-
በፋኖ ትግል ውስጥ ከተሞችን መቆጣጠር የአቅም ማሳያ ተደርጎ ይታያል። በጥቅሉ ሲታይ እውነትነት አለው። ከፕሮፓጋንዳ አንጻርም ዋጋው የሚናቅ አይደለም። ሆኖም ግን ከተማም ሆነ የትኛውንም መሬት መያዝ ብሎም መቆጣጠር ፖለቲካዊ እና ወታደራዊ ትርጉሙ ከትግል ስትራቴጂ እና ግብ አንጻር ሊመዘን ይገባል።
ከተሞች ላይ የሚደረጉ ውጊያዎች በሙሉ ለመያዝ እና ለመቆጣጠር ብቻ ያለሙ አለመሆናቸው ይታወቃል። ከተሞች ላይ በአብዛኛው የሚደረጉት የወረራ ጥቃቶች [Raids] ናቸው። ከዚህ ውጭ የቅጣት ስልት (punishment strategy) አካል ሆነው ግለሰቦች እና የአገዛዙ አቅም የሆኑ የተለዩ ኢላማዎች ላይ ጥቃት ለማድረግም ከተማ ተኮር ወታደራዊ ዘመቻዎች ይደረጋሉ። እነዚህ ውጊያዎች ልዩ ተልዕኮ ያላቸው እና ውስን ኢላማ ላይ ያተኮሩ ናቸው። እነዚህ ውጊያዎች በየአካባቢው ስኬታማ በሆነ መልኩ ተተግብረዋል። ይህ ግን ከተማ ለመያዝ ከሚደረግ ተጋድሎ የተለዬ ነው።
በትግሉ ውስጥ የትኛውንም መሬት መያዝ እና መቆጣጠር የመትከሉ ዋነኛ ቁም ነገር ነው። አስቀድሞ እንዳልነው የወቅቱ የአማራ ትግል በአማራ ህዝብ እና በአማራ መሬት ላይ የተከለ ነው። ይህም ባለፈው አንድ አመት በተጨባጭ የታዬ ሀቅ ነው። እናም ከተማም ሆነ የገጠር መሬት መያዝ ትርጉሙም ሆነ ዋጋው እጅግ የላቀ ነው።
<< መያዝ እና መቆጣጠር >> የሚለው ፖለቲካዊ እና ወታደራዊ ተጋድሎ የመትከሉ አንዱ አካል ቢሆንም ከዚያም የሚሻገር ትርጉም እና አመላካችነት አለው። እንደሚታወቀው አንድን ስፍራ መያዝ ብሎም መቆጣጠር በቀዳሚነት ወታደራዊ ተግባር ነው። ተጋድሎው ወታደራዊ ዘመቻን ከመከላከል ወደ ማጥቃት ያሻግረዋል። ከዚያም አልፎ የተያዘውን ይዞ ለመቆየት መሽጎ ወይም መሬት ይዞ መዋጋትንም ያካትታል። ይህ በትግሉ ውስጥ ወታደራዊ ዘመቻውን ከደፈጣ እና የወረራ ጥቃት አንድ ደረጃ ከፍ በማድረግ ወደ አዲስ ወታደራዊ እውነታን ያዘለ ነው። ይህ ተግባር ከገጠራማ አካባቢዎች ተሻግሮ ወደ ከተሞች ሲገባ እጅግ ትልቅ እና ውስብስብ ወታደራዊ እና ፖለቲካዊ ተለዋጮችንም ያዘለ ይሆናል።
ከተሞች እንደየደረጃቸው የፖለቲካ ማዕከሎች ናቸው። ያንንም ተከትሎ ጉዳዩ ከአስተዳደር እና ከኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴ ጋር በሰፊው ይገናኛል። በተጨማሪ ደግሞ ከተሞች በአገዛዙ ልዩ ትኩረት ስለሚሰጣቸው በእጅጉ የተመሸጉ ናቸው። እንዲሁም በከተሞች ላይ አገዛዙ በአንጻራዊነት ሰፋ ያለ የመረጃ እና የግንኙነት መረቦች አሉት። እናም ከተሞችን ለመያዝ ብሎም ለመቆጣጠር የሚደረጉ ተጋድሎዎች እነዚህን ተለዋጮች በአግባቡ ተሳቢ ማድረግ አለበት። እነዚህ ጉዳዮች የከተማ ወታደራዊ ዘመቻዎችን ልዩት ባህሪ ይሰጡታል።
በተጨማሪም ከተሞችን ለመያዝ የሚደረጉ ተጋድሎዎች ምትክ አስተዳደራዊ መዋቅርን የማስቀመጥ ሀላፊነትን ያስከትላል። ይህ በገጠሩ አካባቢ ያለ ሀላፊነት ቢሆንም ነገሩ በከተሞች ላይ ሲሞከር የራሱ ልዩት ባህሪያት ይኖሩታል። እንዲሁም ከተሞች ከገጠሩ ነዋሪ የተለዬ ማህበረ ፖለቲካዊ እና ማህበረ ኢኮኖሚያዊ ስሪት አላቸው። እናም ከተሞችን ለመያዝ የሚደረጉ ውጊያዎች የድህረ ውጊያ ነባራዊ ሁኔታዎችን በሰፊው ያገናዘበ መሆን አለበት።
መስዋዕትነት የትግሉ አንድ አካል ቢሆንም ስትራቴጂካዊ የሆነ ምዘና እና ስሌት ሲሰራ ተጨማሪ ጥንቃቄ እና ዝግጅት ባለበት አኳኋን ዘመቻዎች መታቀድ አለባቸው።
#AmharaRevolution