•••
እስራኤልን ከግብጽ ባርነት እየመራቸው ማውጣቱን የሚዘከርበት በዓል ነው፡፡ ይህም የሆነው ያዕቆብ በረሃብ 70 ኹኖ ወደ ግብፅ ከወረደ በኋላ ከ215 ዓመታት (አብርሃም ወደ ግብፅ በተሰደደ ከ430 ዓመታት) በኋላ፤ የዮሴፍን ዝና ያልሰማ፥ ዮሴፍን የማያውቅ ፈርዖን በግብፅ ነገሠ፡፡ እስራኤል ከእኛ ይልቅ በዝተዋል ጠላቶቻችን ቢነሱብን ከጣለቶቻችን ጋር ተደርበው ያጠፉናል በማለት አገዛዝ አጸናባቸው ፥ ፍርድ አጓደለባቸው፡፡
•••
የእስራኤል ሴቶች ልጅ ሲወልዱ ወንድ ከሆነ እንዲገደል በማድረግ መከራ አጸናባቸው፡፡ ለ215 ዓመታት በግብፅ በባርነት ከቆዩ በኋላ ከዕብራውያን ወገን የሆነችው ራሔል ጭቃ እያቦካች ምጥ በያዛት ጊዜ ከሥራዋ እንዲያሳርፏት ጠየቀች ፤ ግብጻውያን ግን የሕፃናቱ ደም ጡቡን ያጠነክራል ርገጭ አሏት፡፡ ከማሕፀኗ የወጡ ሁለት መንትያ ልጆቿን እያየች ከጭቃ ጋር ረገጠች ፤ ራሔልም መሪር ልቅሶን አለቀሰች ፤ ስለ ልጆቿም መጽናናትን እንቢ አለች፡፡
•••
የእስራኤል ንጉሥ ሆይ የሆነብንን እይ ስትል ራሷን ይዛ ታለቅስ ጀመር ፥ እንባዋንም ወደ ሰማይ ንጉሥ ወደ እግዚአብሔር ረጨች፡፡ የራሔል እንባዋ የሕዝበ እስራኤልን ሁሉ ጩኸት ፥ እሮሮ ይዛ ቅድመ እግዚአብሔር ደረሰች፡፡ “. . . ራሔል ስለ ልጆቿ አለቀሰች የሉምና ስለ ልጆቿ መጽናናት እንቢ አለች” /ኤር 31፥5፤ ማቴ 2፥17/ እንዲል፡፡
•••
ከዚህ በኋላ እግዚአብሔር ሙሴን አስነሳና፤ በሊቀ መላእክት ቅዱስ ሚካኤል መሪነት፤ 10 ተዓምራትን በምድረ ግብፅ በ11ኛ ተዓምር ደግሞ በኅዳር 12 ( ፈርዖንን ከነሠራዊቱ በኤርትራ ባሕር አስጥሞ ) ወደ ተስፋይቱ ምድረ መራቸው፡፡ ባሕረ ኤርትራን እስራኤላውያን እንደተሻገሩም የእስራኤል ልጆች የሙሴ የአሮን እኅት ማርያም ከበሮ እየመታች ‹‹ ንሴብሖ ለእግዚአብሔር ስቡሐ ዘተሰብሐ ፤ እግዚአብሔር ተዋጊ ነው ስሙም እግዚአብሔር ነው እያሉ፡፡ ››
•••
ጠላታቸውን የመታላቸውን ፥ እነሱንም በተአምራቱ ያሻገራቸውን ፥ ከጠላታቸው እጅ ያዳናቸውን እግዚአብሔርን አመሰገኑ፡፡ ከዚህ በኋላ መጋቤ ብሉይ ቅዱስ ሚካኤል እየመራቸው ፥ መና ከሰማይ እያወረደላቸው ፥ ውሃ ከጭንጫ እያፈለቀላቸው ፥ ቀኑን በደመና ፥ ሌቱን በብርሃን መርቷቸው አርባ ዘመን ተጕዘው የቃል ኪዳን አገራቸው ምድረ ርስት ከነዓንን ( የዛሬዋ ኢየሩሳሌምን ) ወርሰዋል፡፡ /ዘጸ. 15/
•••
ከሙሴ በኋላ እስራኤልን የመራው ነቢዩ ኢያሱም እስራኤልን በሚመራበት ጊዜ ሊቀ መልአኩ ቅዱስ ሚካኤል እስራኤልን ይረዳቸው ነበር፡፡ ከጠላቶቻቸው ጋር ሲዋጉም ሰልፉን ይመራ የነበረው ቅዱስ ሚካኤል ነበር፡፡ ለምሳሌ እስራኤላውያን ከኢያሪኮ አጠገብ በነበሩበት ጊዜ ቅዱስ ሚካኤል ተገልጦ ኢያሱን አነጋግሮታል፡፡
•••
ኢያሱ በኢያሪኮ አጠገብ ሳለ ቀና ብሎ ሲመለከት የተመዘዘ ሰይፍ በእጁ የያዘ አንድ ሰው ከፊቱ ቆሞ አየ፤ ኢያሱም ወደ እርሱ ቀርቦ “ከእኛ ወገን ነህ ወይስ ከጠላቶቻችን?” ሲል ጠየቀው፡፡ እርሱም “አይደለሁም ነገር ግን የእግዚአብሔር ሠራዊት አለቃ በመሆኔ መጥቻለሁ” ብሎታል /ኢያሱ 5፥13-15/፡፡
•••
ይህ የተመዘዘ ሰይፍ ይዞ ከኢያሱ ፊት ለፊት የቆመው መልአክ መልአኩ ቅዱስ ሚካኤል (እንዲሁም መልአኩ ቅዱስ ራጕኤል) ነው፡፡ ይህን ለአብነት አነሣን እጅ እስራኤል በሚበድሉበት ጊዜ ሁሉ ወደ እግዚአብሔር የሚማልድላቸው ይህ ታላቅ መልአክ መጋቤ ብሉይ ቅ/ሚካኤል ነበር ፤ እግዚአብሔር አምላክ በእደ መልአኩ ይጠብቀን ፤ ከበዓሉ ረድኤት ፥ በረከት ይክፈለን ፤ አሜን
••••
የቴሌ ግራም ቻናላችን - https://t.me/Terbinos
የቲክ ቶክ የገፃችን - https://www.tiktok.com/@yeamanuelljochi
የፌስቡኩ ገፃችን - https://www.facebook.com/terbinos