¯¯¯¯¯¯¯¯¯¯
¹ አቤቱ፥ ወደ አንተ ነፍሴን አነሣለሁ።
² አምላኬ፥ አንተን ታመንሁ፤ አልፈር፥ ጠላቶቼ በእኔ አይሣቁብኝ።
³ አንተን ተስፋ የሚያደርጉ አያፍሩም፤ በከንቱ የሚገበዙ ያፍራሉ።
⁴ አቤቱ፥ መንገድህን አመልክተኝ፥ ፍለጋህንም አስተምረኝ።
⁵ አንተ የመድኃኒቴ አምላክ ነህና በእውነትህ ምራኝ፥ አስተምረኝም፤ ቀኑን ሁሉ አንተን ተስፋ አድርጌአለሁ።
⁶ አቤቱ፥ ምሕረትህንና ቸርነትህን አስብ፥ ከጥንት ጀምሮ ናቸውና።
⁷ የልጅነቴን ኃጢአትና መተላለፍ አታስብብኝ፤ አቤቱ፥ ስለ ቸርነትህ ብዛት እንደ ምሕረትህ አስበኝ።
⁸ እግዚአብሔር ቸር ቅንም ነው፤ ስለዚህ ኃጢአተኞችን በመንገድ ይመራቸዋል።
⁹ ገሮችን በፍርድ ይመራል፥ ለገሮችም መንገድን ያስተምራቸዋል።
¹⁰ የእግዚአብሔር መንገድ ሁሉ ቸርነትና እውነት ነው። ቃል ኪዳኑንና ምስክሩን ለሚጠብቁ።
¹¹ አቤቱ፥ ኃጢአቴ እጅግ ነውና ስለ ስምህ ይቅር በለኝ።
¹² እግዚአብሔርን የሚፈራ ሰው ማን ነው? በሚመርጠው መንገድ ያስተምረዋል።
¹³ ነፍሱ በመልካም ታድራለች፥ ዘሩም ምድርን ይወርሳል።
¹⁴ እግዚአብሔር ለሚፈሩት ኃይላቸው ነው፥ ቃል ኪዳኑንም ያስታውቃቸዋል።
¹⁵ እርሱ እግሮቼን ከወጥመድ ያወጣቸዋልና ዓይኖቼ ሁልጊዜ ወደ እግዚአብሔር ናቸው።
¹⁶ እኔ ብቻዬንና ችግረኛ ነኝና ፊትህን ወደ እኔ አድርግ ማረኝም።
¹⁷ የልቤ ችግር ብዙ ነው፤ ከጭንቀቴ አውጣኝ።
¹⁸ ድካሜንና መከራዬን እይ፥ ኃጢአቴንም ሁሉ ይቅር በለኝ።
¹⁹ ጠላቶቼ እንደ በዙ እይ፥ የግፍም ጥል ጠልተውኛል።
²⁰ ነፍሴን ጠብቅና አድነኝ፤ አንተን ታምኛለሁና አልፈር።
²¹ አንተን ተስፋ አድርጌአለሁና የውሃትና ቅንነት ይጠብቁኝ።
²² አቤቱ፥ እስራኤልን ከመከራው ሁሉ አድነው።