የዛሬ 14 ዓመት ገደማ ለግንባታው መሰረት ድንጋይ ሲጣል 80 ቢሊዮን ብር ያስፈልገዋል ተብሎ የተጀመረው የታላቁ ህዳሴ ግድብ፤ ግንባታው 97.6 በመቶ እንደደረሰና ጥቂት የማጠናቀቂያ ስራዎች ብቻ እንደቀሩት የታላቁ ህዳሴ ግድብ ማስተባበሪያ የፕሮጀክት ፅህፈት ቤት ተናግሯል፡፡
ለምን ይሆን ግንባታው ሲጀመር ለሙሉ ስራው በቂ ነው ተብሎ የነበረው 80 ቢሊዮን ብር፣ አሁን ለቀረው የ2.4 በመቶ ስራም 80 ቢሊዮን ብር ያስፈለገው?
በጉዳዩ ዙሪያ የህዳሴ ግድብን የቦንድ ሽያጭ ሲከውን የቆየውን የኢትዮጵያ ልማት ባንክ የካፒታል ገበያ ዳይሬክቶርት ዳይሬክተር አቶ ዳዊት አማረን ጠይቀን የነበረ ቢሆንም የግንባታ ስራው በተለያ ደረጃ ስለሚመራ ስለዚህ ጉዳይ ፕሮጀክቱን የሚመሩት የስራ ሃላፊዎች ናቸው የሚያውቁት ብለውናል፡፡
ይሁንና ልማት ባንክ የቦንድ ሽያጭ ላይ እንደመሳተፉ እስካሁን ከህዝቡ ከ20.2 ቢሊየን ብር በላይ መዋጣቱን መናገር እንችላለን ብለዋል፡፡
ለማጠናቀቂያ ስራው ከሚያስፈልገው ገንዘብ ልማት ባንክ 10 ሚሊዮን ብር መስጠቱንም አቶ ዳዊት ነግረውናል፡፡
ማስተባበሪያ ፅህፈት ቤቱ በበኩሉ በዚህ ዓመት እስከ 1.6 ቢሊዮን ብር ከህዝቡ ለመሰብሰብ አቅዶ እየሰራ መሆኑን ተናግሯል፡፡
የዚህ አካል የሆነና ባንኮችን፣ ኢንሹራንስ ተቋማትንና የብድርና ቁጠባ ተቋማትን ያሳተፈ የገቢ ማሰባሰቢያ መርሃ ግብር ባሳለፍነው ዓርብ አካሂዷል፡፡
በመርሃ ግብሩ 110 ሚሊዮን ብር ለመሰብሰብ የታሰበ ቢሆንም በወቅቱ ከፋናንስ ተቋማቱ መሰብሰብ የተቻለው 25.9 ሚሊዮን ብር ብቻ መሆኑን ተመልክተናል፡፡
ከተዘጋጀው የ110 ሚሊዮን ብር ቦንድ በወቅቱ ለአዳዲሶቹ የፋይናንስ ተቋማት ለሽያጭ የቀረበው 60 ሚሊዮን ብር የሚያወጣ ቦንድ ሲሆን ከዚህ ቀደም ቦንድ ገዝተው የመመለሻ ጊዜው የደረሰ ቦንድ ያላቸው የፋይናንስ ተቋማት ደግሞ ቦንዱን በድጋሚ እንዲያድሱ በማድረግ 50 ሚሊዮን ብር የሚያወጣ ቦንድ ለግዢ ቀርቧል፡፡
ለመሆኑ ቦንድ ማደስ ማለት ምን ማለት ነው? የኢትዮጵያ ልማት ባንክ የካፒታል ገበያ ዳይሬክቶርት ዳይሬክተር አቶ ዳዊት አማረ ይህንን ሲያብራሩ 5 ዓመትና ከዚያ በላይ የቆየ ቦንድ ያላቸው ገንዘባቸውን ከመውሰድ ይልቅ ለቀጣዮቹ ጊዜያት ገንዘባቸውን የመውሰጃ ጊዜውን የሚያራዝሙበት ነው ብለዋል፡፡
ይህ አካሄድ ግድቡን ለማጠናቀቅ የሚያስፈልገውን ገንዘብ ለማግኘት አንዱ የገቢ ማሰባሰቢያ ስልት ስንደሆነም አቶ ዳዊት ያነሳሉ፡፡
ለአብነትም እስካሁን ከህዝቡ ከተዋጣው 20.2 ቢሊዮን ብር ውስጥ ዳስፖራው ያዋጣው ከ1.5 ቢሊዮን ብር ያልበለጠ መሆኑን ከሪፖርቱ ተመልክተናል፡፡
የዳያስፖራውን ተሳትፎ ለማበርታት በመተግበሪያዎች በቀጥታ መክፈል እንዲቻል የሚያስችሉ አሰራሮች እንደተመቻቹ የሚናገሩት የማስተባበሪያ ፅኅፈት ቤቱ ዋና ስራ አስፈፃሚ ደ/ር አረጋዊ በርሄ ሁሉም ማህበረሰብ አስተዋፅኦውን እንዲቀጥል ጠይቀዋል፡፡
ዘገባው የሸገር ሬዲዮ ነው።
@Addis_News
@Addis_News