ምዕራፍ-26
ደራሲ-ዘሪሁን ገመቹ ዋቤ
ፔሩ/ኢኪዬቶስ
ጥዋት ምስራቅ እና ናኦል ከእንቅልፋቸው አርፍደው ቢነቁም እርስ በርስ ለመተያየት ግን ተፋፍረው ነበር፡፡
‹‹ምነው የእኔ ፍቅር አመመሽ እንዴ?››ሲል የመጀመሪያውን ዓ.ነገር ተናገረ፡፡
‹‹አይ ደህና ነኝ…ማታ የጠጣውት የሀገሬው መጠጥ መሰለኝ እራሴን አሞኛል፡፡››
‹‹አዎ አንቺ.. እሱ ነው እንዴ …እኔም እኮ ጭፍግግ ብሎኛል››
‹‹መሰለኝ…በል አሁን ልብሳችንን ለባብሰን እታች እንውረድና ቁርስና ብና ነገር እንጠጣበት››
‹‹..እርግጠኛ ነኝ በቡና ይሻለናል?፡፡››ሁለቱም ተስማሙና ልብሳቸውን ለባብሰው ፊታቸውን ተጣጠቡና ተያይዘው ወደታች ወደሆቴሉ ወረዱ፡፡ ጎን ለጎን ተቀምጠው ቁርስ አዘዙ፡፡ሁለቱም ያስደበራቸው ነገር ምን አንደሆነ ያውቃሉ፡፡ማታ የፈፀሙት ወሲብ ነው፡፡እርግጥ በወቅቱ ሁለቱም ፍፅም ደስታኛ ነበሩ፡፡አሁን እራሷቸውን እስኪያማቸው ድረስ እንዲህ ሀሳብ ላይ የጣላቸው ነገስ እንዴት ነው የምንቀጥለው…?የሚለው ነው፡፡የቀረበላቸውን ቁርስ በልተው ቡናቸውን ጠጥተው ሂሳብ ሲጠይቁ አስተነጋጆ ‹ተከፍሏል› አለቻቸው፡፡ግራ ተጋብተውና ደንግጠው‹‹ማነው የከፈለው ?››ሲሉ በአንድነት ጠየቁ፡፡
‹‹እዛ ጋር ተቀምጦ የነበረው ሰውዬ ነው…ከ5 ደቂቃ በፊት ውጥቶ ሄዶል፡፡ ይሄንን ወረቀት ስጪያቸው ብሎኛል፡፡›› ብላ ብጣሽ ወረቀት አቀበለቻቸው፡፡ናኦል ፈጠን ብሎ ተቀበላትና አንድላይ አነበቡት፡፡
‹‹አሁን ወደ ክፍላችሁ ተመለሱና ሻንጣችሁን ሸክፋችሁ ለጉዞ ዝግጁ ሁኑ፡፡››ይላል፡፡
‹‹ደግሞ ሌላ ጉዞ?››እሱ ነበር ተናጋሪው፡፡
እንደተባሉት ወደ ሆቴላቸው ተመለሱና ሻንጣቸው በፍጥነት ሸከፉ..ወዲያው የሆቴሉ ስልክ ጠራ….ምስራቅ አነሳችው‹‹ወደታች ውረዱ.. ታክሲ ቀሞ ይጠብቃችኋል››የሚል ጎርናና ድምፅ መልዕክቱን ተናገረና ድምፁን አቋረጠው፡፡
ትእዛዙን ተከትለው ..ሻንጣቸውን እንደያዙ ቀጥታ ከሆቴል ሲወጡ ባለታክሲውን አይኑን በጥቁር መነፅር ሸፍኖ በራፍ ከፍቶ ሲጠብቃቸው አገኙ።ያለምንም ንግግር ሻንጣቸውን እየጎተቱ ስሩ ደረሱ።ሻንጣቸውን ተቀበለና ወደመኪናው ኃላ ወስዶ ካሶኒውን ከፈተና ሻንጣዎችን አስገብቶ መልሶ ከደነውና ወደሹፌሩ መቀመጫ ሲሄድ ምስራቅ እና ናኦል ወደውስጥ ገብተው ከኃላ ወንበር ጎን ለጎን ተቀምጠው ነበር።ቀጥታ 25 ደቂቃ በመንዳት ከከተማው ውጭ ነበር የወሰዳቸው።ምን ሊከሰት ነው በሚል ግራ መጋባትና ጉጉት ነገሮችን ሲጠብቁ ቀጥታ ታክሲዎ ቻርተር አውሮፕላን ያለበት ቦታ ደርሶ ነበር ያወረደቻቸው።ከዛ ቆመው እርስ በርስ እየተያዩ ሻንጣቸው ከታክሲዋ ወረደና አውሮፕላኑ ላይ ተጫነላቸው።
ናኦል እና ምስራቅ በተሳፈሩበት አነስተኛ ቻርተር ሄሌኮፍተር ውስጥ ከካፕቴኑ ውጭ ሌላ አንድ ሰው ነው ያለው።ገብተው እንደተቀመጡ መጀመሪያ ሻንጣቸውን እንዳለ ዘርግፎ በውስጡ ያለውን ዕቃ እያብጠረጠረ ተመለከተ። ከዛ በመሳሪያ በመጠቀም መቅረፀ ድምፅ ወይም አቅጣጫ መከታተያ መሳሪያ መያዝ አለመያዛቸውን ፈተሸ።ከዛ በኃላ የሁለቱንም ሞባይል ተቀበለና ያለምንም ማብራሪያ በታክሲ ይዞቸው መጥቶ አሁንም እስኪበሩ ድረስ አታች ቆሞ ይጠብቃቸው ለነበረ የታክሲ ሹፌር በግዴለሽነት ወረወረለት.፡፡አንድን ሲቀልበው ሌላው አምልጦት መሬት ላይ ተፈጠፈጠ.....።ጎንበስ ብሎ አነሳውና ሁለቱንም ኪሱ ከቶ ታክሲው ውስጥ በመገባት መኪናዋን አስነስቶ በመጣበት አቅጣጫ ተመልሶ ሲሄድ በተቀመጡበት ሆነው በገረሜታ ተመለከቱት።
ወዲያው ጎኗቸው ያለው ፈታሻቸው አውሮኘላኑን እንዲያንቀሳቅስ ለካፒቴኑ በእጅ እንቅስቃሴ ምልክት ሰጠው...። ከ3 ደቂቃ በኃላ አውሮኘላኗ አየር ላይ ተሠቀለች።አፍንጫዋን ወደኃላ አዞረችና አረንጎዴ ውቅያኖስ ወደሚመስለው ጥቅጥቅ የአማዞን ደን መክነፍ ጀመረች ።አይናቸውን ዝቅዝቅ ወደታች ሲመለከቱ አማዞን ወንዝ ሰሌሜ ሰሌሜ እየጨፈረ በአማዞን ደን እንብርት ዙሪያ ጥምዝ ሲሰራ የአማዞን ደንን ወገብ ሸብ አድርጎ ለማሰር በእግዜር ከዘንዶ ቆዳ የተሠራ ሰማያዊ ቀበቶ ነው የሚመስለው።
ከሁለት ሰዓት በስጋት የተሞላ ምቾት አልባ በረራ በኃላ አውሮኘላኗ ከፍታዋን መቀነስና አፍንጫዋን ወደታች ደፍታ ለማረፍ መምዘግዘግ ጀመረች። እታች አንድ የተንጣለለ ግቢ ውስጥ ባለአንድ ፎቅ ግዙፍ ህንፃ መኖሩን የታያቸው ለማረፍ መሬት ከተቃረብ ኃላ ነው።
አውሮፕላኖ አርፈ… ሁለቱም ከውስጧ እንዲወጡ ሲደረግ ሜዳው ጠቅላላ እጅግ ዘመናዊ መሳሪያ በታጠቁ አስፈሪ ታጣቂዎች ተሞልቶ ነበር።ናኦል ከመፍራቱ የተነሳ እራሱን ችሎ መቆም አቃተውና ወደምስራቅ ተጠግቶ እጇን ጨምድዷ ያዛት፡፡እሷም የእሱን ያህል አይሁን እንጂ ፈርታለች፡፡ሁኔታዎችም ካሰበቻቸው በላይ አስፈሪና የተወሳሰብ ሆኖባታል። ወዲያው አንድ ታጣቂ ወደእነሱ ቀረበና በተወለካከፈ የእንግሊዘኛ ቃል"ተከተሉኝ"አለና ቀድሞቸው ፊቱን አዙሮ መራመድ ጀመረ...።የተያያዘ እጃቸውን አላቀቁና ተከተሉት ።
ፊት ለፊት ባለው የህንፃው ትልቅ ባለጣውላ በራፍ እየመራቸው ገባና ወደ ውስጥ ይዘልቃል ብለው ሲጠብቁ ወደጎን በመታጠፍ በደረጃው ወደአንደኛው ፎቅ ይወጣ ጀመር። እርስ በርስ ተያዩና በዝምታ ተግባብተው ተከተሉት። የተወሰነ ኮሪደር ካለፍ በኃላ ግዙፍ አዳራሽ መሳይ ሳሎን ውስጥ ነው ይዞቸው የገባው።
የገብበት ክፍል ሳሎን ነው ብለው ከማሰብ ይልቅ ሙዚዬም ነው ማለት ይቀላል።ግድግዳው ላይ በሰልፍ የተገጠገጡ ግዙፍ ስዕሎች ፣በየቦታው የተቀመጡ ቅርስ መሣይ ውድ እቃዎች፣ በሀውልት ቅርፅ የታነፁ የእንስሳትና የሰው ቅርፆች።ልክ ቱሪስት ሆነው በተጋበዙበት ሙዚዪም ዙሪያ ገባውን እየተዞዟሩ እየጎበኙ ያሉ ነው የሚመስለው።ሁኔታውን በመደመም ከሚመለከቱበት "የተከበራችሁ ባልና ሚስቶቹ እንግዶቻችን በቀላሉ ወደማይገባበት...ከገብም ወደማይወጡበት የዘላለም ምድራዊ ቤታችሁ ወደሆነው ወደገንት እንኳን በሰላም መጣችሁ።"የሚል ጎርናና ድምፅ ከኃላቸው ሲሰሙ ነው ከተመስጦቸው ነቅተው ወደአሉበት ነባራዊ ሁኔታ እራሳቸውን የሠበሠብት።ሁለቱም በአንድነት ድምፅ ወደሰሙበት አቅጣጫ እኩል ፊታቸውን አዙረው ተመለከቱ፡፡ ከፊታቸው ያለው ሰውዬ እስከአሁን አካባቢውን ከረገጡ ጀምሮ ካዬቸው ሰዎች የተሻለ የዋህ...ገራገርና ያለቦታው በስህተት የተገኘ የሚመስል ደግ ፊት ያለው ሰው ሆኖ አገኙት ይበልጥ አስገረማቸው።
"ዳግላስ እባላለሁ...ከሀገራችሁ ከኢትዬጰያ ወደእዚህ ያስመጣዎችሁ እኔ ነኝ..ይቅርታ ማለቴ አንተን ያስመጣሁህ እኔ ነኝ ..ባለቤትህ እንኳን በራሷ ፍቃድ የፍቅር ጉዳይ ሆኖባት ነው የመጣችው።"
"ገባን....እንዳልከው ቃልህን አምነን አህጉር አቋርጠን ውቅያኖስ ሰንጥቀን እዚህ ድረስ መጥተናል...አሁን ከእህታችን አገናኘን"ናኦል ነው ጠያቂው።
ዳግላስ ተንከትክቶ ሳቀ....እንደምንም ከሳቁ ወጣና ተጣራ....የተጠራው ልጅ እግር በእጅ አነስተኛ ቦርሳ አንጠልጥሎ እያለከለከ መጥቶ በፍራቻ አንገቱን በመድፍት ስሩ ቆመ "በል ምን ይገትርሀል...ብራስሌቱን አጥልቅላቸው። "ቆፍጣና ትዕዛዝ ሰጠው።