(ተስፋኣብ ተሾመ)
አንዲት መንፈስ መጥታ ማሪያም ነኝ አለችኝ፤ ከዛም ጩቤ ይዤ እንዲዞር፥ ጓድ መንግስቱ ሃይለማርያምን እንድገድል፥ በየጎዳናውም እንድሰግድ አዘዘችኝ። እኔም ሳላመነታ ታዘዝኳት"
ከላይ ያለው ንግግር የልጅ ጨዋታ ቢመስልም የታላቅ ደራሲ እና ጋዜጠኛ የእለት ተዕለት ገጠመኝ ነው።
እሱ እውነተኛ ሰው ሳይሆን በልብወለድ የተሳለ አይታመኔ ገፀባህርይ ይመስላል። ጎዳና ተዳዳሪነት ፥ ልመና፥ የአሮጌ መፅሐፍ ነጋዴነት ፥ የአእምሮ መታወክ(እብደት)፥ ደራሲነት ከህይወት ጓዳናዎቹ መካከል ናቸው።
ትክክለኛ ስሙ ሂሩይ ሚናስ ሲሆን አውግቸው ተረፈ የሚለው የብእር ስሙ ደግሞ ዝነኛ ሆኗል። ለሁለት አመታት ያህል የአይነስውር መሪ ነው። በልመና ስራ የተሰማራን አይነስውር ይመራል፥ በልመና የተገኘውን ገቢ ለእኩል ተካፍሏል።
በጎጃም ደጀን የተወለደው ሂሩይ በ1950ቹ የእህል ለማኝ ነበር። በልመና ያገኘውን እህል በመሸጥ የእለት ተዕለት ኑሮውን መርቷል።
እንደማንኛው ሰው ትዳር መሰረተ፥ ጎጆ አቆመ። ከትዳር በኋላ ሚስቱ ልጅ ስትወልድ ጭንቅ መጣ። እመጫት ሚስቱን የሚያበላት ነገር አልነበረውም። ደራሲው አላመነታም። ወደ ሆቴል አቅንቶ ትርፍራፊ ለምኖ ይዞላት ሄደ። ወላዷ ሴት ትርፍራፊ መብላት አልሆንልሽ ብሏት 'በረሃብ ብሞት ይሻለኛል' አለች። የሚያደርገው ግራ የገባው ደራሲ ተንሰቅስቆ አለቀሰ፥እንደ ህፃን ልጅ ተነፋረቀ።
ለ3 አመታት ያለ አናጋሪ ብቻውን በአንድ ቤት የኖረው አውግቸው የአእምሮ መታወክ ችግር ክፉኛ ጎድቶታል። "ከ1972-1974 ቀን በቀን ጫት እየቃምኩ ከጠዋት እስከማታ ማንበቤ እና በዚህ ወቅት ሳላቋርጥ እበሳጭና እንቅልፍ አጣ ስለነበርኩ ነው ያበድኩት። እንቅልፍ ማጣት፥ ብዙ ማንበብ ፥ የገንዘብ እጦት አሳብዶኛል" ይላል።
ለእንቅልፍ ችግሩ መድሃነት ፍለጋ ሃኪም ዘንድ ሄዶ ነበር። አለመታደል ሆነና ለችግሩ የተሰጠው መድሃኒት ሌላ ችግርን ፈጠረበት። የተሳሳተ መድሀኒት ተሰጥቶት እግርና ወገብ ለሚያሸማቅቅ በሽታ ዳርጎት ብዙ ርቀት መራመድ የማይችል ሆኗል። ቀሪ እድሜውን ሁሉ በዛች የተሳሳተች መድሃኒት ጦስ ሲቸገር ኖሯል።
በእብደት ዘመኑ 'ማሪያም ነኝ' የምትል መንፈስ የምታናግረው ሲሆን እሱ ለመንፈሷ ከመታዘዝ ውጪ የሚያደርገውን አያውቅም። በየመንገዱ እንዲሰግድ ታዘዋለች። ሳያመነታ ይተዘዛል። በጎዳና መሓል በግንባሩ ተደፍቶ ለሱ ብቻ ለምትታየው መንፈስ ይሰግዳል። መንፈሷ ጩቤ እንዲይዝ አዛው ጩቤ ታጥቆ መዞር ጀምሯል። የጩቤው አላማ ያስቃል። 'በታጠቅከው ጩቤ ከሰይጣን ጋር ትፋለምበታለህ' ብላዋለች።
ለደራሲው 'ማሪያም ነኝ' ብላ ራሷን ያስተዋወቀችው መንፈስ ነገረ ስራ ሁሉ ግራ አጋቢ ነው። አንድ እለት የተለየ ተልዕኮ ሰጠችው። "ወደ ቤተመንግስት ሂድ ከጓድ መንግስቱ ሃይለማርያምጋ ፍልሚያ ግጠም፥ ፕሬዝዳንቱን ሳትገድል እንዳትመለስ" አለችው። ሳያመነታ ታዘዛትና ወደ ቤተመንግሥት አቀና።
ቤተመንግሥት ሄዶ ጠባቂዎቹን "ጓድ መንግስቱ ሃይለማሪያምን ፍልሚያ ገጥሜ ልገድለው ስለምፈልግ አገናኙኝ" አለ።
በድርጊቱ የተቆጡ ጠባቂዎች ሊገድሉት ይችሉ ነበር። ነገር ግን የአእምሮ መታወክ እንዳለበት በመታመኑ በይቅርታ ተሸኘ።
መንፈሷ ሌላ ተልዕኮ ሰጠችው። "በባህርዳር በኩል ወደ ሱዳን ሂድ፥ ትራንስፖርት አትጠቀም፥ ከአዲስ አበባ እስከ ሱዳን ያለውን መንገድ በእግርህ ተጓዝ" አለችው። ደራሲና ጋዜጠኛ አውግቸው ተረፈ ሳያቅማማ ታዘዛት። ጉዞ ከጀመረ በኋላ በእጁ የያዘውን ገንዘብ ሁሉ በመንገዱ ጨረሰ።...
ደብረ ማርቆስ ሲደርስ ወደ አእምሮው ቢመለስም የሚባለው የለውም። በኪሱ አንዳች ገንዘብ ስላልነበረ ወደ ፖሊስ ጣቢያ አቀና። "የድርጅቴን ገንዘብ ሰርቄ ስለጠፋው እሰሩኝ" አላቸው። አለመታደል ሆነና ፖሊስ ጣቢያው ምግብ አልነበረውም። ይኸን ሲያውቅ አላመነታም፥ የለበሰውን ሱሪ አውልቆ በ15 ብር ሸጠ።
አውግቸው አንድ የተለየ ነገር ያደርግና መንፈሷ ትታው ስትሄድ ያደረገውን በማስታወሻው ይፅፋል።
..... "እብድ ማለት ሰይጣን ያለበት ማለት አይደለም። የአእምሮ ችግር ተጠቂ ሰዎችን ማግለልና ማሰቃየት ችግራቸውን ማባባስ ነው" ይል ነበር አውግቸው ተረፈ።
በነገራችን ላይ "እብዱ" የሚል ዝነኛ መፅሐፍም አለው።
@Tfanos
@Tfanos