የክርስቶስ በአራቱ እንስሳ በሰው በላም በአንበሳና በንስር በተመሰሉ ወንጌላውያን የተጻፈው ታሪኩ በዕርገት ተጠናቀቀ:: ክርስቶስ እንደ ሰው ተወለደ ፤ እንደ ላህም ተሠዋ ፤ እንደ አንበሳ ከሙታን ተነሣ ፤ እንደ ንስር ዐረገ:: ሐዋርያት እያዩት ደመና ሠውራ ተቀበለችው:: በእርግጥ ደመና ሠውራ ስትቀበለው የመጀመርያ አልነበረም:: በተወለደ ጊዜም እውነተኛዋ ፈጣን ደመና በማሕፀንዋ ሠውራ ተቀብላው ነበር:: አሁን ደግሞ ደመና ሠውራ ተቀበለችው:: ሐዋርያት በዕርገቱ ተስፋ ነግሮአቸዋልና ደስ እያላቸው ተመለሱ::
በሃምሳኛው ቀን የነገራቸውን አጽናኝ ላከው:: በዮርዳኖስ ሲወርድ ለምስክርነት ነውና በርግብ አምሳል ነበረ:: አሁን ግን ኃይል ሊሆናቸው በነፋስና በእሳት አምሳል ወረደ::
ዛሬ እስራኤል ከግብፅ በወጡ በሃምሳኛው ቀን በሲናን ተራራ የወረደው እሳትና በጽላት ላይ የተጻፈው ሕግ የተሠጠበት ቀን ነው:: ፋሲካችን ክርስቶስ በታረደ በሃምሳኛው ቀን በሐዲስ ኪዳንዋ ደብረ ሲና በጽርሐ ጽዮን በእሳት አምሳል መንፈስ ቅዱስ ወርዶ በሐዋርያት በልባቸው ጽላት ቃሉን የጻፈበት ቀን ነው::
በዓለ ሃምሳ እስራኤል ከግብፅ ከወጡ ሃምሳኛው ቀን ነበረ:: ይህ ዕለት ሙሴ ጽላት ይዞ የወረደበት ቢሆንም ሕዝቡ ደግሞ መታገሥ አቅቶት ጣዖት ሲያመልክ ተገኘ:: በዚህ ምክንያት በዚያች ዕለት ሌዋውያ ካህናት ስለዚህ ባዕድ አምልኮ ቅጣት 3000 ሰዎች ገደሉ:: (ዘጸ. 32:28) በሐዲስ ኪዳኑ በዓለ ሃምሳ ግን ሐዋርያት በልባቸው ፅላት ወንጌል ተጻፈ:: "የሞት አገልግሎት" እንደተባለችው ኦሪት 3000 ሰው አልገደሉም:: በጴጥሮስ ስብከት 3000 ሰው አዳኑ እንጂ::
የጰራቅሊጦስ ዕለት ክርስቶስ በደሙ የዘራውን ያጨደበት የመከር ቀን ነው:: የመከሩ ባለቤት ሠራተኞችን የላከበት ቀን ይህ ነው:: ጰራቅሊጦስ መንፈስ ቅዱስ ቤተ ክርስቲያንን ሠራ::
ኤልያስ በእሳት ሠረገላ ተጭኖ ሲያርግ መጎናጸፊያውን ለኤልሳዕ ወረወረለት:: የእኛ መምህር ክርስቶስ ግን ከኤልያስ ይበልጣል:: ኤሎሄ ኤሎሄ ብሎ ሲጮኽ አይሁድ ባልሰማ ጆሮአቸው "ኤልያስን ይጣራል መጥቶ ያድነው" ብለው እንደዘበቱት አይደለም:: የእኛ መምህር ክርስቶስ ወደ ሰማይ ለማረግ ሠረገላ አይፈልግም:: በእርግጥ የመለኮትን እሳት መሸከም የሚችል ሠረገላ ከየት ይመጣል? እያዩት ከፍ ከፍ አለ:: ልብሱን አልወረወረም:: የእኛ መምህር ክርስቶስ ለሁላችን ልብሱን ሳይሆ ሥጋውና ደሙን ሠጥቶን ሔዶአል:: :: በዐሥረኛው ቀን ደግሞ መንፈሱን ደግሞ በበዓለ ሃምሳ አደለን:: እኛ ክርስቶስ ሲያርግ እያየን አንሮጥም:: ወደ ሥጋ ወደሙ እየቀረብን እርሱ በእኛ እኛም በእርሱ ይኖራል::
ጌታ በትንሣኤው ከኃጢአት ሞት በንስሓ እንድንነሣ አስተማረን:: "አንተ የምትተኛ ንቃ ከሙታንም ተነሣ ክርስቶስ ያበራልሃል" ብሎ ከበደል በንስሓ ትንሣኤ እንድንነሣ ጠራን:: ትንሣኤውን አይተን በንስሓ ከተነሣን የሚቀረን ዕርገት ነው:: ከትንሣኤው በኋላ እያዩት ከምድር ከፍ ከፍ ያለው ጌታ ከንስሓ ማግሥት በጽድቅ ሥራ ከፍ ከፍ እያልን ከምድራዊነት እንድናርግ ይፈልጋል:: ዐርገን በቀኙ መቀመጥ ባንችል በጽድቅ ቀኙ እንዲያቆመን መንገዱ ይኸው ነው::
ጰራቅሊጦስ የቤተ ክርስቲያን የልደት ቀን ነው::
በትንሣኤው ተፀንሳ እስከ ዕርገቱ ድረስ ለዐርባ ቀናት ተሥዕሎተ መልክእ (Organ formation) የተፈጸመላት ቤተ ክርስቲያን ዛሬ የተወለደችበት ቀን ነው:: እግዚአብሔር በባቢሎን ሜዳ የበተነውን ቋንቋ የሰበሰበበትና እንዱ የሌላውን እንዳይሰማው እንደባልቀው ያሉ ሥሉስ ቅዱስ አንዱ የሌላውን እንዲሰማ ያደረጉበት ዕለት ዛሬ ነው:: ሰው ወደ ፈጣሪ ግንብ ሰርቶ በትዕቢት ለመውጣት ሲሞክር የወረደው መቅሠፍት ዛሬ በትሕትና ፈጣሪን ሲጠባበቁ ለነበሩ ሐዋርያት ፈጣሪ ራሱ ያለ ግንብ ወርዶ ራሱን የገለጠበት ዕለት ነው::
በዮርዳኖስ ወንዝ ዳርቻ በርግብ አምሳል በትሕትና የወረደው መንፈስ ቅዱስ ዛሬ በእሳትና በነፋስ አምሳል ወደ ሐዋርያቱ የወረደው ዛሬ ነው:: ርግብ ሆኖ የወረደው ሊመሰክርለት እንጂ ኃይል ሊሠጠው ስላልነበረ ነው:: ዛሬ ግን ለሐዋርያቱ ኃይል ሊሠጣቸው ፈልጎ በእሳትና በነፋስ ኃይሉን ገለጠ::
መንፈስ ቅዱስ ሲወርድ በዚያ መገኘት ከፈለጋችሁ በቅዳሴው መካከል ተገኙ:: ካህኑን "ይህች ቀን ምን የምታስፈራ ናት? ይህች ቀን ምን የምታስጨንቅ ናት? መንፈስ ቅዱስ ከመልዕልተ ሰማያት የሚወርድባት?" ሲል ታገኙታላችሁ:: ኢሳይያስ ያየውን ራእይ ማየት ከፈለጋችሁ ወደ ቅዳሴ ገስግሱ:: ሱራፊ በጉጠት ፍሕም ይዞ ኃጢአታችሁን የሚተኩስበትን ደሙን ለመቀበል ከፈለጋችሁ ወደ ቅዳሴው ገስግሱ:: "ፈኑ ጸጋ መንፈስ ቅዱስ ላዕሌነ" እያላችሁ የምታዜሙበት ዕለታዊው ጰራቅሊጦስ ቅዳሴው ላይ ተገኙ:: በአዲስ ቋንቋ ትናገራላችሁ:: የእናንተ ቋንቋ ሳይቀየር የሁሉም ቋንቋ ተናጋሪ ሰምቶ ይረዳችሁዋል::
ለሐዋርያት የተሠጠኸውን ሠጥተኸን ከሐዋርያት ያገኘኸውን ያላገኘህብን ሆይ ቅዱስ መንፈስህ ከእኛ አትውሰድብን:: የማዳንህን ደስታ ሥጠን:: በእሺታም መንፈስ ደግፈን::
ዲያቆን ሄኖክ ኃይሌ
ጰራቅሊጦስ 2016 ዓ.ም.
ዳላስ ቴክሳስ