በመላእክት ከተማ በራማ ካሉት ሦስት ነገዶች ውስጥ አንዱ ነገድ ሥልጣናት ይባላል፡፡ በሥልጣናት ላይ ከተሾሙ ሊቃነ መላእክት ውስጥ አንዱ ሊቀ መላእክት ቅዱስ ሱርያል ይባላል፡፡ ሱርያል የሚለው ስም በአንዳንድ ድርሳናት ካልሆነ በስተቀር እምብዛም አይታወቅም፡፡ ትርጉሙም ‹‹ዐለቴ እግዚአብሔር ነው›› ማለት ነው፡፡ ሱርያል የቅዱስ ዑራኤል ሌላ ስሙ ነው፡፡ በቤተ ክርስቲያንም በስፋት የሚተወቀው ስም ዑራኤል የሚለው ስም ነው፡፡ [ድርሳነ ዑራኤል 1991 ገጽ 14]
ዑራኤል ማለት “ብርሃነ እግዚአብሔር” ማለት ነው። “ዑራኤል ሥዩም ላዕለ ኵሎሙ ብርሃናት፤ ዑራኤል በብርሃናት ላይ ሁሉ የተሾመ ነው” እንዲሁም “ዑራኤል አሐዱ እመላእክት ቅዱሳን እስመ ዘረዓም ወዘረዓድ፤ ከቅዱሳን መላእክት አንዱ ዑራኤል በመብረቅና በነጎድጓድ የተሾመ ነው” እንዲል፡፡ [ሄኖክ 6፥2] ከሊቃነ መላእክት አንዱ መሆኑንና ፍርሃት ረዓድ ላለባቸው ረዳታቸው እንደሆነ የመላእክትን ነገር የተናገረ ሄኖክ ነግሮናል፡፡ “የእግዚአብሔር መልአክ በሚፈሩት ሰዎች ዙሪያ ይሠፍራል” በማለት ነቢዩ ዳዊት እንደተናገረ እግዚአብሔርን በሚፈሩና በሚያከብሩት ሰዎች ጭንቀት ጊዜ በመካከላቸው እየተገኘ ያጽናናቸዋል። [መዝ.33፥7]ምሥጢር ይገልጥላቸዋል፤ ከመከራ ሥጋ ከመከራ ነፍስ ይጠብቃቸዋል።
አንድም ዑራኤል የሚለው ስም “ዑር” እና “ኤል” ከሚሉ ኹለት ቃላት የተመሠረተ ነው። ዑራኤል ማለት ትርጉሙ “የብርሃን ጌታ”፣ ”የአምላክ ብርሃን” ማለት (እግዚአብሔር ብርሃን ነው) ማለት ነው። "በእግዚአብሔር ፊት የሚቆሙ 7 መላእክትን ዐየሁ" [ራዕ. 8፡2] እንዳለ ሊቃነ መላእክት በቊጥር 7 ናቸው። ቅዱስ ዑራኤልም ከ7ቱ ሊቃነ መላእክት አንዱ ሲሆን ከፍጥረተ ዓለም ጀምሮ በመብረቅና በነጎድጓድ ላይ የተሾመ መልአክ ነው። በመሆኑም መባርቅት ለጥጋብና ለበረከት እንዲበርቁ ነጎድጓድም ለሰላም እንዲሆን ያሰማራል። [መ.ሄኖክ. 6፥2] ምስጢረ ሰማይና እውቀትንም ኁሉ ለሄኖክ የገለጸለት የፀሐይን የጨረቃን የከዋክብትንና የሰማይ ሰራዊትን ብርሃንን የሚመራ እርሱ መሆኑን ለሄኖክ ነግሮታል። [መ.ሄኖክ 28፥13] “ቅድስት ድንግል ማርያምን፣ ከልጇ ከአምላካችን ከኢየሱስ ክርስቶስ ጋር ወደ ግብጽ ስትሰደድ መንገድ የመራ፤ ክርስቶስ ለዓለም ቤዛ በተሰቀለ ጊዜ፣ ክቡር ደሙን በብርሃን ጽዋ ተቀብሎ፣ በብርሃነ መነሳንስ በዓለም ላይ የረጨ፤ እውቀት ለተሰዎረባቸው ለነቢዩ ዕዝራ ሱቱኤል ጽዋ ጥበብን ያጠጣ፤ ኢትዮጵያዊውን ሊቅ አባ ጊዮርጊስ ዘጋስጫ መርካታ ቅዱሳት መጻሕፍትን አንዲደርሱ ያገዘ፣ የረዳና የዕውቀት ጽዋን ያጠጣ መልአኩ ቅዱስ ዑራኤል ነው፡፡
የመልአኩ ዓመታዊ ክብረ በዓላት
• ጥር 22 በዓለ ሲመቱ፣
• መጋቢት 27 የጌታችንን ክቡር የሆነ ወርቀ ደሙን ለዓለም የረጨበት ነው፡፡
• ሐምሌ 21 እና 22 ቅዳሴ ቤቱ የሚከበርበትና ለነቢዩ ዕዝራ ሱቱኤል የእውቀት ጽዋ ያጠጣበት ቀን ነው።
አፈቅሮ ፈድፋደ፡- ዑራኤል ሆይ፣ ከመልኮች ሁሉ ይልቅ ያንተን መልክአ ጸሎት እወዳለሁ፡፡ የመልክህ ስነ ጸዳል በደመ ወልድ እግዚአብሔር የታተመ ነውና፡፡
ዑራኤል ሆይ፣ እግዚአብሔር ኃይሉን የሚገልጽብን መልአከ ብርሃናት አንተ ነህ፡፡ በዕለተ ሥቅለት በደመ ወልድ ዓለምን ለመቀደስ ከሁሉ ይልቅ አንተ ተሰይመሃልና፡፡ ስለክብርህ የሰማይ መላእክት አደነቁ፡፡
ለተፈጥሮትከ፡-
ዑራኤል ሆይ፡- ያለ መናገር በጥንት አርምሞ ከነፋስና ከእሳት ለተፈጠረ ተፈጥሮህ ሰላም እላለሁ፡፡ ዑራኤል ሆይ የተፈጥሮና የይቅርታና የቸርነት ክቡር መልአክ ነህና ስለኛ ስለሰው ልጆች ወደ ልዑል እግዚአብሔር ማልድ አማላጅነትህ ዘወትር ከጥፋት ያድናልና፡፡
ለዝክረ ስምከ፡-
ዑራኤል ሆይ፡- ከማርና ከወተት ይልቅ ለሚጥመው ስም አጠራርህ ሰላም እላለሁ፡፡
ዑራኤል ሆይ፡- ክፍልህ /ክንፍህ/ በደመ ወልድ እግዚአብሔር የተከበረ /የታለለ/ ነውና፡፡ ለዓለሙ ሁሉ መድሃኒት ትሆን ዘንድ ግሩም የሚሆን የእግዚአብሔር ሥልጣን በክብር ከፍ ከፍ አደረገ፡፡ [መልክአ ዑራኤል]
በአምላኩ አማላጅነቱን ኑና ተማጸኑት። በጸሎቱ ለተማጸነ ከአምላኩ በረከትን ምህረትን የሚያሰጥ አዛኝ እርሩህ መልአክ ነው። የቅዱስ ዑራኤል በረከት በኁላችንም ላይ ይደር!! አሜን።
✥••┈••●◉ ✞ ◉●••┈••✥