በነቀምት ከተማ አስተዳደር 02 ቀበሌ በተከራየበት ቤት ውስጥ ተደብቆ በመቀመጥ በአጋች ሃይሎች ታግቻለሁኝ በማለት ከቤተሰቦቹ በርካታ ገንዘብ የጠየቀው መምህር በቁጥጥር ስር መዋሉ ተገልጿል ።
የነቀምት ከተማ አስተዳደር ፖሊስ መምሪያ መረጃ እንደሚያመላክተው ተጠርጣሪ ሰለሞን በንቴ የተባለው የነቀምት ጤና ሳይንስ ኮሌጅ መምህር የሆነው ግለሰብ ከጎደኛው ጋር በመነጋገር በተከራየው ቤት ውስጥ ተደብቆ በአጋች ሃይሎች እንደተያዘ በማስመሰል ለማጭበርበር መሞከሩ ተገልጿል ።
ግለሰቡ በጎደኛው ለቤተሰቦቹ በማስደወል 1 ሚሊዮን ብር እንዲልኩ መጠየቁ ተረጋግጧል ። ተጠርጣሪው ወደ ባለቤቱ ስልክ በማስደወል መታገቱን በመግለጽ እንዲሁም በተጨማሪ የባለቤቱ እህት የሆነችው እና ምዕራብ ወለጋ ዞን ጊምቢ ወረዳ የምትኖረዋን ግለሰብ በማስደወል በሶስት ቀናት ውስጥ 1 ሚሊዮን ብር እንድትልክ በተደጋጋሚ እየደወሉ ሲያስጨንቋት እንደነበረም ተገልጿል።
የተጠርጣሪው ቤተሰቦች ገንዘቡን መክፈል ባለመቻላቸው ጉዳዩን ለፖሊስ በማስታወቅ ፖሊስ ባደረገው ክትትል ተጠርጣሪው ከነተባባሪው በቁጥጥር ስር ሊውል ችሏል።
ፖሊስ ጉዳዩን እያጣራ መሆኑንም ገልፆል።