በኦሞ ብሔረ ብፁዓን አቡነ ዜና ማርቆስ እና አባ ጊዮርጊስ ዘጋስጫ አንድነት ገዳም 1800 ኢ-አማንያን የነበሩ ኦርቶዶክሳዊ የቅድስት ቤተክርስቲያንን ትምህርት የተከታተሉ የዳሰነች ብሔረሰብ አባላት ሥርዓተ ጥምቀት የተፈጸመላቸው ሲሆን ምእመናኑን በብፁዕ አቡነ ፊልጶስ የደቡብ ኦሞና አሪ ዞኖች ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ፣ የቅድስት ሥላሴ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ሥርዐተ ጥምቀት እና ቁርባን ተፈፅሞላቸዋል።
ብፁዕ አቡነ ፊልጶስ በቡስካ ደብረ ጽዮን ቅድስት ማርያም እና አቡነ ሙሴ ጸሊም አንድነት ገዳም ሲመሠረት በዳሰነች ወረዳ የሚገኙ ምእመናን በአቅራቢያቸው በኦሞራቴ አካባቢ በዳሰነች ወረዳ አዲስ ቤተክርስቲያን እንዲሠራ ጥያቄ ሲያቀርቡ እንደነበር አስታውሰው እግዚአብሔር መልስ ሰጥቶ ብሔረ ብፁዓን አቡነ ዜናማርቆስ እና አባ ጊዮርጊስ ዘጋስጫ አንድነት ገዳም ቤተመቅደሱ እንዲገነባ ብቻ ሳይሆን ብዙ ሺዎች ምስጢረ ጥምቀት እንዲፈጸምላቸው ፈቃደ እግዘብሔር መሆኑን ገልጸዋል። በተያያዘም ማኅበረ ቅዱሳን ለተጠማቂዎች የአልባሳት ድጋፍ አድርጓል።
የብሔረሰቡ ሽማግሌዎች የአብያተ ክርስቲያናቱ ቁጥር አነስተኛ በመሆኑ ተጨማሪ ቤተክርስቲያን እንዲሠራላቸው ሲጠይቁ በቀጣይ ምእመናኑን የማጽናት ሥራ ተጠናክሮ እንዲቀጥል ብፁዕነታቸው መመሪያ ሰጥተዋል። በዕለቱ በ 3 ወራት ተሠርቶ የተጠናቀቀው ቤተመቅደስ ቅዳሴ ቤት በብፁዕነታቸው ተባርኮ ተከብሯል።
በክብረ በዓሉ እና በሥርዓተ ጥምቀቱ በዓል የዳሰነች ወረዳ አስተዳደር ለገዳሙ የበሬ ስጦታ አበርክቷል። ብፁዕ አቡነ ፊልጶስ ሐዋርያዊ ጉዟቸውን በመቀጠል ወደ ቡስካ ደብረ ጽዮን ቅድስት ማርያም እና አቡነ ሙሴ ጸሊም ገዳም ተጉዘዋል ።