1፤ በውጭ ጉዳይ ሚንስትር ጌዲዮን ጢሞቲዎስ የተመራ የመንግሥት ከፍተኛ ልዑካን ቡድን እንዲሁም የአፍሪካ ኅብረትና ዓለማቀፍ አጋሮች ተወካዮች በትግራይ ሐሙስ'ለት የተጀመረውን የቀድሞ ተዋጊዎችን ትጥቅ የማስፈታትና ከኅብረተሰቡ ጋር የመቀላቀል የመጀመሪያ ዙር መርሃ ግብር ዛሬ በክልሉ ተገኝተው ተመልክተዋል። ዓለማቀፍ አጋሮች ዛሬ ባወጡት የጋራ መግለጫ፣ የብሄራዊ ተሃድሶ ኮሚሽን በፕሮግራሙ 371 ሺሕ 971 የቀድሞ ተዋጊዎችን ትጥቅ አስፈትቶ ወደ ኅብረተሰቡ ለመቀላቀል ማቀዱን ገልጸዋል። ፕሮግራሙ በዓለም ላይ በመጠነ ሰፊነቱ ቀዳሚው እንደኾነ የጠቀሱት አጋሮች፣ የፕሮግራሙ መጀመር በግጭት ማቆም ስምምነቱ መሠረት በአገሪቱ ሰላምን፣ መረጋጋትንና እርቅን ለማጽናትና ልማትን ለማስፈን ወሳኝ እንደኾነ ጠቁመዋል። ለፕሮግራሙ ድጋፍ ከሚያደርጉት ዓለማቀፍ አጋሮች መካከል፣ አሜሪካ፣ ብሪታንያ፣ ካናዳ፣ ጃፓንና አውሮፓ ኅብረት ይገኙበታል።
2፤ የመንግሥት ተቋማት ዝቅተኛ የሠራተኛ ደመወዝ ወለልን ለመወሰን ያላቸው ፍላጎት ዝቅተኛ መኾኑን መንግሥት ያደረገው አንድ ጥናት ማመልከቱን ሪፖርተር ዘግቧል። አንድ ስማቸው ያልተጠቀሰ የመንግሥት ባለሥልጣን፣ ዝቅተኛ የሠራተኛ ደመወዝ ወለል መወሰን የሥራ አጥነት ያሰፍናል የሚል ስጋት እንዳለ ጥናቱ ማሳየቱን እንደተናገሩ ዘገባው ጠቅሷል። ኢሠማኮ በበኩሉ፣ መንግሥት አደረኩት ስላለው ጥናት የሚያውቀው ነገር እንደሌለ ገልጦ፣ በዝቅተኛ ደመወዝ ወለል ዙሪያ ጥናት ሊያደርግ የሚችለው ወደፊት ይቋቋማል ተብሎ የሚጠበቀው ብሄራዊ የደመወዝ ቦርድ ብቻ እንደኾነ ተናግሯል ተብሏል። መንግሥት የደመወዝ ወለልን የሚወስን ቦርድ ማቋቋም እንዳለበት የሠራተኛ አዋጁ ቢደነግግም፣ ቦርዱ ግን እስካኹን አልተቋቋመም።
3፤ የሥራና ክህሎት ሚንስቴር፣ በካናዳና በተለያዩ የአውሮፓ አገራት ዜጎችን ለሥራ ቅጥር ለመላክ ከመንግሥታዊ አካላት ፍቃድ አግኝተናል በማለት ሕዝቡን የሚያጭበረብሩ አካላትን በሕግ ተጠያቂ ለማድረግ እንቅስቃሴ እያደረገ መኾኑን አስታውቋል። ሚንስቴሩ፣ በውጭ አገር ሥራ ሥምሪት ወደ አውሮፓና ሰሜን አሜሪካ ዜጎችን ለሥራ ለማሰማራት ለየትኛውም አካል ውክልና እንዳልሰጠ ገልጧል። ዜጎች ሕጋዊ የሥራ ቅጥር አማራጮችን ብቻ እንዲጠቀሙና ካላስፈላጊ ወጪዎችና አስከፊ አደጋዎች ራሳቸውን እንዲጠብቁም ሚንስቴሩ አሳስቧል።
4፤ የኢትዮ ቴሌኮም ሠራተኞች ማኅበር፣ ኩባንያው ለሠራተኞቹ የደሞዝ ጭማሪ እንዲደረግላቸው ለኩባንያው ሥራ አስፈጻሚ በጻፈው ደብዳቤ መጠየቁን ዋዜማ ተረድታለች። ማኅበሩ ዘንድሮ ለሠራተኞች የደሞዝ ጭማሪ ለማስደረግ ከኩባንያው አመራሮች ጋር ለመወያየት ያደረገው ሙከራ እንዳልተሳካ በደብዳቤው ላይ ገልጧል። የኩባንያው ሠራተኞች በእረፍት ቀናቶች ጭምር ነጻ በመስራት የአገሪቱን የዲጂታል ቴክኖሎጂ ዕቅድ ከግብ ማድረስ ችለዋል ያለው ማኅበሩ፣ ኩባንያው በጥቂት ቀናት ውስጥ የደሞዝ ጭማሪ እንዲያደርግ ጠይቋል።
5፤ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በቅርቡ የብድር ወለድ እና የአገልግሎት ዋጋ ማሻሻያ የሚያደርግ መኾኑን ዛሬ ባሠራጨው መረጃ አስታውቋል። ባንኩ የአገልግሎት ዋጋ ማሻሻያ የሚያደርገው፣ ለደንበኞቹ በሚሰጣቸው የብድር፣ የቅርንጫፍ እና የዲጂታል እንዲኹም ዓለማቀፍ የባንክ አገልግሎቶች እንደኾነ ገልጧል።
6፤ የዛሬው ኦፊሴላዊ የብር ምንዛሬ ዋጋ ከዶላር አንጻር ከትናንቱ ዋጋ ጋር ሲወዳደር በ3 ብር ከ39 ሳንቲም መውረዱን የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ መረጃ አመልክቷል። ንግድ ባንክ፣ ዛሬ አንድን ዶላር ሲገዛበት የዋለው ዋጋ 122 ብር ከ59 ሳንቲም ሲኾን፣ ሲሸጥበት የዋለው ዋጋ ደሞ 125 ብር ከ05 ሳንቲም እንደኾነ ገልጧል። ባንኩ ትናንት አንድን ዶላር የገዛበት ዋጋ 119 ከ20 ሳንቲም የነበረ ሲኾን፣ አንድን ዶላር የሸጠበት ዋጋ ደሞ 121 ብር ከ58 ሳንቲም ነበር።
7፤ የሱማሊያዋ ጁባላንድ ራስ ገዝ አስተዳደር፣ የአፍሪካ ኅብረት የሰላም ሽግግር ተልዕኮና የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ከሞቃዲሾ ወደ ጁባላንድ በረራ የሚያደርጉ አውሮፕላኖቻቸውን ለፌደራሉ መንግሥቱ ፖለቲካዊ ዓላማ ማስፈጸሚያ እንዳያውሉ አስጠንቅቋል። ጁባላንድ ይህን ማስጠንቀቂያ ያወጣችው፣ በቀጣዩ ሳምንት ሰኞ በምታካሂደው ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ ሳቢያ ከሞቃዲሾ ጋር ከባድ ውጥረት ውስጥ መግባቷን ተከትሎ ነው። የራስ ገዟ አስተዳደር የሞቃዲሾው መንግሥት በጁባላንድ አለመረጋጋት ለመፍጠር እንቅስቃሴ እያደረገ ነው በማለት ከሷል። በሞቃዲሾ እና ጁባላንድ መካከል ውጥረት የተፈጠረው፣ ጁባላንድ ፌደራል መንግሥቱ በሚፈልገው ቀጥተኛ የአንድ ሰው አንድ ድምጽ የምርጫ ሥርዓት በተቃራኒ፣ ቀጥተኛ ያልኾነ ምርጫ ለማካሄድ መወሰኗን በመወሰኗ ነው። [ዋዜማ]