ከቤልጂግ አሊ:
መቼም የጎረቤቶቼ ብዛት ሳይደንቃችሁ አይቀርም ። ጀርመን ከፍራንክፈርት ወጣ ብላ በምትገኝ ትንሽ መንደር ውስጥ ነው የምኖረው። እዚች ትንሽ ዝም ያለች መንደር ውስጥ ነው ግማሽ ሕይወቴን ያሳለፍኩት ። አቤት ጊዜው ሲሮጥ ! ሦስት አስርተ ዓመታት እዚህ ኖሮኩ ብል ማን ያምነኛል። ከመንደሯ ትንሽነት የተነሳ በኔ መንገድ አካባቢ ያሉትን ሰዎች በሌላ ቢቀር በዓይን አውቃለሁ።
ዛሬ የምተርክላችሁን ሰው የተዋወቅሁት አንድ ቀን የመኪናውን መብራት ረስቶ ገብቶ ጠዋት አልነሳ ቢለው እንድረዳው ጠይቆኝ ነው።ከዛ ሰላምታ አንዳንዴም ንግግር ተጀመረ ። ጥሩ ስለ አፍሪካ ዕውቀት ስለነበረው ደጋግመን እንጨዋወት ነበረ ። በኋላ ግን እየታመመ መጣ ። ከሚስቱ ጋ የሚደርጉት የእግር ጉዞ ቀረ ። ቤት መዋል አዘወተረ ። ሁል ጊዜ አብረው የነበረችው ሚስቱ ብቻዋን ትታይ ጀመር ። አለፍ አለፍ እያልኩ ስለጤንነቱ እጠይቃት ነበረ ። አንድ ቀን ስጠይቃት ማልቀስ ጀመረች ። እንደሞተ ነገረችኝ ።እኔም በጣም አዘንኩ ። ስለ ቀብሩ ስጠይቃት ካለኔ ሌላ ሰው እንዲቀብረው ስላልፈለገ እኔ ብቻ ነበርኩ አለች ። አይ የፈረንጅ ነገር አምስትና ስድስት ሆኖ መቅበርም ቀርቶ ብቻዋን ቀበረች ። መቼም አስከሬን የለ ያው አመድ አይደል ።
ባለፈው ሳምንት ሰፈራችን አይስ ክሬም የሚሸጥበት ቦታ ሚስቱን አገኘዃት። አሁን አርጅታለች ። የብቸኝነት ድካም ፊቷ ላይ በማየቴ አዘንኩ። ብቸኝነቱ እንዴት ነው? ብዬ ጠየቅሁ። የመለሰችልኝ ግን ከመደነቅ አልፎ አስደነገጠኝ ።
" እንደገና ተመልሼ ከእሱ ጋ ከሆንኩ በኋላ ብቸኝነት አይሰማኝም" አለችኝ ።
ጤንነቷን ጠረጠርኩ ። እንደገና እንዴት ? ብዬ ጠየቅሁ።
"እንደምታውቀው ሞቶ የተቃጠለን ሰው አመድ ወደ ቤት መውሰድ እዚህ ጀርመን ክልክል ነው። በዚህ ዓይነት ሆላንዶችና ሲዊሶች ከእኛ በጣም ይሻላሉ። እዛ እስከፈለከው ድረስ ቤትህ ማስቀመጥ ይፈቀዳል።"
"የኔ ባለቤት ከተቀበረ በኋላ በጣም የሚረብሸኝ ጉዳይ ነበረ ። ታውቀው የለ? ይኼ ከቤታችን በታች ያለው የመቃብር ቦታ ? ድሮ በዛ ሁል ጊዜ ስናልፍ ባለቤቴ ቦታውን ይጠላው ነበረ። እንዴት ሰውን ብቻውን እዚህ ጥለውት ይሄዳሉ ይለኝ ነበረ ። "
"ታዲያ አሁን ሁልጊዜ እዛ መቃብሩ ጋ ስሄድ ይለኝ የነበረው ሳስበው ረበሽኝ። አሰጨነቀኝ ። ቀኑን ሙሉ አብሬው ውዬ ማታ ወደ ቤት ስሄድ አትሂጂ፣ ለማን ጥለሽኝ ነው የምትሄጂው? ማንስ ይጠብቀኛል? የሚለኝ መሰለኝ። ጭንቀቱ ቢበዛብኝ መላ ፈለግኹ። አውጥቼ ወደ ቤቴ መውሰድ እንዳለብኝ ተሰማኝ ። መንገድ መፈለግ ጀመርኩ። በስዊስ ሕግ እንደምችል ተረዳሁ። ሲዊስ ባዝል ከተማ ያለ ኩባንያ ከመቃብር አውጥቶ ወደ ቤት ሊመጣልኝ ተስማማ ። ገንዘቤን ከፍዬ በጠርሙስ ያለውን የባሌ አመድ ቤቴ አስገባሁ። አሁን አብረን እንኖራለን ። ድሮ እንደምናደርገው እግር ኳስ ስንመለከት ቢራ ስለሚከፈት ሁለት ቢራ እከፍታለሁ ። አንዱን እኔ እጠጣለሁ የእሱን በኋላ አፈሰዋለሁ። "
"አሁን ብቸኝነት አይሰማኝም ። ከእሱም ወቀሳ ድኛለሁ። ኑዛዜዬ ላይ ስሞት አብረን እንድንቀበር ፅፌአለሁ። ያኔ እሱም እኔ ስላለሁ አይፈራም ። እኔም እሱ ስላለ ። እውነት የመቃብር ቦታ ያስጠላል አይደል?" አለችኝ ።
ቤቷ ወስዳ ከወዳጄ ጋር ልታገናኘን ቀጠሮ አለን ። እኔ ግን ማየት የምችል አልመሰለኝም ።
ቻናላችንን ለመቀላቀል https://t.me/lehulumbufe በሚለው ሊንክ በኩል ገብተው ጆይን ይበሉ!
ለሀሳብ አስተያየት ደግሞ @lehulum_1bot የሚለውን ይጠቀሙ!
ሼር ማድረጉም እንዳይረሳ!! kehulum lehulum bufe ከሁሉም
ለሁሉም ቡፌ