የአብክመ ሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ከባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ ከጤና ቢሮ እና አጋር ድርጅቶች ጋር በመተባበር በዘላቂ የአዕምሮ ጤና እና የማህበራዊ ስነ-ልቦና ችግሮችን መቅረፍ በሚቻልበት ሁኔታ የምክክር መድረክ ጥር 29/2017 ዓ.ም በባሕር ዳር ከተማ ተካሂዷል።
የአብክመ ሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር አቶ በላይ በዛብህ በግጭት በተጎዱ ማህበረሰቦች ውስጥ ዘላቂ የአዕምሮ ጤና እና የስነ-ልቦና ድጋፍን ለመገንባት የረዥም ጊዜ ተደራሽነትን ለማረጋገጥ የአዕምሮ ጤናን ከመጀመሪያ ደረጃ የጤና እንክብካቤ ጋር ማቀናጀት ይገባል ብለዋል።
በዘላቂነት የተመሰረተ ትብብርና አጋርነት ከችግሮቻችን ለመውጣት ቁልፍ መንገድ በመሆኑ ለአዕምሮ ጤና እና የስነ-ልቦና ድጋፍ በቁርጠኝነት ልዩ ትኩረት ሰጥተን እንሰራለን ብለዋል አቶ በላይ።
በምክክር መድረኩ ላይ የባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ዶክተር መንገሻ አየነ ከሀገር አቀፍ ውዥንብር፣ ግጭቶች እና አሳሳቢ ቀውሶች የአዕምሮ ጤና እና የስነ-ልቦና ችግር እያስከተሉ እና ህብረተሰቡን በከፍተኛ ሁኔታ እየጎዱ መምጣታቸውን ተናግረዋል።
የግጭት ሥነ ልቦናዊ ጉዳቱ ከፍተኛ መሆኑን፣ አካላዊ ውድመት እና ከግጭት በኋላ የማይታዩ ጉዳቶችን የሚያስከትል መሆኑን የገለፁት ዶክተር መንገሻ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ የመጣው አሰቃቂ ድርጊት እና የስነልቦና-ማህበራዊ ጭንቀት በፍጥነት መፍትሄ ካልተሰጠው የግለሰብ ደህንነትን ብቻ ሳይሆን የማህበራዊ አለመረጋጋትን የሚፈጥር፣ የኢኮኖሚ እና የሀገር መሰረትን ጭምር የሚጎዳ ነው ብለዋል።
የአዕምሮ ጤና እና የስነ-ልቦና ተግዳሮቶች ላይ ግንዛቤ ማሳደግ፤ ክፍተቶችን በመለየት እና በማስረጃ ላይ የተመሰረቱ መፍትሄዎችን መፈለግ፤ እንዲሁም ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት እና በሙያ ማህበራት መካከል ያለውን ትብብር ማጠናከር እንደሚያስፈልግ ዶክተር መንገሻ ተናግረዋል።
በባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ የሶሻል ወርክ መምህር ዶክተር ሙሉነሽ አበበ በክልላችን በተለያዩ ጊዜያት በተፈጠሩ ግጭቶች ምክንያት የሰው ሕይወት ጠፍቷል፤ የአብሮነት፣ የመተሳሰብ እና የሰብዓዊነት መሠረት የሆኑ እሴቶቻችን ተሸርሽረዋል፤ በማህበረሰቡ ዘንድ ከፍተኛ የአዕምሮ ጤና መቃወስ እና የስነ ልቦና ጫናዎች ደርሰዋል ብለዋል።
ያጋጠመንን ችግር በቅንጅት እና በመናበብ መፍታት ይጠበቃል ያሉት ዶክተር ሙሉነሽ ምርምር በማድረግ እና በማስረጃ የተደገፈ የመፍትሔ ሀሳብ በማቅረብ ከችግሩ መውጣት እንደሚገባ አሳስበዋል።
በአብክመ ሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት የህብረተሰብ ጤና አደጋዎች መከላከል እና መቆጣጠር መልሶ ማቋቋም ኬዝቲም አሥተባባሪ ቢረሳው ታዛየ ክልሉ ረጅም ጊዜ የቆዬ ግጭት፣ የወባ ወረርሽኝ፣ የሀገር ውስጥ እና የሱዳን ተፈናቃዮች እና ሌሎች በርካታ ውስብስብ ችግሮች ያሉበት በመሆኑ በማህበረሰቡ ላይ የአዕምሮ ጤና እና የሥነ ልቦና ችግሮች እንደፈጠሩ ገልፀዋል።
የአዕምሮ ጤና ችግር በማህበረሰቡ ላይ ለከፋ ጉዳት ስለሚዳርግ ለመከላከል በትብብር መሥራት እንደሚጠበቅ አቶ ቢረሳው ጠቁመዋል።
ለሕብረተሰብ ጤና ልማት እንትጋ!
ጥር 30/2017 ዓ.ም