ሰው ተፈጥሮው በየሰዓቱና በየዕለቱ የሚታደስና የሚለወጥ በመሆኑ ዘወትር ግብዓት ይፈልጋል፡፡ ሆድ በሰዓቱ የሚፈልገውን ካላገኘ ጥያቄ ያነሳል፡፡ ጥያቄውን መመለስ የሚቻለው በጊዜው የሚፈልገውን ማቅረብ ሲቻል ነው፡፡ በርግጥ ሰው ምግብ ሳይበላ ለቀናት ሊቆይ ይችል ይሆናል፡፡ ነገር ግን ቆይታው የስቃይ ነው የሚሆነው፡፡ ምግብ ያላገኘ ሰው መላ ሰውነቱ ይደክማል፤ ማሰብ ያቅተዋል፤ በእጆቹ ሊሰራቸው የሚፈልጋቸውን ስራዎች በቀላሉ መስራት አይችልም፡፡ አቅም፣ ጉልበትና ብርታት ያጣል፡፡
የሰው ልጅ አዕምሮም እንደዛው ነው፡፡ በየቀኑ የሚፈልገውን አዲስ ሃሳብ፣ የተለየ መረጃና ዕውቀት ካላገኘ ይራባል፡፡ ማዕዱ ካልተሟላ ነፍስያው እንደተራበ፣ መንፈሱ እንደከሳ ዕድሜውን ይጨርሳል፡፡ ውስጣዊ ደስታው ይራቆታል፡፡ ማሰብ መመራመር፣ ነገሮችን አብጠርጥሮ ማወቅ አይችልም፡፡ አቅሙና ጉልበቱ ድሮ በተመገበው ሃሳብ ብቻ ይወሰናል፡፡ ወደፊት አሻግሮ ማየት ይሳነዋል፡፡ ጊዜውን የሚዋጅ ሃሳብ ያጣል፡፡ ከዘመኑ ጋር መስተካከል ያቅተዋል፡፡ ነፍስያው ይመነምናል፤ መንፈሱ ይከሳል፣ አዕምሮው ይደክማል፣ ሚዛኑ ይዋዥቃል፣ አስተውሎቱ ይጠብባል፣ አስተሳሰቡ ያንሳል፣ ዕይታው ይጭበረበራል፡፡
ዕውቀት የተራበ ጭንቅላት፤ ሃሳብ የታረዘ ሕሊና ለዓለሙ ያለው ምልከታ የተሳሳተ ይሆናል፡፡ ለፍረጃና ለጭፍን አመለካከት ይጋለጣል፡፡ በደረሰበትና በቆመበት የሃሳብ ሳጥን ብቻ ተወስኖ ሰፊውን ዓለም ሳይመረምርና ሳያውቅ በነሲብ ይደመድማል፡፡
አሜሪካዊው ደራሲ ሪቻርድ ራይት “Native son” በተባለ መፅሐፉ፡-
‹‹የሰው ልጅ ከእንጀራ የበለጠ ሊርበው የሚገባው ራሱን ወይም ማንነቱን ማወቅ ነው›› ይላል፡፡
እውነት ነው! ራስን ማወቅ የዕውቀት መጀመሪያ ነው፡፡ ነገር ግን ራስን ለማወቅ ዓለሙንና አስተሳሰቡን፤ ውስጣውስጥ አመለካከቱን ጠንቅቆ ማወቅ ግድ ይላል፡፡
አለሙን ለማወቅ ደግሞ አዕምሮን በያይነቱ በሆነ መረጃ መመገብ ያስፈልጋል፡፡ መረጃውን በደንብ ማብላላትና የሚጠቅመውን መዋጥ፣ የማይጠቅመውን መትፋት ያሻል፡፡ ጥሩ የተመገበ በፊቱ እንደሚታወቀው ሁሉ በጥሩ ሃሳብ የተሞላ ጭንቅላትም በአኗኗሩ፣ በሕይወቱ፣ በሃሳቡና በተግባሩ ይታወቃል፡፡
አዎ! ሕሊና እንዲያድግ አዳዲስ ሃሳቦችን ዕለት ዕለት መመገብ ግድ ይላል፡፡ ትናንት ያስበብበት በነበረው መንገድ ብቻ እንዳይወሰን አዲስና ከቀድሞው የተለዩ መንገዶችን ማወቅ ይጠበቅበታል፡፡ የሕይወት አቅጣጫውን ከወዲሁ እንዲያውቅ፣ የወደፊቱን ቀድሞ ይተነብይ ዘንድ እንዲችል ተራማጅ አዕምሮ ያስፈልገዋል፡፡ የትናንቱን እያዛመደ፣ የዛሬውን ሃሳብ እየፈተሸ የወደፊቱን መንገድ ማበጀት ግድ ይለዋል፡፡
ንጉስ ዳዊት፡-
‹‹በሰው ልጆች ዘንድ ምናምንቴ ከፍ ከፍ ባለ ጊዜ ክፉዎች በዙሪያው ይሰበሰባሉ፡፡›› ይላል፡፡
እውነት ነው! ንጉስ ዳዊት ምናምንቴ የሚለውን ወደዚህ ዘመን ብናመጣው ዘረኝነት፣ ክፋት፣ ራስወዳድነት፣ ማስመሰል ወዘተ ክፉ ነገሮች ሁሉ ሊሆኑ ይችላሉ፡፡ ዛሬ አብዛኛው ሰው ለዘረኝነትና ለገንዘብ ጣዖት እየሰገደ ነው፡፡ ለጣኦቱም የምስኪን ሕይወት እየተገበረለት ይገኛል፡፡
በዚህ ዘመን ጣኦቱ የበዛው ምናምንቴ አስተሳሰብ ስለበዛ ነው፡፡ አዎ ጭንቅላቱ የተራበ ሰው ለምናምንቴ ሃሳብ እጅ ይሰጣል፡፡ ለማይጠቅመው ያጎበድዳል፡፡ ራሱን የረሳ ጭንቅላት ህሊናውን በወጉ ያልመገበ ነው፡፡ ራሱን መመገብ ያቃተው ራሱን በራሱ ማስተዳደር ያልቻለ ነው፡፡
ለራሱ መሆን ያቃተው ጭንቅላት ለሌሎችም ሆነ ለዓለሙ ዕዳ ነው፡፡ የሌሎች ባሪያ እንጂ የራሱ ጌታ መሆን አይችልም፡፡ በነዱት የሚነዳ፤ ሲገፉት የሚገፋ ጋሪ ይሆናል፡፡
ሃሳብ ያነሰው አዕምሮ ባትሪው እንዳለቀ ስልክ ነው፡፡ በቁሙ ይተኛል እንጂ አይነቃም፤ ያለ ይመስላል እንጂ የለም፡፡ ቢቀሰቅሱት አይሰማም! ሃይል ጨርሷላ!
ወዳጄ ሆይ.... ዕለት ዕለት፣ በየጊዜው አንጎልህን በአዲስ ሃሳብ ቻርጅ አድርገው፡፡ ቀስ በቀስ አቅሙ እንዳይደክምና ሃይሉን እንዳይጨርስ ጭንቅላትህን አዲስ ዕውቀት ሙላው፡፡ ምናምንቴው ሃሳብ ህሊናህን እንዳይገዛ ጥሩ ጥሩውን መግበው፡፡
✍ እሸቱ ብሩ ይትባረክ (እ.ብ.ይ.)
ጭንቅላትህን በየጊዜው አዲስ ሃሳብ መመገብ ፍላጎታችሁ ከሆነ ይህን 👉
የ #facebook #group #join በማድረግ ቤተሰብ ሁኑ!!!
ፅሁፉን አስተማሪ ሆኖ ካገኛችሁት ሌሎችም ይማሩበት ዘንድ #like #copylink #share ማድረግን አትርሱ 🙏