#ጾመ_ነቢያት (የገና ጾም) ከ"ሰባቱ የአዋጅ አጽዋማት" መካከል አንዱ ሲሆን “ጾመ ነቢያት” የተባለበት ምክንያት ነቢያት ስለጾሙት ነው፡፡
📌“ነቢያት የጾሙት ስለምንድን ነው?” ቢሉ ለአዳም የተሰጠውን “አምስት ሺህ አምስት መቶ ዘመን ሲፈጸም ከልጅ ልጅህ ተወልጄ አድንሃለሁ” የሚለውን የተስፋ ቃል በማሰብ ከሰማየ ሰማያት ይወርዳል፣ ከድንግል #ማርያም ይወለዳል፣ በሞቱም ሞት የተፈረደበትን የሰው ልጅ ነፃ ያወጣዋል ብለው ነው፡፡
📌“ይህንን ጾም የትኞቹ ነቢያት ናቸው የጾሙት?” ቢሉ ሊቀ ነቢያት ቅዱስ ሙሴ 40 ቀን ጾሟል (ዘፀ 34፡27)፤ ነቢዩ ኤልያስም 40 ቀን ጾሟል (1ኛ ነገ 19፡1)፡፡ በተጨማሪም በተለያየ ዘመን የነበሩት ነቢዩ ዕዝራ፣ ነቢዩ ነህምያ፣ ነቢዩ ዳንኤል እንዲሁም ክቡር ዳዊት ጾመዋል፡፡
📌"ነቢያት ይወርዳል ይወለዳል ብለው ከጾሙ፤ እኛ እርሱ ወርዶ፣ ተወልዶ ተሰቅሎ ካዳነን በኋላ ያለን የሐዲስ ኪዳን ክርስትያኖች ስለምን የነቢያትን ጾም እንጾማለን?” ቢሉ እኛ የነቢያትን ጾም የምንጾመው እንደቀደሙት ነቢያት ይወርዳል ይወለዳል እያልን ሳይሆን የቀደሙት ነቢያት ይወርዳል ይወለዳል እያሉ የጾሙትን በማሰብ በመጾማችን ድኅነተ ሥጋ፣ ድኅነተ ነፍስ፣ በረከተ ሥጋ፣ በረከተ ነፍስ እንድናገኝበት ነው፡፡”ጾመ ነቢያት (የገና ጾም) ከኅዳር 15 ጀምሮ እስከ ታኅሳስ 29 ቀን (በዘመነ ዮሐንስ እስከ ታኅሳስ 28 ቀን) ድረስ ለ44 ቀናት (በዘመነ ዮሐንስ ለ 43 ቀናት) ይጾማል፡፡ ከእነዚህም መካከል 40 ቀናት ጾመ ነቢያት፣ 3 ቀናት ጾመ አብርሃም ሶርያዊ ሲሆኑ የቀረው 1 ቀን ደግሞ የገሃድ ጾም ነው (ፍትሐ ነገሥት አንቀጽ 15 ቁጥር 565፣ 567)፡፡ ጾመ ነቢያትን ከኅዳር 15 ጀምሮ ሳይጾሙ የልደትን ዋዜማ ብቻ መጾም የቤተክርስቲያን ሥርዓት አይደለም፡፡
➡️ይህንን ጾም በዘመነ ብሉይና በዘመነ ሐዲስ ብዙ ቅዱሳን ጾመውታል፤ በዚህም ምክንያት የሚከተሉት ስያሜዎች አሉት፡፡ እነርሱም፦
✨፩. ጾመ አዳም
✨፪. ጾመ ነቢያት
✨፫. ጾመ ሐዋርያት
✨፬. ጾመ ማርያም
✨፭. ጾመ ፊልጶስ
✨፮. ጾመ ስብከት
✨፯. ጾመ ልደት
✨ጾመ አዳም፦ አዳም ዕፀ በለስን በልቶ ከገነት ከተባረረ በኋላ በፈጸመው በደል አዝኖ ፥ ተክዞ ፤ አለቀሰ [እንባ ቢያልቅበት እዥ እስከሚያፈስ ፤ እዥ ቢያልቅበት ደም በዓይኑ እስከሚፈስና ዓይኑ ይቡስ ወይም ደረቅ እስከሚሆን ድረስ አለቀሰ] ፥ ጾመ፣ ጸለየ፡፡ ከልብ የሆነ ጸጸቱን፣ ዕንባውን፣ በራሱ መፍረዱንም #እግዚአብሔር አይቶ ተስፋ ድኅነት ሰጠው፡፡ "ከአምስት ቀን ተኩል በኋላ ከልጅ ልጅህ ተወልጄ ፣ በደጅህ ድኼ ፣ በዕፀ #መስቀል ተሰቅዬ፣ ሞቼ አድንሃለሁ፡፡" የሚል ነው፡፡ [ገላ. ፬፥፬፣ መጽ.ቀሌምንጦስ] ስለዚህ ጾሙ የተሰጠው ተስፋ ፥ የተቆጠረው ሱባኤ ስለተፈጸመበት "ጾመ አዳም" ይባላል፡፡
✨ጾመ ነቢያት፦ ነቢያትም የምሥጢረ ሥጋዌ ነገር ተገለጦ ስለታያቸው ፣ #ክርስቶስ ለሰው ልጅ የሚከፍለውን የፍቅር ዋጋ በትንቢት ተመልክተው ጾመውታልና ጾመ ነቢያት ይባላል፡፡ ይህ ጾም ከአባታችን አዳም እስከ መጥምቁ ዮሐንስ ድረስ የተነሱ አበውና እናቶች : ድኅነትንና ረድኤትን ሲሹ የጾሙት ጾም ነው:: በተለይ አባታችን አዳም : ቅዱስ ሙሴ : ቅዱስ ኤልያስ ፣ ቅዱስ ዳንኤልና ቅዱስ ዳዊት በጾማቸው የተመሰከረላቸው ቅዱሳን ናቸው:: [ዘዳ.፱፥፲፱ ፣ ነገ.፲፱፥፰ ፣ ዳን.፱፥፫ መዝ.፷፰፥፲ ፻፰፥፳፬] ቅዱሳን ነቢያት በጭንቅ በመከራ ሆነው የጾሙት ጾም ወደ መንበረ ጸባኦት ደርሶ: #ወልድን ከዙፋኑ ስቦታል:: ለሞትም አብቅቶታል::
✨ጾመ ሐዋርያት፦ ሐዋርያት "ትንሣኤን ዐቢይ ጾምን ጾመን እናከብራለን ፣ ልደትን ምን ሥራ ሠርተን እናከብረዋለን?" ብለው ከልደተ #ክርስቶስ በፊት ያሉትን ፵፫ ዕለታት ጾመዋልና፡፡
✨ጾመ ማርያም፦ እመቤታችን ቅድስት ድንግል #ማርያም #እግዚአብሔር_አምላክ ቅድስናዋን አይቶ በቅዱስ ገብርኤል ብሥራት ወልደ አምላክን ያለ ሰስሎተ ድንግልና በግብረ #መንፈስ_ቅዱስ ጸንሳ እንደምትወልደው ቢነግራትም የትሕትና እናት ናትና "ምን ሠርቼ የሰማይና ምድርን ፈጣሪ እችለዋለሁ?" ብላ #ጌታን ከመውለዷ አስቀድማ ጾማለችና "ጾመ ማርያም" ይባላል፡፡
✨ጾመ ፊልጶስ (የፊልጶስ ጾም)›› ተብሎ ይጠራል፡፡ ሐዋርያው ቅዱስ ፊልጶስ በአፍራቅያና አውራጃዋ ዅሉ እየተዘዋወረ በ #ጌታችን_አምላካችንና_መድኀኒታችን_ኢየሱስ_ክርስቶስ ስም ወንጌልን በማስተማር፣ ድንቅ ድንቅ ተአምራትን በማድረግ ብዙዎችን ወደ አሚነ #እግዚአብሔር ሲመልስ ቆይቶ ትምህርቱን በማይቀበሉ የአፍራቅያ ሰዎች አማካይነት በሰማዕትነት ዐርፏል፡፡ ደቀ መዛሙርቱ ሥጋውን ሊቀብሩ ሲሉም ስለ ተሰወረባቸው የሐዋርያውን ሥጋ ይመልስላቸው ዘንድ ሱባዔ ይዘው፣ በጾም በጸሎት ተወስነው በለመኑት ጊዜ #እግዚአብሔር ልመናቸውን ተቀብሎ በ፫ኛው ቀን መልሶላቸው ሥጋውን (አስከሬኑን) በክብር አሳርፈውታል፡፡ ደቀ መዛሙርቱ የሐዋርያውን ሥጋ ካገኙ በኋላ እስከ #ጌታችን ልደት ድረስ ጾመዋል፡፡ ስለዚህም ጾመ ነቢያት ‹‹ጾመ ፊልጶስ›› እየተባለ ይጠራል፡፡
✨ጾመ ስብከት፦ የ #ወልደ_እግዚአብሔርን ሰው መሆን ያስተማሩበት ፥ የሰው ልጆች ተስፋ የተመሰከረበት ፥ የምስራች የተነገረበት ስለሆነ ጾመ ስብከትም ይባላል፡፡
✨ጾመ ልደት ፦ የጾሙ መጨረሻ [መፍቻ] በዓለ ልደት ስለሆነ "ጾመ ልደት" ይባላል፡፡
#አስተምህሮ_(አስተምሕሮ)
#በወቅቱ /ጊዜው፡ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን የዘመን አከፋፈል መሠረት ከኅዳር 6 ጀምሮ እስከ ታኅሣሥ 7 ወይም 13 ቀን ድረስ ያለው ወቅት ዘመነ አስተምሕሮ (አስተምህሮ) ይባላል፡፡
#አስተምህሮ፡ ቃሉ በሃሌታው “ሀ” (“አስተምህሮ” ተብሎ) ሲጻፍ የቃለ #እግዚአብሔር ማስተማሪያ (የትምህርተ ወንጌል) ዘመን ማለት ነው፡፡ ሥርወ ቃሉም “መሀረ – አስተማረ፤ ለመምህር ሰጠ፤ መራ፤ አሳየ፤ መከረ፤ አለመደ” ወይም “ተምህረ – ተማረ፤ ለመደ” የሚለው የግእዝ ግስ ሲሆን፣ ይኸውም የ #እግዚአብሔር ቸርነቱ፣ ርኅራኄው፣ ትዕግሥቱና የማዳን ሥራው በቤተክርስቲያን በስፋት የሚሰበክበት ጊዜ ነው፡፡
#አስተምሕሮ_ቃሉ በሐመሩ
“ሐ” (“አስተምሕሮ” ተብሎ) ሲጻፍ ደግሞ የምሕረት፣ የይቅርታ ዘመን ማለት ነው፡፡ ሥርወ ቃሉም “መሐረ – ይቅር አለ፣ ዕዳ በደልን ተወ” ወይም “አምሐረ – አስማረ፤ ይቅር አሰኘ፤ አራራ፤ አሳዘነ” የሚለው የግእዝ ግስ ነው፡፡ ዘመነ አስተምሕሮ ስለ #እግዚአብሔር ቸርነትና ርኅራኄ፤ እርሱ በደላችንን ሁሉ ይቅር እንደሚለን እኛ ምእመናንም እርስ በእርስ ይቅር መባባል እንደሚገባን ትምህርት የሚሰጥበት ወቅት ነው፡፡
#ዘመነ_አስተምህ(ሕ)ሮ፡ ዘመነ አስተምሕሮ ስለ #እግዚአብሔር ቸርነትና ርኅራኄ፤ እርሱ በደላችንን ሁሉ ይቅር እንደሚለን እኛ ምእመናንም እርስ በእርስ ይቅር መባባል እንደሚገባን ትምህርት የሚሰጥበት ጊዜ ነው፡፡ ይህ ዘመነ አስተምሕሮ ቤተ ክርስቲያን ስለ ልጆቿ ይቅርታ የምትጠይቅበት፤ ምእመናንንም ስለ በደላቸው ይቅርታ የሚጠይቁበት፤ ስለዚህም በስፋት ትምህርት የሚሰጥበት ዘመን ነው፡፡