ምክር ቤቱ የተሻሻለውን የአማራ ክልል ማረሚያ ቤቶች ኮሚሽን ረቂቅ አዋጅን አጸደቀ
የአማራ ብሔራዊ ክልል ምክር ቤት 6ኛ ዙር፣ 4ኛ ዓመት የሥራ ዘመን 9ኛ መደበኛ ጉባኤ በሦስተኛ ቀን ውሎው የቀረቡለትን ረቂቅ አዋጆች መርምሮ አጽድቋል።
ምክር ቤቱ ካጸደቃቸው ረቂቅ አዋጆች መካከል የተሻሻለውን የአማራ ክልል ማረሚያ ቤቶች ኮሚሽን ረቂቅ አዋጅ አንደኛው ነው።
የተሻሻለው የአማራ ክልል ማረሚያ ቤቶች ኮሚሽን ረቂቅ አዋጅን ለምክር ቤቱ ያቀረቡት የአማራ ክልል ማረሚያ ቤቶች ኮሚሽን ኮሚሽነር ሀብታሙ ሲሳይ አዋጁን በተመከተ በዝርዝር ለምክር ቤቱ አቅርበዋል።
የክልሉን ማረሚያ ቤቶች ኮሚሽን ከፌዴራል ማረሚያ ቤቶች ጋር የተናበበ እንዲሆን እና አሠራራቸውን ማዘመን እንደሚያስፈልግ ገልጸዋል።
የተሻሻለው ረቂቅ አዋጅ ማረሚያ ቤቶችን የማረምና የማነፅ ስራውን ምቹ ለማድረግ እንደሚያስችል ኮሚሽነሩ የገለፁ ሲሆን በተመሳሳይ ረቂቅ አዋጁ የሕግ ታራሚዎችን መብት ለማስጠበቅ እና አያያዛቸውን በተመለከተ የተመቸና አለማቀፍ የታራሚዎች አያያዝ ድንጋጌዎችን መሰረት ያደረገ እንዲሆን እንደሚያስችል ነው ያነሱት ።
ኮሚሽነሩ አክለውም ኮሚሽኑ የተቋቋመለትን ዓላማ በአግባቡ እንዲፈጽም ለማስቻል አዋጁ አስፈላጊ ነው ብለዋል። የተሻሻለውን የአማራ ክልል ማረሚያ ቤቶች ኮሚሽን ረቂቅ አዋጅ ለማዘጋጀት ባለድርሻ አካላት እንደተሳተፉበት ገልጸዋል።
አዋጁ ታራሚዎች የተሻሻለ አያያዝ እንዲኖራቸው፣ መብታቸው እንዲጠበቅ እና ራሳቸውን በትምህርት እንዲያበቁ ያደርጋል ነው ያሉት ኮሚሽነሩ።
መረጃው የአማራ ክልል የህዝብ ግንኙነት ክፍል እና የአማራ ሚዲያ ኮርፖሬሽን ነው ።