| ጃንደረባው ሚድያ |ኅዳር 2017 ዓ.ም.|
አዲስ አበባ - ኢትዮጵያ
የኢትዮጵያዊው ጃንደረባ ትውልድ በ2016 ዓ.ም. በአራተኛ እና አምስተኛ ዙር ሱባዔ ጉባኤ በቅድስት ሥላሴ መንፈሳዊ ኮሌጅ አዳራሽ ያስተማራቸውን 2000 ተማሪዎች እንዲሁም በሦስተኛ ዙር የምእመናን የቅዳሴ ተሰጥኦ ትምህርት ያሰለጠናቸውን 100 ተማሪዎች ብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳት በተገኙበት በቦሌ መድኃኔዓለም ዓውደ ምሕረት በደመቀ ሁኔታ አስመረቀ። ከተማሪዎቹ መካከል ከልጆቻቸው ጋር የተማሩ ወላጆች አራስ ሆነው የተማሩ እናቶችም ይገኙበታል::
በምርቃት መርሐ ግብሩ ላይ የጃን ሱባዔ ጉባኤ አስተባባሪ የሆኑት አቶ ሕያው መኮንን እንደገለጹት በኢጃት ከሚተገበሩ መፍትሔ ተኮር ፕሮጀክት መካከል አንዱ የሆነው ሱባዔ ጉባኤ የተሰኘው የትምህርት መርሐ ግብር ሲሆን ሱባዔ ጉባኤ ኢትዮጵያዊው ጃንደረባ በሰረገላ ላይ ሆኖ ለአጭር ጊዜ ለመዳን የሚያበቃውን ትምህርት በዲያቆኑ ፊልጶስ ተምሮ "እነሆ ውሃ እንዳልጠመቅ የሚከለክለኝ ምንድነው?" የሚል መፍትሔን እንዳቀረበ የእኛም ትውልድ የ28 ቀን የሰረገላ ላይ ትምህርትን ወስዶ ከምሥጢራት እንዲካፈል የቤተ ክርስቲያንን ችግር "እነሆ መፍትሔ" በማለት እንዲፈታ ማስቻል ነው" ብለዋል። ምንም እንኳን የትምህርቱ ቀናት ከጥልቁ የቤተ ክርስቲያን ትምህርት አንጻር የቅምሻ ያህል ቢሆንም በሳምንታዊ ኮርሶች መለኪያ ሲታይ የአንድ ዓመት ሥልጠና የሚፈጀውን ያህል 53 ሰዓታት የሚፈጅ ሲሆን ትምህርቱን በእይታ የተደገፈ በማድረግ ጥራቱን ከፍ ለማድረግ የተቻለ ሲሆን በትምህርቱም አዳዲስ መምህራንን በየጊዜው ማፍራት ተችሎአል ብለዋል::
የጃን ቅዳሴ አስተባባሪ የሆኑት መምህር ኃይለኢየሱስ ተሻለ በበኩላቸው ምእመናን ከቅዳሴ ከሚርቁባቸው ምክንያቶች ዋነኛው ተሰጥኦውን አለማወቃቸው መሆኑን ገልጸው ቅዳሴ ማስቀደስ የዚህ ትውልድ ልዩ ምልክት እንዲሆን እና ሥርዓተ ቅዳሴን ለምዕመናን በማስተዋወቅ ሳያስቀድስ መኖር የማይችል ትውልድን ለመፍጠር ፕሮጀክት ቅዳሴ ተቀርጾ ላለፉት ዐራት ዓመታት እየሠራ መሆኑን ገልጸዋል። አያይዘውም በ2017 የቅዳሴ ተሰጥኦ የቪድዮ ትምህርት እንደሚጀመርም አስታውቀዋል::
ኢጃት እስካሁን አራተኛ እና አምስተኛ ዙር ተማሪዎችን ጨምሮ ከ5000 በላይ ተማሪዎችን አስተምሮ ያስመረቀ ሲሆን ከ 2016 ዓ.ም ጀምሮ ከሰንበት ትምህርት ቤት አንድነት ጋር የጋራ ሥምምነት በመፈራረም ሱባኤ ጉባኤ የሰንበት ት/ቤት የመግቢያ ትምህርት እንዲሆን በመስማማት ከ2500 በላይ ተማሪዎች ሱባዔ ጉባኤን ተምረዋል:: በ6ኛ ዙር ተማሪዎች ቀድመው ተመርቀው ወደ ሰንበት ትምህርት ቤት አገልግሎት ተቀላቅለዋል።
የኢጃት ሥራ አመራር ቦርድ ሰብባቢ የሆኑት ዲ/ን ዶ/ር ዳዊት ከበደ የ28ቀኑ የሱባዔ ጉባኤ ትምህርት ዓላማ ቤተክርስታያንን ጠንቅቃችሁ እንድታውቋት ሳይሆን ቢያንስ ቀረብ ብላችሁ እንድታዩአት ፥ ተጠይቃችሁ መመለስ ቢያቅታችሁ ቤተክርስቲያኔ መልስ አላት ብላችሁ በድፍረት መናገር እንድትችሉ ማስቻል መሆኑን በመግለጽ እንደ ባሕር ጥልቅ የሆነውን የቤተክርስቲያናችንን ትምህርት ቀረብ ብላችሁ እንድትማሩ ፣ ከንስሓ እና ከሥጋ ወደሙ ዘውትር እንዳትርቁ ፣ የድኀነታችሁ ምልክት የሆችው ማዕተባችሁን እስከ ዕለተ ሞታችሁ ድረስ ከአንገታችሁ ለቅጽበት እንዳይለያችሁ በማለት ለተመራቂዎች የአደራ መልእክት አስተላልፈዋል።
በምርቃት መርሐ ግብሩ ላይ የተገኙት አቡነ ዲዮስቆሮስ የራያ አላማጣ 6ቱ ወረዳዎች ቤተ ክህነት ሊቀ ጳጳስ፤ የቅርስና ጥበቃ አስተዳደር እንዲሁም የማኅበራት ምዝገባ ክትትልና ቁጥጥር መምሪያ የበላይ ኃላፊ ሊቀ ጳጳስ እና የቅዱስ ሲኖዶስ አባል እንዲሁም ብጹዕ አቡነ ማርቆስ በሰሜን አሜሪካ የሲያትል እና አካባቢው አህጉረ ስብከት ሊቀጳጳስ እና የቅዱስ ሲኖዶስ አባል ለተመራቂ ተማሪዎች አባታዊ ምክር እና ቃለ ምዕዳን ሰጥተዋል።
#በፍጹም_ልብህ_ብታምን_ተፈቅዶአል