,451

subscribers

1,216

photos

18

videos