✟...ገድለ ቅዱስን...✟ @s3a7m14i22 Channel on Telegram

✟...ገድለ ቅዱስን...✟

@s3a7m14i22


" ዝምታ ሃይማኖትን ትጠብቃለች ምግባርም ወደ ሰማያት ታወጣለች "

✟...ገድለ ቅዱስን...✟ (Amharic)

ይህ የቴሌግራም ክፍል የግል ሰራተኞችና ሰብል ስብስብ የሆነ ዜና እና መረጃ እንደሆነ እና አድማጮች እንደሆነ አንዱ ነው። "✟...ገድለ ቅዱስን...✟" የሚለው የቴሌግራም አገልግሎት የያዘን ነው። ቅዱስ መምህርን ለማስፈጠር እና የጽድቅ ሀላፊነትን ለመከታተል ውስጥ ሄዱ አገልግሎት ስለሚሆን አንዱን በመጠቀም ያስገቡ። ምንድን ነው መልእክት? አስተያየታችንን ለማምጣት እና ለሌሎች ከፍተኛ መረጃ ይከታተሉ። አንዳንድ አድማጮችን አስብ።

✟...ገድለ ቅዱስን...✟

04 Sep, 12:11


✝️✝️✝️††† እንኳን ለታላቁ ቅዱስ አባ ዮሐንስ ሐጺር ዓመታዊ የፍልሠት በዓል በሰላም አደረሳችሁ፤ አደረሰን። †††

††† በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን! †††

†††✝️✝️ ቅዱስ አባ ዮሐንስ ሐጺር †††✝️✝️

††† በቤተ ክርስቲያን ያሉ አበው ሊቃውንት እንደሚሉት ከቅዱሳን በቁመቱ የአባ #አርሳኒን ያክል ረዥም አልነበረም:: እርሱ እንደ ዝግባ ቀጥ ያለ ነበር:: በዚያው ልክ ደግሞ የቅዱስ ዮሐንስን (ዛሬ የምናከብረውን) ያህል አጭር አልነበረም:: በዚህ ምክንያት ይሔው ለዘለዓለም " #ዮሐንስ_ሐጺር- አጭሩ አባ ዮሐንስ" ሲባል ይኖራል::

ሊቃውንትም ቁመቱንና ቅድስናውን በንጽጽር ሲገልጡ:-
"ሰላም ሰላም ዕብሎ በሕቁ:
ለዮሐንስ ሐጺር ዘነዊኅ ሒሩተ ጽድቁ" ይላሉ:: "ቁመቱ እጅግ ያጠረ: ጽድቁ ግን ከሰማይ የደረሰ ቅዱስ ዮሐንስን ሰላም ሰላም እንለዋለን" እንደ ማለት ነው::

ቅዱሱ የተወለደው በ4ኛው መቶ ክ/ዘመን በምድረ ግብጽ ነው:: ወላጆቹ ምንም ከሥጋዊ ሃብት ድሆች ቢሆኑም ባለ መልካም ክርስትና ነበሩና በጐውን ሕይወት አስተምረውታል:: ወደ ምናኔ የገባው ገና በ18 ዓመቱ ሲሆን የታላቁ አባ ባይሞይ ደቀ መዝሙር ሆኖ ተጋድሎንና ትሕርምትን ተምሯል::

ቅዱስ ዮሐንስ ሐጺር በወቅቱ ከነበሩ ቅዱሳን ከቁመቱ ባሻገር በትሕትናው: በትእግስቱና በመታዘዙ ይታወቅ ነበር:: አባ ባይሞይ ይጠራውና ያለ ምንም ምክንያት ደብድቦ ያባርረው ነበር:: እርሱ ግን "ምን አጠፋሁ?" ብሎ እንኩዋ ሳይጠይቅ "አባቴ ሆይ! ማረኝ?" እያለ ከእግሩ ሥር ይወድቅ ነበር::

ለብዙ ጊዜ በተመሳሳይ ሲደበድበው: እርሱም እርሱው ተደብድቦ: እርሱው ይቅርታን ሲጠይቅ ኖረ:: አንድ ቀን ግን እንደ ልማዱ ሊገርፈው ሲሔድ 7ቱ ሊቃነ መላእክት ከበውት አይቶ ደንግጦ ተመልሷል::

#አባ_ባይሞይ ይሕንን ሁሉ የሚያደርገው ጠልቶት ወይ ክፉ ሆኖ አይደለም:: አንድ ሰው የሌላኛውን ግፍ መቀበል ካልቻለ ሰይጣንን ድል አይነሳም የሚል ትምሕርት ስለ ነበረ ነው እንጂ::

አንድ ቀን ቅዱስ ዮሐንስ ወደ መምሕሩ ቀርቦ "አባቴ ጅብ ካገኘሁ ምን ላድርግ?" ሲል ጠየቀው:: (የአካባቢው ጅብ መናጢ ነበር) አባ ባይሞይ ግን "ይዘህልኝ አምጣው" አለው:: ትዕዛዝ ነውና ቅዱሱ ወደ በርሃ ወርዶ: ጅብ አልምዶ ይዞለት መጥቷል::

ሌላ ቀን ደግሞ አባ ባይሞይ ቅዱስ ዮሐንስን ጠራውና ተፈልጦ የወደቀ ደረቅ እንጨት ሠጠው:: "ምን ላድርገው አባ?" አለው:: "ትከለውና እንዲያፈራ አድርገው:: ከዚያ አምጥተህ አብላኝ" ሲል መለሰለት:: ይህ ነገር ከተፈጥሮ ሥርዓት ውጪ መሆኑን እያወቀ ቅዱስ ዮሐንስ "እሺ" ብሎ ወስዶ ተከለው::

ከዚያም ለ2 ዓመታት ሳይታክት ውሃ አጠጣው:: ውሃውን የሚያመጣበት ቦታ ደግሞ 10 ኪሎ ሜትር ያህል ከገዳሙ ይርቅ ነበር:: ቅዱሱ ላቡን እያፈሰሰ አሁንም ማጠጣቱን ቀጠለ::

በ3ኛው ዓመት ግን ለምልሞ አበበ: ደግሞም አፈራ:: ካፈራው በኩረ ሎሚም ወስዶ ለመምሕሩ "አባቴ! እንካ ብላ" ብሎ ሰጠው:: አባ ባይሞይ ግን ማመን አልቻለም:: እጅግ አደነቀ: አለቀሰም::

ወዲያው ያን ፍሬ ታቅፎ ወስዶ ለገዳሙ መነኮሳት አላቸው:- "ንሱ ብሉ: በረከትንም አግኙ:: ይህ የዛፍ ሳይሆን የመታዘዝ ፍሬ ነው::" ቅዱስ ዮሐንስ አባ ባይሞይ ቢታመም ለ12 ዓመት አስታሞታል::

መምሕሩ ከማረፉ በፊትም መነኮሳቱን ሰብስቦ የቅዱስ ዮሐንስን እጅ አስጨበጣቸው:: "ይህ የያዛችሁት እጅ የሰው ሳይሆን የመልአክ እጅ ነው" ብሏቸው ዐርፏል:: ቅዱስ ዮሐንስም ከዓመታት ቆይታ በሁዋላ የገዳሙ አበ ምኔት ሆኖ አገልግሏል:: ብዙ ነፍሳትንም ለቅድስና ማርኩዋል::

#መላእክት ንጽሕናው ደስ ስለሚያሰኛቸው አብረውት ይውሉ ነበር:: ሲተኛም በተራ በተራ ክንፋቸውን ያለብሱት ነበር:: ምጽዋትን በጣም ስለሚወድ ሰፌድ እየሰፋ ይሸጥና ገንዘቡን ለነዳያን ያን ያካፍል ነበር::

አንድ ቀን እንደ ልማዱ ወደ ገበያ ወጥቶ ሳለ ተደሞ (ተመስጦ) መጣበት:: ሰማያት ተከፍተው: ቅዱሳን #ሊቃነ_መላእክት #ሚካኤል እና #ገብርኤል በግርማ በጌታ ፊት ቆመው ተመለከተ::

"እጹብ: እጹብ" እያለ ሲያደንቅ አንድ ገዢ መጥቶ "ባለ እንቅብ ዋጋው ስንት ነው?" ቢለው "እኁየ ሚካኤልኑ የዓቢ ወሚመ ገብርኤል - ከሚካኤልና ከገብርኤል ማን ይበልጣል?" ብሎታል:: ገዢውም ደንግጦ "እብድ መነኩሴ" ብሎት ሔዷል::

ቅዱስ ዮሐንስ ሐጺር ወደ #ባቢሎን (የአሁኗ ኢራቅ) ሒዶ ከተመለሰ በሁዋላ በበርበሮች ምክንያት ከአስቄጥስ ወደ #ቁልዝም ተሰዷል:: በዚያም በአባ እንጦንስ በዓት ውስጥ ዐርፏል:: ለ400 ዓመታት በዚያው ቆይቷል::

በ825 ዓ/ም ግን በአባ #ዮሐንስ_ፓትርያርክ ዘመን ክቡር ሥጋው ወደ #ገዳመ_አስቄጥስ ተመልሷል:: ቅዱሱ ያረፈው ጥቅምት 20 ቀን ሲሆን ዛሬ ሥጋው የፈለሠበት ነው:: በዚህ ዕለትም የቅዱስ ዮሐንስ ሐጺርና የታላቁ #ቅዱስ_መቃርስ ሥጋ በተገናኙ ጊዜ ግሩም ተአምር ተደርጉዋል:: ወደ ቤተ ክርስቲያኑ ሲገባም ታላቅ የብርሃን ጐርፍ ሲፈስ ታይቷል::

ሰማያዊ መዓዛም አካባቢውን ሞልቶታል:: ከዻዻሳቱ አንዱ እባረካለሁ ብሎ የቅዱስ ዮሐንስን ሥጋ ቢገልጠው አካባቢው ተናወጠ:: መባርቅትም (መብረቆች) ተብለጨለጩ:: ደንግጠው ቶሎ ቢያለብሱት ጸጥታ ሆኗል:: በዚህ ሁሉ ደስ ያላቸው አበው ቅዱሱን በዝማሬ ሲያወድሱት ውለዋል::

††† አምላከ ቅዱሳን የሐጺር ቅዱስ ዮሐንስን መታዘዙን: ትሕትናውን: ትእግስቱንና ቅንነቱን ያድለን::
በበረከቱም ይባርከን::

††† ነሐሴ 29 ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት
1.ቅዱስ አባ ዮሐንስ ሐጺር (ፍልሠቱ)
2.ቅዱስ አትናቴዎስ ሰማዕት
3.ቅዱሳን ገርሲሞስና ቴዎዶጦስ (ሰማዕታት)
4.አባ ባስልዮስ ጻድቅ (ዘትግራይ)

††† ወርኀዊ በዓላት
1.የፈጣሪያችንና ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በዓለ ልደት
2.ቅድስት አርሴማ ድንግል
3.ቅዱስ ዼጥሮስ ተፍጻሜተ ሰማዕት
4.ቅዱስ ማርቆስ ዘቶርማቅ
5.ቅድስት ፍቅርተ ክርስቶስ ኢትዮዽያዊት
6.ቅዱስ ዘርዐ ክርስቶስ (ጻድቅና ሰማዕት)

††† "እናንተ ደግሞ የታዘዛችሁትን ሁሉ ባደረጋችሁ ጊዜ 'የማንጠቅም ባሪያዎች ነን: ልናደርገው የሚገባንን አድርገናል' በሉ::" †††
(ሉቃ. 17:10)

†††✝️✝️ ወስብሐት ለእግዚአብሔር✝️✝️ †††

✟...ገድለ ቅዱስን...✟

30 Aug, 13:27


ዝክረ ቅዱሳን ማኅበረ ቅዱስ ዳዊት - ዘብሔረ ጎንደር (ዲ/ዮርዳኖስ አበበ):
:
✝️††† እንኩዋን ለታላላቁ ቅዱሳን አቡነ ተክለ ሃይማኖት: ቅድስት ክርስቶስ ሠምራና ቅዱስ ቶማስ ዘመርዓስ ዓመታዊ የዕረፍት በዓል በሰላም አደረሳችሁ †††

††† ቅዱስ ተክለ ሃይማኖት ሐዋርያዊ †††

*ልደት*

=>መልካም ዛፍ መልካም ፍሬን ያፈራልና ተክለ ሃይማኖትን የወለዱት ደጋጉ: ጸጋ ዘአብ ካህኑና እግዚእ ኃረያ ናቸው:: እርሱ በክህነቱ: እርሷ በደግነቷ: በምጽዋቷ ጸንተው ቢኖሩ እግዚአብሔር ጣፋጭ ፍሬን ሰጥቷቸዋል::

+በዳሞቱ ገዢ በሞተለሚ አደጋ ቢደርስባቸው ቅዱስ ሚካኤል: ጸጋ ዘአብን ከሞት: እግዚእ ኃረያን ከትድምርተ አረሚ (ከአረማዊ ጋብቻ) አድኗቸዋል:: በሁዋላም የቅዱሱን መወለድ አብስሯቸዋል::

+ጻድቁ አቡነ ተክለ ሃይማኖት የጸነሱት መጋቢት 24 ቀን በ1206 ዓ/ም ሲሆን የተወለዱት ደግሞ ታሕሳስ24 ቀን በ1207 ዓ/ም ነው:: በተወለዱበት ቀንም ብዙ ተአምራት ተገልጸዋል:: ቤታቸውም በበረከት ሞልቷል::

*ዕድገት*

=>የጻድቁ የመጀመሪያ ስማቸው "ፍሥሃ ጽዮን" ይሰኛል:: ይሕንን ስም ይዘው: አባታቸው ጸጋ ዘአብን ተከትለው አድገዋል:: በተለይ ቅዱሳት መጻሕፍትን (ብሉያት: ሐዲሳትን) ተምረዋል:: በሥጋዊው ጐዳናም ብርቱ አዳኝ እንደ ነበሩ ይነገራል:: ዲቁናም ከወቅቱ ዻዻስ አባ ጌርሎስ ተቀብለዋል::

*መጠራት*

=>አንድ ቀን ፍሥሃ ጽዮስ ለአደን ወጥቶ ሲያነጣጥር ድንገት ከሰማይ አስደንጋጭ ድምጽ ተሰማ:: የክብር ባለቤት ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ አእላፍ መላእክት እያመሰገኑ በሚካኤል ክንፍ ተቀምጦ ወረደ::

+የወጣቱን አዳኝ ፍርሃቱን አርቆ ጌታችን ተናገረ:: "ከዛሬ ጀምሮ ስምህ ተክለ ሃይማኖት (ተክለ ሥላሴ) ይሁን:: ከዚህ በሁዋላ አራዊትን ሳይሆን ነፍሳትን ታድናለህ:: ዘወትር ካንተ ጋር ነኝ" ብሎ በግርማ ዐረገ:: ቅዱስ ተክለ ሃይማኖት ከዚህ ጊዜ በሁዋላ ሰዓትን አላጠፉም:: ንብረታቸውን ለነዳያን በትነው በትር ብቻ ይዘው ቤታቸው እንደ ተከፈተ ወደ ምናኔ ወጡ::

*አገልግሎት*

=>ቅዱስ ተክለ ሃይማኖት ከዻዻሱ ቅስና ተቀብለው የወንጌል አገልግሎትን ጀመሩ:: በመጀመሪያ ስብከታቸው እዚያው ሽዋ (ጽላልሽ) አካባቢ ብቻ በ10ሺ የሚቆጠሩ ሰዎችን አሳምነው አጠመቁ:: ያን ጊዜ ኢትዮዽያ 2 መልክ ነበራት::

+1ኛ ዮዲት (ጉዲት) በፈጠረችው ጣጣና በእስላሞች ተጽዕኖ ወደ ደቡብ አካባቢ ያለው ነዋሪ አንድም ሃይማኖቱን ክዷል: ወይም በባዕድ አምልኮ ተጠምዷል::
+2ኛው ደግሞ በዛግዌ ነገሥታት ጥረት ክርስትናና ምናኔ ተነቃቅቶ ነበር::

+ግማሹ ሃገር በጨለመበት ወቅት የደረሱት ሐዲስ ሐዋርያ አባ ተክለ ሃይማኖት በወጣት ጉልበታቸውና በኃይለ መንፈስ ቅዱስ ብዙ ቦታዎችን አደረሱ:: ሕዝቡን: መሣፍንቱን ወደ ሃይማኖት መልሰው: ማርያኖችን (ጠንቁዋዮችን) አጥፍተዋል::

*ገዳማዊ ሕይወት*

=>ቅዱስ ተክለ ሃይማኖት በወንጌል ብርሃን ኢትዮዽያን ከማብራታቸው ባለፈ ገዳማዊ ሕይወትንም አስፋፍተዋል:: እርሳቸው ከሁሉ የተሻሉ ሳሉም በ3 ገዳማት በረድዕነት አገልግለዋል::

+እነዚህም በአቡነ በጸሎተ ሚካኤል ገዳም ለ12 ዓመታት: በአቡነ ኢየሱስ ሞዐ ዘሐይቅ ገዳም ለ7 ዓመታት: በደብረ ዳሞ ከአቡነ ዮሐኒ ጋር ለ7 ዓመታት: በአጠቃላይ ለ26 ዓመታት አገልግለዋል::

+በአቡነ ኢየሱስ ሞዐ ከመነኮሱ በሁዋላም ወደ ምድረ ሽዋ (ዞረሬ) ተመልሰው በአንዲት በዓት ውስጥ ለ22 ዓመታት ቆመው ጸልየዋል:: በተሰበረ እግራቸውም 6 ጦሮችን በግራና በቀኝ ተክለው ለ7 ዓመታት ጸልየዋል::

*ስድስት ክንፍ*

=>ኢትዮዽያዊው ጻድቅና ሐዋርያ ቅዱስ ተክለ ሃይማኖት ከኢትዮዽያ ወደ ኢየሩሳሌም ተጉዘው ከቅዱሳት መካናት ተባርከዋል:: ጻድቁ ምድረ እሥራኤል የገቡት በየመንገዱ መንፈሳዊ ዘርን እየዘሩ: እያስተማሩና እያሳመኑ ነበር::

+የወቅቱ ሊቀ ዻዻሳት አባ ሚካኤል ጋርም ተገናኝተው ቡራኬን ተሰጣጥተዋል:: ዋናው ጉዳይ ግን ከዚህ በሁዋላ ነው:: ጻድቁ እመቤታችንና ጌታችን ከጽንሰታቸው እስከ ዕርገታቸው የረገጧቸውን ቦታዎች ሲመለከቱ በፍጹም ተደሞ እንባቸው ይፈስ ነበር::

+ምክንያቱም እግዚአብሔር ስላበቃቸው ተክለ ሃይማኖት የሚያዩት ቦታውን አልነበረም:: በገሃድ:-
-በቤተ መቅደስ ብስራቱን
-በቤተ ልሔም ልደቱን
-በቤተ ዮሴፍ ግዝረቱን
-በፈለገ ዮርዳኖስ ጥምቀቱን
-በቤተ አልዓዛር ተአምራቱን ይመለከቱ ነበር::

+የጉብኝታቸው የመጨረሻ ክፍል ወደ ሆነው ቀራንዮ ደርሰው ጌታቸውን እንደ ተሰቀለ ሆኖ ቢመለከቱት ከዓይናቸው ይፈስ የነበረው ቁጡ እንባ መልኩን ቀየረና ዓይናቸው ጠፋ::
በዚያች ቅጽበት ስም አጠራሯ የከበረ እመቤታችን ድንግል ማርያም ፈጥና ደርሳ ተክልየን ወደ ሰማይ አሳረገቻቸው::

+በዚያም:-
-የብርሃን ዐይን ተቀብለው
-6 ክንፍ አብቅለው
-የወርቅ ካባ ላንቃ ለብሰው
-ማዕጠንተ ወርቁን ይዘው
-ከ24ቱ ካህናተ ሰማይም ተደምረው
-ሥላሴን በአንድነቱና ሦስትነቱ ተመልክተው
-"ስብሐት ወክብር ለሥሉስ ቅዱስ ይደሉ" ብለው መንበረ ጸባኦትን አጥነው ወደ መሬት ተመልሰዋል::

*ተአምራት*

=>የተክልየ ተአምራት እንደ ሰማይ ከዋክብት የበዛ ነው::
*ሙት አንስተዋል
*ድውያንን ፈውሰዋል
*አጋንንትን አሳደዋል
*እሳትን ጨብጠዋል
*በክንፍ በረዋል
*ደመናን ዙፋን አድርገዋል::

+ብዙ ደቀ መዛሙርትን አፍርተው ደብረ ሊባኖስን መሥርተዋል:: በዚያም ሴትና ወንድ መነኮሳት እንደ ሕጻናት አብረው ኑረዋል:: በዘመናቸው ሰይጣን ታሥሯልና::

*ዕረፍት*

=>ጻድቅ: ሰማዕትና ሐዋርያ አቡነ ተክለ ሃይማኖት ብርሃን ሆነው መከራን በብዙ ተቀብለው: እልፍ አእላፍ ፍሬን አፍርተው: በተወለዱ በ99 ዓመት: ከ8 ወር: ከ1 ቀናቸው ነሐሴ 24 ቀን በ1306 ዓ/ም ዐርፈዋል:: ጌታ: ድንግል ማርያምና ቅዱሳን ከሰማይ ወርደው ተቀብለዋቸዋል:: 10 ትውልድ የሚያስምር ቃል ኪዳንም ተቀብለዋል::

††† ቅድስት ክርስቶስ ሠምራ †††

=>እጅግ የከበረችና የተመሰገነች እናታችን ቅድስት ክርስቶስ ሠምራን እናመሰግናታለን:: እርሷ በሁሉ ጐዳና ፍጹምነትን ያሳየች ኢትዮዽያዊት እናት ናት:: ገና ከልጅነት የነበራት የትሕትናና የመታዘዝ ሕይወት እጅግ ልዩ ነበር:: እናታችን ቅድስናን ያገኘችው ገና በትዳር ውስጥ እያለች ነው::

+ከተባረከ ትዳሯ 12 ልጆችን አፍርታ: ምጽዋትን የዕለት ተግባሯ አድርጋ ኑራለች:: በዚህ ደግነቷም ሙት እስከ ማንሳት ደርሳለች:: አብያተ ክርስቲያናትን አንጻ አንድ ልጇን (ዳግማዊ ቂርቆስን) አዝላ ምናኔ ወጥታልች::

+በደብረ ሊባኖስ ውስጥ የቆየችው ቅድስት እናት ተጋድሎዋን የፈጸመችው ግን ጣና ሐይቅ ውስጥ ነው:: በተለይ ለ22 ዓመታት ሐይቁ ውስጥ አካሏ አልቆ: አሣ በሰውነቷ ውስጥ እስከሚያልፍ ድረስ ተጋድላለች:: በቀኝና በግራ 12 ጦሮችን ተክላም ጸልያለች::

+ብዙ ኃጥአንን አማልዳ: 12 ክንፎችን አብቅላ: ከፍ ከፍ ብላለች:: ከርሕራሔዋ ብዛት የተነሳ ሰይጣንን እንኩዋ ለማስታረቅ ሞክራለች:: ጌታም ከሲዖል ነፍሳትን እንድታወጣ ፈቅዶላታል:: ቅድስት ክርስቶስ ሠምራ ያረፈችው በዚህ ዕለት ሲሆን አጽሟ ዛሬ በራሷ ገዳም (ጣና ዳር) ይገኛል::

+" ቅዱስ ቶማስ ዘመርዓስ "+

=>ቅዱስ ቶማስ "መርዓስ" በምትባል ሃገር የፈለቀ የንጋት ኮከብ: ጻድቅ: ገዳማዊ: ዻዻስ: ሐዋርያ: ሰማዕትና ሊቅ ነው:: የዚህን ቅዱስ ተጋድሎ እንደ እኔ ያለው ሰው አይቻለውም:: የእርሱ ሕይወት ክርስትና ምን እንደ ሆነ ያሳያል::

✟...ገድለ ቅዱስን...✟

29 Aug, 12:49


††† እንኳን ለሰላሳ ሺ ግብጻውያን ሰማዕታት ዓመታዊ የዕረፍት በዓል በሰላም አደረሳችሁ፤ አደረሰን። †††

††† በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን! †††

††† ሠለስቱ እልፍ ሰማዕታት †††

††† ዘመነ ሰማዕታት አርባ ሰባት ሚሊየን ክርስቲያኖችን በአርባ ዓመታት ከበላ በኋላ በ305 (312) ዓ/ም ቢጠናቀቅም ስለ ሃይማኖት መሞት ግን እስከ ምጽዓት ድረስ ይቀጥላል:: ለእያንዳንዱ ክርስቲያን ከሚቀርቡ ፈተናዎች ሁሉ እጅግ ከባዱ ይሔው ሰማዕትነት ነውና ሊቀበለው ያለው (ያደለው) ይቀበለዋል::

ቤተ ክርስቲያን በባሕር ላይ ያለች መርከብ ናትና ዘወትር በፈተና ውስጥ መኖሯ የሚጠበቅ ነው:: ዘመነ ሰማዕታትን ተከትሎ የመጣው የመናፍቃን ዘመን ሲሆን ለመቶ ሃምሳ ዓመታት ያህል መናፍቃን እንደ አሸን ፈልተዋል:: በዚያው ልክ ከዋክብት ቅዱሳን ሊቃውንት ነበሩና በየጊዜው ጉባኤያትን እየሠሩ: መናፍቃንን አሳፍረዋል:: ምዕመናንንም አጽንተዋል::

በ451 ዓ/ም የተፈጸመው ድርጊት ግን ዛሬም ድረስ ጠባሳው የሚለቅ አልሃነም:: ንጉሡ መርቅያንና ጳጳሱ ልዮን የንስጥሮስን ትምሕርት አለባብሰው ሊያስተምሩ ሲሞክሩ ግጭት በመፈጠሩ ቤተ ክርስቲያን ለመጀመሪያ ጊዜ ወደ ሁለት ተከፈለች::

በጉባኤው የነበሩ ስድስት መቶ ሰላሳ ስድስት ጳጳሳት ስቃይና ሞትን ፈርተው በኑፋቄ መጽሐፍ ላይ በመፈረማቸው "መለካውያን" (ከእግዚአብሔር ይልቅ ለንጉሥ የሚታዘዙ) ተባሉ:: ጉባኤውም "ጉባኤ ከለባት" (የውሾች ስብሰባ): "ጉባኤ አብዳን" (የሰነፎች ጉባኤ) ተብሏል::

የወቅቱ የእስክንድርያ ፓትርያርክ ቅዱስ ዲዮስቆሮስ ግን "በኑፋቄው ላይ አልፈርምም::" ከማለቱ አልፎ መናፍቃኑን አወገዛቸው:: በዚህ ምክንያት ጽሕሙን ነጭተው: ጥርሱንም አርግፈው: ወደ ጋግራ ደሴት ከሰባት ደቀ መዛሙርቱ ጋር አሳደዱት::
በዚያም ለሦስት ዓመታት ቆይቶ በ454 ዓ/ም ዐረፈ::

እግዚአብሔር ፈርዶባቸው ንጉሡ መርቅያን እና ንግሥቲቱ ብርክልያ (ክፉ ሴት ናት) ድንገት ሞቱ:: ፈተናው ግን በዚህ አላበቃም:: በዙፋኑ የተተካው ሌላኛው ጨካኝ ልዮን ነበር:: መንፈሳዊውን አርበኛ አባ ዲዮስቆሮስን በሞት ያጡት የግብጽ ክርስቲያኖች ደቀ መዝሙሩን "አባ ጢሞቴዎስን እንሾማለን::" ቢሉ ንጉሡ ከለከለ::

የሚሾመው መለካዊ ነው ብሎ አብሩታርዮስ የሚባል መናፍቅ ጳጳስ በላያቸው ላይ ሾመባቸው:: ይህንን መታገስ ለሕዝቡና ለካህናቱ ከባድ ነበር:: ተኩላ እንኳን በበጐች ላይ በይፋ ተሹሞ: ተደብቆም ቢሆን እየነጠቀ መብላት ልማዱ ነው:: መናፍቁ ጳጳስ በተለያየ መንገድ ሕዝቡን ለመሳብ ሞክሮ ነበር::

ለምሳሌ አውጣኪን (የክርስቶስን ሰው መሆን ምትሐት የሚል 'የቱሳሔ' አስተማሪ መናፍቅ ነው::) አወገዘው:: እነሱ ግን ተረድተውታልና ቦታ አልሰጡትም:: ምክንያቱም አውጣኪ ከቀድሞም የተወገዘ መናፍቅ ነውና:: የሚገርመው ከሕዝቡ አንድስ እንኳ ከመናፍቁ ጳጳስ የሚባረክ አልነበረም:: ሥጋውን ደሙንም ከእውነተኛ ካህናት በድብቅ ይቀበሉ ነበር::

አንድ ቀን ግን መናፍቁ ጳጳስ አብሩታርዮስ ተገድሎ ተገኘ:: (መልአክ ቀሥፎት ነው የሚሉ አሉ:: እስካሁን ድረስ የገዳዩ ማንነት አልታወቀም::) ግብጻውያን ክርስቲያኖች ግን የእርሱን ሞት ሲሰሙ ደጉን እረኛ አባ ጢሞቴዎስን ሾሙ:: ችግሩ የመጣው ከዚህ በኋላ ነው::

የመናፍቁ ተከታዮች ለንጉሡ ልዮን "አንተን ንቀው: የሾምከውን ገደሉ:: ሌላ ጳጳስም ሾሙ::" ብለው መልዕክት ላኩለት:: በዚህ የተበሳጨው ልዮን ኦርቶዶክሳውያንን ባገኛችሁበት ሁሉ ግደሉ የሚል አዋጅ አወጣ:: ይህን አዋጅ ተከትሎ ሰላሳ ሺ ሰዎች በእስክንድርያ ከተማ ተጨፈጨፉ::

ገዳዮቹ ወንድ: ሴት: ሕፃን: ሽማግሌ ሳይመርጡ የክርስቲያኖችን ደም አፈሰሱ:: ለሦስት ቀናትም ግድያው ቀጥሎ እንደ ነበር ይነገራል::
ልበ አምላክ ቅዱስ ዳዊት "ወኀጥኡ ዘይቀብሮሙ" እንዳለ ቀባሪም አጡ::

ገዳዮቹ ቀጥለውም አባ ጢሞቴዎስን አስረው አጋዙት:: ለአሥር ዓመታትም አሰቃዩት:: ከእነዚህ ዓመታት በኋላ ግን ንጉሡ ተጸጽቶ አባ ጢሞቴዎስን ወደ መንበሩ መልሶታል:: ወገኖቻችን የግብጽ ክርስቲያኖች እንኳን ያኔ ዛሬም በጽናታቸው አብነት ልናርጋቸው የሚገቡ ናቸው::

††† አምላከ ሰማዕታት በቸርነቱ ይጠብቀን:: ከበረከታቸውም ያድለን::

††† ነሐሴ 23 ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት
1.ሰላሳ ሺ የእስክንድርያ (ግብጽ) ሰማዕታት
2.ቅዱስ ድምያኖስ ሰማዕት

††† ወርኀዊ በዓላት
1.ልበ አምላክ ቅዱስ ዳዊት
2.ቅዱስ ጊዮርጊስ ሊቀ ሰማዕታት
3.ነቢየ ጽድቅ ቅዱስ ሰሎሞን (ንጉሠ እሥራኤል)
4.አባ ጢሞቴዎስ ገዳማዊ
5.ቅዱስ ዳንኤል ነቢይ
6.አባ ሳሙኤል
7.አባ ስምዖን
8.አባ ገብርኤል

††† "በጐንም ለማድረግ ብትቀኑ የሚያስጨንቃችሁ ማን ነው? ነገር ግን ስለ ጽድቅ እንኳ መከራን ብትቀበሉ ብጹዓን ናችሁ:: ማስፈራራታቸውንም አትፍሩ: አትናወጡም:: ዳሩ ግን ጌታን እርሱም ክርስቶስን በልባችሁ ቀድሱት:: በእናንተ ስላለ ተስፋ ምክንያትን ለሚጠይቋችሁ ሁሉ መልስ ለመስጠት ዘወትር የተዘጋጃችሁ ሁኑ:: ነገር ግን በየውሃነትና በፍርሃት ይሁን::" †††
(፩ጴጥ. ፫፥፲፫-፲፮)

††† ወስብሐት ለእግዚአብሔር †††

✟...ገድለ ቅዱስን...✟

28 Aug, 07:03


††† እንኳን ለታላቁ ነቢይ ቅዱስ ሚክያስ ዓመታዊ የዕረፍት በዓል በሰላም አደረሳችሁ፤ አደረሰን። †††

†††በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን! †††

††† ቅዱስ ሚክያስ ነቢይ †††

††† ነቢይ ማለት በቁሙ ኃላፍያትን (አልፎ የተሠወረውን ምሥጢር): መጻዕያትን (ገና ለወደ ፊት የሚሆነውን) የሚያውቅ ሰው ማለት ነው:: ሃብተ ትንቢት የእግዚአብሔር የባሕርይ ገንዘቡ ሲሆን እርሱ ለወደደው ደግሞ በጸጋ ይሰጠዋል:: እነዚህም ከጌታ ሃብተ ትንቢት የተሰጣቸው አባቶችና እናቶች "ቅዱሳን ነቢያት" በመባል ይታወቃሉ::

ዘመነ ነቢያት ተብሎ የሚታወቀው ብሉይ ኪዳን ቢሆንም እስከ ምጽዓት ድረስ ጸጋውን እግዚአብሔር ለፈቀደላቸው አይነሳቸውም:: በሐዋርያት መካከልም ቅዱስ አጋቦስን የመሰሉ ነቢያት ነበሩ:: (ሐዋ. 11:27) ቅዱሳን ነቢያት ከእግዚአብሔር እየተላኩ ሰውን ከፈጣሪው እንዲታረቅ ይመክራሉ: ይገስጻሉ::

ከበጐ ሃይማኖታቸውና ንጽሕናቸው የተነሳም እግዚአብሔርን በተለያየ አርአያና አምሳል አይተውታል::
"እስመ በአንጽሖ መንፈስ ርዕይዎ ነቢያት ለእግዚአብሔር: ወተናጸሩ ገጸ በገጽ" እንዳለ አባ ሕርያቆስ:: (ቅዳሴ ማርያም)

የብዙ ነቢያት ፍጻሜአቸው መከራን መቀበል ነው:: እውነትን ስለ ተናገሩ: አንዳንዶቹም በእሳት: አንዳንዶቹም በሰይፍ: አንዳንዶቹም በመጋዝ ተፈትነዋል:: ሌሎቹ ለአናብስት ሲጣሉ ቀሪዎቹ ደግሞ በድንጋይ ተወግረዋል::

ስለዚህም መከራቸው ለቤተ ክርስቲያን መሠረት ተብለዋል:: ጌታም ለደቀ መዛሙርቱ "ሌሎች ደከሙ: እናንተ በድካማቸው ገባችሁ::" ብሎ የነቢያቱን መከራ ተናግሯል:: (ዮሐ. 4:36)

ነቢያት ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ እና ድንግል እናቱን ለማየት ብዙ ጥረዋል: ሽተዋልም:: "ብዙ ነቢያትና ጻድቃን እናንተ የምታዩትን ሊያዩ ሹ::" እንዳለ ጌታ በወንጌል::
(ማቴ. 13:16, 1ጴጥ. 1:10)
ዛሬ ግን በሰማያት ጸጋ በዝቶላቸው: ክብር ተሰጥቷቸው ሐሴትን ያደርጋሉ::

††† ቅዱሳን ነቢያት በዋነኝነት
¤አሥራ አምስቱ አበው ነቢያት:
¤አራቱ ዐበይት ነቢያት:
¤አሥራ ሁለቱ ደቂቀ ነቢያትና
¤ካልአን ነቢያት ተብለው በአራት ይከፈላሉ::

††† አሥራ አምስቱ አበው ነቢያት ማለት:-
*ቅዱስ አዳም አባታችን
*ሴት
*ሔኖስ
*ቃይናን
*መላልኤል
*ያሬድ
*ኄኖክ
*ማቱሳላ
*ላሜሕ
*ኖኅ
*አብርሃም
*ይስሐቅ
*ያዕቆብ
*ሙሴና
*ሳሙኤል ናቸው::

††† አራቱ ዐበይት ነቢያት
*ቅዱስ ኢሳይያስ ልዑለ ቃል
*ቅዱስ ኤርምያስ
*ቅዱስ ሕዝቅኤልና
*ቅዱስ ዳንኤል ናቸው::

††† አሥራ ሁለቱ ደቂቀ ነቢያት
*ቅዱስ ሆሴዕ
*አሞጽ
*ሚክያስ
*ዮናስ
*ናሆም
*አብድዩ
*ሶፎንያስ
*ሐጌ
*ኢዩኤል
*ዕንባቆም
*ዘካርያስና
*ሚልክያስ ናቸው::

††† ካልአን ነቢያት ደግሞ:-
*እነ ኢያሱ
*ሶምሶን
*ዮፍታሔ
*ጌዴዎን
*ዳዊት
*ሰሎሞን
*ኤልያስና
*ኤልሳዕ . . . ሌሎችም ናቸው::

††† ነቢያት በከተማም ይከፈላሉ::
*የይሁዳ (ኢየሩሳሌም):
*የሰማርያ (እሥራኤል)ና
*የባቢሎን (በምርኮ ጊዜ) ተብለው ይጠራሉ::

††† በዘመን አከፋፈል ደግሞ:-
*ከአዳም እስከ ዮሴፍ (የዘመነ አበው ነቢያት):
*ከሊቀ ነቢያት ሙሴ እስከ ነቢዩ ሳሙኤል (የዘመነ መሳፍንት ነቢያት)
*ከቅዱስ ዳዊት እስከ ዘሩባቤል ያሉት (የዘመነ ነገሥት ነቢያት)
*ከዘሩባቤል ዕረፍት እስከ መጥምቁ ዮሐንስ ያሉት ደግሞ (የዘመነ ካህናት ነቢያት) ይባላሉ::

††† ስለ ቅዱሳን ነቢያት በጥቂቱ ይህንን ካልን ወደ ዕለቱ በዓል እንመለስ::

ቅዱስ ሚክያስ ቁጥሩ ከአሥራ ሁለቱ ደቂቀ ነቢያት ሲሆን ዘመነ ትንቢቱም ቅ.ል. ክርስቶስ በ800 ዓ/ዓ አካባቢ ነው:: "ደቂቀ ነቢያት" ማለት በጥሬው "የነቢያት ልጆች" ማለት ነው::
አንድም የጻፏቸው ትንቢቶች ሲበዙ አሥራ አራት ምዕራፍ: ሲያንስ አንድ ምዕራፍ ያላቸው ናቸውና ደቂቅ ይላቸዋል::

ሚክያስ አባቱ ሞራት (ሞሬት) ይባላል:: ሚክያስ ማለት "መኑ ከመ አምላክ - እንደ እግዚአብሔር ያለ ማን ነው!" ማለት ነው:: አንድም "መልአከ እግዚአብሔር" ማለት ነው:: የአባቶቻችን ሁሉ ስማቸው እግዚአብሔርን የሚሰብክ ነው::

ቅዱሱ ነቢይ ገና ልጅ እያለ መላእክት ያነጋግሩት ነበር:: በዚህ ምክንያት ከሰው አይቀርብም:: ትክ ብለው ሲያዩት በፊቱ ላይ ብርሃን ቦግ ቦግ እያለ ይታይ ነበር:: በወጣትነት ዘመኑ እግዚአብሔር ለትንቢት ሲጠራው በእሺታ ታዘዘ:: በሦስቱ ነገሥታት (በኢዮአታም: አካዝና ሕዝቅያስ) ዘመንም ትንቢቶችን ተናግሯል:: ሕዝቡን: መሣፍንቱን: ነገሥታቱን አስተምሮ ገስጿል::

አንድ ቀን በቤተ ልሔም ሲያልፍ የዳዊት ከተማ ፈት ሁና: ዳዋ በቅሎባት ቢመለከት አዘነ:: ወዲያውም ትንቢት ተናገረላት::
"ወአንቲኒ ቤተ ልሔም ምድረ ኤፍራታ: ኢትቴሐቲ እምነገሥተ ይሁዳ: እስመ እምኔኪ ይወጽዕ ንጉሥ: ዘይርዕዮሙ ለሕዝብየ እሥራኤል::"

"አንቺም የኤፍራታ ምድር ቤተ ልሔም: የይሁዳ ነገሥታት ከነገሡባቸው ከተሞች ከቶ አታንሺም:: ወገኖቼን እሥራኤልን የሚጠብቃቸው ንጉሥ (መስፍን) ካንቺ ዘንድ ይወጣልና::" አለ::

ይኸውም አልቀረ ለጊዜው ከሚጠት በኋላ ደጉ ዘሩባቤል ነግሦባታል:: በፍጻሜው ግን የባሕርይ ንጉሠ ነግሥት ኢየሱስክርስቶስ ከንጽሕት ድንግል ማርያም ተወልዶባታል::

ቅዱስ ሚክያስ ወገኖቹን ሲያስተምርና ሲመራ ኑሮ: ሰባት ምዕራፎች ያሉትን ሐረገ ትንቢት ተናግሮ: በመልካም ሽምግልና: በንጉሡ ሕዝቅያስ ዘመን ዐርፏል:: ወገኖቹ ቀብረውታል:: ጌታም በክብረ ነቢያት ከልሎታል::

††† ቸር አምላከ ነቢያት የነቢያቱን መከራ አስቦ ከመከራ: በእንባቸውም ከእንባ ይሰውረን:: ከተረፈ በረከታቸውም አያጉድለን::

††† ነሐሴ 22 ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት
1.ቅዱስ ሚክያስ ነቢይ

††† ወርኀዊ በዓላት
1.ቅዱስ ዑራኤል ሊቀ መላእክት
2.ቅዱስ ሉቃስ ወንጌላዊ
3.ቅዱስ ደቅስዮስ (የእመቤታችን ወዳጅ)
4.አባ እንጦንስ አበ መነኮሳት
5.አባ ጳውሊ የዋህ

††† "ምን ይዤ ወደ እግዚአብሔር ፊት ልምጣና በልዑል አምላክ ፊት ልስገድ? የሚቃጠለውን መስዋዕትና የአንዱን ዓመት ጥጃ ይዤ በፊቱ ልምጣን? እግዚአብሔርስ በሺህ አውራ በጐች: ወይስ በእልፍ የዘይት ፈሳሾች ደስ ይለዋልን? . . . ሰው ሆይ! መልካሙን ነግሮሃል:: እግዚአብሔርም ከአንተ ዘንድ የሚሻው ምንድር ነው? ፍርድን ታደርግ ዘንድ: ምሕረትንም ትወድ ዘንድ: ከአምላክህም ጋር በትሕትና ትሔድ ዘንድ አይደለምን?" †††
(ሚክ. ፮፥፮)

††† ወስብሐት ለእግዚአብሔር †††

✟...ገድለ ቅዱስን...✟

27 Aug, 13:51


†††✝️🌻 እንኳን ለቅዱሳት አንስት ኄራኒ ሰማዕት: ንግሥተ ሳባ እና ንግሥት ዕሌኒ ዓመታዊ በዓል በሰላም አደረሳችሁ፤ አደረሰን። †††✝️🌻

†††✝️🌻 በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን! †††✝️🌻

††† ✝️🌻ቅድስት ኄራኒ ሐዋርያዊት ሰማዕት †††✝️🌻

††† ይህቺ ቅድስት ወጣት መልክ ከደም ግባት: ምግባር ከሃይማኖት: ስም ከመልካምነት የተባበረላት ሰማዕት ናት:: #ኄራኒ ማለት "ሰላማዊት: የተወደደች" ማለት ነው:: አንድም በጥሬው "ሰላምና ፍቅር" ማለት ነው::

ቅድስት ኄራኒ በመጀመሪያው መቶ ክ/ዘመን በታናሽ እስያ የንጉሥ #ሉክያኖስ ልጅ ናት:: ከተወለደች ጀምሮ ስለ ክርስትና ሰምታ አታውቅም:: ምክንያቱም አባቷ ጣዖት አምላኪ ከመሆኑ ባለፈ ክርስቲያኖችን ይቀጣ ስለ ነበር ነው::

ልጁን ማንም እንዳያገኛት ሲል ንጉሡ ለቅድስት ኄራኒ ቤተ መንግስት ሠራላት:: ማንም እንዳይገባ በዙሪያው 12 አጥር አጠረበት:: ጣዖቶቹን እንድታጥን አገልጋዮችንም ሾመላት::

ምናልባት አጥር ሰውን ሊከለክለው ይችላል:: #እግዚአብሔር ግን እግዚአብሔር ነውና ምንም አይከለክለውም:: ጌታ ደግሞ ይህቺን ወጣት ለወንጌል አገልግሎት ይፈልጋታል:: አንድ ቀን አባቷ: ልጁ ምሑር እንድትሆንለት አለ የተባለ ሽማግሌ ፈላስፋ ቀጠረላት::

ጥበበ እግዚአብሔር ማለት ይሔ ነው:: አባቷ ይሕ ሽማግሌ ማንን እንደሚያመልክ አልተረዳም:: አረጋዊው እጅግ የተዋጣለት ክርስቲያን ነው:: ግን ማንም አያውቅበትም:: አረጋዊው ቅድስት ኄራኒን ዝም ብሎ ሊሰብካት አልወደደም::

መጀመሪያ በስነ ምግባር አነጻት:: ቀጥሎ ግን "ጌታ ሆይ! ጐዳናህን ምራት" እያለ ይጸልይላት ገባ:: ጌታችን ልመናውን ሰምቶታልና ቅድስቷ አንድ ቀን ግሩም ራዕይን አየች::

እርሷ ለማዕድ ተቀምጣ ሳለ: የምሥራቅና የምዕራብ መስኮቶቿም ተከፍተው ሳሉ: በምሥራቁ መስኮት ነጭ ርግብ በአፏ የወይራ ዝንጣፊ (ቆጽለ ዘይት) ይዛ ገባችና ማዕዷ ላይ አኑራው ሔደች:: እርሷን ተከትሎ ደግሞ ንስር በአፉ አክሊል ይዞ ገብቶ ማዕዷ ላይ ጥሎት ሔደ::

በ3ኛው ግን ቁራ: እባብ በአፉ ይዞ በምዕራቡ መስኮት ገብቶ ማዕዷ ላይ ጥሎት ወጣ:: ቅድስት ኄራኒ ያየችው ራዕይ ቢጨንቃት ሽማግሌ መምሕሯን "ተርጉምልኝ" አለችው::

እርሱም "ልጄ ሆይ! ለዘመናት ስጠብቀው የነበረ ምኞቴን ነው ጌታ ያሳየሽ:: የሕልምሽ ትርጉም እንዲህ ነው:- ነጭ ርግብ የመንፈስ ቅዱስ (የሃይማኖት) ምሳሌ ናት:: የወይራ ዝንጣፊው ደግሞ #ማሕተመ_ጥምቀት( #ሜሮን) ነው:: ቁራ የክፉ ነገሥታት ምሳሌ ሲሆን እባብ የመከራ ምሳሌ ነው::

ንስር ድል የመንሳት ምልክት ሲሆን አክሊል ደግሞ የመንግስተ ሰማያት ምሳሌ ነው:: ልጄ! ክርስቲያን ሆነሽ የሚደርስብሽን ሁሉ ጌታ አሳይቶሻል" ብሎ ተርጉሞላት ተሰናበታት::

እርሷም ወደ ምሥራቅ ዙራ ጸለየች:- "የማላውቅህ አምላክ ሆይ! ወደ እውነትህ ምራኝ" ስትል ለመነች:: በዚያች ሰዓት የእግዚአብሔር መልአክ መጥቶ አጽናናት:: የሚያጠምቃትም እንደሚልክላት ነገራት::

በዚያን ጊዜ አባቷ ገብቶ "ልጄ! ከመሣፍንቱ ላንዱ ልድርሽ ስለሆነ ምን ትያለሽ?" አላት:: "3 ቀን ስጠኝ" አለችውና ሰጣት:: ወደ ጣዖቶቹ ዕለቱኑ ወርዳ "ላግባ ወይስ ይቅርብኝ?" አለቻቸው:: ከቀድሞም በወርቅ የተለበጡ ድንጋዮች ናቸውና ዝም አሉ:: በሙሉ ቀጥቅጣ ሰባብራቸው ተመለሰች::

በዘመኑ #ቅዱሳን_ሐዋርያት(በተለይ እነ #ቅዱስ_ዻውሎስ) በሕይወተ ሥጋ ነበሩና ከቅዱስ ዻውሎስ ደቀ መዛሙርት አንዱ ቤቷ እንደ ተዘጋ ገባ:: ክርስትናን ከጥንቱ እስከ ተፍጻሜቱ አስተምሮ አጠመቃት::

በ3ኛው ቀን አባቷ "ምን መከርሽ?" ቢላት "የእኔ ምክር #መርዓተ_ክርስቶስ(ሰማያዊ ሙሽራ) መሆን ነው" አለችው:: አባቷ ደነገጠ:: እጅግ ስለ ተናደደ ወደ አደባባይ አውጥቶ: አስሮ መሬት ላይ ጣላትና በመቶ የሚቆጠሩ ፈረሶች እንዲረግጧት አደረገ::

በወቅቱ ሰው የሚጠብቀው የአካሏን ቁርጥራጭ ነበር:: ነገር ግን ጌታ ከእርሷ ጋር ነበርና ልብሷ እንኩዋ ጭቃ አልነካም:: አባቷ ንጉሥ ሉክያኖስና ሠራዊቱ ያዩትን ማመን አልቻሉም:: ሁሉም ድምጻቸውን ከፍ አድርገው "ከክርስቶስ በቀር ሌላ አምላክ የለም" አሉ:: ቅድስት ኄራኒ ምንም ሳትናገር ይህንን ሁሉ ሰው ማረከች::

ወዲያውም ንጉሡ መልእክተኛ ልኮ: የቅዱስ ዻውሎስ ደቀ መዝሙርን አስጠርቶ: ከነ ቤተሰቦቹ ተጠመቀ:: የዚህን ዓለም ክብር ንቆም ንግሥናውን ተወ:: የጸሎት ሰውም ሆነ:: የቅድስት ኄራኒ ተጋድሎ ግን ቀጠለ::

በአካባቢው የነበረ ንጉሥ መጥቶ የአባቷን መንግስት ቀማ:: እርሷንም እጅግ አሰቃያት:: እርሱ አልፎ አርማንዮስ የሚባል ንጉሥ እንዲሁ አሰቃያት:: እርሱም አለፈ:: ከእርሱ ቀጥሎ የመጣው ንጉሥ ብዙ መከራዎችን በእርሷ ላይ አደረሰ:: በጦርም ጐኗን ወግቶ ገደላት::

ከጥቂት ሰዓታት በሁዋላ ግን ልክ ከእንቅልፉ እንደሚነቃ ሰው ተነስታ ጠራችው:: በጣም ደንግጦ "አምላክሽ አምላኬ ነው" ሲል አመነ:: ከ30,000 በላይ ሠራዊቱን ይዞም ተጠመቀ::

ቅድስት ኄራኒ በቀረ ሕይወቷ በስብከተ ወንጌል እስያን አድርሳለች:: ጌታ አብርቶላት: እርሷም አብርታ: እልፍ ፍሬን አፍርታ: በዚህች ቀን ዐርፋለች:: የሐዋርያትንም: የሰማዕታትንም አክሊል ተቀዳጅታለች::

†††✝️🌻 ንግሥተ ሳባ †††✝️🌻

††† ይሕቺ ኢትዮዽያዊት ከ3 ሺ ዘመናት በፊት የነበረች ደግ እናት ናት:: በሥጋዊ ደረጃ ከታንዛንያ እስከ #የመን ያስተዳደረች ስመ ጥር ንግሥት ስትሆን በመንፈሳዊው ደረጃ ደግሞ እግዚአብሔር የቀባውን ሰው ፍለጋ ወደ #ኢየሩሳሌም ተጉዛለች::

ከዚያውም አምልኮተ እግዚአብሔርን ከሥርዓተ ኦሪት ጋር አምጥታለች:: ድንግልናዋን ለታላቁ #ንጉሥ_ሰሎሞን ሰጥታ #ምኒልክን ወልዳለች:: ይህቺ ንግሥት በጌታችን (በፈጣሪ) አንደበትም ተመስግናለች:: (ማቴ. 12:42) በስምም " #ሳባ: #አዜብና #ማክዳ ተብላ ትታወቃለች:: ዛሬ ዕለተ ልደቷ ነው::

††† ቅድስት ዕሌኒ ንግሥት †††

††† ይሕቺ ቅድስት የቅዱስ #ቆስጠንጢኖስ እናቱ: የመስቀሉ ወዳጅ: የቤተ ክርስቲያን ባለውለታ የሆነች ክብርት እናት ናት:: ይህቺም ቅድስት የተወለደቺው በዚሁ ዕለት ነው::

††† የቅዱሳት እናቶቻችን አምላክ እህት እናቶቻችንን ከክፋትም: ከጥፋትም: ይሠውርልን:: ለሃገርም: ለሃይማኖትም የሚጠቅሙ ሴቶችንም ጌታ አይንሳን:: በረከታቸውም ይደርብን::

††† ነሐሴ 21 ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት
1.ተዝካረ ፍልሠታ ለማርያም ድንግል (6ኛ ቀን)
2.ቅድስት ኄራኒ ሐዋርያዊት (ሰማዕት)
3.ቡርክት ንግሥተ ሳባ (ልደቷ)
4.ቅድስት ዕሌኒ ንግሥት (ልደቷ)

††† ወርኀዊ በዓላት
1.ቅድስት ድንግል እግዝእትነ ማርያም ወላዲተ አምላክ
2.አበው ጎርጎርዮሳት
3.አቡነ ምዕመነ ድንግል
4.አቡነ አምደ ሥላሴ
5.አባ አሮን ሶርያዊ
6.አባ መርትያኖስ ጻድቅ

††† " #ንግሥተ_አዜብ በፍርድ ቀን ከዚህ ትውልድ ጋር ተነስታ ትፈርድበታለች:: የሰሎሞንን ጥበብ ለመስማት ከምድር ዳር መጥታለችና:: እነሆም ከሰሎሞን የሚበልጥ ከዚህ አለ::" †††
(ማቴ. 12:42)

††† ወስብሐት ለእግዚአብሔር †††

✟...ገድለ ቅዱስን...✟

24 Aug, 07:06


✞✞✞ በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ ፡፡ አሜን ፡፡ ✞✞✞

❖ ነሐሴ ፲፰ ❖

✞✞✞ እንኩዋን ለሊቁ #ቅዱስ_እለእስክንድሮስ
ዓመታዊ የዕረፍት በዓል በሰላም አደረሳችሁ ✞✞✞

+"+ #ቅዱስ_እለእስክንድሮስ_ሊቅ +"+

=>ቅዱሱ ታላቅ የሃይማኖት ጠበቃ ሲሆን ሃገረ ሙላዱ
(የተወለደባት) #ግብጽ ናት:: የተወለደው በ3ኛው መቶ
ክ/ዘመን ሲሆን በምግባሩ: በትምሕርቱ ለምዕመናን
ጥቅም ሆኗቸዋል:: ቅዱስ እለእስክንድሮስ ገና ልጅ ሳለ
ምሥጢረ ክርስትናን ይማር ዘንድ ወደ #ቅዱስ_ዼጥሮስ
#ተፍጻሜተ_ሰማዕት ሔዷል::

+ቅዱስ ዼጥሮስ የግብጽ 17ኛ ፓትርያርክና ሊቅ ሲሆን
በታሪክ የዘመነ ሰማዕታት መጨረሻ ተብሎ ይታወቃል::
ከዚህ ሰማዕት ሥር የሚማሩ ብዙ አርድእት ቢኖሩም 3ቱ
ግን ተጠቃሽ ነበሩ::
1.ቅዱስ እለእስክንድሮስ (ደጉ)
2.አኪላስ (ውዳሴ ከንቱ ወዳጅ)
3.አርዮስ (የቤተ ክርስቲያን ጠላት)

+ከእነዚህም አርዮስ ቤተ ክርስቲያንን ለማጥፋት ሲታትር
ነበር:: አኪላስ ደግሞ ሆዱ ዘመዱ: ስለ ምንም
የማይጨንቀው ሰው ነበር:: ቅዱስ እለእስክንድሮስ ግን
በጾምና በጸሎት እየተጋ መምሕሩን ቅዱስ ዼጥሮስን
ለመተካት (ለመምሰል) ይጥር ነበር::

+ወቅቱ ዘመነ ሰማዕታት እንደ መሆኑ ቅዱሱ ከመምሕሩ
ጋር ብዙ ነገሮችን አሳልፏል:: አርዮስ ክዶ: ቅዱስ
ዼጥሮስ ካወገዘው በሁዋላ እንደ ባልንጀራ ገስጾ
ሊመልሰውም ሞክሮ ነበር:: ነገር ግን የአርዮስን ክፋት
ከጌታ ዘንድ የተረዳው ቅዱስ ዼጥሮስ ደቀ መዝሙሩን
እለእስክንድሮስን ጠርቶ መከረው::

+"እኔ ከሞትኩ በሁዋላ አኪላስ ይተካል:: ከአርዮስ ጋር
ስለሚወዳጅ በ6 ወሩ ይቀሠፋል:: አንተ ግን ከአርዮስ
መርዝ ተጠበቅ" አለው:: ይህንን ካለው በሁዋላ
ወታደሮች የቅዱስ ዼጥሮስን አንገት ቆረጡ:: ይህ
የተደረገውም እ.ኤ.አ በ311 ዓ/ም ነው::

+ወዲያውም አኪላስ ተሾመ:: እንደ ተባለውም ከአርዮስ
ጋር ስለተወዳጀ በ6 ወሩ ተቀሰፈ:: በዚያው ዓመትም
ቅዱስ እለእስክንድሮስ የእስክንድርያ (ግብጽ) 19ኛ
ፓትርያርክ (ሊቀ ዻዻሳት) ሆኖ ተሾመ::

+ሊቁ ሲሾም መልካም አጋጣሚ የነበረው ያ የመከራ
ዘመን ማለፉ ሲሆን በጣም ከባዱ ግን የአርዮስ
ተከታዮች ከተገመተው በላይ መበብዛታቸው ነው::
ቅዱሱ ሊቅ በዽዽስና መንበሩ ለ17 ዓመታት ሲቆይ
ዕንቅልፍም ሆነ ዕረፍት አልነበረውም::

+በዚህ እየጾመ: እየጸለየ: ሥጋውን እየጐሰመ ለፈጣሪው
ይገዛል:: በዚያ ደግሞ ሕዝቡን ነጋ መሸ ሳይል
ያስተምራል:: ምዕመናንን ከአርዮስ የኑፋቄ መርዝ
ለመታደግ ባፍም: በመጣፍም (በደብዳቤ) አስተማረ::

+ብርሃን የሆነ ደቀ መዝሙሩ #ቅዱስ_አትናቴዎስ
እያገዘው: አርዮስን ከነአበጋዞቹ አሳፈሩት:: ለእያንዳንዷ
የኑፋቄ ጥያቄ ተገቢውን መንፈሳዊ ምላሽ ከመስጠቱ
ባለፈ አርዮስን ከአንዴም 2: 3ቴ በጉባኤ አውግዞታል::

+ነገሩ ግን በዚህ መቁዋጨት ባለመቻሉ ንጉሡ ቅዱስ
ቆስጠንጢኖስ ጉባኤ ኒቅያ እንዲደረግ አዋጅ ነገረ::
እ.ኤ.አ በ325 ዓ/ም (በእኛ በ318 ዓ/ም) ከመላው
ዓለም ለጉዳዩ 2,348 የሚያህሉ ሰዎች ተሰበሰቡ::
ከእነዚህ መካከል 318ቱ ሊቅነትን ከቅድስና የደረቡ: ስለ
ቀናች ሃይማኖት ብዙ መከራ ያሳለፉ ነበሩ::

+ይህንን የተቀደሰ ጉባኤ እንዲመራ ደግሞ መንፈስ
ቅዱስ ቅዱስ እለአእስክንድሮስን መረጠ:: ሊቁም አበው
ቅዱሳንን አስተባብሮ በሺህ የሚቆጠሩ ተከታዮች ያሉትን
አርዮስን ተከራክሮ ረታው::

+በጉባኤው መጨረሻ አርዮስ "አልመለስም" በማለቱ
እርሱን አውግዘው: ጸሎተ ሃይማኖትን ሠርተው: 20
ቀኖናወችን አውጥተው: መጽሐፈ ቅዳሴ ደርሰው:
አሥራው መጻሕፍትን ወስነው: ቤተ ክርስቲያንን በዓለት
ላይ አጽንተው ተለያይተዋል::
የዚህ ሁሉ ፍሬ አበጋዙ ደግሞ ቅዱስ እለእስክንድሮስ
ነው::

+እርሱ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስን "#ወልድ_ዋሕድ:
#አምላክ: #ወልደ_አምላክ: #የባሕርይ_አምላክ"
መሆኑን መስክሮ ክብርን አግኝቷል:: የእምነታችንም
መሠረቱ ይሔው ነው:: ክርስቶስን "ፈጣሬ ሰማያት
ወምድር: የባሕርይ አምላክ: ዘዕሩይ ምስለ አብ
በመለኮቱ (ከአባቱ ጋር በመለኮቱ የሚተካከል)" ብለው
ካላመኑ እንኩዋን ድኅነት ክርስትናም አይኖርም::

+ከጉባኤ #ኒቅያ በሁዋላ ቅዱስ እለእስክንድሮስ
በመልካሙ ጐዳና ሲጋደል: ምዕመናንንም ሲያጸና ኑሯል::
ዘወትር ወንጌልን በፍቅር ያነብ ነበርና ሲጸልይ የብርሃን
ምሰሶ ይወርድለት ነበር::

+ስለ ውለታውም #ቤተ_ክርስቲያን በግብጽ ካበሩ 5ቱ
#ከዋክብት_ሊቃውንት እንደ አንዱ ታከብረዋለች:: ቅዱሱ
ሊቅ በ328 ዓ/ም (በእኛ በ320 ዓ/ም) በዚህች ቀን
ዐርፎ በክብር ተቀብሯል::

=>ቸር አምላከ ቅዱሳን ቤተ ክርስቲያንን ከነጣቂ ተኩላ
ይጠብቅልን:: ከቅዱሱ ሊቅም በረከትን ይክፈለን::

=>ነሐሴ 18 ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት=
1.ተዝካረ ፍልሠታ ለማርያም ድንግል (3ኛ ቀን)
2.ቅዱስ እለእስክንድሮስ ሊቅ
3.ቅዱስ እንድራኒቆስ ዲያቆን
4.አባ ዘክርስቶስ ዘወሎ (ኢትዮዽያዊ ጻድቅ)

=>ወርሐዊ በዓላት
1.ቅዱስ ፊልዾስ ሐዋርያ
2.አቡነ ኤዎስጣቴዎስ ሰባኬ ሃይማኖት (ረባን)
3.አቡነ አኖሬዎስ ዘደብረ ጽጋጋ
4.ማር ያዕቆብ ግብፃዊ
5.ቅዱስ ያዕቆብ ሐዋርያ (ከ72ቱ አርድእት)

=>+"+ . . . ለቅዱሳን አንድ ጊዜ ፈጽሞ ስለ ተሰጠ
ሃይማኖት እንድትጋደሉ እየመከርኩአችሁ እጽፍላችሁ
ዘንድ ግድ ሆነብኝ:: +"+ (ይሁዳ. 1:3)

<<< ወስብሐት ለእግዚአብሔር >>>

✟...ገድለ ቅዱስን...✟

23 Aug, 12:25


††† እንኳን ለሰማዕታት ቅዱስ እንጣዎስ እና ቅዱስ ያዕቆብ ዓመታዊ የዕረፍት በዓል በሰላም አደረሳችሁ፤ አደረሰን። †††

††† በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን! †††

††† ቅዱስ እንጣዎስ አሞራዊ †††

††† ይሕ ቅዱስ በቀደመ ሕይወቱ ክርስቲያኖችን የሚጠላ አስቸጋሪ አረማዊ ነበር:: ሃገሩ #ሶርያ( #ደማስቆ) ሲሆን ግብሩ ጣዖት ማምለክና መስረቅ ነበር:: በቅድስት ቤተ ክርስቲያንና በምዕመናን ላይም ግፍን ፈጽሟል:: በሥጋዊ ጉልበቱ ኃይለኛ ስለ ነበር የተፈራ ነው::

ሁልጊዜ በጠዋት ወደ #ቤተ_ክርስቲያን ይሔዳል:: የሚሔደው ግን ንዋያተ ቅድሳትን ለመዝረፍ: አንድም ካህናትን ለመደብደብ ነበር:: የሚገርመው ግን የወቅቱ ምዕመናንና ካህናት ይህን ሁሉ እያደረገባቸው አይጠሉትም:: ይልቁኑ ይጸልዩለት ነበር እንጂ:: ምክንያቱም ክርስትና ማለት ጠላትን መውደድ ነውና:: (ማቴ. 7)

የእግዚአብሔር ትዕግስትና የምዕመናን ጸሎት ተደምሮው አንድ ቀን ፍሬ አፈራ:: እንጣዎስ እንደ ለመደው ለክፉ ሥራ ወደ #ቅዱስ_ቴዎድሮስ ቤተ ክርስቲያን ይሔዳል:: ከዚያም እንደ ደረሰ ወደ ውስጥ ገብቶ: የሚማታውን ተማቶ: የሚዘርፈውንም ዘርፎ: የተረፉትን ንዋያተ ቅድሳት በእሳት አቃጠላቸው::

#እግዚአብሔር ከዚህም በላይ ታጋሽ ነውና አላጠፋውም:: "ዘኢይፈቅድ ለኃጥእ ሞቶ" እንዲል የኃጢአተኛውን መመለስ እንጂ መሞቱን አይፈልግም:: ለዚያም ነው ዛሬ ይሔ ሁሉ ግፍ በቤተ ክርስቲያን ውስጥ እየተሠራ እግዚአብሔር እንደማያይ ዝም የሚለው:: ለሁሉም ቀን አለውና በፈረደ ቀን ግን በፊቱ የሚቆም አይኖርም::

እንጣዎስ ግን የሠራውን ሠርቶ እወጣለሁ ሲል አልተሳካለትም:: ከበሩ አካባቢ ሲደርስ: ከወደ ሰማይ አካባቢ ድምጽ ሰምቶ ቀና ሲል መላእክት እንደሱ ዓይነት ኃጢአተኞችን አሰልፈው በጦርና በቀስት ሲወጉአቸው ተመለከተ::

ድንገት ግን ከመላእክቱ አንዱ ዘወር ብሎ አንድ ቀስት ወደ እንጣዎስ ወረወረ (ተኮሰ):: ቀስቷ አካሉ ውስጥ ገብታለችና እንጣዎስ መሬት ላይ ወድቆ ለሞት ደረሰ:: ላበቱ በግንባሩ ላይ በጭንቅ እየፈሰሰ ጮኸ::

"ጌታየ ኢየሱስ ክርስቶስ ሆይ! ማረኝ? ራራልኝ? ይቅር በለኝ? በድፍረት ባለ ማወቅም በድየሃለሁ:: ይቅር በለኝና ላምልክህ: ስምህንም ልሸከም" ሲል በጭንቀት ውስጥ ሆኖ አሰምቶ ጸለየ:: በዚያ የነበሩ ምዕመናን ማን: በምን እንደ ወጋው ባያውቁም ባዩት ነገር ግን እጅግ ደስ አላቸው:: እነርሱም የፈለጉትና የጸለዩለት ነገር ይሔው ነበርና::

ወዲያው ግን እንጣዎስ ከሞት ጫፍ ተመልሶ ተነሳ:: መጀመሪያ በቦታው የነበሩ ካህናትና ምዕመናንን "ይቅር በሉኝ?" አለ:: ቀጥሎም ወደ ዻዻስ ዘንድ ሔዶ "አጥምቀኝ" ሲል ጠየቀ:: እርሱ በሚጠመቅበት ቀን ብዙ አሕዛብና ክርስቲያኖች ተሰብስበው ነበር::

እርሱ በከተማዋ ዝነኛ ነበር:: ሥርዓቱ ሁሉ ተደርሶ ቅዱሱ ወደ ውሃ ገንዳው ሲገባ ሁሉ እያዩ የብርሃን ምሰሶ ከሰማይ ወረደ:: ይህንን በገሃድ የተመለከቱ ከ10,000 በላይ አሕዛብ ወዲያውኑ በክርስቶስ አምነው አብረውት ተጠምቀዋል::

ቅዱስ እንጣዎስ ከዚህ በሁዋላ ምስጉን ክርስቲያን ሆነ:: ስለ ቀደመ ሕይወቱ ፈንታ ጾምን: ጸሎትን: ፍቅርን: ምጽዋትን ገንዘብ አደረገ:: ሕይወቱም ለብዙ ሰዎች መስታውት ሆነ:: #እመቤታችን ድንግል ማርያምንም ይወዳት ነበርና ወደ ቅዱሳን ማሕበር ( #ኢየሩሳሌም) ወስዳው በሥጋዊ አንደበት ተከናውኖ ሊነገር የማይቻል ምሥጢርን ገልጣለታለች::

እነዚህን የቅድስና ጊዜያት በስኬት ያሳለፈው ቅዱስ እንጣዎስ መጨረሻው ሰማዕትነት ሆነ::
አረማውያን ወገኖቹና ቀድሞ የሚያውቁት ወደ ቀደመ ክፋትና ክህደት እንዲመለስ ጠየቁት:: "አይሆንም" አላቸው:: በአደባባይ ለፍርድ አቅርበው ደሙ እስኪፈስ ገረፉት::

ጥርሶቹን በሙሉ በድንጋይ አረገፏቸው:: ደሙና ጥርሶቹ መሬት ላይ ተዘሩ:: ነገር ግን ይሕ ስቃይ ቅዱሱን ከፍቅረ ክርስቶስ ሊለየው አልቻለም:: አሕዛብም ተስፋ ቆርጠው በዚህች ቀን ገድለውታል:: ቅዱስ እንጣዎስም ከሁዋለኛው ዘመን #ሰማዕታት እንደ አንዱ ተቆጥሯል::

††† ቅዱስ ያዕቆብ ግብጻዊ †††

††† ቅዱስ ያዕቆብ ተወልዶ ያደገው #መኑፍ (ግብጽ) ውስጥ ሲሆን ዘመኑም 3ኛው መቶ ክ/ዘመን ነው:: ወላጆቹ የተባረኩ ናቸውና እርሱ ሳይወለድ የነበሯቸውን 3 ሴቶች ልጆች "ተማሩ" ብለው ወደ ገዳም ቢያስገቧቸው በዚያው መንነው ቀሩባቸው::

በዚህ ሲያዝኑ #ቅዱስ_ያዕቆብ ተወልዶላቸዋል:: እነርሱም በቃለ እግዚአብሔርና በጥበብ አሳድገውታል:: ትንሽ ከፍ ሲል በአካባቢው ከነበረ አንድ ቅዱስ ሽማግሌ ጋር ተደብቀው ገድልን ይሠሩ ነበር:: ሁሌም መልካም ምግባራትን ከመፈጸም ባለፈ ሙሉውን ሌሊት ባሕር ውስጥ ሰጥመው ይጸልዩ ነበር::

ዘመነ ሰማዕታት በመጣ ጊዜም 2ቱ ተመካክረው ስመ ክርስቶስን በገሃድ ሰብከዋል:: በዚህ ምክንያት ቅዱሱን ሽማግሌ ወዲያው ሲገድሉት ቅዱስ ያዕቆብን ግን ብዙ አሰቃይተውታል:: በመጨረሻም በዚህች ቀን ተሰይፎ የክብርን አክሊል ተቀብሏል::

††† አምላከ ሰማዕታት ቤተ ክርስቲያንን ከመከራ ይጠብቅልን:: ከበረከታቸውም ያሳትፈን::

††† ነሐሴ 17 ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት
1.ተዝካረ ፍልሠታ ለማርያም ድንግል
2.ቅዱስ እንጣዎስ አሞራዊ (ሰማዕት)
3.ቅዱስ ያዕቆብ ግብጻዊ (ሰማዕት)
4.ቅዱስ አክራጥስ ሰማዕት
5.አባ እለእስክንድሮስ ዘቁስጥንጥንያ

††† ወርኀዊ በዓላት
1.ቅዱስ እስጢፋኖስ ሊቀ ዲያቆናት (ቀዳሜ ሰማዕት)
2.ቅዱስ ያዕቆብ ሐዋርያ (ወልደ ዘብዴዎስ)
3.ቅዱሳን አበው መክሲሞስና ዱማቴዎስ
4.አባ ገሪማ ዘመደራ
5.አባ ዸላሞን ፈላሢ
6.አባ ለትጹን የዋህ
7.ቅዱስ ኤዺፋንዮስ ሊቅ (ዘደሴተ ቆዽሮስ)

††† "ኃጢአተኞችን ሊያድን #ክርስቶስ_ኢየሱስ ወደ ዓለም መጣ የሚለው ቃል የታመነና ሁሉ እንዲቀበሉት የተገባ ነው:: ከኃጢአተኞችም ዋና እኔ ነኝ:: ስለዚህ ግን የዘላለምን ሕይወት ለማግኘት በእርሱ ያምኑ ዘንድ ላላቸው ሰዎች ምሳሌ እንድሆን ኢየሱስ ክርስቶስ ዋና በምሆን በእኔ ላይ ትዕግስቱን ሁሉ ያሳይ ዘንድ ምሕረትን አገኘሁ::" †††
(1ጢሞ. 1:15)

††† ወስብሐት ለእግዚአብሔር †††

✟...ገድለ ቅዱስን...✟

24 Jul, 11:48


✞✞✞ በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ ፡፡ አሜን ፡፡ ✞✞✞

✞✞✞ እንኩዋን ለነቢዩ #ቅዱስ_ዮናስ እና ለእናታችን #ቅድስት_አውፎምያ ዓመታዊ የዕረፍት በዓል በሰላም አደረሳችሁ ✞✞✞

✞✞✞ ቅዱስ ዮናስ ነቢይ ✞✞✞

=>በቤተ ክርስቲያን አስተምሕሮ ከ12ቱ #ደቂቀ_ነቢያት አንዱ የሆነው #ቅዱስ_ዮናስ ከክርስቶስ ልደት 800 ዓመታት በፊት እንደ ነበረ ይታመናል:: #ሊቃውንት እንዳስተማሩን ደግሞ እናቱ #ቅዱስ_ኤልያስን የመገበችው የሰራፕታዋ መበለት ናት:: ቅዱስ ዮናስ ገና ሕጻን ሳለ በእሥራኤል ምድር ዝናብ ለ3 ዓመታት ከ6 ወራት ተከልክሎ ነበር::

+ይሕንንም ያደረገው ደጉ ነቢይ ኤልያስ ለአምልኮተ እግዚአብሔር ቀንቶ ነው:: በወቅቱ ኤልያስ በሰራፕታ ሳለ ሕጻኑ ዮናስ ታሞ ሞተ:: ልጇ የሞተባት መበለትም ኤልያስን ለመነችው:: ኤልያስም ወደ ፈጣሪው ማልዶ ሕጻኑን ዮናስን ከሞት አስነስቶታል:: ትንሽ ከፍ ባለ ጊዜም ከጉዋደኞቹ (ከነቢያቱ) #አብድዩና #ኤልሳዕ ጋር ሆነው ታላቁን ነቢይ ኤልያስን ተከትለውታል::

+ኤልያስ ካረገ በሁዋላ ሁሉም በየተሰጣቸው አገልግሎት ተሠማርተዋል:: ቅዱስ ዮናስን #እግዚአብሔር "ወደ ነነዌ ሒደሕ ንስሃን ስበክ" አለው:: ዮናስ ግን የፈጣሪውን መሐሪነት ጠንቅቆ ያውቃልና አልሔድም አለ:: (ተመልከቱ የየዋሕነት ብዛት)

+እግዚአብሔር እየደጋገመ እንዲሔድ ሲነግረው ነቢዩ "እንዲሕ የሚዘበዝበኝ ከፊቱ ብቀመጥ አይደል" ብሎ ሊኮበልል ወጣ:: ነገር ግን አልቀናውም:: በእርሱ ምክንያት ማዕበል ተነሳ:: ሕዝቡም ሊያልቁ ሆነ:: ከእንቅልፉ የነቃው ዮናስ ከመርከቡ ላሉት አሕዛብ አምልኮተ እግዚአብሔርን ሰብኮላቸው: በእርሱ ጠያቂነት ሐምሌ 15 ቀን ወደ ባሕር ጥለውታል::

+አሣ አንበሪም ተቀብሎታል:: በግዙፉ አሣ ውስጥም ያለ እንቅልፍ በጾም: በጸሎትና በምስጋና 3 ለቀን ቆይቷል::
ሙስና ሳያገኘውም በዚህች ቀን አሣ አንበሪው #ነነዌ ዳር ላይ ተፍቶታል:: ቅዱስ ዮናስ እግዚአብሔር እንዳዘዘው "እስከ ሠሉስ ዕለት ትትገፈታእ ነነዌ ዓባይ ሃገር" /እስከ ሦስት ቀን ድረስ ነነዌ ትገለበጣለች (ዮናስ 3:4)/ ብሎ አሰምቶ ሰበከ::

+የነነዌ ሰዎችም በስብከተ ዮናስ አምነው: ንስሃም ገብተው ድነዋል:: በዚህም ጌታችን በወንጌል ላይ አመስግኗቸዋል:: ቅዱስ ዮናስ መኮብለሉ #በሐዲስ_ኪዳን ለሚደረገው ምስጢረ ትንሳኤ ጥላ (ምሳሌ) ነውና ይደነቃል:: (ማቴ. 12:38) ነቢዩ ግን በተረፈ ሕይወቱ ሕዝቡን ሲያስተምር: ፈጣሪውን ሲያገለግል ኑሮ በመልካም ሽምግልና ዐርፏል::

+"+ ቅድስት አውፎምያ ሰማዕት +"+

=>እናታችን #ቅድስት_አውፎምያ (ስሟ አፎምያ አይደለም:: በስሕተት "ው" መካከል ላይ የገባች እንዳይመስልዎ:: እስመ ከመዝ ስማ-ስሟ እንዲሁ ነው የሚጠራው) በ3ኛው መቶ ክ/ዘመን ከነበሩ ወጣት ክርስቲያኖች አንዷ ናት:: ገና ከልጅነቷ ልቧ በፍቅረ ክርስቶስ የተነደፈ ነበር::

+በዚህም ምክንያት ራሷን በጾምና በጸሎት ወስና ትኖር ነበር:: እድሜዋ ገና በአሥራዎቹ ቢሆንም በመንኖ ጥሪት መኖር ምርጫዋ ነበር:: ሊቃውንት አበው ከሰማዕትነቷ ደርበው "ጻድቅት አውፎምያ" እያሉም ይጠሯታል::

+አንድ ቀን ግን መንገድ ወጥታ ነበርና ክርስቲያኖች ሲሰቃዩ ተመለከተች:: ምንም ጥፋት ሳይገኝባቸው ክርስቶስን ስላመለኩ ብቻ ይሙት በቃ ተፈርዶባቸው ሊገደሉ እየተወሰዱ ነበር:: አሕዛብ ግብራቸው የአውሬ ነውና ርሕራሔ የላቸውም:: ሰማዕታቱ ደማቸው በየመንገዱ እየፈሰሰ ጥቁር ሰንሰለት በአንገታቸው: በእጃቸውና በእግራቸው ላይ አድርገው ይጐትቷቸው ነበር::

+ቅድስት አውፎምያ የተደረገውን ሁሉ ተመልክታ አምርራ አለቀሰች:: ፈጠን ብላም ወደ መኮንኑ ቀርባ ገሰጸችው::
"አንተ አእምሮ የጎደለህ! እንዴት ክርስቲያኖችን እንዲህ ታሰቃያለህ? አምላካቸው #ጌታ_ክርስቶስ ታጋሽ ባይሆን ኑሮ በቅጽበት ከገጸ ምድር ባጠፋህ ነበር" አለችው::

+በድፍረቷ የተገረመው መኮንኑ "አንቺስ ማንን ታመልኪያለሽ?" ሲል ጠየቃት:: እርሷም "ሰማይና ምድርን የፈጠረውን: ስለ እኛ ሲል በቀራንዮ አንባ የተሠዋውን #ኢየሱስ ክርስቶስን አመልካለሁ" ስትል መለሰችለት:: በዚያች ሰዓት የመኮንኑ ቁጣ በቅድስቷ ላይ ነደደ::

+ነገር ግን ቁጣውን ከቁም ነገር አልቆጠረችውምና እንዲያሰቃዩዋት አዘዘ:: ወታደሮቹ ሥጋዋን በብዙ አሰቃዩ:: ብላቴናዋ አውፎምያ ግን ጽንዕት ናትና አልቻሏትም:: በመጨረሻ በእሳት ተቃጥላ ትሞት ዘንድ ተፈረደባት::

+እሳቱ ከመሬት ከፍ ባለ ጊዜ ወደ ውስጥ ወረወሯት:: በእሳቱ መካከል ቁማ ለረዥም ጊዜ ጸለየች:: ከዚያም ነፍሷን አሳልፋ ሰጠች:: ምዕመናን በክብር ገንዘው ቀብረዋታል::

=>አምላካችን ከነቢዩና ከሰማዕቷ ወዳጆቹ በረከት ይክፈለን::

=>ሐምሌ 17 ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት=
1.ቅዱስ ዮናስ ነቢይ (ከአሣ አንበሪ ሆድ የወጣበት)
2.ቅድስት አውፎምያ (ጻድቅትና ሰማዕት)
3.ቅዱስ ዮስጦስ ሰማዕት (ታላቁ)
4.ቅዱስ ዘካርያስ

=>ወርኀዊ በዓላት
1.ቅዱስ እስጢፋኖስ ሊቀ ዲያቆናት (ቀዳሜ ሰማዕት)
2.ቅዱስ ያዕቆብ ሐዋርያ (ወልደ ዘብዴዎስ)
3.ቅዱሳን አበው መክሲሞስና ዱማቴዎስ
4.አባ ገሪማ ዘመደራ
5.አባ ዸላሞን ፈላሢ
6.አባ ለትጹን የዋህ
7.ቅዱስ ኤዺፋንዮስ ሊቅ (ዘደሴተ ቆዽሮስ)

=>+"+ በዚያን ጊዜ ከጻፎችና ከፈሪሳውያን አንዳንዶቹ መለሱና:- 'መምሕር ሆይ! ከአንተ ምልክት እንድናይ እንወዳለን' አሉት:: እርሱ ግን መልሶ እንዲህ አላቸው:- 'ክፉና አመንዝራ ትውልድ ምልክት ይሻል:: ከነቢዩም ከዮናስ ምልክት በቀር ምልክት አይሰጠውም:: ዮናስ በአሣ አንበሪ ሆድ ሦስት ቀንና ሦስት ሌሊት እንደ ነበረ እንዲሁ የሰው ልጅ በምድር ልብ ሦስት ቀንና ሦስት ሌሊት ይኖራል:: የነነዌ ሰዎች በፍርድ ቀን ከዚህ ትውልድ ጋር ተነስተው ይፈርዱበታል:: በዮናስ ስብከት ንስሃ ገብተዋልና:: እነሆም ከዮናስ የሚበልጥ ከዚህ አለ:: +"+ (ማቴ. 12:38)

<<< ወስብሐት ለእግዚአብሔር >>>

" ፍቅር ያጌብረኒ ከመ እንግር ዜናሆሙ ለቅዱሳን"::/የቅዱሳንን ዜና(ታሪክ) እንድመሰክር ፍቅር ያስገድደኛል::  አባ ጊዮርጊስ ዘጋስጫ /መጽሐፈ ምሥጢር

✟...ገድለ ቅዱስን...✟

13 Jul, 13:28


††† እንኳን ለሐዋርያው ቅዱስ መርቄሎስ እና ለነቢዩ ቅዱስ ዕዝራ ዓመታዊ የዕረፍት በዓል በሰላም አደረሳችሁ፤ አደረሰን። †††

†††በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን! †††

††† ቅዱስ መርቄሎስ ሐዋርያ †††

††† ቅዱሱ በነገድ እሥራኤላዊ የሆነ የመጀመሪያው መቶ ክ/ዘመን ሰው ነው:: ጌታችን በመዋዕለ ስብከቱ ሲያስተምር በምሥጢሩና በተአምራቱ ተማርኮ ተከትሎታል:: ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስም ከሰባ ሁለቱ አርድእት አንዱ ይሆን ዘንድ አድሎታል:: ከጌታችን ሕማማትና ስቅለት በፊትም ድውያንን መፈወስና አጋንንትን ማስወጣት ከቻሉ አርድእትም አንዱ ነው::

ቅዱስ መርቄሎስ በበዓለ ሃምሳ ጸጋ መንፈስ ቅዱስን ተቀብሎ ለወንጌል አገልግሎት ተሰማርቷል:: በተለያዩ የዓለም ክፍሎች ለሰላሳ አራት ዓመታት በማገልገሉ ሐዋርያት ስሙን "ጳውሎስ" ብለውታል:: ጳውሎስ ማለት ብርሃን ማለት ነውና:: ልክ ሳውል "ጳውሎስ" እንደተባለው ማለት ነው::

ስሙ የግብር (በሥራ የሚገኝ) ስም ነው:: በዚህም ምክንያት ዛሬም ድረስ ቤተ ክርስቲያን የምትጠራው "ጳውሎስ የተባለው መርቄሎስ" እያለች ነው::

ቅዱስ መርቄሎስ በ60ዎቹ ዓ/ም አካባቢ ከቅዱስ ጴጥሮስ ጋር በሮም ይሰብክ ነበር:: ኔሮን ቄሳር ሊቀ ሐዋርያትን ዘቅዝቆ ሲሰቅለው የተመለከተና ይህንኑ የጻፈ እርሱ ነበር:: ወታደሮቹ ቅዱስ ጴጥሮስን ገድለውት ሲሔዱ ቅዱስ መርቄሎስ እያነባ ቀርቦ: ችንካሮችንም ነቅሎ: ሊቀ ሐዋርያትን ከተሰቀለበት አወረደው::

በፍጥነት ዋጋው ውድ የሆነ ሽቱ አምጥቶ በቅዱስ ጴጥሮስ ሥጋ ላይ አፈሰሰና በፍቅርና በክብር ሊገንዘው ጀመረ:: በዚህ ጊዜ ሊቀ ሐዋርያት አይኑን ግልጥ አድርጎ መርቄሎስን ተመለከተውና አለው:- "ልጄ! ምነው ለእኔ ይህንን ያሕል ሽቱ አባከንክ?" አለውና ተምልሶ ዐረፈ::

ቅዱስ መርቄሎስም እግዚአብሔርን እያመሰገነ በንጹሕ በፍታ ገንዞ እርሱ በሚያውቀው ቦታ ሠወረው:: ሊቀ ሐዋርያትን በመገነዙ የክብር ክብር ተሰጥቶታል::

ቅዱሱ አሁንም ስብከተ ወንጌልን ቀጠለ:: ከጥቂት ጊዜ በኋላ ግን እርሱም ተይዞ በኔሮን ፊት ቀረበ:: ኔሮን ቄሳር ቅዱስ መርቄሎስን ጠየቀው:: "እንዴት ባለ አሟሟት ልግደልህ? እንደ መምህርሕ ጴጥሮስ ወይስ ሌላ የምትፈልገው ዓይነት አሟሟት አለህ?"

ቅዱስ መርቄሎስ መለሰለት:- "የትኛውም ዓይነት ሞት እኔን አያስፈራኝም:: የምፈልገው ወደ ጌታዬ ቶሎ መሔድ ብቻ ነው::" አለው:: ንጉሡ ኔሮንም ዘቅዝቃችሁ ስቀሉት አላቸው:: ወታደሮቹም በዚህች ዕለት እንደ ቅዱስ ጴጥሮስ ዘቅዝቀው ሰቅለው ገድለውታል::

††† ቅዱስ ዕዝራ ነቢይ †††

ከክርስቶስ ልደት በፊት በ500 ዓመት አካባቢ የነበረ
¤እሥራኤል ከምርኮ ከተመለሱ በኋላ መጻሕፍት ተቃጥለው ጠፍተው ነበርና ስለ እነሱ አብዝቶ የለመነ
¤ጥበብን ሽቷልና እግዚአብሔር ቅዱስ ዑራኤልን የላከለት
¤በሊቀ መላእክት እጅም ጽዋዐ ልቡናን የጠጣ
¤ብዙ ምሥጢራት የተገለጡለት
¤ለአርባ ቀናት ምግብ ሳይበላ አገልጋዮቹ የጠፉ መጻሕፍትን እየነገራቸው የጻፉለት
¤መጽሐፈ ዕዝራ የተሰኘ መጽሐፍን ያዘጋጀና
¤በብሉይ ኪዳን ከነበሩ ዐበይት ነቢያተ ጽድቅ አንዱ የሆነ ታላቅ የእግዚአብሔር ሰው ነው::

††† ስለ ቅድስናውም ሞትን አልቀመሰም:: በዚህች ዕለት ቅዱሳን መላእክት ብሔረ ሕያዋን ውስጥ አስገብተውታል::

††† እግዚአብሔር ከሐዋርያውና ከነቢዩ በረከትን አይንሳን::

††† ሐምሌ 6 ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት
1.ቅዱስ መርቄሎስ ሐዋርያ (ከሰባ ሁለቱ አርድእት)
2.ቅዱስ ዕዝራ ነቢይ
3.ቅዱስ በርተሎሜዎስ ሐዋርያ
4.ቅድስት ቴዎዳስያ ሰማዕት
5.ቅድስት ንስተሮኒን ዘኢየሩሳሌም

††† ወርኀዊ በዓላት
1.ቅድስት ደብረ ቁስቋም
2.አባታችን አዳምና እናታችን ሔዋን
3.አባታችን ኖኅና እናታችን ሐይከል
4.ቅዱስ ኤልያስ ነቢይ
5.ቅዱስ ባስልዮስ ዘቂሣርያ
6.ቅዱስ ዮሴፍ አረጋዊ
7.ቅድስት ሰሎሜ
8.አባ አርከ ሥሉስ
9.አባ ጽጌ ድንግል
10.ቅድስት አርሴማ ድንግል

††† "እግዚአብሔርም በቤተ ክርስቲያን አንዳንዶቹን አስቀድሞ ሐዋርያትን: ሁለተኛም ነቢያትን: ሦስተኛም አስተማሪዎችን: ቀጥሎም ተአምራት ማድረግን: ቀጥሎም የመፈወስን ስጦታ: እርዳታንም: አገዛዝንም: የልዩ ልዩ ዓይነት ልሳኖችንም አድርጓል:: ሁሉ ሐዋርያት ናቸውን? ሁሉስ ነቢያት ናቸውን? ሁሉስ አስተማሪዎች ናቸውን? . . . ነገር ግን የሚበልጠውን የጸጋ ስጦታ በብርቱ ፈልጉ::" †††
(፩ቆሮ. ፲፪፥፳፰)

††† ወስብሐት ለእግዚአብሔር †††

✟...ገድለ ቅዱስን...✟

29 Jun, 16:18


††† እንኳን ለቅዱሱ አባታችን የዋህ ዻውሊ ዓመታዊ የዕረፍት በዓል በሰላም አደረሳችሁ ፣ አደረሰን። †††

††† በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን! †††

††† ቅዱስ ዻውሎስ የዋህ †††

††† በ4ኛው መቶ ክ/ዘመን መጀመሪያ አካባቢ ግብፅ ውስጥ ተወልዶ ያደገው ቅዱሱ ስሙ ዻውሎስ ቢሆንም ብዙ ጊዜ የሚጠራው "የዋህ ዻውሊ" በሚል ነው:: ይሕስ እንደ ምን ነው ቢሉ:-

የዋህ ዻውሊ ከሕጻንነቱ ጀምሮ መጻሕፍትን የተማረ: ግን ደግሞ ትዕቢት: ቁጣና ቂምን የማያውቅ ገራገር ሰው ነው:: እድሜው ለአካለ መጠን ሲደርስ ቤተሰቦቹ ሚስት አግባ አሉት:: እርሱ ባያስብበትም ወገኖቹን ላለማሳዘን አገባ:: እንዳለመታደል ሆኖ ግን ያገባት ሴት በጣም ቆንጆ በዚያም ላይ ክፉ ነበረች:: የዋህ ዻውሊ ክፋቷን ሁሉ ታግሶ ለበርካታ ዓመታት አብሮ ኖረ:: ልጆችንም አፈሩ::

አሁንም ግን እርሷ ከክፋቷ ልትታገስ አልቻለችም:: ይባስ ብሎ ዻውሊ በሌለበት ከሌሎች ወንዶች ጋር ትዘሙት ያዘች:: የዋሁ ሰው ይሕንኑ ያውቃል ግን የእግዚአብሔርን ሥራ ዝም ብሎ በተስፋ ይጠብቅ ነበር:: ለነገሩስ እሱ ያርሳል: ይቆፍራል: ነዳያንን ያበላል: እንግዳ ይቀበላል እንጂ ክፋትን ለማሰብ ጊዜ አልነበረውም::

አንድ ቀን ግን ለሥራ ወደ በርሃ ወጥቶ አንድ ግሩም ዜና ሰማ:: "አባ እንጦንስ ምንኩስና የሚባል ሕይወተ መላእክትን ጀምሯል: ደቀ መዛሙርትንም ይቀበላል" አሉት:: ግን ሚስትና ልጆች አሉትና ምን ያደርጋል?

የዋህ ዻውሊ ሙሉ ቀን ሢሠራ ውሎ ወደ ቤቱ ሲመለስ ግን የጠበቀው ሌላ ነው:: ሚስቱ በራሱ መኝታ ላይ ከአገልጋይ እረኛው ጋር ራቁታቸውን አገኛቸው:: ልብ በሉልኝ በትክሻው ሞፈርና ምሳር: መጥረቢያም ይዟል:: እርሱ ግን ክፉን አላሰበም:: ጥሩ ልብስ አንስቶ ሁለቱንም አለበሳቸው::
እንዲሕም አላቸው:- "ከዚሕ በሁዋላ እኔ አልመለስም:: ሀብት ንብረቴን ውረሱ: በደስታም ኑሩ:: የልጆቼን ነገር ግን አደራ" ብሏቸው ተነሳ::

በእጁ ምንም አልያዘም:: በትከሻው ያለችውን ብጣሽ ጨርቅ ይዞ ወደ በርሀ ተጉዋዘ:: አባ እንጦንስም ተቀብለው አስተምረው አመነኮሱት:: ከዚያች ቀን ጀምሮ ራስን ዝቅ በማድረግ: በመታዘዝ አገለገለ:: ጾም: ጸሎትና ስግደቱንማ ማን ቆጥሮት::

እያለ እያለ ከብቅዐት ማዕርግ ደረሰ:: ምዕመናንም ሆነ መነኮሳት ሊጠይቁት ሲመጡ የእያንዳንዱ ኃጢአት በግንባራቸው ተጽፎ ይመለከት ነበርና ስለነሱ ሲያለቅስ ቅንድቡ ተላጠ:: ሰውነቱም አለቀ:: አንድ ቀን ጋኔን የያዘውን ሰው ፈውስ ብለው አመጡለት:: እርሱ ግን በአጋንንት ላይ ሥልጣን እያለው በትሕትና ተጠግቶ ጋኔኑን "አባ እንጦንስን ከምጠራብህ ቀስ ብለህ ውጣ" አለው:: ጋኔኑ ግን የፈራው መስሎት በትዕቢት "እንጦንስ ማነው?"አለው::

ያን ጊዜ የዋህ ዻውሊ እንደ እሳት ከጋለ ድንጋይ ላይ ቁሞ "ሕያው እግዚአብሔር ምስክሬ ነው:: ይሕ ጋኔን ካልወጣ አልወርድም" አለ:: ወዲያው በዘንዶ አምሳል ከሴትዮዋ ወጥቶ እየጮኸ ወደ ቀይ ባሕር ገባ::ቅዱስ ዻውሊ የዋሕም እንዲሕ በቅድስና ተመላልሶ በዚሕች ቀን በመልካም ሽምግልና ዐርፏል::

" የመንፈስ ፍሬ ግን ፍቅር: ደስታ: ሰላም: ትእግስት: ቸርነት: በጐነት: እምነት: የውሃት: ራስን መግዛት ነው:: እንደዚህ ያሉትን የሚከለክል ሕግ የለም:: የክርስቶስ ኢየሱስም የሆኑቱ ሥጋን ከክፉ መሻቱና ከምኞቱ ጋር ሰቀሉ::" (ገላ. 5:22)

††† ሰኔ 22 ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት=
1.ቅዱስ አባ ዻውሊ የዋሕ
2.ቅዱሳን ወክቡራን ቆዝሞስና ድምያኖስ (ሰማዕታት)
3.ቅድስት ቴዎዳዳ ሰማዕት (እናታቸው)
4.አንቲቆስ: ዮንዲኖስና አብራንዮስ (ሰማዕታት)

††† ወርኀዊ በዓላት
1.ቅዱስ ዑራኤል ሊቀ መላእክት
2.ቅዱስ ሉቃስ ወንጌላዊ
3.ቅዱስ ደቅስዮስ (የእመቤታችን ወዳጅ)
4.አባ እንጦንዮስ (አበ መነኮሳት)
††† አምላካችን ከቅዱስ ዻውሊ የውሃትን: ትእግስትን: በጐነትን: ጸጋ በረከትን ይክፈለን:: አሜን:: †††

††† ወስብሐት ለእግዚአብሔር †††


" ፍቅር ያጌብረኒ ከመ እንግር ዜናሆሙ ለቅዱሳን"::/የቅዱሳንን ዜና(ታሪክ) እንድመሰክር ፍቅር ያስገድደኛል::  አባ ጊዮርጊስ ዘጋስጫ /መጽሐፈ ምሥጢር/

✟...ገድለ ቅዱስን...✟

28 Jun, 09:48


✞✞✞🌹 በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ ፡፡ አሜን ፡፡ 🌹✞✞✞

🌹 እንኳን አደረሳችሁ 🌹

🌹 ሰኔ 21 ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት🌹

=>ትናንት ለስም አጠራሩ ጌትነት ይሁንና ጌታችንና
መድኃኒታችን ኢየሱስ_ክርስቶስ ወደ ሐዋርያት ወረደ:: ፊልዽስዩስ በምትባል ሃገር በዼጥሮስ እጅ
የመጀመሪያዋን ቤተ_ክርስቲያን አነጸ ብለን ነበር:: በዚህች ዕለት ደግሞ አእላፍ
መላዕክትን: ሰማያውያን ቅዱሳንን እና እናቱን ቅድስት
ድንግል
ማርያምን ይዟት ወረደ::

+ሐዋርያቱ አብዛኞቹ እዛው ሲጸልዩ አድረው ነበርና ጌታችን
ከቅዳሴው በፊት 2 ነገሮችን አሳየ:-
1.አስቀድሞ ቤተ ክርስቲያኗን በድንግል እናቱ ስም አክብሮ
ሥርዓተ ቤተ ክርረስቲያንን አሳየ::
2.ቀጥሎ ደግሞ ሊቀ ሐዋርያት ቅዱስ_ዼጥሮስን ከመካከል አቁሞ "አርሳይሮስ" ሲል ሾመው:: ይኼውም የዓለም ሁሉ ሊቀ ዻዻሳት
(ፓትርያርክ) ማለት ነው:: በዚህ ጊዜ ቅዱሳን መላእክት
"አክዮስ" እያሉ 3 ጊዜ አሰምተው ጮሁ:: አክዮስ ማለት በግዕዙ
"ይደልዎ": በዐማርኛው ደግሞ "ይገባዋል: ያሥምርለት"
እንደ
ማለት ነው::

+ጌታችን ይሕን ከከወነ በኋላ ይቀድስ ዘንድ ጀመረ::
¤አማናዊት ማሕደሩን ድንግል ማርያምን መንበር አድርጎ:
¤ቅዱስ ዼጥሮስ እንደ ተራዳኢ ካህን ቆሞ:
¤ቅዱስ_እስጢፋኖስ ሠራኢ ዲያቆን ሆኖ:
¤ሐዋርያት ድንግልን ከበው:
¤መላእክተ ብርሃን በክብራቸው ቁመው ጌታችን ቀድሶ
ቅዱስ ሥጋውንና ክቡር ደሙን ለወዳጆቹ አቀበለ::

+በዚያች ዕለት በፍጡር አንደበት ተከናውኖ ሊነገር
የማይችል ደስታ ተደረገ:: ከቅዳሴ በኋላ ጌታችን
ሐዋርያትን
አዘዛቸው::
"ከዚህ ቀን ጀምሮ በመላው ዓለም በእናቴ በማርያም ስም
አብያተ ክርስቲያናትን እነጹ:: ይህችን ዕለት የሚያከብራትን
አከብረዋለሁ::" ብሏቸው ከድንግል እናቱ ከመላዕክቱ ጋር
ዐረገ::

+"+ ሰኔ_ጐልጐታ +"+

=>ዳግመኛ በዚህ ቀን ሐዋርያው ቅዱስ ቶማስ
ይታሰባል::
ይኸውም ከሕንድ አውራጃዎች በአንዱ ወንጌልን ሰብኮ
እኩሎቹ ሲያምኑ እኩሎቹ እንቢ አሉ:: ቅዱስ ቶማስም
ያመኑትን
"ከጣዖት አምልኮና ከዝሙት ሸሹ" ብሎ መከራቸው::
+ምክሩን ከሰሙት አንዱ በዚያው ምሽት ሊጠጣ ወደ
መሸታ ቤት ይገባል:: ሰው ሁሉ ከወጣ በኋላ ባለ
መሸተኛዋ ሴት
እንደለመደችው አብረው እንዲተኙ ስትጠይቀው "እንዴት
ሐዋርያው ከዝሙት ሽሹ እያለ እንዲህ ትይኛለሽ?" በሚል
ሰይፍ
አውጥቶ አንገቷን ቆረጣት::

+እርሱ መልካም ያደረገ መስሎታል:: የሠራው ሥራ
(መግደሉ) ግን አሕዛባዊ ግብር ነው:: በማግስቱ ቅዱስ
ቶማስ ነገሩን
ሰምቶ ሰዎችን ሰበሰበና "ይህንን የአውሬ ድርጊት የፈጸመ
ማነው?" ሲል ጠየቀ:: ፈጻሚው ግን አልታወቅም በሚል
ዝም
አለ:: ወዲያው ቅዱሱ ሐዋርያ ዳቦ አንስቶ ቆረሰና
"ለበረከት እያነሳችሁ ውሰዱ" አለ:: ሰውየው ተራውን
ጠብቆ ሊያነሳ
ሲል እጁ ሰለለች::

+ሐዋርያው "ምነው ልጄ! ምን ሆንክ?" አለው:: እሱም
እንዳላመለጠ ሲያውቅ እውነቱን ተናዘዘ:: ቅዱስ ቶማስ
ግን ሕዝቡ
ሁሉ እንደተሰበሰበ ያን ወጣት ገስጾ "አስከሬኑን
አምጡልኝ" አለ:: የወጣቱን እጅ ፈውሶ "በል . . .
የገደልኩሽ
እኔ: የሚያስነሳሽ ግን ጌታየ_ኢየሱስ_ክርስቶስ ነው . . . ብለህ አንገቷን ቀጥለው" አለው::

+እንዳለው ቢያደርግ የሞተችው አፈፍ ብላ ተነሳች::
ይህንን ተአምር ያዩ አሕዛብ አምነው ተጠምቀዋል::

=>ከሐዋርያው በረከት ይክፈለን::

=>ሰኔ 21 ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት=
1.እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም
2.ቅድስት ቤተ ክርስቲያን
3.ቅዱሳን ሐዋርያት
4.ቅዱስ ዼጥሮስ ሊቀ ሐዋርያት
5.ቅዱሳን ዻውሎስና በርናባስ
6.ቅዱስ ቶማስ ሐዋርያ
7.ቅዱስ ባስልዮስ ዘቂሣርያ
8.ቅዱስ ጢሞቴዎስ ዘምስር (ሰማዕት)
9.አባ ከላድያኖስ ሊቀ ዻዻሳት

❖ወርኃዊ በዓላት
1፡ አበው ጎርጎርዮሳት
2፡ አባ ምዕመነ ድንግል
3፡ አባ ዓምደ ሥላሴ
4፡ አባ አሮን ሶርያዊ
5፡ አባ መርትያኖስ
6፡ አቡነ በጸሎተ ሚካኤል

=>+"+ ስለ ጽዮን ዝም አልልም . . .
አሕዛብም ጽድቅሽን: ነገሥታትም ሁሉ ክብርሽን ያያሉ::
የእግዚአብሔርም አፍ በሚጠራበት በአዲሱ ስም
ትጠሪያለሽ::
በእግዚአብሔር እጅ የክብር አክሊል በአምላክሽም እጅ
የመንግሥት ዘውድ ትሆኛለሽ:: +"+ (ኢሳ. 62:1-3)

<<< ወስብሐት ለእግዚአብሔር >>>

""ፍቅር ያጌብረኒ ከመ እንግር ዜናሆሙ ለቅዱሳን""::/የቅዱሳንን ዜና(ታሪክ) እንድመሰክር ፍቅር ያስገድደኛል::  አባ ጊዮርጊስ ዘጋስጫ /መጽሐፈ ምሥጢር/

✟...ገድለ ቅዱስን...✟

27 Jun, 10:53


††† እንኳን ለእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ዓመታዊ ሕንጸተ ቤታ (ሕንጸታ) በሰላም አደረሳችሁ፣ አደረሰን። †††

†††በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!

††† በዓለ ሕንጸታ †††

††† በዚሕች ቀን : በሐዲስ ኪዳን የመጀመሪያዋ ቤተ ክርስቲያን በአምላክ እናት ስም ታንጻለች::
ጥንተ ነገሩስ እንደ ምን ነው ቢሉ:-
ለስም አጠራሩ ጌትነት ይሁንና አምላካችን ኢየሱስ ክርስቶስ ደቀ መዛሙርቱን "ሑሩ ወመሐሩ ኩሎ አሕዛበ" (አሕዛብን ሁሉ ሒዱና አስተምሩ) /ማቴ. 28:19/ ባላቸው ቃል መሠረት ዓለምን በወንጌል ያርሷት ዘንድ በዕጣ ተካፍለዋታል::

የሰው ልጅ ድኅነቱ የሚፈጸመው ቅዱስ ሥጋውንና ክቡር ደሙን ሲቀበል ነውና (ዮሐ. 6:56) አበው ሐዋርያት ቁርባንን በተመረጡ ሰዎች ቤት እያዘጋጁ ቀድሰው ያቆርቡ ነበር::

በመጀመሪያ በጽርሐ ጽዮን: ቀጥሎም በተለያዩ ሰዎች ቤት እንዲሕ ይከናወን ነበር:: ለጸሎት ሥራ ደግሞ አንዳንዴ ምኩራበ አይሁድን ይጠቀሙ ነበር:: እየቆየ ሲሔድ ግን ከአሕዛብ ያመኑ ሰዎች ቁጥር እጅጉን በዛ::

በተለይ ቅዱስ ጳውሎስ ያሳመናቸው ለጸሎት እያሉ ወደ ጣዖት ቤት መግባት አመጡ:: በዚሕ ምክንያት መምሕራን ሕዝቡን "ካመናችሁ በኋላ እንዴት ወደ ጣዖት ቤት ትገባላችሁ?" ቢሏቸው "እኛ ምን እናድርግ! የምንጸልይበት እንደሆን የለን" ሲሉ መለሱላቸው::

ነገሩ ሲያያዝ ከደጋጉ ሐዋርያት ጳውሎስና በርናባስ ደረሰ:: ወዲያውኑ አንዳንድ ወንድሞች "ለምን አናንጽም" ብለው ነበር:: ቅዱስ ጳውሎስ ግን "ሊቀ ሐዋርያቱ ሳይፈቅድ አይሆንም" አለ:: (ለዚሕ ነው ዛሬም ሊቀ ጳጳስ ካልፈቀደ ቤተ ክርስቲያን የማይታነጸው::)

ከዚያ ቅዱሳን ጳውሎስና በርናባስ ሐዋርያቱ ወዳሉበት ሔደው ነገሩን ለቅዱስ ጴጥሮስ አስረዱ:: ሊቀ ሐዋርያቱም "የጌታችን ፈቃዱ መሆኑን እናውቅ ዘንድ ተያይዘን ሱባዔ እንግባ" ብሎ አዋጅ ነገረ::

በዓለም ያሉ ክርስቲያኖች ሁሉ በአንድ ልብ ሱባዔ ገቡ:: በሱባዔአቸው መጨረሻም ክብር ይግባውና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በግርማ ወደ እነርሱ ወረደ::

ሁሉንም ሐዋርያት በደመና ጭኖ ፊልጵስዩስ አደረሳቸው:: ከከተማ ወጣ ብሎ ባለ መሬት ላይም "ቤተ ክርስቲያንን በእናቴ ስም አንጹ" ብሎ አዘዛቸው:: ለቅዱስ ጴጥሮስም ሦስት ዓለቶችን ሰጠው::

እነዚያን መሬት ላይ ተክሎ : ጌታችን ቆሞለት : ሐዋርያቱ እየተራዱት : ግርምት የምትሆን ሦስት ክፍል ያላትን የመጀመሪያዋን ቤተ ክርስቲያን በ52 ዓ/ም በዚህች ቀን አንጿል::

¤ቤተ ክርስቲያኗን ነገ ጌታችን ቀደሳት የምንል ነንና ይቆየን::

††† አምላካችን የድንግል እናቱን ፍቅር : የተቀደሰች ቤቱን ጸጋ : የቡሩካን ሐዋርያቱን በረከት ያሳድርብን::

††† ሰኔ 20 ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት
1.እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም
2.ቅድስት ቤተ ክርስቲያን
3.ቅዱሳን ሐዋርያት
4.ቅዱስ ኤልሳዕ ነቢይ (ዕረፍቱ)

††† ወርኀዊ በዓላት
1.ቅዱስ ቴዎድሮስ ሊቀ ሠራዊት (ሰማዕት)
2.ቅዱስ ዮሐንስ ሐፂር
3.ቅዱስ አክሎግ ቀሲስ
4.ቅዱስ አፄ ካሌብ ጻድቅ (ንጉሠ ኢትዮጵያ)
5.አባ አሞንዮስ ዘሃገረ ቶና
6.ቅድስት ሳድዥ የዋሒት

††† "በድካም: አብዝቼ በመገረፍ: አብዝቼ በመታሠር: አትርፌ በመሞት ብዙ ጊዜ ሆንሁ:: በድካምና በጥረት: ብዙ ጊዜም እንቅልፍ በማጣት: በራብና በጥም: ብዙ ጊዜም በመጦም: በብርድና በራቁትነት ነበርሁ . . . የቀረውን ነገር ሳልቆጥር ዕለት ዕለት የሚከብድብኝ የአብያተ ክርስቲያናት ሁሉ አሳብ ነው::" †††
(፪ቆሮ. ፲፩፥፳፫-፳፰)

††† ወስብሐት ለእግዚአብሔር †††


""ፍቅር ያጌብረኒ ከመ እንግር ዜናሆሙ ለቅዱሳን""::/የቅዱሳንን ዜና(ታሪክ) እንድመሰክር ፍቅር ያስገድደኛል::  አባ ጊዮርጊስ ዘጋስጫ /መጽሐፈ ምሥጢር/

✟...ገድለ ቅዱስን...✟

25 Jun, 06:19


††† እንኳን ለጻድቅ ሊቀ ጳጳሳት አባ ድምያኖስ ዓመታዊ የዕረፍት በዓል በሰላም አደረሳችሁ፣ አደረሰን። †††

††† በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን! †††

††† አባ ድምያኖስ †††

††† አባ ድምያኖስ ተወልደው ያደጉት ግብጽ ውስጥ ነው:: ቤተሰቦቻቸው ክርስቲያኖች በመሆናቸው ገና በልጅነት ዕድሜአቸው ቅዱሳት መጻሕፍትንና በጐ ምግባራትን ተምረዋል:: ዕድሜአቸው ወደ ወጣትነቱ ሲጠጋ ሥርዓተ መነኮሳትን ለማጥናት ወደ ገዳመ አባ ዮሐንስ ሔዱ:: በዘመኑ ማንኛውም ሰው ተገቢውን ፈተና ሳያልፍ እንዲመነኩስ አይፈቀድለትም ነበር::

አንድ ሰው ሊመነኩስ ካሰበ በትክክል መናኝ መሆኑ ቢያንስ ለሦስት ቢበዛ ደግሞ ለአሥራ ሁለት ዓመታት እንዲፈተን ቅድስት ቤተ ክርስቲያን ታዝዛለች:: ይኸውም "ሥርዓተ አመክሮ" ይባላል:: ከአሥራ ሁለት ዓመታት በላይ መቆየት ከፈለገ ግን ይፈቀድለታል::

በዚህም መሠረት አባ ድምያኖስ ለአሥራ ሰባት ዓመታት በአጭር ታጥቀው ገዳሙን አገልግለዋል:: ገዳሙም ይገባሃል በሚል ዲቁና እንዲሾሙ አድርጓል:: ከዚህ በኋላ ከአባቶች ተባርከው: ገዳሙንም ተሰናብተው ወጡ:: ነገር ግን የወጡት ወደ ዓለም ሳይሆን ራቅ ወዳለ ገዳም ነው::

የረድዕነት ዘመናቸውን ጨርሰዋልና አዲስ በሔዱበት ገዳም ወደ መደበኛው ገድል ተሸጋገሩ:: ያም ማለት በጾም: በጸሎት: በስግደት: በትሕርምት: በትሕትናና በፍቅር ሙሉ ጊዜአቸውን ማሳለፍ ጀመሩ:: በእንዲሕ ያለ ግብርም ዘመናት አለፉ::

የወቅቱ የግብጽ ፓትርያርክ አባ ጴጥሮስ በእረኝነት ሥራ የሚያግዛቸው ሰው እንዲፈለግላቸው በጠየቁት መሠረት ትምሕርትም: ጽሕፈትም: በጐ ምግባራትም የተሟላለት ሰው እንደ አባ ድምያኖስ አልተገኘምና ያለፈቃዳቸው ወደ እስክንድርያ ተወስደው የፓትርያርኩ ረዳት ሆነው ተሾሙ:: በረዳትነት በቆዩበት ጊዜ በወንጌል አገልግሎትና በመንኖ ጥሪት ሕዝቡንና ሊቀ ጳጳሳቱን አስደስተዋል::

ልክ አባ ጴጥሮስ ሲያርፉ ሕዝቡና ሊቃውንቱ በአንድ ድምጽ አባ ድምያኖስን ለፓትርያርክነት መርጧቸዋል::

ጻድቁ ሊቀ ጳጳሳት በዘመነ ፕትርክናቸው ከግል የቅድስና ሕይወታቸው ባለፈ እነዚህን ፈተናዎች በመወጣታቸው ይመሰገናሉ::
1.ሕዝቡ ከሃይማኖታቸው እንዳይወጡና በምግባር እንዳይዝሉ ተግተው አስተምረዋል::

2.በአካል ያልደረሱባቸውን በጦማር (በመልዕክት) አስተምረዋል::

3.በዘመናቸው የተነሱትን መናፍቃን ተከራክረው : የተመለሰውን ተቀብለው : እንቢ ያሉትን አውግዘዋል::

4.ከአንጾኪያ ፓትርያርክ የመጣውን የኑፋቄ ጦማር (መልዕክት) በይፋ ተቃውመው አውግዘዋል::

ለአርባ ሦስት ዓመታት የእስክንድርያ ሊቀ ጳጳሳት ሆነው ያገለገሉት አባ ድምያኖስ ከብዙ ትጋት በኋላ በመልካም ሽምግልና በዚህች ቀን ዐርፈዋል:: ከግብጽ አበው ሊቃነ ጳጳሳት ዝርዝር ውስጥም አርባ አምስተኛ ሆነው ተመዝግበዋል::

††† ልመናቸው : ክብራቸው : ጸጋ ረድኤታቸው አይለየን::

††† ሰኔ 18 ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት
1.አባ ድምያኖስ ጻድቅ ሊቀ ጳጳሳት
2.ቅዱስ ኤስድሮስ ሰማዕት

††† ወርኀዊ በዓላት
1.ቅዱስ ፊልጶስ ሐዋርያ
2.አቡነ ኤዎስጣቴዎስ ሰባኬ ሃይማኖት (ረባን)
3.አቡነ አኖሬዎስ ዘደብረ ጽጋጋ
4.ማር ያዕቆብ ግብጻዊ

††† "ስለዚህ በገዛ ደሙ የዋጃትን የእግዚአብሔርን ቤተ ክርስቲያንን ትጠብቁአት ዘንድ መንፈስ ቅዱስ እናንተን ጳጳሳት አድርጎ ለሾመባት : ለመንጋው ሁሉና ለራሳችሁ ተጠንቀቁ:: ከሄድሁ በኋላ ለመንጋው የማይራሩ ጨካኞች ተኩላዎች እንዲገቡባችሁ እኔ አውቃለሁ:: ስለዚህ ሦስት ዓመት ሌሊትና ቀን በእንባ እያንዳንዳችሁን ከመገሰጽ እንዳላቋረጥሁ እያሰባችሁ ትጉ::" †††
(ሐዋ. ፳፥፳፰)

††† ወስብሐት ለእግዚአብሔር †††

✟...ገድለ ቅዱስን...✟

24 Jun, 07:13


✞✞✞ በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ
አምላክ ፡፡ አሜን ፡፡ ✞✞✞

❖ እንኳን አደረሳችሁ ❖

❖ ሰኔ 17 ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት

❇️አባ_ገሪማ (ይስሐቅ) መደራ❇️

=>አቡነ ገሪማ የተወለዱት በ5ኛው መቶ ክ/ዘመን ሮም
ውስጥ ነው:: ወላጆቻቸው መስፍንያኖስና ሰፍንግያ
እግዚአብሔርን የሚወዱ የሮም ከተማ ንጉሥና ንግሥት
ነበሩ:: ልጅ በማጣታቸው እመቤታችንን ለመኑ፡፡

+እመ ብርሃንም ደግ ፍሬ ሰጠቻቸው:: ስሙን ይስሐቅ
ብለው አሳደጉት:: ገና በልጅነቱ አባቱ ድንገት በመሞቱ
ይስሐቅ በዙፋኑ ተተክቶ ነገሠ:: ለ7 ዓመታት ሕዝቡን
በፍትሕ
እያስተዳደረ: መጻሕፍትንም እያጠና ኑሯል::

+አንድ ቀን ግን ከግብፅ በርሃ የተላከ ደብዳቤ ደረሰው::
ላኪው አባ_ዸንጠሌዎን ሲሆኑ መልዕክቱ "ምድራዊ
ንግሥና ምን ያደርግልሃል?
ይልቁኑስ በሰማይ ለዘለዓለም እንድትነግሥ ወደ በርሃ ና"
የሚል ነበር::

+ንጉሥ ይስሐቅ አላመነታም ሌሊት ተነስቶ ወደ ፈጣሪው
ጸልዮ በለበሳት ልብስ ብቻ ዙፋኑን ጥሎ መነነ:: ድንገት
ግን ቅዱስ_ገብርኤል ደርሶ በቀኝ ክንፉ ነጥቆ ግብፅ አባ
ዸንጠሌዎን በዓት ላይ አኖረው::

+እርሳቸውም ተቀብለው ፍኖተ አበውን አስተምረው
አመነኮሱትና ዘጠኝ ሁነው ወደ ኢትዮዽያ
መጡ:: ተስዓቱ ቅዱሳን በሃገራችን ብዙ ሲሰሩ አንዱና
ታላቁ አባ ይስሐቅ (ገሪማ) ናቸው:: ሰውነታቸውን በገድል
ቀጥቅጠውት ቆዳና አጥንታቸው ተጣብቆ ነበር::

+አንድ ቀን አባ ይስሐቅ በልቶ ቀደሰ ብለው ነግረዋቸው
አባ ዸንጠሌዎን አዘኑ:: ልምከር ብለው "ልጄ ይስሐቅ
የሰማውብህ ነገር አለና ሰዎችን አርቅልኝ" አሉ:: አባ ይስሐቅ ግን
"ሰዎች ብቻ አይደሉም: ዛፉም እንጨቱም ገለል ይበል"
ቢሉ የቤተ ክርስቲያኑ አጸድ አንድ ምዕራፍ (800 ሜትር)
ተጠራርጎ ሸሸ::

+ይሕንን የተመለከቱት አባ ዸንጠሌዎን
"ወልድየ_ይስሐቅ_ገረምከኒ (ልጄ ይስሐቅ ገረምከኝ)
አሏቸው:: ከዚያ ጊዜ ጀምሮም
"አቡነ_ገሪማ" ተብለው ቀሩ፡፡

+አቡነ ገሪማ ወደ መደራ ሲሔዱ እነዚያ የሸሹ ዛፍና
ድንጋዮች "ገሪማ ለእኛም
ግሩም ነህ" እያሉ በዝማሬ ተከትለዋቸዋል::

+ጻድቁ ወንጌልን: ገዳማትን ከማስፋፋት ባለፈ ብዙ
ተአምራትን ሰርተዋል:-

1.ስንዴ ጠዋት ዘርተውት በ9 ሰዓት ያፈራ ነበር "በጽባሕ
ይዘርዕ: ወበሠርክ የአርር" እንዲል::
2.ጧት የተከሉት ወይን በ9 ሰዓት ያፈራ ነበር::
3.አንድ ቀን ምራቃቸው ቢወድቅ ጸበል ሆኖ ዛሬም አለ::
4.ብዕራቸው ወድቃ አብባ አፍርታለች::
5.አንድ ቀን ድርሳን እየደረሱ ሊመሽ በመሆኑ ፀሐይን
አቁመዋታል::

+ከእነዚህ ሁሉ ዘመናት በኋላ ጌታችን
ተገልጦ በማይዋሽ ንጹሕ አንደበቱ ቃል ኪዳን ሰጣቸው::
"ስምሕን የጠራ: መታሰቢያህን ያደረገ: እስከ 12 ትውልድ
እምርልሃለሁ:: አንተ ግን ሞትን አትቀምስም" ብሏቸው
ተሰወረ:: ያን ጊዜ መላእክቱ በሠረገላ ጭነው እየዘመሩ
ብሔረ_ሕያዋን አድርሰዋቸዋል፡፡

✞ አባ ለትጹን የዋህ ✞

=>ስመ ጥሩ ጻድቅ አባ ለትጹን በ4ኛው መቶ ክ/ዘመን
በግብጽ የተወለዱ:
¤በፍጹም ተግሣጽ ያደጉ:
¤ከልጅነታቸው ጀምሮ ራሳቸውን በሕገ ወንጌል የመሩ:
¤አንድ ቀን በሰሟት የወንጌል ቃል የመነኑ:
¤ገዳም ገብተው በትሕትና ለዘመናት ያገለገሉ:
¤በመጨረሻም ወደ ትልቅ ተራራ ወጥተው ተጋድሏቸውን
የፈጸሙ ታላቅ አባት ናቸው::

+ከየዋሕነታቸው የተነሳ ኃጢአተኛ ሰው ሲያገኙ ራሳቸው
ንስሃ ይገቡ ነበር:: አንዴ ግን እናቱን 10 ጊዜ በዝሙት
ያረከሰ: ስትጸንስም መርዝ አጠጥቶ ጽንሱን በማሕጸኗ
የገደለና በሥጋ ወደሙ ላይ የተዘባበተ ሰው ሊሞት ሲል
ደረሱ::

+አጋንንት ሲዖል ታች ሲጥሉትም ተመለከቱ:: ኃጢአቱ
ጭንቅ ቢሆንም የእርሱን ንስሃ ሊቀበሉ ጀመሩ: ከንስሃቸው
ጽናት
የተነሳ ሞቱ:: ጌታችን ከሞት አስነስቶ "አትለምነኝ:
አልምረውም" አላቸው::

+ጻድቁ ተስፋ አልቆረጡምና ቀጠሉ:: ለ2ኛ ጊዜ ሞቱ::
አሁንም ቀጠሉ: 3ኛ: 4ኛ: 5ኛ ጊዜም ሞቱ:: በ6ኛው ግን
መፍትሔ መጣ:: ጌታችን አእላፍ መላእክትን አስከትሎ:
ያችንም ኃጥእ ነፍስ ይዞ መጣ:: "ፍርዴ አይታጠፍምና
ወደ ገነት
አላስገባትም:: ስለ አንተ ጽድቅና የዋሕነት ደግሞ ሲዖል
አልጥላትም:: ስለዚሕም እንዳልተፈጠረች ትሁን" ብሎ
እፍ
አለባት:: ፈጥና ወደ ትቢያነት ተቀየረች::

+ጻድቁም የፈጣሪያቸውን ቸርነት አድንቀው ሰገዱ:: ከብዙ
ዘመናት ተጋድሎ በኋላም በዚህች ቀን ዐረፉ::

✞ አባ_ዸላሞን_ፈላሲ ✞

=>ቤተ ክርስቲያን ካፈራቻቸው ታላላቅ ገዳማውያን አንዱ
አባ ዸላሞን የአባ ለትጹን ወዳጅ ነበር:: ይሕ ቅዱስ
ከአጋንንት
ጋር በገጠመው ጦርነት ምክንያት ለየት ይላል:: ከ60
ዓመታት በላይ እንኳን ሳቅና ደስታ ቀና ብሎም ሰው
አላየም::

+በነዚሁ ዘመናት ሁሉ ቅንድቡ እስኪላጥ አልቅሷል::
በዓለም ያሉ አጋንንት ሁሉ ተሰብስበው አሰቃይተውታል::
እርሱ ግን
በእግዚአብሔር ቸርነት: በወዳጁ በአባ ለትጹን ጸሎትና
በትጋት አሸንፏቸው ዛሬ ዐርፏል::

=>ቸሩ አምላካችን ከታላላቁ ቅዱሳን ጸጋ በረከት
ይክፈለን:: በምልጃቸውም ይቅር ይበለን::

=>ሰኔ 17 ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት=
1.ብጹዕ አባ ገሪማ (ይስሐቅ) ዘመደራ
2.አባ ለትጹን ዐቢይ ወየዋሕ
3.አባ ዸላሞን ፈላሲ
4.ቅድስት አርሴማ ጻድቅት
5.ሰማዕታት እለ አኮራን
6፡ ፯፼ ፹፻ ሰማዕታት ማኅበረ ቅዱስ ተክለሃ ይማኖት

❖ወርኃዊ በዓላት
1፡ ቅዱስ እስጢፋኖስ ቀዳሜ ሰማዕት
2፡ ቅዱስ ኤጲፋንዮስ ዘቆጵሮስ
3፡ ቅዱሳን መክሲሞስ ወደማቴዎስ
4፡ ቅዱስ ያዕቆብ ሐዋርያ

=>+"+ እግዚአብሔር ፍርድን ይወድዳልና::ቅዱሳኑንም
አይጥላቸውምና::
ለዘለዓለምም ይጠብቃቸዋል. . . ጻድቃን ምድርን
ይወርሳሉ::
በእርስዋም ለዘላለም ይኖራሉ::የጻድቅ አፍ ጥበብን
ያስተምራል::
አንደበቱም ፍርድን ይናገራል::የአምላኩ ሕግ በልቡ
ውስጥ ነው::
በእርምጃውም አይሰናከልም:: +"+ (መዝ. 36:28-31)

<<< ወስብሐት ለእግዚአብሔር >>>

✟...ገድለ ቅዱስን...✟

22 Jun, 10:18


✞✞✞ በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ
አምላክ ፡፡ አሜን ፡፡ ✞✞✞

እንኳን አደረሳችሁ ❖

✞ ✞ እንኩዋን ለሰማዕቱ #ቅዱስ_ሚናስ ዓመታዊ
የቅዳሴ ቤት በዓል በሰላም አደረሳችሁ ✞ ✞

+"+ #ቅዱስ_ሚናስ ምዕመን ሰማዕት +"+

=>ቅዱስ ሚናስ ( #ማር_ሚና ) በምድረ ግብጽ ተወዳጅ
ከሆኑ ሰማዕታት ዋነኛው ነው:: ልክ በሃገራችን
#ቅዱስ_ጊዮርጊስ ልዩ ቦታ እንዳለው ሁሉ ግብፃውያን
ማር ሚናስን ጠርተው አይጠግቡትም::

+ምክንያቱም ከታላላቅ ሰማዕታት አንዱ በመሆኑና ዛሬም
ድረስ ለጆሮና ለዐይን ድንቅ የሆኑ ተአምራትን ስለሚሠራ
ነው:: በተለይ ለታመመ: ለደከመና ለተጨነቀ ፈጥኖ
ደራሽ: ባለ በጐ መድኃኒት ፈዋሽና አማላጅ ነው::

+ግብጽ ውስጥ ቅዱሱን የማያውቅ ሰው ካገኛችሁ እርሱ
ኦርርቶዶክሳዊ አይደለም ማለት ነው ሲባልም ሰምተናል::
በነገራችን ላይ ለቅዱሳን ተገቢውን ክብር በመስጠት:
ታሪካቸውን በመጻፍ: በማጥናት: በመጽሔት: በፊልምና
በመሳሰሉት ለሕዝብ በማስተዋወቅ ግብጻውያኑ ከእኛ ብዙ
ርቀት ሒደዋል:: ዛሬ እንኩዋ የምንጠቀምበትን ስንክሳር
80 ከመቶ እጁን ያዘጋጁት እነርሱ ናቸው::

+አባቶቻችንና እናቶቻችን #ኢትዮዽያውያን_ቅዱሳን ግን
አብዛኞቹ ተረስተው ቀርተዋል:: መጽሐፈ ገድላቸውንም
ብል በልቶታል:: ዛሬም የቤት ሥራው የእኛ ብቻ ነው::

+ወደ ቀደመ ነገራችን እንመለስና ቅዱስ ሚናስ (ትርጉሙ
ታማኝና ቡሩክ ማለት ነው):-
¤በ3ኛው መቶ ክ/ዘመን የነበረ የደጋግ ክርስቲያኖች ልጅ
¤በልጅነቱ የቅድስና ሕይወትን ያጣጣመ
¤በዘመኑ ሰው እጅግ ተወዳጅ የነበረ
¤ሃብትን: ክብርን: ሥልጣንን ንቆ በጾምና በጸሎት የተወሰነ
¤በመጨረሻም በክርስቶስ ስላመነ አላውያን የገደሉት
ሰማዕት ነው::

+እርሱ ሰማዕት ከሆነ ከበርካታ ዘመናት በሁዋላ
ምዕመናን ክቡር አካሉን ፈልገው ያጡታል::

+የሚገለጥበት ጊዜ ሲደርስ ግን እርሱ የተቀበረበት
ምድረ በዳ የበጐችና የእረኞች መዋያ ነበርና ተአምራትን
አደረገ:: አንድ እረኛ በጐቹ ድውያን ሆኑበት:: በዚያ ሰሞን
ከቅዱሱ መቃብር ላይ ጸበል ፈልቆ ነበርና እረኛው ተርታ
ውሃ ነው ብሎ በጎቹን ሲያጠጣቸው አንዱ ድውይ በግ
ወደ ጸበሉ በመዘፈቁ ዳነ::

+በዚህ የተገረመው እረኛ ሁሉንም የታመሙ በጐቹን
አምጥቶ ነከራቸው:: እነርሱም ተፈወሱ:: ይህ ዜና
በምድረ ግብፅ ሲሰማ ድውያን ሁሉ እየመጡ ይፈወሱ
ገቡ:: ግን እነሱም ሆነ እረኛው ምክንያቱን ማወቅ
አልቻሉም::

+ነገሩ በሮም ንጉሥ ዘንድ ሲሰማ ሴት ልጁን ከሠራዊቱ
ጋር ላካት:: ምክንያቱም እርሷ ከብዙ ዘመን ጀምራ
መጻጉዕ ነበረችና ፈውስን አጥታ ነበር:: መጥታ
ተጠመቀች: ፈጥናም ተፈወሰች:: እርሷ ግን እንደ ሌሎች
ያዳናትን ማንነት ሳታውቅ መሔድ አልፈለገችምና ሱባዔ ገባች::

+#ቅዱስ_ሚናስ በሌሊት ራዕይ መጥቶ ሥጋው እንዳለ
ነገራት:: እርሷም መሬቱን አስቆፍራ የቅዱሱን አካል
በክብር አስወጣች:: ከዚያም በንጉሡ ትዕዛዝ ምድረ
በዳው ከተማ እንዲሆን ተቀየረ:: ስሙም " #መርዩጥ "
ተባለ:: ጸበሉ የነበረበት ቦታም ላይ የማር ሚናስ
#ቤተ_ክርስቲያን ታንጾበት በዚህች ዕለት ቅዳሴ ቤቱ
ተከብሯል::

=>አምላካችን ከቅዱሱ ሰማዕት በረከትን ይክፈለን::

=>ሰኔ 15 ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት=
1.ቅዱስ ሚናስ (ማር ሚና) ሰማዕት (ቅዳሴ ቤቱ)

=>ወርሐዊ በዓላት
1.ቅዱስ ቂርቆስና እናቱ ኢየሉጣ
2.ቅዱስ ኤፍሬም ሶርያዊ (አፈ በረከት)
3.ቅድስት እንባ መሪና
4.ቅድስት ክርስጢና

=>+"+ ፈጥኜ ወደ አንተ እንድመጣ ተስፋ አድርጌ ይሕን
እጽፍልሃለሁ:: ብዘገይ ግን በእግዚአብሔር ማደሪያ ቤት
መኖር እንዴት እንደሚገባ ታውቅ ዘንድ እጽፍልሃለሁ::
ቤቱም የእውነት ዓምድና መሠረት የሕያው እግዚአብሔር
ቤተ ክርስቲያን ነው:: እግዚአብሔርንም የመምሠል
ምሥጢር ያለ ጥርጥር ታላቅ ነው:: +"+ (1ጢሞ.
3:14)

<<< ወስብሐት ለእግዚአብሔር >>>

✟...ገድለ ቅዱስን...✟

21 Jun, 12:21


✞✞✞ በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ
አምላክ ፡፡ አሜን ፡፡ ✞✞✞

✞ ✞ እንኩዋን ለአራቱ ቅዱሳን አበው ሰማዕታት
ዓመታዊ የዕረፍት በዓል በሰላም አደረሳችሁ ✞ ✞

=> #4ቱ_ቅዱሳን አበው የዘመነ ሰማዕታት ፍሬዎች ሲሆኑ
ስማቸው #አባ_አክራ : #አባ_ዮሐንስ : #አባ_አብጥልማ
እና #አባ_ፊልዾስ ይባላሉ:: ከመከራ ዘመን በፊት
(ማለትም በቀደመ ሕይወታቸው) ካህናትና ሃብታሞች
ነበሩ:: ሀብቱ ግን በሥራ ብቻ የተገኘ ነው::

+ታዲያ ቅዱሳኑ በያሉበት ሆነው በሀብታቸው እንግዳ
እየተቀበሉ: ድሆችን እያበሉ: በክህነታቸው ደግሞ
እያስተማሩና እየናዘዙ ትጉሃን ስለ ነበሩ በሰውም ሆነ
በእግዚአብሔር ዘንድ ሞገስ ነበራቸው:: በእንዲህ ያለ
ግብር ሳሉ ዘመነ ሰማዕታት አሐዱ አለ:: "ክርስቶስን ካዱ:
ለጣዖት ስገዱ" እያሉ መኩዋንንቱና ነገሥታቱ ሕዝበ
ክርስቲያኑን ያሰቃዩ ገቡ::

+በዚህ ጊዜ 4ቱ ቅዱሳን አንድ ነገር መከሩ:: በየእሥር
ቤቱ የተጣሉ ክርስቲያኖችን ለማገልገል ቆረጡ:: እግረ
መንገዳቸውን እያስተማሩ እሥረኞችን ያጽናኑ ገቡ::
የራበውን ያበላሉ: የተሰበረውን ይጠግናሉ: በቁስሉም ላይ
መድኃኒትን ያደርጉ ነበር:: የመከራው ዘመን ግን እየረዘመ:
ግፉም ከልክ እያለፈ መጣ::

+በዚህ ጊዜ 4ቱ ቅዱሳን ትልቁንና የመጨረሻውን ውሳኔ
አስተላለፉ:: ከሰማዕታት ወገን ይቆጠሩ ዘንድ
መርጠዋልና: ክርስቶስን በሞቱ ይመስሉት ዘንድ ሽተዋልና:
የሩጫቸው መጨረሻ ሰማዕትነት እንዲሆን መረጡ::

+አራቱም ያላቸውን ንብረት ሁሉ ሰብስበው ለነዳያን
አካፈሉ:: በትከሻቸው ካለች አጽፍ በቀር ስባሪ ገንዘብ
ከሃብታቸው አላስቀሩም:: ከዚያ ጉዞ ወደ ምስክርነት
አደባባይ (ዐውደ ስምዕ) አደረጉ::

+በዙፋኑ የተቀመጠው የመኮንኑ ግርማ: መሬት ላይ
የፈሰሰው የወገኖቻቸው ደም: የሠራዊቱ ድንፋታ ቅዱሳኑን
አላስፈራቸውም:: በይፋ "ክርስቲያን ነን" ሲሉ ተናገሩ::
በዘመኑ እንዲሕ ብሎ መናገር አንገት የሚያስቆርጥ ትልቅ
ድፍረት ነበር::

+መኮንኑም ከበጐ ሃይማኖታቸው ይለያቸው ዘንድ በእሳት
አቃጠላቸው:: እግዚአብሔር አዳናቸው:: በቀስትም:
በስለትም: በብረትም ለቀናት አሰቃያቸው:: ቅዱሳኑ ግን
አምላካቸውን አምነው ሁሉን በአኮቴት ተቀበሉ::
በመጨረሻ ግን በዚሕች ዕለት የሞት ፍርድ ተፈርዶባቸው
ተገድለዋል:: ስለ ምጽዋታቸው: በጎ አገልግሎታቸውና
ሰማዕትነታቸው ጻድቅ: ፈራጅ ከሆነ ፈጣሪ አክሊልን
ተቀብለዋል::

=>የበረከት አምላክ ከወዳጆቹ ጸጋ ክብርን ያድለን::

=>ሰኔ 14 ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት=
1.ቅዱሳን አበው ሰማዕታት (አባ አክራ: አባ ዮሐንስ: አባ
አብጥልማ: አባ ፊልዾስ)

=>ወርሐዊ በዓላት
1.አቡነ አረጋዊ (ዘሚካኤል)
2.ቅዱስ ገብረ ክርስቶስ መርዓዊ
3.ቅዱስ ፊልዾስ ሐዋርያ
4.ቅዱስ ሙሴ (የእግዚአብሔር ሰው)
5.አባ ስምዖን ገዳማዊ
6.አባ ዮሐንስ ጻድቅ
7.እናታችን ቅድስት ነሣሒት

=>+"+ እግዚአብሔር ቅዱሳንን ስላገለገላችሁ: እስከ
አሁንም ስለምታገለግሏቸው ያደረጋችሁትን ሥራ:
ለስሙም ያሳያችሁትን ፍቅር ይረሳ ዘንድ ዓመጸኛ
አይደለምና:: በእምነትና በትእግስትም የተስፋውን ቃል
የሚወርሱትን እንድትመስሉ እንጂ ዳተኞች እንዳትሆኑ
ተስፋ እስኪሞላ ድረስ እያንዳንዳችሁ ያን ትጋት እስከ
መጨረሻ እንድታሳዩ እንመኛለን::+"+ (ዕብ. 6:10-13)

<<< ወስብሐት ለእግዚአብሔር >>>

✟...ገድለ ቅዱስን...✟

19 Jun, 06:29


††† 🌹እንኳን ለሊቀ መላእክት ቅዱስ ሚካኤል እና ለቅዱሳኑ ዓመታዊ በዓል በሰላም አደረሳችሁ፣አደረሰን። †††

††† በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን! †††

††† በዚህች ቀን ሊቀ መላእክት ቅዱስ ሚካኤልን ጨምሮ ቅዱስ ላሊበላ: ቅድስት አፎምያና ቅዱስ ባሕራን ቀሲስ ይከበራሉ::

††† ቅዱስ ሚካኤል ሊቀ መላእክት †††

††† ቅዱስ ሚካኤል በጥንተ ተፈጥሮ በኢዮር: ኃይላት በተባሉት ነገደ መላእክት ተሹሞ ነበር:: ሳጥናኤል በካደ ጊዜ እግዚአብሔር ባወቀ: አንድም በትሕትናውና ደግነቱ በ99ኙ ነገደ መላእክት ላይ ሁሉ ተሹሟል::

ከፍጥረት ወገን ከእመቤታችን ቀጥሎ የቅዱስ ሚካኤልን ያሕል ክብርና ርሕሩሕ የለም:: በምልጃውም: በረዳትነቱም የታወቀ መልአክ ነው:: መጽሐፍ "መልአከ ምክሩ ለእግዚአብሔር" ይለዋል:: "ወስሙ መስተሣሕልም" ይለዋል:: ቂም የሌለው: ለምሕረት የሚፋጠን: ደግ መልአክ ነውና::

በብሉይ ኪዳን በመከራ ለነበሩ ቅዱሳን ሁሉ ሞገስ: ረዳትና አዳኝ ቢሆናቸው "መጋቤ ብሉይ" ተሰኝቷል:: እሥራኤልን 40 ዘመን በበርሃ መርቷል: መግቧልም:: ቅዱስ መጽሐፍ ስለ እርሱ ብዙ ይላል:: (ዘፍ. 48:16, ኢያ. 5:13, መሳ. 13:17, ዳን. 10:21, 12:1, መዝ. 33:7, ራዕይ. 12:7)

ደስ የሚለው ደግሞ ርሕሩሑ መልአክ ከእመቤታችን ጋር ልዩ ፍቅር አለው:: ከእናቷ ማሕጸን ጀምሮ እስከ ዛሬ እነሆ አብሯት አለ:: ደስ ብሎት ይታዘዛታል:: ማማለድ ሲፈልግም "እመቤቴ ሆይ! ቅደሚ" ይላታል:: ወደ እሳት መጋረጃ አብረው ገብተው ለዓለም ምሕረትን: በረከትን ያወርዳሉ::

ቅዱስ ሚካኤልን በዚሕች ዕለት ስለ እነዚህ ነገሮች እናከብረዋለን:-
1.በመላእክት ሁሉ ላይ አለቃ ሆኖ መሾሙን
2.ቅዳሴ ቤቱን (ግብፅ ውስጥ)
3.ቅድስት አፎምያን መርዳቱን
4.ቅዱስ ባሕራንን መጎብኘቱን
5.ቅዱስ ላሊበላን ወደ ሰማያት ማሳረጉን
6.ለፍጥረታት ሁሉ ምሕረት የሚጠይቅበት ዕለት ነውና::

††† ሊቀ መላእክት በክንፈ ረድኤቱ ከክፉ ሁሉ ይጠብቀን::

††† ቅዱስ ላል ይበላ ንጉሥ †††

††† በ12ኛው መቶ ክ/ዘመን መጨረሻ ላይ በሃገራችን የነገሠው ቅዱስ ላሊበላ:-
¤በብሥራተ መልአክ ተወልዷል
¤ቅዱሳት መጻሕፍትን ገና በልጅነቱ አጥንቷል
¤የንጉሥ ዘር ቢሆንም በጾምና ጸሎት: በትሕርምት አድጓል
¤በወንድሙ ቢገረፍም ቂም አልነበረውም
¤ስለ ወዳጆቹ ፍቅር መርዝ ጠጥቷል
¤በዙፋን ላይ የኢትዮዽያ ንጉሥ ሆኖ ቢቀመጥም እርሱስ አኗኗሩ ገዳማዊ ነበር
¤ከተባረከች ሚስቱ ቅድስት መስቀል ክብራ ጋር አንዲት ማዕድ ብቻ በቀን ይቀምሱ ነበር:: ለዛውም ለምለሙን ለነዳያን ሰጥተው እነርሱ የሚበሉት የእንጀራውን ቅርፍት (ጠርዝ) ብቻ ነበር::

በአካለ ሥጋ ወደ ሰማያት ተነጥቆ ብዙ ምሥጢራትን አይቷል
¤በምሳሌውም ሃገረ ሮሃን (ላስታን) ገንብቷል
¤ዛሬም ድረስ ምስጢር የሆኑት ፍልፍል አብያተ መቃድስ የእጆቹ ሥራዎች ናቸው::

ሥራውን ከፈጸመ በኋላ መንግሥቱን ለቅዱስ ነአኩቶ ለአብ አውርሶ: በመንኖ ጥሪትና በቅድስና ኑሮ በዚሕች ቀን አርፏል:: ጌታችን ስምህን ያከበረ: ዝክርህን የዘከረ: ከቤትህ ያደረውን: ከርስተ መንግስተ ሰማያት አካፍለዋለሁ ሲል ቃል ኪዳን ገብቶለታል::

††† በረከቱን: ክብሩን ያድለን::

††† ቅድስት አፎምያ †††
ከቅዱስ አስተራኒቆስ ጋር በተቀደሰ ትዳር የኖረች
¤ምጽዋትን ያዘወተረች
¤በፍቅረ ቅዱሳን የጸናች
¤ንጽሕናዋን ጠብቃ ሰይጣንን ያሳፈረች ደግ እናት ናት:: ዛሬ የቅዱስ ሚካኤልን ስዕል ታቅፋ: በትእምርተ መስቀልም አማትባ አርፋለች: ቅዱሱ መልአክም ወደ ገነት አሳርጓታል::

††† ቅዱስ ባሕራን ቀሲስ †††

የደጋግ ክርስቲያኖች ግን የድሆች ልጅ:
¤በሕጻንነቱ በግፍ ወደ ባሕር የተጣለ:
¤በእግዚአብሔር ጥበብ አድጎ የግፈኛውን ንብረት የወረሰ:
¤በመልካም ትዳር በቅስና ያገለገለ:
¤ምጽዋትን ያዘወተረ: አብያተ ክርስቲያናትን ያሳነጸ ደግ ክርስቲያን ነው::
¤በዚህች ቀን አርፎ ቅዱስ ሚካኤል ወዳጁ በዕረፍተ ገነት አኑሮታል::

††† አምላካችን እግዚአብሔር ከቅዱሳኑ በረከት ይክፈለን:: አሜን:: †††

††† ሰኔ 12 ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት
1.ቅዱስ ሚካኤል ሊቀ መላእክት
2.ቅዱስ ላሊበላ ጻድቅ (ንጉሠ ኢትዮዽያ)
3.ቅድስት አፎምያና ባለቤቷ ቅዱስ አስተራኒቆስ
4.ቅዱስ ባሕራን ቀሲስ
5.ቅዱስ እለ እስክንድሮስ ሊቅ
6.አባ ዮስጦስ ሊቀ ዻዻሳት (የሐዋርያው ቅዱስ ማርቆስ ደቀ መዝሙር)
7.አባ ቄርሎስ ሊቀ ዻዻሳት

††† ወርሐዊ በዓላት
1.ቅዱስ ማቴዎስ ሐዋርያ
2.ቅዱስ ድሜጥሮስ
3.ቅዱስ ዮሐንስ አፈ ወርቅ
4.ቅዱስ ቴዎድሮስ ምሥራቃዊ (ሰማዕት)
5.ቅድስት ክርስቶስ ሠምራ
6.አቡነ ሳሙኤል ዘዋልድባ

††† "በሰማይም ሰልፍ ሆነ:: ሚካኤልና መላእክቱ ዘንዶውን ተዋጉ:: ዘንዶውም ከመላእክቱ ጋር ተዋጋ:: አልቻላቸውምም:: ከዚያም ወዲያ በሰማይ ሥፍራ አልተገኘላቸውም:: ዓለሙንም ሁሉ የሚያስተው ዲያብሎስና ሰይጣን የሚባለው ታላቁ ዘንዶ እርሱም የቀደመው እባብ ወደ ምድር ተጣለ::" †††
(ራዕይ. 12:7)

††† ወስብሐት ለእግዚአብሔር †††

✟...ገድለ ቅዱስን...✟

13 Jun, 07:30


እንኩዋን ለብርሀነ ዕርገቱ በሰላም አደረሳችሁ ።

"ዐርገ በስብሐት ውስተ ሰማያት ወነበረ በየማነ አቡሁ፣
በክብር በምስጋና ወደ ሰማይ ዐረገ በአባቱም ቀኝ ተቀመጠ"  ( ጸሎተ ሃይማኖት ) ።

እንደ ኢትዮጵያ ኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን አስተምህሮ መሰረት  በዐለ ዕርገት  ከጌታችን ከመድሃኒታችን ከኢየሱስ ክርስቶስ  ዘጠኙ በዐላት አንዱና ዋንኛው በዐል ነው።
በዓለ ዕርገት ጌታችን አምላካችንና መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ መቃብር ክፈቱልኝ መግነዝ ፍቱልኝ ሳይል  ከሙታን ከተነሣ በኋላ ለዐርባ ቀናት በግልጽም በስውርም ለቅዱሳን ሐዋርያትና ለቅዱሳት አንስት መጽሐፈ ኪዳንን ፣ ትርጓሜ መጻሕፍትን ፣ ምሥጢራትን ፣ ሕግጋትንና ቀኖናተ ቤተ ክርስቲያንን ሲያስተምር ቆይቶ ወደ ቀደመ ዙፋኑ ወደ ሰማይ በክብር በምስጋና ማረጉን የሚነገርበት ታላቅ ዕለት ነው ።

ጌታችን መድሃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሞትን ድል አድርጎ መቃብር ክፈቱልኝ መግነዝ ፍቱልኝ ሳይል ከተነሳ በኋላ ለ39 ቀናት ያህል ለቅዱሳን ሐዋርያት አባቶቻችን  በተለያየ ጊዜ እየተገለጠ ስለ እግዚአብሔር መንግስት ምስጢር እያስተማራቸው ከቆየ በኋላ በ40ኛው ቀን ወደ ሰማይ አረገ ። ያረገበትም ቦታ ቢታንያ አጠገብ ደብረ ዘይት ተራራ ላይ ነው ። 11ዱን  ቅዱሳን  ሐዋርያት ደብረ ዘይት ተራራ  ድረስ ከወሰዳቸው በኋላ ባርኳቸው እያዩት ዐርጓል ። ወደ ቀደመ ክብሩ፤ በመለኮታዊ ክብሩ ወደ ሰማይ አርጎ በአባቱ ቀኝ ተቀመጧል " አንትሙሰ ንበሩ ሐገረ ኢየሩሳሌም እስከ ትለብሱ ኀይለ እምአርያም ፣ እናንተ ግን ከላይ ኃይል እስክትለብሱ ድረስ በኢየሩሳሌም ከተማ ቆዩ። እስከ ቢታንያም አወጣቸው እጆቹንም አንሥቶ ባረካቸው። ሲባርካቸውም ከእነርሱ ተለየ ወደ ሰማይም ዐረገ" ( ሉቃ. 24፥48-51) " በዚህ ጊዜ  ደመና ከዓይናቸው ሰውራ ተቀበለችው። በእግዚአብሔርም ቀኝ ተቀመጠ።   "እያዩት ወደሰማይ ዐረገ”(ሉቃ .24÷50 ፣ሐዋ .1÷9) "ዐረገ እግዚአብሔር በይባቤ፤ ወእግዚእነ በቃለ ቀርን፤ ዘምሩ ለአምላክነ ዘምሩ፣ እግዚአብሔር አምላክ ብእልልታና በመለከት ድምጽ ወደ ሰማይ አረገ ዘምሩ ለአምላካችን ዘምሩ" ( መዝ . 46፥5-6)

ጌታችን መድሃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሞትን ድል አድርጎ መቃብር ክፈቱልኝ መግነዝ ፍቱልኝ ሳይል በተነሣ በ40 ኛው ቀን ያረገውም በለበሰው ሥጋ በመሆኑ እና ለሁለተኛ ጊዜ ለፍርድ በሚመጣበት ጊዜ ይህን ክብር እኛም  እንድናገኝ ሊያስተምረን ነው። " በሚመጡ ዘመናትም በክርስቶስ ኢየሱስ ለእኛ ባለው ቸርነት ከሁሉ የሚበልጠውን የጸጋውን ባለ ጠግነት ያሳይ ዘንድ፥ ከእርሱ ጋር አስነሣን በክርስቶስ ኢየሱስም በሰማያዊ ስፍራ ከእርሱ ጋር አስቀመጠን። (ኤፌ .2፥6 ፣ ዮሐ .12፥32) " ወላጆች እንደ ሌላቸው ልጆች አልተዋችሁም፤ ወደ እናንተ እመጣለሁ " ።( ዮሐ . 14፥18)
" እኔ ግን እውነት እነግራችኋለሁ፤ እኔ እንድሄድ ይሻላችኋል። እኔ ባልሄድ አጽናኙ ወደ እናንተ አይመጣምና፤ እኔብሄድ ግን እርሱን እልክላችኋለሁ።( ዮሐ . 16፥7)

ነቢዩ ዳንኤል ስለ ጌታችን ዕርገት እና በአብ ቀኝ ስለመጡ  " በሌሊት ራእይ አየሁ፤ እነሆም፥ የሰው ልጅ የሚመስል ከሰማይ ደመናት ጋር መጣ በዘመናት ወደ ሸመገለውም ደረሰ፤ ወደ ፊቱም አቀረቡት ወገኖችና አሕዛብ በልዩ ልዩ ቋንቋም የሚናገሩ ሁሉ ይገዙለት ዘንድ ግዛትና ክብር መንግሥትም ተሰጠው ግዛቱም የማያልፍ የዘላለም ግዛት ነው መንግሥቱም የማይጠፋ ነው " ( ዳን .7፥13-14)
ጌታ ኢየሱስም ከእነርሱ ጋር ከተናገረ በኋላ ወደሰማይ ዐረገ በእግዚአብሔርም ቀኝ ተቀመጠ። (ማር. 16፥9-19)

ቅዱስ ሉቃስ ስለ ጌታችን መድሃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ዕርገት ሲጽፍ እንዲህ ብሎአል ፦ " ደግሞ አርባ ቀን እየታያቸው ስለ እግዚአብሔርም መንግሥት ነገር እየነገራቸው፥ በብዙ ማስረጃ ከሕማማቱ በኋላ ሕያው ሆኖ ለእነርሱ ራሱን አሳያቸው። ከእነርሱም ጋር አብሮ ሳለ ከኢየሩሳሌም እንዳይወጡ አዘዛቸው፥ ነገር ግን። ከእኔ የሰማችሁትን አብ የሰጠውን የተስፋ ቃል ጠብቁ፤ ዮሐንስ በውኃ አጥምቆ ነበርና፥ እናንተ ግን ከጥቂት ቀን በኃላ በመንፈስ ቅዱስ ትጠመቃላችሁ አለ። እነርሱም በተሰበሰቡ ጊዜ። ጌታ ሆይ፥ በዚህ ወራት ለእስራኤል መንግሥትን ትመልሳለህን? ብለውጠየቁት። እርሱም አብ በገዛ ሥልጣኑ ያደረገውን ወራትንና ዘመናትን ታውቁ ዘንድ ለእናንተ አልተሰጣችሁም፤ ነገር ግን መንፈስ ቅዱስ በእናንተ ላይ በወረደ ጊዜ ኃይልን ትቀበላላችሁ፥ በኢየሩሳሌምም በይሁዳም ሁሉ በሰማርያም እስከ ምድርዳርም ድረስ ምስክሮቼ ትሆናላችሁ አለ። ይህንም ከተናገረ በኋላ እነርሱ እያዩት ከፍ ከፍ አለ፤ ደመናም ከዓይናቸው ሰውራ ተቀበለችው እርሱም ሲሄድ ወደ ሰማይ ትኵር ብለው ሲመለከቱ ሳሉ  እነሆ ነጫጭ ልብስ የለበሱ ሁለት ሰዎችበአጠገባቸው ቆሙ ደግሞም የገሊላ ሰዎች ሆይ ወደስማይ እየተመለከታችሁ ስለ ምን ቆማችኋል? ይህ ከእናንተ ወደሰማይ የወጣው ኢየሱስ ወደ ሰማይ ሲሄድ እንዳያችሁት፥ እንዲሁ ይመጣል አሉአቸው። (ሐዋ.1፥3-11) 
ቅዱስ ጳውሎስም ስለ ጌታችን እርገት እንዲህ ሲል ይመክረናል " እንግዲህ ከክርስቶስ ጋር ከተነሣችሁ ክርስቶስ በእግዚአብሔር ቀኝ ተቀምጦ ባለበት በላይ ያለውን እሹ በላይ ያለውን አስቡ እንጂ በምድር ያለውን አይደለም ሞታችኋልና ሕይወታችሁም በእግዚአብሔር ከክርስቶስ ጋር ተሰውሮአልና  ሕይወታችሁ የሆነ ክርስቶስ በሚገለጥበት ጊዜ በዚያን ጊዜ እናንተ ደግሞ ከእርሱ ጋር በክብር ትገለጣላችሁ ( ቆላ. 3፥1-4 )

"ሥፍራ  አዘጋጅላችሁ ዘንድ እሄዳለሁ"  (ዮሐ.14፥2)
በድጋሜ  እንኳን ለብርሃነ ዕርገቱ በሰላም አደረሳችሁ!!

✟...ገድለ ቅዱስን...✟

10 Jun, 14:00


††† እንኳን ለኢትዮዽያዊው ጻድቅ አቡነ ተጠምቀ መድኅን እና ለእናታችን ቅድስት ማርታ ዓመታዊ የዕረፍት በዓል በሰላም አደረሳችሁ፣አደረሰን። †††

††† በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን! †††

††† አቡነ ተጠምቀ መድኅን †††

††† ጻድቁ የተወለዱት በአፄ ሱስንዮስ ዘመን በ1610 ዓ/ም ሲሆን ወላጆቻቸው #ወልደ_ክርስቶስና #ወለተ_ማርያም ይባላሉ:: ታሕሳስ 2 ቀን እንደ መወለዳቸው ክርስትና የተነሱት ጥር 11 ቀን ነበርና ካህኑ "ተጠምቀ መድኅን" አላቸው:: በምድረ #ጐጃም ከበቀሉ ታላላቅ #ቅዱሳን አንዱ የሆኑት አባ ተጠምቀ መድኅን ገና ከሕጻንነታቸው ጀምሮ #ጸጋ_እግዚአብሔር የጠራቸው ነበሩ::

ሕጻን እያሉ #ቃለ_እግዚአብሔር መማር ቢፈልጉም አባታቸው በግድ እረኛ አደረጋቸው:: እርሳቸው ግን በሕጻን ልባቸውም ቢሆን ቤተሰብን ማሳዘን አልፈለጉም::

ይልቁኑ ወደ በርሃ ይወርዱና አንበሳውን: ነብሩን: ተኩላውን ሰብስበው:- "በሉ እኔ ልማር ልሔድ ስለ ሆነ እስከ ማታ ድረስ ጠብቁልኝ" ብለው ለአራዊቱ አደራ ይሰጣሉ:: አራዊቱ ከበጉ: ከፍየሉ: ከላሙ ጋር ሲቦርቁ ይውላሉ:: ተጠምቀ መድኅን ደግሞ ዳዊቱን: ወንጌሉን ሲማሩና ሲጸልዩ ውለው ማታ ይገባሉ::

ተጠምቀ መድኅን በሕጻንነታቸው ቁርስና ምሳቸውን ለነዳያን በመስጠት በቀን አንድ ማዕድ ብቻ ይቀምሱ ነበር:: 23 ዓመት ሲሞላቸው ወደ #መርጡለ_ማርያም ሔደው መንኩሰዋል:: ከዚሕ ጊዜ በሁዋላ ለ37 ዓመታት:-

1.በፍጹም ተጋድሎ ኑረዋል
2.ራሳቸውን ዝቅ አድርገው አገልግለዋል
3.ከጐጃም እስከ ሱዳን ድረስ ወንጌልን ሰብከው በርካቶችን አሳምነው አጥምቀዋል (ካህን ናቸውና)
4."7" ገዳማትንና "12" አብያተ ክርስቲያናትን አንጸዋል::

††† ጻድቁ በተሰጣቸው መክሊት አትርፈው በ60 ዓመታቸው በ1670 ዓ/ም (በአፄ #ዮሐንስ_ጻድቁ ዘመን) ዐርፈዋል::
እግዚአብሔር የምሕረት ቃል ኪዳን የገባላቸው ሲሆን አጽማቸው ዛሬ #በጋሾላ_ቅዱስ_ጊዮርጊስ የእናቶች ገዳም ውስጥ ይገኛል::

††† ቅድስት ማርታ †††

††† እናታችን ቅድስት ማርታ በቀደመ ሕይወቷ እጅግ ኃጢአቷ የበዛ ሴት ነበረች:: እጅግ ቆንጆ መሆኗን ሰይጣን ለኃጢአት እንድትጠቀምበት አባበላት:: እርሷም ተቀበለችው:: በወጣትነት ዘመኗ በመልኩዋና በገላዋ በርካቶችን ወደ ኃጢአት ሳበች::

መጽሐፍ እንደሚል ለሁሉም ሰው የመዳን ቀን ጥሪ አለውና አንድ ቀን (በበዓለ ልደት) ወደ ቤተ ክርስቲያን ሔደች:: ዘበኛው ግን ሲያያት ተጸይፏልና አትገቢም አላት:: ተከራከረችው: ለመነችው:: ግን አልተሳካላትም:: ሰዓቱ የቅዳሴ ቢሆንም እርሷ እሪ አለች:: ለቅዳሴ የቆሙ ሁሉ በመታወካቸው ዻዻሱ ወጥቶ ገሰጻት::

ያን ጊዜ ነበር ወደ ልቧ የተመለሰችው:: በጉልበቷ ተንበርክካ መራራ ለቅሶን አለቀሰች:: ዻዻሱንም ተማጸነችው:- "እጠፋ ዘንድ አትተወኝ:: ወደ ጌታየ አድርሰኝ" አለችው:: ወዲያውም ወደ ቤቷ ሔዳ የዝሙት እቃዋን አቃጠለች:: ጸጉሯን ተላጨች:: ንብረቷን ሁሉ ለነዳያን አካፈለች:: ዻዻሱም ንስሃ ሰጥቶ ወደ ገዳም አሰናበታት::

ወደ ገዳም ገብታ: በዓት ተቀብላ: ጾምና ጸሎትን ከእንባ ጋር አዘወተረች:: ለ25 ዓመታት በፍጹም ተጋድሎ ከበዓቷ ሳትወጣ: አንድም ሰው ሳታይ ኖረች:: ከማረፏ በፊትም ብዙ ተአምራትን አድርጋለች::

††† የቅዱሳን አምላክ ለእኛም እድሜ ለንስሃ: ዘመን ለፍስሐ አይንሳን:: ከበረከታቸውም ያድለን:: †††

††† ሰኔ 3 ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት=
1.ቅድስት ማርታ ተሐራሚት
2.አቡነ ተጠምቀ መድኅን ጻድቅ (ኢትዮዽያዊ)
3.ቅዱስ ኢላርዮን ሰማዕት
4.ቅዱስ ኮርዮን ሰማዕት

†††ወርኀዊ በዓላት
1.በዓታ ለእግዝእትነ ማርያም ድንግል ወላዲተ አምላክ
2.ቅዱሳን ኢያቄም ወሐና
3.ቅዱሳን ሊቃነ ካህናት አበው (ዘካርያስና ስምዖን)
4.አባ ሊባኖስ ዘመጣዕ
5.አቡነ ዜና ማርቆስ
6.አቡነ መድኃኒነ እግዚእ ዘደብረ በንኮል

††† "አልሞትም: በሕይወት እኖራለሁ እንጂ::
የእግዚአብሔርንም ሥራ እናገራለሁ::
መገሠጽስ እግዚአብሔር ገሠጸኝ::
ለሞት ግን አልሠጠኝም::
የጽድቅን ደጆች ክፈቱልኝ::
ወደ እነርሱ ገብቼ እግዚአብሔርን አመሰግናለሁ::
ይህች የእግዚአብሔር ደጅ ናት::
ጻድቃን ወደ እርስዋ ይገባሉ::
ሰምተኸኛልና:
መድኃኒትም ሆነኸኛልና አመሰግንሃለሁ::" †††  (መዝ. 117:17-22)

††† ወስብሐት ለእግዚአብሔር †††