CRRSA: ጥር 3/2017ዓ.ም
አዲስ አበባ
የሲቪል ምዝገባ እና የነዋሪነት አገልግሎት ኤጀንሲ እያደረግ ባለው የተቋም ግንባታ የሚሰጣቸውን አገልግሎቶች ወደ ቴክኖሎጂ ማሸጋገሩ ይታወሳል። ይህ በእንዲህ እንዳለ የኤሌክትሪክ መቆራረጥ በሚገጥምበት ወቅት አገልግሎት ላይ ጫና እየፈጠረ መሆኑ በህብረተሰቡ በስፋት የሚነሳ ቅሬታ ሲሆን ምንም እንኳን 2/3 በሚሆኑት የተቋሙ የወረዳ ጽ/ቤቶች የጄኔሬተር አቅርቦት ቢኖርም ከአዋጭነት እና ከቀጣይነት አኳያ ክፍተት ያለው መሆኑ ታይቷል።
ይህንኑ መነሻ በማድረግ አማራጭ ታዳሽ የፀሃይ ብርሃን ሃይል ተጠቅሞ አገልግሎት በወረዳዎች እንዳይቋረጥ ማድረግ የሚያስችል ሙከራ ከፍተኛ የተገልጋይ ፍሰት ካለባቸው ወረዳዎች አንዱ በሆነው የቦሌ ወረዳ 12 ጽ/ቤት ዛሬ ተግባራዊ ተደርጓል። በድምሩ 18 ፓናል ገጠማ የተደረገ ሲሆን እስከ 20ሺ KW ሃይል ማመንጨት የሚያስችል አቅም ተፈጥሮለታል።
ኤጀንሲው የፀሃይ ሃይልን በመጠቀም አገልግሎት ሳይቋረጥ መስጠት የሚያስችለውን የሶላር ቴክኖሎጂ ከCorner Stone Investment Group የሚባል የአሜሪካ ድርጅት በድጋፍ ያገኘ ሲሆን የBIZET PLC ስራውን በማስተባበር የሙከራ ትገበራው ዛሬ ተከናውኗል።
በዕለቱ መርሃ-ግብር የኤጀንሲው ዋና ዳይሬክተር አቶ ዮናስ አለማየሁ ፣ የቦሌ ክ/ከተማ ዋና ስራ-አስፈፃሚ ወ/ሮ አለምፀሃይ ሽፈራው እንዲሁም የኢኖቬሽን እና ቴክኖሎጂ ልማት ቢሮ ምክትል ቢሮ ሃላፊ አቶ የማነ ደሳለኝ ተገኝተዋል።
አቶ ዮናስ በዕለቱ ባስተላለፉት መልዕክት ኤጀንሲው በህዝብ ቅሬታ የሚቀርብባቸውን ችግሮች ለይቶ አንድም ሳይቀር ለመፍታት ጥረት እንደሚያደርግ ገልፀው በተያዘው በጀት ዓመት የሃይል አማራጭ ስራውን በሁሉም ክ/ከተሞች የተመረጡ ወረዳዎች ለማዳረስ ጥረት እንደሚደረግ ጠቁመዋል። ሃላፊው አክለውም ከተማችን ታዳሽ ሃይልን የመጠቀም አማራጮችን በመከተል አዲስ አባባን ስማርት የማድረግ ውጥኗን ማሳካት የሚቻለው በእንዲህ ዓይነት አማራጮች እንደሆነ አምስተዋል።
ለበለጠ መረጃ፣ ጥቆማ ወይም ማብራርያ በተገልጋይ የስልክ መስመራችን 7533 ደውለው ያግኙን
ዌብ ሳይት (website): https://www.aacrrsa.gov.et
የፌስቡክ (facebook): https://www.facebook.com/profile.php?id=100064083391686
ቴሌግራም (telegram): https://t.me/addisvaitalpress