ወደ ግሎ ማክዳ ምድር እንዳደረሱት በዚያ ያሉ ቅዱሳን በደስታ ተቀበሉት፡፡ ስማቸውም ማርቆ፣ ክርስቶስ አምነ፣ አባ ሲኖዳና ማማስ ናቸው፡፡ ማማስም ለአባታችን ለጸሎት የሚሆነውን የድንጋይ ዋሻ አሳየው፡፡ አባታችንም ‹‹ይህች ዋሻ ለዘላለም ማረፊያዬ ናት›› ብሎ ውስጧን በድንጋይ ይወቅር ጀመር፡፡ በውስጧም አገልገሎቱን ፈጸመ፡፡ ወደ ቅዱሳኑ ወደ እነ አባ ማርቆስ፣ ክርስቶስ አምነ እና ሲኖዳ መጥተው የመቃብር ጉድጓድ እንዲቆፍሩ መልአክት ላከባቸው፡፡ በቀዳሚት ሰንበት ዕለትም ደቀ መዝሙሩ ዕንባቆም በአገኘውና ‹‹ነገ አባትህን ወደ መቃብር ትጥለዋለህ›› አለው፡፡ በማግሥቱም እሁድ ቀን ደቀ መዛሙርቱን ሁሉ ሲመክራቸው ዋለ፡፡ በመጨረሻም አንዱን ደቀ መዝሙሩን ብቻ አስከትሎ ወደ ዋሻዋ ግቶ በ4ቱም ማዕዘን ባረካት፡፡ ከዚህም በኋላ እጁንና እግሩን ዘርግቶ ነፍሱን በፈጣሪው እጅ አስረከበ፡፡ ነቢዩ ‹‹የጻዲቅ ሰው ሞቱ በእግዚአብሔር ፊት ክቡር ነው›› እንዳለ ያለ ምንም ጻዕር ዐረፈ፡፡ መዝ 115፡6፡፡
ደቀ መዛሙርቱም በመጡ ጊዜ ዐርፎ አገኙት፡፡ እነርሱም መሬት ላይ ወድቀው ‹‹አባት እንደሌላቸው እን ሙት ልጆች ለማን ትተወናለህ፣ በስውር የሠራነው ኃጢአትስ ማን ይነግረናል….›› እያሉ ጽኑ ልቅሶን አለቀሱ፡፡ አስቀደሞም እርሱ ደቀ መዛሙርቱ በስውር የሚሠሩትን ሥራ ሁሉ እርሱ በግልጽ እያየ ‹‹አንተ ይህን ሠርተሃልና ንስሓ ግባ›› እያለ ይመክራቸው ነበርና፡፡ ልቅሶአቸውንም ከፈጸሙ በኋላ ራሱ በጠረባት የድንጋይ ዋሻ ውስጥ ቀበሩት፡፡ የሀገሪቱም ሰዎች ክፉዎች ናቸውና ከጊዜም በኋላ ደቀ መዛመርቱ የአባታችች ዐፅሙን አፍልሰው ወደ ሌላ ቦታ አስቀመጡት፡፡ እስከ ኢትዮጵያ ጳጳስ አባ ያዕቆብ መምጣት ድረስ ደብቀው አኖሩት፡፡ አባ ያዕቆብም የአባታችንን ዐፅም ያመጡለት ዘንድ አዘዘቸው፡፡ ከጊዜም በኋላ ዐፅሙን ወደ ጋስጫ አፍልሰውታል፡፡ ይኸውም ጋስጫ ከሊቁ አባታችን ከአባ ጊዮርጊስ ዘጋስጫ ገዳም ሥር የሚገኝ ነው፡፡ ዋሻ ቤተ መቅደሱም በግሩም አሠራር የተሠራ ነው፡፡
የአቡነ በጸሎተ ሚካኤል ረድኤት በረከታቸው ይደርብን በጸሎታቸው ይማረን!
(ምንጭ፡- ገድለ አቡነ በጸሎተ ሚካኤል፣ የሐምሌ ወር ስንክሳር)