ርእሰ ሊቃውንት አባ ገብረ ኪዳን እመቤታችን “ያስተበፅዑኒ ኩሉ ትውልድ" ብላ ከተናገረችላቸው አንዱ ናቸው። ለዚህም ምስክሬ ትምህርታቸው ነው። በዐውደ ምሕረት "የምድር ጌጥ" ይሏታል። በጉባኤ ቤት "ብርሃንኪ የዐቢ እምብርሃነ ፀሐይ” ይሏታል። በበዐታቸው "ሰአሊ ለነ ቅድስት" ይሏታል። ዛሬ ደግሞ ተነቦ የማይጠገብ ውዳሴዋን በመጽሐፍ አቅርበውልናል።
ይሄ መጽሐፍ በትውፊት የምናወርሰው፥ ነገር ግን እያየነው የተደረሰ አዲሱ አርጋኖን ነው። ቅድመ ዓለም በአምላክ ኅሊና ከታሰበው ድኅረ ዓለም በነቢያት እስከተነገረው፥ በመላእክት ከተዘመረው በሐዋርያት እስከተሰበከው ሊጠቀስ የሚገባው ተጠቅሷል። የእመቤታችን ነገር ሐረግ ነው፤ በነካነው ጊዜ ሁሉ ብሉያትን ሐዲሳትን ሊቃውንትን ያንቀሳቅሳል።
ርእሰ ሊቃውንት እንደ ሐረግ ሳቢ አንድ ጥቅስ በመዘዙ ጊዜ የመጻሕፍት ሁለንተናቸው ይንቀሳቀሳል። ከብሉይ ኪዳን ጀምሮ በእግዚአብሔር መንፈስ የተጻፈ መጽሐፍ ሁሉ እመቤታችን የሌለችበት መጽሐፍ አይገኝም።ይህን መጽሐፍ ባነበባችሁ ጊዜ ይህንን እውነት ትረዱታላችሁ። "አሐቲ ድንግል" አንድ መጽሐፍ ብቻ አደለም። ትርጓሜ፤ ድርሳን፤ ምዕላድ፤ ውዳሴም ነው። ሁልጊዜ የርእሰ ሊቃውንት አባ ገብረ ኪዳንን ስብከት ስሰማ የምመኘው ይህንን መጽሐፍ ነበር። አንዳንዴ ስብከት መሆኑን ረስቼ መጽሐፍ የሚያነቡልኝ ይመስለኝ ነበርና። እነሆ የተመኘሁት መጽሐፍ በብራና ተጠቅሎ በቤተ መጻሕፍት ተጥሎ አገኘነው። ከእኔ ጋራ የተወለደውን የመጻሕፍት ንጉሥ ታዩ ዘንድ ኑ!
ሊቀ ሊቃውንት ስምዐ ኮነ መልአክ የ፬ቱ ጉባኤያተ መጻሕፍት ምስክር መምህር