መጽሐፍ የሚለው ሞት እንደማይለመድ እና ሁልጊዜም ሐዲስ እንደሆነ ነው።
በእኛ ሀገር ያለው ሞት ግን የተለመደ የቅርብ ዘመድ የቅርብ ጎረቤት ከሆነ ዘገየ።
ጧት ማታ ስለ ሚጎበኘን አስፈሪነቱን ተላመድነው።
የሞት መልእክተኞች ሹማምንት ሁል ጊዜ ሥራውን ስለ ሚያሳልጡለት እንግድነቱ ተረስቶ ሁል ጊዜም የሚጠበቅ የግድ ዘመድ ሁኗል።
ጧትም ሞት፣ማታም ሞት፣በየሰዓቱ ሞት፣በየሸንተረሩ ሞት፣ሞት ሞት..በየቀኑ ሞት የማይሰማበት መንደር ስለሌለ የጆሮ ዘመድ ሁኖ ግብሩ ተለምዶ ሁሉን ድንዙዝ አደረገው።
ይልቁንም ይሄው ሞት በንጻሓን ላይ በትረ ሥልጣኑን ስለሚያጸና እኖራለሁ ባይ እስኪታጣ ቅርብ ዘመዱን በቀቢጸ ተስፋ ባሕር እያሰጠመው ነው።
ሞት አዳማዊ ርሥት ቢሆንም የሚወረሰው በድንገት እንደ ሌባ አመጣጥ ነበር።
አሁን አሁንማ በዕቅድ በክፉዎች ፈቃድ በትውልድ ቅነሳ ምክንያት ርሥትነቱ በድንገት ሳይሆን በልምምድ ሁኗል።
ትልቁ ድንዛዜ ጥፋትን መለማመድ ነው።"ከሰይጣን ልማድ ይከፋል"እንደ ሚባለው ከክፋት ሁሉ ክፋት የልምምድ ጥፋት ነው።
መጽሐፍ እንደ ሚለው ለሁሉም ጊዜ ነበረው፦"ለመወለድ ጊዜ አለው ለመሞትም ጊዜ አለው።"መክ.፫፥፪ እንዲል።
ከእኛ ሀገር ግን ለመወለድ እንጂ ለመሞት ጊዜ የለውም።
ባላሰቡት ዕለት ባልጠረጠሩት ሰዓት ያለ ጊዜው በጥፋት ልምምድ ሰው ሁሉ ይሞታል።
ይህ ጥፋት፣ይህ መቅሰፍት፣ይህ የሞት ዕቅድ፣ይህ ድምሳሴ..የሚለወጠው እንዴት ነው?
እኛ ግን ከሐዋርያው ጋራ እንዲህ እያልን እንዘምራለን፦"አዎን፥ ሙታንን በሚያነሣ በእግዚአብሔር እንጂ በራሳችን እንዳንታመን፥ እኛ ራሳችን የሞትን ፍርድ በውስጣችን ሰምተን ነበር።እርሱም ይህን ከሚያህል ሞት አዳነን ያድነንማል።፪.ቆሮ.፩፥፱