ሀጢዓቴ በዝቶ መቆም አቅቶኛል
እባክህ ደግፈኝ ምህረትህ ያሻኛል
ባልተፈታው ኑሮ የሕይወት ቋጠሮ
ጓዳዬ ሚስጥሬ ሁሉ ተበርብሮ
ከሀጢዓት በቀር ዱብም የሚል ጠፋ
አንድስንኳ ሳይኖር የሚሰጠኝ ተስፋ
አንዲት ጽድቅ አጣሁኝ አንዲትም ጠብታ
ህይወቴን የሚያድስ የሚሰጠኝ ደስታ
እባክህ መልሰኝ ቤትህ ይሻለኛል
የዚህ ምድር ኑሮ አለም ሰልችቶኛል
ለነገሩ አለም ሰለቸሁት እንጂ ከቶ አልሰለቸኝም
ምክንያት ይሁነኝ እንጂ...ማራኪ ናት አለም
በፍጹም ትህትና ምኞት ተቀብላ
ከሀጢአት ማህደር "ተቃመሰኝ" ብላ
የሀሰት ጣዕሟን የወይን ዘለላ
ከቋጠሮው ስንቋ ለኔም አከፋፍላ
ጊዝያዊትን ደስታ ፌጭታና ዕልልታ
ላላስተዋለ ልብ ገበታን ዘርግታ
የህይወት ወላፈንን አሰባጥራ
አዘበራርቃብኝ የኑሮዬን ዳራ
አለም ብልጣ ብልጦ ጉድ አደረገችኝ
ባዶዬን ላከችኝ እያየሁ አፍዝዛኝ
በአስመሳይ ገጽታ እኔነቴን ሸንግላ
የጣዕምን ጭምብል አጥልቃ...አድርጋኝ ተላላ
ታድያ ጥፋት ያለው እኔጋ ነው እሷጋ?
እጅ እግሬው ቀላቅሎኝ ከስህተቷ መንጋ
ጭለማን ካባዬ መሸሸግያ አድርጌ
የሀጢዓት ጉራንጉሩን እኔው ፈላልጌ
ስንት ጉድ ሰራሁኝ በገዛ እጅ እግሬ
እያገዘኝ ሰይጣን አባ ጋሽ አጅሬ
ይሄም የኔው ወሬ
ምክንያት እንዲሆነኝ እውነትን ቀብሬ
በእርሱም አልፈርድም አሳሳተኝ ብዬ
እራሴን ሰጥቼው ወጥቼ ከአንድዬ
ሰይጣንም ደስ አለው ሰጠኝም ፈተና
ኋላ እራሴው ወደቅኩ ቁርጥምጥም አልኩና
ይኸው የሀጥያት ጽዋ ትንሽ ቀመስኩና
በደጅህ ወደቅኩኝ መጣሁ እንደገና
የፍቅር እናት ማርያም "ልጄ" እንድትለኝ
"እባክሽ እናቴ እቀፊኝ" እያልኩኝ
ማለድኳት ተማልዳ እንድታማልደኝ
ወደ አባቴ ቤት እንድትመልሰኝ!
ወስብሐት ለእግዚአብሔር
ያለፈው ዘመኔ ይበቃኛል/2×/
በአምላክ መታመኔ ይሻለኛል/2×/
እግዚአብሔር የንስሀ ልቡና ይስጠል
👆👆