+++ ቅዱስ ሉቃስ እና ቅዱስ ኤፍሬም በቀዶ ጥገና ክፍል ውስጥ +++
X. P. ሲል ስሙን በምሕጻር ያስቀመጠ አንድ የ46 ዓመት ጎልማሳ በቅዱሳኑ የተደረገለትን ተአምር እንዲህ ያወጋናል።
"ስሜ X. P. ይባላል። እድሜዬ አርባ ስድስት ዓመት ሲሆን በሰሜናዊው የግሪክ ክፍል ነዋሪ ነኝ። እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር በ2004 ዓ.ም ናላዬ ላይ በተፈጠረ እጢ (Brain tumor) አማካኝነት የቀዶ ሕክምና አድርጌ ነበር። ነገር ግን ይህ ከሆነ ከሦስት ዓመት ከስድስት ወር በኋላ እንደገና እጢው በናላዬ ላይ ታየ። በዚህም ምክንያት ብዙ ዶክተሮች ጋር የሄድኩ ቢሆንም አንዳቸውም ግን ቀዶ ጥገና ሊያደርጉልኝ ፈቃደኛ አልነበሩም። በዚህም ተበሳጭቼ እና ከፍተኛ ጭንቀት ውስጥ ገብቼ ነበር።
በመጨረሻም ይህን አስቸጋሪ ቀዶ ጥገና ለማድረግ የተስማማ አንድ ሐኪም አገኘሁ። አንዳንድ የቅርብ ዘመዶቼም የታመሙትን የሚረዳ ባለመድኃኒት የሆነውን ቅዱስ ሉቃስን እንዳከብረው እና ሌሎች ሕሙማንን እንደረዳ እኔንም ይረዳኝ ዘንድ እንድማጸነው ነገሩኝ። እኔም በሁኔታው ተሰማምቼ ቅዱሱን ለማክበርና ለመማጸን ሕንጻ መቅደሱ ወዳለበት የግሪክ ከተማ ተጓዝኩኝ። በዚያም እጅግ የዋህና ትሁት የሆነ አንድ ካህን አገኘሁ (የእርሱንም ስም በምሕጻር Fr. K ይለዋል)።
እርሱ ጥንካሬና ብርታትን ሰጠኝ ፣ ጸሎትም አደረገልኝ። እኔም ኃጢአቴን ተናዝዤ ሥጋ ወደሙን ተቀብዬ ፤ የቀዶ ጥገናው ቀን በመቃረቡ ወደ መጣሁበት ተመለስኩ። ከእለታት በአንደኛው ምሽት በሕልሜ ቅዱስ ኤፍሬምን አየሁት። እርሱም እንዳልረበሽና ነገሮችም በጥሩ ሁኔታ እንደሚሄዱ ነገረኝ።
በመጋቢት 13 ፣ 2007 ዓ.ም ቀዶ ጥገና ወደሚደረግበት ክፍል ገባሁ። ምንም በመድኃኒት የደነዘዝኩ ብሆንም እንኳን ፤ ከቅዱስ ሉቃስና ከቅዱስ ኤፍሬም ጋር ሆነው ቀዶ ጥገናውን የሚያደርጉትን ፤ ትንንሽ ክብ መነጽር ያደረጉና ስለቶች በእጃቸው የያዙ ሐኪሞችን ማየት እችል ነበር። ቅዱስ ኤፍሬም እንዳልፈራ እየነገረኝ እጄን ይዞታል ፤ በግራ እጁ ደግሞ ራሴ አካባቢ የሚያበራ መብራት ይዞ ነበር።
ቀዶ ጥገናው እንደተጠናቀቀም ወደ ከፍተኛ ክትትል ክፍል ወሰዱኝ። በዚያም ድጋሚ ቅዱስ ሉቃስ መጥቶ "በቀዶ ጥገናው ክፍል ውስጥ አብሬህ ነበርኩ" አለኝ። እኔም "አውቃለሁ" ብዬ መለስኩለት። አስቀድሞ ከቀዶ ጥገናው ክፍል ስወጣ ሐኪሙ "እንዲህ ዓይነት ሕመም ሆኖ ነገር ግን ቀላል ቀዶ ጥገና ሳደርግ የመጀመሪያዬ ነው።" እያለ ሲነግረኝ ሰምቼዋለሁ።
ከዚህ በፊት ስለ እነዚህ ሁለት ቅዱሳን ምንም የማውቀው ነገር አልነበረም። አሁን ግን በዙሪያዬ የሚከቡኝ ጠባቂዎቼ ሆነዋል።
Source : http://www.pravoslavie.ru/english/75865.htm
ትርጉም : ዲያቆን አቤል ካሳሁን
[email protected]