መንግስት መንገድ ለማኅበረ-ኢኮኖሚያዊ እና ለሀገር ግንባታ ያለውን ጠቀሜታ በመገንዘብ፣ ለመንገድ መሠረተ-ልማት ዝርጋታ በየጊዜው ከፍተኛ መዋዕለ ነዋይ ፈሰስ ያደርጋል፡፡ ከፍተኛ የሀገር ሀብት የሚፈስበት የመንገድ ሃብት የሚጠበቅበትን አገልግሎት እንዲሰጥ ተገቢ ጥበቃ እና እንክብካቤ ያስፈልገዋል፡፡ መንገዶችን ለብልሽት ከሚዳርጉ ምክንያቶች አንዱና ዋነኛው ከተፈቀደው ክብደት በላይ በመጫን መጓዝ ነው። በዚህ ረገድ የኢትዮጵያ መንገዶች አስተዳደር በመላው ሀገሪቱ ባቋቋማቸው 14 የክብደት እና መጠን መቆጣጠሪያ ጣቢያዎቹ በኩል ቁጥጥር ያደርጋል፡፡
የተሽከርካሪዎችን ክብደት የመቆጣጠር ዋና ዓላማ በመንገዶች ላይ የሚንቀሳቀሱ ተሽከርካሪዎች ከተፈቀደላቸዉ የአክስል ክብደት መጠን በላይ ጭነት ጭነዉ በከፍተኛ ወጪ የተገነቡ የመንገድ አውታሮች ላይ ጉዳት እንዳይደርስ የመከላከል እንዲሁም መንገዶች እና ድልድዮች ዲዛይን ለተደረጉበት የአገልግሎት ጊዜ በጥሩ ሁኔታ ላይ ሆነው አገልግሎት መስጠት እንዲችሉ ማድረግ ነዉ፡፡
ከዚህም አኳያ ተቋሙ የተሽከርካሪ ክብደትና መጠንን ለመወሰንና ለመቆጣጠር በወጣው የሚኒስትሮች ምክር ቤት ደንብ ቁጥር 491/2014 አንቀጽ 20 ንዑስ አንቀጽ 6 መሰረት “በዚህ ድንብ ላይ የተሽከርካሪ ክብደትን በመተላለፍ ለተቀመጡት ቅጣቶች የሚከፈል ክፍያ ለኢትዮጵያ መንገዶች አስተዳደር የሚከፈል ሲሆን የተሽከርካሪ መጠንን በመተላለፍ ለተቀመጡ ቅጣቶች የሚከፈል ክፍያ ለሚኒስቴሩ ይከፈላል” በሚል በግልፅ እንደተመለከተው ትርፍ የጫነ ተሽከርካሪ ለጫነው ትርፍ ጭነት ቅጣት ተቀጥቶ፣ ቅጣቱን ኢ.መ.አ. ለዚሁ አገልገሎት በከፈተው ሂሳብ ቁጥር ገቢ የሚደረግ ሲሆን፣ ትርፍ የጫነ ተሽከርካሪ ጉዞውን መቀጠል የሚችለው ጭነቱን ካስተካከለ በኋላ ብቻ ነው።
በደንቡ አንቀጽ 3 ንዑስ አንቀጽ 1 መሰረት “ይህ ደንብ በማናቸውም የኢትዮጵያን መንገድ በሚጠቀሙ ጠቅላላ ክብደታቸዉ ከ3,500 ኪሎ ግራም በላይ በሆኑ ተሽከርካሪዎች፣ የተጣመሩ ተሽከርካሪዎች እና ተሳቢዎች ላይ ተፈጻሚ ይሆናል” በሚል የደንቡን ተፈፃሚነት ወሰን አስቀምጧል::
በደንቡ አንቀጽ 9 መሰረት ለእያንዳንዱ አክስል የተፈቀደ ከፍተኛ ክብደት የሚከተለው ነው፡-
I. የነጠላ አክስል (Axle) ሁለት ወይም ሶስት ጎማዎች የተገጠሙለት ተሽከርካሪ የፊት እና የኋላ የአክስል (Axle) ክፍሎች ጠቅላላ የክብደት መጠን የሚከተለዉ ነዉ፡-
ሀ) የፊት አክስል (የመሪ አክስል) Steering Axle የክብደት መጠን ከ7.7 ቶን (77 ኩንታል) መብለጥ እንደሌለበት፤
ለ) ከመሪዉ አክስል (Steering Axle) ዉጪ ሆኖ ነጠላ ጎማ የተገጠመለት ተሸከርካሪ ከሆነ ጠቅላላ ክብደቱ ከ8 ቶን (80 ኩንታል) መብለጥ እንደሌለበት፤
ሐ) የኋላዉ የአክስል ክፍል አራት ጎማዎች የተገጠሙለት ከሆነ የአክስል ክብደቱ ከ10 ቶን (100 ኩንታል) መብለጥ እንደሌለበት፡፡
II. የተሸከርካሪዉ የአክስል ክፍል ባለ ሁለት (Tandem Axle Unit) ወይም ባለሶስት (Tri-dem axle) ሲሆን፣ ለተሽከርካሪዉ የማይፈቀድ የአክስል (Axle) ክብደት መጠን እንደሚከተለዉ ነዉ፡-
ሀ) ስምንት ጎማዎች ለተገጠሙለት የጥንድ አክስል (Tandem Axle) ጠቅላላ የአክስል ክብደቱ በአንድ ላይ ተደምሮ ከ18 ቶን (180 ኩንታል) መብለጥ እንደሌለበት በሕጉ ላይ ተቀምጧል፡፡
ለ) እያንዳንዳቸው አክስሎች ላይ አራት ጎማ የተገጠመላቸው ባለ ሶስት አክስል ክፍል (Tri-dem axle) ጠቅላላ የአክስል ክብደቱ በአንድ ላይ ተደምሮ ከ24 ቶን (240 ኩንታል) መብለጥ እንደሌለበት በሕጉ ላይ ተቀምጧል፡፡
በደንቡ መሰረት በሚደረግ የአክስል ክብደት ቁጥጥር ላይ በሚታዩ ተግዳሮቶች የቁጥጥር ሂደቱ ላይ አሉታዊ ተፅኖ እየፈጠሩ የሚገኝ ሲሆን፣ ለዚህም ከምንግዜውም በላይ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በጋራ እና በቅንጅት መስራት ያስፈልጋል ነገር ግን ደንቡን ለማስፈፀም ከፍተኛ ሚና ያላቸው እና ሚዛን ጣቢያዎቸ በተተከሉብት አካባቢ የሚገኙ አንዳንድ የመስተዳደር አካላት በሚፈለገው ልክ ድጋፍ እያደረጉ ባለመሆኑ በትርፍ ጭነት ቁጥጥር ሂደቱ ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ እየፈጠረብን ይገኛል፡፡
ስለሆነም ከፍተኛ መዋለ ንዋይ የወጣባቸ ለሀገራችን ኢኮኖሚያዊ እድገት ጉልህ ሚና ያላቸው የመንገድ እንዲሁም ድልድይ ሀብታችንን በትርፍ ጭነት ምክንያት ከሚደርስ ጉዳት ለመከላከል በጋራ እንድንሰራ ለሁሉም የህብረተሰብ ክፍል ሀገራዊ ጥሪያችንን እያቀረብን በተለይም የፀጥታ እንዲሁም የክልልና ዞን መስተዳድር አካላት የምንጊዜም ትብብራችሁ ተጠናክሮ እንዲቀጥል ስንል እንጠይቃለን፡፡ በቁጥጥር ሥርዓቱ ላይ የሚስተዋሉ ማንኛውም ችግሮች ካሉ፣ ተገልጋዮች ከሥር በተቀመጡት የጥቆማ አማራጮች እንዲያሳውቁን እንጠይቃለን።
በተጨማሪ
› አጭር መልዕክት 8561
› ፖስታ ሳጥን ቁጥር 1770
› ድህረገጽ www.era.gov.et
› ፊስቡክ https://www.facebook.com/www.era.gov.et
› ቴሌግራም https://t.me/ethioroads
› ትዊተር https://twitter.com/EthiopiaRoadsAd
› ኢሜል
[email protected]› ዩቲዮብ www.youtube.com/@ethioroads