ነቢዩ ዮናስም ይህን አይቶ በየዋሕነቱ ‹‹እንግዲህማ ሊምራቸው ነው፣ እኔም ሐሰተኛ ነቢይ ልባል ነው›› ብሎ እያዘነና ከሕይወት ሞት ይሻላል ነፍሴን ከእኔ ውሰድ እያለ ከከተማ ወጥቶ ዳስ ሠርቶ ተቀመጠ፡፡ እግዚአብሔርም በውኑ ትቆጣ ዘንድ ይገባሃልን አለው፡፡ /ዮናስ. 4፥3-11/ አምላካችን መሐሪ በመሆኑ /አባት ለልጆቹ እንደሚራራ እንዲሁ እግዚአብሔር ለሚፈሩት ይራራል ፍጥረታቸውን እሱ ያውቃልና መዝ. 102፥8-14፡፡ ጥበብ 3፡፡/ ብለዋል፤ አምላካችንም /እናንተ ክፉዎች ስትሆኑ ለልጆቻችሁ መልካም ስጦታ መስጠትን ካወቃችሁ በሰማይ ያለው አባታችሁ ለሚለምኑት እንዴት አብልጦ መልካም ነገርን አይሰጣቸው ብሏል ማቴ. 7፥12/ ቀጥሎም ነቢዩ ዮናስ እንቅልፍ እንቅልፍ ብሎት ተኝቶ ቢነቃ ከራስጌው ቅል በቅላ ፀሐይ ስትከለክልለት አየና እጅግ ደስ አለው፡፡ ሁለተኛም ተኝቶ ቢነሣ ቅሏ ጠውልጋ፥ ደርቃ አገኘና አዘነ፡፡ እግዚአብሔርም ‹‹አንተ ላልተከልካትና ውኃ ላላጠጣሃት ቅል እንዲህ ስታዝን እኔስ በዝናም አብቅዬ፥ በፀሐይ አብስዬ ለምመግባቸው ሕዝቤ አላዝንምን?›› አለው፡፡ ነገር ግን እግዚአብሔር የዮናስን ፈቃዱን ይፈጽምለት (ሐሳዊ ነቢይ እንዳይሉት) ለምልክት እንዲሆን በሦስተኛው ቀን እሳት ከሰማይ ወርዶ ከፍ ከፍ ያሉትን ዕፅዋት ጫፍ ጫፋቸውን በልቶ ተመልሷል፡፡
ነቢዩ ቅዱስ ዮናስ በቀሪ ዘመኑ ፈጣሪውን እያገለገለ ኑሮ፤ በመልካም ሽምግልና በ170 ዓመት እድሜም መስከረም 25 አርፏል፡፡ ዮናስ በሕይወት ሥጋ ሣለ ሰማርያንና ነነዌን ብቻ ነበር ያስተማረው፤ ከሞተ በኋላ ግን ዛሬ ዓለምን የሚያስተምር ነቢይ ነው፡፡
ከጾሙ ረድኤት በረከት ይክፈለን፤
/በፍኖተ ሕይወት ሰ.ት.ቤት ሚድያና ሕዝብ ግንኙነት ዋና ማስተባበሪያ ክፍል የተዘጋጀ።/