______________________________
የአመራር እና የስራ አፈጻጸም ችግሮችን ለይቶ የመፍታት አቅማችንን የበለጠ በማጎልበት የኦሞ ፋብሪካዎችን ውጤታማነት ለማሳደግ የተጀመረው ጥረት ተጠናክሮ እንደሚቀጥል የስኳር ኢንዱስትሪ ግሩፕ ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ ወዮ ሮባ አስታወቁ፡፡
ዋና ስራ አስፈጻሚው ከሐምሌ 2016 ዓ.ም. ጀምሮ ሲካሄድ የቆየው የአቅም ግንባታ እና የስራ አፈጻጸም ማሻሻያ ግምገማዊ ስልጠና በዋናው መስሪያ ቤት እና በፋብሪካዎች ጭምር በተሳካ ሁኔታ መጠናቀቁን በማስታወስ በወቅቱ አጠቃላይ የስራ አፈጻጸም ግምገማ ማካሄድ አስፈላጊ መሆኑን ያመላከቱ ሁኔታዎች ነበሩ ብለዋል፡፡
በዚሁ መሰረት በኦሞ 2 እና በኦሞ 3 ስኳር ፋብሪካዎች የእያንዳንዱን ሰው ሚናና አስተዋጽኦ መለየት በሚያስችል ሁኔታ ዝርዝር ግምገማ ሲደረግ መቆየቱን ተናግረዋል፡፡ በተለይ የኦሞ 3/1 ስኳር ፋብሪካ ከሚገኝበት መልክዓ ምድራዊ ስፋት እና ከያዘው የሰው ኃይል እንዲሁም ከአገዳ ማሳ ስፋት አንጻር በልዩ ትኩረት የግምገማ ስራው እንዲካሄድ ተወስኖ የዋና መስሪያ ቤት የስራ ኃላፊዎች ጭምር በተሳተፉበት ሁኔታ ላለፉት ሶስት ሳምንታት ሰፊ እና ዝርዝር ግምገማ ሲካሄድ መቆየቱን አመልክተዋል፡፡
ቅዳሜ ህዳር 07 ቀን 2017ዓ.ም. በኦሞ 3/1 ስኳር ፋብሪካ የመሰብሰቢያ አዳራሽ ከቀትር በፊት ከስራ መሪዎች ጋር ከቀትር በኋላ ደግሞ ከሰራተኞች ጋር የማጠቃለያ የውይይት መድረክ በተካሄደበት ወቅት የቀረበው የማጠቃለያ ሪፖርት እንዳመለከተው አብዛኛው ሰራተኛ የተቋሙን ችግር ለመቅረፍ የበኩሉን ጥረት እያደረገ እንደሚገኝ ለመረዳት ቢቻልም፤ ውስን የፋብሪካው ኃላፊዎችና ሰራተኞች ዝርፊያ፣ የጸጥታ ማደፍረስ፣ ስራ ማደናቀፍና ያልተገባ ጥቅም ለማግኘት አለአግባብ መንቀሳቀስን ጨምሮ ከባድ የዲሲፒሊን ጥሰት ላይ ተሳትፈው ተገኝተዋል፡፡
እንዲህ ያለው ህገ-ወጥ እንቅስቃሴ ከስራ መሪዎችና ሰራተኞች የማይጠበቅ ከመሆኑም በላይ የፋብሪካውን የስራ አፈጻጸም የመጉዳት ትልቅ አቅም እንዳለውም ሊታይ እንደሚገባ ዋና ስራ አስፈጻሚው አመልክተዋል፡፡
በስራ አመራር፣ ስራ አፈጻጸምና በባለቤትነት ስሜት ኃላፊነትን መወጣት ላይ ትኩረት አድርጎ በተካሄደው በዚህ ግምገማ አንዱ ለስኬት ሌላው ደግሞ ለውድቀት አልሞ ይንቀሳቀስ እንደነበር ከሪፖርቱ መረዳት መቻሉን አቶ ወዮ አመልክተው በዚህ ሁኔታ እድገትም ሆነ ውጤታማነትን ማሰብ ፈጽሞ እንደማይቻል ጠቁመዋል፡፡ ከዚህ ይልቅ የአላማ አንድነትንና የባለቤትነት ስሜት ፈጥሮ ወደፊት መራመድ ላይ አተኩሮ መስራት ለሁሉም የሚጠቅምና ከሁሉም የሚጠበቅ እንደሆነ አስገንዝበዋል፡፡
በዚሁ የግምገማው ውጤት መሰረት ተገቢው የማስተካከያ እርምጃ እንደሚወሰድ የጠቆሙት የግሩፑ ዋና ስራ አስፈጻሚ ፋብሪካው ወደኦፕሬሽን ስራ ለመግባት ጥቂት ቀናት ብቻ የቀሩት እንደመሆኑ የማስተካከያ እርምጃው ፈጥኖ እንደሚተገበር አረጋግጠው በሂደቱ ፋብሪካውን ውጤታማ ለማድረግ ተቋማዊ ውግንና ይዘው አጥፊዎችን ለይተው ለማውጣት በንቃት የተሳተፉትን እንዲሁም ሂደቱን በማስተባበር ለተሳተፉት ሁሉ ዋና ስራ አስፈጻሚው ምስጋና አቅርበዋል፡፡
በማጠቃለያ መድረክ ላይ የተሳተፉ ኃላፊዎችና ሰራተኞች ከአቅም ግንባታው ስልጠና ጀምሮ እስከ ዝርዝር ግምገማ የዘለቀው የፋብሪካውን ተልእኮ ከማሳካት አኳያ የእያንዳንዱ ኃላፊና ባለሙያ ሚናን አስተዋጽኦ ለመለየት የተሰራው ስራ በቀጣይ የፋብሪካውን ውጤታማነት እያሻሻሉ ለመሄድ ትልቅ አስተዋጽኦ እንደሚኖረው ተናግረዋል፡፡
የኦሞ ፋብሪካዎች እ.ኤ.አ. ከታህሣሥ የመጀመሪያ ሳምንት ጀምሮ ስኳር ወደማምረት ስራ እንደሚገቡ ይጠበቃል፡፡