⏱️ቢዚ - ቢዚ፤ ለሁሉ ጊዜ አለው ወይስ አለን?
በጋሽ ንጉሤ ቡልቻ
ይረዳን እንደ ሆነ እስቲ መላ ልምታ፡፡ በጎ ትብብራችሁን ስጡኝና ይህን ጥያቄ በጥሞና መልሱልኝ “ለመሞት አንድ ወር ቀርቶሃል የምትሠራውን ሁሉ በነዚህ ሠላሳ ቀናት ጨርስ” ብትባሉ ቀኖቹንና ሌሊቶቹን ምን ታደርጉባቸው ነበር?
ብጣሽ ወረቀት አውጡና የምታደርጓቸውን ነገሮች በቅደም ተከተል ጻፉዋቸው፡፡ ልምምዱ ምናልባት ዋና የምትሉትን ዋና ካልሆኑት ለመለየት ይረዳችሁ ይሆናል፡፡
የሕይወታችሁ ዋና ዓላማ ምንድን ነው? የደም ግፊታችሁን እየጨመረ፣ ናላችሁን እያዞረ፣ ትንፋሽ አሳጥቶ የሚያስሮጣችሁን ነገር ሁሉ ከዚህ ዋና ዓላማ አንጻር ፈትሹት፡፡ ወደ ዓላማው የሚፈስ ነባር ወንዝ ነው ወይስ በየመስኩ የፈነዳ መድረሻው ያልታወቀ የውሃ ምንጭ? የክርስቶስ ተከታይ ዋና ዓላማ ምንድን ነው የተባለ እንደሆነ ሐዋርያው ጳውሎስ ባጭሩና በግልጽ ከተናገረው ከዚህ ጥቅስ የተሻለ መግለጫ አላገኘሁም፡፡ “አንዱ ስለ ሁሉ ሞተ፣ እንግዲያውስ ሁሉ ሞቱ በሕይወትም ያሉትም ስለ እነርሱ ለሞተውና ለተነሣው እንጂ ወደ ፊት ለራሳቸው እንዳይኖሩ ስለ ሁሉ ሞተ፡፡” 2ኛ ቆሮ 5፡13
የክርስቶስ ተከታይ ግለ ሰብም ሆነ ማኅበረ ሰብ የሕይወት ዓላማው ንድፍ ተሠርቶለት አልቋል፡፡ የምንሠራው ሁሉ የምናስበው ሁሉ የዚህ ዋና ንድፍ (Master Plan) አካል ካልሆነ ሕገ ወጥ ግንባታ ነው፤ ለፍቶ መና ነው፡፡ እያንዳንዱዋ የእንቅስቃሴ ቅንጣት መፈተሸ ዋጋዋም መተመን አለባት፡፡ መሮጥ ብቻውን ዋጋ ቢስ ነው፤ ሕይወት መሮጫ ግብ ይሻል፤ ግቡም በአንጻሩ የመገስገሻ መስመር አለው፡፡ ሐዋርያው ትንፋሽ ሊሰበስብ ሲቃረብ ሩጫ ጨረስኩ ሳይሆን ‹‹ሩጫውን ጨረስኩ›› ማለቱ የተሰመረ መንገድ፣ የሚደረስበት ግብ መኖሩን ሲያመለክተን ነው፡፡
የቢዚነት ጉዳይ ግን ከዓላማ አንጻር ብቻ ሳይሆን በጊዜ አስተዳደር አንጻርም ሊታይ ይገባል፡፡ ጊዜ ከፈጣሪ የተሰጠን ሀብት ነው፡፡ ጊዜ ሀብት ከሆነ እንግዲያው እያንዳንዳችን “መጋቤ ጊዜያት” ሆነን በዚህ ሀብት ላይ ተሹመናል፡፡ የጊዜ መጋቢነት እንዴት ይከወን ስንል ባለ ሙያዎች ከሚመክሩን መካከል ሦስቱን ብቻ ልጥቀስ፡-
ጊዜዬ የት ጠፋ? ምን አደረግሁት? እያልክ የምትጠይቅ ከሆነ ሥራዬ ብለህ የዕለት ዕለት እንቅስቃሴህን ለተከታታይ ሰባት ቀናት ያደረግከውን ነገር ስም እየሰጠህ ልትጽፈው ትችላለህ፡፡ ከሳምንቱ በኋላ የጊዜ አጠቃቀምህን በዐይነቱ ስትሰድረው ጊዜህ ምን ላይ እንደዋለ የጊዜ ምጋቤ ባህርይህን ትረዳዋለህ፡፡ ያኔ ያላግባብ የባከነ ወይም በቂ ጊዜ ያልተሰጠው ምን እንደሆነ ግልጽ ይሆናል፡፡
ይህ የጊዜ ውሎ ግምጋሜ ወደ ሁለተኛው ዋና ነገር ይመራሃል ይህም ጊዜህን የሚሰርቁ የጊዜ መንታፊዎቸን ለይቶ ማወቅ ነው፡፡ ከታወቁት የጊዜ መንታፊዎች መካከል፡-
👉መወላወል (የቱን ላንሳ የቱን ልጣል)
👉ዝርክርክነት (ካርዱን የት ነበር ያደረግኩት)
👉መግቻ የሌላቸው የስልክ ጥሪዎች
👉ነገ ይደርሳል እያሉ መሳነፍ
👉ተራ/ወረፋ ጥበቃ
👉ጥድፊያ (ጥድፊያ ሲበዛ ፍጥነት ይቀንሳል ይባላል)
👉ድንገት የሚከሰቱ መስተጓጉሎች ይገኙበታል፡፡
እነዚህን የጊዜ ሌቦች እንዴት ነቅተህ እንደምትጠብቅ ከራስህ ጋር ተመካከር፡፡
ሦስተኛው ርምጃ ለሕይወትህ ዓላማ መሳካት የሚረዳ ከአንተ ባህርይና ሁናቴ ጋር የሚጣጣም የጊዜ ሰሌዳ መንደፍ ነው፡፡ የጊዜ መርሃ ግብር እንደሚያወጡት ቀላልነት ሳያዛንፉ መከተሉ ቀላል አይደለም፡፡ ላወጣኸው የጊዜ ሰሌዳ መገዛት ቢያቅትህ እንደገና መከለስና ማሻሻል ምንም ነውር የለበትም፡፡
ይህን ሁሉ ስታደርግ ልብ ማለት የሚገባህ ሕይወት ሥራ ብቻ÷ የግል ኑሮ ብቻ እንዳይደለ መገንዘብ ነው፡፡ የሥራና የዕረፍትን ሚዛን፣ የግልና የማኅበር ኑሮን ሚዛን፣ የዕለቱንና የዘላለሙን ሚዛን የሚጠብቅ የሕይወት ስልት መቀየስ ሁሉ ጎናዊ ስምረት እንዲኖረን ይረዳል፡፡
ወገኖቼ ጤናችን እስኪዛባ ደስታችን እስኪጠፋ ቢዚ ከሆንን እየቆየ ወደ ክስመት (burn out) ልንሄድ እንችላለን፡፡ በእምነት እጦት ሰበብ ሩጫ ያበዙትን ሕዝበ እስራኤል እግዚአብሔር እንደገሰጻቸውና እንደመከራቸው እኛንም ያስጠነቅቀናል፡፡
“የእስራኤል ቅዱስ ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላልና በመመለስና በማረፍ ትድናላችሁ፣ በፀጥታና በመታመን ኃይል ይሆንላችኋል፡፡”
(ኢሳ 30፡15)
ቁምላቸው ፈንታሁን ወደ አማርኛ ተርጉሞት በቃለ እግዚአብሔር አንባቢዎች ማኅበር በኩል ከታተመው መጽሐፍ ይህን አስተዋይ ጸሎት ልብ እንድንለው አብረንም እንድንጸልየው እጋብዛለሁ፡፡
ሰከን አርገኝ ጌታ!
ለአእምሮዬ ፀጥታ ለግሰህ፣ የልቤን ድውድውታ ቀንሰው፡፡
በጊዜ ውስጥ የዘላለምን አፅናፍ ራእይ ስጠኝና ጥድፊያዬ ልጓም ይበጅለት፡፡
በቀናት ዑደት ቱማታና ግርግር መካከል፣
የዘላለም ዓለም ኮረብቶች ግርማዊ አርምሞ በኔ ላይ ያርብብ፡፡
የሠራ አካላቴ ውጥረት በትውስታዬ በሚኖሩ
ዘማሪ ጅረቶች የሚያሳርፍ ሙዚቃ ይርገብ፡፡
የእንቅልፍን አስማታዊ አዳሽ ኃይል እንድገነዘብ እርዳኝ፡፡
ጥበብን አካፍለኝና የደቂቃ እርፍቶች በየመካከሉ እየወሰድኩ፡-
አበቦችን ልመልከት፣ ከወዳጅ ጋር ልጫወት፣
በጫካው መካከል ልመላለስ፣ ሸረሪት ድሯን ስትሸምን ልያት
ህፃኗን በፈገግታ ልቀበላት፣ እንባዎቿንም ላብስላት፡፡
ሩጫ ሁልጊዜ ለፈጣኖች እንዳይደለ፣
የኑሮ ሁለንተና ፍጥነት እየጨመሩ መኖጥ እንዳይደለ በየዕለቱ አስታውሰኝ፡፡
ቀና ብዬ ደመኖቹንና ሰማዩን
እንዲሁም ያዘመመን ዛፍ ልመልከታቸው፣
ዛፉ ዛሬ ይህን አክሎ ያደረገው፣ የበረታው በሕይወት ሰጪ ፀሐይህ ሙቀት
በዝግታ በማደጉ መሆኑን ልገንዘብ፡፡
ሰከን አርገኝ ጌታ ከአንተ ጋር ኅብረት በማድረግ በጥልቅ እኔነቴ የሚያሹኝን ሰላምና እረፍት ልጎናጸፍ፡፡
ምንጭ :- semayawithought.com
ወደ ቻናሉ ለመ🀄️ላ🀄️ል፦ @Holy_scriptures