(አሌክስ አብርሃም)
አንድ የሰፈራችን ባለሱቅ የሆነ ቀን በበሩ ሳልፍ "ወንድሜ" ብሎ በአክብሮት ጠራኝና እዚህ ሰፈር ነው የምትኖረው? ብሎ ጠየቀኝ! "አወ" አልኩት እንዴት ረሳኝ ብየ በመገረም! የረዢም አመት ደንበኛየ ነበር። ቀጠል አድርጎ
ሲጃራ ታጨሳለህ እንዴ?
አይ አላጨስም
አቁመህ ነው?
አይ ከመጀመሪያውም አላጨስም
ጫትስ ትቅማለህ እንዴ?
አይ አልቅምም
አቁመህ ነው?
ቅሜ አላውቅም! ለምንድነው ግን የምትጠይቀኝ አልኩ ገርሞኝ ። ጥያቄየን ችላ ብሎ
እ...የስልክ ካርድ ከኔ ትወስድ ነበር እንዴ?
አወ (ደግሞ እውነቴን ነው ከሱ ሱቅ ነበር የምገዛው)
ባለስንት ነበር የምትገዛው?
ባለመቶም ፣ ባለ ሃምሳም ...ባለ ....
ተወው አስታወስኩ! የመቶ ብር ካርድ አለብህ ስምህን መዝገብ ላይ አይቸዋለሁ
ማነው ስሜ ?
ስምህ ምን ያረጋል ጋሸ? ዋናው ካርዱ ነው ....😀
በኋላ ስሰማ ይሄ ሚስኪን ባለሱቅ አእምሮውን ታሞ አማኑኤል ሆስፒታል ገብቶ ነበር አሉኝ። ሚስቱን ነበር ሱቁ ውስጥ ለረዢም ጊዜ የማያት! እና ዘለግ ላለ ጊዜ ታክሞ ከአማኑኤል ተሽሎት ወጣ። ሁሉ ነገር ተስተካክሎ አንድ ነገር ብቻ ትንሽ ልክ አልመጣለትም እየተባለ ይወራል። ማንኛውም በሱቁ በር የሚያለፍ ሰው ዱቤ ወስዶ ያልከፈለው ይመስለው ስለነበር እያስቆመ አጭር መስቀለኛ ኢንተርቪው ያደርጋል። ከምንም በላይ ግን ያሳቀቀን እትየ ማርታን ጠርቶ ጠየቃት የተባለው ነገር ነው። እትየ ማርታ ዕድሜዋ 40 የተሻገረ ዘናጭ ሴት ናት!
"እህቴ ይቅርታ እዚህ ሰፈር ነሽ?" አላት
አወ ምን ልርዳህ? አለች በሚያምር ፈገግታ
ፔሬድ ማየት አቁመሻል እንዴ ወይስ ታያለሽ ? አበደች ...
"ስድ ምናባህ አገባህ?" በኋላ ባሏ ተነግሮት ሊያናፍጠው ወደሱቁ ሲሄድ "ሞዴስ በዱቤ ወስዳ ያልከፈለችኝ መስሎኝ ነው ጋሸ ! ግን ከመጣህ አይቀር ታጨሳለህ እንዴ.....😀"
@wegoch
@wegoch
@paappii