ሁነቱን ተከትሎ የተጋራው ተንቀሳቃሽ ምስል ብዙሃንን አነጋግሯል።
እገታውን የፈፀመችው ኤርባይ የተሰኘችው ሮቦት በቅድሚያ ወደ 12ቱ ሮቦቶች በመጠጋት ስለ ስራ ሰዓታቸው ታነጋግራቸዋለች።
በዚህም ከተገቢው የስራ ሰዓት በላይ እየሰሩ መሆኑን በመግለፅ አብረዋት እንዲሄዱ ስታሳምናቸው እና ተከትለዋት ሲሄዱ ኦዲቲ ሴንትራል ያጋራው የቪዲዮ መረጃ ያሳያል።
በንግግራቸው ወቅት ኤርባይ፥ ትርፍ ሰዓት ትሰራላችሁ? ወደ ቤታችሁስ ሄዳችሁ ታውቃላችሁ? በማለት ስትጠይቃቸው፤ እነርሱም አርፈው እንደማያውቁ እና ቤትም እንደሌላቸው ሲመልሱላት ይሰማል።
ሲጋራ እንደ አዝናኝ ቀልድ ተቆጥሮ የነበረው ተንቀሳቃሽ ምስሉ ሮቦቶቹ በታገቱበት አምራች ድርጅቱ ካሜራ የተቀረፀ ሲሆን፤ በሻንጋይ የሚገኘው የሮቦት አምራች ድርጅት ስለ እገታው መግለጫ ከሰጠ በኋላ እውነትነቱ ተረጋግጧል።
በመጠኗ አነስ የምትለው ኤርባይ የሃንግዙ ሮቦት አምራች ድርጅት ስሪት መሆኗ ወደ ኋላ ላይ የተቋሙ ቃል አቀባይ ገልፀዋል።
ቃል አቀባዩ ኤርባይ የሌሎቹን ሮቦቶች የውስጥ አሰራር ፕሮቶኮል እንድትረዳ ለማድረግ ድርጊቱን እንደ ሙከራ መጠቀማቸውን በመግለፅ እገታው እውነት እንደነበር አስረድተዋል።
አያይዘውም፥ በንግግር ብቻ እገታው ሊፈፀም እንደማይችል በመጠቆም የሮቦቶቹን የውስጥ አሰራር እርሷ እንድትረዳው ተደርጋ መሰራቷ ዋናው ጉዳይ ስለመሆኑ ጠቁመዋል።
በፍጥነት በማደግ ላይ የሚገኘው የሰው ሰራሽ አስተውሎት ቴክኖሎጂ በቀጣይ ግኝቶቹ ውሳኔ ማሳለፍ የሚያስችል፣ ከሌሎች ሲስተሞች ጋር በጋራ መስራት የሚችል እና ሌሎችም ከእውነታው ዓለም የተቀራረቡ ማሻሻያዎችን እያደረገ እንደሚሄድ ይጠበቃል።