(ክፍል 2 ~ የመጨረሻ ክፍል)
ማሳሰቢያ!
ማንም ሰው ይሄን ታሪክ አንብቦ ሳይጨርስ እንዳያልፈው!
በክፍል አንድ ታሪካችን … ሕይወት ከምሥራቅ ወለጋ ታፍኖ የጠፋባትን ፍቅረኛዋን ለማግኘት ወደ አዲስ አበባ መጥታ ሜክሲኮ ያለው የፌደራል ፖሊስ ቢሮ ሄዳ ስትጠይቅ "እንደዛ የሚባል ሰው የለም" ብለዋት ግቢውን በጩኸት ካደበላለቀችው በኋላ፤ ኮሚሽነር ጀነራል ደመላሽ ገብረ ሚካኤል ቢሮ ተወስዳ፤ ጄነራሉሜ ጀርባውን ሰጥቶ "አሸባሪ ባል ምን ያደርግልሻል? ሀገር የሚያሸብር! እኛ ደግሞ መንግሥት ለመገልበጥ የሚሠሩትን አንታገሳቸውም። በተለይ ዐማራዎችን" በማለት ከትከት ብሎ ስቆባት ነበር የተጠናቀቀው።
ቀጣዩንና የመጨረሻውን ክፍል እነሆ፦
…እያለቀስሁ ልወጣ ስል እጄን ያዝ አደረገና "ምርመራው አልቋል ሰኞ ፍ/ቤት ይቀርባል። ፍ/ቤት መምጣት ትችያለሽ?" አለና መቀመጫዬን ቸብ አድርጎ አስወጣኝ። ወደ አክስቴ ቤት ኃይሌ ጋርመንት አካባቢ ሄጄ ሰኞን መጠባበቅ ጀመርኩ። ሰኞ በማለዳ ልደታ ፍ/ቤት ሄድሁ።
በፍጹም ማመን አልቻልሁም። በእውነት የኔ ፍቅር ነው? የራስ ጸጉሩ አድጎ ተንጨፋሯል። ጉንጩ የጺም ጫካ ሆኗል። እጁ በሰንሰለት ታስሯል። ሰውነቱ አልቋል። የኔ ድሀ ርሀብተኛ ሆኗል። ተንደርድሬ ላቅፈው ስል አንዱ ፖሊስ ወደ ኋላ ገፈተረኝ። ፍቅር ወደ ኋላ ዙሮ እያያኝ ዕንባው ሲፈስ ታየኝ። ወደ ችሎቱ ገባሁ። እንደምንም ብሎ እኔን ለማዬት ሲቀበዘበዝ ሳዬው አልቻልኩም። ዕንባዬን ለቀቅሁት። ዓይን ለዓይን እየተያየን ተላቀስን።
ለካ ያቺ ቀን የመጨረሻዋ የብይን ቀን ነበረች። የተከሰሰው መጀመሪያ "የአብንና የፋኖ አባል ነህ" ተብሎ ነው። "በአሸባሪነት ሕገመንግስታዊ ሥርዓቱን በኃይል ለመናድ" ተብሎ ነበር.... ዓይኔ እያዬ ምንም በማያውቀው ወንጀል የት እንዳለ ሳላውቅ ሁለት ዓመት ታስሮ ቆየ። በዛች ቀን በነበረው ችሎት ደግሞ ዓመት ከስድስት ወር አጠቃላይ ሦስት ዓመት ከስድስት ወር ማለት ነው ፈረዱበት። እንደምንም ጥርሴን ነክሸ እሱን ለማበርታት ማተቤን ይዥ ራሴን እየነቀነቅሁ አሳየሁት። ማተቤን በፍጹም አልበጥስም ምንም ቢፈጠር ከሞት በስተቀር የሚለየን የለም ማለቴ ነበር።
ቃሊቲ ከወረደ በኋላ ለ30 ደቂቃ ቢሆንም ለማግኘት ቻልሁ። ቢያንስ በወር አንዴ አዲስ አበባ እሄዳለሁ። እንዲህ እንዲህ ያለ አንድ ዓመት አለፈ። ሊወጣ ሦስት ወር እንደቀረው ሳስብ ተስፋዬ ለመለመ።
አንድ ቀን 10 ሠዓት አካባቢ ስልክ ተደወለ።
"ሀሎ"።
"ሕይወቴ" ሲለኝ በድንጋጤ ወደቅሁ። ውኃ ደፍተውብኝ ከተረጋገሁ በኋላ እንደገና አናገርኩት። ልምጣ ስለው እኔ ራሴ እመጣለሁ ነገ አለኝ። ማመን አቃተኝ። ገና ሦስት ወር ይቀረው ነበር ይቅርታ ተደርጎለት መሰለኝ እናት አባት ስለሌለው ከኔ ውጭ የትም አይሄድም። እናቱም ሚስቱም እኔ ነኝ። "ከአቺ ሌላ ምን መሄጃ አለኝ" ሲለኝ አውነት ለመናገር ልቤ ተንሰፈሰፈ።
ለቤተሰቦቸ ነግሬ ሰሞኑን ትንሽ ቀይ መስቀል እረድቶን ነበርና በግ ተገዛ። ቢራ ተገዛ። ዘመድ አዝማድ ተጠራ። ከአዲስአበባ ተሳፍሮ ወደ ደብረብርሃን መምጣት ጀመረ። በየሠዓቱ አብሮት በአንድ ወንበር በተቀመጠው ሰውዬ ስልክ አገኘዋለሁ። እኔ ደግሞ ጸጉሬን ተሠራሁ። ገላዬን ታጠብሁ። ነጭ የበዓል ቀሚስ ለበስሁ። አንባር አደረግሁ። የጎረቤት ሰው እንኳን ደስ አለሽ በማለት አጨናነቀኝ። ከላይ ከላይ እስቃለሁ።
10 ሠዓት ሆነ። "ለምን ተሎ አይደርሱም?" ብዬ ስደውል ስልኩ አይጠራም። ጨነቀኝ። መቶ ጊዜ ሞከርኩት አይሠራም። ወደ ውጭ ወጣሁ የሚመጣ ሰው አይታየኝም። ቤት ገብቸ ተቀመጥሁ። አስጠለኝ። እናቴ እስኪ አሁንም ደውይ አለችኝ። ደወልኩ ምንም ነገር የለም። ትንሽ ቆይቶ በቢሮ ስልክ ተደወለ። "ወይዘሮ ሕይወት" አለኝ። አወ ነኝ ማን ልበል አልኩት። "ከደብረብርሃን ጠቅላላ ሆስፒታል ነው የምደውልልሽ ፍቅር የሚባል ሰው ይፈልግሻል" ሲለኝ አላስጨረስኩትም። ቦርሳዬን ይዥ በአባዱላ መኪና በረርሁ። ቤተሰቦቸ ከኋላ ተከተሉኝ።
ፍቅርደብረብርሃን ሊደርስ 4 ኪሎሜትር ሲቀረው ነው አደጋ የደረሰበት።
ይሄን አሳዛኝ ታሪክ ሕይወት ከጻፈችው በኋላ ታሪኩ አልቀጠለም። ቤተሰቦቿ እንደነገሩኝ ከሆነ ግን ወደ ሆስፒታል ሄደች። ፍቅረኛው ፍቅር በመኪና አደጋ ተጎድቶ ሆስፒታል ተኝቶ አገኘችው። ፍቅር ዓይኗን ዓይቶ እጇን እንደያዘ አረፈ። ሕይወት ወዲያው መርዝ ገዝታ ጠጥታለች። ነፍሷን ለማትረፍ ወደ አዲስ አበባ መገናኛ አካባቢ የሚገኘው ላንሴት ጠቅላላ ሆሰረፒታል በአምቡላንስ ብትመጣም ነፍሷን ማትረፍ አልተቻለም።
ከላይ በማስታወሻዋ እንደጻፈችው መረዳት የሚቻለው "ከአንተ ከሞት በስተቀር የሚለየኝ የለም" እንዳለችውና ፍቅር ሲሞት ሕይወትም አብራ እንደሞተች ነው።
ፍቅር እስከ መቃብር ይሉታል ይኼው ነው። አይ የወለጋ ዐማራ ነጻነታችን ባይቀርም ብዙ ዋጋ እየከፈልን ነው ።
የፍቅርና የሕይወትን እስከሞት ድረስ የተሰውለትን የነጻነት ትንቅንቅ እኛ እኅት ወንድሞቻቸው በመተማመንና በመከባበር አንድ ሁነን ታግለን ነጻነታችንን ማወጅ አለብን።
1970:2017
ቢዛሞ ሚዲያ