የቀድሞ ታጣቂዎችን በዘላቂነት ለማቋቋም ትጥቅ የማስፈታትና ወደ ተሃድሶ ማዕከላት የማስገባት ሥራ በነገው ዕለት ህዳር 12 ቀን 2017 ዓም እንደሚጀምር የብሔራዊ ተሃድሶ ኮሚሽን አስታወቀ።
የኮሚሽኑ ኮሚሽነር ተመስገን ጥላሁን ዛሬ በሰጡት መግለጫ ከሰባት ክልሎች ከ371 ሺ በላይ የቀድሞ ተዋጊዎችን ትጥቅ በማስፈታት ወደ ማዕከላት ለማስገባት የመለየት ሥራ መጠናቀቁን ተናግረዋል፡፡
በ2 ዓመታት ውስጥ በሚከናወነው የቀድሞ ታጣቂዎችን ትጥቅ የማስፈታትና ወደ ማህበረሰቡ የመቀላቀል ሥራ ከ760 ሚሊየን ዶላር በላይ በጀት መያዙንም አንስተዋል፡፡
በዚህም መሰረት መንግስት በመደበው 1 ቢሊዮን ብር እና ከአጋሮች በተገኘ 60 ሚሊዮን ዶላር በመጀመሪያው ምእራፍ በትግራይ ክልል የሚገኙ 75ሺ የቀድሞ ታጣቂዎችን ትጥቅ የማስፈታትና በዘላቂነት የማቋቋም ስራ ይጀመራል ብለዋል።
በክልሉ በመቀሌ፣ እዳጋሀሙስ እና አድዋ ሶስት ማዕከላት ተለይተዋል ያሉት ኮሚሽነሩ በመቀሌ ማዕከል በዚህ ሳምንት 320 የቀድሞ ታጣቂዎችን መቀበል እንጀምራለን በማለት ገልጸዋል።
የቀድሞ ታጣቂዎች ከዛሬ ህዳር 11 ቀን 2017 ጀምሮ በስፍራው የሚገኘው የአፍሪካ ህብረት ስር ሂደቱን የሚቆጣጠር፣ የሚያረጋግጥና የሚያስከብር የተልዕኮ ቡድን አባላት በሚታዘቡበት ለመከላከያ ሰራዊት ትጥቃቸውን ማስረከብ ይጀምራሉ ብለዋል።
በዚህም በቀጣይ 4 ወራት 75ሺ የቀድሞ የትግራይ ታጣቂዎችን ትጥቅ በማስፈታት፣ በዘላቂነት በማቋቋም ወደ ማህበረሰቡ የመቀላቀል ስራ ይከናወናል ሲሉ አረጋግጠዋል።
በ2 አመታት ውስጥም በሀገር አቀፍ ደረጃ ያሉ 371, 971 የቀድሞ ታጣቂዎች ወደ ማህበረሰቡ ተቀላቅለው በዘላቂነት ለማቋቋም መታቀዱን ከኢዜአ የተገኘው መረጃ ያሳያል።