በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን።
የቃና ዘገሊላ ታሪክ ውስጥ አስደናቂ ከኾኑ ክስተቶች ውስጥ አንዱ የወይን ማለቅ ጉዳይ ነው። በእርግጥ ቃና ዘገሊላ ውስጥ የተፈጸመው የሰርግ ጉዳይ ጥልቅ መልእክቶችን የተሸከመ መኾኑ በብዙ የሚብራራ ነው። ታሪኩን በጥልቀት ለመረዳት ግን ወደ ታሪኩ ጥልቀት ውስጥ የምንገባበትን በር ማግኘት አለብን። የዮሐንስን ወንጌል ምሥጢራዊነት ወደ መረዳት ከፍታ እስካልወጣን ድረስ በወንጌሉ ውስጥ የተፈጸሙትን አስደናቂ ክስተቶች በአግባቡ መረዳት አንችልም። ማክሲመስ ተናዛዚው መጽሐፍ ቅዱስን በጥቅሉ በቤተ ክርስቲያን ይመስልና የዮሐንስን ወንጌል ደግሞ በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ያለችውን ቅድስተ ቅዱሳን ትመስላለች ይላል። ይህ የሚያመለክተው ወንጌሉ የተሸከመውን ጥልቅ ምሥጢር ነው። እንዲያውም ቀለሜንጦስ ዘእስክንድርያ ሦስቱን ወንጌላት በሥጋ የዮሐንስን ወንጌል ደግሞ በመንፈስ ይመስላል። የሌሎቹ ወንጌላት እስትንፋሳቸው የዮሐንስ ወንጌል ነውና!!
ከዚህ ሁሉ በላይ ደግሞ የዮሐንስን ወንጌል ለመረዳት ሊቁ ኦሪገን እንዳለው ወደ ጌታ ደረት ጋር ጠጋ ብሎ እንደ ዮሐንስ ከጌታ እመቤታችንን መቀበልን ይጠይቃል። ይህ ኹሉ የሚያመለክተው በወንጌሉ ላይ የተጻፉ ክስተቶችን በችኩልነትና በለብ ለብ ስሜት አልፈን እንዳንሄድና በጥልቀት እንድንመረምር ነው። ሰርግ የተፈጸመባት የገሊላዋ ቃና ንጽሕት ቅድስት ድንግል ማርያምን በመያዟ ከሚመጣባት ጉድለት ስትድን እንመለከታለን። ከክርስቶስ ጋር ለምናደርገው ግንኙነት የእመቤታችን ልመና እጅግ አስፈላጊ ነው። እርሷ ቀድማን ጉድለታችንን ባታሰማልን ኖሮ መሽራው ክርስቶስ እንዴት ይቀበለን ነበር!!
@እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ከቤተ አይሁድ ወገን ስለ ኾነች የአይሁድን ጉድለት በእጅጉ ታውቀዋለች፤ ስለዚህ የሚጠቅማቸውን ወይን ይሰጣቸው ዘንድ ትለምናለች። በመጽሐፍ እንዲህ ተብሏል “እናንተ ሰካራሞች ንቁ ለመስከርም ወይን የምትጠጡ እናንተ ሁላችሁ! ተድላና ደስታ ከአፋችሁ ጠፍተዋልና አልቅሱ፤ እዘኑም።" ኢዩ 1፥5። በመኾኑም አይሁድ የድኅነትን ደስታ በማጣት በኀዘን ውስጥ ናቸው፤ ይህ ነውና የወይን ማጣት!! ወይን እኮ የላቸውም የድኅነት ደስታ ከደጃቸው ጠፍታለችና ስጣቸው ማለቷ ነበር። በተራው ምድራዊ ወይን ሰክረው የድኅነትን ወይን በማጣት ጨለማ ውስጥ ገብተው ነበርና ጉድለታቸውን የምታውቅ ፈጣኗ እናት ለመነችላቸው።
@ወይን እኮ የላቸውም ርቱዕ እምነት የላቸውም። አኹንም በኦሪታቸው ውስጥ የምትታየውን አንተን ወደ ማወቅ አልመጡምና አይኖቻቸውን ከፍተህ ብርሃነ ወንጌልህን ግለጥላቸው። በጨለማ ውስጥ ያለን ነገር ለማየት የግድ ብርሃን እንዲያስፈልግ በእምነት ጨለማ ውስጥ ያሉትን ወይን ርቱዕ እምነትን ሰጥተህ አድናቸው ማለቷ ነው። ያለ እምነት እግዚአብሔርን ደስ ማሰኘት አይቻልም ብሎ ቅዱስ ጳውሎስ እንደ ተናገረው በሐዲስ ኪዳኗ ትክክለኛዋ እምነት በኩል ከእግዚአብሔር ጋር እስካልተገናኘን ድረስ በእርግጥም ወይን እኮ የለንም!!
#እመቤታችን ወይን እኮ የላቸውም ማለቷ ሰዎች ከፈሪሓ እግዚአብሔር በመራቃቸው ምክንያት የደረሱበትን መልከ ጥፉነት ለማመልከትና ከዚያ እንድንፈወስ ለማስደረግ ነው። መዝ 127 “ብፁዐን ኩሎሙ እለ ይፈርሕዎ ለእግዚአብሔር ወለ እለ የሐውሩ በፍናዊሁ። ፍሬ ጻማከ ተሴሰይ፣ ብፁዕ አንተ ወሠናይ ለከ፤ ብእሲትከ ከመ ወይን ሥሙር ውስተ ጽርዓ ቤትከ - እግዚአብሔርን የሚፈሩ ኹሉ የተመሰገኑ ናቸው፣ የድካምህን ዋጋ ትበላለህ፤ ምስጉን ነህ መልካምም ይኾንልሀል፤ ምስትህም በቤትህ ውስጥ እንደ ወይን የተወደደች ናት።" በማለት በብዙ አንቀጽ ጀምሮ በአንድ አንቀጽ ወደ ማውራት ይመጣል። ይህ የሚያመለክተው የክርስቶስንና የእርሱ የኾነችውን ቤተ ክርስቲያን ግንኙነት ነው። በቤትህ እንደ ወይን የተወደደች ናት በማለት የቅድስት ቤተ ክርስቲያንን ውበት ያነሣል። ስለዚህ በፈሪሓ እግዚአብሔር ውስጥ የሚኖሩ የቤተ ክርስቲያን አካሎች የምግባር ውበታቸውን ሳያጡት እንደሚኖሩ፤ ወይን እኮ የላቸውም የተባሉት በዚህ ዓለም ፍልስፍናና ፍቅር የነጎዱትን ነው። የጠፉትን ወደ በረቱ ለመሰብሰብ የተደረገ የፍቅር ጥሪ ነው!!
#ወይን እኮ የላቸውም። ፍቅረ ቢጽ ወፍቅረ እግዚአብሔር የላቸውም። የራሳቸውን ስሜት በመውደድ የሠለጠኑ ናቸውና ወይን ፍቅር የላቸውም!! ወይን ጣዕሟ እንደሚያረካ ነፍሳቸው የምትረካባቸው ቃለ እግዚአብሔር የላቸውም!! ቃልህ ለእግሬ መብራት ለመንገዴ ብርሃን ነው ተብሏል እነርሱ ግን ይህ በአንተ ቃል የመመራት ሐሳብ የላቸውምና በቃልህ የመመራት ኃይልን ሙላባቸው!! እንግዳ ክፉ ፈቃድ ተነሥቶባቸዋልና ይህን ድል የሚያደርጉበትን ወይን ትዕግሥትን ስጣቸው። መናፍቃን ለሚያቀርቡባቸው ጥያቄዎች መልስ ሰጥተው ሰውነታቸውን በእውነት መሠረት ላይ ይገነቡት ዘንድ ወይን ማስተዋል የላቸውምና ማስተዋሉን አድላቸው!
#ወይን ሕገ ወንጌል ናት። በሕገ ወንጌል ወይን ውስጥ ገብተው ይኖሩ ዘንድ ወይን የወንጌል ምሥጢራትን የሚረዱበት ሀብተ ትርጓሜ የላቸውም። በወንጌል ውስጥ የተዘገበው ሰላም ቀድሞ ባለበሳቸው ጥላቻ ምክንያት አልተገኘላቸውምና “ወይን እኮ የላቸውም" ። የሕይወት ወይን አንተን ራስህን በማጣት ሕማም ውስጥ ገብተው ቆስለዋልና አምላክነትህን ገልጠህ አሳያቸው። በሕይወት ውጣ ወረድ ውስጥ የሚገጥማቸውን መከራ በጽናት ይቀበሉ ዘንድ ወይን እኮ የላቸውም። በእርግጥ የእመቤታችን ድምጿ በልጇ ዘንድ ይሰማል። የእኛ ጉድለትም ስለ እርሷ ሲባል ይሟላል። ብቻ እናታችን ቅድስት ኾይ ከመዝሙር ይልቅ ዘፈን ደስ የሚያሰኘንን እኛን ወይን እኮ የላቸውም በይልን!! ጌታ ሆይ ወይን ደምህን ጠጥተን ምሬተ ኃጢአታችንን ታስወግድ ዘንድ ስለ እናትህ ብለህ ወይንህን ስጠን! አሜን።