የአካባቢያዊ ተፅዕኖ ግምገማ ረቂቅ አዋጅ ወቅቱ የደረሰበትን ኢኮኖሚያዊ፣ ማህበራዊና ሌሎች ለውጦች ከግምት ውስጥ ያስገባ መሆኑ ተገለጸ
---------------------------
(ዜና ፓርላማ) ህዳር 12 ፡ 2017 ዓ.ም፤ በሥራ ላይ የሚገኘው የአካባቢ ግምገማ አዋጅ ከ21 ዓመታት በኋላ ሊሻሻል መሆኑና አዋጁ ወቅቱ የደረሰበትን ኢኮኖሚያዊ፣ ማህበራዊና ሌሎች ለውጦች ከግምት ውስጥ ያስገባ መሆኑ ተገለፀ።
የውሃ ፣ መስኖ እና ቆላማ አካባቢና የአካባቢ ልማት ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ በአዋጁ ዙሪያ ከባለድሻ አካላት ጋር ይፋዊ የሕዝብ ውይይት አካሂዷል።
የቀድሞው አዋጅ ያልዳሰሳቸውን ጉዳዮች በማካተት አዲሱ ረቂቅ አዋጅ የአካባቢያዊ ተፅዕኖ ግምገማ አዋጅ በሚል መዘጋጀቱ ተገልጿል።
ኘሮጀክቶች ተግባራዊ በሚሆኑበት ወቅት በአካባቢና በማህበረሰቡ ላይ የሚያደርሱትን ተፅዕኖ በአግባቡ የመገምገም አቅም እንደሚያሳድግ ተመላክቷል።
በፕሮጀክቱ አተገባበር ጉዳት ሊደርስባቸው የሚችሉ የማህበረሰብ ክፍሎች ስለ ፕሮጀክቱ ግንዛቤ እንዲኖራቸውና አስተያየት እንዲሰጡ የማድረግ ኃላፊነት በባለሥልጣኑ ላይ የሚጥል ነው።
የይሁንታ ፈቃድ ሳያገኙ ኘሮጀክቶችን በሚጀምሩ አካላት ላይ ከ 500 ሺህ እስከ 10 ሚሊዮን ብር ቅጣት እንደሚጣልም በረቂቅ አዋጁ ላይ ተገልጿል።
የአካባቢና ማህበራዊ ተፅዕኖ ጥናትና ውጤትን እንደ ቅድመ ሁኔታ ሳያስቀምጡ ፈቃድ የሚሰጡ አካላትም ሊቀጡ ይገባል የሚሉ ሀሳቦች በውይይቱ ተነስተዋል።
ኘሮጀክቶች ከተጠናቀቁ በኋላ በአካባቢው ላይ ያደረሱትን ተፅዕኖ እና ለውጦች ወደነበሩበት ሊመልሱ ይገባል ተብሏል።
ባለ ፕሮጀክቶች በየሁለት ዓመቱ የአካባቢና ተፅዕኖ ግምገማ ማድረግ እንደሚገባቸውም በቀረበው ረቂቅ አዋጅ ላይ ተመላክቷል።
ይሁንታ ፈቃድ ያገኙ የፕሮጀክት ባለቤቶች በየሶስት ዓመቱ የአካባቢና ማህበራዊ ተፅዕኖ አጠባበቅ ዕቅዶችን ለባለሥልጣኑ ሊያቀርቡ እንደሚገባ በረቂቅ አዋጁ ተመልክቷል።
(በ በለጠ ሙሉጌታ)
ተጨማሪ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
በፌስቡክ http://www.facebook.com/hoprparliament
በዩቲዩብ
https://www.youtube.com/@FDREHOPR
በቴሌግራም
https://t.me/ParlamaNews
በትዊተር
http://twitter.com/fdrehopr
በዌብሳይት
www.hopr.gov.et ይከታተሉ።