👉 የተወደዳችሁ አንባብያን እመቤታችን እግዚአብሔር ወልድን የመውለድዋ የእናትነቷ ምሥጢር ከአብ ጋር ያመሳስላታል፡፡ ይህ እንደምንድ ነው ቢሉ ፦
፩– በቀዳማዊ ልደት አብ ያለ እናት ወልድን ወለደው በድኃራዊ (በሁለተኛ) ልደት ደግሞ እመቤታችን ያለ አባት ጌታን ወልዳለችና በዚህ የአብ ምሳሌው ሆነች፡፡ ስለዚህ ነገር አበው ‹‹ ልደት ቀዳማዊ ተዓውቀ በድኃራዊ ልደት ›› ያሉት አምስት ሺህ አምስት መቶ ዘመን ሲፈጸም ከእመቤታችን ያለአባት መወለዱ ቅድመ ዓለም ከአብ ያለእናት እንደተወለደ ያስረዳል፡፡ ቅዱስ ዳዊትም ስለዚህ ነገር በዝማሬው ‹‹ እግዚአብሔር በይሁዳ ታወቀ ስሙም በእስራኤል ታላቅ ነው ›› ኣለ ይኸም ከይሁዳ ወገን (በነገድ) ከሆነች ከእመቤታችን ያለኣባት በመወለዱ ከአብ ያለ እናት የመወለዱን ሃይማኖት ተገለጸ ማለት ነው፡፡
፪. አብ የወለደው ወልድን ነው እመቤታችንም ሥግው ቃልን እንጂ የሩቅ ብእሲ እናት ባለመሆኗ አብን መሰለችው፡፡ ስለዚህም እመቤታችንን ወላዲተ አምላክ እንላታለን፡፡
👉 ቅዱስ ያሬድም « ወይቤላ እግዚአብሔር ለማርያም አዝማንየ አዝማንኪ አምጣንየ አምጣንኪ ማርያም ሐቀፍኪዮ ወአነ ዮም ወለድክዎ» ( እግዚአብሔር ማርያምን ዘመኖቼ ዘመኖችሽ መጠኖቼ መጠኖችሽ ናቸው። እኔ ዛሬ ወለድኩት ማርያም ሆይ አንቺ ታቀፍሺው) (ቅ ያሬ ድጓ) « ዘመኖቼ ዘመኖችሽ ናቸው » ማለቱ ዓለም ከመፈጠሩ ዘመን ከመቆጠሩ በፊት በእርሱ ኅሊና መኖሯን የሚያስረዳ ነው። ይህም አዳምን ሳይፈጥረው በፊት እንደሚበድል እና በርስዋም አማካኝነት እንደሚያድነው ያውቅ ነበር ለማለት ነው። ቅዱስ ጳውሎስ « ዓለም ሳይፈጠር በፊቱ ቅዱሳን፥ ንጹሓንና ያለ ነውር በፍቅር ያደረገን ዘንድ ለእርሱ መረጠን » (ኤፌ ፩፥፬) በማለት ዓለም ሳይፈጠር ፍጥረታት ሁሉ በአምላክ የታወቁ መሆናቸውን ገልጾልናል።
፫. ‹‹ እም ኀበ አብ ወጽአ ቃል ዘእንበለ ድካም ወእም ድንግል ተወልደ ዘእንበለ ሕማም ›› (ውዳሴ ማርያም ዘሐሙስ ) እንዲል ከአብ አካል ዘእምአካል ባሕርይ ዘእምባሕርይ ድካም ሳይሰማው እንደተወለደ አምስት ሺህ አምስት መቶ ዘመን ሲፈጸም ከድንግል ሕማም ሳይሰማት እርሱም ሕጻናትን የሚሰማው ሳይሰማው ተወልዷል በዚኽም እመብርሃን አብን መሰለችው፡፡
ዛሬ ሴት ስትወልድ ታምጥ የለምን ቢሉ ይህስ አድፈን ለመንጻታችን ምልክት ነው እንላለን፡፡ ቀድሞ በኦሪት 40 ዕለት በምጥ ተጨንቀው የሚቆዩበት ጊዜ ነበር በዚህም የምጥ ጽናት እና ብዛት በጥፍራቸው በጣታቸው ምድርን እስከመቆፈር ይደርሱ ነበር፡፡ ዛሬ በሐዲስ ኪዳን ግን ይህንን መርገም ጌታችን በቸርነቱ ብዛት በመስቀል በፈጸመው ካሳ ኣርቆልናል፡፡ ዛሬ የተወሰነ ምጥ መኖሩ እንዲህ ያለ መከራ ኣበረብን ጌታ ግን ከዚህ ሁሉ ኣዳነን ብለን ለማመስገን እንዲሆነን ነው፡፡ እመቤታችን ግን በዘር ይተላለፍ የነበረ ይህ መርገም ቀድሞውኑ ያልደረሰባት፤ እንደኛም ኣድፋ ኋላ የነጻች ስላልሆነች ጌታን ስትወልደው ምንም ሕማም ጣር ሳይኖርባት ነውና በዚህ ኣብን መሰለችው፡፡
፬. ወልድ ለአብ ተቀዳሚ ተከታይ የሌለው ብቸኛ የበኸር (የበኩር) ልጁ እንደሆነ ለእመቤታችንም ተቀዳሚ ተከታይ የሌለው ብቸኛ የበኸር ልጇ ነውና በዚህም አብን መሰለችው፡፡ ውልድ ለአብ ብቸኛ እና የበኸር ልጁ ለመሆኑ በመጽሐፍ ቅዱስ ተገልጧል ለምሳሌ፡-ቅዱስ ጳውሎስ ‹‹ በኩሩን ወደ ዓለም ሲያስገባ›› (ዕብ 1፤6) በማለት የበኸር ልጅነቱን ሲገልጥልን ቅዱስ ዮሐንስ በወንጌል ‹‹ እግዚአብሔርን ያየው ኣንድስ እንኳ የለም በአባቱ እቅፍ ያለው ኣንድ ልጁ ገለጠልን እንጂ ›› ባለው እና ‹‹ አንድያ ልጁን እስኪሰጥ ድረስ ዓለሙን ወዷልና ›› (ዮሐ 1፤18/ 3፤17) በማለቱ ብቸኛ ልጁ መሆኑን ገልጦልናል፡፡
ይህማ በመስቀል ስር ከቅዱስ ዮሓንስ በስተቀር ሌላ ወንድ ሰው ቢያጣ ነው እንጂ ልጆችዋ እነስምኦን ፡ ዮሳ… አሉ የሚል ቢኖር እኛም መልሰን አንተ ሰው ‹‹ አንተን በመስቀል ላይ ቢሰቅሉህ እናትህን እና እውነተኛ ባልንጅራህን በመስቀል ሥር ብታይ ያን ባልንጅራህን እባክህን ያጽናኗት ዘንድ ወደ ልጅዎችዋ እና ወደ ባልዋ (ወደ ወንድሞቼ እና ወደ አባቴ) ወስደህ ስጥልኝ ትለዋለህ እንጂ እነሆ እናትህ ብለህ እርሱ እንዲወስዳት ታዘዋለህን? ›› ይኸስ ከልማድ ውጪ ነው፡፡
👉 ለፍጥረትስ ሁሉ ምግባቸውን የሚሰጥ ጌታ ወተት እየመገቡ ያሳደጉን ክቡር ጡቶቿን ፍጡር እንዴት ሊቀርበው ይቻለዋል ‹‹ ስላጠባኸው ጡቶቿ ›› እያሉ ይማጸኑበታል እንጂ፡፡ ቀድሞ በኦሪት ፈጣሪ ሊቀ ነቢያት ሙሴን ሲያዘው ከሰውም ሆነ ከእንስሳት ወገን የእናቱን ማህጸን አስቀድሞ ከፍቶ የሚወጣውን (የሚወለደውን) የእርሱ እንደሆነና እንዲለይለት ኣዞታል፡፡ ዳግመኛም ከሚያገኙት ከኣሥር ኣንድ (አሥራትን) ለፈጣሪ ብቻ እንደሆነ ለሰውም ሆነ ለተለያዩ ጥቅም እንደማያደርጓቸው ሁሉ እመቤታችንም ለእርሱ ለፈጣሪ እናትነት ብቻ የተለየች በመሆኑዋ ሌላ ልጅንም ባለመውለዷ እግዚአብሔር አብን መሰለችው፡፡ (ዘዳ 1፤31)
👉 ስለዚህ ሁሉ ነገር እመቤታችንን ‹‹ አብን ያየንብሽ ›› እያልን እናመሰግናታለን፡፡ ይህንንም ጌታችን ‹‹ እኔን ያየ አብን አይቷል ›› (ዮሓ፲፬ ) በማለቱ ገልጦልናል፡፡ ‹‹እኔን ያየ›› ሲል በመለኮቱ አይደለም መለኮት በሥጋ ድንግል ተገልጦ ቢታይ ዲዳሰስ ነው እንጂ፡፡ ከድንግል የሚታይ የሚዳሰስ ሥጋን ባይነሳ (ገንዘብ ባያደርግ) ኖሮ ባላየነው ባልዳሰስነውም ነበር፡፡ ወልድ በሥጋ ድንግል ተገልጦ ማየታችን ከእርሱ ጋር በሕልውና አንድ የሆነ አብን እንደማየት ነው፡፡ ስለዚህ ጌታችን ‹‹ እኔን ያየ አብን ዓየ›› አለ፡፡ በዚህ ሁሉ ነገር እመብርሃን አብን መሰለችው ለዚህ ታላቅ ክብር በመብቃትዋ ከፍጡራን በላይ ከፈጣሪ በታች መሆንዋ ተገለጠ፡፡ ስለሁሉም ነገር ፈጣሪ የተመሰገነ ይሁን የወላዲተ አምላክ ረድኤት ኣይለየን፡፡ ይቆየን
✍️ አምኃ ሥላሴ / መኩሪያ ተስፋዬ
https://t.me/+VBt2ld_HeykCaELL (ቴሌግራም ቻናል )
https://t.me/+Vd4rG3DjWHFlDGCo (ቴሌግራም ግሩፕ)
https://m.facebook.com/mekuria.tesfaye.71
https://www.youtube.com/channel/UC8v52_jNY156sxZtplafDtw/about (የዩቱብ አድራሻ)