ዜና እወዳለሁ። በተቻለኝ መጠን ሁሉንም ሚዲያዎች እከታተላለሁ። ሁሉም አይነት ፅንፍ ላይ የቆሙ መገናኛ ብዙሃን የሚሉትን እሰማለሁ። (የኢትዮጵያን ፖለቲካ ለመረዳት የተሻለው መንገድ ሁሉንም ዋልታ መከታተል ነው ብዬ አስባለሁ)
በዚህ ሁሉ መሓል የአሻም ቴሌቪዥን ዜናዎች ይለዩብኛል። ድምፅ ለሌላቸው ድምፅ ሆነዋል። ጋዜጠኞቹ ራሳቸውን አደጋ ላይ ጥለው ከህዝብ ጎን ቆመዋል።
ጋዜጠኞች እውነተኛ ነፃነት ያስፈልጋቸዋል። ከተዋጣለት ዘገባ ጀርባ የሞያ ነፃነት እና እውቀት አለ። የአሻም ዜና ክፍል ይህን ያገኘ ይመስለኛል።
የአሻምን ዜናዎች በመከታተል ብቻ የዜና ክፍል ሃላፊው ፕሮፌሽናል እንደሆነ አምኛለሁ። የዜና ክፍል ሃላፊው ለሞያው መርሆች የሚታመን ፥ ለህዝብ የሚወግን ፥ ከእውነት የሚተባበር ባይሆን ኖሮ የአሻም ዜናዎች ሌላ መልክ ይኖራቸው ነበር።
መገናኛ ብዙሃን ለጥቅማጥቅም በገበሩበት ዘመን ፥ ለሹማምንት በተንበረከኩበት ወቅት አሻም ቴሌቪዥን ከእውነት እና ከመርህ ጋር ተባብሯል። የአሻም ቴሌቪዥን ዜናዎች ከሐቅ ጋር ሲወግኑ የዜና ክፍሉ መሪ ዮሐንስ የሚባል ግለሰብ ነው። እንዴት ያለ መሪ እንደ ሆነ ዜናዎች ምስክር ናቸው።
አንድ ቀን ለአሻም ቴሌቪዥን ጋዜጠኛ ሚስጥረ ስላሴ ታምራት "ዜናዎቻችሁን እወዳለሁ" አልኳት። አመሰገነችኝ።
"የዜና ክፍሉ መሪ ማን ይባላል?" ብዬ ጠየቅኳት
"ጆዬ ነው"
"ፕሮፌሽናል ሰው መሆኑን ዜናዎቻችሁ ይመሰክራሉ"
"ከምትገምተው በላይ ምርጥ ሰው ነው"
ሚስጥረ ስለ ዮሐንስ አውርታ አትጠግብም። ሐቀኛ እና ጎበዝ መሆኑን እልፍ ጊዜ ነግራኛለች። በተገናኘን ቁጥር ከአንደበቷ ከማይጠፉ ስሞች መካከል ዮሐንስ ይገኝበታል።
ሌላኛዋ የአሻም ጋዜጠኛ ህሊና ተክሌም ስለ ዮሐንስ በጎ ነገሮችን ነግራኛለች።
አንድ መሪ በሰራተኞቹ የሚወደድ ከሆነ እድለኛ ነው። ዮሐንስ በዚህ እድለኛ ነው።
ዛሬ ዮሐንስ ከአሻም ቴሌቪዥን ለቋል። እኚያን የህዝብ ድምፅ የሆኑ ዜናዎችን የመራው ዮሐንስ ከአሻም ተለያይቷል።
በቅርቡ የአሻም ቴሌቪዥን ባለቤት በፀጥታ ሐይሎች ታፍነው ነበር። (ኢትዮ ፎረም እንደዘገበው ከሆነ ይህን ክስተት ተከትሎ የቴሌቪዥኑ ስራ አክኪያጅ ለቀዋል)
ዛሬ ደግሞ ዮሐንስ መልቀቁ ተሰምቷል።
ዮሐንስን ከስራው ውጪ አላውቀውም። እሱም አያውቀኝም። ነገር ግን ባላደንቀው ባለ እዳ እሆናለሁ።
በሄደበት መልካም ይግጠመው
@Tfanos