በአዲስ አበባ ከተማ በካዛንችሽ አካባቢ በሚካሄደው የኮሪደር ልማት እና በቀበና የወንዝ ዳርቻ የልማት ፕሮጀክት ምክንያት ከግንፍሌ አካባቢ የተነሱ 1,051 የሚሆኑ ነዋሪዎች በዕጣ የተላለፉላቸውን ምትክ ቤቶች ጎብኝተዋል፡፡
በትናንትናው እለት የምትክ ቤት ዕጣ ያወጡት እነዚህ ነዋሪዎች በዛሬው ዕለት ቤቶቻቸው በሚገኙባቸው የተለያዩ ሳይቶች በአካል በመገኘት የደረሷቸውን ቤቶች ያሉበትን ሁኔታ ተመልክተዋል፡፡
በአያትና በአራብሳ የጋራ መኖርያ የግንባታ ሳይቶች በተካሄደው ጉብኝት ላይ የተገኙት የአዲስ አበባ ከተማ የቤቶች ልማትና አስተዳደር ቢሮ ኃላፊ ወ/ሮ ቅድስት ወ/ጊዮርጊስ ነዋሪዎቹ በከተማዋ እየተካሄዱ ከሚገኙት የልማት ስራዎች ተቋዳሽ በመሆናቸው ሊደሰቱ እንደሚገባቸው አመላክተው ቤቶቹ መሰረተ ልማቶች የተሟሉላቸው መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡
ወደፊት ያልተሟሉ ጥቃቅን ችግሮች ካሉ በየግንባታ ሳይቶች የሚገኙ የስራ ኃላፊዎች በቅርበት እየተከታተሉ ለመፍታት ዝግጁ መሆናቸውንም ኃላፊዋ ጨምረው ገልጸዋል፡፡
የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ ፅህፈት ቤት ምክትል ኃላፊ አቶ መኮንን ያኢ በበኩላቸው ቤቶቹ የሚገኙት ምድር ቤት በመሆናቸው ከፎቅ ከፍታ ጋር በተያያዘ ሲነሳ የነበረው ቅሬታ መፈታቱን ጠቅሰው ሌሎች ችግሮች ካሉ በሂደት እየታዩ መፍትሔ እንደሚሰጣቸው ተናግረዋል፡፡
ስራ አጥ ለሆኑ ነዋሪዎችም አቅም በፈቀደ መልኩ በየአካባቢያቸው የስራ እድል እንደሚመቻችላቸው ጠቅሰዋል፡፡
በአካል በመገኘት ቤቶቻቸውን የተመለከቱ ነዋሪዎች በበኩላቸው በከተማዋ እየተካሄዱ የሚገኙ የልማት ስራዎችን እንደሚደግፉ ገልጸው በደረሷቸው ቤቶችና በአዩት ነገር መደሰታቸውን ተናግረዋል፡፡
ቤቶቹና የሚገኙባቸው አካባቢዎች እስከዛሬ ሲኖሩባቸው ከነበሩት የተሻለ መሆኑን ገልጸው የትራንስፖርት አቅርቦት በመንግስት በኩል ትኩረት ሊሰጠው እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡
በጉብኝቱ ላይ የአዲስ አበባ ቤቶች ልማትና አስተዳደር ቢሮ ኃላፊ ወ/ሮ ቅድስት ወ/ጊዮርጊስ፣ የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ ፅህፈት ቤት ምክትል ኃላፊ አቶ መኮንን ያኢ፣ የአዲስ አበባ ቤቶች ልማት ኮርፖሬሽን ዋና ዳይሬክተር አቶ ሽመልስ ታምራትና ሌሎች የሚመለከታቸው የስራ ኃላፊዎች እና ምትክ ቤት የተላለፈላቸው ነዋሪዎች ተገኝተዋል፡፡