መስቀላቸውን በግንባራቸው አድርገው፤ “በል እንግዲህ የፈለከውን አድርግ” በማለት ተናገሩ። ወዲያውኑ የወታደሮቹ አዛዥ የተኩስ ትዕዛዝ ሰጠ። ከእነ አቡነ ሚካኤል እና ከአርበኞች ፊት ለፊት በተርታ ተደርድረው ጠመንጃቸውን ያነጣጠሩት የጠላት ወታደሮች የእሩምታ ተኩስ ተኮሱ። ብፁዕነታቸውና ሁለቱ አርበኞች በተተኮሰባቸው ጥይት ተመተው ወደቁ። ብፁዕነታቸው ኅዳር ፳፭ ቀን ፲፱፻፳፱ ዓ.ም. በፋሽስቱ እጅ በመትረየስ ጥይት ተደብድበው ለእናት ሀገራቸው ለኢትዮጵያ የነፃነት ታጋይ አርበኛ መሆናቸውን አስመስክረው ሰማዕትነትን በመቀበል ሕይወታቸውን አሳልፈው ሰጡ፡፡ስዊድናዊው ኮሎኔል ካውንት ካርል ስለ ብፁዕ አቡነ ሚካኤል ሲናገር፤
“ብፁዕ አቡነ ሚካኤል ከማልዘነጋቸው ቆራጥ ኢትዮጵያውያን አርበኞች አንዱ ናቸው፡፡ ጳጳሱ በሞት ፊት ያሳዩት ድፍረት እና የሀገር ፍቅር ስሜት ምንጊዜም አይረሳኝም፤” በማለት ገልጿቸዋል፡፡ የቀብራቸውም ሥነ ሥርዓት በአግባቡ አልተፈፀመም ነበር። አቶ ወልደ አብ የተባሉ የአገር ፍቅር ያደረባቸው የአካባቢው ነዋሪ በሌሊት ተነሥተው ቀበሯቸው። ብፁዕ አቡነ ሚካኤል ከተረሸኑ በኋላ አጽማቸው ከነበረበት አልባሌ ሥፍራ ተለቅሞ በሣጥን ተደርጎ፣ በጎሬ ደብረገነት ቅድስት ማርያም ቤተክርስቲያን በክብር የተቀመጠው፤ ጠላት ከሀገር ተባሮ ነፃነት ከተመለሰ ከ1935 ዓ.ም. በኋላ ነው፡፡
የሰማዕትነት መታሰቢያ
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ ለጎሬው ብፁዕ አቡነ ሚካኤል ቅድስናን ሰጥታለች፡፡ ግንቦት ፲፬ ቀን ፳፻፰ ዓ.ም. መሥዋዕት በሆኑባት ጎሬ ከተማ በሚገኘው በደብረ ገነት ቅድስት ማርያም ቤተ ክርስቲያን ደጀ ሰላም ውስጥ ሐውልት ቆሞላቸዋል፡፡ በጎሬ ከተማ ውስጥ በ፲፱፻፷ ዓ.ም. በስማቸው የተቋቋመው አቡነ ሚካኤል አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት፤ በማስታወሻነት ተገንብቷል።
የኢሊባቡር ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ የነበሩት ብፁዕ አቡነ ቄርሎስ የአቡነ ሚካኤልን ፎቶ ግራፍ ከግብጽ አሌክሳንድርያ አስመጥተው በጎሬ ከተማ ቅድስት ማርያም ቤተክርስቲያን ፊት ለፊት በሚገኘው አደባባይ ላይ ከ፲፱፻፶፪ ዓ.ም እስከ ፲፱፻፷፯ ዓ.ም ድረስ በመስታወት ውስጥ አስቀምጠውት ነበር። በደርግ አስተዳደር ወቅትም በቦታው መንገድ አቋርጦ ያልፍበታል ተብሎ ፎቶ ግራፋቸው እንዲነሣ ተደረገ።
የሰማዕቱ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ሚካኤል የምስክርነት ሐውልት ግንቦት ፲፬ ቀን ፳፻፷ ዓ.ም. በብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወእጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት፣ ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት፣ የአርበኞች ማኅበር ፕሬዝዳንት፣ ማኅበረ ካህናት እና ማኅበረ ምእመናን በተገኙበት ሰማዕትነትን በተቀበሉበት በጎሬ ከተማ ተመርቋል፡፡
ምን እናድርግ?
ሰማዕተ ጽድቅ ብፁዕ አቡነ ሚካኤል በፋሺስት ኢጣሊያ እጅ ለቅድስት ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያንና ለኢትዮጵያ ፍቅር በጠላት ጥይት ተደብድበው የተገደሉ የሀገር ባለውለታ ናቸው፡፡ ይሁንና እኒህ ሰማዕት በሀገር አቀፍ ሰደረጃ ሲወሱ አይታይም፡፡ በዓለማችን ላይ በርካታ ሀገራት ለራሳቸው ታላላቅ ሰዎች ሐውልት ያቆማሉ፣ መንገድ ይሰይማሉ፤ ይህን የሚያደርጉት ሌሎች ታላላቅ ሰዎች እንዲፈጠሩ ለማበረታታት ነው፡፡ በእኛ ሀገር ግን ያለውን ሁኔታ ስናይ ከዚህ ተለየ ነው፡፡
እኚህን ታላቅ ለሀገርና ለቤተክርስቲያን ሲሉ ሰማዕት የሆኑ አባትን ስንቶቻችን እናውቃቸዋለን? ስንቶቻችንስ ታሪካቸውን ጠንቅቀን እናውቃለን? በሀገር አቀፍስ ደረጃ የሚታወሱበት ምን ተሠራላቸው? ይሄ የሁላችንም ጥያቄ ሊሆን ይገባል፡፡
የኢሉባቦር ሀገረ ስብከት ሰማዕቱን ለማዘከር የአቅሙን ያህል እየሠራ እንደሚገኝ ይታወቃል፡፡ ሊቀ ትጉኃን ብርሃኑ መንገሻ እንደጸናገሩት የሀገረ ስብከቱ ዋና ሥራ አስኪያጅ እንደተናገሩት “ሰማዕቱ ብፁዕ አቡነ ሚካኤል በዓለም አቀፍ ደረጃ በታሪክ ቢታወቁም፤ በሀገር አቀፍ ግን ብዙ አልተነገረላቸውም፤ ስለዚህ ትውልዱ ትኩረት ሰጥቶ ሰማዕቱ የሚዘከሩበትን ሥራ መሥራት ይገባል” ብለዋል፡፡ ብፁዕ አቡነ ኤውስጣቴዎስ (ዶ/ር) የኢሉባቦር ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ እንደተናገሩት “ለቤተክርስቲያን ሲሉ ሰማዕቱ ብፁዕ አቡነ ሚካኤል ሰማዕት የሆኑት ለሁሉም ኢትዮጵያውያን ነው በሀገር አቀፍ ደረጃ ሊዘከሩ ይገባል” በማለት አብራርተዋል፡፡ ቅዱስ ሲኖዶስም የሰማዕቱን ጉዳ ትኩረት በመስጠት አርበኞች ማኅበር፣ ሀገር ወዳድ ኢትዮጵያውያን ሁሉ የሰማዕቱ ብፁዕ አቡነ ሚካኤል በሀገር አቀፍ ደረጃ እንዲዘከሩ ማድረግ ይገባል እላለሁ፡፡ እናንተስ ምን ትላላችሁ?
የሰማዕቱ ብፁዕ አቡነ ሚካኤል ረድኤትና በረከት ይደርብን