ቅዱስ ሚካኤል ሊቀ መላዕክት
ኅዳር ዐሥራ ሁለት በዚች ቀን ለሰው ወገን የሚያዝንና የሚራራ በእግዚአብሔር ጌትነት ዙፋን ፊት ሁልጊዜ በመቆም ለፍጥረቱ ሁሉ የሚማልድ የመላእክት አለቃ በሰማያትም ለሚኖሩ ኃይሎች ሁሉ አለቃቸው ለሆነ ለቅዱስ ሚካኤል የበዓሉ መታሰቢያ ነው።
ዳግመኛ በዚህች ዕለት ቅዱስ ሚካኤል ኢያሱን የተራዳበት ቀን ነው።
ይህም በንጉሥ ጭፍራ አምሳል በታላቅ ክብር ሁኖ የነዌ ልጅ ኢያሱ ያየው ነው ከእኛ ሰዎች ወገን ነህን ወይስ ከጠላቶቻችን ወገን ነህ አለው። እኔስ የእግዚአብሔር ሠራዊት አለቃ ነኝ አሁንም ወዳንተ መጥቻለሁ አለው ።
ኢያሱም ወደ ምድር በግንባሩ ተደፍቶ ሰገደለትና በእኔ በባሪያህ ዘንድ ምን አቁሞሃል አለው ። የእግዚአብሔር የሠራዊቱም አለቃ ሚካኤል ኢያሱን የቆምክባት ምድር የከበረች ቦታ ናትና ጫማህን ከእግርህ አውልቅ አለው ኢያሱም እንዳለው አደረገ ።
እግዚአብሔርም ኢያሱን እንዲህ አለው በውስጧ ያለውን ንጉሧን ከኃያላኑና ከአርበኞቹ ጋር በእጃችሁ ኢያሪኮን እነሆ አስገባታለሁ ። ይህም የከበረ መልአክ ከቅዱሳን ሰማዕታት ጋር በመሆን ገድላቸውን እስከ ሚፈጽሙ የሚያጸናቸውና የሚያስታግሣቸው ነው ።
ስለዚህም ስለ ልዕልናውና ስለ አማላጅነቱ በየወሩ በዐሥራ ሁለት ቀን ለመታሰቢያው በዓል ተሠራለት እርሱ ስለ እኛ የምድሩን ፍሬ ይባርክልን ዘንድ ዝናሙንም በጊዜው እንዲአወርድልን የወንዙንም ውኃ እንዲመላልን ነፋሱንም የምሕረት ነፋስ እንዲአደርግልን ሁሉንም የተስተካከለ እንዲአደርግልን ወደ እግዚአብሔር በጸሎት ይማልድልናልና። ለእግዚአብሔርም ምስጋና ይሁን እኛንም በሊቀ መላእክት ቅዱስ ሚካኤል ጸሎት ይማረን የቅዱስ ሚካኤል በረከቱም ከእኛ ጋር ትኑር ለዘላለሙ አሜን።
https://t.me/ethioadbarat