ኅዳር 14 ቀን 2017 ዓ.ም (ተ.ሚ.ማ/አዲስ አበባ)
ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ቴዎፍሎስን እና ኢትዮጵያን በቅንነት ያገለገሉ ባለውለታዎች በግፍ የተገደሉበት ሃምሳኛ ዓመት በመንበረ ጸባኦት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል ብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳት በተገኙበት የጸሎት ሥነ ሥርዓት በዛሬው ዕለት ተካሂዷል፡፡
ዛሬ ሃምሳኛ ዓመታቸው የተዘከረላቸው ሰማዕታት ኅዳር 14 ቀን 1967 ዓ.ም በደርግ የተገደሉ አባቶች እና ከአምስት ዓመት በኋላ ሐምሌ 7 ቀን 1971 ዓ.ም ከእስር ቤት በሰንሰለት እየታሰሩ ተወስደው ከተገደሉት መካከል ከሰብአዊነት ውጭ በሆነ በግፍና በሚያሰቅቅ ሁኔታ በገመድ ታንቀው የተገደሉት ሁለተኛው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ፓትርያርክ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ቴዎፍሎስም ይገኙበታል፡፡
በጸሎት ሥነ ሥርዓቱ ላይ ብፁዕ አቡነ ያዕቆብ የእንግሊዝና አካባቢው ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ፣ ብፁዕ አቡነ ኤጲፋንዮስ የምሥራቅ ጉራጌ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ እና የቀድሞ የኢፌዴሪ ፕሬዚዳንት ክብርት ሣህለ ወርቅ ዘውዴ ተገኝተዋል፡፡
በግፍ የተገደሉት ለሀገራቸው፣ ለቤተክርስቲያናቸው በርካታ አስተዋጽኦ ያደረጉ መሆናቸው በዕለቱ የተገለጸ ሲሆን፤ ልጅ ዳንኤል ጆቴ መስፍን እንደተናገሩት “ዛሬ ኅዳር 14 ቀን የምናዘክራቸው የኢትዮጵያ አባቶች ከማይጨው ጦርነት ጀምሮ ሃይማኖታቸውን፣ ባሕላቸውን ጠብቀው የነበሩ፡፡ ዳዊታቸውን እየደገሙ፣ ኢትዮጵያን ያስተዋወቁ ስለ ሀገር፣ ስለ ቤተክርስቲያን ብሎም ስለ ዓለም የሚጸልዩ ታላቅ ኢትዮጵያውያን አባቶች ነበሩ ብለዋል፡፡ እነዚህ ናቸው በአንድ ቀን በገዛ ልጆቻቸው የተገደሉት ፤ እነዚህን ያለ አግባብ የተገደሉትን ትውልዱም ታሪካቸውን እንዲያውቅ፣ እንዲያዘክራቸውም በከተማው ውስጥ ሐውልት ሊቆምላቸው ይገባል” ሲሉ ገልጸዋል፡፡
“ዛሬ የምስጋና ቀን ነው” ያሉት አቶ ዓምዴ አካለ ወልድም እንደተናገሩት “በግፍ በገመድ ታንቀው ከተገደሉት አንዱ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ፓትርያርክ መሆናቸውን” አውስተዋል፡፡ “ይህ በዓል የእኛ ቤተሰብ ብቻ ሳይሆን የኢትዮጵያም ታሪክ ነው” ሲሉ አክለው ገልጸዋል፡፡ እነዚህን ለማዘከርም “የታሪክ አደራ” የሚል የበጎ አድራጎት ማኅበር ማቋቋማቸውን አስረድተዋል፡፡
ኅዳር 14 ቀን 1967 ዓ.ም የተገደሉት ኢትዮጵያውያን ሲቪል ባለሥልጣናት፣ ወታደራዊ መኮንኖችና ከአምስት ዓመት በኋላ በ 1971 ዓ.ም በሰንሰለት እየታሠሩ በግፍና በስቃይ በደርግ የተገደሉት አባቶች የመታሰቢያ ሐውልትና ዐጽማቸው ያረፈበት ቦታ በዘመናዊ አሠራር ለጉብኝት በሚያመች ሁኔታ በመንበረ ጸባዖት በቅድስት ሥላሴ ካቴድራል ተሠርቶላቸዋል፡፡ ዐጽማቸው ያረፈበትን ቦታም ቤተሰቦቻቸው፣ ጥሪ የተደረገላቸው በርካታ እንግዶች እና ሥነ ሥርዓቱን ለመታደም የመጡ ጎብኝተውታል፡፡
በ1971 ዓ.ም የተሰዉት ሰማዕቱ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ቴዎፍሎስ ዐጽም ሐምሌ 4 ቀን 1984 ዓ.ም አሟሟታቸውንና የት እንደተቀበሩ በዐይኑ ባየ በወቅቱ የደርግ ደህንነት ክፍል ወታደር ጥቆማ ወጥቶ ሐምሌ 4 ቀን 1984 ዓ.ም በጎፋ ቅዱስ ገብርኤል ካቴድራል በክብር ዐረፈ፡፡ የሌሎቹ በግፍ የተገደሉት ዐጽም ከወደቀበት ሥፍራ ተሰብስቦ የካቲት 9 እና ሐምሌ 19 ቀን 1984 ዓ.ም በመንበረ ጸባዖት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል በጊዜያዊነት ተቀምጦ፤ ከዚያም በዚሁ ቅዱስ ስፍራ ሐምሌ 20 ቀን 1984 ዓ.ም ዐረፈ፡፡ የሐውልቱ ሥራም ሰኔ 8 ቀን 1984 ዓ.ም ተጀምሮ ኅዳር 14 ቀን 1986 ዓ.ም ተጠናቆ እንደተመረቀ በሐውልቱ ላይ የተጻፈው ጽሑፍ ያስረዳል፡፡
©eotc tv