ኪነጥበብ ዘሰንበት ት/ቤት @sundayschoolstudents Channel on Telegram

ኪነጥበብ ዘሰንበት ት/ቤት

@sundayschoolstudents


የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ልጆች የሰንበት ት/ቤትና ግቢ ጉባኤያት መንፈሳዊ ግጥሞችን፣ መነባንቦችን፣ ትረካዎችን፣ ዜናዎችን ፣ደብዳቤዎችን፣ ድራማዎችን፣ እንቆቅልሾችን፣ አጫጭር ጭውውቶችን፣ እንካሰላንቲያዎችንና መንፈሳዊ ማስታወቂያዎችን... የሚቀርቡበት የሰንበት ት/ቤቶች የኪነጥበብ ቻናል ነው።

ኪነጥበብ ዘሰንበት ት/ቤት (Amharic)

ህወሓት፣ አገር፣ ምሕረት፣ መንግሥታዊ እና ሃምቢስ በታላቅ ተወዳጁበት ምላሽ ከሆነ ህዝባዊ እና ሊቀ ማክበረኛ ተማሪዎችን የማካበረኝና የማእጄን የተወያያዩ ፈሳሽ ተወካዮችን ከሚገልጽባት ሕገ-መንግሥት ለቤቱ ማሰራት ቅሬታና የፈሳሽ ተወካዮችን እንወስዳለን፡፡ nnአስመልክተን እኛ ንፁህ ተ/ቤቱን ታማኝን ት/ቤትን ለመናገር በጣም ይጠይቃል፡፡ ይህ ት/ቤት የህወሓትን መምህር ለማብራራት እንጠቀማለን፡፡ ስለዚህ በአገሮች መንገድ አሉት ለሰላም፣ ኣነጋራት ወደመቆራት ወደ ፍቅር ለመምለም በማደርግ እንደምንችልበት እና ለማፈጋገም እናመሰግናለን፡፡

ኪነጥበብ ዘሰንበት ት/ቤት

06 Feb, 02:43


++ ሥነጽሑፍ - ግጥም !
 
( ርዕስ - የንስሐ ግጥም )

አባ ስማ ድምፄን ደጅህ ቆሚያለሁኝ
የጠፋሁት ልጅህ በር እየመታሁኝ
በሀፍረት ታጥሬ እንደተሸማቀቅኩ
በፀፀት ታጅቤ እንደተኮራመትኩ
ከናፈቅኩት ቤትህ አይኔን እያማተርኩ
ቁጭ ብያለሁ ደጅህ አንተን እየጠበኩ
አባ ተመልከተኝ እንዲህ ተጎድቼ
የልጅነት መልኬን ወዜን ሁሉ አጥቼ
ካንተ የተቀበልኩት ጥሪቴን አጥፍቼ
በዚህች ወረተኛ አለም ተከድቼ
አዎን መጥቻለው ጉስቁልቁል እንዳልኩኝ
እርቃኔን ሳልሸፍን እንደተራቆትኩኝ
የህሊና እስረኛ መንገድ የጠፋብኝ
ሆኜ ቀርቻለው አለም ተጫውታብኝ
አባ ያንን ጊዜ ካንተ እንደተለየው
የዝ'ችን አለምን ጉድ ስንት ነገር አየው
ለካንስ እውነት ነው ምድር ከንቱነቷ
አያልቅም ተወርቶ ኮተታኮተቷ
አሳስቃ ወስዳ እያታለለችኝ
ይኸው አንገዋላ ከመንገድ ጣለችኝ
የምሸሸግበት ማርፍበት እስካጣ
ወዳጅ ተለውጦ እስኪሆን ባላንጣ
አይመስለኝም ነበር የጭካኔዋ ጥግ
አላስተዋልኳትም ያሻትን ስታደርግ
በርሀብ እና በጥም እየተሰቃየው
መሄድ እስኪያቅተኝ እየተንገላታው
የችግሬን ዳገት ብቻዬን ስገፋው
አልደረሰልኝም ወዳጅ ያልኩትም ስው
ግን ጥርሴን ነክሼ ሰው ለመሆን ዳግም
ስቃይ ያደቀቀው ማንነቴን ላክም
በጉልበቴ ድኼ እንዲያ ስፍገመገም
ያን ጊዜ አየሁት ፊት ለፊቴ ሲቆም
ትንሿን ተስፋዬን ድጋሜ ሊያጨልም
ለካን ውሸት ኖሯል ፍቅራችን የይምሰል
ለካን ለጌጥ ሆኗል የለበስነው መስቀል
ይሄኔ ነው ታዲያ ልቤ ቤትህን ናፍቆ
ይቅርታ ሊጠይቅ ከእግሮችህ ስር ወድቆ
የመጣው በድፍረት ተስፋውን ሰንቆ
አባ አደራህን እንዳትጨክንብኝ
በርህን ለመክፈት እንዳትዘገይብኝ
በመከራ ምክር  በጣም ስለደከምኩ
መኖር መርጫለው ለአንተ እያገለገልኩ
እንጂማ ከእንግዲህ ሌላም እቅድ የለኝ
አባ ቶሎ መተህ እንዳረከኝ አርገኝ
ወዲህ ወዲያም ሳልል ቆሚያለው በርህ ላይ
በይቅርታ አይኖችህ ዳግም እስከምታይ
ፈራ ተባ እሚለው ልቤን እየሞገትኩ
እስካሁን በርህ ለይ እንደተኮራመትኩ
ቁጭ ብያለው እና አንተን እየጠበኩ
አባ ናልኝ ባክህ ኧረ እኔስ ተጨነኩ
አንዴ ብቻ መተህ በሩን ከፍተህ ካየህ
በልጅህ መሰበር ስንቱን ታስባለህ
ግን አንድ እውነት እውቅ ከመምጣትህ በፊት
በርህን ደብድቤ ብጣራም በድንገት
አጥፍቼው ብመጣም ያንን ሁሉ ንብረት
ገንዘብ የማይገዛው ልብን ገዝቻለው
ከትናንቱ ግብሬ ዛሬ ተሽያለው
ስለዚህ ስትመጣ በሩን ልትከፍትልኝ
በዛሬ እኔነቴ እንድትቀበለኝ
ከቤት አስገብተህ አገልጋይህ አድርገኝ
ልጅህ ልባል እንደው አልሻም ከ'ንግዲህ
አገልጋይህ ሆኜ ልሩጥ ወዲያ ወዲህ
አዎን አባ መጥተህ በሩን ስትከፍትልኝ
አልሻም ድጋሜ
የአባትነት ዋጋን እንድትከፍልልኝ
ከቤታችን ካሉት ከአገልጋዮች ጋራ
እንድትፈቅድልኝ አብሬ እንድስራ
እለምንሀለው እሺ በለኝ  ባክህ
ያንን የትናንቱን ደጉን ቀን አስብህ
እንጂማ እንደግብሬ እንደ'ኔማ ቢሆን
አንተን ባለፈለኩህ ወዳጁ አውሬ ሲሆን
በቃኝ ስልችቶኛል ደክሞኛል እንግልት
በደንብ ገብቶኛል የምድር ከንቱንት
ላልመልሰው ፊቴን እርም ይሁን ብያለው
ቤትህ ነው አለሜ አባ ተምሪያለው!!!

======///========

ለሁላችንም መሃሪ ይቅር ባይ አምላካችን ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ለንስሐ ሞት ያበቃን 🙏

ወስብሐት ለእግዚአብሔር
ወለወላዲቱ ድንግል
ወለመስቀሉ ክቡር ይቆየን !

የኪነጥበብ ቤተሰብ ይሁኑ !
@sundayschoolstudents
የሰንበት ት/ቤት ኪነጥበብ ክፍል !

ኪነጥበብ ዘሰንበት ት/ቤት

28 Jan, 06:36


++ ስነጽሑፍ - ዘአስተርዮ ማርያም !

  ( ርዕሰ - አስተርዕዮ ማርያም )

አስተርዮ ማርያም ስልሽ ደስ ይለኛል
የመገለጥ ሚስጢር ተከናውኖልኛል
ገና ልጅም ሆኜ አስተርዮ ሲባል
እሰማ ነበረ እስኪደርስ ያጓጓል፡፡
አሁን ትልቅ ሆኜ ታሪኩ ሲገባኝ
ለካስ እናቴ ነሽ አምላኬ የሰጠኝ
የመድሃኔ ምክንያት ተስፋዬ የሆንሽኝ፡፡
የሆነውም ሆነ እሱ የወሰነው
የአምላክ እናት ሆነሽ ሞትን እንድትቀምሽው፡፡
የአዳም ልጆች ጠላት አስደናቂው ሞትም
ወረደ ወደ አንቺ ግዳጁን ሊፈጽም
እረፍት እንጅ ላንቺ ሞት ባይስማማሽም፡፡

ሞተች ሲባል ሰምተው የአንቺ ጠላቶችሽ
መጡ ከያሉበት በእሳት ሊያቃጥሉሽ፡፡
መሆንሽን እረስተው የፈጣሪ እናት
ክብር እንደ መስጠት በስተት ላይ ስህተት፡፡
ነገሩንም ጭረው ወደ ኀላ ሲሉ
ቅደም ታውፋንያ አንተ ጀግና እያሉ
ታውፋንያ ሞኙ በእሳት ሊያቃጥላት
የተዘጋጀውን ስጋዋ እንዲያርፍበት
የአልጋውን ሸንኮር ሲነካ በድፍረት
ምንም ሳያስበው መላኩ በቅፅበት
ሁለቱን እጆቹን በሰይፍቆረጠለት፡፡
ይህ ነው መጨረሻው ማን አለብኝ ማለት
ያ ሁሉ ፉከራ መሬት ገባ ድንገት
አይ የሰው ልጅ አቅም ያሳዝናል በእውነት፡፡

እጆቹንም ሲያጣ ጀግና የተባለው
የቀረው አማራጭ ወደ እሷ ማልቀስ ነው
እጆቹ እንዲድኑም አማልጅኝ ማለት ነው፡፡
እሱ መቼ አወቀ የእሷን ሕያው መሆን
ሞተች ሞተች ሲሉ ሲሰማ ወሬውን
መጣ እንጅ ዝም ብሎ ሊያቃጥል ስጋዋን፡፡
የእኛም እናት ድንግል የማታሳፍረው
የሞተች ብትመስልም ህያው የሆነችው
አማላጅነቷን አሳየችው ወዲያው እጆቹን ቀጥላ ስለ ሆኑህያው፡፡
እንዲህ ናት የእኛ እናት ጠላቶቷን የማትወድ
ማርያምን ይወቃት የማያውቃት ትውልድ
በጦር የወጋውን አይኑን እንዳበራ
ልጇ መድሃኔ አለም
ልጇ እንዳደረገ አደረገች እርሷም፡፡
ስሟ ማር ወለላ ፍቅር ናት የእኛ እናት
የማያውቅ ይወቃት የሚያውቅም ያክብራት።

======///========

ልደትን በላሊበላ፤ ጥምቀትን በጎንደር ደምቀው እንደሚከበሩ ሁሉ “አስተርዕዮ ማርያም” ደምቀው ከሚከበርባቸው ገዳማት አንዷ “የርዕሰ ርዑሳን መርጡለ ማርያም ገዳም” ናት። ኑ! አስተርዕዮን በርዕሰ ርዑሳን መርጡለ ማርያም ገዳም ታከብሩ ዘንድ ተጠርታችኋል!!

የተወደዳችሁ የኪነጥበብ ቤተሰቦች፥ እንኳን ለበዓለ አስተርዕዮ ማርያም (ለእመቤታችን እረፍት) አደረሳችሁ አደረሰን 🙏

የኪነጥበብ ቤተሰብ ይሁኑ !
@sundayschoolstudents
የሰንበት ት/ቤት ኪነጥበብ ክፍል !         

ኪነጥበብ ዘሰንበት ት/ቤት

27 Jan, 19:30


++ ስነጽሑፍ - ግጥም !!

( ርዕስ - በሃይማኖት ጽና )

ልብ ያለህ አስተውል ጆሮ ያለህ ስማ፣
እግርህ እንዳይገባ ከክህደት ከተማ።
የያዝከውን አጽና ልብህ አይጨነቅ፣
ለጥያቄህ መልስም ሊቃውንትን ጠይቅ።

ለእውነት የቆመ ሃይማኖቱን የሚያውቅ፣
ንባብ ትርጓሜን ጠንቅቆ የሚዘልቅ፣
ተናገር ዩሐንስ አንተ ልሳነ ወርቅ።
ቄርሎስን ጠይቀው የተዋህዶን ምስጢር፣
የክርስቶስ ነገር እንዴት እንደነበር፣
ከብሉይ ከሐዲስ በማቀነባበር፣
እንዳመሰጠረው በብዙ ምስክር።

ነቢዩ ኢሳያስ ብርሃነ ዓለም ጳውሎስ፣
መዝሙረኛው ዳዊት ሐዋርያው ሉቃስ፣
አባ ዝክረ ማርያም ወአባ ጴጥሮስ፣
የስነ ዘፍጥረት ሊቅ ኤጲፋኒዮስ፣
ዝም አትበል ተናገር ቅዱስ ሳዊሮስ፣
በሥጋው ማክበሩን አምላክ ክርስቶስ።

ጊዮርጊስ ተናገር አንተ የጥዋት ጮራ፣
ክርስቶስ መሲሕም ተብሎ እንደሚጠራ።
ወልድ ቅብዕ በማለት ክህደት አስተማሩ፣
የሥግው ቃል ነገር መች ገባቸው ዳሩ።
የተዋሕዶ ምስጢር ሳይገባቸው ቅሉ፣
ሃይማኖት ከምስጢር ይደባልቃሉ።

ክርስቶስ በሥጋ እንደሞተ ሲያውቁ፣
በሥጋስ መክበሩን እንዴት አላወቁ፣
ሊቃውንት እያሉ ለምን አይጠይቁ።
በተዋሕዶ ከበረ ብለው ሲናገሩ፣
ለዚህ ብሂላቸው የታል ምስክሩ።

ግብርን በማፋለስ አንድ ገጽ ካለው ከሰባልዮስ
አንድነትን ትቶ ሁለት አካል ካለው ከእርጉም ንስጥሮስ፣
መንፈስ ቅዱስ ሕጸፅ ካለው ከመቅዶንዮስ፣
ወልድ ፍጡር ካለው ከእርጉም ከአርዮስ፣
የዚህ ክህደቱ በምንም አያንስ።
ፈላጊዋ ጠፍቶ እውነት አለቀሰች፣
ግብራቸው ተቃርኖ ሀሰት ጥላት ሄደች።

ዳሩ ግን ወገኔ ይህ ክህደት ነውና፣
ቀኑ ሳይመሽብህ መንገድህን አቅና፣
እውነትን ከፈለክ ታገኛለህና፣
እረፍት ስላላት የህይወት ጎዳና፣
የያዝከውን ይዘህ በሃይማኖት ጽና።

ወስብሐት ለእግዚአብሔር
ወለወላዲቱ ድንግል
ወለመስቀሉ ክቡር አሜን !!

========///========               

የአባቶቻችንን ትምህርት እናስተምራለን ፤ ተስፋቸውንም ተስፋ እናደርጋለን ፤ የምናምንባት፤ የተማርናት፤ ተስፋ የምናደርጋት ሃይማኖት ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ክርስትናችን ይቺ ናት። እንኖርባታለን፤ እንሞትባታለን፤ በእግዚአብሔር ፈቃድ እንነሣባታለን።

( ሐይማኖት አበው፤ አባ ገብርኤል )

የኪነጥበብ ቤተሰብ ይሁኑ !
@sundayschoolstudents
የሰንበት ት/ቤት ኪነጥበብ ክፍል !         

ኪነጥበብ ዘሰንበት ት/ቤት

24 Jan, 08:34


++ ስነጽሑፍ - ግጥም !

(ርዕስ - አንቺ ትኖሪያለሽ)

የኑፋቄ ትምህርት እንክርዳድ ቢዘራ
ያሸነፈ መስሎት አሕዛብ ቢያቅራራ
ወጀብ ቢወጅብም ቢነሳ ዐውሎ ነፋስ
ውቅያኖስ ቢያናውጽ ዛፍን ቢገረስስ
ንውጽውጽታ በዝቶ ቢሰማ ነጐድጓድ
ሜዳው ቢጥለቀለቅ ተራራውም ቢናድ።

እልፍ ቢኮበልል ጥርጥሩ በዝቶ
ሚሊዮኑ ቢክድ መከራውን ፈርቶ
ወይም ሌላው
ማስተዋል ቢያቅተው አዕምሮውን አጥቶ
ብኩርናውን ንቆ የምሥር ወጥ ጓጉቶ
ሊሸጥሽ ቢስማማ ሊኖር ሆዱን ሞልቶ።
የጥፋት ደመና ከሰማይ ቢያንዣብብ
ዝናቡ ቢዘንብ ወጀቡ ቢወጅብ
ምንም ቢመስላቸው የምትሰጥሚ በቅርብ
ቅድስት ቤተ ክርስቲያን አማናዊት መርከብ።

የእነ ጴጥሮስ እምነት ኰኵሐ ሃይማኖት
የቀጠቀጠባት የአርዮስን ክህደት
የተቀደሰችው የአትናቴዎስ እምነት
በፍጹም አትፈርስም ከቶም አትሞከር
የገፋሽ ሊወድቅ የቀሰጠሽ ሊያፍር
አፍራሽሽ ሊፈርስ ቀባሪሽ ሊቀበር
ቃል እንደገባልሽ አምላክሽ እግዚአብሔር።

ትናንትን እንዳለፍሽ በወጀብ መካከል
ክር ላያቃጥል እሳት ሲንቀለቀል
ጸጥ እረጭ ሊል እሱ ሲቀሰቀስ
ማዕበል ቢነሳ ዐውሎ ነፋስ ቢነፍስ
በከሀዲ ክፋት ቢፈርስ መቅደስሽ
እሱ እንደፈረሰ አንቺ ግን እንዳለሽ
የዛሬው እንክርዳድ ወደ እሳት ተጥሎ
የዘመኑ ዑደት ሒደቱን ቀጥሎ
ጌታ እስከሚመጣ እስከ ምጽአት ድረስ
ስሙን እየቀደስሽ ክብሩን እያወረስሽ
አጥፊሽ እየጠፋ አንቺ ትኖሪያለሽ።

========///========

“ሰውን ብትታገልና ብትዋጋ ታሸንፈዋለህ ወይም ያሸንፍሃል፤ ቅድስት ቤተክርስቲያንን ግን ለማሸነፍ አይቻልም። ቤተክርስቲያን ሁል ጊዜ ትዋጋለች ተሸንፋ ግን አታውቅም ዲያቢሎስ ዝናሩን አራገፈ ቀስቱን ጨረሰ ቤተክርስቲያንን ግን አልጎዳትም፡፡”

(ሐዋርያዊት ቤተክርስቲያናችን በአባቶች አንደበት(የቁስጥንጥንያው ሊቀ ጳጳስ ዮሐንስ አፈወርቅ ))

የኪነጥበብ ቤተሰብ ይሁኑ !
@sundayschoolstudents
የሰንበት ት/ቤት ኪነጥበብ ክፍል !                            

ኪነጥበብ ዘሰንበት ት/ቤት

18 Jan, 08:20


++ ኪነጥበብ - መንፈሳዊ ዜና !

የጥምቀት  በዓል በመምጣቱ ጫማዎች ደስተኛ መሆናቸውን ተናገሩ፡፡ ዝርዝሩ እንደሚከተለው ይቀርባል።

ከተለያየ አይነት ከኤርገንዶ እስከ አንበሳ ጫማ ያሉ ጠቅላላ ጫማዎች ባካሄዱት ስብሰባ እና ባወጡት የአቋም መግለጫ እንደገለጹት ከሆነ የጥምቀት በዓል በመምጣቱ በጣም ደስተኞች ነን ለአባቶቻችን ለሰው ልጆች እንኳን  መላ አካላችሁ ከኃጢአት ለጥቂት ጊዜም ቢሆን ለሚያርፍባት የጥምቀት በዓል በሰላም አደረሳችሁ ማለት እንፈልጋለን ብለዋል፡፡

የጉባኤው አስተባባሪ የሆኑት ሸራ ጫማ ጉባኤውን ለማካሄድ ያነሳሳችሁ አቢይ አላማ ምንድን ነው ተብሎ ለቀረበላቸው ጥያቄ ማብራሪያ ሲሰጡ እኛ ይህን ስብሰባ እንድናካሂድ እና ደስታችንን እንድንገልጽ ያደረገን ዋናው ምክንያት ወደ ቤተ እግዚአብሔር የምንመጣበት ጊዜ የለንም አለቆቻችን ከጽድቅ ይልቅ ኃጢአትን፣ወደ ቅድስና ስፍራ ከመሄድ ወደ ጭፈራ መሄድን ስለሚመርጡ እኛ አምላካችንን የምናመሰገንበት ጊዜ አጥተን ጨንቆን ነበር ነገር ግን በዚህ በጥምቀት ወቅት ምእመናኑ በወረት ወደ ቤተ ክርስቲያን ስለሚመጣ እኛም በዚያው በረከት ስለምናገኝ ነው ብለዋል።

በስተመጨረሻም አቶ ሸራ  በሰጡትሁ አስተያየት እባካችሁ የሰው ልጆች አምላካችሁን አትዘንጉት ቅድስናችሁን አታርክሱት እግሮቻችሁ ሁሌም እኛን ተጠቅመው ወደ ቤተ እግዚአብሔር ይገስግሱ  ከኃጢአት ይሽሹ ለኛም በረከት ይትረፈን ሰሉ አስተያየታቸውን አጠናቀዋል፡፡

======///=======

የተወደዳችሁ የኪነጥበብ ቤተሰቦች፥ እንኳን ለጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ብርሃነ ጥምቀት በሠላም በፍቅር አደረሳችሁ አደረሰን !!!

የኪነጥበብ ቤተሰብ ይሁኑ !
@sundayschoolstudents
የሰንበት ት/ቤት ኪነጥበብ ክፍል !

ኪነጥበብ ዘሰንበት ት/ቤት

02 Jan, 12:46


++ ሥነጽሑፍ - ግጥም !

( ርዕስ - የዘመን ርኩሰት )

ዘመናችን ረክሶ በበደል ቆሸሸ፤
ጊዜው እየመሸ ሰዉም ተበላሸ።
አባቶቹ ደክመው የሠሩትን መቅደስ፤
ትውልዱ ግን ከፍቶ ጀመረ ለማፍረስ።
ምላሱ ረዥም ነው ዘወትር ይሳደባል፤
ጽድቅ እየመሰለዉ ጻድቃንን ይጠላል።
ሀገር ስትታጠን ሰው በእሳት ሲቃጠል፤
ጽድቅ አይመስላችሁ እግዚአብሔር ያዝናል።

የኢትዮጵያን ታሪክ አታበላሹብን፤
ምስኪኑን ገድላችሁ መቅሰፍት አታምጡብን።
ለልማት ተነሱ ይቅር መገፋፋት፤
ጠባብነት እንጂ ኢትዮጵያ ሰፊ ናት።
ከአንደበታችን መርዝ እየፈለቀ፤
በደል የሌለበት ብዙ ሰው አለቀ።
ሁሉም ዓይን ለዓይን እየተናቆረ፤
ግፍ እየ ተሠራ ዘመን ተቆጠረ።
ንቦቹ ተባብረው ማር ይጋግራሉ፤
ጉንዳኖች ተባብረው ወንዝ ይሻገራሉ።
ሰው ግን ከነዚ አንሶ ክፉ ስለሆነ፤
መደመሩ ቀርቶ መደማማት ሆነ።

አንድነቱ ጠፍቶ ልዩነት ሲስፋፋ፤
መተናነቅ እንጂ መከባበር ጠፋ።
ከሞባይል በታች የሰው ዋጋ ወርዶ፤
ስንቱ ወድቆ ቀረ በጨለማ ታርዶ።
ኃብታም ዘመድ ከብቦት ብር ላይ ይተኛል፤
ደሀው ዘመድ አጥቶ በብርድ ላይ ያድራል።
ሁሉም ዘርማንዘሩን ደጋግሞ ቢቆጥረው፤
አዳም ዘንድ ደርሶ መቆሙ ግድ ነው።

ነገር ግን ዝምድናው በጥላቻ ፈርሶ፤
ምድራችን ጨቀየች የምስኪን ደም ፈስሶ።
ዘረኝነት ሁሉን ስላ ደነዘዘ፤
ጥላቻ ነገሠ ፍቅር ቀዘቀዘ።
ጥርሳችን ቢስቅም ሰው እያታለለ፤
ምላሳችን ወግቶ ስንቱን አቆሰለ።
ዘመናችን ረክሶ በበደል ቆሸሸ፤
ጊዜው እየመሸ ሰዉም ተበላሸ።

=======///========

በዛሬዋ ኢትዮጵያችን ብዙ የማንኮራበት አለ፤ የምናዝንበት የምንታመምበት እልፍ ነው። በየቀኑ የእናቶችና ሕፃናት እንባ እንዲታበስ እና ሞት እዲቆም፤ በጭካኔ የተበደሉ ወገኖቼ ሁሉ ፍትህ እንዲያገኙ እመኛለሁ። ነገር ግን ስለ ትላንቱ የአያቶቻችንን ደማቅ የወርቅ ታሪክ እና ለነገው የእኛ ትውልድ ትልቅ የተስፋ ብርሃን ስንል ዛሬም ከነህመማችን የሀገራችን ሠላሟ ተመልሶ ሰንደቋ ሁሌም ከፍ እንዲል እንመኛለን !!!

የኪጥበብ ቤተሰብ ይሁኑ !
@sundayschoolstudents
የሰንበት ት/ቤት ኪነጥበብ ክፍል !

ኪነጥበብ ዘሰንበት ት/ቤት

28 Dec, 13:10


( ሠላም ተዋሕዶ )

ሰላም ተዋሕዶ ሰላም ኦርቶዶክስ
የአትናትዮስ ሐውልት የዲዮስቆሮስ
የአዳም መመኪያ የሔዋን ሀገር
አንቺ አይደለሽም ወይ የቅዱሳን ክብር
የአብርሃም ቃልኪዳን የአቤል መስዋዕት
የሔኖክ ሃይማኖት ያዳንሽው ከሞት
አንቺ የኖህ መርከብ ዕፀ መድኃኒት፡፡
በአብርሃም ድንኳን ተወልደሽ ያደግሽ
የይስሐቅ መአዛ ወደር የሌለሽ
የዮሴፍም አፅናኝ #ተዋሕዶ_ነሽ ፡፡

የሙሴ ጽላት ነሽ የአሮን በትር
የኢያሱ ሐውልት የጌዲዮን ፀምር
የሳሙኤል ሙዳይ የእሴይ ትውልድ
የዳዊት በገና የሰሎሞን ዘውድ
የታተመች ገነት የምስጢር ጉድጓድ ፡፡
ቱሳሔና ሚጠት ውላጤም ጭምር
ያልተቀላቀለሽ ንጽሕቲቱ ምድር
ኢሳይያስም አይቶ በሩቅ መነፅር
ስለ ቅድስና ሆነ ያነቺ ምስክር ፡፡
የነ ኤልያስ ቤት የወርቅ መሶብ
ውስጥሽ የተሞላ የምስጢር ምግብ
የኤልሳ ማሰሮ የሕይወት መዝገብ ፡፡

ፋራን የምትባይ የእንባቆም ተራራ
ሁሉንም የምታሳይ በቀኝም በግራ ፡፡
የሕዝቅኤል አልፍኝ ባለ አንድ በራፍ
የማትከፈችው የኬልቄዶን ቁልፍ፡፡
የሕግ መፍለቂያ የነፃነት ቦታ
የሚክያስ ሀገር አንቺ ነሽ አፍራታ ፡፡
በውስጥም በውጭም የሌለብሽ እንከን
የሕይወት መዝገብ ነሽ ተዋሕዶአችን ፡፡
ሐዋርያት ይምጡ ያውሩ ያንቺን ዜና
የሚያውቅ ሲናገር ደስ ያሰኛልና ፡፡
ሰማዕታት ልጆችሽ የፃፉልሽ በደም
የሕይወት መጽሐፍ ነሽ የጽድቅ የሰላም።

=======///=======

" የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያንን አንብቧት ፤ ተርጉሟት ፤ ኑርባት ያን ጊዜ ሕይወት ታገኛላችሁ ! "

( ብፁዕ አብነ ናትናኤል )

የኪጥበብ ቤተሰብ ይሁኑ !
@sundayschoolstudents
የሰንበት ት/ቤት ኪነጥበብ ክፍል !

ኪነጥበብ ዘሰንበት ት/ቤት

27 Dec, 15:20


( እምነቴን አልክድም )

ሃይማኖት አንድት ናት የሕይወት ጎዳና፣
ጻድቃን የሄዱባት መንገዷ የቀና፣
ይህቺ ናት እምነቴ የሰጠኝ ክርስቶስ፣
ከአበው የአገኘዋት እምዬ ኦርቶዶክስ።
ቢርበኝ ቢጠምኝ ዘመድ እንኳ በአጣ፣
ክፉውን አልፈራም የመጣው ቢመጣ።
መስቀሉ ሃይሌ ነው አለ በልቤ ላይ፣
እናቴም ማርያም ናት አገሬም በሰማይ።

የአንገቴ ማህተም የአሰርኩት ጥቁር ክር፣
ስለ ተዋሕዶ ይናገራል ምስጢር።
እናም አልበጥስም ማኅተቤን ከአንገቴ፣
ብኩርናዬ እኮ ናት ኦርቶዶክስእነቴ።
የደሙን መሰረት ተዋሕዶን ጥዬ፣
እንደት ፍልስፍናን ልመን እውነት ብዬ።
የመሠረተውን ማንም ሰው ተነሰቶ፣
እንደት ይታመናል ፍልስፍና ከቶ።

ሃይማኖቴን ክጄ ገነትን ከማገኝ፣
ኦርቶዶክስ ሆኜ አምላክ ይኮንነኝ።
እምነቴን ከምክድ ለገንዘብ ለእንጀራ ፣
ይቅርብኝ መክበሩ  ስሜም አይጠራ፣
ጓዳዬ ሳይሞላ ኑሮየ ሳያምር፣
ከአባ መቃብር ላይ ከዋሻው ልቀበር፣
ነፍስ ያስምራልና የቃል ኪዳኑ አፈር፡፡

በክብር ከምለብስ የሳኦልን ካባ፣
ሌጦው ይሻለኛል የአባቶቼ ዳባ።
ከእነርሱ አልላይም ማንም ሰው አይለዬኝ፣
የስባአር አጽማቼው እሾህ ሆኖ ይውጋኝ።
ያአመንኩት እውነት ነው አልጠራጠርም፣
እሞታለሁ እንጂ እምነቴን አልክድም።
ከሰማእታቱ ከጻድቃኑ ሕይወት፣
ይሄን ነው ያማውቀው ስለ ስሙ መሞት።

=======///========

የአባቶቻችንን ትምህርት እናስተምራለን ፤ ተስፋቸውንም ተስፋ እናደርጋለን ፤ የምናምንባት፤ የተማርናት፤ ተስፋ የምናደርጋት ሃይማኖት ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ክርስትናችን ይቺ ናት። እንኖርባታለን፤ እንሞትባታለን፤ በእግዚአብሔር ፈቃድ እንነሣባታለን።

( ሐይማኖት አበው፤ አባ ገብርኤል )

የኪጥበብ ቤተሰብ ይሁኑ !
@sundayschoolstudents
የሰንበት ት/ቤት ኪነጥበብ ክፍል !

ኪነጥበብ ዘሰንበት ት/ቤት

25 Dec, 18:12


( መልሰኝ እቤትህ )

ሀጢዓቴ በዝቶ መቆም አቅቶኛል
እባክህ ደግፈኝ ምህረትህ ያሻኛል
ባልተፈታው ኑሮ የሕይወት ቋጠሮ
ጓዳዬ ሚስጥሬ ሁሉ ተበርብሮ
ከሀጢዓት በቀር ዱብም የሚል ጠፋ
አንድስንኳ ሳይኖር የሚሰጠኝ ተስፋ
አንዲት ጽድቅ አጣሁኝ አንዲትም ጠብታ
ህይወቴን የሚያድስ የሚሰጠኝ ደስታ

እባክህ መልሰኝ ቤትህ ይሻለኛል
የዚህ ምድር ኑሮ አለም ሰልችቶኛል

ለነገሩ አለም ሰለቸሁት እንጂ ከቶ አልሰለቸኝም
ምክንያት ይሁነኝ እንጂ...ማራኪ ናት አለም

በፍጹም ትህትና ምኞት ተቀብላ
ከሀጢአት ማህደር "ተቃመሰኝ" ብላ
የሀሰት ጣዕሟን የወይን ዘለላ
ከቋጠሮው ስንቋ ለኔም አከፋፍላ
ጊዝያዊትን ደስታ ፌጭታና ዕልልታ
ላላስተዋለ ልብ ገበታን ዘርግታ
የህይወት ወላፈንን አሰባጥራ
አዘበራርቃብኝ የኑሮዬን ዳራ

አለም ብልጣ ብልጦ ጉድ አደረገችኝ
ባዶዬን ላከችኝ እያየሁ አፍዝዛኝ
በአስመሳይ ገጽታ እኔነቴን ሸንግላ
የጣዕምን ጭምብል አጥልቃ...አድርጋኝ ተላላ

ታድያ ጥፋት ያለው እኔጋ ነው እሷጋ?
እጅ እግሬው ቀላቅሎኝ ከስህተቷ መንጋ
ጭለማን ካባዬ መሸሸግያ አድርጌ
የሀጢዓት ጉራንጉሩን እኔው ፈላልጌ
ስንት ጉድ ሰራሁኝ በገዛ እጅ እግሬ
እያገዘኝ ሰይጣን አባ ጋሽ አጅሬ

ይሄም የኔው ወሬ
ምክንያት እንዲሆነኝ እውነትን ቀብሬ

በእርሱም አልፈርድም አሳሳተኝ ብዬ
እራሴን ሰጥቼው ወጥቼ ከአንድዬ

ሰይጣንም ደስ አለው ሰጠኝም ፈተና
ኋላ እራሴው ወደቅኩ ቁርጥምጥም አልኩና

ይኸው የሀጥያት ጽዋ ትንሽ ቀመስኩና
በደጅህ ወደቅኩኝ መጣሁ እንደገና
የፍቅር እናት ማርያም "ልጄ" እንድትለኝ
"እባክሽ እናቴ እቀፊኝ" እያልኩኝ
ማለድኳት ተማልዳ እንድታማልደኝ
ወደ አባቴ ቤት እንድትመልሰኝ!

ወስብሐት ለእግዚአብሔር
ወለወላዲቱ ድንግል
ወለመስቀሉ ክቡር ይቆየን !!

========///=======

ያለፈው ዘመኔ ይበቃኛል/2×/
በአምላክ መታመኔ ይሻለኛል/2×/
እግዚአብሔር የንስሀ ልቡና ይስጠን

የኪጥበብ ቤተሰብ ይሁኑ !
@sundayschoolstudents
የሰንበት ት/ቤት ኪነጥበብ ክፍል !

ኪነጥበብ ዘሰንበት ት/ቤት

23 Dec, 17:26


++ ኪነጥበብ - ጭውውት !

( ርዕስ - የናቡቴ ርስት )

( ዳምጤ ወደ አጥሩ ተጥግቶ ያጠረውን ጠንክር የተባለ ጎረቤቱን እስኪያገኝ ቸኩሏል፤ ዱላ ይዞ እየተንቆራጠጠ )

ዳምጤ፡- (በሽለላ መልክ)ኧረ ጎራው ኧረ ጎራው ኧረ ጎራው እባብ ዘለግላጋ መንታ ነው ምላሱ እባብ ዘለግላጋ መንታ ነው ምላሱ ድንበሬን የነካ አለቀውም እሱ ኧረ ጎራው ኧረ ጎራው

ይምጣት ዛሬ ብቻ (እያለ ሲንጎራደድ ጠንክር ይገባል)

ዳምጤ:-
          አንተ ወስላታ አንተ ሌባ ቀማኛ
          የሰው ሐቅ በልተህ አርፈህ ልትተኛ
          እኔማ ይቺን ቀን ስጠብቅ ነበረ
          ባንተ ይሄ ድፍረት እንዴት ተሞከረ
           ንገረኝ እስኪ ኧረ?

ጠንክር :-
  አንተ ሰውዬ እረፍ እኔ አልደረስኩብህም
      አንተም ካልነካኸኝ እኔም አልነካህም

ዳምጤ:-  ኧረ መደፋፈር
ጠንክር:- የራሴንም አልሰጥ
               የሰውም አልነካ
        ይሄ ከሆነ ኃጥያት በላ ልጠየቃ
    አጥሬን ድንበሬ ላይ አምጥቼ መትከሌ
    ይህ ከሆነ ጥፋት ሌባ ለመባሌ

ዳምጤ፡- የትኛው ድንበርህ ባክህ
             ጥንት አባቶቼ ሲወርሱ ያመጡት
              ሲወርድ ሲዋረድ ለኔ ያስረከቡት
  ፊት አውራሪ በላይ ለቀኝ አዝማች ሲሳይ
ከቀኝ አዝማች ሲሳይ ለግራ አዝማች ከልካይ
ከደጃች እርገጤ ለአልጋ ወራሽ ጌጤ

ጠንክር:- ቀጥል እንጅ ዳምጤ

ዳምጤ:-
      ሲወርሱ ያመጡት የደማቸው ዋጋ
      የዘር ርስት ነው
      በዘመናት ጀግና ያልደፈረው
      ትልቅ ታሪክ ያለው ይህ እኮ ርስት ነው

ጠንክር፡-
ከደጃች እርገጤ ለአርጋ ወራሽ ጌጤ ከአልጋ ወራሽ ጌጤ
ለነገረኛው ዳምጤ

(በዚህን ጊዜ ይጣላሉ መሬት ላይ ይወድቃሉ)

ዳምጤ፡- ያን በታገስኩ ደግሞ አሁን ልትሰደበኝ

ጠንክር :-መከበር ካልፈለክ አዋርድሃለሁ
       አሁንስ በቅቶኛል በጣም ታግሻለሁ
    የትኛው ቅርስህ ነው ካንተ የተነካ
    እንኳን ድንበርህን ካባ ማታስነካ
    ራስህን እንደቸር ስለምን ታያለህ
   አንተ እኮ ቢነግሩህ በጣም ችግር አለህ

ዳምጤ፡- አንተ ሠውዬ እረፍ የሚያናግርህን ሰው ደርሰህ አትናቀው
እንዲህ የዋዛ ሰው መስሎሃል
ሲፈልግ ተለማምጦ
አልያም እረግጦ ይገዛሃል

ጠንክር:- አሂሂ በላ እንየዋ
            መቼስ መርገጥን የወደደ
            መረገጥን የለመደ

ዳምጤ ፡- ማለት ማለት?
ጠንክር:-አሳልፈኝ ወዳጄ ከኔ ለመጣላት
              ይህ አይሆንም ምክንያት
  
ዳምጤ:(ሊሄድ ሲል መንገድ እየዘጋበት)
         ኧረ ወዴት ወዴት?

ጠንክር:- አሳልፈኝ ወዳጄ?

ዳምጤ፡- ወዳጄ?
     በአጓጉል ቃላት ሽንገላህን ትተህ
  ያን ደንቃራ አጥርህን ከድንበሬ አንስተህ
  እንዳሻህ ለመሆን ያኔ ትችላለህ
  
ጠንክር:-
  እንዳሻዬ ለመሆን አንተ አታስፈልገኝም
  ድሮውንም ጠንክር ማንም አያሻኝም
  አሁን አሳልፈኝ በጣም ቸኩያለሁ
  የመቻልን ጥበብ ትእግስት ጨርሻለሁ

ዳምጤ:-
   ብጨርስስ ምን ልትሆን
    አንተ ጨምላቃ ጭምልቅልቅ
    አንተ ርካሽ በድን

ጠንክር፡- ተው (በዱላው እየጠቆመ)
ዳምጤ፡- ባልተውስ (እሱም እየተዘጋጀ)
ጠንክር :- ተው?
ዳምጤ:- እንግዲህ ነገርኩህ
         ከርስት ከድንበሬ ተነሳ ነው ያልኩህ

ጠንክር:- ድንበር ድንበር አትበል
     እኔ ያንተን ድንበር ቅንጣት አልነካሁም
     ለምን አትረዳኝም ለምን አይገባህም?

ዳምጤ:- አ....ይ....ገ....ባ....ኝ.......ም
ጠንክር:- አይገባኝም?
         ታድያ ካልገባህ እዳኛ ዘንድ ሄደ ፍርዳችንን እንወቃ

ዳምጤ:- ና እንሂዳ?

( ወደ ፍርዱ ሲገቡ ሽማግሌ ዳኞች ቁጭ ብለዋል )

ዳኛ:- እሺ የነገራችሁን መነሻ ከግንዱ
        ምንም ሳትዋሹ በእውነት አስረዱ
        ልጅ ዳምጤ ጀምር
        እንቅጩን እንጂ ሃሰት ሳትጨምር

ዳምጤ:- (ለዳኞች እጅ ይነሳና)
        በልሃ ልበልሃ
        ወግና እምነትህን ህግንም ካላወቅ
         ተጠየቅ?

ጠንክር :- ልጠየቅ!

ዳምጤ:-
     ከቀድሞ ድንበርህ አጥርህን አንስተህ
     ቀስ እያልክ ገፍተህ እኔ ክልል ገብተህ
      መሬት መውሰድህን አሁን ትክዳለህ?

ጠንክር:- (ለዳኞች እጅ ይነሳና)
        በልሃ ልበልሃ
        ወግና እምነትህን ህግንም ካላወቅ
         ተጠየቅ?

ዳምጤ:-  ልጠየቅ!

ጠንክር:-
   እርግጥ ነው የቀድሞ ድንበሬን
   ገባ ብዬ ነው ያጠርኩት
   ኋላም መሬቱን ለሥራ ፈለኩት
    ከዚያም ከነበረበት አንስቼ
    እድንበሬ ጫፍ ተከልኩት

ዳምጤ፡- ውሸት ውሸት
         በዚህ በዚህማ ሞኝህን አታልበት

ጠንክር:-
     ቀድሞን ልነግርህ ስል
      አልሰማህም አልከኝ
      እኔ ከዚህ ኋላ ቃላትም አላገኝ
     የተናገርኩት ነገር ካረገኝ ቀማኛ
      ሸንጎ የገባውን ይፍረዱልኝ ዳኛ

ዳኛ፡- እሺ ነገራችሁን ሰምተናል
         ከልብ አድምጠናል
    ወንድማማች እንዴት በመሬት ይጣላል
  ባታውቁት ነው እንጂ ሁሉም እኮ ያልፋል

ዳምጤ:- እሱማ እኮ ያልፋል
       ለርስቱ ሲል መስሎኝ ናቡቴ የሞተው
       ታሪኩን ካላወቀ በሰፊው ልንገረው

ጠንክር:- እሱንማ አውቃለሁ
               ድንበርህን ስጠኝ
               አልያም ለውጠኝ አላልኩም
      የሰው ሃቅ የሰው ነው እኔ አልፈልግም
     
ዳምጤ:- ታድያ እኔ ነኛ የሰው ቀዬ ገብቼ
     ከዚህ ጫፍ አንስቼ እ.....ን...ዲ....ህ
     አድርጌ ያጠርኩት
(በዱላው ዙርያውን እየጠቆመ)

ጠንክር:- አይደለም እንዲህ ቀርቶ
      እ.....ን....ዲ.....ህ አድርጌ ባጥረው
      አንተ ምን አገባህ
(እሱም ዱላውን ይዞ ዙርያውን እየተሽከረከረ)

በዚህን ጊዜ ሁለቱም መጣላት ይጀምራሉ
ዳኛውም በብስጭት አስቁመው...

ዳኛ፡- በቃ በቃ!
         ነገራችሁን ሰምተናል
         በአንድ ነገር ግን እጅጉን አዝነናል
         ናቡቴ የሞተው ቢሆንም ለርስቱ
        ያቺ ርስቱ መልካም ፍሬ ያላት
        ነች እኮ ሃይማኖቱ
        በአባቶች ተባርኮ የተሰጠው
       አምላክም በፍቅር በዋጋ የባረከው
       በማጭበርበር በስርቆት
       በደም  ያልጨቀየው
        እርሱ እርስቱ ነው
       እናንተ ግን ዛሬ የምትጣሉበት
   ማጭበርበር ስርቆት የሰው ደም ያለበት
    ይህ ነው ርስት??
    እንግዲህ ፍርድን ስጠን ካላችሁ
    ፍርድን እሰጣለሁ
    በግሌ ግን ተስማሙ እላለሁ

(ሁለቱም ይተያዩና ይተፋፈራሉ)

ዳኛ:- ምንድነው ልፍረድ???
ዳምጤ :- ኧረ እኛው እንስማማለን
ዳኛ:- ጎሽ በሉ እስቲ ተቃቀፉ
(በገጠሩ ሰላምታ ሰላም ይባባላሉ ይታረቃሉ)

ዳኛ:-
ጎሽ ተባረኩ ፍቅር ይስጠን ለሃገራችን
ሰላም ይሙላ በቤታችን
(ብለው መርቀው አሰናበቷቸው)

=======///=======

ለሰንበት ት/ቤቶች የሚሆኑ፥ የገጠር ለዛ የተላበሱ አስተማሪና ታሪካዊ ቁምነገሮችን በእንዲህ አይነት ጭውውቶች ካላችሁ አድርሱን !

የኪጥበብ ቤተሰብ ይሁኑ !
@sundayschoolstudents
የሰንበት ት/ቤት ኪነጥበብ ክፍል !

ኪነጥበብ ዘሰንበት ት/ቤት

22 Dec, 10:54


++ ኪነጥበብ - ጭውውት !

( ይቺ ጭውውት፥ አጠር ያለች አዝናኝና ቁምነገር የተላበሰች የገጠር እረኞች ጭውውት ናት። ጭውውቱም በእረኝነት ሜዳ ላይ ሲገናኙ ይጀምራል)

👶ስማማ አንተው
👷እህ
👶እንዲያው ስፈልግህ ነው ያገኘሁህ! ይዴ በለኝ ይዴ?
👷ይዴ
👶በቃ ያችን ሸጋ ኩብል ከጅለህ በተስኪያን መዝለቅ ጭራሽ ተውከው እንዴ?
👷(የኩራት ሳቅ ይስቅና) አለምዋን ማለትህ ነው?
👶እህሳ
👷ይኮ በለኝ ይኮ
👶ይኮ
👷እንዲያው መታ አጫውተኝ ብትል አላስከፋት ብዬ ነውኮ
👶አ...ይ ልክ አለዋ! ሰሞኑን የኔታ ስላንተ ደጋግመው እየጠየቁኝ ነው። ደሞ የልጅቱ አባት ከበርቴ ባለጠጋ ናቸው አሉ! ኋላ እንዳታስቀፈድድህ
👷አታሟርት እንግዲ! እኔ ምልህ? ይዴ በለኝ ይዴ?
👶ይዴ
👷እንዲያው ታድያ ለየኔታ ስለ አለምዋ ነገርካቸው እንዴ?
👶እኔ ምን ነገር አስመዘመዘኝ አንተው? እንዲህ አይነቱ አመልም የለኝ እንዲያው ባልንጀራዬ ሲስት እያየሁ ጆሮ ዳባ ልበስ ከማለት ብዬ እንጂ!
👷ሰሞኑን ዘልቃለሁ አንተው
👶ተው ጃል። በሐይማኖትማ አትሳሳ! እንዴ...በማይቀለደው!
👷እሱስ ልክ ነህኮ ደምስ። እንዲያው ሰሞኑን ነገሮችን አመቻችቼ መዝለቄስ አይቀርም
👶ይልቅ እሱን ተወውና በል እስቲ ጨዋታ እንቀይር? ዬኔታ መምጫቸው ተያ ግድም ነው። ኋላ እንዲ ስንነቋቆር ድንገት መተው እንዳይሰሙን
👷ደህና....ሸጋ ሀሳብ ነው! በል ተቀበል እንግዲ እንካ ሰላምትያ
👶በምንትያ?
👷በጻህል
👶ምናለህ በጻህል
👷(እያሾፈ)ሳይሻል አይቀርም ብጠመቅ በጠበል
👶አትቀልድ አንተ...እንዲያው የእውነት ሳያሻህ አይቀርም! እንካ እንጂ ሰላምታ......በዕጣን......ኽበተስኪያን ባንጠፋ ነው ለኛ እሚበጀን
👷እንካ ሰላምታ.....በወርሀ ነሐሴ......ታሁን ቧላ ላልቀር ቃል ገባሁ ለራሴ
👶አዎን ጃል እሱ ነው ሚበጀን። እንካ ሰላምታማ.....በበገና......ሳንወላውል በተዋህዶ እስተመጨረሻ እንጽና
👷አዎን አዎን ልክ ብለሀል! እንካ ሰላምታ እንጂ.....በጥምጣም.......አዛኚቱ እማምላክ ታማልደን ዘላለም
👶እንካ ሰላምታ አንተው......በደመራ......ኦርቶዶክስ ተዋህዶ የእውነት ግንድ ናትና በሐይማኖትህ ኩራ!
👷እንካ እንጂ ሰላምታ.....በቁስቋም......እኔስ ተዋህዶን ዘላለም አልክድም
👶እውነት ነው እውነት ነው (ዞር ዞር ብሎ አይቶ ደንገጥ ይልና) ኧራ...ኧረ አንተው አንዲቱ ላሚት የለችም
👷የቱዋ
👶ያቺ አዲሲቱ፤ የቀይ ዳማዋ! ኧረ ወዴት ገባች አንተው? አረ ተነስ እንፈልጋት?
👷የት ትሄዳለች ቅርብ ናት
(ላሟን ፍለጋ ብለው ከመድረክ ይወጣሉ)

======//======

ጭውውቱ በገጠር ልጆች ለዛ ሲጫወቱት እንዲህ አይነት ጭውውቶች አዝናኝና አስተማሪና ሳቢም ናቸው። እስኪ እናንተ ቤት ምን ዓይነት ጭውውት አላችሁ ፥ አድርሱን !

የኪጥበብ ቤተሰብ ይሁኑ !
@sundayschoolstudents
የሰንበት ት/ቤት ኪነጥበብ ክፍል !

ኪነጥበብ ዘሰንበት ት/ቤት

19 Dec, 07:33


++ ሥነጽሑፍ - ግጥም !

( ርዕስ - ቤተ መቅደስህ )

ጌታዬ . . !
ቤተክርስቲያን እኔ ፥ በመቅደስህ ሳለው
ራሴን ስመረምር ፥ ዙርያዬን ስቃኘው
የመቅደስህ ታዛ ፥ እጅግ አሸብርቋል
በቀለም ተውቧል ፥ እዩኝ እዩኝ ይላል
የህንፃ ቤተክርስቲያንህ ፥ የአሰራር ጥበብ
ፈፅሞ ቢደንቀኝ ፥ አልኩኝ መንክር ዕፁብ።

የቤተክርስቲያንህ አፀድ ፥ ልምላሜን ታጥቆ
ንፁሕና ፅዱ ሆኖ ፥ በደንብ ተጠብቆ
መዓዛው ያውዳል ፥ ሜትሮችን ርቆ።
በውስጥ የሚገኙ ፥ ችግኞች በሙሉ
የሚተጉላቸው ፥ ወንድሞች ስላሉ
መጠውለግ መጠንዘል ፥ ምንም ሳይኖራቸው
ባለ ደምግባቶች ፥ ተወዳጆች ናቸው።

ይህንን ተመልክቼ
በዚህ ተደስቼ
በአድናቆት እንዳለሁ . . !
ወደ ራሴ ሳይ ግን ፥ እኔ ያንተ መቅደስ
ለመውደቅ ተዛምሜ ፥ ተንጋድጀ ልፈርስ
ለመንፈሳዊ ዓይን ፥ ደም ግባቴ ጠፍቶ
በረቂቅ ለሚያሸትተኝ ፥ ሽታዬ ከርፍቶ
ከጸጋ ሁሉ ተራቁቸ እንዳለው
ይህንን ዐያለሁ . . !

ደግሞም የሚገርመው
ለታቦትህ ማደርያ ፥ ቅፅር የሚተጉ
ሲቆሽሽ የሚያፀዱ ፥ የሚያደገድጉ
የቅጥርህን ችግኞች ፥ ውሃ የሚያጠጡ
የጠወለጉ ቅርንጫፎችን ፥ በጊዜው የሚቆርጡ
ብዙ ሰራተኞች ፥ እንዳሉ አይቼ
ይህንንም ፥ ተመልክቼ . . !
ራሴን ዐያለሁ ፥ ውስጤን አደምጣለሁ
ህንፃ ቤ/ክን ፥ ለሰው ነው እላለሁ
የሰው ልጅ እንዲድን
ከአምላክ የተሰጠን።

እኔ ጉስቁል ልጅህ . . !
በሐጢአት ስቆሽሽ ፥ አንተን ስበድልህ
መንፈሳዊ ደም ግባት ፥ ሲለየኝ
ስጋዊ መሻት ጸንቶብኝ ፥ ከቤትህ ሲያስወጣኝ
በእግረ ስጋ ፥ በአካል እንኳን ብገኝ
ልቤ ካንተ ሲርቅ ፥ ባዶነት ሲሰማኝ
"ወንድሜ ደክማሃል ፥ ወንድሜ ጠፍተሀል
ያ የቀድሞ ፥ ፍቅርህ አሁንስ ወዴታል ?"
ክርስቲያን የመባል ፥ የአንተ ጨውነትህ
የቀድሞ አገልግሎትህ ፥ለቤተ መቅናትህ
ውበት ደም ግባትህ . . !

እኮ ወዴት አለ ?
ክፉ ሃሳብ ፥ ክፉ ግብር በአንተ ዘንድ ሰልጥኗል
የንግግርህ ለዛ ፥ አካሄድህ ሁሉ በርግጥ ተቀይሯል
ወንድሜ ተመለስ ፥ ክፉ ግብርህን ተው
ውበትህና ክብርህ ፥ በቤቱ መኖር ነው።
እኛ ወንድሞችህ ፥ እንዲሁም መላእክት
ርኅርህተ ህሊና ፥ ድንግል የአምላክ እናት
የፍቅር አምላክ መድኃኔያለም ፥ የዓለም መድኃኒት
ለቤተክርስቲያን ወገኖች ፥ ለሁላችን በአንድነት
ያንተ መመለስ ፥ ደስታችን ነው በእውነት።"
እኔን ምስኪን ልጅህን ፥ ወዳንተ ሊመልስ
ለማደርያህ እንድሆን ፥ ሊያደርገኝ ውብ መቅደስ
እኔን የሚፈልግ ፥ ማን እንደሆን ሳስስ . . !

አንዳንዶች ፥ የኔ የልጅህን መጥፋት
ለስላቅና ለፌዝ ፥ ለከንቱ ሲያደርጉት
መውደቅን ስለማማት ፥ መውደቅን ሲያጭዱበት
የመሰናከያ ድንጋይ ሆኗቸው ፥ ሲፈጠፈጡበት
ሌሎች ፥ ምንም እንዳልተፈጠረ ፥ በቸልታ ሲያልፉ
ያሉያም ፥ ይሄ ይሻለዋል ብለው ፥ ከአንተ መራቄን ሲደግፉ
በርታ ጎበዝ ሲሉኝ
በሀሳብ ሲያበረቱኝ . . !

ጌታዬ . . !
ዙርያዬን ስመለከት ፥ ዙራያዬን ስቃኘው
ይህንን እላለሁ ፥ ይህንን አያለሁ
መከሩ ብዙ ነው
ሰሪው ግን ጥቂት ነው
ማለትህ እውነት ነው።
ከቤትህ ከጠፉ ፥ ፈላጊው ጥቂት ነው።
ይገርማል !
ህንፃ ቤተክርስቲያን ለመስራት ፥ እንዲሁም ለማደስ ብዙዎች ሲተጉ ፥ ብዙ ጉልበትና ብዙ ፥ ንዋይ ሲፈስስ
ነገር ግን ፦
ሕንፃ ሰብ ሲጎሳቆል ፥ ዕለት ዕለት ሲፈርስ
በፍትወት ሲቃጠል ፥ ከሰውነት ሲያንስ
ቅጠልነቱ ጠውልጎ ፥ ልምላሜ ሲለየው
ዘወር ብሎ የሚያይ ፥ አይዞህ ባይ ጥቂት ነው።

======///======

“ሰዎች የተራሮችን ከፍታ የባህርን ሞገድ የወንዞችን ረዥም ፍሰት ለማድነቅ ወደ ብዙ ሃገራት ይጓዛሉ ፤ የከዋክብትን ውበትም ያደንቃሉ። አንድን አስደናቂ ፍጥረት ግን ቸል ብለው ያልፉታል። ይህም ድንቅ ፍጥረት የሰው ልጅ ነው።” . . . ያውም የእግዚአብሔርን ቤተመቅደስ !

( ሊቁ አውግስጢኖስ )

የኪጥበብ ቤተሰብ ይሁኑ !
@sundayschoolstudents
የሰንበት ት/ቤት ኪነጥበብ ክፍል !

ኪነጥበብ ዘሰንበት ት/ቤት

17 Dec, 18:19


++ ሥነጽሑፍ - ግጥም !

( ርዕስ - ምን ተሰምቶህ ይሆን ?! )

ሀገር የምትኖረው ፥ ሀገር የምትድነው
ለሀገር ፅኑ ደዌ ፥ ፈውስ የሚገኜው
አንተ የሀገር ልጅ ፥ ጠቢብ ስትሆን ነው !

ርሃብ ቸነፈር ፥ ከሀገር የሚጠፋው
ደስታና ሀሴት ፥ ፍስሐ የሚሆነው
መሰደድ ተሰድዶ ፥ ባይንህ የምታየው
በሀሳብ ልዑል ስትሆን ፥ ልጄ ስትማር ነው !

ያለማወቅ ፅልመት ፥ ከሀገር ተወግዶ
ህዝብ ሰላም ሆኖ ፥ ርስ በርስ ተዋድዶ
በሀገር የሚኖረው
ልጄ ስትማር ነው !

የመሻገርና ፥ የማሻገር ተስፋ ፥ እውን የሚሆነው
ሀገርን የመምራት ፥ ለወገን የመድረስ ፥ ቁልፉ ጉዳይ ያለው
በማወቅህ ብዛት ፥ በብልህነት ጥግ ፥ በመማርህ ላይ ነው
እናም እልሀለሁ ....!
አፈ ሙዝን ማንሳት
ኃይልና ጉልበት
መፍትሔ የነበረው
በድሮው ዘመን ነው ።
ኢላማና ተኩስ ፥ ያረጀ ያፈጀ ፥ ድሮ የቀረ ነው
ያሁን ዘመን ፍልሚያ ፥ የሀሳብ ብቻ ነ..ው ።

በአሁን ዘመን ኖሮ ፥ ትልቁ ትጥቅ ያለው፤
ስልጣን የሚያዘው ፥ ሀገር የሚመራው
በሀሳብህ ልዑልነት ፥ በሰላም ትግል ነው
በመማር ማኅፀን ፥ በመማር ወገብ ነው ።

ሀገርህን ብትወድ ፥ ህዝብህን ብታፈቅር
በመማርህ ትጋት ፥ በተግባር አስመስክር

ብለህ የመከርከኝ ፤ የቀድሞው መምህሬ
ስለዚህ ንግግርህ ፥ ምን ተሰማህ ዛሬ?

ማሰብና መወቅ
አዲስ ሀሳብ ማፍለቅ
በእውነት ጥዩፍ ሆኖ
አለማወቅና አለማመን ገንኖ
ሀሳብ አለን ያሉ
ለወይኒ ሲጣሉ
በሰይፍ ሲቀሉ
በጥይት ሲቆሉ
መምህሬ ፥ አባቴ ፥ ይህንንስ እያዬህ
አሁንም ተማሩ ፥ አሁንም አስቡ ፥ ብለህ ትመክራለህ?
ደግሞስ
ለህዝብ ለወገን
ለራስህም ቢሆን
ማሰብ ከእኛ በላይ ፥ እንዲያው ለአሳር ነው
ማሰብህ ጥፋት ነው ፥ ማሰብህ ቅዠት ነው
እናም ለአንተ አኗኗር ፥ በርግጥ የሚበጀው
ራስህን ቆርጠህ ፥ ሃሳብህን ጥለህ
በእኛ ራስነት ፥ መኖርህ ብቻ ነው !

ሰላም ነህ ከተባልህ
የታለ ሰላሙ ፥ ስለ ምን ትላለህ?
አድገሀል ከተባልክ ፥ በርግጥም አድገሀል
ሌላ ማስረጃና ፥ ተጠየቁ ሁሉ ፥ ምን ያደርግልሀል?
እኛ ያንተ አለቆች ፥ እኛ ያንተ ገዦች ፥ በልተሀል እያልንህ
የታል የጠገብኩት ፥ ብለህ መሞገትን ፥ ከቶ እንደምን ደፈርህ
ምንስ አይነት ሰይጣን በልብህ ገባብህ ?
ጭራሽ ይባስ ብሎ ፥ የአንተን አሳቢነት ፥ ለእኔ ልታሳዬኝ
የሰላም ሰልፍ ብለህ ፥ ልትወጣ ሲያምርህ ሳይ ፥ እጅጉን ገረመኝ

መማርና ማወቅ ፥ ጥበብ የሚጠቅመው
ሀሳብን ለሚያከብር ፥ ህዝብና ንጉስ ነው
እናም ይህን እውነት ፥ ንገረን ከአልከን
እኛ ያንተ ገዦች ፥ አንወድም ማሰብክን
ደግሞም የማንወደው ፥ እጅግ የምንፈራው
ማሰብህን ብቻ ያይደል ፥ ማሰባችንም ነው!

በሚል መሪና ፥ ገዢ ፊት ስንቆም
የእኛ መማርና ፥ የእኛ ማወቃችን
ለጥበብ መሰደር ፥ ቀለም መቁጠራችን
መንስኤ ሲሆነን ፥ ለመገደላችን ለመወገራችን
ይህንን ስለማዬት ...
ስለ ቀደመ ምክርህ ፥ ምን ተሰማህ በእውነት ?

የኢትዮጵያ ሀገራችንን ሰላሟን ይመልስልን 💚💛❤️!

የኪጥበብ ቤተሰብ ይሁኑ !
@sundayschoolstudents
የሰንበት ት/ቤት ኪነጥበብ ክፍል !

ኪነጥበብ ዘሰንበት ት/ቤት

11 Dec, 20:02


++ስነ ጹሑፍ -  የባዕታ ለማርያም ግጥም!

(ርዕስ - ገባች ቤተመቅደስ!)

በቀናችው መንገድ  በሃይማኖት ጸንተው፣
በቅዱስ ጋብቻ ትእዛዙን አክብረው፣
ምግባር ከሃይማኖት አሰተባብረው  ይዘው፤
ጸሎት ያልተለየው ቅዱስ ሕይወታቸው፣
ኢያቄም ወሐና ልጅ ወልዶ ለመሳም ቢፈቅድም ልባቸው፣
ሳይወልዱ ሳይከብዱ ገፋ ዘመናቸው።
ጸሎታቸው ቢደርስ   ልጅን ቢሰጣቸው፣
ብጽዓት ነውና ከአምላክ ውላቸው
የአምላክ አያት ሆነው ድንግልን ሰጣቸው፡፡

ሐናና ኢያቄም  ከሁሉም ልቀዋል፣
ፈጣሪን የምትወልድ ድንግልን ወልደዋል።
ጸሎት ያልተለየው ቅዱስ ሕይወታቸው፣
የፈጣሪን እናት መውለድ አስቻላቸው።
የሐና የኢያቄም የከበረች ፍሬ፣
ምስጋና እየሰማች ውዳሴ ዝማሬ፣
በቤተ መቅደስ ውስጥ ልትኖር አገልግላ፣
ገባች ቤተ መቅደስ ሦስት ዓመት ስትሞላ።

ሐና ሰጥታት ስትሄድ አድርሳት ከመቅደስ፣
ድንግል ወደ እናቷ ስትሄድ ስትመለስ፣
ዝቅ አለ ፋኑኤል ከሰማይ ወረደ፣
በክንፎቹ ጋርዶ መግቧት ዐረገ።
የሦስት ዓመት ሕፃን ትንሽ ብላቴና፣
የበኩር ልጃቸው የኢያቄም የሐና፡፡

በክንፎቹ ጋርዶ መልአክ የመገባት፣
ቤተ መቅደስ ገባች የአማኑኤል እናት።
ሰማዮችን ቀደህ ምነው ብትወርድ ያለው፣
የኢሣይያስ ስብከት ፍጻሜው ደርሶ ነው።
አምላክን ለመውለድ ቀድማ የታሰበች፣
አሥራ-ሁለት ዓመት ቤተ መቅደስ ኖረች።
ኢያቄም ወሐና እናትና አባትሽ፣
ኅልም አይተው ነበረ ድንግል መጸነስሽ።
ተአምሩ ብዙ ነው እም አምላክ ልደትሽ፣
ቤተ መቅደስ ሆነ ድንግል ሆይ ዕድገትሽ።

ዝናብ የታየብሽ ትንሿ ደመና፣
አንቺ መሶበ ወርቅ ውስጥሽ ያለ መና።
«እንደ ልቤ» ብሎ አምላክ ስም የሰጠው፣
ከእረኝነት መርጦ ንጉሥ ያደረገው፣
በጸጋ ተመልተሽ ቢመለከት ከብረሽ፣
በግርማ በሞገስ ወርቅ ተጎናጽፈሽ፣
በሰማይ በክብር በቀኝ በኩል ቢያይሽ፣
ወትቀውም ንግሥት ብሎ ተቀኘልሽ።
የሁላችን ተስፋ የአዳም የስብከት ቃል፣
የነቢያት ምሥጢር የሲና ሐመልማል፣
የሕዝቅኤል ራእይ የነቢያት ትንቢት፡
ቅኔው ለሰሎሞን መዝሙሩ ለዳዊት።

ተሰምቶ አይጠገብ ውዳሴሽ መብዛቱ፣
ለአባ ሕርያቆስ አንቺ ነሽ ድርሰቱ።
እናታችን ማርያም ጥዑመ ስም ያለሽ፣
ጥዑመ ስም ያለው ክርስቶስን ወልደሽ፣
ዓለም ይባረካል ይኸው እስከ ዛሬ፣
መድኃኒት ነውና ከአንቺ የወጣው ፍሬ።
የነደደው እሳት በሲና ሐመልማል፣
ምሳሌ ለድንግል ምሳሌ ነው ለቃል።
ያንን ነበር ያየው ሙሴ በድንቁ ቀን፣
መለኮት ማደሩን በድንግል ማኅፀን።

አባ ሕርያቆስ ውዳሴሽ በዝቶለት፣
የምስጋናሽ ነገር ምሥጢር ተገልጦለት፣
የክብርሽን ነገር በአድናቆት በማየት፣
ይመሰክር ጀመር በጣፈጠ አንደበት።

እግሩ ከምድር ሳይለቅ ሐሳብ አመጠቀው፣
በደመና ጭኖ የኋሊት ወሰደው።
ያሬድ በዝማሬው ንዑድ ክቡር ያለሽ፣
ድንግል እናታችን የገነት ቁልፍ ነሽ።

ወስብሐት ለእግዚአብሔር ወለወላዲቱ ድንግል ወለመስቀሉ ክቡር አሜን።

=====///======

እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያምም ሰማያዊ ኅብስትና መጠጥ እየተመገበች  በቤተ መቅደስ ለ፲፪ ዓመታትም ኖራለች። የእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም አማላጅነትና ተራዳኢነት አይለየን፤ በረከቷ ይደርብን፤ አሜን!!!

የኪጥበብ ቤተሰብ ይሁኑ !
@sundayschoolstudents
የሰንበት ት/ቤት ኪነጥበብ ክፍል !

ኪነጥበብ ዘሰንበት ት/ቤት

11 Dec, 18:32


++ ሥነጽሑፍ - ግጥም !

( ርዕስ - ምን ይሆን ምስጢሩ ? )

መርከብ ልቦናችን ፥ በባህር ዓለም ውስጥ
ማዕበል ሲያማታው ፥ በሞገድ ሲናወጥ
የኑፋቄና የክህደት ፥ ጎርፍና ውሽንፍር
የዓለማዊነት ትኩሶት ፥ የዘረኝነት ሀሩር
በላያችን ሲወርድ ፥ ልባችን ሲሸበር
እንዲህ ስንቸገር ...
በጥፋት ውሃ ፊት ፥ ከሞት ጋር ተፋጥጠን
የፈርዖን ግልምጫ ፥ ፊታችን ሲገርፈን
የዲዮቅልጥያኖስ ጡጫ ፥ ሲያደማን ሲገፋን
እንዲህ ባሁን ዘመን ...
እናርፍበት ወደብ ፥ እንከለልበት ጥሩር
እንመክትበት ጋሻ ፥ እንሸሽበት አውጋር
መጠጊያ ፍለጋ ፥ ነፍሳችን ተርባ
በዓይናችን ሲያቀርር ፥ ፅኑ ትኩስ እንባ
ድረስልን አምላክ ፥ ራራልን ጌታ
የሚል ተማፅኖና ፥ የምዕመናን ዋይታ
መቅደሱን ሲሞላው ...
በጸሎቱ የሚደግፍ
በቃሉ የሚያሳርፍ
ለሕይወታችን ጨው ፥ ለጨለማችን ብርሀን
የሕይወት መንገድን ፥ ገልጦ የሚያሳየን
የምንድንበትን መርከብ ፥ የአሰራር ብልሀት
ጥበብን የሚነግረን ፥ የምስጢር ባለቤት
ኖኅን የምንሻ ፥ ሳለን የእናንተ ልጆች
ኖኅን የምትመስሉ ፥ ብፁዓን አባቶች
በአሳቻ ሰዓት ፥ ከእኛ መለየት
ምስጢሩ ምን ይሆን ፥ አልገባኝም በእውነት?

ከፊታችን ሆኖ ፥ በእረኝነት በትር
የኤርትራን ባህር ፥ ከፍሎ የሚያሻግር
መዓትና መቅሰፍት ፥ በእኛ ላይ እንዳይወርድ
ራሱን አስይዞ ፥ ስለ እኛ የሚማልድ ፥ ስለ እኛ የሚጋረድ
የክርስቶስን መንጋ ፥ ከጥፋት የሚያድን
ከነዓን ሊያስገባን ፥ የተሰጠው ኪዳን
ሙሴን የምናሻ ፥ ልጆቻችሁ ሳለን
የደጋግ አባቶች ፥ ከእኛ ዘንድ መለየት
ምስጢሩ ምንድን ነው ፥ አልገባኝም በእውነት !

ስለ ሀገርና ስለ ሃይማኖት ክብር
በጥብዓት የሚቆም፥ አዋጅ የሚያስነግር
ሰማዕትነትን ባርኮ ፥ ለእኛ የሚሰጠን
የእምነት አርበኛ ፥ ስንሻ ጴጥሮስን
አሁን በዚህ ሰዓት ፥ የእናንተ መለየት
ምስጢሩ ምን ይሆን ፥ አልገባኝም በእውነት !

ይህንን ስለ ማሰብ ፥ ይህንን ስለ ማየት
ሀዘናችን በረታ ፥ አቃተን መጽናናት

እንኪያስ እኛም ፥ ከእናንተ አባቶቻችን አንበልጥም
በረከታችሁ ደርሶን ፥ የምናርፍበት ተራው የኛ ይሁን !

=====///=====

ልበ አምላክ ቅዱስ ዳዊት፥ “ ኢትዮጵያ ታበጽሕ እደዊሃ ሃበ እግዚአብሔር/ ኢትዮጵያ እጆቿን ወደ እግዚአብሔር ታደርሳለች” ብሎ የዘመረልሽ የአምላክ ባለሟል እምዬ ኢትዮጵያ ሆይ መቼ ይሆን ግን መከራሽ የሚያበቃው? መች ይሆን ግን ፍጻሜው? መች ይሆን ሰላም የሚሰፍነው? መቼ ይሆን ግን የአንድነት ወንጌል ሲሰበክ የምንሰማው . . ?!

በአማን ሠላም፣ አንድነት እና ፍቅር ይቅርባይ አምላካችን አብዝቶ ለሀገራችን እምዬ ኢትዮጵያ እንዲያድለን ከልብ እመኛለሁ !!

የኪጥበብ ቤተሰብ ይሁኑ !
@sundayschoolstudents
የሰንበት ት/ቤት ኪነጥበብ ክፍል !

ኪነጥበብ ዘሰንበት ት/ቤት

09 Dec, 04:56


ስለ ማኅበረ ቅዱሳን ምን ያህል ያውቃሉ ? 

ማኅበረ ቅዱሳን በሐዋርያነት ተልዕኮ ወጣቱን ትውልድ ከቤተ ክርስቲያን የሚያስተዋውቅ እግዚአብሔር ያከበራቸው የነቢያት፣ የሐዋርያት፣ የጻድቃንና የሰማዕታት በአጠቃላይ የቅዱሳን ገድል፣ ትሩፋትና አማላጅነት የሚዘከርበት በመሆኑ ‹‹ማኅበረ ቅዱሳን›› የሚል ስያሜውን አግኝቷል፡፡

ማኅበሩ የተመሰረተው በከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ሆነው በቅድስት ቤተክርስቲያን የተለያዩ መንፈሳዊ አገልግሎቶች ሲፈጽሙ የቆዩ ወጣቶች በአንድ ማኅበር ቢሰባሰቡ የሚሰጡት አገልግሎት ከፍተኛ እየሆነ ሲመጣ በመላእክት ስም፣ በእመቤታችን ስም፣ በቅዱሳን ስም የተሰበሰቡት ሁሉ አንድ ማኅበር ለመመሥረት ወሰኑ፤ ወስነውም አልቀሩ መሠረቱት፤ ማኅበረ ቅዱሳንን፡፡

ማኅበረ ቅዱሳን አሁን ላይ የቅድስት ቤተ ክርስቲያቱ መዋቅር ያልሸፈነችውን ክፍተቶች በመሙላት ወደ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማ የሚገቡትን የዘመኑን ትውልድ ከመንፈሳዊነትና ከቅድስት ቤተ ክርስቲያን ትምህርት ጋር በማዋሐድና ከአበው በማቀራረብ ቤተ ክርስቲያን የምትጠብቅበትን ድርሻ እንድንወጣ ለማድረግ የማኅበረ ቅዱሳን አገልግሎት አስፈላጊ ነው፡፡

የማኅበረ ቅዱሳን ዋና ዓለማውም በከፍተኛ ትምህርት ተቋማ ውስጥ የሚማሩ ወጣቶችን በማኅበሩ ሥር አደራጅቶ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያንን እምነት፣ ሥርዓት እና ትውፊት እንዲማሩ እና የአባቶች ተተኪ እንዲሆኑና፣ የቤተክርስቲያን እምነትና ሥርዓት ሳይለውጥ ተጠብቆ ከትውልድ ወደ ትውልድ እንዲተላለፍ ለማድረግ ይቻል ዘንድ ለዘመኑ ትውልድ ትምህርተ ሃይማኖት እንዲዳረስ ማድረግ ነው።

እንዲሁም ከሚመለከታቸው የቤተ ክርስቲያኒቱ አካላት ጋር በመነጋገርና በማስፈቀድ ትምህርተ ወንጌልን በተለያዩ ዘዴዎች በመጽሔት፣ በጋዜጣ፣ በበራሪ ጽሑፎች፣ በካሴት እና በመሳሰሉት እንዲስፋፋ በማድረግ፣ የተማረው የኅብረተሰብ ክፍል የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያንን በገንዘብ፣ በዕውቀቱና በጉልበቱ እንዲያገለግል አስፈላጊውን ሁሉ እያመቻቸ ስለ ኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ጥናት የሚያደርጉ ሰዎችን በተለይ ወጣት ምሁራንን ማበረታታና በሚቻለው ሁሉ መርዳት፡፡

#የማኅበሩ_ርእይ ፦ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን መንፈሳዊ አገልግሎትና ኢኮኖሚያዊ አቅም ተጠናክሮ የጌታችን የመድኃኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ትምህርተ ወንጌል በመላው ዓለም ተስፋፍቶ በሃይማኖት ጽኑዓን የሆኑ ምእመናን በመላው ዓለም በዝተው ማየት፡፡

#የማኅበሩ_ተልእኮ ፦ ማኅበሩ የሳይንስና ቴክኖሎጂ ውጤት የሆኑትን የተለያዩ ትምህርተ ሃይማኖት ማስፋፊያ ዘዴዎችን በመጠቀም ግቢ ጉባኤያትና ምእመናን የወንጌልን ትምህርት፣ ሥርዓት፣ ትውፊት፣ እንዲያቆዩና እንዲጠበቁ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን አስተዳደራዊ መዋቅር እንዲጠናከር አቅሙ እንዲያድግ ማድረግና በየዘመኑ የሚከሰቱ ተለዋዋጭ ሃይማኖታዊ፣ ማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ችግሮች በመቃኘት የቤተ ክርስቲያኒቱን ሐዋርያዊ አገልግሎት ማጠናከር ነው፡፡

ስለዚህ የቅድስት ቤተ ክርስቲያናችን ጌጥ፣ ዋልታና ማገር የሆነውን «ማኅበረ ቅዱሳንን» ሁላችንም የኦርቶዶክሳዊት ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን ልጆች በቻልነው መንፈሳዊ አገልግሎት ሁሉ መደገፍ ሐዋርያትነት ግዴታ አለብን !!

በተጨማሪም ስለ ማኅበረ ቅዱሳን ይበልጥ ለማወቅ በማኅበረ ቅዱሳን ኦዲቶሪያል ፖርድ ተዘጋጅቶ ከግቢ ጉባኤ ያገኘሁትን ዶክመንተሪ ቪዲዮ ተመልክታችሁ ሁላችሁም እወቁትና ተጠቀሙበት እላለሁ !!

https://youtu.be/4ND2C0cxR8w?si=VFmZCta-9BneQwkU

Subscribe 👇 Our YouTube Channel

ዩቲዩብ=https://www.youtube.com/@TobiyaMedia

እምነት፣ እውነት፣ እውቀት፣ ጥበብ፣ ፍቅር ሰውን ነጻ ያወጣሉ !

#ጦቢያሚዲያ #TobiyaMedia
© ጦቢያ ሚዲያ

ኪነጥበብ ዘሰንበት ት/ቤት

07 Dec, 11:17


++ ሥነጽሑፍ - ግጥም !!

( ርዕስ - ሰንበት ተማሪ ነኝ! )

ትዕዛዙን ልከተል ፣ ያቅሜን የምታትር
ዘወትር በምስጋና ፣ ስሙን የምዘክር
ከማህሌቱ ቆሜ ፣ ኪዳኑን አድርሼ
ሰዓተ ሩፋዱን ፣ ፆሜ አስቀድሼ
እርሱ እንደወደደኝ ፣ ልወደው የምሻ
ቀዳሚ የምገኝ ፣ ከፀበሉ ቅምሻ

በትጋት፣በፍቅር
ምስጢር ፣ ምመረምር
አጋንንት የሚጥል ፣ ንፁህ እምነት ያለኝ
የብርሃን ኮከብ ፣ ሰንበት ተማሪ ነኝ።
ስለ ማህተቤ አንገቴን የምሰጥ
ለሚያልፍ ማዕበል ፣ የማልንቀጠቀጥ
ወንጌልን ገልጬ ፣ የምማር አንድምታ
የረቀቀ ምስጢር ፣ ቅኔ የምፈታ

የትግስቴን አጥር ፣ ክፋት የማይንደው
ጠፊ እንግዳ ስብከት ፣ ልቤን የማይወስደው
እምነቴን አስይዤ ፣ ለንዋይ የማልወድቅ
ዝሙትን የምሸሽ ፣ የማልዋሽ ፣ የማልሰርቅ
ሰባት ጊዜ ብወድቅ ፣ ሰባቴ ምነሳ
በጥበብ በብልጠት ፣ የማጠፋ አበሳ

መመላለስ ሳይሆን ፣ መመለስ የምመኝ
የፃድቅ አወዳሽ ፣ ሰንበት ተማሪ ነኝ።
መልካም ምግባር ይዤ ፣ ከደጁ ማልጠፋ
ተግሳፅ የምቀበል ፣ ክብር የማልገፋ
በሽብሻቦ እልልታ ፣ በያሬድ ዝማሬ
በውዳሴ ማርያም ፣ በኢየሱስ ፍካሬ

ቀኔን የማሳምር
በፈተና ዓለም ፣ ምሬት የማልሰፍር
ለውበት ሰግጄ ፣ ተስፋዬን የማልሸጥ
እንደ ወይራ በትር ፣ የማልለማመጥ
ሰንበት ተማሪ ነኝ ...
በቅዱሳን ስፍራ ፣ ፀሎት አደርሳለሁ
የወላዲተ አምላክ ፣ምልጃዋን አምናለሁ።

====///=====

ይህ ቻናል ለሰንበት ት/ቤቶችና እና ለግቢ ጉባኤዎች የኪነጥበብ ክፍሎች ተደራሽ ይሆን ዘንድ ተከፈተ። ቻናሉ ከዓመት እስከ ዓመት የኪነጥበብና ሥነጽሑፍ፣ ጭውውትና ድራማዎችን ወ.ዘ.ተ. . . ሁሉን በአንድ ስለሚያቀርብላችሁ ለሰንበት ት/ቤት ጓደኞቻችሁ ሸር | Share አድርጉት !

እስቲ ሰንበት ተማሪዎች እጃችሁን አውጡ 🙏

የኪጥበብ ቤተሰብ ይሁኑ !
@sundayschoolstudents
የሰንበት ት/ቤት ኪነጥበብ ክፍል !

ኪነጥበብ ዘሰንበት ት/ቤት

30 Nov, 08:29


++ ስነ ጹሑፍ - የሕዳር ጽዮን ግጥም !

( ርዕስ - የማርያም ንግስ ዕለት )

የማርያም ንግስ ዕለት
አደፋ ነጠላ፣
በቀጠነ ገላ ነፋስ በሚጥለው
የነተበ ጫማ፣
ጥቁር ያዘን ቀሚስ ኑሮ ያጨቀየዉ፣
ለብሳ የተገኘች፣
ከቤተክርስቲያን አፀድ ቆማ ከዋርካ ስር፣
አንዲት ሚስኪን ባልቴት ትለማመን ነበር።

አደራሽን ማርያም፣
አደራሽን ማርያም፣
እበላው የለኝም መሶቤ ተራቁቶአል፣
እለብሰው የለኝም ጀርባዬ በርዶታል፣
ወድቃ እየተነሳች፣
እምባ እያፈሰሰች፣
ተስፋዋ ማርያምን ትለምናት ነበር።

የደብሩ አለቃ፣
ካባ ላንቃ ለብሶ ሞጣህቱን ደርቦ፣
ልክ የሌለው ቦርጩን ወደ ፊት ተርቦ፣
የንግሱን ምዕመን ወደ ፊቱ ስቦ፣
ጮክ ብሎ ያወራል፣
ጮክ ብሎ ያስተምራል፣
፩፦የመቅደሱ ቀለም ሊታደስ ይገባል፣
፪፦የካህናት ደመወዝ ሊጨመር ግድ ይላል፣
፫፦ደጀ ሰላም ወንበር እጅጉን ያንሰናል።

አናም....
በዚህ ታላቅ ደብር ይህ ችግር ስላለ፣
ለማርያም የሚሆን እጃቹ የት አለ?
እያለ...
ህዝብን ያስተምራል፣
ህዝብን ይደልላል።

ለንግሱ የመጡ፣
ባለ ብዙ ብሮች፣
ብዙ ባለጠጎች፣
ጥለት የለበሱ በሽቶ የራሱ፣
ቆመዉ  የነበሩ እፊት ከመቅደሱ፣
ቀለም እንዲቀባ እንዲታደስ ደብሩ፣
ለደጀ ሰላሙ ደግሞም ለወንበሩ፣
በሺ የሚቆጠሩ
ብሮች ወረወሩ።

የደብሩ አለቃ ግንባር በጣም ወዛ፣
የሚወረወረው  ብሩም በጣም በዛ፣
የዛች የሚስኪን ነፍስ፣
ያች ታላቅ መቅደስ፣
ቆማ ከዋርካ ስር፣
ተስፋዋ ማርያምን ትለማመን ነበር።

አደራሽን ማርያም፣
አደራሽን ማርያም፣
እበላው የለኝም መሶቤ ተራቁትዋል፣
እጠጣው የለኝም ማድጋዬ ጎድልዋል፣
እለብሰው የለኝም ጀርባዬን በርዶታል፣
አንቺው ነሽ ተስፋዬ የኔ ተስፋ ሞትዋል፣
ወድቃ እየተነሳች፣
እምባ እያፋሰሰች፣
ግን ለዛሬ ለክብርሽ እንዲሆን፣
ተቀበይ ስጦታ ውሰጂ አምሃዬን፣
የምዋች ባሌን ማስታወሻ የአንገት ሃብሌን።

ወስብሐት ለእግዚአብሔር
ወለወላዲቱ ድንግል
ወለመስቀሉ ክቡር ይቆየን !!

የተወደዳችሁ የኪነጥበብ ዘሰንበት ት/ቤት ቤተሰቦች፥ እንኳን ለሕዳር ፅዮን ማርያም አመታዊ ክብረ በዓል በሰላም አደረሰን  አደረሳችሁ !!!

ሕዳር ፳፩ ቀን የእመቤታችን አመታዊ ክብረ በዓል ነዉ ብለን በተለየ መልኩ የምናከብርበት ምክንያት ታቦተ ጽዮን በምርኮ ከሀገረ ፍልስጤም “ዳጎን” የተባለ የአሕዛብ ጣኦትን አድቅቃ በድል የተመለሰችበትን ዕለት በማሰብ እናከብራለን። እንዲሁም ታቦተ ጽዮን ንጉሡ ሰለሞን ወደ ሰራላት ቤተ መቅደስ በክብር የገባችበትን እለት በማሰብ ነዉ። ይኸውም ቀዳማዊ ሚኒሊክ ከአስራሁለቱ ነገደ እስራኤል የበኩር ልጅ ጋር  ሊቀ ካህናቱን አዛርያስንና ታቦተ ጽዮንን ይዞ አክሱም የደረሰበትን እለት በማሰብ የምናከብረው ታላቅ በዓል ነዉ።

ጽዮን ማርያም ሆይ ብረሳሽ ቀኘ ትርሳኝ ባላስብሽም ምላሴ በጉሮሮየ ትጣበቅ ፤ . . . ድንግል እናታችን ጽዮን ማርያም ሆይ የአስራት ሀገርሽን ኢትዮጵያችንን ሰላም አድርጊልን አሜን !!

ኢትዮጵያ ለዘላለም ትኑር !!

የኪነጥበብ ቤተሰብ ይሁኑ !
@sundayschoolstudents
የሰንበት ት/ቤት ኪነጥበብ ክፍል

ኪነጥበብ ዘሰንበት ት/ቤት

29 Nov, 11:03


++ ኪነጥበብ - መነባንብ !!

( ዳግም ምን አሏቸው? )

እናታለም ተዋህዶ
ባንችነትሽ የሚኮራ
በስምሽ ስም የሚጠራ
ዛሬ ጠፋ የሚያበራ
ስለፍቅርሽ ቀልጠው ነደው
ስለ አምላካቸው ተማግደው
በሃይማኖት ፍቅር እጅጉን ተነክተው
ካንቺ ጉያ በኖሩ
እግሮችሽ ስር በተማሩ
ለምን/2/ ተዋህዶ ጠላቸው መንደሩ
ምን አሏቸው ደግሞ ቅዱሳን አበውን
አንቺን እናት እምነት ከዚህ ያበቁትን
ምን አሏቸው ደግሞ አበው ሊቃውንትን
አንድምታውን ፈተው ባመሰጠሩልን
ሚስጢርን መሰጥርው ለኛ ባኖሩልን
ብራና ወጥረው አምድ በፃፉልን
ውለታቸው ታዲያ ይህ ነው?
ስላደረጉልን የምንከፍለው
ጭራሽማ አምላክ ባከበራቸው
አክሊሉን በደፋላቸው
በሀሴት በተቀበላቸው
ልባችን ለምን አመፀ ለምንድን ማይቀበል
ተፈትኖ ያለውን የተፃፈላቸውን የህይወት ገድል
ለምንድን! የማናምን በምልጃቸው
እሱ እግዚአብሔር በሰጣቸው
ደግሞስ ምን አሏቸው?

እሄ......./በለቅሶ/

ሁሌም እውነት ነው
መልከ መልካም ሙሽራዋ
የፀናች በድንግልናዋ
ማን አለ እንደዝች እንደ ቅድስት እናት
ያልተረታ በነገስታት
አንገቷን ለሰይፍ የሠጠች
ክርስቶስን ብላ የኖረች
እኮስ ምን አሏት ይህችን እናት
የስጋ ፋላጎት ያልሠበራት።
ተዋህዶ እናት አለም
እንደድሮ ፀንቶ የሚኖር ልጆችሽ ፈርተዋል የሉም
የምልጃ ታላቅ ስራ
ለህዝቦቿ እያበራ
እየለመኑ ምህረት
ሲያስተዳድሩ አናብርቱ አናብስቱን
ከባህር ውስጥ የፀለዩ
በስራቸው የተለዩ
ገብረ መንፈስ ቅዱስ ታላቅ አባት
ምን አሏቸው ይሆን አንቺ ምስኪን እምነት
አይደል እንዴ ተዋሕዶ
ስጋቸውን የገበሩ
በእርኩሳን መናፍስት የተፈሩ
በእግዜር ጥበብ የከበሩ
ምን አሏቸው ቅዱሳንን ሰማዕታት ፃድቃናትን
የክርስቶስ ደቀመዝሙር ሃዋርያት
ትንቢት ፀሀፊ ነቢያት
ተዋህዶ ውዷ እናቴ ምን አሏቸው?
በዕቶን ውስጥ ማግደዋቸው
እንደ እንስሳ አረደዋቸው
በቁም ቆመው ቆዳቸውንገፈዋቸው
ላንቺ ቋሚ ልጆችሽን ምን አሏቸው
አይ ተዋህዶ....

በአንድ እግራቸው ሰባት ዓመት የፀለዩ
ባንቺ የፍቅር መግቦትሽ ከዓለም ላይ የተለዩ
የተክለሃይማኖት እናት አንቺ ቅድስት እምነት
አያማልዱም ሲላቸው ልጆችሽን
ዛሬ ምን ተሰማሽ ንገሪኝ በእውነት
የልጆችሽን ምልጃ ሊያስታርቅ ሊቃትት
መቻል ደጉ....
ስንቱን ቻልሽው እናታለም....
እሄ......

የእመብርሃን አስራት ኢትዮጵያ
የቅዱሳን የፃድቃን መፍለቂያ
አንቺስ ጋር ምን አሏቸው
መሠረቶችሽን ሲገፏቸው
ምን አልሻቸው ይሆን እንደው ዝም አልሻቸው
የመኖሬ ምስጢር
የመኖሬ ዘመን እምነቴ እሷናት ብለሽ ሳትነግሪያቸው
የቅዱሳንን ምልጃ የፃድቃንን ምልጃ ሳታሰተምሪያቸው
ለዚህ ይሆን አማላጅ አይደሉም ብለው የናቋቸው
ለነገሩ አይደለም
ስንቴ አስተማርሻቸው
በግልጽ አሳይተሽ አስቀምጠሽላቸው
ሰብከሻቸው ነበር ጊዜ ነጎደና በመናፍቅ እስር
የማማላዳቸው ያን ሁሉ ምስክር
ቀበሩት ከአፈር
እና ተዋህዶ ያንቺን ጓዳ የሚያውቁ
በፍቅርሽ ማነቆ የታነቁ
ቀስ በቀስ ወጡ እያለቁ
አሁንማ እናቴ
ባንቺ ጉያ እየኖሩ
አንቺንም እያሳፈሩ
ፈሉብሽ እንደ አሸን ቅዱሳንሽን እየካዱ
አያማልዱም ብለው ረግጠው እየሄዱ
ታዲያ ምን አሏቸው
ያንቺን ልጆች በቤታቸው
ዛሬስ ምን አሏቸው???

ወስብሐት ለ እግዚአብሔር ወለወላዲቱ ድንግል ወለመስቀሉ ክቡር አሜን !!

የኪነጥበብ ቤተሰብ ይሁኑ !
@sundayschoolstudents
የሰንበት ት/ቤት ኪነጥበብ ክፍል !

ኪነጥበብ ዘሰንበት ት/ቤት

31 Jul, 20:12


ርዕስ  - ዝም በል . . . !

አገርና ሃይማኖት ይለያል ይሉኛል፣
ኢትዮጵያን ክብሬን ስል…
ይሄን ፖለቲካ አስቀምጠው ይሉኛል፣
አፌን ያስይዙኛል፣
መንግሥትን መገሰፅ አትችልም ይሉኛል፣
ምዕራፍ ቁጥር ጠቅሰው ሙግት ይገጥሙኛል፣
ይከራከሩኛል።

የእግዚአብሔር መንግሥት በሚሰበክበት፣
ሥጋውና ደሙ በሚፈተትበት፣
ይሄን የማርክስን የፑሉቶን እብደት፣
የእነ ፍሮይድ'ን፣ የእነ አፍላጦንን ፍልስፍና ቅዠት፣
የእነ ሂትለርና የእነ ሞሶሎኒ የጭካኔ ዝቅጠት፣
አትችልም በአትሮንሷ ልትዘባርቅበት፣
እያሉ ይሉኛል፣
አፌን ያስይዙኛል፣
ትርጉሙን አፋልሰው ግራ ያጋቡኛል።

ሲገድሉህም ዝምበል ሃይማኖተኛ ነህ፣
ሲዘርፉህ ተዘረፍ መንፈሳዊ ሰው ነህ፣
ፍርድ ቢጓደልም ደሃዋ ብታለቅስ፣
ራሷ ትወጣው አታምጣው ከመቅደስ፣
አንተ ምን ቸገረህ? ሥራህ እንደው መቀደስ!፣
የተገደለች ቀን ለፍትሐቷ መድረስ።
እያሉ ይሉኛል፣
ሕይወቷን ነጥቀውኝ ሞቷን ይሠጡኛል።

ድንገት ትክ ብዬ…
በእጄ ላያ ያለውን አርዌ በትሬን ሳየው፣
ሙሴ ሲዋቀሰኝ ሲሟገተኝ አየሁ፣
ዝምታህን ስበር ወይ በት'ሬን ተወው።
እያለ ወቀሰኝ፣
ቃሉን አስታወሰኝ።

ለሕዝቡ ነፃነት ከፈርዖን ቤት ወጥቶ፣
የግብፅን ብዙ ወርቅ ምቾቱን ሰውቶ፣
አብሯቸው ሲሰደድ ብድራቱን አይቶ፣
ትዝ አለኝ ታሪኩ፣ ትዝ አለኝ ጭካኔው፤
ሕዝቡ አምላክ በድሎ ላጠፋው ነው ሲለው፤
ከሕይወት መፅሐፍ ደምስሰኝ እንዳለው፤
ይሄንን ዘፀአት አምጥቶ ፊቴ ላይ ድንገት ዘረገፈው።

ነገረኝ አጥብቆ… ሕዝብ አገር ሳይኖረው፣
እምነት ብሎ ነገር፣
ኪዳን ብሎ ነገር፣
ባሕልና ትውፊት እንደማይሞከር።

ለዚህ ነው ፈርዖንን "ሕዝቤን ልቀቅ" ያለው፣
ግብፅ ምድር ሳለ ኪዳኑን ያልሠጠው፣
ታቦቱን ያልሠጠው፤
የፂዮን ዝማሬ በባቢሎን ወንዞች እንዳይዘመር ነው።
ታዲያ ለምንድነው?
እኔስ ፈርዖኖቼን፣
እኔም ጨቋኞቼን፣
ተው! እንዳልላቸው፣
ዝም በል የምባለው?
በሃይማኖት ሰበብ፣
አገሬን ሲነጥቁት ቁጭ ብዬ የማየው፣
መስዋዕቴን ወስጄ የት እንድሰዋው ነው?

ኧረ ዝም አልልም፤ ማንስ ዝም እንዳለው?!
ርስቱን ተነጥቆ ናቡቴ ሲገደል፣
ኤልያስ ዝም አለ?!
ንጉሡን ገስፆ እጥፍ ያስከፈለ፣
ታዲያ ምን አገባው? ሃይማኖት አይደለ!
አንድ ደሃን እንጂ አክዓብ ያስገደለ።

ኦዝያን ንጉሡ ወደ መቅደስ ገብቶ፣
የአሮንን ክህነት በሥልጣን ቀምቶ፣
ለማጠን ሲጀምር በድፍረት ተሞልቶ፣
ካህኑ አዛርያስ መች ዝም አለው ከቶ?!
መቅደሱን እስኪለቅ ጨርሶ እስኪወጣ፣
ቦታ አልነበረውም ለንጉሡ ሥልጣን ለኦዝያን ቁጣ።

ኢሳያስ ነው እንጂ፣ ኢሳያስ ነቢዩ፤
ይሄን ድፍረት አይቶ፣
በዝምታ ቢያልፈው ንግሥናውን ፈርቶ፣
እግዚአብሔር ተቆጣ ትንቢቱን ነጠቀው፣
ከናፍሩን መታ በለምፅ አነደደው፣
በዝምታው ሰበብ እግዚአብሔር ተለየው።

ይሄን እያያችሁ አፌን አትለጉሙኝ፣
ዝምታ እመም እንጂ፤ "ወርቅ ነው" አትበሉኝ፣
ባለቦታው ተረት ልቤን አታድክሙኝ፣
ላገሬ ለእምነቴ ልጩህላት ተውኝ።

ያ! ጃንደረባ'ኮ ፊሊጶስ ያገኘው፣
ብሉይ ኪዳን ይዞ መንፈስ ቅዱስ ያየው፣
በማመን ሲጠመቅ በሐዲሱ ኪዳን፣
በልቡ መቅደስ ውስጥ ይዟት ነው ኢትዮጵያን።
መጥቶ የነገረን ይህንን ምስጢር ነው፣
እኛም በክብር ይዘን ጠብቀን ያኖርነው፣
ጠዋትና ማታ በዜማ ምንጮኸው።

ተዋሕዶ እምነቴ፣
ኦርቶዶክስነቴ፣
ያገሬ ፀጋ ነው፤
ኢትዮጵያዊ ባልሆን ከሌላ ምድር ላይ የማልቀበለው።
ታዲያ ሃይማኖቴን፣
ከኢትዮጵያዊነቴ፣ እንዴት ነው ምለየው?

እምዬ ምኒሊክ በድንግል ስም ምለው…
አዋጁን ያወጁት፣
የግምባሯን ማሪያም፤
ያራዳውን ጊዮርጊስ ይዘው የዘመቱት፣
ባንድነት ቢያምኑ ነው፣
አገሩን ከእምነቱ ለይተው ባያዩት።

አቡኑም ይናገር ጴጥሮስ ሰማዕቱ፣
እንኳን ሰውን ቀርቶ ምድርን መገዘቱ፣
ባንድነት ሲቆም ነው ላገሩ ለእምነቱ።

እናም ይበቃኛል ዝም በል አትበሉኝ፣
ብትሉም… አልልም!፤
ከሚሞት ጋር እንጂ ገዳይ ጋር አልቆምም።
ሕዝብ ሳይኖር አገር፣
አገር ሳይኖር እምነት በፍፁም አይኖርም።

(በዲያቆን መኩሪያ ጉግሣ)

ውድ ኢትዮጵያውያን በሆነው እየሆነ ባለው በሚሆነው ነገር ሁሉ አትጨነቁ። እየሆነ ያለውን ነገር በጥሞና አስተውሉ፤ ዙርያ ገባውን በጥንቃቄ  ተመልከቱ ፤ ዓለም ከየት ወዴት እየሄደች እንደሆነ መርምሩ፤ የዘመኑንም መለወጥ ተረድታችሁ ስለ ራሳችሁ እዘኑ።

ቅዱስ እግዘብሔር የመግረፊያ ጂራፉን በምድሪቱ ላይ ባሉ አምሳለ ቀያፋ ወሐና ላይ ይጥላል፤ ከመጋረጃ በስተጀርባ ያለውን ጉድ በገሃድ ይገልጥ ዘንድ በሹመት ያዋርዳል፤ ይህ ሁሉ የሚሆነው ስንዴና እንክርዳዱን ይለይ ዘንድ ነው። አሁን ሁሉም ነገር ይገልጥ ዘንድ ከአውደ መህረቱ ላይ መለከቱ ይነፋል . . .ጊዜ ገቢር ለኩሉ ይሉ ዘንድ ንቁም በበህላዌነ ! ! !

የኪነጥበብ ቤተሰብ ይሁኑ !
@sundayschoolstudents
የሰንበት ት/ቤት ኪነጥበብ ክፍል !

ኪነጥበብ ዘሰንበት ት/ቤት

25 Jul, 13:55


++ እናት ሀገር ኢትዮጵያ !

“አንቺ እማማ ኢትዮጵያ  አንቺ እናት ዓለም”
ሎሬትሽ እያቆላመጠ  ይነግርሽ እንደነበር በቀለም፤
እወቂበት ከእንግዲህ  አብጂለት ፍቱን መላ፣
የሚሞትልሽ እንጂ  የሚገልሽ ላይበላ፤

ህዋሳትሽ ይንቀሳቀስ  ሰሜን-ደቡብ ምዕራብ-ምሥራቅ፣
የአለላ ተምሳሌቱ  የሕዝቦችሽ ኅብረት ይድመቅ፤
ብድግ በይ ተራመጂ  በእንፉቅቅ መዳኽሽ ያብቃ፣
የውብ ሕይወት አዲስ ምዕራፍ  በግዛትሽ ይገንባ!

እናት አገር ባለታሪክ  ተነሽ ቤትሽን አጽጂ፣
የተዝረከረከውን  በፕሮፓጋንዳ ፈንጂ፣
በተከፈተው ጉድጓድ ይግባ  ጠራርገሽ አስወግጂ።
ዳግም እንዳትረቺም  ባባይ-ጠንቋይ ጋጋታ፣
እጆችሽን ከምር ዘርጊ  ወደ ፈጠረሽ ጌታ፣
አምላክሽ ካንቺው ነውና  የእስላም የክርስቲያኑ፣
ፍጠኚ ታሪክ ይከወን  ሳያልፍብሽ ዘመኑ።

‘ዳዊቶችሽ’ በጠጠር  ‘ጎልያድን‘ ሲፋለሙ፣
የዝናሽን ውድ ዕሴት  ሰንደቅሽን ሲሸከሙ፣
አግዢያቸው በተፈጥሮሽ፣  እስኪ ለእኩይ ማድላት ያብቃ፣
ለዘላለም-ዓለም ክብርሽ  እንዲሆኑ ዋስ ጠበቃ፤
ለምስኪኖች ዜጎችሽ  አንቺን ብለው ካንቺው ላሉት፣
ለክብራቸው፣ ለማዕረግሽ.. በደማቸው ለሚዋጁት፣
እስኪ መላ! እናት ሀገር! ተዓምር ስሪ አምላክ ይርዳሽ፣
ጸበል ይረጭ መላው ምድርሽ  የድል ጽዋ ያጎናጽፍሽ!

እንደ ጨው ዘር ተበትነው  በምድረ-ዓለም የባከኑ፣
አሉሽና ውድ ልጆች  ባንቺው ፍቅር የተካኑ፣
እቅፍሽን ዘርግተሽ  ሰብስቢያቸው ባንድ ላይ፣
ከወንዛቸው ቀላቅያቸው  ላገር ዕድገት ላገር ሲሣይ።
ባዲስ ራዕይ መልካም ውጥን  በፋኖስሽ ብርሃን ፈለግ፣
ጀግኖችሽን ከየሥፍራው  አድነሽ በመፈለግ፣
አሰማሪ ለነጻነት፣…  ለልጆችሽ ልዕልና፣
ላንድነትሽ ህያው ክብር  ለትውልድሽ ህልውና።

እናት አገር የሁላችን
ዞሮ መግቢያ ቤታችን፣
እኩልነት፣ ፍትሕ፣ ርትዕ.. የተፈጥሮ መብቶች አውራ፣
የነጻነት ብርሃን ቀንዲል  በግዛትሽ ደምቆ ያብራ!
በልጆችሽ አኩሪ ገድል  ህልውናሽ ተጠብቆ፣
ለዘልዓለም ዓለም ኑሪ! ህያው ክብርሽ ባለም ደምቆ።

ለቅድስት ሀገራችን ኢትዮጵያ እግዚአብሔር ምህረቱንና ሠላሙን ይመልስልን አሜን 🙏

የኪነጥበብ ቤተሰብ ይሁኑ !
@sundayschoolstudents
የሰንበት ት/ቤት ኪነጥበብ ክፍል !

ኪነጥበብ ዘሰንበት ት/ቤት

17 Jul, 03:23


" ማነው የሚያብሰው "

አይ ኢትዮጵያ ሀገሬ
ወዴት ይሆን ጉዞሽ
እንዲህ በየቀኑ
ሲያነቡ ልጆችሽ
እውነት አውሪኝ እስኪ
ማነው ጥፋቸኛ ?
እንዲህ በየቀኑ
ያረገሽ ቀበኛ
የገዛ ወገኑን ሰው ሰውን ሲበላ
እስኪ ተጠየቂ እንዲት አጣሽ መላ
ተሰምቶም የሚቀፍ ግራ የሚያጋባ
ይኽን ከንቱ ትውልድ ምንም የማይረባ
ከየት አመጣሽው ? ከወዴት በቀለ ?
የናት ጡት ነካሹን ሀገር ያቃጠለ
ልጠይቅሽ እስኪ ንገሪኝ እማማ ?
የቦይ ውሃ ፈሳሽ ታሪክ የማይሰማ
ንገሪኝ በሞቴ አንቺ ኢትዮጵያ ÷
የድንግል ስጦታ
ማነው የሚያብሰው የወገኔን እንባ ÷
ሌላው እንዳልሰማ ሲሆን በዝምታ።

#አቤል_ባለሀገር

የኪነጥበብ ቤተሰብ ይሁኑ !
@sundayschoolstudents
የሰንበት ት/ቤት ኪነጥበብ ክፍል !

ኪነጥበብ ዘሰንበት ት/ቤት

22 Dec, 07:16


ርዕስ - የተካደ ትውልድ !!

የተካደ ትውልድ
አይዞህ  ባይ የሌለው
ታዳጊ የሌለው
ወይ ጠባቂ መላክ፥ ወይ አበጀ በለው
ደርሶ ከቀንበሩ ፥የማይገላግለው፤

የተካደ ትውልድ

አብዝቶ የጾመ፥ ተግቶ የጸለየ
ጥቂት መና ሳይሆን፥ ጥይት  ሲዘንብ ያየ
እድሜ ይፍታህ ተብሎ፥ የተወለደ ለት
አምባሩ ካቴና፥ ማተቡ ሰንሰለት፤

ምቾትን የማያውቅ፥ ረፍት የተቀማ
አልጋው ያጋም እሾህ፥ ምኝታው የሳማ፤

የተካደ ትውልድ

ሞቶ እንኳን ሬሳው፥ አይላላለት ቀንበር
በዘብ እጅ ተገድሎ ፥ በሹም የሚቀበር
ከጡት አስጥል በላይ፥ ኑሮ የመረረው
እንዳይሄድ ጎዳናው ፥ የተደናገረው
ድል ያልሰመረለት ፥ትግል ሳይቸግረው: :

የተካደ ትውልድ
በስጋ በነፍሱ
በቀልቡ በገላው
ከቶ ምንድን ይሆን?
ምንድን ይሆን መላው?

(በዕውቀቱ ሥዩም)

ባክሽ ኢትዮጵያ ነይ ተሎ 💚💛❤️

የተወደዳችሁ የኪነጥበብ ቤተሰቦች፥ የእግዚአብሔር ሠላምታዬ ይድረሳችሁ 🙏🙏🙏

የኪነጥበብ ቤተሰብ ይሁኑ !
@sundayschoolstudents
የሰንበት ት/ቤት ኪነጥበብ ክፍል !

ኪነጥበብ ዘሰንበት ት/ቤት

31 Jul, 14:52


ርዕስ - እኔ አልወለድም !!

( የአቤ ጎበኛ መጽሐፍ ታሪክ - ላነበባችሁም ላላነበባችሁም ታሪኩ ባጭሩ ሲተረክ)

ፍትህ በሌለበት፣ በዚህ ቀጣፊ ዓለም፣
እውነት በሌለበት፣ በዚህ የውሸት ዓለም፣
አድሎ በሞላበት፣ በዚህ አድሎኛ ዓለም፣
ፍቅር በሌለበት፣ በዚህ የጥል ዓለም፣
ሰላም በሌለበት፣ በጦርነት ዓለም፣
እኔ አልወለድም፣ ይቅርብኝ ግዴለም።
ሰው በሰውነቱ፣ እኩል ካልተዳኘ፣
በሃብቱ እየታየ፣ ዳኝነት ካገኘ፣
መኖር ካልተቻለ፣ ሰዉ እንደተመኘ፣
ሰዉ የላቡን ዋጋ፣ ሰርቶ ካላገኘ፣
ከሰዉ ተለይቶ፣ ሃብታም ከተሰኘ፣
ከሰዉ ተለይቶ፣ ድሃ ከተሰኘ፣
ድሃ ሃብታም ብሎ፣ ሰዉ ከተለያየ፣
እንዴት ይወለዳል፣ ሰዉ ይሄን እያየ።
እባካችሁ ተውኝ፣ እኔ አልወለድም !
ድህነት እርሀብን፣ ለማየት አልወድም፣
ችግርን ስቃይን፣ በፍፁም አለምድም፣
ከማህፀን አልወጣም፣ እኔ አልወለድም፣
ለስቃይ ለመከራ፣ እቢ አልወለድም፣
ፍትህ አልባ ሥራት፣ በፍጹም አልወድም፣
ፍርደ ገምድል ስራት፣ ላይ አልገደድም፣
ፍትህ አልባ ሥራት፣ በፍፁም አለምድም፣
እኔ በዚህ ዓለም፣ እቢ አልወለድም፣
ለእኔ እንድወለድ፣ መች ያጓጓ ዓለም፣
እንድወለድ ሚያደርግ፣ አንድም ነገር የለም፣
ብታምኑም ባታምኑም፣ መጥፎ ነዉ ይህ ዓለም፣
እኔ ምወለደዉ፣ ለሃብታም አገልጋይ ለመሆን አይደለም፣
ለኗሪ አኗኗሪ፣ ለመሆን አልመጣም፣
ከእናቴ ማህፀን፣ በፍፁም አልወጣም፣
አድሎና በደል፣ በበዛበት አለም፣
እኔ አልወለድም፣ ሚያስገድደኝ የለም፣
ለግፍ ለመከራ፣ እኔ አልወለድም፣
አጉል ተወልጀ፣ መከራን አለምድም።
ላይሆን ተወልጄ፣ ኑሬ ከምከፋዉ፣
እኔዉ ተወልጀ፣ ስቃይ ከምገፋው፣
እናታለም ተይኝ፣ ኑሪየን ከዚህ ልግፋዉ።
እናታለም ተይኝ፣ እኔ አልወለድም፣
አረመኔ ሥራት፣ በፍፁም አልወድም፣
የለመዳችሁትን፣ በፍፁም አለምድም።
እኔ አልወለድም !
ሳልወለድ ልሙት፣ እዚሁ ግደሉኝ፣
ከእናቴ ማህፀን፣ ሳልወጣ ቅበሩኝ፣
እኔ አልወለድም !
ሳልፈልግ ፈጥራችሁ፣ ተወለድ አትበሉኝ፣
ምጠይቃችሁን፣ እስኪ መልሱልኝ፣
የምጠይቃችሁ፣ ብዙ ጥያቄ አለኝ።
ከእሱ ለእኔ ሚሆን፣ ምን ነዉ ሚጠብቀኝ ?
የዓለምን መከራ፣ ሳስበው ጨነቀኝ።
ከእሱ ለእኔ ሚሆን፣ እኮ ምንድን አለ፣
ከዚህ ያልተሟላ፣ ከዚህ የጎደለ?
እኮ መልሱልኝ፣ በዓለም ምንድን አለ?
እኔ የማላዉቀዉ፣ ለእኔ የጎደለ፣
እስኪ መልሱልኝ፣ በዓለም ምን ጥሩ አለ?
ለእኔ የሚስማማ፣ መቼ ሰላም አለ?
ነፃነት የት አለ፣ ፍትህስ የት አለ፣
ሰላምስ የት አለ፣ ፍቅርስ የት አለ፣
ዓለም የተሞላዉ፣ በክፋት አይደለ?
በዓለም የተስፋፋዉ፣ ጦርነት አይደለ?
ተወለድ ምትሉኝ፣ ምን ደግ ነገር አለ?
ታዲያ ይህ ሁል ነገር፣ ከሌለ በምድር፣
ኧረ አልወለድም፣ ተዉኝ ከዚህ ልቅር።
እኔ አልወለድም !
በዳይ እና ተበዳይ፣ ገዢና ተገዢ፣
ሚል መደብ እያለ፣ ሎሌና ገዢ፣
ተይኝ እናታለም፣ በይ ስበብ አታብዢ።
እማ ! አልወለድም፣ አትሻኝም ዓለም፣
ከአንቺ ጋ ነዉ ምኖር፣ እኔ አልወለድም።
እኔ አልወለድም !
የዋሁን ደሀ ህዝብ፣ ጉልበቱን በዝብዞ፣
ሀብታሙ ካለልክ፣ ብዙ ሃብቱን ይዞ፣
ድሃዉ ግን ተርቦ፣ ድሃዉ ግን ተርዞ።
እኩልነት ፍትህ፣ በሌለበት ዓለም፣
እባካችሁ ተዉኝ፣ እኔ አልወለድም።
ሃብታምና ጌታ፣ እራሱን ኮፍሶ፣
ሁሉን ሚያግበሰብስ፣ ቀማኛን አንግሶ፣
ፍፁም ግድ ማይሰጠዉ፣ የድሆች እለቅሶ።
ይሄንን ሁሉ ግፍ፣ በተሸከመ ዓለም፣
እኮ ምን ልሰራ፣ እኔ አልወለድም፣
እንደዚህ ባለ ዓለም፣ ለመኖር አለምድም፣
እንደዚያ ያለ ህይወት፣ ለመኖር አልወድም፣
እማ የእናንተ ዓለም፣ ከዚህ አያስወጣም፣
እንደ እናንት ያለ ህይወት፣ ለመኖር አልመጣም፣
የእናት የግፍ ዓለም፣ ምኑነዉ የሚጥም፣
ከዚህ ከአለሁበት፣ ማህፀን አይበልጥም፣
ከዚች ከእኔይቱ ዓለም፣ ሁሉም ነዉ የሚጥም፣
እሱ የእናንተ ዓለም፣ ከእኔ ዓለም አይበልጥም፣
ከዚህ ሁሉም ሰላም፣ እኔ ተወልጀ፣ ስቃይን አልመርጥም።
ተወለድ ካላችሁ፣ እኔ ምወለደዉ፣
ከእርሱም ከሆነ ነዉ፣ ከዚ እንደምወደዉ።
ሰው በሰውነቱ፣ እኩል ከተዳኘ፣
ሰዉ በሚሰራዉ ልክ፣ ክፍያ ካገኘ፣
አድሎ ከጠፋ፣ ፍትህ ከተገኘ፣
ሰዉ መኖር ከቻለ፣ እሱ እንደተመኘ።
ድሃ ሃብታም ተብሎ፣ በሃብት ካልተለየ፣
የሰዉ ልጅ በሙሉ፣ በአንድ እጅ ከታየ።
ስላምና ፍቅር፣ በዓለም ከተስፋፋ፣
ለእኔም ይኖረኛል፣ የመወለድ ተስፋ።
የሰውን ልጅ ሁሉ፣ ዓለም እኩል ስታይ፣
ሃብታም ድሃ ብላ፣ ከፋፍላ ሳትለያይ።
ዓለም ምቹ ስትሆን፣ መኖር ስታጓጓ፣
አንድ አይነት ከሆነ፣ ከዚም ጋ ከሱም ጋ፣
እወለድ ይሆናል፣ በፈጣሪ ፀጋ።

( በጌታቸው ሙላቱ )

በእውነት በዚህ ምስቅልቅል ጨለማ ዓለም እንዴትስ መወለድ ያስመኛል 🤔 ፥ በአሁናዊ የኢትዮጵያ ሁኔታስ ?!

የኪነጥበብ ቤተሰብ ይሁኑ !
@sundayschoolstudents
የሰንበት ት/ቤት ኪነጥበብ ክፍል !

ኪነጥበብ ዘሰንበት ት/ቤት

23 Jul, 11:33


( አማላጄ መንገዴን አቅኚ )

የጭንቀቴ ደራሽ ድንግል  እመቤቴ
ሰላሜ ነሽ ድንግል መቅረዝ የህይወቴ።
የልቤ ፍሥሐ አፅናኝ አለኝታዬ
ከቶ መች አፍራለሁ ወላዲቴ ብዬ።
የቤቴ ብርሀን ነሽ የመንገዴ ፋና
ህይወቴ  ሙሉ ነው አንቺ አለሽኝና።
አንቺ የአዳም ተስፋ የገነት በር ነሽ
በማህፀንሽ ፍሬ አለም የዳነብሽ።
ስምሽን ጠርቼ አላፈርም ዘላለም
ምርኩዜ ሆነሻል አልንገዳገድም።
ከመንገድ ብወድቅስ ከቶ መች ይርበኛል
ስለ እመ አምላክ ብዬ ማን ዝም ብሎኝ ያልፋል።
በእንተ ስሟ ብሎ ተማሪው ሲጠራሽ
መቼ ዝም ያስብላል ልብ ያራራል ስምሽ።
ውሃ ቀለም ቢሆን ሠማይም ብራና
ያንቺን ክብር ገልጦ መች ይጨርስና።
ሀጢያቴም ቢበዛ ብሆን አመፀኛ
ክብር ለሥላሴ ሰቶኛል መዳኛ።

=====///=====

የምህረት ባለቤት እናት የሆንሽው ኪዳነምህረት ሆይ እየሆነብን ያለውን፣ የሚሆንብንን ሁሉ ልጅሽ እንዲያርቅልን አንቺ ለምኝልን። ቅድስት ሆይ ለምኝልን !!!

የኪነጥበብ ቤተሰብ ይሁኑ !
@sundayschoolstudents
የሰንበት ት/ቤት ኪነጥበብ ክፍል !

ኪነጥበብ ዘሰንበት ት/ቤት

22 Jul, 11:04


ሥነጽሑፍ - ግጥም !

ርዕስ - ሞት አለች በጀርባ

አንባቢ - ደሴ ቢተው ከመርጡለ ማርያም

ድንቅ አስተማሪ ግጥም ነው 🥰

የኪነጥበብ ቤተሰብ ይሁኑ !
@sundayschoolstudents
የሰንበት ት/ቤት ኪነጥበብ ክፍል !

ኪነጥበብ ዘሰንበት ት/ቤት

17 Jul, 23:34


#ምን_ብዬ_ልንገርሽ ?! 🤔

ባለሁበት ሀገር ይሄ ዘመን ከፍቷል
የሚጥለን እንጂ የሚያነሳን ጠፍቷል
ክፋት ምቀኝነት ተንኮል ተንሰራፍቷል
በዶክተር ዝምታ ብዙ ታማሚ አልቋል
የሚመልስ የለም የሚጠይቅ ሞልቷል።
.
አይገርምሽም . . . ! 🤔
ባለሽበት ሀገር ባለሁበት መንደር
ለውጥ ማይፈልግ ጠንካራ ሚኒስቴር
ልማትን የማይወድ ምቀኛ አስተዳደር
የቆመ አፓርታማ ቤት ጠፋ የሚለን
የሚነግሩን ታሪክ ትክክል ነው ብለን
ሴራቸው ሳይገባን እልፍ ዘመን ሆነን።
.
ብቻ ምን መሰለሽ ባለሁበት ሀገር
ቡዙ ግፍ ተሰማ ብዙ አይነት ሰቀቀን
በዚች ትንች ጊዜ በዚች አጭር ዘመን
ባለሁበት ሀገር ውሸትን ማይወድ ሀቅን የጨበጠ
ባለሁበት ሀገር ያጭበርባሪን ተንኮል ሴራ ያጋለጠ
ባለሁበት ሀገር ወህኒ ቤት ይወርዳል እየተረገጠ።
...
እናልሽ የኔ አካል . . . 🙄
ጭጭ ካለ መንደር
ፀጥ ካለ ሰፈር ዝምታ ተረግዞ ጩኸት ይወለዳል
ባለሁበት ሀገር ሀቀኛው ተዋርዶ ሌባ ይወደሳል
ከዘነጠች ሀገር ዕርዛት ያዘለ ትውልድ ይፈጠራል
ባለሁበት ሀገር እልፍ የድሀ ጎጆ በጉልበት ይፈርሳል
እንዲህ ነው የኛ ዕጣ ባጀብ ተጀምሮ ባጀብ ይጨረሳል።

=======///========

ነፍስ ጡሯ በማህጸንሽ ያሉ ልጆችሽ  የሚንጡሽ ምስኪና አምሳለ ራሔል ኢትዮጵያ ሆይ ድንኮንሽ ሲጨነቁ ያየው ነብየ እግዚአብሔር ለምን ይሆን ድንኳኗ ከወጀብና ከማዕበል የሚረጋው ዘመንንስ ያልነገረን?! ይህ ሁሉ የሚያልፍበት፣ ፀሐይ የሚወጣበት፣ ተንኮለኞች የሚዋረዱበትና ኢትዮጵያ የምትቀናበት አማን በአማን ጊዜ አላት! ! !

የኪነጥበብ ቤተሰብ ይሁኑ !
@sundayschoolstudents
የሰንበት ት/ቤት ኪነጥበብ ክፍል !

ኪነጥበብ ዘሰንበት ት/ቤት

14 Jul, 20:07


++ ሥነጽሑፍ - ግጥም !

( ርዕስ - የማጀት ስር ወንጌል )

ሙያተኛ ሀገሬ ከማጥገብ ጎደለ በረከት እራቀው የገበታሽ ለዛ፣
ተሻምቶ ለመጉረስ ከበላነው ይልቅ የደፋነው በዛ፡፡
ሙያሽ ባያስደፍር አጀብ ቢሰኙበት፣
ማዕዱ ቢሙላላ ዓይነቱ ቢያምርበት፣
አበዛዙ አይደለም አበላሉ ላይ ነው የገበታሽ ውበት፡፡
እየተማመንን! የፉክክር ቅሚያ በርሃብ እየናጥን፣
ከደፋነው ጠግቦ ውሻችን በለጠን፡፡
ከምርት አላነስን፣
ጎተራችን ሙሉ ጀግና አራሽ መች አጥተን፣
ማሰብ የጎደለው አያያዛችን ነው ገደል የከተተን፡፡
ይልቅ ግዴለሽም! ከምግባር ምጣድ ላይ ሳንበስል አንጋግተሸ ከማዕድ አትምሪን፣
ገበታሽ እንዲያምር ከእግዜር የሚያስታርቅ ፍቅር አስተምሪን፡፡
ገበታ ዕድሜ ነው ባለ ማሰብ መክነን፣
ሳንፀነስ ጃጀን፣
ሳንጣድ አረርን፣
ከዘመን ገበታ ከፊደል አቅድመን ዘር እየቆጠርን፡፡
ገበታ ሀቅ ነው በክፋት ሊጥ ጋግረው ያሻገቱት እውነት፣
በሆዳም እስክስታ ረግጠው ያፈኑት የምስኪናን ጩኸት፡፡
እስከ ልጠይቅሽ በጥም ደዌ ደቆ የረሃብ ጠኔ ደፍቶት እልፍ ትውልድ ያልፋል፣
ቢራ ለመጥመቂያ ሚበተን ገብስ ግን ከሀገር መች ይጠፋል፡፡
ከሆድ በማይሻገር የማጀት ቤት ዕውቀት አጥብበሽ አትለኪን፣
እስቲ መኖር ይግባን ከማስተዋል መቅደስ ሰው መሆን ስበኪን፡፡
ዘመን ካልገበረው ከችጋር ተራራ ከሲኦል ዳር ኑሮ፣
እንዴት ነው መሻገር ከመርፌ ቀዳዳ በጠበበ አይምሮ፡፡
ከምስኪን ዘመን ላይ የማይኖሩበትን ዕድሜ መበዳደር፣
ለአንዲት ማምሻ ደስታ በአያት እስትንፋስ ላይ ቁማር መደራደር፣
ያሳፍራል አይደል?
እያደጉ ማነስ እያነሱ መዝቀጥ፣
አጎንብሶ ያፀናን የድሃ እናት ጉልበት በጭካኔ መርገጥ፣
ያሳምማል አይደል?
መንገስ ከሚያባላስ መጥገብ ከሚያቃቅር ማግኘት ከሚያጎለን፣
ማጣት ውሎ ይግባ ባርነት ይሰንብት ድህነት ይግደለን፡፡
ከረፈደ ፀፀት ደረት እየደቁ ከእግዜር ቢዋቀሱ፣
ትርጉሙ ምንድነው ሲኖር ተቃቅሮ ሲሞት መላቀሱ፡፡
በእናታችን አድባር በፍቅሯ ይሁንብን፣
መድመቅ ካጋደለን ቆሽሸን ይመርብን፡፡
በመጠማት ሲቃ እስትንፋስ እስኪያንቃት ነፍሳችን ትርበትበት፣
ብቻህን ከመጥገብ አብሮ መራብህ ነው ሰው የመሆን ውበት፡፡
በድፍን ግልብ እሚያጋድል ህዝብ የመሆን መንጋ አይንዳን፣
በማሰብ ስር እንፈወስ በሰውነት ፀበል እንዳን፡፡
አየህ! ሰው ስትሆን ከመንጋነት ሚያግድ እረኛ አያሻህም ከህሊናህ በላይ፣
ስታስብ መሪ ነህ በብስለት ከፍታ በማስተዋል ሰማይ፡፡
አየህ! ሰው ስትሆን የጎጥ አረም ነቅለህ በአንድነት መስክ ላይ ፍቅር ትዘራለህ፣
በወረወሩብህ የጥላቻ ድንጋይ ትውልድ የሚያፋቅር ድልድይ ታበጃለህ፡፡
አየህ! ሰው ስትሆን ዝምታህ ኃያል ነው ጀግና የሚያንበረክክ፣
ከፈሪ ቀረርቶ ከባዶ ሰው ጩኀት፣
ሀገር ላምስ ከሚል በመንደር አጀንዳ በአሽኮለሌ ተረት፡፡
አየህ! ሰው ስትሆን ነጻ ነህ እያሉህ መታሰር ያምርሃል፣
መቀመቅ መበስበስ፡፡
የኖርክለት እውነት ሀገር እስኪፈታ፣
በሀቁ እስኪመዘን ስለ በርባን ክብር የቆሸሸው ፍቅር የታሰረው ጌታ፣
ከድል ታሪክ ሰማይ ከሥልጣኔ ዳር ከጥበብ ከፍታ፣
እንሻገራለን ህዝብነትን ትተን ሰው የሆንን ለታ፡፡
በትረ ጥበበ ቢካን ዓለም ሊያንቀጠቅጥ ድል ሥልጣን ቢሰጠው፣
ጀግና መሪ አይደለም ብርቱ ተመሪ ነው ሀገር ሚለውጠው፡፡
አስተውል ወዳጄ ጠልተን ላንጣላ ችለን ላንጋደል ነደን ላንፋጀው፣
የኛው ትርምስ ነው በልቶ ለሚያባላ ጠላት ሚበጀው፡፡
ስጋና ደም እንጂ የአንድነታችን ውል የፍቅራችን ቀለም፣
ያሰመርነው ክልል የታጠርንበት ዘር ቋንቋችን አይደለም፡፡
ከመዋሃድ መቅደስ ትውልድ እናስተምር፣
ዘመን ይመርቀን ፍቅራችን ምን ጎድሎት ደማችን ያስታርቀን፡፡
በልጆቿ አጥንት በደም ኪዳን ምለን የገባንላት ቃል፣
ከጩኀት ያለፈ ዘመን የሚሻገር ተግባር ይጠይቃል፡፡
በአንድ ሃሳብ ተጋምደን በድል ድር እናብር ውድቀታችን ያንቃን፣
ሠርተን እናሳምን ሆነን ድል እንንሳ የአፍ ጀግንነት ይብቃን፡፡
ምስኪኒቷ እናቴ! በሞላ ጎዳና ባልጠበበ ድንበር በዘር ገመድ ታግዳ፣
ነጻ ነኝ ትላለች መንጋነት ያሰረው ባሪያ ትውልድ ወልዳ፡፡
የጀግንነት እብሪት ልባችንን ደፍኖት ማሰብ እየከዳን፣
እንዴት ነው ነጻነት እንዳበደ ፈረስ ስሜት እየነዳን፡፡
ገድሎ የመንገስ ጥማት ጩኀት ላገነነ አመጽ ላጀገነው፣
ለዚህ ምስኪን ትውልድ በጅምላ እየነዱት፣
በመንጋ እያሰበ ነጻነት እንዴት ነው?
ነጻነት ምርጫ ነው አምሮ ቢደላደል ጥፋት ያመነነው የመንጋዎች መንገድ፣
እንቅፋቱን ወዶ ለኖሩለት እውነት ለብቻ መራመድ፡፡
ነጻነት ማመን ነው ቀን ወዶ ቢያጀግን ቀን ጠልቶ ቢከዳም፣
ቢቆሽሹም ቢደምቁም እራስን መቀበል ራስን መምሰል ነው የነጻነት ገዳም፡፡
ነጻነት ማሰብ ነው በአንድነት መለምለም የኔነትን አረም ከህሊና ማጥፋት፣
ዘር ሆኖ ከማነስ ሀገር ሆኖ ማበብ ዓለም ሆኖ መስፋት፡፡
ንገሯት ለሀገሬ በጀግኖቿ ትግል ድንበር ባታስደፍር ከእጀ ገዥ ብትወጣ፣
ነጻ ነኝ እንዳትል በገዛ ልጆቿ በእጅ አዙር ተሸጣ ፡፡
ስሩን ካልሸመነው በመዋሃድ ጥለት በማስተዋል ሸማ፣
ታሪክ አናደምቅም በጭብጨባ ድግስ በሆይ ሆይታ ዜማ፡፡
ምን ብናቀነቅን በየሰልፉ ሜዳ ወኔ ብንደግስም፣
በፈረሰ አይምሮ በደቀቀ አንድነት ሀገር አናድስም፡፡
በጭፍን ከመሮጥ አስቦ ማዝገም ነው የመራመድ ውሉ፣
ሁሉም እንቅፋቶች እስኪጥሉን ድረስ ምርኩዝ ይመስላሉ፡፡
በድፍን ግልብ እሚያጋድል ህዝብ የመሆን መንጋ አይንዳን፣
በማሰብ ስር እንፈወስ በሰውነት ፀበል እንዳን፡፡
ከእግዜር ልንወዳጅ ለምህረቱ ጥላ እምባ ብንደግስም፣
ልብን ሳይመልሱ ለንስሃ መሮጥ ከጽድቅ አያደርስም፡፡
ውብ ነገን እናውርስ ትላንትን አክመን በይቅርታ ፀበል፣
ትውልድ ይጨርሳል ያረገዝነው እምባ የቋጠርነው በቀል፣
ከመስጠት አንጉደል ከቀማኞች ገደል ተረግጠን ብንጣል፣
ካሸከሙን በቀል ምናወርሰው ፍቅር ሀገር ይለውጣል፡፡
ከዕድሏ ጣሪያ ላይ ዘር የቀዳደው ሽንቁሯ ቢበዛም፣
ያ ከንቱ ፎካሪ ባፈጀ ቀረርቶ ሺህ ጉራ ቢነዛም፣
ሚሊዮን ዘር ቢሸጥ አንድ ሀገር አይገዛም፡፡
ኢዮጵያዊነት ነው የትርታችን ልክ የነፍሳችን ግጥም፣
መልስ ቤት በራቀው በከረመ ፀሎት ሰርክ ብታንጋጥም
አጎንብሳ ድሃ ባፀናችው ጉልበት ብትረጋገጥም
ነፍሷን አደህይታ ባሻረችው ቁስል ብትገሸለጥም፣
ሀገር ሆና ገዝፋ በየ ጎጣጎጡ አትርመጠመጥም፡፡
የዘመን እውነት ነን ከደግነት ሰማይ በጥበብ የኖርን፣
ትዕግስትም ልክ አለው ፈርተን እንዳይመስለው ስላቀረቀርን፡፡
ማተብ አስሮን እንጂ ተጣልተን እንዳንቀር በክፍፍል ገደል፣
ከሀገር ክብር በልጦ ሞት ብርቃችን አይደል፡፡
ንገሩት ለዛ ሰው ከዓለም ጫፍ እስከ ጫፍ ኃይል እንደ ተራራ ገዝፎ ቢከመርም፣
ክንዱን አፈርጥሞ እልፍ የሰገደለት ጀግና ቢሰድርም፣
ዓለም የሞተበት የጠላት ማርከሻ ጦር ቢደረድርም፣
በአንድ ዓይናችን ሰላም በተዋህዶ ክብር አንደራደርም!!!

[ ገጣሚ ህሊና ደሳለኝ]

ኢትዮጵያ ሀገራችን ያለችበትን ሁኔታ በትንሹም ቢሆን ያስቃኘናል። ያስተምረናልም ። ግጥሙ የቆዬ ቢሆንም ገጣሚዋን እግዚአብሔር ይስጥልን ። እኛ ግን አሁንም እንላለን «ቅድስት ሀገራችንን ሠላሟን ይመልስልን !» አሜን ።

የኪነጥበብ ቤተሰብ ይሁኑ !
@sundayschoolstudents
የሰንበት ት/ቤት ኪነጥበብ ክፍል !

ኪነጥበብ ዘሰንበት ት/ቤት

26 Jun, 11:46


( ኢትዮጵያን አፋልጉኝ )

ሠላም ለኪ ፅዮን ሆይ
እባክሽ የዛሬን ታደጊኝ
ኢትዮጵያን አፋልጊኝ
ያቺ የፍቅር ዋዕይ
ያቺ የምህረት ራዕይ
ያቺ የፃድቃን ደብር
ያቺ የትንሣኤ ግብር
ያቺ የዘመን ኪዳን
ያቺ የታሪክ አስኳል
ያቺ ዘንፋላ እመቤት
የልቧ የአንጀት ጎረቤት
ያቺ የአምባ ላይ ዋርካ
ያቺ የጎራው ሰገን
ያቺ የሞፈር ወገን
ያቺ የቡራኬ ማዕድ
ያቺ የፅናት አዕማድ
ያቺ ሦስትጉልቻ
ያቺ የጥርስ እንጎቻ
ያቺ የትንቢት መድብል
ፀዳለ ሰማይ ዐይን እንክብል
ያቺ የብቃት ደውል
ያቺ የእምነት ፅናፅል
“ ሀ “ ብላ በ ሀ ግዕዝ “ ፐ “ ድረስ
እምታስቀጽል
ምን አገኛት ኢትዮጵያዬን ?
አልታይህ አለኝ ፊቷ
አልገለፅልህ አለኝ ትውፊቷ
አልለይህ አለኝ ወንፊቷ
አላደርስህ አለኝ ግፊቷ
ፅዮን ሆይ አደራሽን የሷን ነገር
ብቻዬን ምንም ነኝ ምንም
እንኳን ልናገር የማልጋገር
የአባይ ና ጣና ቋጠሮ
የግማደ መስቀሉ ቀጠሮ
የቤተ - ዛጉዬ አለት እንድምታ
የፀጥታውስጥ ቅኝት - የዋይታ ማህል
ዝምታ
የፊደል የቀለም ቅይጥ
የውህደት ማህቶት ነፀብራቅ
በሞት ውስጥ ያለች መወለድ -
በምዕራብ ሙክራብ ውስጥ ያለች
ምስራቅ
የእረኛው ዋሽንት የሩቅ ጥሪ
የአዳኝ ክራር ስግትሪ
ሲማር - እንደ አሮን - እምቢ ሲል በሙሴ
በትር
የአዕዋፍ የአራዊት ሠራዊት
በአንድ ደግሞ እንደ ዳዊት
አንድ አዝምሞ እንደ ሸዊት
ላይጥለው ላይጎነጥለው
ያገር ያለህ ሲል - ሲያስመነጥለው
አቆልቋዮን በሠዓቱ
የአስራት ስፍሩን በበዓቱ
ያራስ ጥሪው ማህበር ጥዋው
ጠግቦ ሲያድር ሠማይ ህዋው
እኛን ዛዲያ ምን ይበጀን
መጀን ያልነው እያስፈጀን
የታመንለት ካልዋጀን
ምን ይበጀን ?
እናቴ ፅዮን
አንችና እሷ መሀል ያለው ሠነድ
በሲዖል እቶንም አይነድ
የፋኖ ዝናር ስናድር
የፈሪ ቤዛ ግድር
ኢትዮዽያን አንዳች ነገር
ውል ያልለየለት ተጠናውቷት
ጀንበር ነጎደ ትቷት
ቋሚው አጥንት ማገሩ ጎድን- አንድ ላይ ታስሮ
ጅብ ሊጋልበው እርጥብ ጋን ሠብሮ
ቀን እያቦካ - ሌት እየከካ ቢገረድፈው
እንኳን ለቋቱ ለመጅ ተረፈው ! ! !

© - ( ባለቅኔው ሙሉጌታ ተስፋዬ )

የሀገራችንን ሠላሟን ይመልስልን 💚💛❤️!

የኪነጥበብ ቤተሰብ ይሁኑ !
@sundayschoolstudents
የሰንበት ት/ቤት ኪነጥበብ ክፍል !

ኪነጥበብ ዘሰንበት ት/ቤት

02 Jun, 06:30


++ ሥነጽሑፍ - የግቢ ጉባኤ ግጥም !

( ርዕስ - ግቢ ጉባኤያችን )

ወደ ግቢ ሕይወት ሳልገባ አስቀድሜ፤
በከንቱ በመዋል ጠፍቶ ነበር ስሜ ።
ምንም የዛልኩ ቢሆን በመንፈሳዊ ሕይወት፤
“በርታ ! ጠንክር ! ” ነበሩኝ ወንድሞች ።
“ይቅርብኝ” አሻፈረኝ እያልኩ ስዋልል፤
ሥጋዬን ለማስደሰት በኀጢአት ስማልል።
ድንገት ደረሰና የግቢ መግቢያዬ ዕለት፤
ስለ ተቋም ትምህርት ስለ ግቢ ሕይወት።
አስረግጦ የሚነግር ሰውን ሳፈላልግ፤
አገኘሁ አንድ ወንድም እኔን የሚታደግ።
የግቢ ጉባኤ ቀደምት ታሪኮችን፤
ሲነግረኝ አንድ ባንድ ፈተሽኩ እኔነቴን።
ውስጤን ማንነቴን ዞር ብዬ አይቼ፤
ላቀና ተቻኮልኩ ከሰው ተጠግቼ።
አሳቤን ሳቃና መሬት ወድቆ እንዳይቀር፤
ደግሜ ጠየቅኩት ጠቃሚ የሆነ ምክር።
እርሱም ሳይሰለቸ ጊዜውን ሰውቶ፤
አወጋኝ ነገረኝ ሳይሰለቸኝ ከቶ።
እኔም ስንቄን ይዤ ወደ ተቋም ስሄድ፤
የወንድሜን ምክር ላለመጣል መንገድ፤
በጽኑ ዓላማ በብርቱ ፍላጎት፤
በሚያስደስት ፍቅር ወሰዱኝ ወንድሞች።
ወንድማዊ ፍቅር ሁሉም ሲለግሱኝ፤
ትንሽ እንደቆየሁ ቤተሰብ መሰሉኝ።
አስኳላውን የሚያግዝ ትምህርት አዘጋጅተው፤
እንደተኛ እንዳይቀር ሁሉንም ቀስቅሰው፤
ሲያግዙ ስመለከት በጣም በመመሰጥ፤
ጠልቄ ገባሁኝ ከግቢ ጉባኤው ውስጥ።
የግቢ ጉባኤው አንድ አካል ሆኜ፤
ስሳተፍ ሳሳትፍ ሁሉንም በርትቼ፤
ይመስጠኝ ጀመር አጋፔ ውይይቱ፤
የኅብረት የአንድነት ጽዋና ጸሎቱ ።
በጉዞ ተሳትፈን ስናይ ገዳማትን፤
ከአበው በረከቶች ተካፋይ ስንሆን፤
ለአምልኮ እግዚአብሔር ምክንያት የሆኑን፤
ግቢ ጉባኤያችንን እግዚአብሔር ያጽናልን ።

=======///=========

በእውነት “ማኅበረ ቅዱሳን” ን እግዚአብሔር ለቅድስት ቤተክርስቲያን ሕልዎና ሲል ያጽናልን። በግቢ ጉባኤ ሕይወት ያልቆዬ የወጣትነት ሕይወት ስለ ማኅበሩ አስተዋጽኦ አያውቅም ማለት ይቻላል ። በተለይም ለግቢ ጉባኤ የሚያሳትሟቸው ጉባኤ ቃና፣ ሐመር እና ሥምዓ ጽድቅ መጽሔቶች እንዲሁም የኮርስ መጽሐፎችን እያሳተመ አስተምህሮናል ።

ማኅበረ ቅዱሳን ስንቶቻችንን መዘምራን፣ ዲያቆናት፣ ሊቃውንት፣ ካህናት፣ ደራሲ፣ ጸሐፊ እና እንቁ የቤተክርስቲያን ጠበቆችን አፍርቶ የቅድስት ቤተክርስቲያን አለኝታ አድርጓል ።

ይቺን አጭር ግጥም በሐረማያ ዩኒቨርስቲ ሐረር ጤና ሳይንስ ግቢ ጉባኤ በሐረር ቅድስት ሥላሴ ቤተክርስቲያን በአገልግሎት በነበርኩበት ጊዜ በዕጣ ለማስተዋሻ ከያዝኳት ጉባኤ ቃና ዘኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ለግቢ ጉባኤ ተማሪዎች በጥቅምት 2006 ዓ.ም ከታተመች መጽሔት የከተብኩት ነው። 

ምንጭ ፦ ( ጉባኤ ቃና ዘኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ለግቢ ጉባኤ ተማሪዎች በማኅበረ ቅዱሳን )

ሥለ “ግቢ ጉባኤ” ሕይወት ይቺን አጭር ስታነቡ ትዝታ የተሠማችሁ እስቲ ሀሳብ አስተያየት ስጡን 🙏🙏🙏 @harabirhanu21

የኪነጥበብ ቤተሰብ ይሁኑ !
@sundayschoolstudents
የሰንበት ት/ቤት ኪነጥበብ ክፍል !

ኪነጥበብ ዘሰንበት ት/ቤት

27 May, 05:22


++ ሥነጽሑፍ - የጰራቅሊጦስ ግጥም !

( ርዕስ - ጰራቅሊጦስ )

ከኤማሁስ ተመልሰው
በኢየሩሳሌም ተቀምጠው
ሲጠብቁ ከልብ ፀንተው፤
የተስፋው ቃል ዕውን ሆኖ
ወረደ ተከፋፍሎ
በእሳት አምሳል ተመስሎ።
መቼ ሆነና የጉሽ ጠላ
አድሮ ውሎ የሚጣላ፣
ነበረ እንጂ መንፈስ ቅዱስ
ሕይወት ሰጥቶ የሚፈውስ
ኃይልን አድሎ ልብ የሚያድስ።
ጴጥሮስ አትፍራ ተመላለስ
በአንተ ላይ አድሯል መንፈስ ቅዱስ፤
ያለ ታንኳ ተራመድ በባሕሩ
ዓለም ይግባው ምስጢሩ
መንፈስ ቅዱስ ሲያበረታ
ሀዘንን አጥፍቶ ሲሆን አለኝታ፤
ፍርሃትን አስወግዶ
ድፍረትን አለማምዶ
በከሃዲዎች ፊት መቆምን አስወድዶ፤
ኃይልን ሊሰጥ ለወገኑ
ቃሉን አጥተው ለመከኑ፤
ጉስቁሉናቸው ሲጠፋ
ሊታደላቸው የጽድቅ ተስፋ
በክርስቶስ ሊታመኑ
ቀለው ላይገኙ ሲመዘኑ
በክርስትናቸው ሊታወቁ
በምግባራቸው ሊደምቁ
ሲቀርላቸው መናቁ
የተስፋው ቃል ዕውን ሆኖ
ወረደ ተከፋፍሎ
በአሳት አምሳል ተመስሎ
መንፈስ ቅዱስ ሕይወት ሆኖ
የታመመውን ሊፈውሱ
አሮጌውን ሊያድሱ
በትምህርታቸው ሊያንጹ
ጠማማውን ሲገስፁ
በምስጢረ ጥምቀት ሊያከብሩ
ዕውሩን ሊያበሩ
ዓይንን ሊፈጥሩ በግንባሩ
የመንፈስ ቅዱስን ኃይል ሊናገሩ
በዓለም ዙሪያ ሊመሰክሩ
ተነሱ ሐዋርያት እየዘመሩ
ለስሙ በድንጋይ ሊወገሩ
ስጋቸውን ክደው ለነፍሳቸው ሊያድሩ።
የተስፋው ቃል ሰውን ሆኖ
ወረደ ተከፋፍሎ
በአሳት አምሳል ተመስሎ
መንፈስ ቅዱስ ሕይወት ሆኖ ።

ለበዓለ ጰራቅሊጦስ በሠላም ያድርሰን !

የኪነጥበብ ቤተሰብ ይሁኑ !
@sundayschoolstudents
የሰንበት ት/ቤት ኪነጥበብ ክፍል !

ኪነጥበብ ዘሰንበት ት/ቤት

26 May, 04:54


( ጌታ ሆይ ዕርገትህ )

አንተ ትነሣለህ ፥ አንተ ታርጋለህ
ከምድር ወደ ሰማይ ፥ ከፍ ከፍ ትላለህ
በቃለ ቀርን በይባቤ ፥ በሆታ በደስታ
ዐርገ በስብሀት ፥ ዐርገ በዕልልታ
የሰማይ የምድር ፥ ዝማሬ ነው ጌታ።

እነሆ
ይህንን እያያች
ምድር ታደንቃለች
ሰማይ ትሰግዳለች

መላእክትን ሳይቀር ፥ ባስገረመ ቁመት
ደቀመዛሙርትህ ፥ ቆመዋል በአንድነት
ሰማይ - ሰማይ ያያሉ ..
የዕርገትህን ነገር ፥ ዕፁብ ድንቅ ይላሉ0
ምስጢር ያወጣሉ ፥ ምስጢር ያወርዳሉ።

እኛም
የሐዋርያትን ዐይን ፥ ዐይናችን አድርገን
በወንጌል ልብነት ፥ በመንፈስ ተነጥቀን
ስታርግ ልናይህ ፥ ቢታንያ ወጥተን
በመቅደስህ አንፃር ፥ ደጅ እንጠናሀለን።

ታዲያ
በዚህች ዕለት በዚህች ቀን
የምናቀርብልህ ፥ ይህ ነው ጸሎታችን
አቤቱ
በዕርገትህ ፥ ፍፁም ደስ እንዲለን
ትንሣኤ ልቡናን ፥ እባክህ አድለን

ደግሞም
ጌታችን ማረግህ
ወደ ሰማይ መውጣትህ

አሳባችንን ሰብስቦ
ልባችንን ወዳንተ ስቦ
በትንሣኤ ልቡና አክብሮ
በክብርህ ሰረገላነት ሰውሮ
የምድሩን አስንቆ
ከፍቅርህ አጣብቆ
ደመናውን ሰንጥቆ
ወደ ሰማይ ያውጣን
የማደርያህ ሰማይ ፥ እንድንሆን ያብቃን።

እንኳን ለብርሃነ ዕርገቱ በሠላም አደረሳችሁ አደረሰን !

የኪነጥበብ ቤተሰብ ይሁኑ !
@sundayschoolstudents
የሰንበት ት/ቤት ኪነጥበብ ክፍል !

ኪነጥበብ ዘሰንበት ት/ቤት

20 May, 05:54


++ ሥነጽሑፍ - የቅዱስ ያሬድ ግጥም !

( ርዕስ - ዝክረ ቅዱስ ያሬድ )

የመላእክት ልጆች ፥ ከቅዱስ ተራራ
በዝሙት ሲወርዱ ፥ ወደ ቃየል ተራ
ስድስተኛው ትውልድ ፥ የአዳም ዘር ውላጅ
ያለ ግብሩ ሲሆን ከክፋት ሲወዳጅ
ውርዝውናን ረስቶ ያለ ጊዜው ሲጃጅ
የዛፉም ቅርኝጫፍ የትውልዱም እትብት
መውረዱን ሲያረዱ ያሬድ ብለው ጠሩት።

መውረዱ ቀጥሎ ፥ ወርዶ ወርዶ ወርዶ
የሰው ልጅ ከጽድቁ ፥ ከከፍታው ነጉዶ
ስሙ ከስማቸው ፥ ከአፋቸው ተላምዶ
ለመሬት ጥሬ ፥ ከአፍ እንዳመለጠ
ዘመን እየጣለ ፥ ቀን እየረገጠ
ቤተ ቀጢን ጓሮ ፥ ለአንድ ብላቴና ለያሬድ ተሰጠ።

ይህንን ሲሰማ
ያሬድ ምስጢራዊ ነፍሱ ደነገጠ
ለጌታም አደረ መጽሐፍም ገለጠ
ቀለም አልሆን ቢለው ፥ ንባብ ባይሰምርለት
ወደባይ ወረደ ባለማወቅ ቁጭት ፥ በጥቂት ልጅነት

ጅማሬ ውጥንህን ፥ ማለዳህን አይተው
ያሬድ ሰነፍ ነበር ፥ ት/ምት የማይገባው
ቢሉህ ባለማወቅ ፥ ማየት ተስኗቸው
አይደለም ስህተት ነው ፥ ይህ ንግግራቸው።

በድካምህ እቅፍህ ፥ ትጋትህ ለታየኝ
ሕይዎትህ ለገዛኝ ፥ ቅኔህ ላማለለኝ
የመቆጨት እንባህ ፥ ባርያህን ይጠበኝ
ከዕብደት ከስንፍና ፥ ያጣላኝ ያናቁረኝ

ያሬድ አጋፋሪ ፥ ለሰው ያቃመሰ ከመላእክት እንጀራ
ያሬድ ባለ ቅኔ ያሬድ ባለ መጽሐፍ ያሬድ ባለ እንዚራ
የሊቅነትህ ምንጭ የዜማህ ሀሌታ
ለሳባዊት ምድር የሆናት የኔታ
ፈትሎ ያለበሰ የሊቅነት ኩታ
ከዕብነ ሀኪም ውሃ ወይስ ከመላእክት
ወይስ ከመ/ሩ ከጌድዬን ጸሎት
የወንዝነትህ ምንጭ የዝጋባነትህ ስር
የጥምጣምህ ክብደት ከየት ነው የሚጀምር?

ባለማወቅ መሐል ስንፍናን የናቀ
ሰማየ ሰማየት በአካል ያስመጠቀ
ውድቀትን መቀበል ሞትን እንቢ ያለ
ከድክመትህ ጀርባ ጽናትን ያዘለ
ትጋት ሞቃትነት መራር ቁጭት አለ።

´ሰላም ለኪ ብፅዕት ሰላም ለኪ ቅድስት
ሰላም ለኪ አንቲ አንቀጸ ብርሃን መዓርገ ሕይዎት
ሰላም ለኪ ጽዮን አርያማዊት ምዕራፍ
መሄዴ ነውና ወደ ልጅሽ እቅፍ
ቡራኬሽን ስጭኝ የእጅን መዳፍ።

ብሎ ልቡ ቆርጦ ፥ አንብቶ የእንባ ጎርፍ
ተከዘኔን ተሻግሮ ፥ ወይቃልን ረግጦ ፥ ሳኒር ገብቶ ቀረ አገቱኒን ቀለም በሀሌ ለውጦ።

በዳሞ በሙራድ ፥ አራራይ ያስቀኘ
በጣና በደባርቅ ፥ በረከት ላስገኘ
<<ሀ>> ገደል ሆኖብኝ ፥ ፊደል ለሚያስፈራኝ
ጥልቅ እንቅልፍ ለተኛሁ ፥ ስንፍናየ ደልቶኝ
ምስጢርህን አልሻም ፥ ቅኔህ አይድረሰኝ
ዝማሬህን ሳስብ ፥ እንባ ለሚቀድመኝ
ወድቆ ቀረ ስባል ፥ ተነስቼ እንድገኝ
ሦስት ቀን ጨልሞ ፥ ሺ ሌሊት ይንጋልኝ።

ምንጭ፦ ዝክረ ቅዱስ ያሬድ - ማ/ቅዱሳን 2013

ወስብሐት ለእግዚአብሔር
ወለወላዲቱ ድንግል
ወለመስቀሉ ክቡር ይቆየን !!!

የኪነጥበብ ቤተሰብ ይሁኑ !
@sundayschoolstudents
የሰንበት ት/ቤት ኪነጥበብ ክፍል !

ኪነጥበብ ዘሰንበት ት/ቤት

20 May, 05:45


ዛፍዋም ከአንድም ሁለት ሦስቴ ብትነገረኝ እኔ ዘዴዬ ያዋጣኛል ብዬ ብልጠት ለመጠቀም ሞከርኩ፡፡ ብልጠቴ ምን መሰላችሁ፡፡ ጌታችሁ ከዘጠኝ ሰዓት በኋላ ለአምስት ሺ አምት መቶ አመታት ሲሰቃዩ የነበሩትን ነፍሳት ለማውጣት ሲኦል እንደሚወርድ አውቅ ነበር፡፡

እኔም ጌታችሁ በራሱ ሥልጣን ዘጠኝ ሰዓት ቅድስት ነፍሱን ከክቡር ሥጋው ሳይለይ ቀድሜ ሞቼ ሲኦል ዱቅ ብዬ ልጠብቀው ወሰንኩ ምክንያቱም ከሲኦል ከሚወጡት ነፈሳት ጋር አብሬ ልወጣ፡፡ ኡኡቴ ተዘይዶ ተሞቷል፡፡

ጌታችሁም ብልጠቴን አውቆ ከዛፉ በጢንቢራዬ ቢጥለኝ አንጀቴ ተዘርግፎ ለአርባ ቀን በሰቀቀን ሳልሞት ቆየሁ፡፡ ጌታችሁ በሲኦል ያሉትን ነፍሳት ጥርግርግ አድርጎ ካወጣ በኋላ እኔ በአርባ ቀኔ ሞትኩ፡፡ አዳሜ ገነት ለመግባት የሚያስፈልገው ዘዴ/ብልጠት/ ሳይሆን ሕጉን መጠበቅ፣ ምግባር መሥራት ወዘተ ነው፡፡ በብልጠት የትም አትደርሱም፡፡ 

ጀለሶቼ ሲኦል ስሄድ ከሦስት ሰዎች በስተቀር ሲኦል ኦና ሆና ጠበቀችኝ፡፡ እነዚህ ሦስት ሰዎች ያልኳችሁ ጌታ በእለተ አርብ ከሲኦል ያላወጣበት ምክንያት በደላቸው፣ ኃጢአታቸው አገር አቀፍ ስለሆነ ነው፡፡ እነሱም ፈርዖን፣ ጽሩ ጻይዳ እና ሔሮድስ ናቸው፡፡

የፈርዖንን በደል እና ኃጢአት ዘመናችሁን ስትሰሙት፣ ስትማሩት ነው ያደጋችሁት ታሪኩን ለእናንተ ትቻለሁ፡፡  ጽሩ ጻይዳ በምድያምና በሜዶን አምልኮተ ጣዖትን አስፋፍቷል፤ ይባስ ብሎ ንጹሐኑን የመቃቢስን ልጆች ሲላ፣ አብያና ፈንቶስን አስገድሏል፡፡

ሔሮድስም እንደምታውቁት አሥራ አራት እልፍ/መቶ አርባ ሺ ሕፃናትን አስፈጅቶ፣ እስራኤልንም በደም ውሃ አርግቶ ግፍ ሠርቷል፡፡ እነዚህ ሦስቱ ክፉ ሰዎች ጌታችሁ በዲያቢሎስ መንግሥት በሲኦል ተዋቸው፡፡ ምክንያቱም ፍዳቸው ፅኑ ነውና፡፡ ሲዖልም አትለቅም ገነትም አትቀበልም፡፡ 

ጋይስ አጅሬም በሲዖል ብቻዬን አገኘኝ፡፡ ተዉ ያደረገልኝን የመከራ አቀባበል በቃላት ልነግራችሁ አልችልም፡፡ ጌታ የማረከበትን የሺ ዓመታቶች ነፍሳት ብስጭት እኔ ላይ ተወጣ፡፡ ያላደረገኝ ያላሰቃየኝ ነገር የለም፡፡ ስቃዩን ስትመጡ ስለምታዩት ያኔ ትረዱኛላችሁ፡፡

ነፍሳት ከሲኦል ሲወጡ፣ በሲኦል እንደ ተዋጡ የቀሩ ሦስቱ የሲዖል ጀለሶቼ ‹‹ዩዲ አይዞኝ እኛም እንዳንተ ተከርቸም ውስጥ ገብተን በነፍሳችን ቶርች ስንደረግ ነው የከረምነው፣ ዩዲ ሲዖል ቻል ነው የሚደረገው እንጂ አይለቀስም፡፡ ለነገሩ ብታለቅስ ማን ሊደርስልህ›› ብለው መከሩኝ ልበል አጽናኑኝ አላውቅም፡፡

ይኸው ሲኦልን ግዛቴ ርስቴ አድርጌ ከተቀመጥኩ ሁለት ሺ ዓታት አለፉኝ፡፡ ወድጄም በትንቢት ተገድጄም ጌታዬን ብሸጥም ለሳጥናኤል በሲኦል እየተገዛሁ እኖራሉ፡፡ ጀለሶቼ ገና ምን አየሁ ያ ‹‹ገሃነመ እሳት›› የሚባል ይጠብቀኛል አሉ፡፡

ዞሮ ዞሮ ነብዩ ኤርምያስ በትንቢቱ ‹‹ከእስራኤል ልጆችም አንዳንዶቹ የገመቱትን፣ የተገመተውን ዋጋ ሠላሳ ብር ያዙ›› የተባለው ቀደምት ትንቢት፤ የዕንባቆምም ንግርት፤ ጌታችሁም የተናገረብኝ ሁሉ ደርሶብኝ ባልበላሁት ሠላሳ ብር ጌታችሁን ሽጬ ለዘመነ አዝማናት አሳሬን እበላለሁ፡፡

ጋይስ እኔ አሁን በሲኦል እየተቀበልኩ ያለሁት መከራ ከበቂዬ በላይ ነው፡፡ ግን  እናንተ ሁሌም በየዓመቱ ስትረግሙኝ ስትደበድቡኝ በኋላ በሲኦል ተገናኝተን ከምንላቀስ፤ ለራሳችሁ ብትጠነቀቁ፣ የጌታችሁን ትዕዛዛት ብትጠብቁ፣ ንስሐም ገብታችሁ ብትጸድቁ ነው የሚያዋጣችሁ፡፡ ለማንኛውም የእኔ ፋሲካ በሲኦል መሰቃየት ስለሆነ እችለዋለሁ፡፡ ‹‹ላይችል አይሰጥ›› አሉ!

አንድ ነገር እወቁ የሲኦል የመግቢያ በር ላይ ለሚመጡት ምስኪን ነፍሳት አቀባበል የማደርገው እኔ ስለሆን ወደ ተሻለ የስቃይ ቦታ ለመሄድ ከፈለጋችሁ በመልክ ባታውቁኝም ‹‹ዩዲ›› ካላችሁኝ የሐበሻ ፈገግታ እና ሰላምታ ሳቀርብ እኔ መሆኔን እወቁ፡፡ ይቺ የሲኦል የመግባብያ ኮዳችን ትሁን፡፡

እኔ ካለሁበት እስክትመጡ በሲኦል ናፍቆት እጠብቃቹኃለሁ፡፡

ዩዲ ከሐዲ ነኝ ከሲኦል!

( በቀሲስ  ሄኖክ ወልደ-ማርያም )

++++++ ተፈጸመ ++++++

የኪነጥበብ ቤተሰብ ይሁኑ !
@sundayschoolstudents
የሰንበት ት/ቤት ኪነጥበብ ክፍል !

ኪነጥበብ ዘሰንበት ት/ቤት

20 May, 05:45


እኔ ሆዬ የጨላ ከረጢቴን አጥብቄ እንደያዝኩ አንድ ሐሳብ አወጣ አወርድ ጀመር፡፡ ጌታችሁም ሐዋርያትን ለማረጋጋት እኔ እንጂ እነሱ አሳልፈው እንደማይሰጡት እንደማይሸጡት ለማሳወቅ ‹‹እኔ ቁራሽ አጥቅሼ የምሰጠው እርሱ ነው›› ብሎ ለእኔ ሰጠኝ፡፡ ይገርማቹኃል ያኔ በገንዘብ ፍቅር የገባው ሳይሆን ዋናው ሰይጣን በልቤ ገባ፡፡

ስፖንሰሬን ልብ አላችሁ? ጌታችሁም ‹‹የምታደርገውን ቶሎ አድርግ›› አለኝ፡፡ ጌታችሁ እንዲህ ሲለኝ ሐዋርያት አልባነኑም ነበር፡፡ እነሱ ጌታቸው ለበዓሉ የሚያስፈልገውን ነገር እንድገዛ ለድሆች እንድመጸውት ያዘዘኝ ነው የመሰላቸው፡፡ አይገርምላችሁም! ካላመናችሁ ዮሐ 13÷29 አንብቡ፡፡ ያኔ ሰይጣን እራሴን መቆጣጠር እስኪያቅተኝ ድረስ ወሰወሰኝ፣ ጌታችሁን ሽጥ ሽጥ አለኝ፡፡

የሚገርማቹ ሰው እንደ ዕቃ መሸጥ ባልተለመደበት እንዴት ጌታችሁን እንደሸጥኩት እስከ ዛሬ ይገርመኛል፡፡ ምን ላድርግ ትንቢት ነዋ፡፡ ደግሞም የጨላዋ ከረጢት በእጄ እያለች ጌታችሁን ለመሸጥ መሯሯጤ ዛሬም ምን ነክቶኝ ነው እላለሁ፡፡ ግን ትንቢት ነዋ፡፡

ብዙዎች ‹‹ጌታህን ለምን በሠላሳ ብር ብቻ ሸጥከው›› ይሉኛል፡፡ ትንቢቱ እንዳለ ሆኖ ዮሴፍ የሚባል ጻድቅ ሰው ወንድሞቹ በሃያ ብር ሽጠውት እንደነበር ሰምቻለሁ። ከዮሴፍ ላስበልጠው ብየ ነው በሠላሳ ብር የሸጥኩት፡፡ ደግሞም እኔ ሆኜ ነው ሠላሳ ብር የሸጥኩት፡፡ አይሁድ ጌታችሁን ይጠሉት ስለነበር እንኳን ሠላሳ ብር አንድ ብርም አይሸጡትም ነበር፡፡

እውነት እናውራ ከተባለ "ይሁዳ ጌታውን ሸጠ" ትላላችሁ። እናንተ ጌታችሁን ስንቴ ሽጣቹኃል? ስንቴ ክዳቹታል? ስንቴ በድላቹታል? ስንቴ ሕጉን አፍርሳቹኃል? በቤተ ክርስቲያን እያገለገለ ሰዉግ በመተት የሚያሰቃየው መተተኛ ኃጢአቱ ከእኔ ቢብስ እንጂ የሚያንስ አይደለም።

በቤተ ክርስቲያን እያገለገሉ እየተመላለሱ መተት የሚመትቱ እኮ ከእኔ  የባሰ ጌታቸውን የካዱ ናቸው። ሙዳየ መጽዋት የሚገለብጡት፣ ከቤተ ክርስቲያን ገንዘብ የሚዘርፉት አገልጋይ ተብዬዎች በምን ሞራላቸው ነው "ይሁዳ ጌታውን በሠላሳ ብር ሸጠ" ብለው የሚናገሩ የሚያስተምሩ? ስለ እውነት ፍረዱ!

እኔ አንዴ ነው ጌታችሁን የሸጥኩት የካድኩት። መቶ ጊዜ ጌታችሁን የካዳችሁ፣ የሸጣችሁ የላችሁም?  እኔ ጌታችሁን አንዴ ነው ያሳዘንኩት የካድኩት። እናንተ ጌታችሁን ስንት ጊዜ አሳዝናቹኃል ክዳቹኃል? ትንቢት ሳይነገርባችሁ ትንቢት የምትፈጽሙ አይደላችሁ?

በእውነት ጌታችሁ በዚህ ዘመን ሊሰቀል ቢመጣ እንደው ስንት ብር ትሸጡት ነበር? በዳይሬክት ነው ወይስ በጨረታ? ደላሎችስ ስንት ብር በጌታችሁ ላይ ፈርቅ ትይዙ ነበር? የሚስማር ፋብሪካዎች ‹‹እኔ ከንጽህ ብረት የተዘጋጀ ምርጥ ሚስማር ችንካር አቀርባለሁ›› ይላል፡፡

አንዱ የእንጨት ፋብሪካ ‹‹እኔ ለስቅላት የሚያመች፣ እጅ እግር ከወርች የሚያስቸነክር ጠንካራና ጌታን የሚሸከም መስቀልኛ እንጨት አቀርባለሁ›› ይላል፡፡

አንዱ የቆዳ ፋብሪካ ‹‹ተረፈ ምርት ከሆነው ቆዳ ደንበኛ ሥጋን የሚያሳርር ደንበኛ መግረፊያ ጠፍር አቀርባለሁ›› ይላል፡፡ እናንተስ ስቃዩን እንደ ዮሐንስ እያለቀሳችሁ ከማየት ይልቅ ሰልፊ ለመነሳት አይደል የምትሯሯጡት?

ፎቶውን በፌስ ቡክ፣ በኢንስታ ግራም ወዘተ ላይ ፖስት ለማድረግ እንጂ ፎቶውን እያያችሁ ለማንባት አትቸኩሉ፡፡ ብቻ ጉድ ነው!

ከዛማ ጌታችሁንና ሐዋርያትን ትቼ ጌታችሁን ለመሸጥ ገዢ ፍለጋ ወጣሁ፡፡ ስበር ስከንፍ ሄጄ የአይሁድ አለቆችን አገኘሁ፡፡ እኔም ‹‹እንደ ጠላት የምታዩትን ሰው አሳልፌ እሰጣችኃለሁ ምን ትሰጡኛላችሁ›› አልኳቸው፡፡

እነሱም የጨላ ነገር እንደማይሆንልኝ ማን እንደነገራቸው አላውቅም ‹‹ሠላሳ ብር እንገጭኃለን አንተ ብቻ አሳልፈህ ስጠን›› አሉኝ፡፡ እኔም ተስማማሁ፡፡ ሠላሳ ብር ገጩኝ፡፡ ከዛማ በቃ ጌታችሁን ለመሸጥ ቀብዲ ኸረ የምን ቀብዲ ሙሉ ክፍያውን ተቀብዬ ጌታችሁን አሳልፌ የምሰጥበትን መንገድ ማሰብ ሥራዬ ሆነ፡፡

አንድ ቀን ጌታችሁ እኔን ሳይጨምር ደቀ መዛሙርቱን ይዞ ሊጸልይ ወደ ደብረ ዘይት ተራራ ሄደ፡፡ ይህ ቦታ ጌታችሁ እንደሚውልበት እንደሚያድርበት አውቅ ስለነበር ከዚህ የበለጠ ምቹ ጊዜ አላገኝም ብዬ የአይሁድ አለቆችንና ወታደሮችን አስከትለን እሱ ወደለበት ሄድን፡፡

አይሁድም ‹‹እሱን በምን እናውቃለን›› አሉኝ። አይሁድ ይህን ያሉት ጌታችሁ እና የድሮ ጓደኛዬ ዮሐንስ በመልክ ስለሚመሳሰሉ መለየት ስለማይችሉ ነው። እኔም ‹‹ቀጥታ ሄጄ የምስመው እርሱ ስለሆነ ያኔ ያዙት›› ብዬ ነገርኳቸው፡፡

ይገርማቹኃል ጌታችሁ እኔን ሲያይ ፊቱ ላይ ያለው የፍቅር ፈገግታው አሁንም በሲኦል ሆኜ አልረሳውም፡፡ ጌታ በፍቅር ሲቀበለኝ እኔ በተንኮል መሳም ሳምኩት።  እሱም ስላወቀብኝ ‹‹ይሁዳ ሆይ፣ በመሳም የሰውን ልጅ አሳልፈህ ትሰጣለህ›› ሲለኝ አንጀቴ ሳይሆን ነፍሴ ተላወሰች፡፡

ግን ምን ላድርግ እኔ ጌታችሁን አሳልፌ የሰጠሁት ስስመው ሳይሆን ሠላሳ ብር ስቀበለው ስለሆነ አሳልፌ ሰጠሁት፡፡ ዛሬም እናንተ ጌታችሁ የሰጣችሁን ጸጋ፣ ክብር፣ አደራ፣ ታማኝነት፣ እምነት ለኃጢአት/ለሰይጣን አሳልፋችሁ ትሰጣላችሁ፡፡

ጌታችሁን ሲያንገላቱት ሲመቱት ሳይ አንዳች ነገር ተሰማኝ፡፡ ገንዘብ ወዳድነቴ፣ ሌባነቴ፣ ከሃዲነቴ፣ እምነት አጉዳይነቴ፣ ላመነኝ ጌታችሁ አለመታመኔን ሳስብ ወዲያው የአይሁድ አለቆች ጋር ሄጄ ‹‹ንጽህ ደም አሳልፌ በመስጠት በድያለሁ›› ብዬ በጸጸት ተናገርኩ።

ሠላሳ ብሩንም ውሰዱ አልኩ፡፡ እነሱም ‹‹አንተው ተጠንቀቅ እራስህ ተወጣው›› አሉኝ፡፡ እኔም ጌታችሁን የሸጥኩበትን ሠላሳ ብር በቤተ መቅደስ ጥዬ ሄድኩ፡፡ በጣም የሚያሳዝነው ፈራጆች ሠላሳ ብሩን ላልበላው ላልጠቀምበት ነው ጌታችሁን የሸጥኩት። በቃ ትንቢት ነዋ! ባደረኩት ነገር እራሴን ወቅሼ ለማረጋጋት ባለመቻሌ ለእኔ ሞት ይገባኛል ብዬ እራሴን ሰቅዬ አጠፋሁ፡፡

ግን አንድ ነገር ልብ በሉ፡፡ ብዙ ሰው ጌታችሁን መሸጤን እንጂ ክፍኛ መጸጸቴን ልብ አይሉም፡፡ በእጃችሁ ያለው መጽሐፍ ቅዱስ ጸጸቴን አስመልክቶ ‹‹ተጸጸተ›› ብሎ መስክሮልኛል ደግሞም ጸጸቴ የእውነት ሳይሆን የውሸት ቢሆን ኖሮ የእውነት ቃልን የያዘው ቅዱሱ መጽሐፍ ‹‹ተጸጸተ›› ብሎ አይመሰክርልኝም ነበር፡፡ በእውነት መጸጸቴን ካላመናችሁ የማቴዎስ ወንጌል ምዕራፍ 27፥ 3 አንብቡ!

ታድያ እናንተ በሠራችሁት ስህተት እና ኃጢአት እንደ እኔ ተጸጽታችሁ ታውቃላችሁ? ብትጸጸቱማ ከስንት የክፋት መንገዳችሁ፤ ከስንት የዝሙት ወዘተ የኃጢአት ሕይወታችሁ ትመለሱ ነበር፡፡ ግን ማትመለሱት ጸጸታችሁ ጊዜያዊ ስለሆነ ነው፡፡

ኤኒ ወይስ ጌታችሁን የሸጥኩበት ብር ለእኔም ለአይሁድም ሳይሆን አይሁድ ‹‹የደም ዋጋ ነው›› ብለው ለእንግዶች የመቃብር ስፍራ እንዲሆን መሬት ገዙበት፡፡ ያ የደም መሬት ዛሬም እስራኤልና ፍልስጥኤም ደም ሲፋሰሱበት ይኖራል፡፡ የዛሬ ሁለት ሺ ምናምን ዓመት ጌታችሁን የሸጥኩበት የሠላሳ ብር ገዳፋ፣ እስራኤልንና ፍልስጥኤምን ዛሬም ሲያዳፋ ይኖራል።

የሚያሳዝነው ያኔ ጌታችሁ እንደ ጴጥሮስ የሰጠኝን የንስሐ እድል ብጠቀምበት ኖሮ ዛሬ መኖርያዬ ሲኦል ሳይሆን ገነት ነበር፡፡ እራሴን ላጠፋ ዛፍ ላይ ስንጠለጠል ዛፍዋ ‹‹ይሁዳ ሆይ እንደ ወንድምህ እንደ ጴጥሮስ ንስሐ ግባ›› ስትለኝ አልሰማም አልኩኝ፡፡ ዛሬም ንስሐ ግቡ ሲባሉ የማይሰሙ እንደ እኔ የደነደነ ልብ ያላቸው ስንት አሉ፡፡

ኪነጥበብ ዘሰንበት ት/ቤት

20 May, 05:45


++ ኪነጥበብ - መንፈሳዊ ወግ !

( ርዕስ - የይሁዳ ብሶት ከሲኦል )

ክፍል ሁለት /የመጨረሻው/

ጋይስ ይሁዳ ነኝ! እንዴት ዋላችሁ አደራችሁ ልል ብዬ በሲኦል ቀንና ማታ የሚባል የለም፡፡ ስለዚህ በሲኦል መዋል ማደር የለም በስቃይ መኖር እንጂ፡፡ ይህንን ማመን ካቃታችሁ ስትመጡ አይታችሁ ታምናላችሁ፡፡ አይ ሐበሻ አቤት ወሬ ስትወዱ፡፡ አሁን የእኔን ብላክ ስቶሪ ለመስማት ቸኩላቹኃል አይደል፡፡ ለነገሩ ከእኔ ብትማሩ ባትማሩም ልንገራችሁ ምክንያቱም እኔም ከጌታዬ ስላልተማርኩ፡፡

ዳይ ወደ ገደለው፡፡ እናላችሁ… በሰፈሬ አንበሳ ሳልሆን አደገኛ የዝንጀሮ ገመሬ ሆኜ አደኩ፡፡ በኋላ ያሳደገኝ የአስቆሮቱ አገርና የወላጅ አባቴ የይሁዳ አገር ሰዎች ጦርነት ገጠሙ፡፡ እኔ ሆዬ ምንሽሬን ይቅርታ ቀስቴን ታጥቄ፣ ጦሬን ሰብቄ፣ ጋሻዬን በደረቴ ደቅድቄ ዘመትኩ ጦርነቱም ተጀመረ፡፡

ጥቂት እንደተዋጋን አንድ ጠና ያለ ሰው ‹‹እጅ በአየር፣ መሳርያ በምድር›› ብሎ ሊማርከኝ ፈለገ፡፡ እኔም ዩዲ ‹‹ሳትቀደም ቅደም›› ብዬ ፊቴ የቆመውን ጠና ያለው ሰውዬ ላይ እንደ ነብር በመወርወር ወደቅሁበት፡፡ ሰውዬውም ጥንቢራው ዞሮ እራሱን ሳተ፡፡ እኔ ልምታው መላክ ይቅሰፈው አላወቀም፡፡ ጓደኛዬ ‹‹ዩዲ ሳትሰለብ ስለብ›› አለኝ፡፡ በነገራችን ላይ ዩዲ ጓደኞቼ ይሁዳ የሚለውን ስም ሲያቆላምጡ የሚጠሩኝ ስም ነው፡፡

እኔም ጠና ያለውን ሰውዬ ገድዮ ሰለብኩት፡፡ ምርኮውን ከበዘበዝኩ በኋላ ወደ ጠላት ሰፈር ስገባ አንዲት ጎልማሳ ሴት አግኝቼ ማረኩ፡፡ የማረኳትን ሴት ሚስት ትሆነኝ ብዬ ወሰድኳት፡፡ አብረንም አደርን። መቼም አብረን ስናድር ጣራ ስንቆጥር እንደማናድር ታውቃላችሁ። የሚሆነው ነገር ሁሉ አድርገን አደርን፡፡ ኦህ ዩዲ…ታሳዝናለህ!

ታድያ አብሮ ያደረ ሰው ግለ ታሪክ መጠያየቁ አይቀርምና ያገሬውን የወንዜውን አውርተን ወደ ራሳችን ታሪክ መጣን፡፡ በሚያሳዝን ሁኔታ ያቺ የማረኳት እንደ ሚስትም ያደረኳት ሴት ወላጅ እናቴ ሆና ተገኘች፡፡ እኔም ልጇ ሆኜ እርፍ አልኩት፡፡

በጦርነቱም ወቅት የገደልኩትና ብልቱን የሰለብኩት ጠና ያለ ሰውዬም ወላጅ አባቴ መሆኑን አወኩ። የነብዩ የእንባቆም ትንቢትም "እናቱን ያገባል፣ አባቱን ይገድላል ይሰልባል" የተባለው ጠብ ሳይል በእኔ ተፈጸመ።

ያ ድራማቲክ የመሰለ ሕይወት በእኔ ሲከሰት ግራ በመጋባት እጅግ ተጨነኩ፡፡ ያ ዘመን ደግሞ ጌታችሁ መጥቶ ወንጌል የሚያስተምርበት፣ ድውያንን የሚፈውስበት በአጠቃላይ ጌታችሁ በኢየሩሳሌም ልዩ ክስተት የነበረበት ዘመን ስለሆነ ከማዙካ ጋር ተነጋግረን በሼም የታጠረውን ታሪካችንን ይዘን ወደ ጌታ መጭ አልን፡፡ ወደ ጌታችሁ ለመሄድ የወሰነው ኃጢአተኞችን ያቀርባል፣ ይቅር ይላል፣ ሲበዛ ሰው ወዳድ ነው የማለውን ወሬ ሰምተን ነው።

ጌታ ጋር ደርሰን ያለውን ሂስቶሪ ዋን ባይ ዋን ነገርነው፡፡ ጌታም በገጠመን ነገር እኛን ከመኮነን ይልቅ በማዘን አጽናናን፤ ብዙ መከረን አስተማረን፡፡ በተለይ እኔን ዓይን ዓይኔን እያየ ሲናገረኝ ነብሴ ትንቀጠቀጥ ነበር፡፡ ያ የሐዘኔታና ‹‹ትሸጠኛለህ›› የሚል ዕይታው ዛሬም ድረስ በሲኦል ውልብ ይልብኛል፡፡

ጌታችሁም ሳያሳፍረን/ጌታችሁ የምለው ጌታዬ ብዬ ለመጥራት በሥራዬ ስለማፍር ነው/ ማዙካን ከሠላሳ ስድስቱ ቅዱሳን አንስት፤ እኔንም ከአሥራ ሁለቱ ሐዋርያት ጋር ቆጠረን፡፡ ለእኔም እንደ ጓደኞቼ ስልጣን ጸጋን ሰጠኝ፡፡

ምን ዋጋ አለው እኔ ሁሌ ምሾፈው ስልጣኔን፣ ጸጋዬን ሳይሆን እንደ ዘመኑ አንዳንድ ካህናትና አስተዳዳሪዎች በሙዳየ ምጽዋት ውስጥ የምትገባውን ጨላ ብቻ ነው፡፡ በነገራችን ላይ ጌታችሁ በሰጠኝ ስልጣንና ጸጋ ድውይ ስፈውስ፣ ለምጽ ሳነጻ አጋንንት ሳስወጣ እንደነበር ስንቶቻችሁ ታውቃላችሁ?

በተለይ አንድ ቀን እንዴት እንደተናደድኩ ልነግራችሁ አልችልም፡፡ ታሪኩ እንዲህ ነው፡፡ በዛ በለምጻሙ በስምዖን ቤት ተጋብዘን፤ ከጌታችሁ ጋር ሰብሰብ ብለን እያለን አንዲት ሴት በውድ ዋጋ የተገዛ ሽቱ ይዛ ከች አለች፡፡ አልባስጥሮስ ሽቱውን ስከልመው ፐ ብሸጠው ብዬ ጆፌዬን ጣልኩበት፡፡

ልጅቷም ተአምረኛ ነች ያንን ሁሉ ሽቱ ጌታዋ ላይ አርከፈከፈችው፡፡ እኔ ዝም ብዬ ከልማታለሁ፡፡ እሷም አውቃለች መሰለኝ በቆረጣ እያየችኝ ሽቶውን በሙሉ ጌታ ላይ አርከፍክፋ ስትጨርስ ይባስ ብላ የጌታዋን እግር  በእንሳዋ አበሰችው፡፡ ዞር ብዬ ስሾፍ ጌታችሁ ላይ ያርከፈከፈችውን ሽቶ ባዶ ጠርሙሱን  እግሬ ስር ጣለችው። በጣም ተናድጄ "ቁረሌው መሰልካት እንዴ ሽቶ የሌለውን ባዶ ጠርሙስ እግሬ ስር የምትጥለው" ብዬ ልናገራት አልኩና ጌታችሁን ፈርቼ ተውኩት።

በተለይ የሽቱው ብልቃጥ ባዶውን መሬት ላይ ሆኖ ስከልም በቅናት ተቃጠልኩ፡፡ መሬት መሬቱን እያየሁ ለጌታችሁ አንድ ሐሳብ አቀረብኩለት ‹‹ይህ በብዙ ዋጋ ተሸጦ ለድሆች ሊሰጥ ይችል ነበር›› ብዬ አዛኝ አንጓች ሆንኩ፡፡ ጌታችሁም ነውር የነበረ ንግግሬን በፍቅር ‹‹ድሆች ሁል ጊዜ ከእናንተ ጋር ይኖራሉ፣ እኔ ግን ሁል ጊዜ ከእናንተ ጋር አልኖርም›› ብሎ ሴቲቱን መልካም ሥራ እንደሠራች በሁላችን ፊት አመሰገናት፡፡  ካላመናችሁ ማቴ 26÷6-13 አንብቡ፡፡

ጭራሽ ያደረገችው ነገር ‹‹ወንጌል በሚሰበክበት ቦታ ሁሉ ለመታሰብያ ይሆናል›› ብሎ ቃል ኪዳን ገባላት፡፡ ጉድ በል ሳጥናኤል….ከዛማ የእኔ ነገር ጨላ ላይ ማፍጠጥ፤ ካዝና ላይ ማጉረጥረጥ ሆነ፡፡ ከመቶ አስሬን እየቦጨኩ ፍራንካውን እንዲው ላልበላው መቀገር ሆነ ሥራዬ፡፡ በገንዘብ እና በሰይጣን መለከፍ አያድርስ ነው!

የሚገርማችሁ አሁን በየ ቤተ ክርስትያኑ ያሉ አገልጋይ ሳይሆኑ ተገልጋዮች ሙዳየ ምጽዋት እየከለሙ መገልበጥ መስረቅ የጀመሩት ከእኔ ኮርጀው ነው፡፡ አሁን ባልጠፋ ነገር እኔን ለሲኦል ዳፋ የዳረገኝን ነገር ከእኔ አይማሩ? ለዚህ እኮ ነው ‹‹ስንት ይሁዳ እያለላችሁ፤ ለምን እኔን በየዓመቱ ትወግራላችሁ›› የምለው፡፡ የምር በየ በተስክያኑ ስንት የሚወገር አስተዳዳሪ፣ ሒሳብ ሹም፣ ጸሐፊ፣ ተቆጣጣሪ፣ ጨላ ቆጣሪ አለላችሁ፡፡

ኤኒ ወይስ ችግር የለውም እያንዳንድሽ እኔ ጋር ስትመጪ የሙዳየ ምጽዋዕት ገንዘብ ገልብጠሸ፣ ቆጥረሽ የበላሽ ሁላ መከራሽን ትቆጥርያለሽ፡፡ ማን የሚሉት ዘፋኝ ነው ‹‹እኛን ነው ማየት ስትመጪ እሱ ብሎት፤ ለጉድ ተናንቀን በእንባ አንገት ላንገት›› ያለው፡፡ ጌታችሁ ሳይሆን ሥራችሁ ፈርዶባችሁ ሲኦል ስትመጡ ተቃቅፈን እንደምንላቀስ ተስፋ አለኝ፡፡

ከዚህ በኋላማ በውስጤ የጌታችሁ ፍቅር ሳይሆን የጨላ ፍቅር አደረ፡፡ ነጋ ጠባ ስለ ገንዘብ ነው የማስበው፡፡ ከመቶ አሥር የማገኘው አልበቃ ሲለኝ ከሐዋርያት ልቀፍል እፈልግ ነበር፡፡ ምን ዋጋ አለው እነሱ ጋር የማይነጠቅ የጌታቸው ጸጋና ፍቅር እንጂ የሚቀፈል ጨላ የላቸውም፡፡

ትዝ ይለኛል! የጸሎተ ሐሙስ ቀን ጌታችሁን ከጓደኞቼ ጋር ግራ ቀኝ ከበነው የመጨረሻ እራት እየበላን ሳለን፤ እኔ የጨላ ከረጢቴን ይዤ ዱቅ እንዳልኩ ጌታችሁን ሳየው አንድ ነገር እንደሆነ ያስታውቅ ነበር፡፡ ጌታችሁም ‹‹ከእናንተ አንዱ አሳልፎ ይተጠኛል›› አለ፡፡ ጌታችሁ ይወደው የነበረው ዮሐንስ የሚባለው ወደ ጌታ ደረት ጠጋ ብሎ ‹‹ጌታ ሆይ ማነው›› አለው፡፡ ሐዋርያትም እጅግ ተጨነቁ "እኔ እሆን እኔ እሆን" እያሉ ታወኩ፡፡

ኪነጥበብ ዘሰንበት ት/ቤት

19 May, 06:32


ምን አለ ያኔ እናቴ ሆድ ውኃ ሆኜ በቀረሁ፡፡ ማዙካ በዚህ ዘመን ኖራ ቢሆን በጥቂት ገንዘብ ሜሪ ስቶፕ ታስወጣኝ ነበር፡፡ ድግሞም ትንቢት ስለነበር እሷ በነበረችበት ዘመን ምንም ልታደርግ አልቻለችም፡፡ እኔም ከች አልኩ ተወለድኩ፡፡

ፋዙካም እርግማኑንና ትንቢቱን ሽሽት ምንም የማላውቀውን ሕፃን በሳጥን ውስጥ ዱቅ አድረጎ በባህር ላይ ጣለኝ፡፡ ያልታደለ ግን ለነፍስ ያለ ያስቆሮቱ ሰው አግኝቶኝ አሳደገኝ፤ በነገራችን ላይ የአስቆሮቱ ይሁዳ  የተባልኩት ከባህር ላይ አንስቶኝ ባሳደገኝ ሰው ስም እንደሆነ ቲንክ አደረጋችሁ? ኦኬ!  እኔም ኃይለኛ ጦረኛ ሆንኝ፡፡ ማን አባቱ ከፊቴ ይቆማል፡፡

በል ያለኝን በካልቾ፣ የጠገበውን በእንጭብጭቢት በስግሪት መታው ነበር፡፡ /አዳሜ የእንጭብጭቢት እና የስግሪት አመታት እዛው ሲኦል ስንገናኝ አሳይሻለሁ/

እባካችሁ ደከመኝ! የሲኦሉም አሳት አቃጠለኝ! ለዛሬ እዚህ ላይ ይብቃ  ነገ ሁሉንም ጥቁር ታሪኬን አጫውታቹኃለሁ፡፡ ሰላም ዋሉ እደሩ ልላችሁ ብዬ እኔ ሰላም ያለበት ቦታ ስላልሆንኩ እንደፈለጋችሁ ሆናችሁ ዋሉ እደሩ፡፡

( ይሁዳ ነኝ ከሲኦል! )

ክፍል - 2 ይቀጥላል …….

በቀሲስ ሄኖክ ወልደ-ማርያም

የኪነጥበብ ቤተሰብ ይሁኑ !
@sundayschoolstudents
የሰንበት ት/ቤት ኪነጥበብ ክፍል !
           

ኪነጥበብ ዘሰንበት ት/ቤት

19 May, 06:32


++ኪነጥበብ - መንፈሳዊ ወግ !

( ርዕስ - የይሁዳ የሲኦል ብሶት )

ይሁዳ ነኝ! እነሆ ጌታችሁ ከተሰቀለ ይቅርታ አሳልፌ ሰጥቼው፣ በማይረባ በሠላሳ ብር ሽጬው ተሰቅሎ ከሞተ ሁለት ሺ ምናምን ዓመት አለፈው፡፡ ከሲኦል እሳታማው ሰላምታዬ እኔ ካለሁበት ለመምጣት ተፍ ተፍ ለምትሉት ያልከበረ ሰላመ ቢስ ሰላምታዬ በየጭፈራ ቤቱ በዝሙት ለሚንገላቱ፤ በየጫትና ሐሺሽ ቤቱ ለሚጀዝቡ፤ በትዳርና በእጮኛቸው ላይ ለሚቀስጡ፣ እየዘሞቱ ለሚያላግጡ፤ ዛሬም እንደ እኔ ጌታቸውን በክህደት፣ በገንዘብ ወዘተ ለሚለውጡ ይድረሳችሁ ብያለሁ፡፡

አዳሜ ብልጣ ብልጥ እንደ እኔ በአቋራጭ ገነት ገባለሁ ብለሽ ያሰብሽ ሁላ ሳታስቢው እኔ ያለሁበት ሲኦል ከች ትያለሽ፡፡ ይቅርታ በሲኦል አፌ ስማቸውን መጥራት ስለከበደኝ ነው። እነዛ ጓደኞቼ ሐዋርያት ጌታቸውንና ጽድቁን ሲፈል፤ እኔ ሆዬ ጨላዋ ላይ ሳፈጥ ይኸው በሳጥናኤል ስደፈጠጥ እኖራለሁ፡፡ የሚገርማችሁ ሐዋርያት የጌታቸውን ወንጌል ለመሸከም ሲጥሩ እኔ ደግሞ ሙዳየ ምጽዋትዋን ብቻ ስሸከም ይኸው እነሱ በገነት እኔ በሲኦል ገፈት እኖራለሁ፡፡

እየውላችሁ ስንት ሺ ዓመታት በሲኦል ሆኜ እያንዳንድሽን ስታዘብ ከርሜ ነበር፡፡ ዛሬ ግን ትዝብቴን ልተንፍሰው ብዬ ነው፡፡ ‹‹የበሰበሰ ዝናብ አይፈራም›› አይደል የምትሉት፡፡ መቼም ካለሁበት ስቃይ ያ ገሃነመ እሳት እስኪከፈት የበለጠ አይመጣ፡፡

ዛሬ በሲኦል ሆኜ ፍርፍር ብዬ ስስቅ ነው የዋልኩት፡፡ ነገርዬው ምን መሰላችሁ! እናንተው ‹‹የእምዬን ወዳብዬ አይደል የምትሉት፡፡ የጌታችሁን መከራ ለማሰብ ያንን የመሰለ ሥርዓት ስታከናውኑ ውላችሁ ማምሻውን ‹‹ይሁዳ ወልዱ እምውሉደ ውሉዱ ይደምሰስ›› እያለችሁ ስንት ይሁዳን ስራችሁ አስቀምጣችሁ በስሜ ስትደበድቡኝ ስትረግሙኝ ነው ያሳቀኝ፡፡

ጋይስ እኔ አንዴ ጌታዬን ሽጬ፣ በሲኦል ተቀምጬ፣ የዛ የሲኦል አበጋዝ መጫወቻ ሆኛለሁ፡፡ ግን ስንቶች አሉ በቤተ ክርስትያን አገልጋይ ነን እያሉ ጌታቸውን በስውር ሽጠው የሚኖሩ፡፡ ስንት አሉ እኔን በመቋሚያ እየደበደቡ በጀርባ እየጠነቆሉ፣ ሙዳየ ምጽዋቱን እየገለበጡ፣ የድሆች ኪስ እየመጠመጡ እሚኖሩ፡፡ ስንት ሴቶች ወንዶች አሉ ክብራቸውን በገንዘብ እየሸጡ ጌታቸውን የሚያስቆጡ፡፡

ስንት አሉ ቅድስናቸውን እያረከሱ፣ በኃጢአት ባህር የሚንከላወሱ፡፡ ኸረ የናንተን ጉድ ዘርዝሬ አልጨርሰውም፡፡ ምንኩስናሽን ያፈረሽ፣ ክህነትሽ የጣልሽ ንስሐ ካልገባሽ በሲኦል የስቃይ ስፖንሰር የምሆናችሁ እኔ ነኝ፡፡ አዳሜ እኔ ወዳለሁበት ስትመጪ የኃጢአት ሒሳብሽን እንደ እኔ በስቃይ በመከራ ታወራርጃለሽ፡፡

ምን እንደምመኝ ታውቃላችሁ! ጌታችሁ እድሉን ቢሰጠኝ እኔን ‹‹ይሁዳና ዘር ዘሮቹ ይጥፉ›› የሚሉትን ነጭ ለባሽ ሁላ በያዙት መቋምያ እግር ከወርች እያልኩ ነርታቸው ነበር፡፡ ደግሞም ንስሐ ሳይገቡ በዓመት አንዴ ለስግደት የሚመጡትን፤ በሥራ እንደ እኔ እንደ ይሁዳ፤ በአለባበስ ግን ጸአዳ የመሰሉትን በመቋምያ እየሸከሸኩ ልክ አገባቸው ነበር፡፡ ምን ዋጋ አለው ሰውን የሚቀይረው ዱላ ሳይሆን ወንጌል በመሆኑ ነው፡፡

እንደው ግን ‹‹ይሁዳና ዘር ዘሮቹ ይጥፉ›› እያላችሁ ቤተ ክርትያን ውስጥ ያላችሁ በመቋሚያ፤ ውጭ ያላችሁ ደግሞ በድንጋይ ስትወግሩኝ ስትረግሙኝ ትንሽ ሼም አይዛችሁም፡፡ ፈጣሪያችሁ ፊት የማያቆም ሥራ ይዛችሁ፣ እንደ ድንጋይ የከበደ ኃጢአት ተሸክማችሁ፣ በየዓመቱ ስትወግሩኝ ስትደበድቡኝ ግርም ይለኛል፡፡ መቼም ጌታ ለእኔ የሰጠኝን ያልተጠቀምኩበትን የንስሐ እድል ለናንተም ስለማይነሳችሁ ነው እንደ ፈለጋችሁ የምትሆኑት፡፡

እስኪ አንዳንድ አዛኝ አንጓቾች፣ ሌሎቹም አጉል ፈራጆች ሁሌ ‹‹ይሁዳ እንዴት በሰላሳ ብር ጌታውን ይሸጣል? እንዴት የንስሐ እድሉን ያበላሻል? እንዴት እራሱን ያጠፋል? እንዴት የሐዋርያነት እድሉን ያበላሻል?›› ለምትሉ ገብስ ገብሱን እነግራቹኃለሁ፡፡

በመጀመርያ ‹‹ይሁዳ እንዴት ጌታውን በሰላሳ ብር ይሸጣል?›› ለምትሉ ስለ እውነት ከሆነ እኔ ጌታዬን መሸጥ አልፈልግም ነበር፡፡ ግን ምን ላድርግ ትንቢቱ ቀድሞ ለእኔ ተነገረ በእኔም ላይ ወደቀ፡፡ ቲንክ እያረጋችሁ ነው ወይስ እያሽሟጠጣችሁ? ኦኬ እኔ ጌታዬን ወድጄ ሳይሆን በትንቢት ተገድጄ እንደሸጥኩ ለእያንዳንድሽ መረጃ አቀርባለሁ፡፡ መቼም ዘመናችሁ የመረጃጃ ሳይሆን የመረጃ እንደሆነ ሲኦል ሆኜ መረጃ ይደርሰኛል፡፡

እስኪ ጌታዬን እንዴት እንደሸጥኩት ከመንገሬ በፊት ከማዙካ የሰማሁትን ልንገራችሁ፡፡ እኔ አስቀድሞ ‹‹አባቱን ይሰልባል፣ እናቱን ያገባል፣ ጌታውን ይሸጣል›› የሚል ትንቢት ነበረኝ፡፡ ታድያ ምን ሆነላችሁ! ያ መናጢ አባቴ ስሙን ሰይጣን ይጥራውና አንድ ዕንባቆም የተባለ ነብይና መምህር ነበር፡፡ አንድ ቀን ዕንባቆም የተባለው ሰው ሊያስተምር ሲሄድ በሚያልፍበት መንገድ ላይ ፋዙካ ድንጋይ ላይ ዱቅ ብሎላቹኃል፡፡

በአገራችን መምህር ክቡር ስለሆነ የፋዙካ ጀለሶች ነብዩ ዕንባቆምን ሲያዩት አክበረውት ተነሱለት፡፡ ፋዙካ በንቀት ይሁን በኩራት እግሩን አንፈራግጦ ተቀምጦ ነበር፡፡ ነብዩ የፋዙካ ጀለሶችን መርቆ፣ ፋዙካን ንቆ ላሽ አለ፡፡ ነብዩ አስተምሮ ማታ ላይ ሲመለስ አሁንም ፋዙካ ያችው ድንጋይ ላይ ዱቅ ብሏል፡፡

ነብዩንም ሲያየው ባላየ ብሎ መንጬ ሊል ብሎ በገገመኛ እዛው ዱቅ አለ፡፡ ነብዩም ‹‹ከዚህ ሰው የሚወለደው አባቱን ይሰልባል፤ እናቱን ያገባል፤ ጌታውን ይሸጣል›› ብሎ ትንቢት ተናገረበት፡፡ ፋዙካም በነብዩ ትንቢት ድንግጥ ሳይል ነብዩንም ይቅርታ ሳይጠይቅ እዛው ድንጋይ ላይ ዱቅ እንዳለ ቀረ፡፡

ፋዙካም ሲመሽ ወደ ማዙካ ጋር ሄደ፡፡ ማዙካም የፋዙካ ፊት አሮ፣ ያ ነጭ ፊቱ እንደ ከሰል ጠቁሮ/ይቅርታ ለካ ከሰል የለም ሲኦል/ ብቻ ምን ልበላቹ ግራ ተጋብቶ ስታየው ‹‹ምንሆንክ? ዛሬ ምን አገኘህ?›› አለችው፡፡

እሱም ‹‹ምን… ባክሽ አንድ ነብይ የሚሉት ሰው በመንገድ ሲሄድ እኔ ድንጋይ ላይ ተቀምጬ ለምን አልተነሳህልኝም፤ ለምን አላከበርከኝም ብሎ ተናገረኝ›› አለ፡፡ ማዙካም ተደናግጣ ዓይኗን አፍጥጣ ‹‹ምን አለህ›› አለችው›› ፋዚካ ነብዩ የተናገረውን ነገራት፡፡

እሷም ‹‹እንዴት እንደዚህ ታደርጋለህ? በእኔስ ላይ ይህንን እርግማን ታመጣለህ›› ብላ አለቀሰች፡፡ ፋዙካ ዓይኑን በጨው የታጠበ ደንታ ቢስ ነበርና እሷ ስታለቅስ ምንም አልመሰለውም፡፡ ምን ቢላት ጥሩ ነው ‹‹በቃ አይዞሽ የነብዩ ትንቢት እንዳይፈጸም እኛም ያችን ነገር አንፈጽምም›› አላት፡፡ እሷም ለጊዜው ተረጋጋች፡፡ ዝም ብላችሁ እዩልኝ በእነዚህ ነገሮች ውስጥ ሁሉ እኔ የለሁበትም፡፡

አንድ ቀን ፋዙካ ከጀለሶቹ ጋር ሆኖ የግብጦ አረቄ/ይቅርታ በሐበሽኛ ለማስረዳት ስል ነው የግብጦ አረቄ ያልኩት/ ወይን ጠጁን ልፎ ልፎ ሰክሮ ተንጀፍጅፎ ጀለሶቹ ተሸክመውት ቤት ገባ፡፡

ማዙካ ሸበጡን አውልቃለት፣ ልብሱን ቀናንሳለት አስተካክላው ልታስተኛው ስትል እሱ አስተካክሎ ሳማት፡፡ እሷም ‹‹ተው አይሆንም የነብዩን ትንቢት አስብ ያ የተባለው ልጅ እንዳይፈጠር›› ስትለው መስሚያውን ጥጥ አድርጎ ያለ ውድ በግድ ተገናኛት፡፡ እኔም ተፈልጌ ሳልሆን ሳልፈለግ፣ በትንቢት ወግ ተጸነስኩ፡፡ እስኪ ፈራጆች! እንኳን ጌታዬን የሸጥኩበት መንገድ ቀርቶ የተወለድኩበት መንገድ አይገርማችሁም? አሁን ሰው በእኔ ይፈርዳል? ብቻ አይወለድ የለ ተወለድኩ፡፡

ኪነጥበብ ዘሰንበት ት/ቤት

19 May, 01:51


++ መንፈሳዊ ወግ !

( ርዕስ - የይሁዳ የሲኦል ብሶት )

ስንት ይሁዳ እያለላችሁ እኔን ለምን በየዓመቱ ትወግራላችሁ?

በወጉ ላይ የአራዳ ቋንቋ የተጠቀምኩት አራዳ ልሁን ያለውን ይሁዳን እያሰብኩት ነው።  ስለ ቋንቋው ይቅርታ! እንድትማሩበት ነው። ደግሞ በጣም ደስ የሚል ለእኛ ለዘመኑ ክርስቲያኖች አስተማሪም ነው ።

ወጉ በሁለት ክፍል የተሰናዳ ነው ፤ እንዲሁም በትረካ ብታቀርቡልን ደስ ይለናል። እናም ከመፍረዳችሁ በፊት በደንብ አንብቡት እራሳችሁን እዩበት እንላለን !!!

ምንጭ ፦ በቀሲስ ሄኖክ ወልደ-ማርያም

ጠብቁኝ 🥰🥰🥰

5,601

subscribers

54

photos

9

videos