በኦሮሚያ ክልል ምዕራብ ወለጋ ቤጊ ወረዳ 42 የጤና ተቋማት መዘረፋቸውን ተከትሎ አግልግሎት ማቆማቸው ተገልጿል።
100 ሺሕ የሚገመቱ ነዋሪዎች ባሉበት የቤጊ ወረዳ አብዛኛው የጤና ተቋማት በመዘረፋቸውና በመጎዳታቸው፤ አስቸኳይ ሕክምና የሚፈልጉ እንዲሁም ለሕይወት አስጊ የሆኑ የጤና እክሎች ያጋጠማቸው ታካሚዎች አገልግሎት እንዳያገኙ አድርጓል ሲል ዓለም አቀፉ የቀይ መስቀል ማህበር አስታውቋል። ለአብነትም በዚያው አካባቢ ከአምስት በላይ ወረዳዎችን ያስተናግዳል የተባለው የጉዱሩ የመጀምሪያ ደረጃ ሆስፒታል ግድግዳው በጥይት መመታቱና የዉኃ ማጠራቀሚያ ገንዳው ጉዳት የደረሰበት መሆኑ የተገለጸ ሲሆን፤ አልጋዎች፣ የቀዶ ሕክምና መሳሪያዎች፣ መድሃኒቶች እና አምቡላንሶችም መዘረፋቸው ተመላክቷል።
የሆስፒታሉ ሜዲካል ዳይሬክተር ኹሉም መድኃኒቶችና ቁሳቁሶች መወሰዳቸውንና የድንገተኛ መድኃኒቶች እጥረት መኖሩን ጠቅሰው፤ ምንም ዓይነት የቀዶ ጥገና ክፍል አለመኖሩን እንዲሁም በውሃ ማጠራቀሚያ ገንዳው ላይ በደረሰው ጉዳት የውሃ አቅርቦት እጥረት መኖሩን ተናግረዋል።
በተመሳሳይ በተለያዩ አካባቢዎች ተፈናቅለው በሺዎች የሚቆጠሩ ዜጎች ወደ ከተማ ሲገቡ የሕክምና ፈላጊዎች ቁጥር በከፍተኛ ሁኔታ የሚጨምር ቢሆንም፤ አገልግሎት በቀላሉ ማግኘት የማይችሉ መሆኑ ነው የተገለጸው።
በክልሉ እየተካሄደ ያለው ግጭት ወሳኝ የሆኑ መሰረተ ልማቶች ላይ በተለይም የጤና እና የውሃ ተቋማት ላይ ከፍተኛ ጉዳት ማድረሱም ተነግሯል።
ዓለም አቀፉ ቀይ የመስቀል ኮሚቴ ከኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማኅበር ጋር በመተባበር በኦሮሚያ ክልል ምዕራባዊ ክፍል ሥራውን ቢቀጥልም ችግሮችን ለመፍታት በርካታ ፈተናዎች እንዳሉበት ተመላክቷል።
በአካባቢው ራሱን የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት ብሎ በሚጠራውና በመንግሥት ኦነግ ሸኔ በሚል በአሸባሪነት የተፈረጄው ታጣቂ ቡድን በሚሰነዝረው ጥቃት፤ እንደ ቡቡል፣ ቤጊ፣ ኮንዶሌ፣ ባሎ፣ ባሬዳ እና ኮምቦልቻ ያሉ አካባቢዎች ክፉኛ ጉዳት የደረሰባቸው መሆኑ የተገለጸ ሲሆን፤ የሰብአዊ ድጋፍ አቅርቦት እጥረት መኖሩም ተጠቁሟል።