*#የቅድስት_ሥላሴ_ተኣምር*
*እንኳን #ለቅድስት_ሥላሴ ክብረ በዓል በሰላም አደረሳችሁ!
✝️ ሐምሌ 7 ቀን 2013 ዓ.ም. በቅድስት ሥላሴ ካቴድራል ዐዲስ አበባ ታቦቱ ቆሞ የተመሰከረ #የቅድስት_ሥላሴ ተኣምር!
✝️ መስካሪዋ እናት ናቸው።
የሁለት ልጆች እናት።
ሁለተኛው ልጃቸው የአራት አመት ልጅ ሆኖ በድንገት ራሴን ወጋኝ ዐይኔንም አቃጠለኝ ብሎ አለቀሰ።
✝️ ልጁ ሕመሙ ጸናበት፤
በአራተኛው ቀን ሁለት አይኖቹ ታወሩ።
ሁለት ጆሮዎቹም ደንቆሩ።
ከዚህ ይሰውረን!
ጤነኛ ልጅ ወልዶ
በአንድ ጊዜ እንዲህ ዐይነት ችግር ውስጥ መውደቅ ያሳዝናል።
✝️ አሜሪካን አገር የሚኖረው የዳንኤል አባት ፍጹም ሐዘን እና ጭንቀት ውስጥ ወደቀ።
እናት ሥራቸውን ለቀቁ፤
በርካታ ገንዘብ እየተከፈለ የዳንኤል ሕክምናው በየአቅጣጫው ቀጠለ።
አልተሳካም።
✝️ ወላጅ እናት ሕጻን ዳንኤልን ይዘው በየጠበሉ ጉዞ ሆነ፤
አራት ዓመት ሙሉ በጸሎት ታገሉ፤
በጠበል ታገሉ፤
በእምነት ታገሉ።
ለአራት ዓመታት ሙሉ ልጅ ዳንኤል
ዐይኑ እንደታወረ፣
ጆሮውም መስማት እንደተሳነው
ኑሮ ቀጠለ።
የአባት እና እናት ጸሎት እና ተማጽኖ ቀጠለ።
✝️ ሐምሌ 6 ቀን 2013 ዓ.ም. እናት : ልጅ ዳንኤልን በመኪናቸው ይዘው አራት ኪሎ #ቅድስት_ሥላሴ ካቴድራል መጡ።
✝️ ቅዳሴ የተቀደሰበትን እምነት፣
ግቢው ውስጥ ባለው #የቅድስት_ሥላሴ ጠበል በጥብጠው፣ ልጃቸው ዳንኤልን በስመ ሥላሴ በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም ብለው የታወሩ አይኖቹን እና ሁለቱ ጆሮዎቹን በእምነቱ ለቀለቋቸው።
✝️ እንዲህ ብለውም ተማጸኑ፦
"አጋዕዝተ ዓለም ሥላሴ እርዱኝ ልጄ ቢያንስ ድምፄን ስምቶ እንድንግባባ፥
ጆሮውን እንኳን ክፈቱልኝ " ብለው ተማጸኑ።
ከዚያም ልጃቸውን ይዘው መኪናቸውን እየነዱ ወደቤታቸው ሄዱ።
✝️ በዚያኑ ዕለት ሌሊቱን ሐምሌ 6 ቀን 2013 ዓ.ም. ከሌሉቱ 7:00 ሰዓት ላይ ሕጻን ዳንኤል በአልጋው ሆኖ እናቱን ተጣራ።
"ምነው ልጄ ደሞ አዕምሮውን ታመመብኝ ይሆን፤ በሌሊት የሚጠራኝ " ብለው ወደ ሕጻኑ ሄዱ።
✝️ " እማዬ አይታይሽም? አይታይሽም? አይታይሽም? " ብሎ ጮኽ ሕጻን ዳንኤል።
የሚሰማኝ ይመስል " ምንድነው " ስለው: ልጄ ዳንኤል ድምጼን ሰማኝ!
"እማ እማ " አለ.....ጆሮው ተከፍቶ ድምጼን ሰምቶ!
"እይው እይው... ያንን መስቀል" አለኝ።
✝️ ለእኔ የሚታየኝ ነገር አልነበረም ፈዝዤ ቀረሁ።
"እይው የሚያበራ መስቀል እና መስቀሉ ላይ ያሉትን ሦስት ትልልቅ ሰዎች እያቸው እያቸው እያቸው" አለኝ።
"እነዚህ ሦስት ሰዎች መስቀሉ ላይ ሆነው አይኔን አበሩልኝ ጆሮዬንም አዳኑኝ" ብሎ ተናገረ።
✝️ እናት "እ እ እ... ልጄ..ድምጼን እየሰማህ ነው? እእእ እኔ እኔ እታይሃለሁ"
"አዎ አዎ እማዬ"።
እናት እንዲህ አሉ "...ልብስ ደረብኩ እና ምን ዐይነት ልብስ ነው የለበስኩት?" አልኩት ልጄን
" እናቴ ነጭ እኮ ነው " ብሎ በትክክል ነገረኝ።
✝️ እናት እና ልጅ ተቃቅፈው በለቅሶ ተዋጡ።
ከአራት ዓመታት በኋላ ልጅ የእናቱን ድምጽ ሰማ! የእናቱን ፊት አየ.....
✝️ ወዲያው እናት እና ልጅ ልብሳቸውን ለብሰው ሌሊቱን እናት መኪናቸውን እየነዱ ወደ #ቅድስት_ሥላሴ ካቴድራል መጡ።
ሥላሴ ቤተክርስቲያን ሲገቡ ልጅ #የቅድስት_ሥላሴን ሥዕል አየ።
"እማዬ እነዚህ ናቸው እኮ ማታ መስቀሉ ላይ ያየዋቸው! እነዚህ ናቸው እኮ ያዳኑኝ" ብሎ በገሀድ ተናገረ።
እልልታ እና ለቅሶ ቀጠለ....
✝️ ምስክርነቱ ተሰጠ።
ታቦቱ ዞሮ እንደቆመ ሊቃነ ጳጳሳቱም እንደቆሙ እኛ ሁላችን እንደቆምን ምስክርነቱ በገሃድ ለሕዝበ ክርስቲያን ታወጀ።
✝️ አይኖቻቸው በዕንባ የረጠቡ አዕላፍ ምእመናን በማያቋርጥ እልልታ ግቢውን አናጉት።
እልልልል
እልልልል
እልልልል......
የደስታ እንባ ከሁላችንም አይኖች ፈሰሰ....
ምን ልበላችሁ!?! ወገኖቼ በእምነታችን እንጽና!
✝️ ምስጋና ለአብ ወልድ መንፈስ ቅዱስ ሥላሴ!
ሐምሌ 7 ቀን 2013 ዓ.ም. ይህንን ተኣምር ታቦቱ ፊት ቆሜ እንደሰማሁ ወዲያውኑ ከጠዋቱ 5:05 ሰዓት ላይ ጻፍኩት፤
ለእናንተም አደረስኩ።
ዛሬም ተኣምሩ ልቤ ላይ ታትሟልና
ለሥላሴ ወዳጆች ዳግም ይደርስ እና #ሥሉስ-ቅዱስ ይመሰገኑ ዘንድ እነሆ ላኬያለሁ።
ሥላሴን አመስግኑ!
+ ዘአክሎግ+
✝️ *ብሩህ በዓል* ✝️