ጠበቃና የሕግ ባለሙያ ጥጋቡ ደሳለኝ፣ በሴቶችና ህፃናት የወሲብ ጥቃት ፈጻሚዎች ላይ “ ከ15 እስከ 25 ዓመት ጽኑ እስራት ” የሚለው ድንጋጌ ችግሩ እንዲስተካከል ስላላደረገ መሻሻል እንዳለበት ተናገሩ።
ቲክቫህ ኢትዮጵያ ከጠበቃና የሕግ ባለሙያው ጋር ያደረገውን ቆይታ ያንብቡ።
Q. ህፃናትን የደፈሩ የስጋ ዝምድና ያላቸው ግለሰቦች ላይ ፍ/ቤቶች የሚጥሉት ቅጣት በማነሱ ድርጊት ፈጻሚዎችን “ አይዟችሁ በርቱ የሚል እየሆነ ነው ” የሚሉ ትችቶች ተበራክተዋል፣ ከሕጉ አንጻር በፍርድ አሰጣጥ ምን መስተካል አለበት ?
አቶ ጥጋቡ ደሳለኝ ፦
“ በወንጀል ሕጉ ህፃናት ላይ የሚፈጸሙ የአስገድዶ መድፈር ወንጀሎች የቅጣት ደረጃ ‘ከ እስከ’ የሚል የግርጌና የራስጌ አይነት የቅጣት ስርዓት ነው ያለው። ሰፊ ነው ክፍተቱ።
ለምሳሌ እድሜያቸው ከ13 ዓመት በታች በሆኑ ህፃናት የአስገደድዶ መድፈር ወንጀል የፈጸመ ሰው ከ15 - 25 የሚደርስ፤ ማፈን፣ ማታለል፣ ማነቅ አይነት ተደራራቢ ወንጀል ካለው የእድሜ ልክም ሞትም ሊሆን ይችላል።
እድሜያቸው ከ14 ዓመት በላይ የሆኑ ህፃናትና አጠቃላይ በሴቶች የሚፈጸም ወሲባዊ ጥቃት ከሆነ ደግሞ እንደ ድርጊቱ አፈጻጸም ከ5 ዓመት እስከ 25 ዓመት ጽኑ እስራት እንዲፈረድ የሚል ነው።
ዳኞች 10፣ 15 ዓመት ቢፈርዱ ልክ ናቸው በሕገ መንግስቱ አንቀጽ 79 መሰረት ዳኞች የሚሰጧቸው ውሳኔዎች ፍትሃዊ፣ ነጻና ገለልተኛ እንደሆነ ታሳቢ ይደረጋል።
የእኛ አገር ዳኝነት በተጻፈ ሕግ ብቻ ነው ፍርድ የሚሰጠው። ነገር ግን መሰጠት ያለበት በተጻፈ ሕግ ብቻ ሳይሆን በርትዕ (በሕሊና ፍርድ) ጭምር ነበር።
ነገር ግን ዳኞቻችን ብዙ ጊዜ የሚሰጧቸው ውሳኔዎች የጻፈውን ሕግ እንጂ ርትዕን ታሳቢ አያደርጉም።
ዳኞቻችን ደግሞ ከምልመላው እስከ ሹመቱ ድረስ ችግር ባለበት ሂደት ነው የሚመጡት። ሕግ የተማሩ ሁሉ ዳኛ አይሆኑም በመርህና በዓለም አቀፍ ደረጃ።
ኢትዮጵያ ውስጥ ግን ዳኛ ከሆነና በዐቃቢ ሕግም ይሁን በሕግ ባለሙያነት አምስት ዓመት ከሰራና ምልመላውን ካለፈ በምክር ቤት ይሾማል። የዳኞቻችን የውሳኔ አሰጣጥ ችግር አለባቸው። ደካማ ውሳኔ ነው የሚሰጡት።
ሕጋዊ ውሳኔ መስጠትና ፍትሃዊ ውሳኔ መስጠት ይለያያሉ። ሕጋዊ ውሳኔ ማንም የመወሰን ስልጣን ያለው የሚሰጠው ውሳኔ ነው። ለምሳሌ የአንድ ተቋም ጥበቃ ‘ደንበኛ ተፈትሾ ነው የሚገባው’ ቢል ያ የጥበቃው ሕጋዊ ወሳኔ ነው።
በሕግ ደግሞ ፍትሃዊ የሚባለው ከዚህ ውሰኔና አስተሳሰብ ይለያል። የወጡ ሕጎችንና ማስጃዎችን መሠረት ከማድረግ ባሻገር ርትዕን/የህሊና ፍርድን ታሳቢ ያደረገ፣ ተጎጂዎችን ሊክስ የሚችል ጥራት ያለው ውሳኔን ታሳቢ ያደረገ ነው።
ከፍርድ ቤት የሚጠበቀው ፍትሃዊ ውሳኔ እንጂ ሕጋዊ ውሳኔ አይደለም። በየፍርድ ቤቱ ያሉ ዳኞቻችን የሚሰጧቸው ውሳኔዎች ግን ፍትሃዊ ሳይሆን ሕጋዊ ውሳኔዎች ሆነዋል።
በጥያቄው መሰረት በየፍ/ቤቱ የሚሰጡ ውሰኔዎች ደካማ፣ ሕጋዊ ውሳኔ ብቻ፣ የመወሰን ስልጣን ስላላቸው ብቻ የሰጧቸው ውሳኔዎች ናቸው።
ነገር ግን ፍትህ በመርህ ደረጃ ፈውስ፣ ህክምና፣ ኢንሹራንስ በመሆኑ ያንን ታሳቢ ያደረገ ጥራትና ብቃት ያለው ውሳኔ ሊሰጡ ይገባል።
ለምሳሌ አንድ የፍርድ ውሰኔ የሰጠ ዳኛ ቢጠየቅ ‘ሕጉ ከ5 እክከ 25 ዓመት ስለሚል የተጠቀሰበትን አንቀጽ አይቼ፣ የቀረቀውን ማስረጃ መዝኜ፣ የተከሳሹን የቅጣት ማቅለያ ግምት ውስጥ አስገብቼ ተቀናንሶ 13 ዓመት ወሰንኩበት፤ ምን አጠፋሁ?’ ይላል።
ነገር ግን ኢትዮጵያ ውስጥ በፍርድ ቤቶች በኩል ዳኞች ላይ በጣም መሰራት ያለበት፦ የተጎጂዎቹን እንባ የሚያብስ፣ አጥፊዎችን የሚያርም፣ ሌላውን የሚያስጠነቅቅ ርትዕን ታሳቢ ያደረገ ውሳኔ መስጠት ላይ ነው።
በፍርድ ቤቶች እየተሰጡ የሚስተዋሉት እነዚህ አነስኛ ቅጣቶች ሕጋዊ እንጂ ፍትሃዊ ውሳኔ አይደሉም። ነገር ግን ዳኞቹ በቅጡ አይረዱትም እንጂ የዳኞች ውሳኔ ከሕጋዊ ውሳኔ የላቀ መሆን አለበት። ”
Q. ሰሞኑን የሲዳማ ክልል ፍትህ ቢሮ ያወጣው መረጃ የ9 አመት ልጁን የደፈረው አባት በ17 ዓመት እስራት እንደተቀጣና የሌሎቹንም ወንጀልና የቅጣት ውሳኔ በመጥቀስ፣ በአባቷ፣ በእህቷ ባለቤት የተደፈሩት ህፃናት መደፈር ብቻ ሳይሆን በወላጅና በቅርብ ሰው እንደተደፈሩ ጨምር ነው በአእምሯቸው የሚያቃጭልባቸው። ለመሆኑ የቅጣት ውሳኔው አላነሰም ?
የሕግ ባለሙያ ጥጋቡ ደሳለኝ ፦
“ በአስገድዶ መድፈሩ ተጨማሪ የወንጀል ድርጊት አለ። ለምሳሌ ለህብረተሰቡ ሞራል ተቃራኒ የሆኑ ድርጊቶችን መፈጸም የሚል በወንጀል በህጋችን አለ።
ለህብረተሰቡ ሞራል ተቃራኒ የሆነ ድርጊትን መፈጸም ራሱ ወንጀል ነው። እንግዲህ በተከሳሾቹ ላይ ሁለተኛ ክስ ሆኖ ቀርቦባቸው ይሁን አይሁን ባናውቅም ቢያንስ ግን ሁለት ክስ ሊቀርብ ይገባል።
የወንጀል ሕጉ መከላከል፣ ወላጅ ልጁን እንዳይደፍር የሚያስተምር፣ የሚያስጠነቅቅ ነው ዓላማው። ስለዚህ ቅጣቱ ዝቅ ሲል እድሜ ልክ ከፍ ሲል የሞት ፍርድ ቅጣት ነው የሚያሰጠው። ነገር ግን 17 ዓመት መሆኑ ተገቢነት የለውም።
የባለቤቱን እህት የደፈረውም ለህብረተሰቡ ሞራል ተቃራኒ የሆነ ድርጊት ፈጽሟል። ዝምድና በሁለት አይነት መንገድ ይፈጠራል በቤተሰብ ሕጉ አንድም በመወለድ አንድም በጋብቻ።
በዚህ የመደፈር ወንጀል ጋብቻ አለ። ጋብቻ ካለ ደግሞ ዝምድና ተፈጥሯል። ዝምድና ከተፈጠረ ደግሞ በዘመዳሞች መካከል የአስገድዶ መድፈር ወንጀል ብቻ ሳይሆን በማህበረሰቡ ገደቦች አሉ።
ነገር ግን ይህን የማህበረሰቡን ወግና ባሕል ጥሶ ተላልፎ አስገድዶ መድፈር በባለቤቱ እህት ላይ ከፈጸመ 14 ዓመት የሚለው ፍርድ ያንሳል። በ23 ዓመት ዝቅ ካለ ደግሞ 20 ዓመት መቀጣት ያስፈልገዋል።
ይህም በቂ ነው እያልኩ አይደለም። እድሜ ልክ እስራት ተገቢ ነው። ግን የሚሰጡት ውሳኔ የዘፈቀደ ነው።
ዳኝነትን ዳኞቻችን እንደሚገነዘቡት ዳኝነት ስራ አይደለም። አገልግሎት ነው እንጂ። ለአገልግሎት የሚሆኑ ጥሩ ሰዎች ተመልምለው ተሹመው በፍርድ ቤት መቀመጥ አለባቸው።
ለሥራ ተብሎ ከሆነ የሚገቡት ሌላ የስራ መስክ መማር አለባቸው። ሰዎች ከስብዕናቸው፣ ከሚኖራቸው ተልዕኮና ጥሪ አንፃር ራሳቸውን መገምገም አለባቸው። ስለዚህ ከላይ የተነሱት ውኔዎች አስተማሪ አይደሉም ማለት ነው። ”
Q. መቼም ዳኞች በተቀመጠላቸው ሕግ መሠረት ነው ፍርድ የሚሰጡት። የቅጣት ውሳኔው ግን አስተማሪ አይደለም። ስለዚህ ችግሩ ያለው ከድንጋጌው አይደለም ? ሕጉ መሻሻል የለበትም?
የሕግ ባለሙያ ጥጋቡ ደሳለኝ ፦
“ የወንጀል ሕጉ ላይ መሻሻል የሚያስፈልጋቸው ነገሮች እየታዩ ነው። አንደኛ ተደራራቢ ወንጀለኞች እየተፈጸሙ ነው። ሁለተኛ ከእስከ (ከ15 ዓመት እስከ 25 ዓመት) የሚለው ስለሰፋ ወንጀለኞችን አላርም አላስተካክል እያለ ነው።
ስለዚህ ከ እስከ የተባለው ነገር ሰፊ ስለሆነ በሴቶችና ሕፃናት ላይ ያለውን ጥቃት ለመቀነስ መሻሻል አለበት ማለት ነው።
የቅጣት መጠኑ ጠንከር ማለት አለበት። ለምሳሌ በእስራት ከሆነ 25 ዓመት ወይም ዕድሜ ልክ ከዚያም ሲያልፍ ደግሞ የሞት ቅጣት ተብሎ አንደዚህ አይነት ነገሮች በወንጀል ሕጉ መሻሻል አለባቸው። ”
#TikvahEthiopiaFamilyAA
@tikvahethiopia