መጋቤ ሐዲስ ሮዳስ ታደሰ (ዶክተር) Dr Rodas Tadese @rodas9 Channel on Telegram

መጋቤ ሐዲስ ሮዳስ ታደሰ (ዶክተር) Dr Rodas Tadese

@rodas9


ትክክለኛው ቻናሌ ይሄ ብቻ ነው። በዚ ብቻ ትምህርተ ሃይማኖትንና የኢትዮጵያ ምስጢራትን ሳይንሳዊ ጉዳዮችን በጥልቀት እንዳስሳለን። ሌሎቹ ቻናሎች የእኔ አይደሉም

መጋቤ ሐዲስ ሮዳስ ታደሰ (ዶክተር) Dr Rodas Tadese (Amharic)

ሐዲስ ሮዳስ ታደሰ (ዶክተር) Dr Rodas Tadese በተለያዩ ቻናሌ ውስጥ በጥልቀት የተጋባላችሁት መምሪያ ምልክታችን ነው። ይህ ብቻ የኢትዮጵያ ትምህርት ሃይማኖትንና ምስጢራትን በማድስ የሚከታተሉትን ሳይንሳዊ ጉዳዮች ለመጋባና ለመመለስ በቻናሌ መምሪያ ተመልክተዋል። ሌሎቹ ቻናሎች ከሚታወቁ አይዲዮን በቀጥታ ላይ እንዲጠቀሙና ማድረግ እና ለመገናኘት በማሰመጠን የቻናሎችን እናቶች እንዲጠቀሙ ይጠይቃሉ። እኛም ሆነ ሌሎቹ ቻናሎች የእኛ አምላክ አሰልጣኞቹ ናቸው።

መጋቤ ሐዲስ ሮዳስ ታደሰ (ዶክተር) Dr Rodas Tadese

23 Nov, 21:18


https://youtu.be/pK2McHhQioo?si=DpTthE3tMv4zh-4d

መጋቤ ሐዲስ ሮዳስ ታደሰ (ዶክተር) Dr Rodas Tadese

23 Nov, 21:14


ልዑል እግዚአብሔር ቢፈቅድ ገዳሙ ድረስ ኼዳችኊ ያን ልዩ በረከት እንድትሳተፉና የቅዱሱን ሰማዕት አካል እንድትዳስሱ እመኛለኊ፡፡
[የቅዱስ ሚናስ በረከት ይደርብን]፡፡
ከመጋቤ ሐዲስ ዶክተር ሮዳስ ታደሰ [በድጋሚ post የተደረገ]

መጋቤ ሐዲስ ሮዳስ ታደሰ (ዶክተር) Dr Rodas Tadese

23 Nov, 21:14


[ኅዳር 15 ዕረፍቱ ሠኔ 15 ቅዳሴ ቤቱ የኾነው በምልጃው ፈጥኖ በመድረስ የሚታወቀው የቅዱስ ሚናስ ድንቅ ታሪክና በኢትዮጵያ ሊቃውንት የቀረበለትን ምስጋና]
በመጋቤ ሐዲስ ዶክተር ሮዳስ ታደሰ
ቅዱስ ሚናስ በመላው ዓለም በተለይ በግብጽ ቤተ ክርስቲያን ልክ እንደ ሰማዕቱ ቅዱስ ጊዮርጊስ በእጅጉ የሚወደድና ተአምር አድራጊ ሲጠራ ፈጥኖ የሚደርስ "ገባሬ ተአምር ወመንክር" (wonder-worker) በመባል የሚታወቅ ሰማዕት ነው። በተማፀኑት ጊዜ በምልጃው ፈጥኖ ነው የሚደርሰው፡፡

ይኸውም ከደጋግ ቤተሰቦች የተገኘ ሲኾን አባቱ ኢዩዶክሲዮስ፤ እናቱ ኢዩፎሚያ ትባላለች። ልጅ ስላልወለደች በእመቤታችን በዓል ዕለት ወደ ቤተ ክርስቲያን ገብታ ልጅን ይሰጣት ዘንድ ወደ እግዚአብሔር እንድትለምንላት በሥዕለ ማርያም ተማፀነቻት፤ ያን ጊዜ ከእመቤታችን ሥዕል አሜን የሚል ቃል ተሰማ፡፡

ከዚያም ይኽነን ለባሏ ነገረችው፤ ከዚያም እግዚአብሔር የተባረከውን ልጅ በ285 ዓ.ም ላይ ሰጣት፤ ስሙንም ከእመቤታችን ሥዕል “አሜን” የሚል ቃል ስለተሰማ ርሱንም ሚናስ ብለው ሠይመውታል፡፡

ዜና ገድሉ Mina was his original name, according to the story his mother called him "Mēna" because she heard voice saying amēn. Minas [Μηνας] is how he is known in Greek, while in Armenian and Arabic he is known as "Mīna" [مينا].
ይላል፤ እነርሱም የቤተ ክርስቲያንን ትምህርት በስፋት አስተማሩት፤ በዐሥራ ኹለት ዓመቱ አባቱ ሲያርፍ ከሦስት ዓመት በኋላ እናቱ ዐርፋ ቅዱስ ሚናስ ብቻውን ቀርቷል፤ ከዚያም መኳንንቱም አባቱን ይወድዱት ስለነበር በአባቱ ፈንታ ምስፍናን ሾሙት፡፡

ዲዮቅልጥያኖስ ክርስቶስን በካደ ጊዜ ቅዱስ ሚናስ ሹመቱን ትቶ ወደ ገዳም ገብቶ ተጋድሎን ዠመረ፤ ከዕለታት ባንዳቸው ሰማይ ተከፍቶ ሰማዕታትን የብርሃን አክሊልን ሲቀዳጁ ተመለከተ ከዚኽ በኋላ ወደ ከተማ ተመልሶ ስለ ክርስቶስ አምላክነት መሰከረ፤ መኰንኑ ቅዱስ ሚናስ በወገን የከበረ መኾኑን ያውቃልና ብዙ የሹመት ቃል ኪዳን ቢገባለትም ከክርስቶስ ፍቅር ሊለይ እንደማይችል ነገረው፨

ያን ጊዜ ብዙዎች ሥቃያት አድርሶበት ስለሰለቸው ራሱን በሰይፍ እንዲቈርጡት አዝዞ ከክርስቶስ ቃል ኪዳን ተቀብሎ ኅዳር ዐሥራ ዐምስት የሰማዕትነትን አክሊል ተቀዳጀ፤ በተሰጠው ቃል ኪዳን መሠረት ለሚጠሩት በምልጃው እጅግ ፈጥኖ ይደርስላቸዋል።

የሰማዕትነት አክሊል ሲቀዳጅ ከሰማይ “ሚናስ ንኡድ ክቡር ነኽ፤ ከልጅነትኽ ዠምሮ የቅድስናን ሕይወት በመምረጥ ሦስት አክሊላትን ሰጥቼኻለኊ፤ አንደኛው ስለቅድስናኽ፣ ኹለተኛው ስለ ብቸኝነትኽ፤ ሦስተኛው ስለ ሰማዕትነትኽ” የሚል ድምፅን ከጌታችን ሰምቷል፡፡

ከዚያም መኰንኑ የቅዱስ ሚናስ ሥጋ ወደ እሳት እንዲጣል ቢያስደርግም እሳት ለ3 ቀናት ፈጽሞ ሥጋውን ሊነካ አልቻለም፤ ምእመናንም ሥጋውን ወስደው ባማሩ ልብሶች ገንዘው አኖሩት፤ የመርዩጥ አገር ሰዎች ሰራዊትን ሊአከማቹ ስለወደዱ ምልጃው ይረዳቸው ዘንድ የቅዱስ ሚናስን ሰውነት ወሰዱ፤ እነርሱም በባሕር በመርከብ ውስጥ ሳሉ ፊታቸው እንደ ከይሲ አንገታቸው እንደ ግመል አንገት ያሉ አውሬዎች ከባሕር ወጥተው አንገታቸውን ወደ ሚናስ ሥጋ በዘረጉ ጊዜ ከሰውነቱ እሳት ወጥታ እነዚያን አራዊት አቃጥላቸዋለች፤ ሰዎቹም ይኽነን አይተው በእጅጉ ተደንቀዋል፡፡

ወደ እስክንድርያ ደርሰው ሥራቸውን ፈጽመው ወደ ሀገራቸው በሚመለሱ ጊዜ የቅዱስ ሚናስን ሥጋ ከርሳቸው ጋር ሊወስዱ ወድደው በገመል ላይ በጫኑት ጊዜ ገመሉ ከቦታው የማይነሣ ኾነ፤ ኹለተኛም ሌላ ገመል ቢጭኑ ርሱም የማይነሣ ኾነ፤ ስለዚኽ ዛሬ ድረስ የቅዱስ ሚናስ ሥዕል ሲሳል እነዚኽ ገመሎች አብረው ይሳላሉ፤ እነርሱም ያ ቦታ እግዚአብሔር የፈቀደለት ቦታ መኾኑን ዐውቀው የከበረ ሥጋውን በዚያው አኖሩት፤ ከዚያም ታላቅ ቤተ ክርስቲያን ታንጾለት ሠኔ 15 ቅዳሴ ቤተ ክርስቲያኑ ተፈጽሞ ብዙዎች ድንቆች ተደርገዋል።

ብዙዎች ሕሙማን የከበረ ሥጋውን እየዳሰሱ ሲፈወሱ በቦታው ሳለኊ በዐይኖቼ ተመልክቼያለኊ፤ ዛሬም የከበረ ዐፅሙ በግብጽ ይገኛል፤ እኔም ለሐዋርያዊ አገልግሎት ግብጽ በኼድኩበት ጊዜ በእግዚአብሔር ፈቃድ በወርቃማ መጎናጸፊያ የተቀመጠ የቅዱስ ሚናስን የከበረ ሰውነቱን ለመዳሰስና ለመጸለይና ሻማ ለማብራት ችያለኊ፡፡

ቦታው እጅግ የከበረ መኾኑ ሊታወቅ እመቤታችን በጸሎት ለሚማፀኗት ከቅዱስ ሚናስ ጋር በመገለጽ እንደምትባርካቸው ይነገራል።

በግብጽ ያሉ ክርስቲያን ወንድሞቻችን እና እኅቶቻችን ቅዱስ ሚናስ ከጌታችን በተቀበለው ቃል ኪዳን በተማፀኑት ጊዜ ፈጥኖ ስለሚደርስላቸው በእጅጉ ይወዱታል፤ በተለይ ከአቡነ ሺኖዳ በፊት ለነበሩት በቅድስና ሕይወታቸው ይታወቁ ለነበሩት ለአቡነ ቄርሎስ ቅዱስ ሚናስ ተገልጦላቸው እንደባረካቸው ይነገራል፨

ከጥቂቶች በቀር በዚኽ ዘመን ያለን ብዙዎቻችን ስለዚኽ ሰማዕት ታሪክ ስላላወቅን በቃል ኪዳኑ መጠቀም አቅቶናል፤ የቅዱስ ሚናስ ቤተ ክርስቲያን በሀገራችን ኢትዮጵያ ከባሕር ዳር 15 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ከአቡነ ሐራ ድንግል ቤተ ክርስቲያን አጠገብ እንዳለ ሰምቼያለሁ፤ ይኽም እጅግ ደስ የሚያሰኝ ነው፨

የኢትዮጵያ ቀደምት ሊቃውንት የቅዱስ ሚናስን የተጋድሎ ታሪክ እና ቃል ኪዳኑን በማወቃቸው እጅግ የተጠቀሙ ሲኾን አመስግነውት አይጠግቡም ነበር፤- በተለይ ቅዱስ ያሬድ በድጓው ላይ በእጅጉ ያወደሰው ሲኾን ለምሳሌ ያኽል፡-

“ብፁዕ አንተ ሚናስ ዘመነንከ ክብረ ዘበምድር ወኀረይከ ዘበሰማይ ወኮንከ ሐራሁ ለክርስቶስ”
(የምድር የኾነ ክብርን ንቀኽ የሰማይ ክብርን የመረጥኽ የክርስቶስ ጭፍራው የኾንኽ ሚናስ አንተ ንኡድ ክቡር ነኽ)፡፡

“ሚናስ ኅሩይ በታዕካ ሰማይ ገጹኒ ብሩህ ከመ ፀሓይ በብዙኅ ሰላም አዕበዮ እግዚአብሔር”
(በሰማይ አዳራሽ የተመረጠው ሚናስ፤ ፊቱም እንደ ፀሓይ ብሩህ ነው፤ ብዙ በኾነ ሰላም እግዚአብሔር ከፍ ከፍ አደረገው) ይለዋል (ድጓ ዘሚናስ)

ሊቁ ዐርከ ሥሉስም ይኽነን የቅዱስ ሚናስን ተጋድሎውን፦
“ሰላም ለከ ሐራዊ መስፍን
ሰማዕተ መድኅን
ዘሰመየተከ ሚናስ ዘጾረተከ ማሕፀን
አመ ጸለየት ጸሎተ እንዘ ይእቲ መካን
እምሥዕለ ማርያም ሰሚዐ ዘይቤ አሜን”
(መካን ሳለች ጸሎትን እየጸለየች ሳለች ከእመቤታችን ማርያም ሥዕል አሜን የሚልን ቃልን ሰምታ የተሸከመችኽ ማሕፀን ሚናስ ብላ የሰየመችኽ የመድኅን ክርስቶስ ምስክር፤ የጦር መኰንን ለኾንኽ ላንተ ሰላምታ ይገባል) በማለት ቅዱስ ሚናስን አወድሶታል፡፡

ሊቁ አባ ጊዮርጊስ ዘጋሥጫም በተአምኆ ቅዱሳን መጽሐፉ ላይ፡-
“ሰላም ለሚናስ ኅሩይ ዘክርስቶስ ሐራይ
ጽድቀ ዘአብደረ እምነ ንዋይ፤
አምሳለ ወርኅ ወከመ ፀሓይ ብሩህ”፡፡
(የክርስቶስ ምርጥ ጭፍራ ከገንዘብ ይልቅ ጽድቅን የመረጠ እንደ ምሳሌው እንደጨረቃ ለደመቀና እንደ ፀሓይም ብሩህ ለኾነ ለሚናስ ሰላምታ ይገባል) በማለት አወድሶታል፡፡

በግብጽ ያለው የቅዱስ ሚናስ ገዳም እጅግ አስደናቂ ሲኾን ከማልረሳው ነገር በገዳሙ ስለ ሰማዕትነቱ ታሪክ ያስተማርኩትና በወርቃማ መጎናጸፊያ የተሸፈነ የቅዱስ ሚናስ የከበረ ሰውነቱን (አካሉን) ስዳስስ እጅግ ልዩ የበረከት የደስታ ስሜት ውስጤን ጎብኝቶታል።

መጋቤ ሐዲስ ሮዳስ ታደሰ (ዶክተር) Dr Rodas Tadese

20 Nov, 17:59


[የሊቀ መላእክት የቅዱስ ሚካኤል ክብር]
በመጋቤ ሐዲስ ዶክተር ሮዳስ ታደሰ
💥❖መልአክ የሚለው ቃል የግእዝ ቃል ሲኾን “ለአከ” ማለት (ላከ) ማለት ነው፤ ስለዚኽ መልአክ ማለት መልእክተኛ ማለት ነው፤ ይኸውም ሰው የጸለየውን ጸሎት ያቀረበውን መሥዋዕት ወደ እግዚአብሔር የሚያቀርቡ የእግዚአብሔርን ምሕረት ወደ ሰው የሚያመላልሱ የሚላኩ ስለኾነ የተሰጣቸው ሥያሜ ነው፡፡

💥❖ ልዑል እግዚአብሔር ሰባቱን ሰማያት ከፈጠረ በኋላ በዚያው በዕለተ እሑድ መላእክትን “እምኀበ አልቦ ኀበ ቦ” (ካለመኖር ወደ መኖር) ማእምራን (ዐዋቂዎች) ለባውያን (አስተዋዮች) አድርጎ ፈጥሯቸዋል፡፡ ከነዚኽ መላእክት ውስጥ አንደኛውና የመላእክት አለቃ የኾነው ቅዱስ ሚካኤል ነው፡፡

💥❖ ቅዱስ ሚካኤል የሚመራቸው ነገደ ኀይላት የሚባሉ በኢዮር ሰማይ የሚኖሩ መላእክትን ነው፤ ሊቁ ቅዱስ ኤጲፋንዮስም በሥነ ፍጥረት መጽሐፉ ላይ “ወለራብዕ ጾታ ዐሠርቱ ስሞሙ ኀይላት ወሊቆሙ ሚካኤል ወአንበሮሙ በራብዕ ሰማይ” ይላል አራተኛው ዐሥሩን ነገድ ስማቸውን ኀይላት ሲላቸው እነዚኽም ባለሰይፍ ሲኾኑ የእግዚአብሔርን ወዳጆች ሲጠብቁ ጠላቶቹን ይቀጣሉ፤ የእነዚኽ ነገደ መላእክት አለቃቸው ቅዱስ ሚካኤል ሲኾን በኢዮር በአራተኛው ከተማ አስፍሯቸዋል እንዲል፡፡

💥❖ ሳጥናኤል “እኔ ፈጣሪ ነኝ” ብሎ የስሕተት ንግግርን በተናገረ ጊዜ አስቀድሞ ሰራዊቱን በመያዝ ከነገደ ዲያብሎስ ጋር የተዋጋ መልአክ ነውና፤ ዮሐንስም ስለ ቅዱስ ሚካኤል ኀያልነት በራእ ፲፪፥፯-፱ ላይ፡- “በሰማይም ሰልፍ ኾነ፤ ሚካኤልና መላእክቱ ዘንዶውን ተዋጉ፤ ዘንዶውም ከመላእክቱ ጋር ተዋጋ አልቻላቸውምም ከዚያም ወዲያ በሰማይ ስፍራ አልተገኘላቸውም ዓለሙንም ኹሉ የሚያስተው ዲያብሎስና ሰይጣን የሚባለው ታላቁ ዘንዶ ርሱም የቀደመው እባብ ተጣለ፤ ወደ ምድር ተጣለ መላእክቱም ከርሱ ጋር ተጣሉ” በማለት ዲያብሎስን የተፋለመ መልአክ መኾኑን ገልጾታል፤ በዚኽም “መልአከ ኀይል” ተብሏል (ዳን ፲፥፲፫፤ ፲፥፳፩፤ ፲፪፥፩)፡፡

💥 በመጽሐፈ ሔኖክ ምዕራፍ 20 ላይ እንደምናነበው ከመላእክት በተለየ መልኩ "አካዕ" የሚለው ስመ አምላክ በእጁ ላይ ቀርጾለታል። ደራሲውም "ሰላም ለእራኅከ ስመ መሐላ ዘጸበጠ" (የመሐላ ስምን ለጨበጠ መዳፍኽ ሰላምታ ይገባል) በማለት ያወድሰዋል።

💥❖ የ99ኙ ነገደ መላእክት አለቃ ስለኾነው ስለ ቅዱስ ሚካኤል ክብር፣ ውበት፣ ምልጃ ማሕቶተ ቤተ ክርስቲያን ቅዱስ ያሬድ በመጽሐፈ ድጓው እንዲኽ ይላል፡-
👉 ስለ ቅዱስ ሚካኤል የመላእክት አለቃነቱ ቅዱስ ያሬድ እንዲኽ ይለዋል፡-
╬ “ክብረ ሚካኤል ናሁ ተዐውቀ
በትሕትናሁ ዐብየ ወልሕቀ
ዲበ አእላፍ ዘተሰምየ ሊቀ
ዘይትዐፀፍ መብረቀ ይተነብል ጽድቀ”
(የሚካኤል ክብረ እነሆ አኹን ታወቀ፤ በትሕናውም ፈጽሞ ላቀ ከፍ ከፍ አለ፤ በአእላፍ ነገደ መላእክት ላይ አለቃን የተባለ መብረቅን የሚጐናፀፍ ርሱ ጽድቅን ይለምናል) ይላል፡-

💥❖ የ99ኙ ነገደ መላእክት አለቃ ከመኾኑ ጋር ይልቁኑ ዮሐንስ በራእዩ በምዕ 8፡2 ላይ “በእግዚአብሔርም ፊት የሚቆሙትን ሰባቱን መላእክት አየሁ፥ ሰባትም መለከት ተሰጣቸው” ካላቸው፤ ከሰባቱ ሊቃነ መላእክት በመዠመሪያ የሚጠቀሰው ቅዱስ ሚካኤል ነውና ሊቁ፡-

╬ “እስመ እምአፉሁ ይወጽዕ ነጐድጓድ
ሕብረ ክነፊሁ ያንበለብል ነድ
እምሊቃነ መላእክት የዐቢ በዐውድ
ሚካኤል ውእቱ መልአኩ ለወልድ”
(የወልድ አገልጋዩ ሚካኤል ነው፤ በዙሪያው ኹሉ ካሉት ከሊቃነ መላእክት ይበልጣል፤ የክንፉ መልክ ነባልባላዊ እሳትን ያቃጥላል፤ ከአንደበቱ ነጐድጓድ ይወጣልና)

╬ “አዕበዮ ንጉሠ ስብሐት
ለሚካኤል ሊቀ መላእክት
ዘይስእል በእንተ ምሕረት
መልአከ ሥረዊሆሙ ለመላእክት”
(የምስጋና ባለቤት ክርስቶስ ለመላእክት ጭፍሮች አለቃቸው የኾነ ስለ ምሕረት የሚማልድ የመላእክት አለቃ ሚካኤልን ከፍ ከፍ አደረገው) በማለት ይጠቅሰዋል፡፡

💥❖የስሙ ትርጓሜንም ስንመለከት ሚካኤል ማለት ቃሉ የዕብራይስጥ ሲኾን ሚ- ማለት “ማን”፤ ካ- “እንደ”፤ ኤል- “አምላክ” ማለት ነውና ሚካኤል ማለት “መኑ ከመ አምላክ” (ማን እንደ አምላክ) ማለት ነው፡፡
👉 የመልክአ ሚካኤል ደራሲም ይኽነን ይዞ
╬ “ሰላም ለዝክረ ስምከ ምስለ ስመ ልዑል ዘተሳተፈ
ወልደ ያሬድ ሄኖክ በከመ ጸሐፈ”
(የያሬድ ልጅ ሄኖክ እንደጻፈው ከልዑል ስም ጋር ለተባበረ ስም አጠራርኽ ሰላምታ ይገባል) ይለዋል፡፡

💥❖ቅዱስ ያሬድም፡-
╬ “መልአከ ፍሥሐ ሚካኤል ስሙ
ለመላእክት ውእቱ ሊቆሙ
መልአኮሙ ሥዩሞሙ
የሐውር ቅድሜሆሙ እንዘ ይመርሆሙ”
(ስሙ ሚካኤል የተባለ የደስታ መልአክ ለነገደ መላእክት አለቃቸው ነው፤ የተሾመላቸው አለቃቸው ርሱ እየመራቸው በፊት በፊታቸው ይኼዳል) ይላል

💥❖በብሉይ ኪዳን ለአበው ነቢያት እየተገለጠ፤ ለሐዋርያትም በስብከት አገልግሎታቸው እየተራዳ፤ ለሰማዕታት፣ ለቅዱሳን አበው በተጋድሏቸው እየተገለጠላቸው አስደሳች መልኩን ያዩት ነበር፤ ይኽነን የቅዱስ ሚካኤልን ውበት ቅዱስ ያሬድ እንዲኽ ይገልጠዋል፡-
╬ “መልአከ ፍሥሐ ዘዐጽፉ መብረቅ
ሐመልማለ ወርቅ ሚካኤል ሊቅ”
(መጐናጸፊያው መብረቅ የኾነ የደስታ መልአክ፤ አለቃ ሚካኤል የወርቅ ዐመልማሎ ነው)

💥❖የመልክአ ሚካኤል ደራሲም ይኽነን ውበቱን ሲገልጠው፡-
╬ “ሰላም ለአክናፊከ እለ በሰማያት ያንበለብሉ
ከመ ሠርቀ ፀሓይ ሥነ ጸዳሉ”
(የጸዳሉ ውበት እንደ ፀሓይ አወጣጥ የኾነ በሰማያት ለሚያንበለብሉ ክንፎችኽ ሰላምታ ይገባል) ይለዋል፡፡

💥❖ ቅዱስ ያሬድ ደግሞ፡-
╬ “ውእቱ ሊቆሙ ወመልአኮሙ ሚካኤል ስሙ
ዐይኑ ዘርግብ ልብሱ ዘመብረቅ
ሐመልማለ ወርቅ”
(ዐይኑ የርግብ (እንደ ርግብ የዋህ፣ ጽሩይ) የኾነ ልብሱ የመብረቅ መጐናጸፊያ የኾነለት የወርቅ ዐመልማሎ ስሙ ሚካኤል የተባለ ርሱ የመላእክት አለቃቸው መሪያቸው ነው) ይላል፡፡

💥❖የቅዱስ ሚካኤል ተራዳኢነትና አማላጅነት ቅዱስ ያሬድ እንዲኽ ይገልጠዋል፡-
╬ በ፲ወ፬ቱ ትንብልናከ ዐቢይ ልዕልናከ
በመንክር ትሕትናከ
አስተምህር ለነ ሰአልናከ”
(በዐሥራ አራቱ ልመናኽ ምልጃኽ፤ በታላቅ ልዕልናኽ በሚያስደንቅም ትሕትናኽ ሚካኤል ትለምንልን ዘንድ ማለድንኽ)

╬ “ዘወሀበ ትንቢተ ለኤልዳድ ወሙዳድ
አመ ምጽአቱ ይምሐረነ ወልድ
ሰአል ለነ ሚካኤል መንፈሳዊ ነገድ
ከመ ንክሃል አምስጦ እምሲኦል ሞገድ”
(ለኤልዳድና ለሙዳድ የትንቢትን ጸጋ የሰጠ የሚኾን ወልድ በሚመጣ ጊዜ ይምረን ዘንድ ከረቂቅ ነገድ ወገን የኾንኸው ሚካኤል ከሲኦል እሳታዊ ሞገድ ማምለጥ እንችል ዘንድ ለእኛ ለምንልን) ይላል፡፡

╬ “ከናፍሪሁ ነድ ዘእሳት አልባሲሁ ዘመብረቅ ሚካኤል ሊቀ መላእክት ውእቱ ይዕቀብክሙ ነግሀ ወሠርከ ሌሊተ ወመዐልተ” (ከናፍሮቹ የእሳት ልብሶቹ የመብረቅ የኾነ የመላእክት አለቃ ሚካኤል በተራኢነቱ በጠዋትም፤ በሠርክም፤ በቀንም በሌሊትም ይጠብቃችኊ) እንዲል።

💥❖ቅዱስ ሚካኤልን ጨምሮ እነዚኽ ቅዱሳን መላእክት ሰው የጸለየውን ጸሎት ያቀረበውን መሥዋዕት ቅድመ እግዚአብሔር በማድረስ የእግዚአብሔርን ምሕረት ወደ ሰው በማምጣት ሰውን ከአምላካቸው ጋር በማማለድ ጸንተው ያሉ እንደኾኑ በብዙ ሥፍራ ላይ ተዘርዝሯል፡- ለምሳሌ ያኽል ዘፍ 48፥15፤ ዘጸ 23፥20፤ መሳ 6፥11፤ ኢዮ 33፥23፤ መዝ 33፥7፤ 88፥6፤ 90፥11፤ 1ነገ 19፥5፤ 2ነገ 6፥15፤ ዳን 3፥17፤ 4፥13፤ 8፥15-19፤ ዘካ 1፥12፤ ማቴ 18፥10፤ ሉቃ 1፥19፤ 13፥6-9፤ 15፥7፤ ዮሐ 20፥11፤ የሐዋ 12፥6፤ ዕብ 1፥14፤ ራእ 8፥3-4ን ይመልከቱ)፡፡

መጋቤ ሐዲስ ሮዳስ ታደሰ (ዶክተር) Dr Rodas Tadese

20 Nov, 07:58


ኅዳር 11 የቅድስት ሐና ዕረፍት አስመልክቶ ስለ ክብሯ የጻፉ የኢትዮጵያ ሊቃውንት ምስክርነት
በመጋቤ ሐዲስ ዶክተር ሮዳስ ታደሰ
[በሊቁ የአባ ጊዮርጊስ ዘጋሥጫ መጻሕፍት]
[እመቤታችንን ስለመውለዷ]
❖“ሰላም ለሐና እንተ ወለደታ ለማርያም
ዘኮነት ተንከተመ ጽድቅ ለኲሉ ዓለም፤
ድንግል ወእም፤
ወላዲቱ ለፀሓይ
ዳግሚት ሰማይ”፡፡

(ፀሓይን የወለደችው ኹለተኛዪቱ ሰማይ፤ ድንግልም እናትም፤ ለዓለሙ ኹሉ የእውነት ድልድይ (መሸጋገሪያ) የኾነችዪቱን ማርያምን ለወለደቻት ለሐና ሰላምታ ይገባል) (አባ ጊዮርጊስ ዘጋሥጫ በተአምሆ ቅዱሳን)

[ቅድስት ሐና እመቤታችንን ስለፀነሰችበት ዕለት]

“ወይእዜኒ ኦ ውሉደ እግዚአብሔር ወማኅበረ ቅድስት ቤተ ክርስቲያን ናስተብፅዖሙ ለሐና ወለኢያቄም ዘወለዱ ለነ ዛተ ቡርክተ ወቅድስተ መርዓተ፤ አይ ይእቲ ዕለት ዕለተ ሩካቤሆሙ ንጽሕት እንተ ባቲ ሐንበበት ፍሬ ቡርክተ ድንግልተ አስራኤል ኢጽዕልተ፤ አይ ይእቲ ዛቲ ዕለት ቅድስት ዕለተ ድማሬሆሙ ለእሉ በሥምረተ እግዚአብሔር ተገብረ ተፀንሶታ ለርግብ ንጽሕት ዘእምቤተ ይሁዳ፤ አይ ይእቲ ዕለት ዕለተ ፍሥሓ እንተ ባቲ ኮነ ተመሥርቶ ንድቅ ለማኅፈደ ንጉሥ”

(አኹንም የእግዚአብሔር የጸጋ ልጆችና የቅድስት ቤተ ክርስቲያን ማኅበሮች ሆይ ይኽቺን የተባረከችና የተመረጠች ሙሽራ የወለዱልንን ኢያቄምንና ሐናን እናመስግናቸው የማትነቀፍ የእስራኤል ድንግልን የተባረከችዋን ፍሬ ያፈራችበትን ንጽሕት የምትኾን የሩካቤያቸው ዕለት እንደምን ያለች ዕለት ናት? ከይሁዳ ወገን ለኾነችው ንጽሕት ርግብ መፀነስ በእግዚአብሔር ፈቃድ የተደረገ የጾታዊ ተዋሕዷቸው ቀን ይኽቺ እንዴት ያለች የተመረጠች ቀን ናት፤ ለንጉሥ ማደሪያ አዳራሽ መመሥረት የተደረገባት (የኾነባት) የደስታ ቀን እንዴት ያላት ቀን ናት?) (አባ ጊዮርጊስ ዘጋሥጫ አርጋኖን ዘረቡዕ)

[የኢሳይያስ ትንቢት ቅድስት ሐና በወለደቻት በእመቤታችን ስለመፈጸሙ]
በከመ ፈቀደ ወአልቦ ዘይከልኦ ገቢረ ዘኀለየ በከመ ጽሑፍ ዘይብል ትወፅእ በትር አምሥርወ ዕሴይ ወየዐርግ ጽጌ እምጒንዱ ምንት ውእቱ ፀአተ በትር እምሥርወ ዕሴይ ወየዐርግ ጽጌ እምጒንዱ ምንት ውእቱ ፀአተ በትር እምሥርው ዘእንበለ ዘርዐ ሙላድ ዘቅድስት ድንግል እንተ ኮነት እምኀበ ኢያቄም ውስተ ማሕፀነ ሐና እስመ ዘርዐ ዕሴይ ውእቱ ኢያቄም አቡሃ ለማርያም ወምንትኑመ ካዕበ ዕርገተ ጽጌ እምጒንድ ዘእንበለ ሥጋዌ መለኮት እምወለቱ"

(ከዕሴይ ሥር በትር ትወጣለች፤ ከግንዱም አበባ ይወጣል የሚል እንደተጻፈ፤ ያሰበውን ለማድረግ የሚከለክለው የለም፤ ከኢያቄም አብራክ ተከፍላ በሐና ማሕፀን ከተፀነሰች ከቅድስት ድንግል የትውልድ ዘር በቀር የበትር ከሥሩ መውጣት ምንድን ነው? የእመቤታችን የማርያም አባቷ ኢያቄም ከዕሴይ ዘር ነውና፤ ዳግመኛም ከኢያቄም ሴት ልጁ የመለኮት ሰው መኾን በቀር የአበባ ከግንዱ መውጣት ምንድን ነው?) (አባ ጊዮርጊስ ዘጋሥጫ፤ መጽሐፈ ምስጢር)

[ስለ ቅድስት ሐና የሊቁ የአባ ጽጌ ድንግል ምስክርነት]
❖[ቅድስት ሐና እመቤታችንን ስለፀነሰችባት ዕለት]
“ሚ ቡርክት ወቅድስት ይእቲ
ሰዓተ ትፍሥሕት ሐና ዘጸገየተኪ ባቲ
ወፈረየኪ ለሕይወት ኢያቄም መዋቲ
እሴብሕ ተአምረኪ ርግብየ አሐቲ
ወድኀኒተ ኲሉ ዓለም እስመ ኮንኪ አንቲ”

(ሐና አንቺን የፀነሰችባት የደስታ ቀን ምን ያኽል የተባረከች የተቀደሰች ናት፤ ሟች ኢያቄምም ለሕይወት አንቺን ያፈራባት ቀን ምን ያኽል የተባረከች የተቀደሰች ናት፤ አንዲቱ ርግቤ ማርያም አንቺ የዓለሙ ኹሉ መድኀኒት ኾነሻልና ታምርሽን አመሰግናለኊ) (ማሕሌተ ጽጌ)

[ስለ ሐና ማሕፀን]
“ጸግይየ ሣዕረ ዘኪሩቤል ልሳነ
ተአምረኪ በነጊር እመ ኢፈጸምኩ አነ
ባሕቱ አአኲት ማርያም ዘጾረተኪ ማሕፀነ
እንዘ ሀለወት ፀኒሳ ኪያኪ ርጢነ
ለለገሰስዋ ላቲ ትፌውስ ዱያነ”

(ሳርን የኾንኊ እኔ የኪሩቤል አንደበትን ገንዘብ አድርጌ ታምርሽን በመንገር በማስተማር ባልፈጽምም ነገር ግን ማርያም የተሸከመቺሽን የሐናን ማሕፀን አመሰግናለኊ፤ መድኀኒት አንቺን ፀንሳ ሳለች ርሷን የዳሰሷትን ድዉያንን ኹሉ ትፈውስ ነበር) (ማሕሌተ ጽጌ)

[ስለ ሐና አበባ ስለ ድንግል ማርያም]
“ለንጉሠ ነገሥት ሰሎሞን ከመ ተፈሥሐ ልቡ
በዕለተ ወፃእኪ መርዓት ለአንበሳ ትንቢት እምግቡ
ማእከለ ማኅበር ፍሡሓን ተአምረኪ እንዘ እነቡ
እዜምር ለኪ ጽጌ ሐና ወፍኖተ ነፈርዐጽ እሌቡ
ከመ ጣዕዋ ሐሊበ ዘይጠቡ”

(ትንቢት ከተነገረለት ከአንበሳ ጉድጓድ፤ ድንግል ሙሽራ በተገኘሽ ጊዜ የንጉሦች ንጉሥ የሰሎሞን ልቡ እንደተደሰተ፤ ደስ ባላቸው በመላእክት አንድነት ፊት ታምርሽን እየተናገርኊ የሐና አበባ ማርያም እዘምርሻለኊ፤ ወተትን ጠብቶ እንደሚዘልል እንቦሳም ዝለል ዝለል ይለኛል) (ማሕሌተ ጽጌ)

[ቅድስት ሐና እመቤታችንን ይዛ ወደ ቤተ መቅደስ ስለመግባቷ]
❖“የሐዝነኒ ማርያም ዘረከበኪ ድክትምና
አመ ቤተ መቅደስ ቦእኪ እንዘ ትጠብዊ ሐሊበ ሐና
ወያስተፌሥሐኒ ካዕበ ትእምርተ ልህቀትኪ በቅድስና
ምስለ አብያጺሁ ከመ አብ እንዘ ይሴስየኪ መና
ፋኑኤል ጽጌ ነድ ዘይከይድ ደመና”

(ማርያም የሐናን ወተት እየጠባሽ ወደ ቤተ መቅደስ በገባሽ ጊዜ ያገኘሽ ብቸኝነት ያሳዝነኛል፤ ዳግመኛም በደመና የሚመላለስ ደመናን የሚረግጥ የእሳት አበባ ፋኑኤል ከጓደኞቹ መላእክት ጋር መናን እየመገበሽ በንጽሕና የማደግሽ ተአምር ደስ ያሰኘኛል) (ማሕሌተ ጽጌ)

[በሊቁ በዐርከ ሥሉስ ለቅድስት ሐና የቀረበ ውዳሴ]

"ሰላም ለኪ ለጸሎተ ኩሉ ምዕራጋ
ከመ አስካለ ወይን ዲበ ሐረጋ
ሐና ብፅዕት ተፈሥሒ እንበለ ንትጋ
እስመ ረከብኪ ሞገሰ ወአድማዕኪ ጸጋ
እምሔውተ አምላክ ትኩኒ በሥጋ"

(በሐረጓ ላይ እንዳለች የወይን ፍሬ ለጸሎት ኹሉ መውጫዋ ለኾንሽ ሰላምታ ይገባሻል፤ በሥጋ የአምላክ አያት ልትኾኚ ሞገስና ጸጋን ያገኘሽ ያለ ጉድለት ብፅዕት የኾንሽ ሐና ደስ ይበልሽ) [ዐርከ ሥሉስ፤ ዐርኬ]

በነግሥ ላይ፦
"ክልኤቱ አእሩግ አመ በከዩ ብካየ
ረከቡ ወለተ ዘታስተሰሪ ጌጋየ
ለወንጌላውያን ኩልነ ዘኮነተነ ምጉያየ
ኢያቄም ወሐና ወለዱ ሰማየ
ሰማዮሙኒ አሥረቀት ፀሐየ"

(ኹለቱ አረጋውያን ልቅሶን ባለቀሱ ጊዜ ለኹላችን ወንጌልን ለምናስተምር መሸሻን የኾነችን በደልን በምልጃዋ የምታስደመስስ ልጅን አገኙ፤ ኢያቄምና ሐና ሰማይን ወለዱ፤ ሰማያቸውም ፀሐይን አወጣች) (ነግሥ)

በመጋቤ ሐዲስ ዶክተር ሮዳስ ታደሰ

መጋቤ ሐዲስ ሮዳስ ታደሰ (ዶክተር) Dr Rodas Tadese

16 Nov, 21:04


በቀንዱ የማይበራታ ላሕም ተብሎ የተመሰገነው የወልደ እግዚአብሔር ቅዱስ ሥጋው የሚፈትትባት፤ ክቡር ደሙ የሚቀዳባት በአራቱ ኪሩቤል አምሳል አራት መአዝን ያላት ቤተ ክርስቲያንን በገጸ ላሕም አምሳል ገልጦ በተአምኆ ቅዱሳን ላይ ስማቸውን በመጥቀስ ሲያወድሳቸው፦

[“ሰላም ለ፬ እንስሳሁ ለአብ እለ ይጸውሩ መንበሮ እለ ስሞሙ አግርሜስ ገጸ አንበሳ፡፡ አግርሜጥር ገጸ ሰብእ፡፡ ባርቲና ገጸ ላሕም፡፡ አርጣን ገጸ ንስር፡፡ ለቀዳማዊ ገጹ ከመ አንበሳ፤ በአምሳለ ፈጣሪሁ ዘውእቱ አብ፡፡ ለካልዕ ገጹ ከመ ሰብእ በአምሳለ ወልድ፤ ዘውእቱ ነሥአ ፍጹመ ስባኤ፡፡ ለሣልስ ገጹ ከመ ንስር በአምሳለ መንፈስ ቅዱስ ዘውእቱ አስተርአየ በርእየተ ርግብ በሥጋ፡፡ ወለራብእ ገጹ ከመ ላሕም በአምሳለ ቅድስት ቤተ ክርስቲያን፤ እስመ ፬ቱ መኣዝኒሃ”፡፡]

(የአብ ዙፋኑን ለሚሸከሙና ስማቸውም የአንበሳ መልክ ያለው አግርሜስ፤ የሰው መልክ ያለው አግርሜጥር፤ የላም መልክ ያለው ባርቲና፤ የንስር መልክ ያለው አርጣን ለተባሉ ለአራቱ እንስሳ ሰላምታ ይገባል፤ የመዠመሪያው ፊቱ እንደ አንበሳ ነው፤ ያውም በፈጣሪው በአብ ምሳሌ ነው፤ የኹለተኛውም ፊቱ ያውም ፍጹም ሰውነትን ገንዘብ ባደረገ በወልድ አምሳል እንደ ሰው ነው የሦስኛውም ፊቱ ያውም አካል ባለው ርግብ አምሳል በተገለጠ በመንፈስ ቅዱስ አምሳል እንደ ንስር ነው፤ ያራተኛውም ፊቱ እንደ ላም ነው፤ በቅድስት ቤተ ክርስቲያን ምሳሌ፤ መኣዝኗ አራት ናቸውና) በማለት ሰላምታን አቅርቦላቸዋል፨
[በመጋቤ ሐዲስ ዶክተር ሮዳስ ታደሰ]
[የኪሩቤልና የሱራፌል በረከት አይለየን]
ከመጋቤ ሐዲስ ዶክተር ሮዳስ ታደሰ (በድጋሚ ፓስት የተደረገ)

መጋቤ ሐዲስ ሮዳስ ታደሰ (ዶክተር) Dr Rodas Tadese

16 Nov, 21:04


[ኅዳር 8 የእግዚአብሔርን ዙፋን የሚሸከሙ የኪሩቤልና የሱራፌል ዓመታዊ በዓል፤ ክብራቸውና ስማቸው]
በመጋቤ ሐዲስ ዶክተር ሮዳስ ታደሰ
ክብራቸው ታላቅ የኾኑት የኪሩቤልን ነገር ሊቁ ኤጲፋንዮስ “ስሞሙ ኪሩቤል ካህናተ ቅዳሴ ወውዳሴ እምታሕተ ሐቌሆሙ አሐዱ ወእምላዕለ ሐቌሆሙ አርባዕቱ እለ ግሉፋን በአዕይንት” ብሎ እንደገለጸው ኹለተኞቹ አመስጋኞች የኾኑት ዐሥሩን ነገድ ስማቸው ኪሩቤል ሲባሉ ከወገባቸው በታች አንድ ከወገባቸው በላይ አራት አድርጎ ሲፈጥራቸው ዐይናቸው ብዙ ነው፤ አለቃቸውም ኪሩብ ሲኾን የሰው መልክና የአንበሳ መልክ ያለው ነው፡፡

ሦስተኛውን ዐሥሩን ነገድ ስማቸው ሱራፌል ሲባል የእነዚኽ አለቃቸው የንስር መልክና የእንስሳ መልክ ያለው ነው፤ አለቃቸውም ሱራፊ ሲባል ሲፈጥራቸውም ስድስት ስድስት ክንፍ አድርጎ ፈጥሯቸዋል፨

ልዑል እግዚአብሔር ከነገደ ኪሩቤል ኹለት ገጸ ሰብእ እና ገጸ አንበሳን፤ ከሱራፌል ኹለት ገጸ ንስርና ገጸ እንስሳን አንሥቶ ከኢየሩሳሌም ሰማያዊት በላይ ከሰማይ ውዱድ በታች አቁሞ በነርሱ ላይ ሰማይ ውዱድን እንደ መረሻት ጫነባቸው፤ በላይም ሕብሩ በረድ የመሰለውን ዙፋን እንደ ሠረገላ ጭኖባቸዋል፤ እነዚኽንም በምሥራቅ፣ በምዕራብ፣ በሰሜን፣ በደቡብ በአራቱ መኣዝን ዠርባቸውን ወደ ውስጥ ፊታቸውን ወደ ውጪ እያደረገ አቁሟቸዋል።

ነቢዩ ሕዝቅኤል ስለዚኽ ነገር በምዕ ፩፥፲፪ ላይ “እያንዳንዱም ወደ ፊት ቀጥ ብሎ ይኼድ ነበር መንፈስም ወደሚኼድበት ኹሉ ይኼዱ ነበር ሲኼዱም አይገላመጡም ነበር” በማለት እንደተናገረ ገጽ ለገጽ ሳይተያዩ ሥላሴ በፈቀዱት ፍኖት አንዱ በኼደበት ሦስቱ እየተከታተሉ ይኼዳሉ፡፡

እነዚኽንም እንደ ነቢዩ ሕዝቅኤል ገለጻ ፲፮ ሲኾኑ የቀሩት ከውስጥ ስለኾኑ ስለማይታዩ አራቱ ግን ብቅ ብቅ ብለው ስለሚታዩ ዮሐንስ አራት ብሏቸዋል እንጂ እንደ ሕዝቅኤል ገጻቸው ፲፮ ነው ይላሉ መተርጉማን፡፡

ሊቁ “እምርእሶሙ እስከ ሐቌሆሙ አርባዕቱ ወእምሐቌሆሙ እስከ እግሮሙ አሐዱ ከመ ርእየተ እለ ቄጥሩ ዘውእቱ ዖፍ ዘይነብር በሀገረ ፋርስ” እንዲላቸው፤ ሊቁ ቅዱስ ያሬድም “ከመ ርእየተ እለቄጥሩ ገጸ በገጽ ኢይትናጸሩ” ብሎ እንደገለጻቸው በፋርስ ሀገር የሚኖረው እለቄጥሩ የተባለውን ዎፍ ከወገቡ በታች አንድ ከወገቡ በላይ አራት እንደኾነ እነዚኽንም ከወገባቸው በታች አንድ ከወገባቸው በላይ አራት አድርጎ ፈጥሯቸዋል ፡፡

ዮሐንስ በራእዩ በምዕ 4:7-9 ላይ "ፊተኛውም እንስሳ አንበሳን ይመስላል፥ ሁለተኛውም እንስሳ ጥጃን ይመስላል፥ ሦስተኛውም እንስሳ እንደ ሰው ፊት ነበረው፥ አራተኛውም እንስሳ የሚበረውን ንስር ይመስላል። አራቱም እንስሶች እያንዳንዳቸው ስድስት ክንፎች አሉአቸው፥ በዙሪያቸውና በውስጣቸውም ዓይኖች ሞልተውባቸዋል፤ ቅዱስ፥ ቅዱስ፥ ቅዱስ፥ የነበረውና ያለ የሚመጣውም ሁሉንም የሚገዛ ጌታ አምላክ እያሉ ቀንና ሌሊት አያርፉም" ይላቸዋል።

ኪሩቤልን “እለ ብዙኃት አዕይንቲሆሙ” አላቸው፤ ከላይ እስከ ታች ድረስ ዐይንን የተመሉ ናቸውና፤ ይኽስ አይደለም እንደ ብርሌ እንደ ብርጭቆ እያብለጨለጨ ለዐይን ባልተመቸም ነበር ብሎ ዐልፎ ዐይን ዐልፎ ዐይን ነው፤ እንደ አልጋ መለበሚያ እንደ ሱቲ መጠብር እንደ ቀሽመሪ መታጠቂያ፣ እንደ ነብር ለምድ፣ እንደ ዐይነ በጎ፣ እንደ ማር ሰፈፍ ይላሉ፤ ይኽስ አይደለም ብሎ ዐይናቸው ከአንገታቸው በላይ ሰድ ነው፤ ይኽም እንደ መስታዮት እያወለወለ እንደ ብርጭቆ እያንጸበረቀ አይደለም ብሎ ኀላፍያትን መጻእያትን የሚያውቁ ስለኾነ እንዲኽ አለ እንጂ ዐይናቸውስ ኹለት ነው ይላሉ የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ቀደምት መተርጉማን ፡፡

በኢሳ ፮፥፩-፫ ላይ፡- “ንጉሡ ዖዝያን በሞተበት ዓመት እግዚአብሔርን በረዥምና ከፍ ባለ ዙፋን ላይ ተቀምጦ አየኹት የልብሱም ዘርፍ መቅደሱን መልቶት ነበር፤ ሱራፌልም ከርሱ በላይ ቆመው ነበር ለእያንዳንዱም ስድስት ክንፍ ነበረው በኹለት ክንፍ ፊቱን ይሸፍን ነበር በኹለቱም ክንፍ እግሮቹን ይሸፍን ነበር በኹለቱም ክንፍ ይበር ነበር፤ አንዱም ለአንዱ ቅዱስ፣ ቅዱስ፣ ቅዱስ የሰራዊት ጌታ እግዚአብሔር ምድር ኹሉ ከክብሩ ተመልታለች እያለ ይጮኽ ነበር” ይላል ይኽ መሸፈናቸው ያድናቸዋል ቢሉ? ትእምርተ ፍርሀት ነው፤ ዛሬ በዚኽ ዓለም ሴቶችን ሕፃናትን እንመታችኋለን ባሏቸው ጊዜ እጃቸውን መጋረዳቸው የሚያድናቸው ኾኖ ሳይኾን ትእምርተ ፍርሀት እንደኾነ ኹሉ፡፡

አንድም በኹለት ክንፋቸው ፊታቸውን መሸፈናቸው ፊትኽን ማየት አይቻለንም ሲሉ በኹለት ክንፋቸው እግራቸውን መሸፈናቸው ከፊትኽ መቆም አይቻለንም ሲሉ፤ ኹለት ክንፋቸውን ወዲያና ወዲኽ ያደርጋሉ አለ ትእምርተ ተልእኮ ነው፡፡

አንድም በኹለት ክንፋቸው ፊታቸውን መሸፈናቸው ባሕርይኽን መመርመር አይቻለንም ሲሉ፤ በኹለት ክንፋቸው እግራቸውን መሸፈናቸው ባሕርይኽን መረማመድ መተላለፍ አይቻለንም ሲሉ፤ ኹለት ክንፋቸውን ወዲያ ወዲኽ ያደርጋሉ ከእእምሮ ወደ አእምሮ ለመፋለሳቸው፡፡

አንድም ኹለት ክንፋቸውን ወደ ላይ አድርገው ይታያሉ አለ ወደላይ ቢወጡ ቢወጡ አትገኝም ሲሉ፤ ኹለት ክንፋቸውን ወደታች አድርገው ይታያሉ ወደታች ቢወርዱ ቢወርዱ አትገኝም ሲሉ፤ ክንፋቸውን ወዲያና ወዲኽ ያደርጋሉ ወዲያና ወዲኽ ቢሉ አትገኝም ሲሉ፤

አንድም ወደላይ መዘርጋት በሰማይ ምሉእ ነኽ ሲሉ ወደታች መዘርጋቸው በምድርም ምሉእ ነኽ ሲሉ፤ ወዲያና ወዲኽ መዘርጋታቸው በኹሉ ምሉእ ነኽ ማለታቸው ነው፤

አንድም ወደላይ መዘርጋት ትእምርተ ተመስጦ ወደታች መዘርጋት ትእምርተ ትሕትና፤ ወዲያና ወዲኽ ረብቦ መታየት ትእምርተ ተልእኮ ነው

በአጠቃላይ ኹለት ክንፋቸውን ወደላይ ኹለት ክንፋቸውን ወደታች ኹለት ክንፋቸውን ወዲያና ወዲኽ አድርገው ትእምርተ መስቀል መሥራታቸው በብሉይ ኪዳን ከኾነ እንዲኽ ባለ መስቀል ተሰቅለኽ ዓለምን ታድነዋለኽ ሲሉ በዘመነ ሐዲስ የኾነ እንደኾነ እንዲኽ ባለ ትእምርተ መስቀል ተሰቅለኽ ዓለምን አድነኸዋል ሲሉ ነው፡፡

የእነዚኽ አርባዕቱ እንስሳ መላእክት ፊታቸው በርካታ ምስጢራትን ሲያመለክቱ ገጸ ሰብእ በማቴዎስ፤ ገጸ አንበሳ በማርቆስ፤ ገጸ ላሕም በሉቃስ፤ ገጸ ንስር በዮሐንስ ተመስሏል።

ዳግመኛም የሰው ፊት ያለው መልአክ ለሰው ልጆች ይማልዳል። የአንበሳ ፊት ያለው መልአክ ለዱር አራዊት ይለምናል። የላም ፊት ያለው መልአክ ለእንስሳት ይጸልያል። የንስር ፊት ያለው መልአክ ለሰማይ አዕዋፋት ኹሉ ይለምናል በማለት ሊቃውንት ያመሰጥራሉ።

በሌላ ምስጢር የሰው ገጽ ያለው የጌታን ሰው የመኾንን ነገር፤ የላም መልክ ያለው በቀራንዮ ላይ ደሙን ማፍሰሱ፤ የአንበሳው መልክ ያለው የጌታችንን ትንሣኤ፤ የንስር መልክ ያለው የጌታን ዕርገት እንደሚያመለክቱ ቀደምት መተርጒማን ይተነትኑታል።

ዐምደ ሃይማኖት አባ ጊዮርጊስ ዘጋሥጫም እጅግ ምጡቅ በኾነው ዕውቀቱ ዕጓለ አንበሳ የተባለው የወልድ የባሕርይ አባቱን አብን በአንበሳ ይመስለዋል።

ሥጋን ተውሕዶ ፍጹም ሰው የኾነው ወልድን የሰው መልክ ባለው መስሎ ገልጾታል፡፡

በአምሳለ ርግብ ወርዶ በወልድ ራስ ላይ ተቀምጦ የታየው መንፈስ ቅዱስን የንስር መልክ ባለው መስሎ አብራርቶ ጽፎታል።

መጋቤ ሐዲስ ሮዳስ ታደሰ (ዶክተር) Dr Rodas Tadese

14 Nov, 19:46


[የቁስቋም ክብር በኢትዮጵያ ቀደምት ሊቃውንት]
በመጋቤ ሐዲስ ዶክተር ሮዳስ ታደሰ
ከ3 ዓመት የስደት ውጣ ውረድ በኋላ የአምላክ እናት ልጇ አምላካችን ክርስቶስን ይዛ አረጋዊ ዮሴፍና ሰሎሜን አስከትላ ከመዐዲ ወደ ላዕላይ ግብጽ በጀልባ ደግሞ ከካይሮ በስተደቡብ 320 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ በላዕላይ ግብጽ በምትገኘው ወደ ደብረ ቊስቋም ገብተው በመንገድ ጒዞ ካገኛቸው ድካም 6 ወር ከ10 ቀናት ዐርፈዋልና ኅዳር 6 በደመቀ መልኩ በዓሏ ይከበራል፡፡

በደብረ ቁስቋም ሳሉ ጨካኙ ሄሮድስ እንደሞተ የጌታ መልአክ በግብፅ ለዮሴፍ በሕልም ታይቶ "የሕፃኑን ነፍስ የፈለጉት ሞተዋልና ተነሣ፥ ሕፃኑን እናቱንም ይዘኽ ወደ እስራኤል አገር ኺድ" ብሎታል (ማቴ 2፡19-20)።

ይኽቺን ጌታ ከእናቱ ጋር ያረፈባትን የተቀደሰች ቦታን ጌታችን ባርኳት ወደ ናዝሬት ተመልሰዋል። ጌታችን ካረገ ከብዙ ዘመን በኋላ በኅዳር ስድስት ቀን “አስተጋብኦሙ እግዚእነ ለሐዋርያቲሁ ቅዱሳን ውስተ ዝንቱ ደብረ ቊስቋም ወቀደሰ ታቦተ ወቤተ ክርስቲያን ወሠርዐ ቊርባነ ወመጠዎሙ ሥጋሁ ቅዱሰ ወደሞ ክቡረ” ይላል (በዚኽ በደብረ ቊስቋም ቅዱሳን ሐዋርያቱን ሰበሰባቸው ታቦትንና ቤተ ክርስቲያንንም አክብሮ የቊርባን መሥዋዕትንም ሠርቶ ቅዱስ ሥጋውን ክቡር ደሙን ሰጥቷቸዋል) ይላል፡፡

በዚኽ ምክንያት ደብረ ቁስቋምን የእስክንድርያ ቤተ ክርስቲያን ሊቃውንት በግብጽ የመጀመሪያዋ ቤተ ክርስቲያን ይሏታል፤ የግብጽ ኦርቶዶክስ ምእመናን በእጅጉ የሚወዷት የቁስቋም ገዳም ስትኾን በ1993 ዓ.ም. ላይ እመቤታችን በገዳሙ ተገልጣ እንደነበር ይናገራሉ፤ በዚኽችም ገዳም 100 መነኮሳት ይገኙበታል፤ ከቦታዋ ክብር የተነሣ "ዳግሚት ቤተልሔም" ይሏታል፤ በገዳሙም በቅዱሳት መጻሕፍት የተመላ ታላቅ ቤተ መጻሕፍት አለ፨

በጌታ በተባረከችው ይኽቺ ቦታ ላይ በ3ኛው መቶ ክፍለ ዘመን ላይ ቅዱስ ጳኩሚስ ገዳምን የገደመ ሲኾን፤ የእስክንድርያ 23ኛ ፓትርያርክ ቴዎፍሎስ በታናሿ ሕንጻ ቤተ ክርስቲያን ምትክ ታላቅ ቤተ ክርስቲያን ለመሥራት ባሰበ ጊዜ እመቤታችን ተገልጻለት የልጇ የክርስቶስ ትሕትናው በገዳሙ እንዲታሰብበት ባለበት እንዲኾን ነግራዋለች።

በርካቶች የኢትዮጵያ ሊቃውንት እመቤታችን ከልጇ ጋር ወደ ቊስቋም የመግባቷን ነገር የጻፉ ሲኾን ለምሳሌም አባ ጊዮርጊስ ዘጋሥጫ በሰዓታት መጽሐፉ ላይ በስፋት ሲዘረዝረው፡-

[“በሊዓ ሕፃናት ሶበ ኀለየ ሄሮድስ አርዌ ሰማይ
ምስለ ዮሴፍ አረጋይ
ነገደት ቊስቋመ ናዛዚተ ሐዘን በብካይ”]
(የሰማዩ አውሬ ሄሮድስ ሕፃናትን መብላት ባሰበ ጊዜ፤ ከሐዘንና ከልቅሶ የምታረጋጋ ማርያም ከአረጋዊዉ ዮሴፍ ጋራ ወደ ቊስቋም ኼደች (ተሰደደች))

“አሥረጸት ማርያም አክናፈ ረድኤት አምሳለ ዖፍ ለዐሪገ ቊስቋም
ህየ ከመ ትትዐቀብ ዘመነ ወአዝማነ ወመንፈቀ ዘመን በከመ ይቤ መጽሐፍ”
(ማርያም ወደ ቊስቋም ተራራ ለመውጣት እንደ ዎፍ የረድኤት ክንፎችን አበቀለች በመጽሐፍ እንደተናገረ በዚያ በዘመንና በዘመናት በዘመን እኩሌታም ትጠበቅ ዘንድ)

“ብጽዐን ለኪ ኦ ደብረ ቊስቋም
እምኲሎን አድያም እምናዝሬት እስከ ቤተልሔም
ዘተጸወነ ላዕሌኪ መድኀኔ ኲሉ ዓለም”
(ከናዝሬት እስከ ቤተ ልሔም ካሉ አውራጆች ኹሉ የዓለም ኹሉ መድኀኒት ወደ አንቺ የተጠጋ የቊስቋም ተራራ ሆይ ክብር ይገባሻል)

“በቃለ ውዳሴ ጥዑም ይደሉ ሰላም
ለዕበይኪ ፍጹም አድባረ ቊስቋም
ማኅደረ ልዑል ዘአርያም”
(በአርያም ያለ የልዑል ማደሪያው የኾንሽ የቊስቋም ተራራ ሆይ ፍጹም ለሚኾን ክብርሽ በሚጣፍጥ የምስጋና ቃል ሰላምታ ማቅረብ ይገባል) በማለት ዘርዝሮ ጽፎላታል፡፡

ቅዱስ ያሬድም ቅድስት ድንግል ማርያም ልጇ ኢየሱስ ክርስቶስን ይዛ በስደቷ ወቅት በደብረ ቊስቋም ስለማረፏ በድጓው ላይ ሲጽፍ፡-

“መንግሥቱ ሰፋኒት ዘእምቅድመ ዓለም
ወልደ ቅድስት ማርያም
ኀሠሠ ምእራፈ ከመ ድኩም
ንጉሥ ዘለዓለም
ግሩም እምግሩማን ብርሃነ ሕይወት ዘኢይጸልም
ኀደረ ደብረ ቊስቋም”
(ቅድመ ዓለም የነበረች ጌትነቱ ምልእት ስፍሕት የኾነች የቅድስት ድንግል ማርያም የባሕርይ ልጅ የዘለዓለም ንጉሥ ሲኾን እንደ ደካማ ማረፊያን ፈለገ፤ ከግሩማን ይልቅ ግሩም፤ የማይጨልም የሕይወት ብርሃን ርሱ በደብረ ቊስቋም ዐደረ)

“መንክር ወመድምም ዘተገብረ በደብረ ቊስቋም
መንክር ወመድምም ዘይሴባሕ በአርያም
አምላክ ፍጹም ኀደረ ውስቴቱ መድኀኔ ዓለም
ዘሀሎ እምቅድም
ኀደረ ውስቴቱ ለዝንቱ ደብር ዘአብ ቃል
ምስለ እሙ ድንግል ደመና ቀሊል”
(በደብረ ቊስቋም የተደረገው የሚያስደንቅ እና የሚያስገርም ነው፤ በአርያም የሚመሰገን ፍጹም የባሕርይ አምላክ መድኀኔ ዓለም በውስጡ ዐደረ፤ ቅድመ ዓለም የነበረ የአብ አካላዊ ቃል ፈጣን ደመና ከተባለች ከድንግል እናቱ ጋር በዚኽ ደብር በውስጡ ዐድሯል) በማለት መስክሮላታል፡፡

እኔም ለወንጌል አገልግሎት ወደ ግብጽ ኼጄ በነበረ ጊዜ እመቤታችን ልጇን ይዛ ከስደት ስትመለስ ከአረጋዊ ዮሴፍና ከሰሎሜ ጋር ከድካም ያረፉበት ይኽቺን ቅድስት ቦታ ገዳመ ቁስቋምን ስረግጣትና ጌታችን ከእናቱ ጋ የተቀመጡበት ዋሻ ውስጥ ገብቼ የተቀደሰችውን ቦታ ስስማት መጀመሪያ ያሰብኩት ቅዱሱ አባት አባ ጽጌ ብርሃን በማሕሌተ ጽጌው ላይ፦

“ተአምረ ግፍእኪ ለአርእዮ እምገጸ ሄሮድስ መስቴማ
አመ ጐየይኪ ማርያም በሐዊረ ፍኖት እለ ደክማ
ምስለ እግረ ጽጌኪ ልምሉም ኀበ አእጋርኪ ቆማ
ለምድረ ገዳምኪ ቅድስት ቊስቋም ስማ
እምፈተውኩ በጺሕየ በሰጊድ እሰዓማ”
(ማርያም የግፍሽን ተአምር ለመግለጥ ከጠላት ሄሮድስ ፊት በሸሸሽ ጊዜ ከለመለመች ከልጅሽ እግር ጋር መንገድን በመኼድ የደከሙ እግሮችሽ የቆሙባት ስሟ ቊስቋም የተባለ የተቀደሰች ገዳምሽን እኔም ደርሼ ብሳለማት እመኛለሁ እወዳለሁ) በማለት የጸለያት ጸሎትን ነበር፡፡

የእመቤታችን በረከት ይደርባችኊ፤ ቦታዋን ያላያችሁ ለመሳለም ኹላችኹንም ያብቃችሁ እላለሁ፡፡
[ከመጋቤ ሐዲስ ዶክተር ሮዳስ ታደሰ] [በድጋሚ ፓስት ያረኩት]

መጋቤ ሐዲስ ሮዳስ ታደሰ (ዶክተር) Dr Rodas Tadese

07 Nov, 18:39


https://youtu.be/ZtPRXjvIG_A?si=pLpldjZ5KHP2d5nh

መጋቤ ሐዲስ ሮዳስ ታደሰ (ዶክተር) Dr Rodas Tadese

06 Nov, 20:34


"ዕውቀት እንደ ጎርፍ የሚፈስበት የደለዊ (አኳሪየስ) የነፋስ ዘመን ምድራችን ተቀላቅላለች። በአኳሪየስ ቴክኖሎጂ ጫፍ ላይ ዕውቀት በቀላሉ ይፈስሳል። በዓመታት ውስጥ ትምህርት ቤቶችም ላይኖሩ ስለሚችሉ፤ ወዳጄ ከዘመኑ ጋር ለመወዳደር ዕውቀትን አልፈህ ጥበብን ያዝ"
(ዶክተር ሮዳስ ታደሰ)

መጋቤ ሐዲስ ሮዳስ ታደሰ (ዶክተር) Dr Rodas Tadese

02 Nov, 01:49


https://youtu.be/qyGsXfT8fqs?si=UZb9pJEzUiWyrdUV

መጋቤ ሐዲስ ሮዳስ ታደሰ (ዶክተር) Dr Rodas Tadese

28 Oct, 15:18


💥ታላቅ የምሥራች💥 በመቅደላ ጦርነት በእንግሊዞች ከተወሰዱት ውስጥ "የመቅደላ ጋሻ" (The Shield of Magdala) በመባል የሚታወቀው የንጉሠ ነገሥት የዐጼ ቴዎድሮስ ጋሻ ወደ ሀገሩ ኢትዮጵያ ዐርብ ጥቅምት 22/ 2017 ዓ.ም. ይገባል።
👉 ይኽ ታላቅ ታሪካዊ ቅርስ እንግሊዝ ባለው "አንደርሰን ኤንድ ጋርላንድ" በኩል ጨረታ ላይ ቢወጣው በዐጼ ኃይለ ሥላሴ የልጅ ልጅ በልዑል ኤርምያስ ሣሕለ ሥላሴ ኃይለ ሥላሴ በኩል በተቋቋመው የሮያል ትረስት ተቋም በከፍተኛ ውይይት ወደ ኢትዮጵያ ሊመለስ መኾኑን ዓለም ዐቀፍ ሚዲያዎች እየዘገቡት ነበረ።
👉 ጥረቱ በመሳካቱ የመቅደላ ጋሻ አሁን በሰሜን አሜሪካ በኦሀዮ ቶሌዶ የኪነ ጥበብ መዘክር እጅግ በርካት የውጪ ሀገር ተመራማሪዎች፣ የክብር እንግዶች በተገኙበት ቅዳሜ ጥቅምት 16 በሰሜን አሜሪካ በኦሀዮ ቶሌዶ የኪነ ጥበብ ቤተ መዘክር ከፍተኛ የአቀባበል ሥርዓት ተደርጓል። በዕለቱም በዶክተር አሉላ ፓንክረስት ከመቅደላ በተወሰዱት የኢትዮጵያ ቅርሶች ዙሪያ ጥናታዊ ጽሑፍ የቀረበ ሲኾን እኔም በቦታው በክብር እንግድነት በመገኘት ጋሻው ወደ እናት ሀገሩ ኢትዮጵያ ዐርብ ጥቅምት 21 ከመግባቱ በፊት ለመጎብኘት ችያለኹ። 👉 በዚኹ አጋጣሚ የዐጼ ኃይለ ሥላሴ የልጅ ልጅ ቃለ መጠይቅ ያደረኩ ሲኾን በመቅደላ ጦርነት በ15 ዝኆኖች በ200 በቅሎዎች ከኢትዮጵያ የወጡት ውድ ቅርሶችና የብራና መጻሕፍት ወደ እናት ሀገራቸው እንዲመለሱ ዲፕሎማሲያዊ ጥረት እንደሚያደርጉ ገልጠዋል ሊንኩን https://youtu.be/oSZrLtDqwlw?si=yKDltLnhJbupPJ3w

👉 የአቀባበል ሥርዓት የተደረገበት በቶሌዶ የኪነ ጥበብ ቤተ መዘክር ውስጥ እጅግ ብዙ ቅርሶች የሚጎበኙ ሲሆን በርካታ ጥንታውያት ብራና መጻሕፍት፣ መስቀሎች፣ ቅዱሳት ሥዕላት የሚገኙ ሲኾን ሰፊ ጉብኝት ለ2 ቀናት ለማድረግ ችያለኹ።

👉 የመቅደላ ታሪክን ለማስታወስ ያኽል ዐጤ ቴዎድሮስ ወደ ሺሕ የሚጠጉ በልዩ ልዩ ጌጥ ያጌጡ፤ በልዩ ልዩ ሐረግ የተንቈጠቈጡ የብራና መጻሕፍትን ከመላው ኢትዮጵያ ካሉ ገዳማትና አድባራት አሰብስበው በመቅደላ መድኀኔ ዓለም ቤተ ክርስቲያን አኑረውት ነበር፡፡

👉 የእንግሊዝ ጦር በጄኔራል ናፒየር እየተመራ ድል ካደረገ በኋላ ስለተወሰዱት ቅርሶች ጆሴፍ ፍራንሲስ “Tewodros Prince of Ethiopia” በሚለው ጽሑፉና ተክለ ጻድቅ መኩሪያ በኢትዮጵያ ታሪክ መጽሐፋቸው እንደገለጡት፡-
✍️ “በንጉሣዊ ቤተ መጻሕፍት የሚገኙ በሺዎች የሚቆጠሩ የሀገሪቱ ጥንታዊ ድርሳናትና የብራና መጻሕፍት፤ ዐሥር አስደናቂ ታቦታት፣ መንበሮች፣ ንዋያተ ቅድሳት፣ ሥዕላት፣ የተለያዩ ውብና ድንቅ የወርቅ ጌጣጌጦች፤ የወርቅ፣ የብር፣ የነሐስ መስቀሎች፣ ለክብረ በዓላት ብቻ የሚወጡ አስደናቂ ቅርጽ ያላቸው መስቀሎች፣ የአቡኑ አክሊልና ታላቅ ማኅተም ተወሰዱ። የተወሰዱት ንብረቶች ቅርሶች በ15 ዝኆኖችና በ200 በቅሎዎች ጭነው ወሰዱ። የማይፈልጉትን ድርሳናትና ቅርሶችን እንዲጠፉ በአምባው በየአግጣጫው ወረወሩት፤ እነዚኽም በ፭ ኪሎ ሜትር ርቀት ሙሉ ተጥለው ይገኙ ነበር፤ የተወሰደው ቅርስ ከብዛቱ የተነሣ ለኹለት ቀናት ለፈጀ ጨረታ አቅርበውት ነበር፤ የእቃው ክምችት ግማሽ ኤከር (4,047 ካሬ ሜትር) ስፋት ያለውን መሬት ሸፍኖት ነበረ።
ዘመቻውን ተከትሎ የመጣው የእንግሊዝ ሙዚየም ባልደረባ የኾነው ሆልምስ ታላቁ ተጫራች ነበር፤ የተወሰዱ ቅርሶች በጊዜው በእንግሊዝ ገንዘብ ሠላሳ ሰባት ሚሊየን ፓውንድ ነበር ወይም አንድ ቢሊየን ብር ይገመታሉ” ይላል ፡፡

👉 ዐምስት መቶውንን ድንቅ የኢትዮጵያውያን የብራና መጻሕፍትን እንግሊዝ ባሉት ቤተ መጻሕፍት ተከፋፍለው እንዲቀመጡ ሲደረጉ፤ የመጻሕፍቱን ዝርዝር እንግሊዛዊዉ ዊሊያም እና ጀርመናዊዉ ዲልማን ጽፈዋቸዋል፡፡ ከአራት ዓመት በኋላ ዐጤ ዮሐንስ ከመቅደላ የተዘረፉትን ቅርሶች ይልቁኑ የጌታችን ኲርዐተ ርዕሱ (ራሱ በዘንግ ሲመታ) የሚያሳየውን እጅግ የሚያስደንቅ ኢትዮጵያዊ ሥዕል እንዲመለስ የእንግሊዟን ንግሥት ቪክቶሪያን ቢጠይቁም እንግሊዞች ግን እንደማይመልሱ በመናገር ከመቅደላ ከወሰዷቸው ዐምስት መቶ የብራና መጻሕፍት ውስጥ መርጠው አንዱን “ክብረ ነገሥትን” ብቻ መልሰውልናል፡፡

👉 ዐጼ ቴዎድሮስ ከእንግሊዞች ጋር ባደረጉት ጦርነት ዐጼ ራሳቸውን በማጥፋታቸው የተበሳጩት አንግሊዞች የንጉሠ ነገሥቱን ሹሩባ (ቁንዳላ) ቆርጠው ከመቅደላ ወስደው በእንግሊዝ አርሚ ሙዚየም ውስጥ ከ 154 ዓመታት በላይ ከቆየ በኋላ የኢትዮጵያውያን ቅርስ ወደ ኢትዮጵያ ተመልሶ በመጋቢት 2011 ዓ.ም ወደ ከብሪታኒያ ወደ ኢትዮጵያ መመለሱ ይታወሳል። ጥቀምት 22 ዐርብ ደግሞ ጋሻቸው ይገባልና

"ታጠቅ ብሎ ፈረስ ካሳ ብሎ ስም
ዐርብ ዐርብ ይሸበራል ኢየሩሳሌም"
ተብሎ በተገጠመላቸው ግጥም በማብቃት በሰሜን አሜሪካ በተገኙ ታላላቅ እንግዶች የነበረው ታላቅ የክብር አቀባበል ድንቅ ነበርና ወደ እናት ሀገሩ በዶክተር አሉላ ፓንክረስት ጥቅምት 22 ሲመለስ ደረጃውን የመጠነ ሀገራዊ አቀባበል ለንጉሠ ነገሥቱ ጋሻ እንደሚደረግ አምናለኹ።
መጋቤ ሐዲስ ዶክተር ሮዳስ ታደሰ
#RoyalEthiopiantrust

መጋቤ ሐዲስ ሮዳስ ታደሰ (ዶክተር) Dr Rodas Tadese

28 Oct, 15:12


https://youtu.be/oSZrLtDqwlw?si=LNWTaLHnbOJpcOLe

መጋቤ ሐዲስ ሮዳስ ታደሰ (ዶክተር) Dr Rodas Tadese

21 Oct, 23:58


888, 37 Alpha 73

መጋቤ ሐዲስ ሮዳስ ታደሰ (ዶክተር) Dr Rodas Tadese

16 Oct, 17:36


https://www.instagram.com/s/aGlnaGxpZ2h0OjE4MjM2NzIxNTQ3MjU3Njg5?story_media_id=3375487640801826685_5523912516&igsh=aDNuZnN4dTJpMzhi

መጋቤ ሐዲስ ሮዳስ ታደሰ (ዶክተር) Dr Rodas Tadese

16 Oct, 13:45


👉 የሕትመት ዋጋ በመጨመሩ አንባብያን በመጻሕፍት መሸጫ ዐጥተውት በጠየቁት መሠረት የመጋቤ ሐዲስ ዶክተር ሮዳስ ታደሰ "888" መጽሐፍ ለአራተኛ ጊዜ ታትሞ ለአንባብያን ቀርቧል።
👉 መጽሐፉ በሀሁ የመጻሕፍት ማከፋፈያ እና በተለያዩ መሸጫዎች ይገኛል።

💥 መጽሐፉ በ27 ምዕራፍ የተከፈለ ሲኾን በኢትዮጵያ የፊደል ቀመር ውስጥ የሚገኙ:-
👉 የፊደላት ጂኦሜትሪ፣ ድምፅ፣ ቁጥር
👉 በመቅረዙ ውስጥ የተቀመጠው የ7 የብርሃን ቀመር
👉የ አ ቡ ጊ ዳ ሙሉ ቀመር
👉 በመጽሐፈ ሔኖክ የሚገኘው የስመ አምላክ ቀመር
👉 በገነት ውስጥ የነበሩ የዕፀ ሕይወት እና ዕፀ ጥበብ ቀመር
👉 በግእዝ ፊደላት ያለው የ3.14 የፓይ ቀመር
👉 የ DNA እና RNA ቀመር
👉 የፔሪዮዲክ ሠንጠረዥ የንጥረ ነገራት ቀመር
👉 የፕሩቶንና የኤሌክትሮን ቀመር
👉 የልብ እና የአእምሮ ዐይኖች መክፈቻ የግእዝ ቀመር
👉 በ182 የግእዝ ፊደላት የተቀመረው የኢኪውኖክስ (Equinox) ቀመር
👉 በፊደላችን የሚገኝ የሥርዐተ ፀሐይ ቀመር
👉 ከአድማስ እስከ ናጌብ የምድር ልኬት ቀመር
👉 በፊደላችን የተገለጸ የጨረቃና የምድር ራዲየስ ልኬት
👉 በግእዝ ፊደላችን የተገለጸ በሜትር ፐር ሰከንድ የሚቀመር የድምፅ ፍጥነት
👉 በፊደላችን የተገለጸ በሚክሮሜትር የሚቀመር የቀይ የደም ሴል፣ በደም ቧንቧ ውስጥ ያለው ቀመር
👉 በግእዝ ፊደላት ውስጥ የሚገለጸው ቀመረ ምጽአትና የርኅወተ ሰማይ (የሰማይ ደጃፍ) Portals መክፈቻ ቀመር እና ሌሎች ብዙ ድንቅ ምስጢራት ተካተውበታል።
👉 በውጪ ሀገር የምትኖሩ በቀላሉ በአማዞን ላይ ማግኘት ይቻላል። ሊንኩም https://www.amazon.com/dp/B0BGZ14FBD/ref=cm_sw_em_r_mt_dp_X81QK1M112XS84KPYFSY

#የሀሁ_መጽሐፍት_መደብር

አድራሻ  ቁ.1 አራት ኪሎ አብርሆት ጎን
               2 ሜክሲኮ ደብረወርቅ ሕንጻ
              ስ.ቁ  0911006705/0924408461

37,995

subscribers

510

photos

35

videos