=====================================
ሳተናው!
አንድ ወንድምህ በፈተና ተንጦ፣ በንባብ ረግቶ፣ በልምድም በስሎ ያገኛቸውን መራር ሐቆች በምክር መልክ አቅርቦልሃል፤ አንተ ግን በወደድከው ኑር!
ይህ ብዙም ጠልቀን የማንሄድበት የፍኖተ-አባወራ ሥልጠናን ግማሽ የሚወስደው የምስኪን ጠባዕያት ትንታኔና ማብራሪያ ላይ የሚገኝ ነው።
ምስኪን እውነትን ይዞ፣ በስልትና በአመክንዮ ሞግቶ፣ ልምዱንም ተንተርሶ፦ ራሱን ችሎ ከመቆም ይልቅ የሰው ስሜት አድማጭ፣ ጠባቂ፣ ጠንቃቂ ነው።
ይህንንም ደግሞ "ጥሩ ሰው ኹን፣ መልካም ሰው ኹን፣ መንፈሳዊ ሰው ኹን..." በሚባሉ የምክርና አንዳንዴም የሽንገላ ቃላት ከቤት እስከ ሰንበት ትምህርት ቤት(ቤተክርስትያን) ድረስ በማኅበረሰቡም እየተመከረ በተለይ በቤተሰቡ ይበልጡንም በእናቱ ማስጠንቀቂያ ያደገበት ነው።
ስለኾነም እርሱ የእኔ የሚለው፣ ደረቱን ነፍቶ የሚያውጀው፣ በቃላት ገልጦ የሚናገረው፣ በምክንያትና ስልት ሞግቶ፦ የሚቆምለት፣ የሚኖርለትና የሚሞትለት የራሱ የስሜትም ኾነ የፍላጎት እንዲሁም የአቋም ብያኔ የለውም።
ይልቁንስ እንዳደገበት "ጥሩ ሰው፣ መልካም ሰው፣ መንፈሳዊም..." ለመባል የሌሎችን ስሜት ሲያዳምጥ፣ ሲከተል፣ ሲያነሳና ሲጥል ይኖራል።
ለዚህም ነው "ምስኪን የስሜት ልክስክስ ነው" የምለው! እኔ ልጆቼ እንኳን ወንዶቹ ሴቶቹም የስሜት ልክስክስ እንዲኾኑ አላበረታታም! እንደውም እንዲጥሉት እሞግታቸዋለሁ እንጂ እነርሱም እንደዚሁ!
ወንድምዓለም! ምስኪን "ጥሩ፣ መልካምና መንፈሳዊ ሰው" ኾኖ እንዲታይ እንዲያም ይባል ዘንድ የሰውን ስሜት በተለይም የሴቶችን መስማት፣ መከተልና መጠበቅ ጠባዩ ነው።
ልብ አድርግ! ይህ የወንድ ባሕርይ አይደለም! በጭራሽ! ነገር ግን እርሱ የአስተዳደግ በደል አለበትና እንዳደገበት "የጥሩ ሰው፣ መልካም ሰው ኹን አደራህን እንዳታሰድበኝ እንዳታሳዝነኝ" በሚሉ፤ በተለይ የእናት ማስጠንቀቂያ የተነሳ ሰውን ላለማሳዘን ራሱን ረስቶ፣ አቅሉን አጥቶ፣ ሕሊናውን ክዶ እንዲህ ይኾናል።
ስለኾነም በሰዎች ዘንድ ለመወደድ በተይም በሴቶች ዘንድ ተቀባይነትን ለማግኘት ወደ እነርሱ የስሜት ሞገድ ቀርቦ፣ ስሜት ለስሜት ተናቦ፣ ይገናዘባል።
በአጭሩ ምስኪን ሴቶችን በጠባይ፣ በመናበብና በመገናዘብ ይመስላቸዋል። ይህ ጠባዩ በሴቶች ዘንድ ቢያስወድደውም ቅሉ እንደ ታናሽ ወንድም ቢያስቆጥረው ቢያስመርጠው እንጂ እንደ ባል በተለይም እንደ አባወራ አያስከጅለውም አያስከብረውምም!
ይኹን እንጂ ከአባወራው ወንድ ይልቅ ምስኪኑ ቁጭ ብሎ ውሎ አድሮም ቢኾን የሴቶችን ሮሮ፣ ወሬ፣ ብሶት፣ ለቅሶ፣ ክስ፣ ጨዋታ፣ ፌዝ ለመስማት ፈቃደኛ ነው።
እነርሱም እንዲህ ያለው ጉዳይ ሲገጥማቸው ከአባወራው ወንድ ወይንም ባላቸው ይልቅ ምስኪኑን ይመርጣሉ፤ የቀደመው ለዚህ ጊዜና ቦታ እንደሌለው ያውቃሉና።
ታዲያ የምስኪን ልክስክስነት በዚህን ጊዜ ይመጣል! ሴቷ ከአባወራው ባሏ ያጣችውን፣ የተከለከለችውን፣ የነፈጋትንም እርሱ ምስኪኑ ሊሰጥ በዚያም ውዳሴና ይኹንታ ቀለቡን ሊሸምት ይቀርባል።
ከሰው ሚስት እየደረሰ "እሺ...፣ እና....፣ ኧረ ባክሽ...፣ አትዪኝም...፣ አያደርገውም...፣ ሂጅ.. ሂጅ...፣ ጉድ እኮ ነው...፣ ሄኖክን ሳውቀው እኮ እንዲህ አልነበረም፣ ይገርማል፣ እንግዲህ ውጊያ ነው፣ መስቀል ነው ተዋጊ፣ አይዞሽ፣ አንቺ ጥሩ ሴት ነሽ፣ በዚያ ላይ የተማርሽ ኮሌጅ የበጠስሽ፣ በእርሱ ላይ መንፈሳዊነት የደረብሽ....." ይላል።
ሊረዳት ቢፈልግ እንኳ አንድ ቀን ጨክኖ ባሏን "ለምን እንዲህና እንዲያ ኾነ?" ብሎ መጠየቅ አይችልም። ያውቀዋላ የራሱን ስሜታዊነት፤ እርሱና እርሷ "ግትር" የሚሉትን የባሏን ስልታዊና ምክንያታዊነት።
እርሷም "እንቶኔ አንተ ባትኖር ለማን እተነፍሳለሁ፣ የውስጤን ስለምትረዳኝም አመሰግናለሁ፣ አንተን የሰጠኝም......." ስትለው የተራበውን ምግብና፣ የፈለገውን ቀለቡን፣ የናፈቀውን ማዕዱን ያገኛል፤ በዚህም ደስስስስ ይለዋል! ምስኪን ነዋ!።
ለምን መሰላችሁ እርሱ እንደ አባወራው ወንድ ወደ ተፈጠረለት ልዕልና፣ ወደ ወንድነቱ ቁና ይወጣ ዘንድ ራሱ ላይ መጨከን አይችልም፤ አይፈልግምና!
ይህንን እኔ የምስኪን ልክስክስነት እለዋለሁ! እንደ ሴሰኛው ሴቷን እስኪተኛት፣ አንድቀንም እስኪማግጥ ያውም፣ እረፍት ለማታገኝበት፣ ትርፉም ጸጸት ብቻ ለኾነበት .....
ስንት ሴቶች በእንዲህ ያለው ምስኪን ልክስስነት ትዳራቸው ፈረሰ፣ ቤተሰባቸው ተበተነ፣ ልጆቻቸውም.... አይ! ምስኪን ልክስክሱ!
"እኔ እኮ ከባሌ ይልቅ እንቶኔ የምለው ሳልናገር ይገባዋል፣ ብነግረው ይረዳኛል፣ እንዳው ሚስቱ ታድላ..." የሚሉ ሴቶች፣ የሚባልላቸው ወንዶችስ አልገጠሟችሁም።
አዎን! እንግዲህ እነ "እንቶኔ" የስሜት ልክስክስ መኾናቸው ነዋ! አንተም ብትኾን ያው ነህ! ይኹንታና ውዳሴ ቀለቡ ምስኪን ከሰው በተለይም ከአባወራው ሚስት ደርሶ አድማጭ ኾኖ በስሜት የሚልከሰከስ እንዲህ ነው!
ሴሰኛ ከስሜት ቀጥሎ፣ ስሜትን ጨምሮ አንድም በስሜት መልከስከስ ላይ የወሲብ ልክስክስነትን የደረበ ወራዳ፣ ውርደቱንም ከከብር የቆጠረ ነው!
ጉዳዩ ሰፊና ጥልቅ ነው! በተለይ በነገው የፍኖተ-አባወራ ሥልጠናችን ላይ ፦ የምስኪን ሐተታና የጠባያቱ ትንታኔን በጥልቀት እናየዋለን!
ዛሬ በማኅበረሰባችን በተለይም በቤተክርስትያን የምናየው የምስኪን ብዛት፣ የትዳራችን ፈተና፣ የማኅበረሰባችን ውድቀት የእነዚህና ሌሎችም ድምር ውጤት ነውና!