"አዲስ አበባን ቄራ አደረጓት"
የዕለቱን ሁኔታ ፕሮፌሰር ባህሩ ዘውዴ 'የኢትዮጵያ ታሪክ ከ1847 እስከ 1983' በሚለው መፅሐፋቸው እንዲህ ይተርኩታል።
" ... "ጥቁር ሸሚዝ" እየተባሉ የሚታወቁት የፋሽስት ደቀመዛሙርት በፋሽስቱ አገዛዝ አይዞህ ባይነት አዲስ አበባን ቄራ አደረጓት። የሠው ልጅ ጭንቅላት እንደ ዶሮ እየተቀነጠሰ ወደቀ። ቤቶች ከነነዋሪዎቻቸው ጋዩ። እርጉዝ ሴቶች በሳንጃ ተወጉ። የጭፍጨፋው ተቀዳሚ ዒላማ የተማሩ ኢትዮጵያውያን ነበሩ።
በተለይም የጥቁር አንበሳ አባላት ከራስ እምሩ ጋር እጃቸውን ከሰጡ በኋላ በከተማይቱ ይገኙ ስለነበር በወረንጦ እየተለቀሙ ተረሸኑ። ይህ የምሁራን ጭፍጨፋ አንድ ትውልድ እንዳለ ያጠፋ በመሆኑም በሃገሪቱ የፖለቲካና ምሁራዊ ታሪክ ላይ የማይሻር ቁስል ጥሎ አለፈ።"
በዚህ ዘግናኝ ጭፍጨፋ በሶስት ቀናት ውስጥ ብቻ ከ30 ሺህ በላይ ኢትዮጵያውያን መስዋዕትነት ተቀበሉ። በሌላ በኩል ይሄ ጭፍጨፋ ሲወላውል የነበረውን፣ መሃል ሠፍሮ የነበረውን፣ "ጣልያኖች ቢያስተዳድሩን ምን ችግር አለው?" ..... ይል የነበረውን ኢትዮጵያዊ በሙሉ ለአንድ ዓላማ አብሮ እንዲቆምና 'ዱርቤቴ' እንዲል ያደረገ ክስተትም ነበር።
#ክብር_ለሰማዕታት!